በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከከንቱ ነገሮች’ ራቁ

‘ከከንቱ ነገሮች’ ራቁ

‘ከከንቱ ነገሮች’ ራቁ

“ከንቱ ተስፋን [“ነገር፣” የ1954 ትርጉም] የሚያሳድድ ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል።”—ምሳሌ 12:11

1. ካሉን ጠቃሚ ነገሮች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? በእነዚህ ነገሮች መጠቀም የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?

ሁላችንም የተለያዩ ጠቃሚ ነገሮች አሉን። በተወሰነ መጠን ጤንነትና ጥንካሬ እንዲሁም በተፈጥሮ ያገኘነው ችሎታ ወይም ቁሳዊ ሀብት ይኖረን ይሆናል። ይሖዋን ስለምንወድ እነዚህን ነገሮች እሱን ለማገልገል በማዋል “እግዚአብሔርን በሀብትህ . . . አክብረው” የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስደስተናል።—ምሳሌ 3:9

2. መጽሐፍ ቅዱስ ከንቱ ስለሆኑ ነገሮች ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል? ይህ ማስጠንቀቂያ ቃል በቃል ምን ትርጉም አለው?

2 በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ከንቱ ስለሆኑ ነገሮች የሚገልጽ ሲሆን እነዚህን በማሳደድ ያሉንን ነገሮች እንዳናባክን ያስጠነቅቀናል። በዚህ ረገድ ምሳሌ 12:11 ምን እንደሚል ልብ በል:- “መሬቱን የሚያርስ የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤ ከንቱ ተስፋን [“ነገር፣” የ1954 ትርጉም] የሚያሳድድ ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል።” ይህ ምሳሌ ቃል በቃል ምን ትርጉም እንዳለው መረዳት ከባድ አይደለም። አንድ ሰው ጊዜውንና ጉልበቱን ተጠቅሞ ጠንክሮ በመሥራት ቤተሰቡን የሚረዳ ከሆነ በተወሰነ ደረጃ አስተማማኝ ሁኔታ ይኖረዋል። (1 ጢሞ. 5:8) ይሁን እንጂ ጊዜውንና ጉልበቱን ከንቱ ነገሮችን በማሳደድ የሚያባክን ከሆነ “ማመዛዘን ይጐድለዋል።” እንዲህ ዓይነቱ ሰው መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት ሊቸገር እንደሚችል ግልጽ ነው።

3. መጽሐፍ ቅዱስ ከንቱ ስለሆኑ ነገሮች የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ከአምልኳችን ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

3 የዚህን ምሳሌ መሠረታዊ ሥርዓት ከአምልኳችን ጋር አያይዘን ብንመለከተውስ? ይሖዋን በትጋትና በታማኝነት የሚያገለግል ክርስቲያን እውነተኛ መተማመኛ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ የአምላክን በረከት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ከመሆኑም በላይ ለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ አለው። (ማቴ. 6:33፤ 1 ጢሞ. 4:10) በሌላ በኩል ግን አንድ ክርስቲያን ከንቱ በሆኑ ነገሮች ትኩረቱ የሚሰረቅ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድናም ሆነ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። እንዲህ ዓይነት አደጋ እንዳይደርስብን ምን ማድረግ እንችላለን? በሕይወታችን ውስጥ ከምናከናውናቸው ነገሮች መካከል ‘ከንቱ’ የሆኑትን ማስተዋል እንዲሁም እነዚህን ነገሮች ለማስወገድ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።—ቲቶ 2:11, 12ን አንብብ።

4. በጥቅሉ ሲታይ ከንቱ ነገሮች ምንድን ናቸው?

4 ታዲያ ከንቱ የተባሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? ጠቅለል አድርገን ለመግለጽ፣ እነዚህ ነገሮች ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን እንዳናገለግል እንቅፋት የሚሆኑብንን ነገሮች በሙሉ ያካትታሉ። መዝናኛዎችን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። እርግጥ ነው፣ መዝናኛ በልኩ ሲሆን ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ ከአምልኳችን ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ቸል ብለን በመዝናኛ ብዙ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ፣ መዝናኛ መንፈሳዊነታችንን የሚጎዳ ከንቱ ነገር ይሆናል። (መክ. 2:24፤ 4:6) ይህ እንዳይሆን አንድ ክርስቲያን ውድ ጊዜውን እንዴት እየተጠቀመበት እንዳለ በጥንቃቄ በመመርመር ሚዛናዊ ለመሆን ጥረት ያደርጋል። (ቈላስይስ 4:5ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) ይሁን እንጂ ከመዝናኛ የበለጠ አደገኛ የሆኑ ሌሎች ከንቱ ነገሮችም አሉ። ከእነዚህ መካከል የሐሰት አማልክት ይገኙበታል።

ከከንቱ አማልክት ራቁ

5. “ከንቱ” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት እንዴት ነው?

