በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የምናገኘው መዳን ቀርቧል!

በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የምናገኘው መዳን ቀርቧል!

በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የምናገኘው መዳን ቀርቧል!

“መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን።”—ማቴ. 6:10

1. የኢየሱስ ትምህርት በዋነኝነት ያተኮረው ምን ላይ ነበር?

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በተራራ ስብከቱ ወቅት ለናሙና የሚሆን ጸሎት ያስተማረ ሲሆን በዚህ ጸሎት ውስጥ ዋና ዋና ትምህርቶቹ ተካትተዋል። ተከታዮቹ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:9-13) ኢየሱስ “የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ” ያልፍ ነበር። (ሉቃስ 8:1) እንዲሁም ተከታዮቹን “ከሁሉ አስቀድማችሁ . . . የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 6:33) በዚህ ርዕስ ውስጥ የምታገኛቸውን ትምህርቶች በአገልግሎትህ እንዴት ልትጠቀምባቸው እንደምትችል ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ምን ብለህ እንደምትመልስ አስብ:- ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው መልእክት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? የሰው ዘር መዳን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ለሰዎች መዳን የሚያስገኘው እንዴት ነው?

2. ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው መልእክት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

2 ኢየሱስ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 24:14) ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው። በእርግጥም በዓለም ላይ ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ የሆነ መልእክት ነው! በዓለም ዙሪያ ከ100,000 በላይ በሚሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት መቋቋሙን ለሰዎች በመናገር ተወዳዳሪ በሌለው የስብከት ሥራ እየተካፈሉ ነው። የዚህ መንግሥት መቋቋም፣ አምላክ ምድርን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር አስተዳደር በሰማይ መመሥረቱን የሚጠቁም በመሆኑ የምሥራች ነው። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድርም ይሆናል።

3, 4. የአምላክ ፈቃድ በምድር መፈጸሙ ምን ለውጦች ያመጣል?

3 የይሖዋ ፈቃድ በምድር ላይ መፈጸሙ ለሰው ልጆች ምን ጥቅም ያስገኛል? ይሖዋ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) ሰዎች ፍጹማን ባለመሆናቸውና በወረሱት ኃጢአት ምክንያት መታመማቸው እንዲሁም መሞታቸው ይቀራል። “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ” የሚገልጸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ በአምላክ መታሰቢያ ላይ የሰፈሩት ሙታን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሚያገኙ ያረጋግጥልናል። (ሥራ 24:15) ጦርነት፣ በሽታ ወይም ረሃብ የሚወገድ ሲሆን ምድርም ወደ ገነትነት ትለወጣለች። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ አደገኛ የሆኑት እንስሳትም እንኳ ከሰዎች ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው በሰላም ይኖራሉ።—መዝ. 46:9፤ 72:16፤ ኢሳ. 11:6-9፤ 33:24፤ ሉቃስ 23:43

4 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሰው ዘር እንዲህ ያሉ አስደናቂ በረከቶችን የሚያገኝ በመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ በዚያን ጊዜ የሚኖረውን ሕይወት አስመልክቶ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” የሚል አስደሳች ሐሳብ ማስፈሩ ምንም አያስገርምም። ክፉ ስለሆኑ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? መጽሐፍ ቅዱስ “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም” ይላል። “እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ።”—መዝ. 37:9-11

5. አሁን ያለንበት ሥርዓት ምን ይሆናል?

5 ይህ ሁሉ እንዲፈጸም ከተፈለገ ግን እርስ በርስ የሚጋጩትን መንግሥታት፣ ሃይማኖትንና የንግዱን ዓለም ጨምሮ ይህ ሥርዓት መወገድ ይኖርበታል። በሰማይ የተቋቋመው መንግሥትም የሚያደርገው ይህንኑ ነው። ነቢዩ ዳንኤል በመንፈስ ተነሳስቶ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል:- “በነዚያ ነገሥታት [በአሁኑ ጊዜ ባሉት መንግሥታት] ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት [በሰማይ] ይመሠርታል፤ እነዚያን [በአሁኑ ጊዜ ያሉትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” (ዳን. 2:44) ከዚያም የአምላክ መንግሥት ማለትም በሰማይ የተቋቋመው አዲስ መስተዳድር በምድር የሚገኘውን አዲስ ኅብረተሰብ ይገዛል። በዚያን ወቅት ‘ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ ይኖራል።—2 ጴጥ. 3:13

በአሁኑ ወቅት መዳን በጣም ያስፈልጋል

6. መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ የሚፈጸመውን ዓመጽ በተመለከተ ምን ይላል?

