በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በወጣትነታችሁ ይሖዋን ለማገልገል ምረጡ

በወጣትነታችሁ ይሖዋን ለማገልገል ምረጡ

በወጣትነታችሁ ይሖዋን ለማገልገል ምረጡ

“አንተ ግን በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና።”—2 ጢሞ. 3:14

1. ይሖዋ፣ ወጣት ምሥክሮቹ የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንዴት ይመለከተዋል?

ይሖዋ፣ ወጣቶች ለሚያቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ትልቅ ቦታ ስለሚሰጥ እነሱን በተመለከተ ትንቢት አስነግሯል። መዝሙራዊው “ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣ ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል” በማለት ዘምሯል። አክሎም “ጐልማሶችህ እንደ ንጋት ወዳንተ ይመጣሉ” ብሏል። [የግርጌ ማስታወሻ] (መዝ. 110:3) አዎን፣ ይሖዋን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ወጣቶች በእሱ ፊት ውድ ናቸው።

2. በዛሬው ጊዜ ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ የሚከተሉትን አካሄድ በተመለከተ ምን ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል?

2 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የምትገኙ እናንት ወጣቶች፣ ራሳችሁን ለይሖዋ ወስናችኋል? ብዙ ወጣቶች እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል መወሰን ይከብዳቸው ይሆናል። ወጣቶች በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮሩ ግቦች እንዲያወጡ መምህሮቻቸውና በንግዱ ዓለም የተሳካላቸው ሰዎች እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የቤተሰባቸው አባላት ብሎም ጓደኞቻቸው ተጽዕኖ ያደርጉባቸዋል። በዚህም ምክንያት ወጣቶች መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ያፌዙባቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በሕይወት ውስጥ ከሁሉ የተሻለው አካሄድ እውነተኛውን አምላክ ማገልገል ነው። (መዝ. 27:4) ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመለከታለን:- አምላክን ማገልገል ያለብህ ለምንድን ነው? ሌሎች ሰዎች የሚሉት ወይም የሚያደርጉት ምንም ይሁን ምን፣ አንተ ራስህን ለይሖዋ ወስነህ በምትመራው ሕይወት ስኬታማ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? በቅዱስ አገልግሎት መካፈል የምትችልባቸው ምን ግሩም አጋጣሚዎች አሉ?

ይሖዋን ማገልገል ልታደርገው የሚገባ ትክክለኛ ነገር ነው

3. የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ምን እንድናደርግ ሊያነሳሱን ይገባል?

3 እውነተኛውንና ሕያው የሆነውን አምላክ ማገልገል ያለብህ ለምንድን ነው? ራእይ 4:11 ዋነኛውን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።” ሁሉንም ነገር ግሩም አድርጎ የፈጠረው ይሖዋ ነው። ምድራችን ምንኛ ውብ ናት! ዛፎችን፣ አበቦችን፣ እንስሳትን፣ ውቅያኖስን፣ ተራሮችን እንዲሁም ፏፏቴዎችን ሁሉ የፈጠረው ይሖዋ ነው። መዝሙር 104:24 ‘ምድር በአምላክ ፍጥረት እንደተሞላች’ ይገልጻል። አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ በምድርና በላይዋ ባሉት ነገሮች ለመደሰት የሚያስችል አካልና አእምሮ ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ታዲያ ድንቅ ለሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ ያለን ልባዊ አድናቆት እሱን እንድናገለግለው ሊያነሳሳን አይገባም?

4, 5. ኢያሱ ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ ያደረጉት አምላክ ያከናወናቸው የትኞቹ ነገሮች ናቸው?

4 ይሖዋን እንድናገለግል የሚገፋፋንን ሌላ ምክንያት ደግሞ የእስራኤል መሪ የነበረው ኢያሱ ገልጾታል። ኢያሱ በሕይወቱ ማብቂያ አካባቢ የአምላክን ሕዝቦች እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ፣ በፍጹም ልባችሁ በፍጹም ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ፤ አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።” ኢያሱ እንዲህ ብሎ ሊናገር የቻለው ለምን ነበር?—ኢያሱ 23:14

