በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶች፣ ታላቁ ፈጣሪያችሁን አስቡ

እናንት ወጣቶች፣ ታላቁ ፈጣሪያችሁን አስቡ

እናንት ወጣቶች፣ ታላቁ ፈጣሪያችሁን አስቡ

“በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።”—መክ. 12:1

1. ይሖዋ እሱን በሚያመልኩ ወጣቶች እንደሚተማመን የገለጸው እንዴት ነው?

ይሖዋ ወጣት ክርስቲያኖችን እንደ ውድ ሀብት የሚያያቸው ከመሆኑም ሌላ መንፈስን እንደሚያድስ ጠል አድርጎ ይመለከታቸዋል። በዚህም ምክንያት ልጁ ኢየሱስ ‘ለጦርነት በሚወጣበት’ ቀን ወጣቶች እሱን ለማገልገል ራሳቸውን ‘በገዛ ፈቃዳቸው’ እንደሚያቀርቡ ትንቢት ተናግሯል። (መዝ. 110:3) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን የሚያገኘው አብዛኞቹ ሰዎች ለአምላክ አክብሮት የሌላቸው፣ ራሳቸውንና ገንዘብን የሚወዱ እንዲሁም ለመታዘዝ እምቢተኞች በሆኑበት በዚህ ዘመን ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ እሱን የሚያመልኩ ወጣቶች ከሌሎች ሰዎች የተለዩ እንደሚሆኑ ያውቃል። እናንት ወጣቶች፣ ይሖዋ በእርግጥም ይተማመንባችኋል!

2. ይሖዋን ማሰብ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

2 አምላክ፣ ወጣቶች ታላቁ ፈጣሪያቸውን ሲያስቡ ሲመለከት ምን ያህል እንደሚደሰት ገምት! (መክ. 12:1) ይሖዋን ማሰብ ሲባል እርምጃ መውሰድ ማለትም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ሕጎቹንና መመሪያዎቹን ጠብቀን በመመላለስ እሱን የሚያስደስተውን ማድረግ ማለት ነው። ከዚህም ሌላ ስለ እኛ ከልብ እንደሚያስብ በመገንዘብ በይሖዋ መታመንን ይጨምራል። (መዝ. 37:3፤ ኢሳ. 48:17, 18) አንተስ ታላቁ ፈጣሪህ እንደሚያስብልህ ይሰማሃል?

‘በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን’

3, 4. ኢየሱስ በይሖዋ እንደሚታመን ያሳየው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜስ በይሖዋ መታመን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 በአምላክ በመታመን ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ በምሳሌ 3:5, 6 ላይ የተገለጸውን የሚከተለውን ሐሳብ በሕይወቱ ተግባራዊ አድርጓል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” ኢየሱስ ከተጠመቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰይጣን የዓለምን ሥልጣንና ክብር እንዲቀበል ፈተና አቀረበለት። (ሉቃስ 4:3-13) ኢየሱስ ግን አልተታለለም። እውነተኛ ‘ሀብት፣ ክብርና ሕይወት’ የሚገኘው ‘ትሑት በመሆንና ይሖዋን በመፍራት’ መሆኑን ያውቅ ነበር።—ምሳሌ 22:4

4 በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ተስፋፍቷል። በመሆኑም በዚህ ዘመን ስንኖር የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ጥበብ ነው። ሰይጣን፣ የይሖዋን አገልጋዮች ወደ ሕይወት ከሚወስደው ጠባብ መንገድ ለማስወጣት ማንኛውንም ማባበያ ከማቅረብ ወደኋላ እንደማይል አስታውሱ። ሰይጣን ሁሉም ሰው ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ ላይ ሲጓዝ ማየት ይፈልጋል። እናንት ወጣቶች፣ ሰይጣን አያታልላችሁ! ከዚህ ይልቅ ታላቁ ፈጣሪያችሁን ለማሰብ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። ሙሉ በሙሉ በእሱ ታመኑ፤ እንዲሁም በቅርቡ የምናገኘውን እርግጠኛ የሆነ ‘እውነተኛ ሕይወት’ አጥብቃችሁ ያዙ።—1 ጢሞ. 6:19

ወጣቶች ሆይ፣ ጥበበኞች ሁኑ!