5 መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ “ከንቱ” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የተሠራበት የሐሰት አማልክትን ለማመልከት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ትሰግዱላቸው ዘንድ ጣዖታትን [“ከንቱ አማልክትን፣” NW] አታብጁ፤ ምስል ወይም የማምለኪያ ዐምድ አታቁሙ፤ በምድራችሁም ላይ የተቀረጸ ድንጋይ አታኑሩ።” (ዘሌ. 26:1) ንጉሥ ዳዊት ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ምስጋናውም ብዙ ነው፤ ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ የሚገባው ነው። የአሕዛብ ሁሉ አማልክት ጣዖታት [“ከንቱ አማልክት፣” NW] ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።”—1 ዜና 16:25, 26

6. የሐሰት አማልክት ከንቱ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው?

6 ዳዊት፣ ለይሖዋ ታላቅነት ማስረጃ የሚሆኑ በርካታ ነገሮች እንዳሉ ገልጿል። (መዝ. 139:14፤ 148:1-10) እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን መግባታቸው እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነበር! በሌላ በኩል ግን ሕዝቡ ከእሱ ዘወር ብለው ለተቀረጹ ምስሎችና ለማምለኪያ አምዶች መስገዳቸው ሞኝነት ነበር! ሕዝቡ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ፣ የሐሰት አማልክቶቻቸው ከንቱ እንደሆኑና የሚያመልኳቸውን ሰዎች ቀርቶ ራሳቸውን እንኳ ማዳን እንደማይችሉ ታይቷል።—መሳ. 10:14, 15፤ ኢሳ. 46:5-7

7, 8. “ገንዘብ” እንደ አምላክ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

7 በዛሬው ጊዜም በበርካታ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች፣ የሰው እጅ ሥራ ለሆኑ ምስሎች ይሰግዳሉ፤ እነዚህ አማልክት በጥንት ጊዜ እንደነበሩት ሁሉ ዛሬም ከንቱ ናቸው። (1 ዮሐ. 5:21) መጽሐፍ ቅዱስ ከምስሎች በተጨማሪ ሌሎች ነገሮችንም እንደ አማልክት አድርጎ ይገልጻቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል:- “አንድ ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም።”—ማቴ. 6:24

8 “ገንዘብ” አምላክ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? በጥንቷ እስራኤል የሚገኝን አንድ ድንጋይ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ድንጋዩ፣ ቤት ለመሥራት ወይም ግንብ ለመገንባት ሊያገለግል ይችላል። በሌላ በኩል ግን “የማምለኪያ ዐምድ” ወይም “የተቀረጸ ድንጋይ” ተደርጎ ከተበጀ ለይሖዋ ሕዝቦች ማሰናከያ ይሆናል። (ዘሌ. 26:1) በተመሳሳይም ገንዘብ አስፈላጊ ሲሆን በተገቢው መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን። ገንዘብ፣ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚያስፈልገን ከመሆኑም በላይ በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ በሆነ መንገድ ልናውለው እንችላለን። (መክ. 7:12፤ ሉቃስ 16:9) ሆኖም ገንዘብን ከክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ካስበለጥነው አምላካችን ሆነ ማለት ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።) ሀብት ማካበት ከፍ ተደርጎ በሚታይበት ዓለም ውስጥ በዚህ ረገድ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ ይኖርብናል።—1 ጢሞ. 6:17-19

9, 10. (ሀ) ክርስቲያኖች ለሰብዓዊ ትምህርት ምን አመለካከት አላቸው? (ለ) ከፍተኛ ትምህርት መከታተል ምን አደጋ አለው?

9 ጠቃሚ ቢሆንም ከንቱ ሊሆን የሚችለው ሌላው ነገር ደግሞ ሰብዓዊ ትምህርት ነው። ልጆቻችን ሲያድጉ መተዳደሪያ ማግኘት እንዲችሉ ጥሩ ትምህርት እንዲማሩ እንፈልጋለን። ከዚህም በላይ በደንብ የተማረ ክርስቲያን፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን አንብቦ ለመረዳት እንዲሁም ችግር ሲያጋጥመው በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተጠቅሞ ጥሩ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ብሎም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማስተማር ይችላል። ጥሩ ትምህርት ማግኘት ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም ውጤቱ የሚክስ ነው።