5 ኢያሱ ያደገው በግብፅ ስለነበር ይሖዋ ለእስራኤላውያን የራሳቸውን ምድር እንደሚሰጣቸው ቃል እንደገባ ሰምቶ መሆን አለበት። (ዘፍ. 12:7፤ 50:24, 25፤ ዘፀ. 3:8) ከዚያም ይሖዋ በግብፅ ላይ አሥሩን መቅሰፍቶች በማምጣት እብሪተኛው ፈርዖን፣ እስራኤላውያንን እንዲለቅ አደረገው፤ በዚህ መንገድ ይሖዋ የገባውን ቃል መፈጸም ሲጀምር ኢያሱ ተመልክቷል። ይሖዋ ቀይ ባሕርን አቋርጠው እንዲሻገሩ በማድረግ ሕዝቡን ሲያድናቸው እንዲሁም ፈርዖንና ሠራዊቱ ባሕሩ ውስጥ ሲሰምጡ ኢያሱ ተመልክቶ ነበር። እስራኤላውያን ‘ጭልጥ ባለውና አስፈሪ በሆነው’ የሲና ምድረ በዳ ባደረጉት ረጅም ጉዞ ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዳሟላላቸውም አይቷል። ውኃም ሆነ ምግብ አጥቶ የሞተ አንድም ሰው አልነበረም። (ዘዳ. 8:3-5, 14-16፤ ኢያሱ 24:5-7) እስራኤላውያን በከነዓን ምድር የነበሩትን ኃያላን ብሔራት ድል በማድረግ ተስፋይቱን ምድር መውረስ ባስፈለጋቸው ጊዜም ይሖዋ እነዚህን ብሔራት እንዲያሸንፉ እንዴት እንደረዳቸው ኢያሱ ተመልክቷል።—ኢያሱ 10:14, 42

6. አምላክን የማገልገል ፍላጎት ለማዳበር ምን ሊረዳህ ይችላል?

6 ኢያሱ፣ ይሖዋ የገባውን ቃል እንደፈጸመ ያውቅ ነበር። በመሆኑም “እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] እናመልካለን” ብሏል። (ኢያሱ 24:15) አንተስ? እውነተኛው አምላክ ከዚህ ቀደም ስለፈጸማቸውና ወደፊት ስለሚፈጽማቸው ተስፋዎች ስታስብ ኢያሱ እንዳደረገው አምላክን ለማገልገል ትነሳሳለህ?

7. ጥምቀት ወሳኝ እርምጃ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

7 በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች እንዲሁም እሱ በሰጣቸው አስደናቂና አስተማማኝ ተስፋዎች ላይ ማሰላሰልህ ራስህን ለይሖዋ እንድትወስን ብቻ ሳይሆን ውሳኔህን በውኃ ጥምቀት እንድታሳይም ሊገፋፋህ ይገባል። ጥምቀት፣ አምላክን ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎች ሊወስዱት የሚገባ ወሳኝ እርምጃ ነው። ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ይህንን በግልጽ አሳይቷል። ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ ማገልገል ከመጀመሩ በፊት ለመጠመቅ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ሄዶ ነበር። ይህንን እርምጃ የወሰደው ለምን ነበር? “ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነው” በማለት ከጊዜ በኋላ ተናግሯል። (ዮሐ. 6:38) ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን ማቅረቡን ለማሳየት ሲል ተጠምቋል።—ማቴ. 3:13-17

8. ጢሞቴዎስ አምላክን ለማገልገል የወሰነው ለምን ነበር? አንተስ ምን ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል?

8 የጢሞቴዎስን ሁኔታም እንመልከት፤ ይሖዋ ለዚህ ወጣት ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሥራዎችንና የአገልግሎት መብቶችን ሰጥቶት ነበር። ጢሞቴዎስ እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል የወሰነው ለምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይህ ወጣት ‘የተማረውና የተረዳው’ ወይም አምኖ የተቀበለው ነገር ስለነበረ ነው። (2 ጢሞ. 3:14) አንተም የአምላክን ቃል ከተማርክና በቃሉ ውስጥ የሚገኙት ትምህርቶች እውነት መሆናቸውን አምነህ ከተቀበልክ ሁኔታህ ከጢሞቴዎስ ጋር ተመሳሳይ ነው። በመሆኑም ውሳኔ ማድረግ ያስፈልግሃል። ልታደርገው ስላሰብከው ነገር ለምን ወላጆችህን አታማክራቸውም? ወላጆችህ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር በመሆን፣ ለመጠመቅ የሚያስፈልጉህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች መገንዘብ እንድትችል ይረዱሃል።—የሐዋርያት ሥራ 8:12ን አንብብ።

9. ስትጠመቅ አንዳንድ ሰዎች ምን ሊሰማቸው ይችላል?

9 መጠመቅ እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል የሚያስችል ጥሩ ጅምር ነው። እንዲህ ዓይነት እርምጃ ስትወስድ የረጅም ርቀት ሩጫ ትጀምራለህ፤ ይህም ወደፊት የዘላለም ሕይወት ሽልማት የሚያሰጥህ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ደስታ ታገኛለህ። (ዕብ. 12:2, 3) ከዚህም በላይ በሩጫው ውስጥ የሚካፈሉትን የቤተሰብህን አባላትና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉትን ወዳጆችህን ታስደስታለህ። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ልብ ደስ ታሰኛለህ። (ምሳሌ 23:15ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ለምን እንደወሰንክ ላይረዱ ይችላሉ፤ እንዲሁም ትክክለኛ ውሳኔ እንዳደረግህ አይሰማቸው ይሆናል። አልፎ ተርፎም ይቃወሙህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ፈተናዎች ልትወጣቸው ትችላለህ።

ሌሎች ጥያቄ ሲያቀርቡልህ ወይም ሲቃወሙህ

10, 11. (ሀ) አምላክን ለማገልገል ያደረግከውን ውሳኔ በተመለከተ ሰዎች ምን ጥያቄዎች ይጠይቁህ ይሆናል? (ለ) ኢየሱስ እውነተኛውን አምልኮ በተመለከተ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ ከሰጠበት መንገድ ምን ልትማር ትችላለህ?

10 ይሖዋን ለማገልገል ያደረግከው ውሳኔ አብረውህ የሚማሩትን ልጆች፣ ጎረቤቶችህንና ዘመዶችህን ግራ ያጋባቸው ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ጎዳና ለመከተል ለምን እንደመረጥክ እንዲሁም የምታምንባቸውን ነገሮች በተመለከተ ጥያቄዎች ያነሱ ይሆናል። ታዲያ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብሃል? እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነት ምርጫ ያደረግህበትን ምክንያት ማስረዳት እንድትችል አንተ ራስህ ስለጉዳዩ ያለህን አመለካከትና ስሜት መመርመር ይኖርብሃል። ስለ እምነትህ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመመለስ ረገድ ኢየሱስ ልትኮርጀው የምትችለው ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቷል።

11 የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ትንሣኤን በተመለከተ ኢየሱስን ለማጥመድ ጥያቄዎች ባቀረቡለት ወቅት የአምላክ ልጅ፣ እነዚህ ሰዎች ከዚያ ቀደም አስተውለውት የማያውቁትን ጥቅስ ጠቅሶላቸዋል። (ዘፀ. 3:6፤ ማቴ. 22:23, 31-33) ከጸሐፍት አንዱ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ ተስማሚ የሆነ ጥቅስ የጠቀሰለት ሲሆን ሰውየውም በተሰጠው መልስ ተደስቷል። (ዘሌ. 19:18፤ ዘዳ. 6:5፤ ማር. 12:28-34) ኢየሱስ ጥቅሶችን የተጠቀመበትና የተናገረበት መንገድ “በሕዝቡ መካከል መለያየት” እንዲፈጠር አድርጓል፤ ተቃዋሚዎቹም ምንም ጉዳት ሊያደርሱበት አልቻሉም። (ዮሐ. 7:32-46) ስለ እምነትህ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ስትሰጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቀም፤ እንዲሁም “በትሕትናና በአክብሮት” ተናገር። (1 ጴጥ. 3:15) የቀረበልህን ጥያቄ መልስ የማታውቀው ከሆነ ይህንን በግልጽ በመናገር በጉዳዩ ላይ ምርምር አድርገህ በሌላ ጊዜ መልስ መስጠት እንደምትችል አሳውቃቸው። ከዚያም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ አሊያም በሲዲ የተዘጋጀው ዎችታወር ላይብረሪ በምትችለው ቋንቋ የሚገኙ ከሆነ በእነዚህ መሣሪያዎች በመጠቀም ምርምር አድርግ። ጥሩ ዝግጅት ካደረግህ ‘እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባህ ታውቃለህ።’—ቈላ. 4:6

12. ስደት ሲደርስብህ ተስፋ መቁረጥ የማይኖርብህ ለምንድን ነው?

