በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልንከታተላቸው የሚገቡ ባሕርያት

ልንከታተላቸው የሚገቡ ባሕርያት

ልንከታተላቸው የሚገቡ ባሕርያት

“ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትንና ገርነትን ተከታተል።” —1 ጢሞ. 6:11 NW

1. “ተከታተል” የሚለው ቃል ምን ትርጉም እንዳለው በምሳሌ አስረዳ።

“ተከታተል” የሚለውን ቃል ስትሰማ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? በሙሴ ዘመን ግብፃውያን፣ እስራኤላውያንን ተከታትለው እንዳሳደዷቸውና በቀይ ባሕር እንደጠፉ ታስታውስ ይሆናል። (ዘፀ. 14:23) አሊያም ደግሞ በጥንቷ እስራኤል ሳያስበው ሕይወት ያጠፋ ሰው የሚያጋጥመውን አደጋ ታስብ ይሆናል። ግለሰቡ ከስድስቱ የመማጸኛ ከተሞች ወደ አንዱ በፍጥነት መግባት ነበረበት። እንዲህ ካላደረገ ‘ደም ተበቃዩ በንዴት ተከታትሎ ሊደርስበትና ሊገድለው ይችላል።’—ዘዳ. 19:6

2. (ሀ) አምላክ፣ የተወሰኑ ክርስቲያኖች እንዲከታተሉት የሰጣቸው ግብ ወይም ሽልማት ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ላሉት ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖችስ ምን ተስፋ አዘጋጅቶላቸዋል?

2 ከላይ ከተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በተቃራኒ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ቃል አዎንታዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንደተጠቀመበት እንመልከት:- “እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።” * (ፊልጵ. 3:14) ጳውሎስን ጨምሮ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሰማያዊ ሕይወት ሽልማት እንደሚያገኙ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። እነሱም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን ለአንድ ሺህ ዓመት ምድርን ይገዛሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲከታተሉት የተሰጣቸው ግብ እንዴት ግሩም ነው! በሌላ በኩል ግን በዛሬው ጊዜ ያሉት አብዛኞቹ እውነተኛ ክርስቲያኖች ያላቸው ተስፋ ወይም ግብ ከዚህ የተለየ ነው። ይሖዋ፣ አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር እነዚህ አገልጋዮቹ ማግኘት የሚችሉበት ፍቅራዊ ዝግጅት አድርጓል፤ ይኸውም ፍጹም ጤንነት ኖሯቸው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ነው።—ራእይ 7:4, 9፤ 21:1-4

3. አምላክ ላሳየን ጸጋ አድናቆታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

3 ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ልጆች ትክክል የሆነውን ለመፈጸም በሚያደርጉት ጥረት የዘላለም ሕይወት ማግኘት አይችሉም። (ኢሳ. 64:6) የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚቻለው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት በማመን ብቻ ነው። ታዲያ አምላክ ላሳየን ጸጋ አድናቆታችንን ለማሳየት ምን ማድረግ እንችላለን? አድናቆታችንን የምናሳይበት አንዱ መንገድ “ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትንና ገርነትን ተከታተል” የሚለውን መመሪያ መታዘዝ ነው። (1 ጢሞ. 6:11 NW) ይህንን ጥቅስ መመርመራችን እነዚህን ባሕርያት “በበለጠ ሁኔታ” ለመከታተል ቁርጥ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል።—1 ተሰ. 4:1

“ጽድቅን . . . ተከታተል”

4. “ጽድቅን” መከታተል አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው ምንድን ነው? ጽድቅን ለመከታተል መጀመሪያ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፋቸው በሁለቱም ደብዳቤዎች ላይ ልንከታተላቸው የሚገቡ ባሕርያትን የዘረዘረ ሲሆን በሁለቱም ጊዜያት መጀመሪያ ላይ የጠቀሰው “ጽድቅን” ነበር። (1 ጢሞ. 6:11፤ 2 ጢሞ. 2:22) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ጽድቅን እንድንከታተል በሌሎች ጥቅሶች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት አበረታቶናል። (ምሳሌ 15:9፤ 21:21፤ ኢሳ. 51:1) ይህን ለማድረግ መጀመሪያ መውሰድ ያለብን እርምጃ ‘ስለ እውነተኛው አምላክና እሱ ስለ ላከው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ ነው።’ (ዮሐ. 17:3) አንድ ሰው ጽድቅን መከታተሉ እርምጃ እንዲወስድ ይኸውም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ሲል ከዚያ ቀደም ለፈጸማቸው ኃጢአቶች ንስሐ እንዲገባና ‘ከመንገዱ እንዲመለስ’ ያነሳሳዋል።—ሥራ 3:19

5. በአምላክ ዘንድ የጽድቅ አቋም እንዲኖረንና ይህንንም ይዘን እንድንቀጥል ምን ማድረግ አለብን?