10 በኮሌጅ ወይም በዩኒቨርሲቲ ስለሚሰጠው ከፍተኛ ትምህርትስ ምን ማለት ይቻላል? ስኬታማ ለመሆን እንዲህ ያለው ትምህርት አስፈላጊ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። ያም ሆኖ ግን ከፍተኛ ትምህርት የተከታተሉ ብዙ ሰዎች አእምሯቸው ጎጂ በሆነው በዚህ ዓለም ጥበብ ይሞላል። እንዲህ ያለውን ትምህርት የሚከታተሉ ሰዎች በይሖዋ አገልግሎት ሊውል የሚችለውን ውድ የወጣትነት ዘመናቸውን ያባክናሉ። (መክ. 12:1) ብዙ ሰዎች ከፍተኛ ትምህርት በተማሩባቸው አገሮች ውስጥ በአምላክ የሚያምኑት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በጣም ጥቂቶች መሆናቸው ምንም አያስገርምም። አንድ ክርስቲያን ግን አስተማማኝ ሕይወት ለመምራት ሲል የዚህን ዓለም ከፍተኛ ትምህርት ከመከታተል ይልቅ በይሖዋ ይታመናል።—ምሳሌ 3:5

ሥጋዊ ምኞቶች አምላክህ እንዲሆኑ አትፍቀድ

11, 12. ጳውሎስ ስለ አንዳንዶች ሲናገር “ሆዳቸው አምላካቸው ነው” ያለው ለምን ነበር?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ ሊሆን የሚችል ሌላ ነገርም እንዳለ ጠቁሟል። የእምነት አጋሮቻቸው ከነበሩት አንዳንዶቹን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ከዚህ በፊት ደጋግሜ እንደ ነገርኋችሁ፣ አሁንም እንደ ገና፣ ያውም በእንባ እነግራችኋለሁ፤ ብዙዎች የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፤ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፤ . . . ልባቸው ያረፈው በምድራዊ ነገር ላይ ነው።” (ፊልጵ. 3:18, 19) አንድ ሰው፣ ሆዱ አምላኩ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

12 ጳውሎስ የሚያውቃቸው እነዚያ ሰዎች ከእሱ ጋር ሆነው ይሖዋን ከማገልገል ይልቅ ለሥጋዊ ምኞቶቻቸው ቅድሚያ የሰጡ ይመስላል። አንዳንዶቹ ቃል በቃል ከመጠን በላይ በመብላትና በመጠጣት ሆዳሞች ወይም ሰካራሞች እስከመሆን ደርሰው ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 23:20, 21፤ ከዘዳግም 21:18-21 የ1954 ትርጉም ጋር አወዳድር።) ሌሎቹ ደግሞ በዘመኑ የነበረው ዓለም በሚያቀርባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ለመጠቀም ስለመረጡ ለይሖዋ አገልግሎት ሙሉ ትኩረት መስጠት አቅቷቸው ሊሆን ይችላል። እኛም የተደላደለ የሚባለውን ዓይነት ሕይወት ለመምራት ያለን ፍላጎት ይሖዋን በሙሉ ነፍስ እንዳናገለግል እንቅፋት እንዲሆንብን ፈጽሞ አንፍቀድ።—ቈላ. 3:23, 24

13. (ሀ) መጎምጀት ምንድን ነው? ጳውሎስ እንዴት አድርጎ ገልጾታል? (ለ) መጎመጀትን እንዴት ማስወገድ እንችላለን?

13 ጳውሎስ የሐሰት አምልኮን ሌላ ገጽታም ጠቅሷል። “ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም:- ዝሙት፣ ርኵሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው” በማለት ጽፏል። (ቈላ. 3:5) መጎምጀት፣ የራሳችን ያልሆነውን ነገር ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት ማሳደርን ያመለክታል። ለማግኘት የምንፈልገው ቁሳዊ ነገሮችን ሊሆን ይችላል። መጎምጀት የጾታ ብልግና የመፈጸም ምኞትንም እንኳ ሊጨምር ይችላል። (ዘፀ. 20:17) እንዲህ ያሉት ምኞቶች እንደ ጣዖት አምልኮ መቆጠራቸው ይህ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ያሳያል። ኢየሱስ እንዲህ ያሉ መጥፎ ምኞቶችን ለመቆጣጠር ማንኛውንም ጥረት ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌ ተጠቅሟል።—ማርቆስ 9:47ን አንብብ፤ 1 ዮሐ. 2:16

ከንቱ ከሆኑ ቃላት ተጠበቁ

14, 15. (ሀ) በኤርምያስ ዘመን የነበሩ ብዙ ሰዎችን ያሰናከላቸው “ከንቱ ነገር” ምንድን ነው? (ለ) ሙሴ የተናገራቸው ቃላት ጠቃሚ የነበሩት ለምንድን ነው?

