በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከቤተሰብና ከጉባኤ ርቀው ቢኖሩም አልተረሱም

ከቤተሰብና ከጉባኤ ርቀው ቢኖሩም አልተረሱም

ከቤተሰብና ከጉባኤ ርቀው ቢኖሩም አልተረሱም

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ባልደረቦቹን “ዕድሉ ካለን ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” በማለት አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ገላ. 6:10) ዛሬም ቢሆን ይህን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መመሪያ በመከተል ለእምነት ባልደረቦቻችን መልካም ለማድረግ የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እንፈልጋለን። የክርስቲያን ጉባኤን ፍቅራዊ እንክብካቤ ማግኘት ከሚያስፈልጋቸውና ከሚገባቸው መካከል በመጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ውድ አረጋውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይገኙበታል።

እውነት ነው፣ በአንዳንድ አገሮች ቤተሰቦች አረጋዊ ወላጆቻቸውን በቤት ውስጥ መጦራቸው የተለመደ ነው። በሌሎች አገሮች ግን በርካታ አረጋውያን አብዛኛውን ጊዜ እንክብካቤ የሚደረግላቸው በመጦሪያ ተቋማት ውስጥ ነው። ታዲያ በመጦሪያ ተቋማት ስለሚገኙ አረጋውያን ክርስቲያኖች ምን ለማለት ይቻላል? ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል? ከቤተሰብ አባሎቻቸው ድጋፍ የማያገኙ ከሆነ ሁኔታውን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? የክርስቲያን ጉባኤስ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? እነዚህን አረጋውያን አዘውትረን የምንጠይቃቸው ከሆነ ምን ጥቅም እናገኛለን?

በመጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚያጋጥሙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች

አረጋውያን ክርስቲያኖች የሚገቡባቸው የመጦሪያ ተቋማት የሚገኙት በሌላ ጉባኤ ክልል ውስጥ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት የዚያ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን አረጋውያን ስለማያውቋቸው ቶሎ ቶሎ የመጠየቁ ጉዳይ ወደ አእምሯቸው አይመጣ ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ፣ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ አብረዋቸው የሚኖሩት ሰዎች የሌላ እምነት ተከታዮች እንደሚሆኑ ምንም አያጠራጥርም። ይህም ሁኔታውን አስቸጋሪ ሊያደርግባቸው ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ የመጦሪያ ተቋማት በግቢው ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዲከናወኑ ዝግጅት ያደርጋሉ። በአረጋውያን መንከባከቢያ ተቋም ውስጥ የሚሠራ አንድ ነርስ፣ “ሐሳባቸውን መግለጽ የሚቸግራቸው የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንዳንድ አረጋውያን ፈቃደኝነታቸው ሳይጠየቅ በተሽከርካሪ ወንበር እየተገፉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተወስደዋል” በማለት ተናግሯል። ከዚህም በላይ የተቋሙ ሠራተኞች የነዋሪዎቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ትንሽ ለወጥ ለማድረግ ሲሉ ብዙውን ጊዜ በግቢው ውስጥ የልደት በዓል፣ ገና ወይም ፋሲካ እንዲከበር ያደርጋሉ። በተጨማሪም በመጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ኅሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ምግብ እንዲበሉ ቀርቦላቸዋል። (ሥራ 15:29) አረጋውያን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አዘውትረን የምንጠይቃቸው ከሆነ እንደነዚህ የመሰሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲወጡ ልንረዳቸው እንችላለን።

ከጉባኤው የሚገኝ ድጋፍ

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ጧሪ ቤተሰብ የሌላቸውን አረጋውያንን የመርዳት ኃላፊነታቸውን በትጋት ይወጡ ነበር። (1 ጢሞ. 5:9) በተመሳሳይም ዛሬ ያሉ የበላይ ተመልካቾች በእነሱ ክልል ባለ የመጦሪያ ተቋም ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ችላ እንዳይባሉ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። * ሮበር የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች አረጋውያን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማየትና አብረዋቸው ለመጸለይ በግለሰብ ደረጃ ቢጠይቋቸው ጥሩ ነው። ጉባኤው እነሱን ለመንከባከብ ብዙ ማድረግ የሚችለው ነገር አለ።” አረጋውያንን ለመጠየቅ ጊዜ የምንመድብ ከሆነ የተቸገሩትን ሰዎች መንከባከብ በይሖዋ ፊት ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደተሰጠው የተገነዘብን መሆኑን እናሳያለን።—ያዕ. 1:27

አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሽማግሌዎች በክልላቸው በሚገኙ መጦሪያ ተቋማት ውስጥ ላሉ ወንድሞችና እህቶች በፈቃደኝነት ተነሳስተው እርዳታ ለመስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት ያደርጋሉ። ሮበር አንዱ እርዳታ ምን ሊሆን እንደሚችል ሲገልጽ፣ “አረጋዊ ወንድሞችን እና እህቶችን የሚችሉ ከሆነ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ልናበረታታቸው ይገባል” በማለት ተናግሯል። ይሁን እንጂ አረጋውያኑ ወደ መንግሥት አዳራሽ መሄድ የማይችሉ ከሆነ ሽማግሌዎች ሌላ ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። በ80ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙትና በአርትራይተስ በሽታ የሚሠቃዩት እህት ዣክሊን ስብሰባዎችን በስልክ ይከታተላሉ። ዣክሊን እንዲህ ብለዋል:- “ስብሰባዎቹ ሲከናወኑ በቀጥታ መስማቴ በእጅጉ ጠቅሞኛል። በዚህ ዓለም ላይ ከምንም በላይ እንዲያመልጠኝ የማልፈልገው ነገር ቢኖር ስብሰባ ነው!”

አንድ አረጋዊ ክርስቲያን ስብሰባዎችን በስልክ መከታተል ካልቻሉ ሽማግሌዎች በስብሰባዎቹ ላይ የሚቀርቡትን ንግግሮች በካሴት እንዲቀዱ ማድረግ ይችላሉ። የተቀዳውን ንግግር በመጦሪያ ተቋሙ ውስጥ ለሚገኙ ወንድም ወይም እህት ለማድረስ የሚሄደው ሰው አጋጣሚውን የሚያበረታታ ጭውውት ለማድረግ ሊጠቀምበት ይችላል። አንድ የበላይ ተመልካች፣ “ለአረጋዊ ወንድሞችና እህቶች የጉባኤው አባላት ስላሉበት ሁኔታ ማጫወታችን አሁንም ቢሆን የዚህ መንፈሳዊው ቤተሰብ አባል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል” በማለት ተናግሯል።

የሐሳብ ግንኙነቱ እንዳይቋረጥ ማድረግ

ለብዙ አረጋውያን፣ ወደ መጦሪያ ተቋም መግባት ጭንቀትና ግራ መጋባት እንደሚፈጥርባቸው የታወቀ ነው። በዚህም ምክንያት አንዳንድ አረጋውያን ራሳቸውን ያገላሉ። ይሁን እንጂ አረጋዊ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ወደ መጦሪያ ተቋሙ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ የምንጠይቃቸው እንዲሁም የማያቋርጥ ድጋፍ ልንሰጣቸው እንደምንፈልግ የምንገልጽላቸው ከሆነ ውስጣዊ ሰላማቸውን መልሰው እንዲያገኙና ደስተኛ እንዲሆኑ በእጅጉ እንረዳቸዋለን።—ምሳሌ 17:22

አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች የማገናዘብ ኃይላቸው ወይም የመስማት ችሎታቸው እየተዳከመ ሲመጣ አሊያም ደግሞ እንደ ልብ የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ እንዳይችሉ እንቅፋት የሚሆኑ ሌሎች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው፣ አንዳንዶች እነሱን መጠየቁ ፋይዳ የለውም የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ አረጋውያን ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረጉ ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም እነሱን መጠየቃችንን ለመቀጠል ጥረት ማድረጋችን ‘እርስ በርስ ለመከባበር’ ቀዳሚ መሆናችንን እንዳልተውን ያሳያል። (ሮሜ 12:10) አንድ አረጋዊ ወንድም በቅርብ የተፈጸሙ ነገሮችን የመርሳት ችግር ከጀመራቸው የድሮ ምናልባትም የልጅነት ታሪካቸውን እንዲነግሩን አሊያም ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት እንደሰሙ እንዲያጫውቱን ልናበረታታቸው እንችላለን። ሁኔታውን በትክክል የሚገልጹ ቃላቶች እየጠፉባቸው የሚቸገሩ ከሆነ ምን ልናደርግ እንችላለን? በትዕግሥት በማዳመጥ እንዲሁም አልፎ አልፎ የጠፉባቸውን ቃላት በማስታወስ ወይም ለማለት የፈለጉትን ሐሳብ ጠቅለል አድርገን በማስቀመጥ ታሪኩን እንዲቀጥሉልን ማበረታታት እንችላለን። ቃላት ተምታተውባቸው ወይም የመናገር ችግር ኖሮባቸው ሊነግሩን የፈለጉትን ነገር መረዳት አስቸጋሪ ከሆነብን የድምፃቸውን ቃና በትኩረት በመከታተል ሐሳባቸውን ለመረዳት ጥረት ማድረግ እንችላለን።