5 ከልባቸው ጽድቅን የሚከታተሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሲሆን ይህንንም በውኃ በመጠመቅ አሳይተዋል። የተጠመቅህ ክርስቲያን ከሆንክ፣ ጽድቅን እየተከታተልክ መሆንህ በአኗኗርህ ሊታይ እንደሚገባና መታየቱም እንደማይቀር አስበህ ታውቃለህ? ጽድቅን መከታተልህን በአኗኗርህ ከምታሳይባቸው መንገዶች አንዱ በሕይወትህ ውስጥ ውሳኔዎች ማድረግ በሚያስፈልግህ ጊዜ “መልካሙን ከክፉው” ለመለየት በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም ነው። (ዕብራውያን 5:14ን አንብብ።) ለምሳሌ ያህል፣ ማግባት በምትችልበት ዕድሜ ላይ የምትገኝ ነጠላ ክርስቲያን ከሆንክ ካልተጠመቀ ሰው ጋር ምንም ዓይነት የፍቅር ግንኙነት ላለመጀመር ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ጽድቅን የምትከታተል ከሆነ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ታደርጋለህ።—1 ቆሮ. 7:39

6. በትክክለኛው መንገድ ጽድቅን መከታተል ምን ነገሮችን ያካትታል?

6 ጻድቅ መሆን፣ ራስን ከማመጻደቅ ወይም “እጅግ ጻድቅ” ከመሆን የተለየ ነው። (መክ. 7:16) ኢየሱስ ከሌሎች የተሻሉ ሆኖ ለመታየት ሲሉ ጻድቅ ለመምሰል መሞከርን አውግዟል። (ማቴ. 6:1) በትክክለኛው መንገድ ጽድቅን መከታተል ከልባችን ዝንባሌ ጋር የተያያዘ ነገር ነው፤ ይህም ሲባል የተሳሳተ አስተሳሰብን፣ አመለካከትን፣ ውስጣዊ ግፊትን እንዲሁም ምኞትን ማስተካከል ያስፈልጋል ማለት ነው። እንዲህ ለማድረግ ጥረት ማድረጋችንን ከቀጠልን ከባድ ኃጢአቶችን ከመሥራት ልንቆጠብ እንችላለን። (ምሳሌ 4:23ን አንብብ፤ ከያዕቆብ 1:14, 15 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ ይሖዋ ይባርከናል እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንድንከታተል ይረዳናል።

“ለአምላክ ማደርን . . . ተከታተል”

7. “ለአምላክ ማደር” ምን ማለት ነው?

7 ለአንድ አካል ማደር፣ ከልብ በመነጨ ስሜት ራስን መስጠትና ታማኝ ሆኖ መኖር ማለት ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት “ለአምላክ ማደር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማንኛውም ነገር ለአምላክ ያለንን ፍርሃት እንዳይቀንሰው ጤናማ በሆነ መልኩ መጠንቀቅ” የሚል ሐሳብ እንደያዘ ይገልጻል። እስራኤላውያን፣ አምላክ ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላም እንኳ ታዛዦች ባለመሆን ለአምላክ የማደር ዝንባሌ ሳያሳዩ ቀርተዋል።

8. (ሀ) የአዳም ኃጢአት ምን ጥያቄ አስነስቶ ነበር? (ለ) የዚህ “ቅዱስ ሚስጥር” መልስ ግልጽ የሆነው እንዴት ነበር?

8 ፍጹም ሰው የነበረው አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ፣ “ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ማደር የሚችል ሰው አለ?” የሚለው ጥያቄ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት መልስ አላገኘም ነበር። በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት፣ ኃጢአተኛ ከሆኑት የሰው ልጆች መካከል ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ማደር የቻለ አልነበረም። ሆኖም ይሖዋ እሱ በወሰነው ጊዜ የዚህን “ቅዱስ ሚስጥር” መልስ ግልጽ አደረገው። በሰማይ የሚኖረውን የአንድያ ልጁን ሕይወት ወደ ማርያም ማሕፀን በማዛወር ልጁ ፍጹም ሰው ሆኖ እንዲወለድ አደረገ። ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው ሕይወት እንዲሁም ተዋርዶ በመሞቱ፣ ለእውነተኛው አምላክ ከልብ በመነጨ ስሜት ራስን መስጠትና ሙሉ በሙሉ ታማኝ መሆን ምን ማለት እንደሆነ አሳይቷል። ለአምላክ ያቀረባቸው ጸሎቶች በሰማይ የሚገኘውን አፍቃሪ አባቱን የማምለክ ፍላጎት እንዳለው ይጠቁማሉ። (ማቴ. 11:25፤ ዮሐ. 12:27, 28) በዚህም ምክንያት ጳውሎስ በምሳሌነት የሚጠቀሰውን የኢየሱስ ሕይወት ሲያብራራ ‘ለአምላክ ማደርን’ እንዲጠቅስ የይሖዋ መንፈስ አነሳስቶታል።—1 ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብብ። *

