በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አምላክን በመፍራት ቅዱስ’ ሆናችሁ ኑሩ

‘አምላክን በመፍራት ቅዱስ’ ሆናችሁ ኑሩ

‘አምላክን በመፍራት ቅዱስ’ ሆናችሁ ኑሩ

“ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ . . . ይሖዋ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይሖዋ አምላክ በቅድስናው አቻ የማይገኝለት መሆኑን ይጠቁማል። (ኢሳ. 6:3 NW፤ ራእይ 4:8) “ቅድስና” የሚለውን ሐሳብ የሚያመለክቱት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ረገድ ንጹሕ መሆን እንዲሁም ከርኵሰት መራቅ የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። አምላክ ቅዱስ መባሉ በሥነ ምግባር ረገድ እንከን የለሽ መሆኑን ይጠቁማል።

ቅዱስ አምላክ የሆነው ይሖዋ፣ እሱን የሚያመልኩት ሰዎችም ቅዱስ እንዲሆኑ ማለትም በአካላዊ፣ በሥነ ምግባራዊ እንዲሁም በመንፈሳዊ ንጹሕ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ቅዱስ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። አንደኛ ጴጥሮስ 1:16 “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ይላል። ይሁን እንጂ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች እንደ ይሖዋ ቅዱስ መሆን ይችላሉ? አዎን፣ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በአንጻራዊ ሁኔታ ቅዱስ መሆን ይችላሉ። በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ ሆነን አምላክን የምናመልከው እንዲሁም ከእሱ ጋር ጥብቅ ዝምድና የምንመሠርት ከሆነ እሱም ቅዱስ እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል።

ታዲያ በሥነ ምግባር በቆሸሸ ዓለም ውስጥ ንጽሕናችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ከየትኞቹ ልማዶችስ መራቅ ይኖርብናል? በአነጋገራችንም ሆነ በድርጊታችን ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል? አምላክ፣ በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከባቢሎን ወጥተው ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱት አይሁዳውያን ምን እንደሚጠብቅባቸው የተናገረውን ሐሳብ በመመልከት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንችላለን።

‘በዚያ የተቀደሰ መንገድ ይሆናል’

ይሖዋ፣ በባቢሎን በግዞት የነበሩት ሕዝቦቹ ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ስለ መልሶ መቋቋም የሚናገረው ትንቢት “በዚያ አውራ ጐዳና ይሆናል፤ ‘የተቀደሰ መንገድ’ ተብሎ ይጠራል” የሚል ማረጋገጫ ይዞ ነበር። (ኢሳ. 35:8ሀ) ይህ ትንቢት ይሖዋ፣ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ የሚችሉበትን አጋጣሚ እንደሚከፍትላቸው ብቻ ሳይሆን በመንገዳቸው ላይም ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የሚያሳይ ነው።

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የሚገኙ አገልጋዮቹን የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን በማውጣት “የተቀደሰ መንገድ” አዘጋጅቶላቸዋል። ይሖዋ በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ በመንፈሳዊ ባርነት ተይዘው የነበሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1919 ነፃ ያወጣቸው ሲሆን እነሱም ቀስ በቀስ አምልኳቸውን ከሁሉም የሐሰት ትምህርቶች አጽድተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በዛሬው ጊዜ ንጹሕና ሰላማዊ በሆነ መንፈሳዊ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፤ ይህ ደግሞ ይሖዋን እንድናመልክ እንዲሁም ከአምላክና ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን አስችሎናል።

“ታናሽ መንጋ” የተባለው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን አባላትም ሆኑ ‘በሌሎች በጎች’ ውስጥ የሚካተቱትና ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ቅዱስ በሆነው መንገድ ላይ ለመጓዝ የመረጡ ሲሆን ሌሎች ሰዎችም አብረዋቸው እንዲጓዙ ግብዣ እያቀረቡ ነው። (ሉቃስ 12:32 የ1954 ትርጉም፤ ራእይ 7:9፤ ዮሐ. 10:16) ‘ሰውነታቸውን ቅዱስና አምላክን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ’ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ መጓዝ ይችላሉ።—ሮሜ 12:1

“የረከሱ አይሄዱበትም”

በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን አንድ አስፈላጊ ብቃት ማሟላት ይጠበቅባቸው ነበር። ኢሳይያስ 35:8ለ ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ ለመጓዝ ብቁ የሚሆኑት እነማን እንደሆኑ ሲገልጽ “የረከሱ አይሄዱበትም፤ በመንገዱ ላይ ላሉት ብቻ ይሆናል” ይላል። አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ንጹሑን አምልኮ እንደገና ለማቋቋም ስለነበር ራስ ወዳድ የሆኑ፣ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አድናቆት የጎደላቸው ወይም በመንፈሳዊ ንጹሕ ያልሆኑ ሰዎች በዚያ መንገድ እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም። ወደ አገራቸው የተመለሱት ሰዎች የይሖዋን ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መጠበቅ ነበረባቸው። በዛሬው ጊዜም ቢሆን የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ተመሳሳይ መሥፈርቶችን ማሟላት ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ‘አምላክን በመፍራት ቅዱስ’ ሆነው መኖር አለባቸው። (2 ቆሮ. 7:1) ታዲያ ልንርቃቸው የሚገቡ አንዳንድ ርኵስ ድርጊቶች ምንድን ናቸው?

ሐዋርያው ጳውሎስ “የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው:- ይኸውም ዝሙት፣ ርኵሰት፣ መዳራት [ነው]” በማለት ጽፏል። (ገላ. 5:19) ዝሙት የሚለው ቃል ከጋብቻ ውጪ በጾታ ብልት የሚፈጸምን ማንኛውንም ድርጊት ያመለክታል። መዳራት ወይም ብልግና የሚለው ቃል ደግሞ “ልቅ መሆንን፣ ባለጌነትን፣ እፍረተ ቢስነትን እንዲሁም ወራዳ ምግባርን” ያካትታል። ዝሙትም ሆነ ብልግና ከይሖዋ ቅድስና ጋር የሚጋጩ ድርጊቶች እንደሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን የመፈጸም ልማድ ያላቸው ሰዎች የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን አይችሉም ወይም ከጉባኤው ይወገዳሉ። ‘በማይረካ ምኞት፣ በርኵሰት ሁሉ መኖር’ ተብሎ የተገለጸውን አስነዋሪ ርኩሰት የሚፈጽሙ ሰዎችን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—ኤፌ. 4:19

“ርኵሰት” የተለያዩ ኃጢአቶችን የሚያጠቃልል ቃል ነው። ርኵሰት ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በድርጊት፣ በንግግርና በመንፈሳዊ ሁኔታ የጎደፉ መሆንን ያመለክታል። በተጨማሪም በፍርድ ኮሚቴ መታየት የማያስፈልጋቸውን የርኵሰት ድርጊቶች ያጠቃልላል። * ሆኖም እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ ሰዎች ቅዱስ ለመሆን ጥረት እያደረጉ ነው ሊባል ይችላል?

ለምሳሌ፣ አንድ ክርስቲያን ወሲባዊ ፊልሞችንና ሥዕሎችን በድብቅ ማየት ጀመረ እንበል። ቀስ በቀስ ርኵስ የሆኑ ምኞቶች በውስጡ እያየሉ በመሄዳቸው በይሖዋ ፊት ንጽሕናውን ለመጠበቅ ያደረገው ውሳኔ እንደሚሸረሸር ምንም ጥርጥር የለውም። የዚህ ሰው ድርጊት አስነዋሪ ርኵሰት የሚባለው ደረጃ ላይ አልደረሰ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ‘ንጹሕ የሆነውን፣ መልካም የሆነውን፣ በጎ የሆነውንና ምስጋና የሚገባውን’ ብቻ ከማሰብ በእጅጉ ርቋል። (ፊልጵ. 4:8) ወሲባዊ ፊልሞችና ሥዕሎች ርኵስ ነገሮች ከመሆናቸውም በላይ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር የመሠረተውን ዝምድና እንደሚያበላሹበት ምንም ጥርጥር የለውም። ማንኛውም የርኵሰት ነገር በመካከላችን ከቶ መነሳት አይኖርበትም።—ኤፌ. 5:3

ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። አንድ ክርስቲያን ማስተርቤሽን (የጾታ ስሜትን ለማርካት ሆነ ብሎ የራስን ስሜት ማነሳሳት) የመፈጸም ልማድ አለው እንበል፤ ምናልባትም ግለሰቡ ይህን ሲያደርግ ወሲባዊ ፊልሞችንና ሥዕሎችን የመመልከት ልማድ ይኖረው ይሆናል። ምንም እንኳ “ማስተርቤሽን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም ይህ ድርጊት አስተሳሰብንና ስሜትን የሚያረክስ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። እንዲህ ያለውን ድርጊት መፈጸሙን የሚቀጥል ሰው ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ዝምድና ይበላሽበታል ብሎም በአምላክ ፊት ርኵስ ይሆናል። እንግዲያው ሐዋርያው ጳውሎስ “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” እንዲሁም “ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም:- ዝሙት፣ ርኵሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና . . . መጐምጀት ናቸው” በማለት የሰጠውን ምክር በቁም ነገር እንመልከት።—2 ቆሮ. 7:1፤ ቈላ. 3:5

በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ይህ ዓለም ርኵስ የሆኑ ድርጊቶችን በቸልታ የሚያልፍ ከመሆኑም በላይ ሰዎች እንዲህ ያሉ ተግባሮችን እንዲፈጽሙ ያበረታታል። ርኵስ የሆኑ ድርጊቶችን እንድንፈጽም የሚቀርብልንን ፈተና መቋቋም ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች “በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ [ሊመላለሱ] አይገባም።” (ኤፌ. 4:17) ይሖዋ ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ እንድንጓዝ የሚፈቅድልን፣ በድብቅም ይሁን በግልጽ ርኵስ ድርጊት ከመፈጸም ከራቅን ብቻ ነው።

“አንበሳ አይኖርበትም”

አንዳንዶች፣ ቅዱስ አምላክ የሆነውን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት በድርጊታቸውም ሆነ በንግግራቸው ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ይኖርባቸው ይሆናል። ኢሳይያስ 35:9 እንደሚለው ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ “አንበሳ አይኖርበትም፤ ነጣቂ አውሬም አይወጣበትም።” በድርጊታቸውም ሆነ በንግግራቸው ዓመፀኛና ቁጡ የሆኑ ሰዎች በአውሬ ተመስለዋል። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ጽድቅ በሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ቦታ እንደማይኖራቸው ምንም ጥርጥር የለውም። (ኢሳ. 11:6፤ 65:25) በመሆኑም የአምላክን ሞገስ ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉትን የአራዊት ባሕርያት በማስወገድ ቅዱስ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “መራርነትን ሁሉ፣ ቍጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ” የሚል ምክር ይሰጠናል። (ኤፌ. 4:31) ቈላስይስ 3:8 “ቍጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ” ይላል። በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ላይ የሚገኘው “ስድብ” የሚለው ቃል ጎጂ፣ ሌሎችን የሚያዋርድ ወይም ቅዱስ ነገሮችን የሚያቃልል ንግግርን ያመለክታል።

በዛሬው ጊዜ ጎጂና ጸያፍ የሆኑ ንግግሮችን በቤተሰብ ውስጥ እንኳ ሳይቀር መስማት የተለመደ ሆኗል። የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ከሌላው እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ስሜት የሚጎዳ፣ ደግነት የጎደለው ወይም ክብር የሚነካ ነገር ይናገራሉ። እንዲህ ያለው ንግግር፣ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ መኖር የለበትም።—1 ቆሮ. 5:11

‘አምላክን በመፍራት ቅዱስ’ ሆኖ መኖር በረከት ያስገኛል!

ቅዱስ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማገልገል እንዴት ያለ መብት ነው! (ኢያሱ 24:19) ይሖዋ የሰጠን መንፈሳዊ ገነት በጣም ውድ ነው። በእርግጥም በይሖዋ ፊት ቅዱስ ሆነን መኖራችን ከሁሉ የተሻለ አካሄድ ነው።

አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ የገባው ቃል በቅርቡ ይፈጸማል። (ኢሳ. 35:1, 2, 5-7) እንዲህ ያለውን ዓለም በጉጉት የሚጠባበቁና አምላክ በሚፈልገው መንገድ ሕይወታቸውን የሚመሩ ሰዎች ገነትን በመውረስ ይባረካሉ። (ኢሳ. 65:17, 21) እንግዲያው ንጹሕ መንፈሳዊ አቋም በመያዝ ይሖዋን ለማምለክ እንዲሁም ከእሱ ጋር የመሠረትነውን የቅርብ ዝምድና እያጠናከርን ለመሄድ የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.12 ‘በማይረካ ምኞት ርኵሰት’ በመፈጸም እና “በርኵሰት” መካከል ስላለው ልዩነት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሐምሌ 15, 2006 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 29-31⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አይሁዳውያን ‘በተቀደሰው መንገድ’ ላይ ለመጓዝ ምን ይጠበቅባቸው ነበር?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወሲባዊ ፊልሞችና ሥዕሎችን መመልከት አንድ ሰው ከአምላክ ጋር የመሠረተውን ዝምድና ያበላሽበታል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ጭቅጭቅና ስድብን ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ’