በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ

መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ

መልካም ማድረጋችሁን ቀጥሉ

“መልካም አድርጉ።”—ሉቃስ 6:35

1, 2. ለሰዎች መልካም ማድረግ ብዙውን ጊዜ ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው?

ለሰዎች መልካም ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሰዎች ፍቅር ብናሳያቸውም በምላሹ መልካም አያደርጉልን ይሆናል። ምንም እንኳ ‘የቡሩኩን አምላክ’ እና የልጁን “የክብር ወንጌል” ለሌሎች በማካፈል እነሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት የተቻለንን ያህል ጥረት ብናደርግም ግድ የለሾች ወይም የማያመሰግኑ ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ጢሞ. 1:11) አንዳንዶች ደግሞ ክርስቶስ፣ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል መሞቱን ይክዳሉ። (ፊልጵ. 3:18) ታዲያ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከእነዚህ ሰዎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን ይገባል?

2 ኢየሱስ ክርስቶስ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካም አድርጉ” በማለት ደቀ መዛሙርቱን መክሯቸው ነበር። (ሉቃስ 6:35) እስቲ ይህንን ምክር በጥልቀት እንመርምር። ኢየሱስ ለሰዎች መልካም ማድረግን አስመልክቶ የተናገራቸውን ሌሎች ነጥቦችም በመመልከት ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

“ጠላቶቻችሁን ውደዱ”

3. (ሀ) ኢየሱስ በማቴዎስ 5:43-45 ላይ የተናገረውን ሐሳብ በራስህ አባባል ግለጽ። (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ ስለ አይሁዳውያንና አይሁዳዊ ስላልሆኑ ሰዎች ምን አመለካከት ነበራቸው?

3 ኢየሱስ ታዋቂ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ አድማጮቹ፣ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱና ለሚያሳድዷቸውም እንዲጸልዩ ነግሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 5:43-45ን አንብብ።) በቦታው የተገኙት ሰዎች አይሁዳውያን ስለነበሩ አምላክ የሰጠውን የሚከተለውን ትእዛዝ ያውቁ ነበር:- “ወገንህን አትበቀል፤ ወይም ምቀኛ አትሁንበት [“ቂም አትያዝ፣” የ1954 ትርጉም]፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” (ዘሌ. 19:18) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች፣ “ወገንህ” እና “ባልንጀራህ” የሚሉት ቃላት አይሁዳውያንን ብቻ እንደሚያመለክቱ ይሰማቸው ነበር። የሙሴ ሕግ፣ እስራኤላውያን ከሌሎች ብሔራት እንዲለዩ ያዝዝ ነበር፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ፣ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ሁሉ ጠላቶቻቸው እንደሆኑና ሊጠሉ እንደሚገባ ይሰማው ነበር።

4. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከጠላቶቻቸው ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል?

4 ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 5:44) ደቀ መዛሙርቱ፣ ጥላቻ የሚያሳዩአቸውን ሰዎች ሁሉ በፍቅር እንዲይዙ ይጠበቅባቸው ነበር። የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ፣ ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት እንደተናገረ ገልጿል:- “ለእናንተ ለምትሰሙ እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ፤ የሚረግሟችሁን መርቁ፤ ለሚበድሏችሁም ጸልዩ።” (ሉቃስ 6:27, 28) የኢየሱስን ምክር በቁም ነገር እንደተመለከቱት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ እንደነበሩት ሰዎች ሁሉ እኛም የሚጠሉንን ሰዎች በአክብሮት በመያዝ “ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ” የሚለውን ምክር በተግባር ማዋል እንችላለን። እንዲሁም ‘የሚረግሙንን’ ሰዎች ደግነት በተሞላበት መንገድ በማነጋገር ‘እንመርቃቸዋለን።’ በተጨማሪም ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ‘በመበደልም’ ሆነ አካላዊ ጥቃት በማድረስ ‘ቢያሳድዱንም እንጸልይላቸዋለን።’ እንዲህ ዓይነት ጸሎት ማቅረባችን ለጠላቶቻችን ፍቅር እንዳለን ያሳያል፤ ምክንያቱም ይህን ስናደርግ የሚያሳድዱን ሰዎች ልባቸው እንዲለወጥና የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚያስችላቸውን እርምጃ እንዲወስዱ አምላክን መጠየቃችን ነው።

5, 6. ጠላቶቻችንን መውደድ ያለብን ለምንድን ነው?