6 ሰይጣን እንዲሁም አዳምና ሔዋን ትክክል ወይም ስህተት ስለሆነው ነገር የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ በመምረጥ በአምላክ ላይ ባመጹ ጊዜ የሰው ዘር አደገኛ አካሄድ መከተል ጀመረ። ይህ ከሆነ ከ1,600 ዓመታት በኋላ ማለትም ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት “የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ” እንደነበረ ተገልጿል። (ዘፍ. 6:5) የጥፋት ውኃ ከመጣ ከ1,300 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሁኔታዎቹ በጣም እየተባባሱ በመሄዳቸው ሰሎሞን እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኔም የቀድሞ ሙታን፣ ዛሬ በሕይወት ካሉት ሕያዋን ይልቅ፣ ደስተኞች እንደ ሆኑ ተናገርሁ። ነገር ግን ከሁለቱም ይልቅ፣ ገና ያልተወለደው፣ ከፀሓይ በታች የሚደረገውንም፣ ክፋት ያላየው ይሻላል።” (መክ. 4:2, 3) ዛሬ የምንኖረው ሰሎሞን ይህንን ከተናገረ ከ3,000 ዓመታት በኋላ ቢሆንም በዓለም ላይ የሚፈጸመው ክፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ ነው።

7. በዛሬው ጊዜ አምላክ የሚያመጣው መዳን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

7 ቀደም ካሉት ዘመናት ጀምሮ ክፋት እንደነበረ ባይካድም በተለይ ዛሬ በአምላክ መንግሥት አማካኝነት መዳን ማግኘታችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ባለፉት 100 ዓመታት ሁኔታዎች ከምንጊዜውም ይልቅ መጥፎ የነበሩ ሲሆን በዛሬው ጊዜ ደግሞ እየተባባሱ ነው። ለአብነት ያህል፣ ወርልድዎች የተባለው ተቋም ያወጣው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “[በ20ኛው] መቶ ዘመን በጦርነት ሕይወታቸውን ያጡት ሰዎች፣ ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አንስቶ እስከ 1899 ድረስ በተካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ ከሞቱት ሰዎች በሦስት እጥፍ ይበልጣሉ።” ከ1914 ወዲህ ከ100 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በጦርነት ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል! አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ የሰፈረው ግምታዊ ሐሳብ እንደሚጠቁመው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሞተዋል። ዛሬ ደግሞ አንዳንድ መንግሥታት የኑክሌር መሣሪያ ስላላቸው የሰው ዘር፣ አብዛኛውን የዓለም ኅብረተሰብ ከምድር ገጽ የማጥፋት አቅም አለው። በሳይንሱና በሕክምናው መስክ እድገት ቢኖርም በረሃብ ምክንያት በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን ሕፃናት ሕይወታቸውን ያጣሉ።—ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።

8. የሰው ዘር በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ራሱን ለማስተዳደር ያደረገው ጥረት የትኛውን ሐቅ አረጋግጧል?

8 የሰው ልጆች የሚያደርጓቸው ጥረቶች ክፋትን ማስወገድ አልቻሉም። የዚህ ዓለም የፖለቲካ፣ የንግድና የሃይማኖት ተቋማት የሰው ዘር ሰላም፣ ብልጽግና እንዲሁም ጤና ለማግኘት ያለውን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት ተስኗቸዋል። እነዚህ ተቋማት የሰው ልጆች ለተደቀኑባቸው ከባድ ችግሮች መፍትሔ ከማግኘት ይልቅ ተጨማሪ ችግሮች እየፈጠሩ ነው። የሰው ዘር በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ራሱን ለማስተዳደር ያደረገው ጥረት “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል” የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነት መሆኑን አረጋግጧል። (ኤር. 10:23) አዎን፣ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።” (መክ. 8:9) ከዚህም በላይ “ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት” ላይ ይገኛል።—ሮሜ 8:22

9. እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ “በመጨረሻው ዘመን” ምን ዓይነት ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ይጠብቃሉ?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ ይመጣል’ በማለት ስለምንኖርበት ጊዜ ትንቢት ተናግሯል። ትንቢቱ፣ በሰው ዘር አገዛዝ ሥር በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩትን ሁኔታዎች ከዘረዘረ በኋላ “ክፉዎችና አታላዮች ግን . . . በክፋትም ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13ን አንብብ።) ክርስቲያኖች ‘መላው ዓለም በክፉው’ ማለትም በሰይጣን ሥር እንደሆነ ስለሚያውቁ ከላይ እንደተገለጸው ዓይነት ሁኔታ እንደሚኖር ይጠብቃሉ። (1 ዮሐ. 5:19) ሆኖም አምላክ እሱን የሚወዱትን ሰዎች በቅርቡ የሚያድናቸው መሆኑ የሚያስደስት ነገር ነው። አምላክ እነዚህን ሰዎች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ክፋቱ እየተባባሰ ካለው ከዚህ ዓለም ያድናቸዋል።

መዳን የሚያስገኘው ብቸኛው አስተማማኝ አካል

10. ብቸኛው አስተማማኝ የመዳን ምንጭ ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

10 ምሥራቹን ስትሰብክ፣ መዳን የሚያስገኘው ብቸኛው አስተማማኝ አካል ይሖዋ እንደሆነ ግለጽ። አገልጋዮቹን ከማንኛውም መጥፎ ሁኔታ ለማዳን ኃይሉም ሆነ ፍላጎቱ ያለው እሱ ብቻ ነው። (ሥራ 4:24, 31፤ ራእይ 4:11) ይሖዋ “እንደ ዐቀድሁት በእርግጥ ይከናወናል” ብሎ ቃል ስለገባ ምንጊዜም ቢሆን ሕዝቦቹን እንደሚያድንና ዓላማውን ዳር እንደሚያደርስ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አምላክ የተናገረው ቃል “በከንቱ ወደ [እሱ] አይመለስም።”—ኢሳይያስ 14:24, 25⁠ን እና 55:10, 11ን አንብብ።

11, 12. አምላክ ለአገልጋዮቹ ምን ዋስትና ሰጥቷቸዋል?

11 ይሖዋ በክፉዎች ላይ የቅጣት ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ አገልጋዮቹን እንደሚያድን ዋስትና ሰጥቷል። አምላክ፣ ለኃጢአተኞች በድፍረት እንዲናገር ነቢዩ ኤርምያስን በላከው ወቅት “አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራቸው” ብሎት ነበር። (ኤር. 1:8) በተመሳሳይም ይሖዋ ክፉዎቹን የሰዶምና የገሞራ ነዋሪዎች ሊያጠፋቸው ሲል ሎጥንና ቤተሰቡን ከአካባቢው እንዲያወጧቸው ሁለት መላእክትን ልኮ ነበር። “ከዚያም እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ላይ . . . የሚያቃጥል ዲንና እሳት አዘነበባቸው።”—ዘፍ. 19:15, 24, 25

12 ይሖዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥፋት በሚያመጣበት ጊዜም የእሱን ፈቃድ የሚያደርጉ ሰዎችን ማዳን ይችላል። የጥንቱን ክፉ ዓለም በውኃ ባጠፋበት ወቅት ‘የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖታል።’ (2 ጴጥ. 2:5) ይሖዋ ይህን ክፉ ዓለም በሚያጠፋበት ወቅትም ቅን የሆኑ ሰዎችን ያድናቸዋል። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል:- “እናንት የምድር ትሑታን ሁሉ፣ . . . እግዚአብሔርን እሹ፤ ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ፤ በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን፣ ትሰወሩ ይሆናል።” (ሶፎ. 2:3) ከዚህ ዓለም አቀፍ ጥፋት በኋላ ‘ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።’—ምሳሌ 2:21, 22

13. የሞቱ የይሖዋ አገልጋዮች መዳን የሚያገኙት እንዴት ነው?