9. ለአምላክ ማደርን መከታተል የምንችለው እንዴት ነው?

9 ኃጢአተኞች በመሆናችን ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ማደር ባንችልም ይህንን ባሕርይ ለመከታተል ጥረት ማድረግ እንችላለን። ይህንን ለማድረግ በተቻለን መጠን የክርስቶስን ምሳሌ መከተል ያስፈልገናል። (1 ጴጥ. 2:21) እንዲህ ካደረግን “ሃይማኖታዊ” ወይም ለአምላክ የማደር “መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል” እንደተባለላቸው ግብዞች አንሆንም። (2 ጢሞ. 3:5) ይህን ስንል ግን በእውነት ለአምላክ ያደርን መሆናችን በውጫዊ ሁኔታችን አይታይም ማለት አይደለም። ለአብነት ያህል፣ የሙሽራ ቀሚስ ወይም ገበያ ስንወጣ የምንለብሰውን ልብስ ስንመርጥ አለባበሳችን ‘አምላክን እናመልካለን’ ከሚለው አቋማችን ጋር ምንጊዜም የሚስማማ መሆን አለበት። (1 ጢሞ. 2:9, 10) በእርግጥም፣ ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ለመከታተል በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል።

“እምነትን . . . ተከታተል”

10. እምነታችን ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ምን ማድረግ አለብን?

10 ሮሜ 10:17ን አንብብ። አንድ ክርስቲያን ጠንካራ እምነት ለማዳበርና እምነቱን ይዞ ለመቀጠል እንዲችል በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት ውድ እውነቶች ላይ ማሰላሰል አለበት። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ግሩም የሆኑ በርካታ ጽሑፎችን አዘጋጅቷል። ከእነዚህም መካከል እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው፣ ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) እንዲሁም “መጥተህ ተከተለኝ” (እንግሊዝኛ) የተባሉትን ሦስት ግሩም መጻሕፍት መጥቀስ ይቻላል፤ እነዚህ መጻሕፍት ክርስቶስን የበለጠ እንድናውቀውና እሱን ለመምሰል እንድንችል ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው። (ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ታማኙ ባሪያ የጉባኤ፣ የልዩ፣ የወረዳና የአውራጃ ስብስባዎችንም ያዘጋጃል፤ ከእነዚህ ስብሰባዎች አብዛኞቹ ‘የክርስቶስን ቃል’ የሚያጎሉ ናቸው። አምላክ ለሚያቀርባቸው ትምህርቶች ‘አብልጠህ በመጠንቀቅ’ ከእነዚህ ዝግጅቶች የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ልታደርገው የምትችለው ነገር አለ?—ዕብ. 2:1

11. እምነትን በመከታተል ረገድ ጸሎትና ታዛዥነት ምን ድርሻ አላቸው?

11 ጠንካራ እምነት እንዲኖረን የሚረዳን ሌላው ነገር ጸሎት ነው። የኢየሱስ ተከታዮች በአንድ ወቅት “እምነታችንን ጨምርልን” በማለት ለምነውት ነበር። እኛም አምላክ እንዲህ እንዲያደርግልን በትሕትና መጠየቅ እንችላለን። (ሉቃስ 17:5) እምነት ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ በመሆኑ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እምነታችን እንዲጠናከር እንዲረዳን መጸለይ አለብን። (ገላ. 5:22 የ1954 ትርጉም) ከዚህም በላይ የአምላክን መመሪያዎች መታዘዛችን እምነታችንን ያጠናክርልናል። ለምሳሌ ያህል፣ በስብከቱ ሥራ ላይ የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ እንጥር ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችን ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልናል። ከዚህም በላይ ‘የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን መሻታችን’ በሚያስገኝልን በረከት ላይ ስናሰላስል እምነታችን ያድጋል።—ማቴ. 6:33

“ፍቅርን . . . ተከታተል”

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ የሰጠው አዲስ ትእዛዝ ምንድን ነው? (ለ) የክርስቶስ ዓይነት ፍቅርን መከታተል የምንችለው በየትኞቹ አስፈላጊ መንገዶች ነው?