14 ከንቱ ነገሮች፣ ቃላትንም ሊጨምሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለኤርምያስ እንዲህ ብሎት ነበር:- “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል።” (ኤር. 14:14) እነዚህ ሐሰተኛ ነቢያት በይሖዋ ስም እንደሚናገሩ ቢገልጹም የራሳቸውን ሐሳብና ጥበብ ያስፋፉ ነበር። በመሆኑም የሚናገሯቸው ቃላት “ከንቱ ነገር” እንዲሁም እርባና ቢስ ከመሆናቸውም በላይ የአምላክን ሕዝቦች መንፈሳዊነት የሚጎዱ ነበሩ። እንዲህ ያሉትን ከንቱ ቃላት ይሰሙ የነበሩ በርካታ ሰዎች በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት በባቢሎናውያን ወታደሮች ተገድለዋል።

15 ከዚህ በተቃራኒ ሙሴ ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ። ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ [“ከንቱ፣” የ1954 ትርጉም] ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፤ በምትወርሷትም ምድር ረጅም ዘመን ትኖራላችሁ።” (ዘዳ. 32:46, 47) አዎን፣ ሙሴ የተናገረው በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ነበር። በመሆኑም የተናገራቸው ቃሎች ለብሔሩ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነበሩ። እነዚህን ቃሎች ሰምተው ተግባራዊ ያደረጉ ሰዎች ረጅም ዘመን መኖር ከመቻላቸውም በላይ ባለጸጋ ሆነዋል። እኛም ምንጊዜም ቢሆን ከከንቱ ቃላት በመራቅ ጠቃሚ የሆኑትን የእውነት ቃላት አጥብቀን እንያዝ።

16. ከአምላክ ቃል ጋር የሚጋጩ ሳይንሳዊ ሐሳቦችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

16 በዛሬው ጊዜስ ከንቱ ቃላትን እንሰማለን? አዎን እንሰማለን። ለአብነት ያህል፣ አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብና በሌሎች መስኮች የተደረሰባቸው ሳይንሳዊ ግኝቶች በአምላክ ማመን እንደማያስፈልግና ሁሉም ነገር በተፈጥሮ ሂደት እንደመጣ ያረጋግጣሉ የሚል አመለካከት አላቸው። እንዲህ የመሰሉ እብሪት የተንጸባረቀባቸው ሐሳቦች ሊያሳስቡን ይገባል? በፍጹም! የሰው ጥበብ ከመለኮታዊ ጥበብ የተለየ ነው። (1 ቆሮ. 2:6, 7) ሰብዓዊ ትምህርት አምላክ ከገለጸው ትምህርት ጋር ሲጋጭ ምንጊዜም ቢሆን ስህተት የሚሆነው ሰብዓዊ ትምህርት እንደሆነ እናውቃለን። (ሮሜ 3:4ን አንብብ።) ሳይንስ በአንዳንድ መስኮች እድገት ቢያደርግም መጽሐፍ ቅዱስ የሰውን ጥበብ አስመልክቶ “የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው” በማለት ያሰፈረው ሐሳብ አሁንም ቢሆን እውነት ነው። ተወዳዳሪ ከሌለው የአምላክ ጥበብ ጋር ሲነጻጸር የሰው ልጆች አስተሳሰብ ከንቱ ነው።—1 ቆሮ. 3:18-20

17. የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎችም ሆነ ከሃዲዎች የሚናገሯቸውን ቃላት እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?

17 የሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት መሪዎች ንግግርም ከንቱ ለሆኑ ቃላት ምሳሌ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች በአምላክ ስም እንደሚናገሩ ቢገልጹም አብዛኞቹ የሚናገሯቸው ነገሮች በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፤ ከዚህም በላይ የሚናገሩት ነገር እርባና ቢስ ነው። ከሃዲዎችም በአምላክ ከተሾመው “ታማኝና ልባም ባሪያ” የበለጠ ጥበብ እንዳላቸው በመግለጽ ከንቱ ቃላት ይናገራሉ። (ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ሆኖም ከሃዲዎች የሚናገሩት የራሳቸውን ጥበብ ነው፤ የሚናገሯቸው ነገሮችም የሚሰማቸውን የሚያሰናክሉ ከንቱ ቃላት ናቸው። (ሉቃስ 17:1, 2) ታዲያ እኛ በእነሱ እንዳንታለል ምን ማድረግ እንችላለን?