5. የዚህን ዓለም የወደፊት ዕጣ በተመለከተ ምን ይሰማሃል?

5 ታላቁ ፈጣሪያቸውን የሚያስቡ ወጣቶች ከእኩዮቻቸው የበለጠ ጥበበኞች ናቸው። (መዝሙር 119:99, 100ን አንብብ።) የአምላክ ዓይነት አመለካከት ስላላቸው ይህ ዓለም በቅርቡ እንደሚጠፋ በሚገባ ያውቃሉ። እስከ አሁን ባሳለፋችሁት አጭር ዕድሜ እንኳ አስፈሪና አስጨናቂ ሁኔታዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመሩ መምጣታቸውን ሳታስተውሉ አትቀሩም። ተማሪዎች ከሆናችሁ ስለ አካባቢ መበከል፣ ስለ ምድር ሙቀት መጨመር፣ ስለ ደኖች መጨፍጨፍና ተመሳሳይ ስለሆኑ ሌሎች ችግሮች ሰምታችሁ ይሆናል። እነዚህ ሁኔታዎች አብዛኞቹን ሰዎች በእጅጉ የሚያሳስቧቸው ቢሆንም የሰይጣን ዓለም መጨረሻ መቅረቡን የሚጠቁመው ምልክት ክፍል መሆናቸውን የሚገነዘቡት ግን የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።—ራእይ 11:18

6. አንዳንድ ወጣቶች የተታለሉት እንዴት ነው?

6 የሚያሳዝነው ግን ወጣት የሆኑ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ቸልተኞች ከመሆናቸውም ሌላ ይህ ሥርዓት ሊጠፋ የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ይዘነጋሉ። (2 ጴጥ. 3:3, 4) ሌሎች ደግሞ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር በመግጠማቸው እንዲሁም ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የመመልከት ልማድ ስለተጠናወታቸው ከባድ ኃጢአት ፈጽመዋል። (ምሳሌ 13:20) የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም በቀረበበት በዚህ ወቅት የአምላክን ሞገስ ማጣት ምንኛ የሚያሳዝን ነው! በዚህ ረገድ እስራኤላውያን በ1473 ከክርስቶስ ልደት በፊት ካጋጠማቸው ሁኔታ ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ። በወቅቱ በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍረው የነበሩት እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበው ነበር። ታዲያ ያጋጠማቸው ሁኔታ ምን ነበር?

ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ሲቃረቡ ተሰናከሉ

7, 8. (ሀ) ሰይጣን በሞዓብ ሜዳ ላይ ምን ዘዴ ተጠቅሟል? (ለ) በዛሬው ጊዜስ ምን ዓይነት ዘዴ ይጠቀማል?

7 በወቅቱ ሰይጣን፣ እስራኤላውያን ቃል የተገባላቸውን ውርሻ እንዳያገኙ ለማድረግ ፈልጎ ነበር። ሰይጣን፣ ነቢዩ በለዓም እስራኤላውያንን እንዲረግማቸው ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ሲቀር ይበልጥ መሠሪ የሆነ ዘዴ ተጠቀመ። ይህም እስራኤላውያን የይሖዋን ሞገስ የሚያሳጣቸውን ድርጊት እንዲፈጽሙ ማድረግ ነበር። የሞዓብ ሴቶች እስራኤላውያንን ከእነሱ ጋር ዝሙት እንዲፈጽሙ በማድረግ አሳቷቸው፤ በዚህ ወቅት ዲያብሎስ በተወሰነ መጠን ተሳክቶለት ነበር። ሕዝቡ ከሞዓብ ሴቶች ጋር የጾታ ብልግና የፈጸመ ሲሆን ብኤልፌጎርንም ማምለክ ጀመረ! አምላክ ያዘጋጀላቸውን ውድ ስጦታ ለመቀበል ማለትም ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በጣም ተቃርበው የነበረ ቢሆንም 24,000 የሚያህሉ እስራኤላውያን ሕይወታቸውን አጡ። ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው!—ዘኍ. 25:1-3, 9