12 አንደኛ ጢሞቴዎስ 5:1, 2ን አንብብ። እዚህ ላይ ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ፍቅራቸውን እንዴት በተግባር ማሳየት እንደሚችሉ የሚጠቁም ምክር ሰጥቷል። ለአምላክ ያደርን መሆን፣ ኢየሱስ እርሱ እንደ ወደደን ‘እርስ በርስ እንድንዋደድ’ የሰጠውን አዲስ ትእዛዝ መታዘዝንም ይጨምራል። (ዮሐ. 13:34) ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል:- “ማንም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል?” (1 ዮሐ. 3:17) አንተስ ፍቅርህን በተግባር ያሳየህባቸው ጊዜያት አሉ?

13 ፍቅርን መከታተል የምንችልበት ሌላው መንገድ በወንድሞቻችን ላይ ቂም ከመያዝ ይልቅ ይቅር ባይ መሆን ነው። (1 ዮሐንስ 4:20ን አንብብ።) በዚህ መንገድ የሚከተለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንደምንፈልግ እናሳያለን:- “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ።” (ቈላ. 3:13) በጉባኤ ውስጥ ይህን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ይቅር ልትለው የሚገባ ሰው አለ? ይቅርታ ለማድረግስ ፈቃደኛ ነህ?

“ጽናትን . . . ተከታተል”

14. ከፊላደልፊያ ጉባኤ ምን ልንማር እንችላለን?

14 የአጭር ጊዜ ግብ ላይ ለመድረስ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አንድ ነገር ሲሆን አስቸጋሪ ወይም ከጠበቅነው በላይ ጊዜ የሚወስድ ግብ ላይ ለመድረስ መጣር ግን ከዚህ የተለየ ነው። የዘላለም ሕይወትን ግብ መከታተል ጽናትን እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ጌታ ኢየሱስ በፊላደልፊያ ለነበረው ጉባኤ “በትዕግሥት እንድትጸና የሰጠሁህን ትእዛዜን ስለ ጠበቅህ፣ እኔ ደግሞ . . . ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ” የሚል መልእክት ልኮ ነበር። (ራእይ 3:10) ኢየሱስ ጽናት አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል፤ ይህ ባሕርይ መከራና ፈተና ሲያጋጥመን ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በፊላደልፊያ ጉባኤ ውስጥ የነበሩት ወንድሞች በርካታ የእምነት ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም ምሳሌ የሚሆን ጽናት አሳይተዋል። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ወደፊት በሚያጋጥማቸው ከባድ ፈተና ወቅት ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያደርግላቸው ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል።—ሉቃስ 16:10

15. ኢየሱስ ስለ ጽናት ምን አስተምሯል?

15 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን የማያምኑ ዘመዶቻቸውና ዓለም እንደሚጠላቸው ያውቅ ስለነበር ቢያንስ ሁለት ጊዜ “እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል” በማለት አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 10:22፤ 24:13) ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ጊዜ ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ እንዴት እንደሚያገኙም ጠቁሟቸዋል። ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ፣ “ቃሉን ሲሰሙ በደስታ የሚቀበሉ” ሆኖም የእምነት ፈተና ሲያጋጥማቸው የሚክዱ ሰዎችን ድንጋያማ ቦታ ላይ ካለ መሬት ጋር አመሳስሏቸዋል። ታማኝ የሆኑት ተከታዮቹ ግን የአምላክን ቃል “የሚጠብቁ” እንዲሁም “በመጽናት ፍሬ የሚያፈሩ” በመሆናቸው ከመልካም መሬት ጋር አመሳስሏቸዋል።—ሉቃስ 8:13, 15

16. በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲጸኑ የረዳቸው የትኛው ፍቅራዊ ዝግጅት ነው?

16 ለመጽናት ምስጢሩ ምን እንደሆነ አስተዋልክ? የአምላክን ቃል በአእምሯችንና በልባችን ሕያው አድርገን ‘መጠበቅ’ አለብን። ትክክለኛና ለማንበብ ቀላል የሆነው የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በብዙ ቋንቋዎች መዘጋጀቱ ይህንን ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተወሰኑ ክፍሎች ላይ በየዕለቱ ማሰላሰላችን “በመጽናት” ፍሬ ለማፍራት የሚያስፈልገንን ጥንካሬ እንድናገኝ ይረዳናል።—መዝ. 1:1, 2

“ገርነትን” እና ሰላምን ተከታተል

17. (ሀ) “ገርነት” አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ገርነትን ያሳየው እንዴት ነበር?