በቃል የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ የማይቻል ከሆነ ሌሎች መንገዶችን መጠቀም ይቻላል። ሎራንስ የተባለች አንዲት አቅኚ፣ ማድለን የሚባሉ አንዲት የ80 ዓመት ዕድሜ እህትን በየጊዜው እየሄደች ትጠይቃቸዋለች። እኚህ እህት መናገር አይችሉም። ሎራንስ እንዴት የሐሳብ ግንኙነት እንደምታደርግ ስትገልጽ፣ “አንድ ላይ በምንጸልይበት ጊዜ የማድለንን እጅ እይዛለሁ። በጸሎት ወቅት እጆቼን ጨመቅ በማድረግና ዓይኖቻቸውን በማርገብገብ ለዚህ ውድ ጊዜ ያላቸውን አድናቆት ይገልጻሉ” በማለት ተናግራለች። የአረጋውያን ወዳጆቻችንን እጅ በመያዝ ወይም እቅፍ በማድረግ ፍቅራችንን የምንገልጽ ከሆነ በእርግጥም መንፈሳቸው በእጅጉ እንዲረጋጋ ሊያደርግ ይችላል።

የቅርብ ክትትል ማድረጋችሁ ጥቅም አለው

አረጋውያንን በየጊዜው መጠየቃችሁ በራሱ የተሻለ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። በመጦሪያ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን በመጠየቅ ወደ 20 የሚጠጉ ዓመታት ተሞክሮ ያላት ዳንየል የተባለች እህት፣ “አንድ አረጋዊ በየጊዜው የሚጠየቁ ከሆነ በመጦሪያ ተቋም ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የተሻለ እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል” ብላለች። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሮበር እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አረጋውያንን የሚንከባከቡ ነርሶች፣ አንድን አረጋዊ በቋሚነት የሚጠይቅን ሰው ከሌላው በበለጠ ያዳምጡታል። አልፎ አልፎ ለሚመጣ ጠያቂ እንዲህ ዓይነት አክብሮት ላያሳዩት ይችላሉ።” ነርሶች አብዛኛውን ጊዜ ነዝናዛ ቤተሰቦች ስለሚያጋጥሟቸው አመስጋኝነታቸውን ለሚገልጹ ጠያቂዎች አድናቆት አላቸው። በተጨማሪም ከነርሶቹ ጋር ጥሩ ግንኙነት ካዳበርን በእነሱ እንክብካቤ ሥር የሚገኙ የአንድን አረጋዊ የይሖዋ ምሥክር አመለካከትና እምነት ለማክበር ሊነሳሱ ይችላሉ።

ከዚህም በላይ ቀለል ያሉ ሥራዎችን በማገዝ ከሠራተኞቹ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ እንችላለን። በአንዳንድ አካባቢዎች ብቃት ያለው የሰው ኃይል እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ በመኖሩ ለአረጋውያን የሚሰጠውን እንክብካቤ ጥራት ቀንሶታል። ሬቤካ የተባለች አንዲት ነርስ “በምግብ ሰዓት ሥራ በጣም ስለሚበዛብን ጠያቂዎች በዚህ ሰዓት መጥተው ወዳጃቸውን እንዲመገብ ቢረዱት ጥሩ ነው” በማለት ተናግራለች። በምን ረገድ መርዳት እንደምንችል ሐሳብ እንዲሰጡን የተቋሙን ሠራተኞች ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት አይገባንም።

ወደ አንድ የመጦሪያ ተቋም አዘውትረን የምንሄድ ከሆነ አረጋዊ ወንድማችን ወይም እህታችን ምን እንደሚያስፈልጋቸው ማስተዋልና ሠራተኞቹን በማስፈቀድ ቅድሚያውን ወስደን ፍላጎታቸውን ማሟላት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል የመኖሪያ ክፍላቸውን በወዳጆቻቸው ፎቶግራፎች ወይም ልጆች በሠሯቸው ሥዕሎች አማካኝነት ማስዋብ ይቻላል። የግለሰቡን ደህንነት በአእምሯችን በመያዝ የሚያሞቅ መደረቢያ ወይም ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ማምጣት እንችላለን። ተቋሙ መናፈሻ ቦታ ካለው አረጋዊው ወዳጃችን ንጹሕ አየር እንዲቀበሉ ለማድረግ ማንሸራሸር እንችል ይሆን? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሎራንስ፣ “ማድለን በየሳምንቱ የእኔን መምጣት በጉጉት ይጠባበቃሉ። ልጆች ይዤ ከሄድኩ ወዲያው ፈገግ የሚሉ ሲሆን ዓይናቸውም ይበራል!” ብላለች። እንዲህ የመሰሉ በራስ አነሳሽነት የሚደረጉ የደግነት ተግባራት በመጦሪያ ተቋም ውስጥ ለሚኖሩ አረጋውያን ትልቅ ለውጥ ያመጡላቸዋል።—ምሳሌ 3:27