13 በርካታ የአምላክ አገልጋዮች በሕመም፣ በስደትና በሌሎች ምክንያቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። (ማቴ. 24:9) ታዲያ እነዚህ ሁሉ ሰዎች መዳን የሚያገኙት እንዴት ነው? ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ‘ጻድቃን ከሙታን ይነሣሉ።’ (ሥራ 24:15) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹን ከማዳን የሚያግደው ምንም ነገር እንደሌለ ማወቁ እንዴት የሚያጽናና ነው!

ጻድቅ መንግሥት

14. የአምላክ መንግሥት ጻድቅ መስተዳደር እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ በሰማይ ያቋቋመው መንግሥት ጻድቅ መስተዳደር እንደሆነ በአገልግሎትህ ላይ መግለጽ ትችላለህ። እንዲህ የምንለው ይህ መንግሥት እንደ ፍትሕ፣ ጽድቅና ፍቅር ያሉትን የአምላክ ድንቅ ባሕርያት ስለሚያንጸባርቅ ነው። (ዘዳ. 32:4፤ 1 ዮሐ. 4:8) አምላክ፣ ምድርን ለማስተዳደር ከማንም በላይ ብቁ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ይህን መንግሥት ሰጥቶታል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ከምድር የተዋጁ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ወራሾች በመሆን ምድርን እንዲያስተዳድሩ ዝግጅት አድርጓል።—ራእይ 14:1-5

15. የአምላክን መንግሥት አገዛዝ ከሰብዓዊ አገዛዝ ጋር አነጻጽር።

15 የኢየሱስና የ144,000ዎቹ አገዛዝ፣ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ከሚገዙበት መንገድ ምንኛ የተለየ ነው! የዚህ ሥርዓት ገዢዎች ብዙውን ጊዜ ጨካኞች ናቸው፤ ተገዢዎቻቸውን ወደ ጦርነት በመላክ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ” የሚል ምክር መስጠቱ ምንም አያስገርምም። (መዝ. 146:3) የክርስቶስ አገዛዝ ግን ፍቅር የሚንጸባረቅበት ይሆናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።”—ማቴ. 11:28-30

የመጨረሻው ዘመን በቅርቡ ያበቃል!

16. የመጨረሻው ዘመን የሚደመደመው እንዴት ነው?

16 ከ1914 ጀምሮ ይህ ዓለም የሚገኘው በመጨረሻው ዘመን ወይም “የዓለም መጨረሻ” ተብሎ በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ነው። (ማቴ. 24:3) ኢየሱስ እንደተናገረው በቅርቡ “ታላቅ መከራ” ይመጣል። (ማቴዎስ 24:21ን አንብብ።) ከዚህ በፊት ከደረሱት ሁሉ አስከፊ በሆነው በዚህ መከራ መላው የሰይጣን ዓለም ይጠፋል። ይሁን እንጂ ታላቁ መከራ የሚጀምረው እንዴት ነው? የሚደመደመውስ እንዴት ነው?

17. ታላቁ መከራ በሚጀምርበት ጊዜ ስለሚኖረው ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

17 ታላቁ መከራ የሚጀምረው በድንገት ነው። “ሰዎች፣ ‘ሰላምና ደኅንነት ነው’ ሲሉ” በድንገት ‘የይሖዋ ቀን’ ይመጣባቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:2, 3ን አንብብ።) በትንቢት የተነገረው መከራ የሚጀምረው ብሔራት ከታላላቅ ችግሮቻቸው አንዳንዶቹን ለመፍታት እንደተቃረቡ በሚያስቡበት ወቅት ነው። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት በሆነችው ‘በታላቂቱ ባቢሎን’ ላይ የሚደርሰው ድንገተኛ ጥፋት ዓለም ፈጽሞ ያልጠበቀው ነገር ይሆናል። በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የፍርድ እርምጃ ሲወሰድ ሰብዓዊ ነገሥታትና ሌሎች ሰዎች በጣም ይደነግጣሉ።—ራእይ 17:1-6, 18፤ 18:9, 10, 15, 16, 19

18. ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ይሖዋ ምን እርምጃ ይወስዳል?