8 በዛሬው ጊዜ፣ ከተስፋይቱ ምድር የላቀ ውርሻ ለማግኘት ማለትም ወደ አዲሱ ሥርዓት ለመግባት በጣም ተቃርበናል። ሰይጣን እንደለመደው የአምላክን ሕዝቦች አቋም ለማበላሸት የጾታ ብልግናን መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። በዓለም ውስጥ ያለው የሥነ ምግባር አቋም እያዘቀጠ ከመምጣቱ የተነሳ ዝሙት መፈጸም ምንም ነውር እንደሌለውና ግብረ ሰዶምም የአንድ ሰው የግል ምርጫ እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። አንዲት ክርስቲያን እህት “ልጆቼ ግብረ ሰዶምም ሆነ ከጋብቻ ውጪ የጾታ ግንኙነት መፈጸም በአምላክ ዓይን ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነ የሚማሩት ቤት ውስጥና በመንግሥት አዳራሽ ብቻ ነው” ብላለች።

9. “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ” ላይ ምን ሊያጋጥም ይችላል? ወጣቶች ይህን ችግር መቋቋም የሚችሉትስ እንዴት ነው?

9 ታላቁ ፈጣሪያቸውን የሚያስቡ ወጣቶች የጾታ ግንኙነት ከሕይወትና ከመዋለድ ጋር የተያያዘ ቅዱስ ስጦታ መሆኑን ያውቃሉ። በመሆኑም የጾታ ግንኙነት መፈጸም ያለበት አምላክ ባዘዘው መሠረት ማለትም በትዳር ጓደኛሞች መካከል ብቻ መሆኑን ይገነዘባሉ። (ዕብ. 13:4) ይሁንና የጾታ ፍላጎት በሚያይልበትና የአንድን ሰው አመለካከት ሊያዛባ በሚችልበት “አፍላ የጉርምስና ዕድሜ” ላይ ንጽሕናን ጠብቆ መኖር ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። (1 ቆሮ. 7:36 NW) አላስፈላጊ የሆነ ሐሳብ ወደ አእምሮህ በሚመጣበት ጊዜ ምን ታደርጋለህ? ይሖዋ ንጹሕ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር እንድትችል እንዲረዳህ አጥብቀህ ጸልይ። ይሖዋ ከልባቸው ወደ እሱ የሚጸልዩ ሰዎችን ይሰማል። (ሉቃስ 11:9-13ን አንብብ።) የሚያንጹ ነገሮችን አንስቶ መወያየት አእምሯችን በመልካም ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል።

ግቦቻችሁን በጥበብ ምረጡ!

10. የትኛውን መጥፎ አስተሳሰብ ማስወገድ ይኖርብናል? ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን?

10 በዓለም ውስጥ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች ራሳቸውን የማይገዙና ተድላን በማሳደድ የተጠመዱ የሆኑበት አንዱ ምክንያት “ራእይ” ስለሌላቸው ማለትም መለኮታዊ መመሪያ ስለማያገኙ ወይም አስተማማኝ የሆነ የወደፊት ተስፋ ስለሌላቸው ነው። (ምሳሌ 29:18) እነዚህ ወጣቶች፣ የአምላክን መመሪያ መቀበል ካቆሙት እንዲሁም ‘በተድላና በደስታ፣ ሥጋ በመብላትና የወይን ጠጅ በመጠጣት’ ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመሩ ከነበሩት በኢሳይያስ ዘመን የነበሩ እስራኤላውያን ጋር ይመሳሰላሉ። (ኢሳ. 22:13) በእነዚህ ሰዎች ከመቅናት ይልቅ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ባዘጋጀው ግሩም ተስፋ ላይ ለምን አታሰላስልም? በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምትገኝ የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ አዲስ ዓለም የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት ትጠባበቃለህ? ይሖዋ ከፊትህ የዘረጋልህን ‘የተባረከ ተስፋ በምትጠባበቅበት’ በዚህ ወቅት ‘ራስህን ለመግዛት’ ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለህ? (ቲቶ 2:12, 13) ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ በግብህና በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

11. ተማሪ የሆኑ ወጣት ክርስቲያኖች ተግተው መማር ያለባቸው ለምንድን ነው?