5 ለጠላቶቻችን ፍቅር ማሳየት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ኢየሱስ “እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ” ብሏል። (ማቴ. 5:45) ይህንን ምክር ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋን በመምሰል የአምላክ “ልጆች” እንሆናለን፤ እሱ “ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።” የሉቃስ ዘገባ እንደሚለው አምላክ “ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነው።”—ሉቃስ 6:35

6 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ‘ጠላቶቻቸውን መውደዳቸው’ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የሚወዷችሁን ብቻ የምትወዱ ከሆነ ምን ዋጋ ታገኛላችሁ? ቀራጮችስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ እጅ የምትነሡ ከሆነ ከሌሎች በምን ትሻላላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን?” (ማቴ. 5:46, 47) የሚወዱንን ብቻ የምንወድ ከሆነ እንዲህ ማድረጋችን በአምላክ ዘንድ “ዋጋ” አያሰጠንም ወይም የእሱን ሞገስ አያስገኝልንም። በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የተናቁ የሆኑት ቀረጥ ሰብሳቢዎችም እንኳ የሚወዷቸውን ሰዎች ይወዱ ነበር።—ሉቃስ 5:30፤ 7:34

7. ‘ወንድሞቻችንን’ ብቻ ሰላም የምንል ከሆነ ከሌሎች አንሻልም የምንለው ለምንድን ነው?

7 የተለመደው የአይሁዳውያን ሰላምታ አሰጣጥ “ሰላም” የሚለውን ቃል ይጨምር ነበር። (መሳ. 19:20 የ1954 ትርጉም፤ ዮሐ. 20:19) ይህም ሰላምታ ለሚሰጡት ሰው ጤንነትንና ብልጽግናን እንደሚመኙለት የሚያሳይ ነበር። ‘ወንድሞቻችን’ እንደሆኑ አድርገን የምንመለከታቸውን ሰዎች ብቻ ሰላም የምንል ከሆነ ‘ከሌሎች በምን እንሻላለን’? ኢየሱስ እንደገለጸው ‘አሕዛብም’ እንዲሁ ያደርጋሉ።

8. ኢየሱስ “ፍጹማን ሁኑ” ሲል አድማጮቹ ምን እንዲያደርጉ ማበረታታቱ ነበር?

8 የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከአዳም ኃጢአት ስለወረሱ እንከን የለሽ ወይም ፍጹም መሆን አይችሉም። (ሮሜ 5:12) ያም ሆኖ ኢየሱስ ሐሳቡን ሲደመድም “የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 5:48) ኢየሱስ እንዲህ ሲል አድማጮቹ ፍጹም ፍቅር እንዲያሳዩ ማለትም ጠላቶቻቸውንም ጭምር በመውደድ ‘የሰማዩን አባታቸውን’ ይሖዋን እንዲመስሉ ማበረታታቱ ነበር። እኛም ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ይጠበቅብናል።

ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

9. ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ላይ እንደተገለጸው መልካም ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

9 የበደለንን ሰው ይቅር በማለትም መልካም ማድረግ እንችላለን። ኢየሱስ ባስተማረው የናሙና ጸሎት ውስጥ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን” የሚል ሐሳብ ይገኛል።—ማቴ. 6:12

10. ይቅር ባይ በመሆን ረገድ አምላክን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

10 እኛም፣ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን በነፃ ይቅር የሚለውን አምላክ መምሰል አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ” በማለት ጽፏል። (ኤፌ. 4:32) መዝሙራዊው ዳዊት እንደሚከተለው ሲል ዘምሯል:- “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው። . . . እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። . . . ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል።”—መዝ. 103:8-14

11. አምላክ ይቅር የሚለው እነማንን ነው?