መጠየቃችን የሚያስገኛቸው የጋራ ጥቅሞች

አረጋዊ የሆነን አንድ ሰው በየጊዜው መጠየቃችን ‘የፍቅራችንን እውነተኛነት’ ለማረጋገጥ ያስችለናል። (2 ቆሮ. 8:8) በምን መንገድ? አንድ ወዳጃችን ከቀን ወደ ቀን እየተዳከመ ሲሄድ መመልከት ጭንቀት ሊፈጥርብን ይችላል። ሎራንስ እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “መጀመሪያ ላይ የማድለን አቅም ማጣት በጣም ስሜቴን ይነካው ስለነበር ጠይቄያቸው በተመለስኩ ቁጥር አለቅስ ነበር። ሆኖም አጥብቀን መጸለያችን ፍርሃታችንን እንድንቋቋም የረዳን ሲሆን ለምንጠይቃቸው ሰዎችም ይበልጥ የብርታት ምንጭ እንደምንሆናቸው ተገንዝቤያለሁ።” ሮበር፣ በፓርኪንሰን በሽታ የሚሠቃዩ ላሪ የሚባሉ አንድን ወንድም ለዓመታት ጠይቋቸዋል። ሮበር እንዲህ ብሏል:- “ላሪ በበሽታው በጣም ከመጎዳታቸው የተነሳ የሚናገሩትን አንዱንም ቃል መረዳት አልችልም ነበር። ሆኖም አብረን ስንጸልይ አሁንም የድሮ እምነታቸው እንዳለ ይሰማኛል።”

አረጋውያን የሆኑ የእምነት አጋሮቻችንን በምንጠይቅበት ጊዜ እነሱን መርዳት ብቻ ሳይሆን ራሳችንም እንጠቀማለን። የተለያየ እምነት ባላቸው ሰዎች መካከል እየኖሩም እንኳ ይሖዋን የሙጥኝ ብለው ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኝነት ስንመለከት እኛም እምነት እንዲኖረንና ድፍረት እንድናሳይ ያስተምረናል። አጥርተው የመስማትና የማየት ችግር ቢኖርባቸውም መንፈሳዊ ምግብ ለማግኘት ያላቸው ጉጉት፣ ‘ሰው ከአምላክ አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር’ አጉልቶ ያሳያል። (ማቴ. 4:4) አረጋውያን፣ አንድ ሕፃን በሚያሳየው ፈገግታ ወይም አብሮ እንደ መመገብ በመሳሰሉ ትንንሽ ነገሮች መደሰታቸው እኛም ባለን ነገር መርካት እንዳለብን ያሳስበናል። እነዚህ አረጋውያን፣ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ፍቅር ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል።

እውነት ነው፣ ለአረጋውያን ድጋፍ በመስጠታችን መላው ጉባኤ ይጠቀማል። እንዴት? የአቅም ገደብ ያለባቸው ወንድሞችና እህቶች የወንድሞች ፍቅርና ርኅራኄ በጣም ያስፈልጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ ጉባኤው ርኅራኄን ለማሳየት አጋጣሚ ይፈጥርለታል። እንግዲያው ሁላችንም አረጋውያንን መንከባከብ ሌላውን ማገልገል ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል አንዱ ክፍል መሆኑን ተገንዝበን ረጅም ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም እንኳ ለአረጋውያን አሳቢነት ማሳየት ይገባናል። (1  ጴጥ. 4:10, 11) በዚህ በኩል ሽማግሌዎች ቅድሚያውን የሚወስዱ ከሆነ ሌሎች የጉባኤው አባላት እንዲህ ያለው ተግባር ችላ ሊባል የማይገባው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ መሆኑን እንዲያስተውሉ ይረዷቸዋል። (ሕዝ. 34:15, 16) ከልብ ተነሳስተን ፍቅራዊ ድጋፍ የምናደርግላቸው ከሆነ አረጋውያን የእምነት ባልደረቦቻችን እንዳልተረሱ እንዲሰማቸው ልናደርግ እንችላለን!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 አንድ የጉባኤ ጸሐፊ የጉባኤው አባል የነበሩ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ከጉባኤው ክልል ውጭ ወደሚገኝ የመጦሪያ ተቋም እንደገቡ ሲያውቅ በዚያ አካባቢ ለሚገኙ የጉባኤ ሽማግሌዎች በፍጥነት ማሳወቁ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ ፍቅር የሚንጸባረቅበት ድርጊት ነው።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“አንድ አረጋዊ በየጊዜው የሚጠየቁ ከሆነ በመጦሪያ ተቋም ውስጥ ያሉ ሠራተኞች የተሻለ እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል”

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልባዊ ጸሎት ማቅረባችን አረጋዊ የሆኑት የእምነት አጋራችን ውስጣዊ ሰላማቸውን መልሰው እንዲያገኙ ሊረዳቸው ይችላል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አረጋውያን የሆኑ የእምነት አጋሮቻችንን እንደምንወዳቸው ማሳየታችን ያጠነክራቸዋል