11 ዓለም፣ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ ለሰብዓዊ ግቦች ቅድሚያውን እንዲሰጡ ይፈልጋል። እርግጥ ነው፣ ተማሪዎች ከሆናችሁ መደበኛ ትምህርታችሁን በትጋት መከታተል ይኖርባችኋል። ይሁን እንጂ የምትማሩት ጥሩ ሥራ ለመያዝ ብቻ ሳይሆን ውጤታማ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ለመሆንና በጉባኤያችሁ ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ለማበርከት መሆኑን መዘንጋት አይኖርባችሁም። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ደግሞ ከሌሎች ጋር ሐሳብ ለሐሳብ የመግባባት፣ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የማሰብ እንዲሁም ነገሮችን ረጋ ብሎ በአክብሮት የማስረዳት ችሎታ ሊኖራችሁ ይገባል። ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑና በውስጡ የሚገኙትን መመሪያዎች በሕይወታቸው ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ ወጣቶች ከሁሉ የተሻለውን ትምህርት እያገኙ ከመሆኑም ሌላ ስኬታማና ዘላለማዊ የሆነ የወደፊት ተስፋ ለመውረስ የሚያስችላቸውን ጥሩ መሠረት ጥለዋል።—መዝሙር 1:1-3ን አንብብ። *

12. ክርስቲያን ወላጆች የእነማንን ምሳሌ መኮረጅ ይኖርባቸዋል?

12 በጥንቷ እስራኤል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር ይመለከቱት ነበር። ወላጆች ለልጆቻቸው ሁሉንም የሕይወት ዘርፍ የሚዳስሱ በተለይ ደግሞ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮሩ ትምህርቶችን ይሰጧቸው ነበር። (ዘዳ. 6:6, 7) በመሆኑም ወላጆቻቸውና አምላካዊ ፍርሃት ያላቸው በዕድሜ የጎለመሱ ሰዎች የሚሰጧቸውን ምክር የሚሰሙ ወጣት እስራኤላውያን እውቀት ብቻ ሳይሆን ጥበብና ማስተዋል እንዲሁም ጥሩ የመረዳትና የማሰብ ችሎታ ይኖራቸው ነበር። እነዚህ ደግሞ መለኮታዊ ትምህርት ሊያስገኛቸው የሚችላቸው ውድ ነገሮች ናቸው። (ምሳሌ 1:2-4፤ 2:1-5, 11-15) በዛሬው ጊዜም ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ለማስተማር ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።

ማዳመጥ ያለባችሁ ማንን ነው?

13. አንዳንድ ወጣቶች ምን ዓይነት ምክር ይሰጣቸዋል? ጠንቃቆች መሆን ያለባቸውስ ለምንድን ነው?

13 ወጣቶች ሰብዓዊ ስኬት ላይ እንዲደርሱ የሚያበረታቷቸውን በትምህርት ቤት የሚገኙ አማካሪዎች ጨምሮ ከሌሎች ሰዎች ምክር ይሰጣቸዋል። እናንት ወጣቶች፣ የሚሰጧችሁን ምክሮች የአምላክን ቃል እንዲሁም ታማኝና ልባም ባሪያ የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በመጠቀም መዝኗቸው፤ ይህንንም ስታደርጉ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጣችሁ ጸልዩ። ሰይጣን በዋነኝነት የጥቃት ዒላማ የሚያደርገው ወጣቶችንና ተሞክሮ የሌላቸውን መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችሁ ሳታውቁ አትቀሩም። ለምሳሌ ያህል፣ በኤደን ገነት፣ ብዙ ተሞክሮ የሌላት ሔዋን፣ ሰይጣን ምንም ዓይነት አሳቢነት ያላሳያት ቢሆንም ሰምታዋለች። ሔዋን፣ ለእሷ ያለውን አሳቢነት በተለያዩ መንገዶች የገለጸላትን ይሖዋን ሰምታ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ምንኛ የተለየ በሆነ ነበር!—ዘፍ. 3:1-6

14. ይሖዋንም ሆነ የሚያምኑ ወላጆቻችንን ማዳመጥ ያለብን ለምንድን ነው?