11 ሰዎች የአምላክን ይቅርታ ማግኘት የሚችሉት የበደሏቸውን ሰዎች ይቅር ካሉ ብቻ ነው። (ማር. 11:25) ኢየሱስ ይህንን ነጥብ ሲያጎላ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።” (ማቴ. 6:14, 15) አዎን፣ አምላክ ይቅር የሚለው ሌሎችን በነፃ ይቅር የሚሉ ሰዎችን ብቻ ነው። “ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ” የሚለውን የጳውሎስ ምክር በመከተል መልካም ማድረግ እንችላለን።—ቈላ. 3:13

“አትፍረዱ”

12. ኢየሱስ በሌሎች ላይ መፍረድን በተመለከተ ምን ምክር ሰጥቷል?

12 ኢየሱስ፣ አድማጮቹ በሌሎች ላይ መፍረዳቸውን እንዲተዉ በመናገር መልካም ማድረግ የሚቻልበትን ሌላ መንገድ የጠቆመ ሲሆን ይህን ነጥብ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ምሳሌም ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 7:1-5ን አንብብ።) ኢየሱስ “አትፍረዱ” ሲል ምን ማለቱ እንደነበር እስቲ እንመልከት።

13. ኢየሱስን ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸው ነበር?

13 ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ [“መፍረድ ተዉ፣” NW]” በማለት እንደተናገረ የማቴዎስ ወንጌል ይገልጻል። (ማቴ. 7:1) ሉቃስ እንደጻፈው ደግሞ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “አትፍረዱ [“መፍረዳችሁን ተዉ፣” NW]፤ አይፈረድባችሁም፤ አትኰንኑ፤ አትኰነኑም። ይቅር በሉ፤ ይቅር ትባላላችሁ።” (ሉቃስ 6:37) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ፈሪሳውያን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወጎችን መሠረት በማድረግ በሌሎች ላይ ደግነት በጎደለው መንገድ ይፈርዱ ነበር። ኢየሱስን ያዳምጡ ከነበሩት ሰዎች መካከል እንዲህ የሚያደርጉ ካሉ ‘መፍረዳቸውን በመተው’ የሌሎችን ድክመት ‘ይቅር ማለት’ ነበረባቸው። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ሐዋርያው ጳውሎስም ይቅር ማለትን በተመለከተ ተመሳሳይ ምክር ሰጥቷል።

14. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይቅር ባዮች በመሆን ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሷቸው ይችላሉ?

14 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይቅር ባዮች መሆናቸው ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል። ኢየሱስ “በምትፈርዱበትም ዐይነት ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል” ብሏል። (ማቴ. 7:2) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የምንዘራውን እናጭዳለን።—ገላ. 6:7

15. ኢየሱስ፣ ሌሎችን መንቀፍ ስህተት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ፣ ሰዎችን መንቀፍ ምን ያህል ስህተት እንደሆነ ሲጠቁም እንደሚከተለው በማለት ጠይቋል:- “በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጒድፍ ለምን ታያለህ? በዐይንህ ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን፣ ‘ዐይንህ ውስጥ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ’ ማለት እንዴት ትችላለህ?” (ማቴ. 7:3, 4) ሌላውን የመንቀፍ ልማድ ያለው ግለሰብ በወንድሙ “ዐይን” ውስጥ ያለውን ትንሽ ጉድለት ይመለከታል። እንዲህ ሲያደርግ፣ ወንድሙ ነገሮችን እንደማያስተውልና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንደሌለው መግለጹ ነው። የወንድሙ ስህተት እንደ ትንሽ ጉድፍ ቢሆንም እንኳ ነቃፊ የሆነው ግለሰብ ‘ጉድፉን ለማውጣት’ ይሞክራል። ግብዝ የሆነው ይህ ሰው፣ ወንድሙ ነገሮችን ይበልጥ አጥርቶ ማየት እንዲችል ሊረዳው ይሞክራል።