17 ማንም ሰው ቢሆን ባልተናገረው ወይም ባላደረገው ነገር ሲነቀፍ ደስ አይለውም። ሰዎች ትክክለኛ ያልሆነ ነቀፋ ሲሰነዘርባቸው በንዴት ትችቱን ማስተባበላቸው የተለመደ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን ‘በገርነት’ ወይም በለዘበ አንደበት መልስ መስጠት ምንኛ የተሻለ ነው! (ምሳሌ 15:1ን አንብብ።) ትክክለኛ ያልሆነ ነቀፋ ሲሰነዘርብን ገርነት ማሳየት ከፍተኛ ጥንካሬ ይጠይቃል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1 ጴጥ. 2:23) ገርነትን በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ሙሉ በሙሉ መምሰል ባንችልም በዚህ በኩል ማሻሻያ ለማድረግ መጣር እንችል ይሆን?

18. (ሀ) ገርነት ምን ጥቅም አለው? (ለ) እንድንከታተለው የተመከርነው ሌላ ባሕርይ ምንድን ነው?

18 የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ስለ እምነታችን ‘መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጀን እንሁን’፤ ይህንንም “በትሕትናና [“በገርነት መንፈስና፣ NW] በአክብሮት” እናድርገው። (1 ጴጥ. 3:15) በእርግጥም፣ ገርነትን ማዳበራችን በአገልግሎታችን ከምናገኛቸው ሰዎችም ሆነ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር የአመለካከት ልዩነት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁኔታው ወደ ጦፈ ክርክር እንዳይለወጥ ይረዳናል። (2 ጢሞ. 2:24, 25) ገርነት፣ ሰላም እንዲኖረን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ልንከታተላቸው የሚገቡትን ባሕርያት ሲዘረዝር “ሰላምን” የጠቀሰው ለዚህ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞ. 2:22፤ ከ1 ጢሞቴዎስ 6:11 ጋር አወዳድር።) አዎን፣ ቅዱሳን መጻሕፍት እንድንከታተላቸው ከሚያበረታቱን ባሕርያት አንዱ “ሰላም” ነው።—መዝ. 34:14፤ ዕብ. 12:14

19. ሰባቱን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ከመረመርን በኋላ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል? ለምንስ?

19 እንድንከታተላቸው የተበረታታነውን ሰባት ክርስቲያናዊ ባሕርያት ይኸውም ጽድቅን፣ ለአምላክ ማደርን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ጽናትን፣ ገርነትንና ሰላምን በአጭሩ ተመልክተናል። በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙት ወንድሞችና እህቶች እነዚህን ውድ ባሕርያት በበለጠ ሁኔታ ለማንጸባረቅ ጥረት ሲያደርጉ እንዴት ያለ ግሩም ሁኔታ ይኖራል! ይህ ደግሞ ይሖዋን የሚያስከብረው ከመሆኑም በላይ እያንዳንዳችንን ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ እንዲቀርጸን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ጳውሎስ እዚህ ላይ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል፣ ቀጥተኛ ትርጉም “ማባረር፣ መከታተል፣ ማሳደድ እንዲሁም በምሳሌያዊ አነጋገር አንድን ነገር በቅንዓት መከታተል፣ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ መሞከር፣ አንድን ነገር ለማግኘት መጣር” የሚል ነው።

^ አን.8 አንደኛ ጢሞቴዎስ 3:16 (NW):- “በእርግጥም ይህ ለአምላክ የማደር ቅዱስ ሚስጥር ያለ ምንም ጥርጥር ታላቅ ነው:- ‘በሥጋ እንዲገለጥ ተደረገ፤ በመንፈስ ጻድቅ ተባለ፤ ለመላእክት ታየ፤ በአሕዛብ መካከል ተሰበከ፤ በዓለም ያሉ አመኑበት፤ በክብር አረገ።’”

ልናሰላስልባቸው የሚገቡ ነጥቦች

• ጽድቅንና ለአምላክ ማደርን መከታተል ምንን ይጨምራል?

• እምነትንና ጽናትን ለመከታተል ምን ይረዳናል?

• ፍቅር እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ረገድ ምን ሚና ሊጫወት ይገባል?

• ገርነትንና ሰላምን መከታተል ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ፣ ሰዎችን ለማስደመም ሲባል ጻድቅ መስሎ መታየትን አውግዟል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት እውነቶች ላይ በማሰላሰል እምነትን መከታተል እንችላለን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍቅርንና ገርነትን መከታተል እንችላለን