14 እናንት ወጣቶች፣ ታላቁ ፈጣሪያችሁ እናንተንም ይወዳችኋል፤ ይህ ፍቅሩ ለእናንተ ካለው አሳቢነት የመነጨ ነው። ይሖዋ አሁን ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ደስተኛ ሆናችሁ እንድትኖሩ ይፈልጋል! በመሆኑም እናንተንም ሆነ እሱን የሚያመልኩትን ሁሉ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ ወላጅ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” በማለት ይመክራል። (ኢሳ. 30:21) አምላክን ከልብ የሚወዱ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ማግኘት ተጨማሪ በረከት ነው። በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ነገሮችና የምታወጣቸውን ግቦች በተመለከተ ወላጆችህ የሚሰጡህን ምክር በአክብሮት ማዳመጥህ ተገቢ ነው። (ምሳሌ 1:8, 9) ከዚህም በላይ ወላጆችህ በዓለም ከሚገኘው ሀብትና ክብር የላቀ ዋጋ ያለውን የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ይፈልጋሉ።—ማቴ. 16:26

15, 16. (ሀ) በይሖዋ ላይ ምን ዓይነት ትምክህት ሊኖረን ይችላል? (ለ) ከባሮክ ታሪክ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

15 ታላቁ ፈጣሪያቸውን የሚያስቡ ሁሉ ይሖዋ “ከቶ” እንደማይተዋቸውና “በፍጹም” እንደማይጥላቸው በመተማመን ኑሯቸውን ቀላል ያደርጋሉ። (ዕብራውያን 13:5ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነቱ ጤናማ አመለካከት ከዓለም አስተሳሰብ ጋር ስለሚቃረን የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። (ኤፌ. 2:2) በዚህ ረገድ፣ ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ልትጠፋ በተቃረበችበት አስጨናቂ ወቅት ይኖር የነበረውንና የኤርምያስ ጸሐፊ የሆነውን የባሮክን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት።

16 ባሮክ ቁሳዊ ነገሮችን በማካበት የተደላደለ ሕይወት መምራት ሳይፈልግ አልቀረም። ይሖዋ ሁኔታውን በመመልከት ባሮክ ለራሱ ‘ታላቅ ነገርን’ እንዳይሻ በደግነት ምክር ሰጥቶታል። ባሮክ ይሖዋን በመስማት በኢየሩሳሌም ላይ ከደረሰው ጥፋት መትረፉ ትሑትና ጥበበኛ መሆኑን ያሳያል። (ኤር. 45:2-5) በሌላ በኩል ግን ለራሳቸው ‘ታላቅ ነገርን’ ያከማቹት በባሮክ ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ ባለመስጠታቸው ባቢሎናውያን ጥሪታቸውን በሙሉ ወስደውባቸዋል። አብዛኞቹ ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥተዋል። (2 ዜና 36:15-18) የባሮክ ታሪክ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት በዓለም ከሚገኝ ሀብትና ክብር ይልቅ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል።

ልንኮርጃቸው የሚገቡ ምሳሌዎች

17. ኢየሱስ፣ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ የይሖዋ አገልጋዮች ጥሩ ምሳሌ የሆኑት እንዴት ነው?