18 በዚህ ወቅት “በጨረቃና በከዋክብት ላይ ምልክት ይሆናል” እንዲሁም “የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ላይ ይታያል።” በዚህ ጊዜ ‘መዳናችን ስለተቃረበ ራሳችንን ወደ ላይ ቀና ማድረግ’ እንችላለን። (ሉቃስ 21:25-28፤ ማቴ. 24:29, 30) ሰይጣን ወይም ጎግ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ሠራዊቱን ያሰማራል። ሆኖም ይሖዋ፣ በታማኝ አገልጋዮቹ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎች “የዐይኑን ብሌን” የነኩ ያህል እንደሚሰማው ተናግሯል። (ዘካ. 2:8) በመሆኑም ሰይጣን የይሖዋን አገልጋዮች ለማጥፋት የሚያደርገው ጥረት አይሳካም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሉዓላዊ ጌታ የሆነው ይሖዋ አገልጋዮቹን ለማዳን አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል።—ሕዝ. 38:9, 18

19. የአምላክን ፍርድ የሚያስፈጽሙት ኃይሎች የሰይጣንን ሥርዓት እንደሚያጠፉት እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

19 አምላክ በብሔራት ላይ እርምጃ ሲወስድ ብሔራት ‘እሱ ይሖዋ እንደ ሆነ ያውቃሉ።’ (ሕዝ. 36:23 NW) ይሖዋ በምድር ላይ የቀረውን የሰይጣን ሥርዓት ለማጥፋት በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመሩ እልፍ አእላፋት መንፈሳዊ ፍጥረታትን ይልካል። (ራእይ 19:11-19) አንድ መልአክ “መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ” የአምላክ ጠላቶችን በአንድ ሌሊት ብቻ እንዳጠፋ ስናስታውስ ታላቁ መከራ በአርማጌዶን በሚደመደምበት ወቅት በሰማይ የሚገኘው ሠራዊት በምድር ላይ የቀረውን የሰይጣን ሥርዓት ድምጥማጡን ማጥፋት ቀላል እንደሚሆንለት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (2 ነገ. 19:35፤ ራእይ 16:14, 16) ሰይጣንና አጋንንቱ ለአንድ ሺህ ዓመት ወደ ጥልቁ ይጣላሉ። ከጊዜ በኋላም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:1-3

20. ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ምን ነገሮችን ያከናውናል?

20 በዚህ መንገድ ምድር ከክፋት የምትጸዳ ሲሆን ጻድቅ የሆኑ ሰዎችም ለዘላለም ይኖሩባታል። ይሖዋ ታላቅ አዳኝ መሆኑን ያስመሠክራል። (መዝ. 145:20) ይሖዋ በመንግሥቱ አማካኝነት ሉዓላዊነቱን ያረጋግጣል፣ ስሙን ያስቀድሳል እንዲሁም ለምድር ያለውን ታላቅ ዓላማ ይፈጽማል። በአገልግሎትህ ላይ ይህንን የምሥራች ለሰዎች በማወጅ እንዲሁም “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ” ሰዎች በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የሚገኘው መዳን እንደቀረበ እንዲገነዘቡ በመርዳት ታላቅ ደስታ እንደምታገኝ ተስፋ እናደርጋለን!—ሥራ 13:48

ታስታውሳለህ?

• ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነበር?

• ከምንጊዜውም የበለጠ ዛሬ መዳን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

• በታላቁ መከራ ወቅት የትኞቹ ክንውኖች እንደሚፈጸሙ መጠበቅ እንችላለን?

• ይሖዋ ታላቅ አዳኝ መሆኑን ያስመሠከረው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የአምላክ ቃል፣ በዘመናችን ተወዳዳሪ የማይገኝለት የስብከት ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚካሄድ አስቀድሞ ተናግሯል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ኖኅና ቤተሰቡን እንዳዳናቸው ሁሉ እኛንም ሊያድነን ይችላል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት . . . አይኖርም።”—ራእይ 21:4