12 አንዳንድ ጊዜ ሰዎች፣ አምላክን ለማገልገል ስላደረግከው ውሳኔና ስለ እምነትህ ጥያቄዎች በማንሳት ብቻ አይወሰኑ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ፣ ዓለምን የሚቆጣጠረው የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። (1 ዮሐንስ 5:19ን አንብብ።) ሁሉም ሰው ያደረግከውን ውሳኔ እንደሚያደንቀው ወይም በውሳኔህ እንደሚስማማ መጠበቁ ምክንያታዊ አይሆንም፤ ተቃውሞ ሊያጋጥምህ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች በየጊዜው ‘ይሰድቡህ’ ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:4) ሆኖም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥምህ አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አስታውስ። ኢየሱስ ክርስቶስም ስደት ደርሶበታል። ሐዋርያው ጴጥሮስም ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠመው ሲሆን እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ።”—1 ጴጥ. 4:12, 13

13. ክርስቲያኖች ስደት ሲደርስባቸው የሚደሰቱት ለምንድን ነው?

13 ክርስቲያን በመሆንህ ስደት ወይም ተቃውሞ ቢደርስብህ ልትደሰት ይገባል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በዓለም ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትህ በአምላክ ሳይሆን በሰይጣን መሥፈርቶች እንደምትመራ የሚጠቁም ይሆናል። ኢየሱስ “ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካም ሲናገሩላችሁ ወዮላችሁ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት ያደረጉላቸው ይህንኑ ነበርና” በማለት አስጠንቅቋል። (ሉቃስ 6:26) ስደት፣ ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ይሖዋን በማገልገልህ እንደተናደዱብህ የሚጠቁም ነው። (ማቴዎስ 5:11, 12ን አንብብ።) በመሆኑም ‘ስለ ክርስቶስ ስም መሰደብ’ ያስደስታል።—1 ጴጥ. 4:14

14. አንድ ሰው ስደት ቢደርስበትም ለይሖዋ ታማኝ መሆኑ ምን ጥቅሞች ሊያስገኝ ይችላል?

14 ተቃውሞ ቢያጋጥምህም ለይሖዋ ታማኝ መሆንህ ቢያንስ አራት ጥቅሞች አሉት። ስለ አምላክና ስለ ልጁ ምሥክርነት ትሰጣለህ። በታማኝነት መጽናትህ ክርስቲያን ወንድሞችህንና እህቶችህን ያበረታታል። ይሖዋን የማያውቁ አንዳንድ ሰዎች አንተን በመመልከት ስለ እሱ ለመመርመር ይነሳሱ ይሆናል። (ፊልጵስዩስ 1:12-14ን አንብብ።) ከዚህም በላይ ይሖዋ ፈተናን እንድትቋቋም የሚያስችልህ ጥንካሬ እንደሰጠህ ስትመለከት ለእሱ ያለህ ፍቅር እያደገ ይሄዳል።

‘ታላቅ በር’ ተከፍቶልሃል

15. ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ‘ታላቅ በር’ ተከፍቶለት ነበር?

15 ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ስለሚያከናውነው አገልግሎት ሲናገር “ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 16:8, 9) ጳውሎስ በኤፌሶን ከተማ ምሥራቹን ለመስበክና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የሚያስችለው ታላቅ አጋጣሚ እንደተከፈተለት መናገሩ ነበር። ሐዋርያው በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩና እሱን እንዲያመልኩ ረድቷል።

16. ቅቡዓን ቀሪዎች በ1919 ‘በተከፈተላቸው በር’ የገቡት እንዴት ነበር?

16 ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ በ1919 ለቅቡዓን ቀሪዎች “የተከፈተ በር” አዘጋጅቶላቸው ነበር። (ራእይ 3:8) እነዚህ ቅቡዓንም በዚህ በር በመግባት ከመቼው ጊዜ ይበልጥ በቅንዓት ምሥራቹን እየሰበኩ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር ጀመሩ። አገልግሎታቸው ምን ውጤት አስገኝቷል? በአሁኑ ጊዜ ምሥራቹ እስከ ምድር ዳር ድረስ የተሰራጨ ሲሆን ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።

17. በተከፈተው “ታላቅ የሥራ በር” መግባት የምትችለው እንዴት ነው?

17 ይህ “ታላቅ የሥራ በር” አሁንም ለይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ክፍት ነው። በዚህ በር የሚገቡ ሁሉ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ደስታና እርካታ ያገኛሉ። እናንት ወጣት የይሖዋ አገልጋዮች፣ ሌሎች ሰዎች ‘በወንጌል እንዲያምኑ’ የመርዳቱን ተወዳዳሪ የሌለው መብት ምን ያህል ከፍ አድርጋችሁ ትመለከቱታላችሁ? (ማር. 1:14, 15) የዘወትር ወይም ረዳት አቅኚ ሆናችሁ ለማገልገል አስባችሁ ታውቃላችሁ? አብዛኞቻችሁ ልትደርሱባቸው ከምትችሏቸው የአገልግሎት መብቶች መካከል የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን፣ የቤቴል አገልግሎትን እንዲሁም ሚስዮናዊነትንና ልዩ አቅኚነትን መጥቀስ ይቻላል። ክፉው የሰይጣን ዓለም የሚጠፋበት ጊዜ እየተቃረበ በመሆኑ በእነዚህ የአገልግሎት መስኮች የመሳተፉ ጉዳይ እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር ይበልጥ አጣዳፊ ይሆናል። አንተስ ጊዜው ከማብቃቱ በፊት በዚህ ‘ታላቅ በር’ ትገባለህ?