17 የአምላክ ቃል፣ በሕይወት ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንድንቀጥል የሚረዱና ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ የሕይወት ታሪኮችን ይዟል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ፣ በምድር ላይ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ እጅግ የላቀ ችሎታ የነበረው ቢሆንም ትኩረቱን ለሰዎች ዘላለማዊ ጥቅም ሊያስገኝላቸው በሚችለው ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በመስበኩ ሥራ ላይ አድርጓል። (ሉቃስ 4:43) ሐዋርያው ጳውሎስም ጥሩ ገቢ የሚያስገኝለት ሥራ መሥራት ሲችል ለይሖዋ ምርጡን ለመስጠት ሲል ጊዜውንና ጉልበቱን ምሥራቹን ለመስበክ ተጠቅሞበታል። የጳውሎስ ‘እውነተኛ የእምነት ልጅ’ የሆነው ጢሞቴዎስም የእሱን ግሩም ምሳሌ ተከትሏል። (1 ጢሞ. 1:2) ኢየሱስ፣ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በመረጡት የሕይወት ጎዳና ተቆጭተው ይሆን? በፍጹም! እንዲያውም ጳውሎስ ዓለም ያቀረበለት ነገር አምላክን ለማገልገል ካገኘው መብት ጋር ሲወዳደር እንደ “ጉድፍ” የሚቆጠር መሆኑን ተናግሯል።—ፊልጵ. 3:8-11

18. አንድ ወጣት ወንድም በሕይወቱ ውስጥ ምን ትልቅ ለውጥ አድርጓል? በወሰደው እርምጃ ያልተቆጨው ለምንድን ነው?

18 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች የኢየሱስ፣ የጳውሎስና የጢሞቴዎስ ዓይነት እምነት አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ የነበረው አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እመራ ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ የሥራ እድገት አገኘሁ። ሥራው ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ቢሆንም እኔ ግን ነፋስን እንደምከተል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ለድርጅቱ ኃላፊዎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ያለኝን ፍላጎት ስነግራቸው በሥራው ይቀጥላል ብለው በማሰብ ወዲያውኑ የደሞዝ ጭማሪ አደረጉልኝ። እኔ ግን ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ ነበር። ብዙ ሰዎች ይህን ጥሩ ሥራ ትቼ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር የወሰንኩት ለምን እንደሆነ አይገባቸውም። ይህን ዓይነቱን ውሳኔ የወሰንኩት ራሴን ለአምላክ ስወስን ከገባሁት ቃል ጋር ተስማምቼ መኖር ስለፈለግሁ ነው። በአሁኑ ወቅት ሕይወቴ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ ስለሆነ ገንዘብም ሆነ ዝና ሊያስገኘው የማይችለው ይህ ነው የማይባል ደስታና እርካታ አለኝ።”

19. ወጣቶች ምን ጥበብ ያለበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ተበረታተዋል?

19 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች እንዲህ ያለውን ጥበብ ያለበት ምርጫ አድርገዋል። በመሆኑም እናንተ ወጣቶች፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስቡ የይሖዋን ቀን አቅርባችሁ ተመልከቱ። (2 ጴጥ. 3:11, 12) በዚህ ዓለም የተቻላቸውን ያህል መጠቀም በሚፈልጉ ሰዎች አትቅኑ። ከዚህ ይልቅ ከልብ የሚወዷችሁ የሚሰጧችሁን ምክር አዳምጡ። አስተማማኝና ዘላለማዊ ጥቅም ስለሚያስገኝላችሁ ‘በሰማይ ሀብት አከማቹ።’ (ማቴ. 6:19, 20፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።) አዎን፣ ታላቁ ፈጣሪያችሁን አስቡ። እንዲህ ካደረጋችሁ ይሖዋ ይባርካችኋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ከፍተኛ ትምህርትንና ሥራን በሚመለከት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የጥቅምት 1, 2005 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26-31⁠ን ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• በአምላክ ላይ እምነት እንዳለን እንዴት ማሳየት እንችላለን?

• ከሁሉ የተሻለው ትምህርት የቱ ነው?

• ከባሮክ ምን እንማራለን?

• ግሩም ምሳሌ የሚሆኑን እነማን ናቸው? ለምንስ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን ትምህርት ይሰጣል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባሮክ ይሖዋን በመስማት ከኢየሩሳሌም ጥፋት መትረፍ ችሏል። ከዚህ ምን መማር ትችላለህ?