ከከንቱ ቃላት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

18. በ1 ዮሐንስ 4:1 ላይ ያለውን ምክር በየትኞቹ መንገዶች ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?

18 አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ በዚህ ረገድ እንደሚከተለው በማለት ግሩም ምክር ሰጥቷል:- “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ በመንፈስ የተነገረን ቃል ሁሉ አትመኑ፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ፤ ምክንያቱም ብዙ ሐሰተኛ ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋል።” (1 ዮሐንስ 4:1 NW) ከሐዋርያው ዮሐንስ ምክር ጋር በሚስማማ መልኩ በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች የተማሩትን ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማወዳደር እንዲመረምሩት ሁልጊዜ እናበረታታቸዋለን። ይህ ምክር ለእኛም ጠቃሚ ነው። እውነትን የሚነቅፍ ወይም የጉባኤውን፣ የሽማግሌዎችን አሊያም የወንድሞቻችንን ስም የሚያጎድፍ ወሬ ብንሰማ የሰማነውን ነገር ሳናጣራ ሁኔታውን ዝም ብለን አንቀበልም። ከዚህ ይልቅ እንደሚከተለው እያልን እንጠይቃለን:- “ይህንን ወሬ የሚያናፍሰው ግለሰብ የሚያደርገው ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል? ግለሰቡ የሚናገረው ነገር ወይም የሰነዘረው ክስ የይሖዋን ዓላማ የሚደግፍ ነው? ለጉባኤው ሰላምስ አስተዋጽኦ ያደርጋል?” የወንድማማች ኅብረታችንን ከማነጽ ወይም ከማጠናከር ይልቅ የሚያፈርስ ማንኛውንም ነገር ብንሰማ ይህ ከንቱ ነገር ነው።—2 ቆሮ. 13:10, 11

19. ሽማግሌዎች ከንቱ ቃላትን ከመናገር መቆጠብ የሚችሉት ምን በማድረግ ነው?

19 ከንቱ ቃላትን በተመለከተ ሽማግሌዎችም አስፈላጊ ትምህርት ይማራሉ። ምክር መስጠት በሚኖርባቸው ጊዜ እውቀታቸው ውስን እንደሆነ ስለሚገነዘቡ ካካበቱት ተሞክሮ በመነሳት ምክር ለመስጠት አይሞክሩም። ምንጊዜም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ከተጻፈው አትለፍ” በማለት የሰጠው ምክር ግሩም መመሪያ ይሆናል። (1 ቆሮ. 4:6) ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፈው አልፈው አይሄዱም። ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በመከተል፣ ታማኝና ልባም ባሪያ በአምላክ ቃል ላይ ተመሥርቶ ባዘጋጃቸው ጽሑፎች ላይ ከሚገኘው ምክርም አያልፉም።

20. ከንቱ ነገሮችን ለመራቅ የሚያስችለን እርዳታ የምናገኘው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

20 ከንቱ ነገሮች በሙሉ ማለትም ‘አማልክትም’ ሆኑ ቃላት ወይም ሌሎች ነገሮች በጣም ጎጂ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ነገሮች ለይተን ለማወቅ እንዲረዳን አዘውትረን ወደ ይሖዋ እንጸልያለን፤ እንዲሁም እነዚህን ነገሮች እንዴት መራቅ እንደምንችል ለማወቅ የእሱን መመሪያ እንሻለን። እንዲህ ስናደርግ ልክ እንደ መዝሙራዊው “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ፤ በራስህ መንገድ እንደ ገና ሕያው አድርገኝ” ብለን የተናገርን ያህል ነው። (መዝ. 119:37) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የይሖዋን መመሪያ መከተል ያለውን ጥቅም እንመለከታለን።

ልታብራራ ትችላለህ?

• በጥቅሉ ሲታይ ከየትኞቹ ‘ከንቱ ነገሮች’ መራቅ ይኖርብናል?

• ገንዘብ እንደ አምላክ እንዳይሆንብን ምን ማድረግ እንችላለን?

• ሥጋዊ ምኞቶች እንደ ጣዖት አምልኮ ሊሆኑ የሚችሉት በምን መንገድ ነው?

• ከከንቱ ቃላት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን ከንቱ ነገሮችን ከማሳደድ ይልቅ ‘መሬታቸውን እንዲያርሱ’ ተበረታተዋል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቁሳዊ ነገሮችን ለማግኘት ያለህ ፍላጎት ለይሖዋ አገልግሎት ትኩረት እንዳትሰጥ እንዲያደርግህ ፈጽሞ አትፍቀድ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች የሚናገሩት ነገር ከፍተኛ ጥቅም ሊኖረው ይችላል