‘ይሖዋ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ’

18, 19. (ሀ) ዳዊት፣ ይሖዋን ለማገልገል ጠንካራ ፍላጎት እንዲያድርበት የረዳው ምን ነበር? (ለ) ዳዊት አምላክን በማገልገሉ ፈጽሞ እንዳልተቆጨ የሚያሳየው ምንድን ነው?

18 መዝሙራዊው ዳዊት በአምላክ መንፈስ ተነሳስቶ ‘ይሖዋ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ’ የሚል ግብዣ አቅርቧል። (መዝ. 34:8) የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት እረኛ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ከአራዊት ጥቃት አድኖታል። ከጎልያድ ጋር ሲዋጋም አምላክ የረዳው ከመሆኑም በላይ ከሌሎች በርካታ መከራዎች ታድጎታል። (1 ሳሙ. 17:32-51፤ በመዝሙር 18 አናት ላይ የሚገኘውን መግለጫ ተመልከት።) ዳዊት የአምላክን ታላቅ ፍቅራዊ ደግነት ስለተመለከተ እንደሚከተለው ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቷል:- “እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም።”—መዝ. 40:5

19 ዳዊት ለይሖዋ ያለው ፍቅር እያደገ በመሄዱ እሱን በሙሉ ልቡና ሐሳቡ ለማገልገል ተገፋፍቷል። (መዝሙር 40:8-10ን አንብብ።) ዓመታት እያለፉ ሲሄዱም በሕይወቱ ሙሉ እውነተኛውን አምላክ በማገልገሉ ፈጽሞ አልተቆጨም። ይህ የይሖዋ አገልጋይ ለአምላክ ያደረ ሆኖ መኖሩ ከምንም ነገር ጋር የማይወዳደር ደስታ እንደሚያስገኝና ውድ ሀብት እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ዳዊት ዕድሜው ከገፋ በኋላ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ተስፋዬ፤ ከልጅነቴም ጀምሮ መታመኛዬ ነህና። አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ።” (መዝ. 71:5, 18) ዳዊት ጉልበቱ ቢደክምም በይሖዋ ላይ የነበረው እምነትና ከእሱ ጋር የመሠረተው ዝምድና ይበልጥ እየጠነከረ ሄዷል።

20. ሕይወትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ የምትጠቀምበት አምላክን ስታገለግል ነው የምንለው ለምንድን ነው?

20 ሕይወትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ የምትጠቀምበት አምላክን ስታገለግል መሆኑን የኢያሱ፣ የዳዊትና የጢሞቴዎስ ሕይወት ያረጋግጣል። በዚህ ዓለም ላይ ሰብዓዊ ሥራ መያዝ የሚያስገኘው ጊዜያዊ የሆነ ቁሳዊ ጥቅም ‘ይሖዋን በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ’ ማገልገል ከሚያስገኘው ዘላቂ ጥቅም ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም። (ኢያሱ 22:5) እስካሁን ሕይወትህን ለይሖዋ ካልወሰንክ ‘የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆን የሚያግደኝ ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። የተጠመቅህ የይሖዋ አገልጋይ ከሆንክ ደግሞ በሕይወትህ የበለጠ ደስተኛ መሆን የምትችለው እንዴት ነው? አገልግሎትህን በማስፋትና በመንፈሳዊ ለማደግ ጥረት ማድረግህን በመቀጠል ነው። የሚቀጥለው ርዕስ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ በመከተል መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• አምላክን እንድናገለግል የሚገፋፉንን ሁለት ምክንያቶች ጥቀስ።

• ጢሞቴዎስ አምላክን ለማገልገል እንዲወስን የረዳው ምን ነበር?

• ስደት ቢደርስብህም መጽናት ያለብህ ለምንድን ነው?

• በየትኞቹ የአገልግሎት መብቶች መካፈል ትችላለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሕይወት ውስጥ ከሁሉ የተሻለው አካሄድ ይሖዋን ማገልገል ነው

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ እምነትህ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ትችላለህ?