16. ፈሪሳውያን በዓይናቸው ውስጥ “ግንድ” ነበረ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

16 በተለይ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሌሎችን በጣም ይነቅፉ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ክርስቶስ ማየት የተሳነውን አንድ ሰው ፈውሶ ነበር፤ ይህ ሰው ኢየሱስ የመጣው ከአምላክ እንደሆነ ሲናገር ፈሪሳውያን “ሁለንተናህ በኀጢአት ተነክሮ የተወለድህ፣ አንተ እኛን ለማስተማር እንዴት ትደፍራለህ?” በማለት በቁጣ መለሱለት። (ዮሐ. 9:30-34) ፈሪሳውያን ጥርት ያለ መንፈሳዊ እይታም ሆነ ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር በመመልከት የመፍረድ ችሎታ አልነበራቸውም፤ በዓይናቸው ውስጥ “ግንድ” ስለነበር ሙሉ በሙሉ ታውረዋል። በዚህም የተነሳ ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ።” (ማቴ. 7:5፤ ሉቃስ 6:42) ለሰዎች መልካም ማድረግና ሌሎችን በአግባቡ መያዝ የምንፈልግ ከሆነ በምሳሌያዊ ሁኔታ በወንድማችን ዓይን ውስጥ ሁልጊዜ ጉድፍ ለማግኘት በመሞከር ሰዎችን የመንቀፍ ልማድ አይኖረንም። ከዚህ ይልቅ እኛም ፍጽምና የጎደለን ሰዎች እንደሆንን በመገንዘብ በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ ከመፍረድና እነሱን ከመንቀፍ እንቆጠባለን።

ከሌሎች ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን ይገባል?

17. በማቴዎስ 7:12 መሠረት ሌሎችን እንዴት መያዝ ይኖርብናል?

17 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ አምላክ፣ አገልጋዮቹ ለሚያቀርቡት ጸሎት መልስ ስለሚሰጣቸው እንደ አባት እንደሆነላቸው ገልጿል። (ማቴዎስ 7:7-12ን አንብብ።) በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ የሰጠው የሚከተለው መመሪያ ትኩረት የሚስብ ነው:- “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው፤ ኦሪትም፣ ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉና።” (ማቴ. 7:12) የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው ሰዎችን በዚህ መንገድ የምንይዝ ከሆነ ብቻ ነው።

18. ‘በኦሪት’ ውስጥ የሚገኙት ሕጎች፣ ሰዎች እንዲያደርጉልን የምንፈልገውን ነገር ልናደርግላቸው እንደሚገባ የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

18 ኢየሱስ፣ ሰዎች ሊያደርጉልን የምንፈልገውን እኛም ልናደርግላቸው እንደሚገባ ከተናገረ በኋላ “ኦሪትም፣ ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉ” ብሏል። ሰዎችን ኢየሱስ በገለጸው መንገድ የምንይዝ ከሆነ ‘ከኦሪት’ ወይም ከሕጉ ዓላማ ጋር የሚስማማ ነገር እያደረግን ነው፤ እዚህ ላይ “ኦሪት” የተባሉት ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት፣ ይሖዋ ክፋትን የሚያስወግድ ዘር የማስነሳት ዓላማ እንዳለው ከመግለጻቸውም ባሻገር አምላክ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤል ብሔር የሰጠውን ሕግ ይዘዋል። (ዘፍ. 3:15) በሕጉ ውስጥ ከሚገኙት ትእዛዛት መካከል እስራኤላውያን በትክክል እንዲፈርዱ፣ አድሎ እንዳያደርጉ እንዲሁም ለድሆችና በአገራቸው ለሚኖሩ መጻተኞች መልካም እንዲያደርጉ የሚያዙትን ግልጽ መመሪያዎች መጥቀስ ይቻላል።—ዘሌ. 19:9, 10, 15, 34

19. “ነቢያት” ለሌሎች መልካም ማድረግ እንዳለብን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

19 ኢየሱስ “ነቢያት” ብሎ ሲናገር በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን የትንቢት መጻሕፍት መጥቀሱ ነበር። እነዚህ መጻሕፍት መሲሑን የሚመለከቱ ትንቢቶችን የያዙ ሲሆን ትንቢቶቹም በክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በተጨማሪም እነዚህ መጻሕፍት፣ የአምላክ ሕዝቦች በእሱ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ሲያደርጉና ሌሎችን በተገቢው መንገድ ሲይዙ እሱም እንደሚባርካቸው ያሳያሉ። ለአብነት ያህል፣ የኢሳይያስ ትንቢት ለእስራኤላውያን የሚከተለውን ምክር ይዞ ነበር:- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ፍትሕን ጠብቁ፤ መልካሙን አድርጉ። . . . ክፉን ከማድረግ እጁን የሚሰበስብ፣ የሚገታ፣ እነዚህን የሚፈጽም ሰው የተባረከ ነው።’” (ኢሳ. 56:1, 2) አምላክ፣ ሕዝቦቹ መልካም ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ይጠብቅባቸዋል።

ምንጊዜም ለሌሎች መልካም አድርጉ

20, 21. ኢየሱስ በተራራ ላይ የሰጠውን ትምህርት ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች ምን ተሰምቷቸው ነበር? አንተስ በዚህ ትምህርት ላይ ማሰላሰል ያለብህ ለምንድን ነው?

20 ኢየሱስ ተወዳዳሪ በሌለው የተራራ ስብከቱ ላይ ከጠቀሳቸው በርካታ ጠቃሚ ነጥቦች ውስጥ እስካሁን የተመለከትነው ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ያም ቢሆን ግን በዚያ ወቅት ንግግሩን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች ያደረባቸውን ስሜት በቀላሉ መረዳት እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ኢየሱስ ማስተማሩን በፈጸመ ጊዜ፣ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ። ምክንያቱም እንደ አይሁድ ሃይማኖት መምህራናቸው ሳይሆን እንደ ባለ ሥልጣን አስተምሮአቸው ስለ ነበር ነው።”—ማቴ. 7:28, 29

21 ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረለት “ድንቅ መካር” እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። (ኢሳ. 9:6) የተራራው ስብከት፣ ኢየሱስ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን አመለካከት ምን ያህል እንደሚያውቅ የሚጠቁም ግሩም ምሳሌ ነው። እስካሁን ከተመለከትናቸው ነጥቦች በተጨማሪ የተራራው ስብከት፣ እውነተኛ ደስታ ማግኘትና ከሥነ ምግባር ብልግና መራቅ ስለሚቻልበት መንገድ ያብራራል፤ ከዚህም በላይ ጽድቅን ማድረግ እንዴት እንደሚቻል፣ አስተማማኝና አስደሳች የወደፊት ሕይወት እንዲኖረን ምን ማድረግ እንዳለብን እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ሐሳብ ይዟል። በማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሐሳብ ትኩረት ሰጥተህ በድጋሚ በማንበብ በጸሎት እንድታስብበት እናበረታታሃለን። በእነዚህ ምዕራፎች ላይ በሚገኘው ግሩም የሆነ የኢየሱስ ምክር ላይ አሰላስል። ክርስቶስ በተራራ ስብከቱ ላይ የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ አውል። እንዲህ ካደረግህ ይሖዋን ይበልጥ ማስደሰት፣ ሌሎችን በአግባቡ መያዝ እንዲሁም መልካም ማድረግህን መቀጠል ትችላለህ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ጠላቶቻችንን እንዴት ልንይዛቸው ይገባል?

• ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ በሰዎች ላይ ስለ መፍረድ ምን ተናግሯል?

በማቴዎስ 7:12 መሠረት ሰዎችን እንዴት መያዝ ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ “መፍረድ ተዉ” ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሚያሳድዱን ሰዎች የምንጸልየው ለምንድን ነው?

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምንጊዜም ቢሆን ሰዎች እንዲያደርጉልህ የምትፈልገውን ታደርግላቸዋለህ?