በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ እምነትህ ለማስረዳት ዝግጁ ነህ?

ስለ እምነትህ ለማስረዳት ዝግጁ ነህ?

ስለ እምነትህ ለማስረዳት ዝግጁ ነህ?

ስለ እምነትህ ማስረዳት እንዳለብህ እንዲሰማህ የሚያደርግ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? በፓራጓይ የምትኖረው ሱሳና የተባለች የ16 ዓመት ወጣት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ይህች እህት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ስትሆን የግብረገብ ትምህርት በሚሰጥበት ክፍለ ጊዜ አንድ ተማሪ፣ የይሖዋ ምሥክሮች “ብሉይ ኪዳንን” እንደማይቀበሉ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስም ሆነ በማርያም እንደማያምኑ ሲናገር ሰማች። ከዚህም በላይ አንዳንዶች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና እርዳታ ከመቀበል ይልቅ ሞትን የሚመርጡ ጽንፈኞች እንደሆኑ ተናገሩ። አንተ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ ኖሮ ምን ታደርግ ነበር?

ሱሳና ወደ ይሖዋ ከጸለየች በኋላ እጇን አወጣች። የትምህርቱ ክፍለ ጊዜ ሊያበቃ ስለነበር ስለ እምነቷ ንግግር ማቅረብ ትችል እንደሆነ አስተማሪዋን ፈቃድ ጠየቀቻት። አስተማሪዋም በዚህ ተስማማች። ሱሳና በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የይሖዋ ምሥክሮችእነማን ናቸው? ምን ብለው ያምናሉ? (እንግሊዝኛ) በሚለው ብሮሹር በመጠቀም ንግግሯን ተዘጋጀች።

በመጨረሻም ንግግሯን የምታቀርብበት ቀን ደረሰ። ሱሳና፣ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራበትን ምክንያት አብራራች። ቀጥላም የወደፊቱ ተስፋችን ምን እንደሆነ እንዲሁም ለምን ደም እንደማንወስድ አስረዳች። ከዚያም የክፍሏ ተማሪዎች ጥያቄ ካላቸው እንዲጠይቁ ጋበዘቻቸው። አብዛኞቹ ተማሪዎች እጃቸውን አወጡ። ይህች ወጣት ለጥያቄዎቻቸው ከቅዱሳን መጻሕፍት መልስ መስጠቷ አስተማሪዋን አስገርሟት ነበር።

ከተማሪዎቹ አንዱ “አንድ ቀን ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄጄ ነበር፤ በዚያ አንድም ምስል አላየሁም” በማለት ተናገረ። አስተማሪዋም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ምስል የሌለው ለምን እንደሆነ ሱሳናን ጠየቀቻት። ሱሳና፣ መዝሙር 115:4-8⁠ን እንዲሁም ዘፀአት 20:4⁠ን አነበበች። አስተማሪዋም “ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ምስልን የሚያወግዝ ከሆነ ቤተ ክርስቲያኖቻችን በምስል የተሞሉት ለምንድን ነው?” በማለት በመገረም ተናገረች።

ተማሪዎቹ ጥያቄ ሲጠይቁ ሱሳና እየመለሰችላቸው ውይይቱ ለ40 ደቂቃ ቀጠለ። ሱሳና፣ ደም አልወስድም—የሕክምናው መስክ መፍትሔ አስገኝቷል የተባለውን የቪዲዮ ፊልም ማየት ይፈልጉ እንደሆነ ተማሪዎቹን ስትጠይቃቸው ሁሉም ፊልሙን ለማየት ተስማመሙ። በመሆኑም አስተማሪዋ ውይይቱ በነጋታው እንዲቀጥል ዝግጅት አደረገች። ሱሳና ቪዲዮውን ካሳየቻቸው በኋላ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የሚቀበሏቸውን አማራጭ የሕክምና ዘዴዎች አብራራች። አስተማሪዋ እነዚህን ሕክምናዎች በተመለከተ እንዲህ አለች:- “ያለ ደም የሚሰጡ የዚህን ያህል በርካታ አማራጭ ሕክምናዎች እንዳሉ አላውቅም ነበር፤ ያለ ደም የሚደረገው ሕክምና የሚያስገኛቸውን ጥቅሞችም አላውቅም ነበር። እነዚህ ሕክምናዎች የሚሰጡት ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነው?” አስተማሪዋ፣ ሁሉም ሰው የዚህ ዓይነት ሕክምና ማግኘት እንደሚችል ስታውቅ “ከዚህ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቴ ሲመጡ ለመወያየት ፈቃደኛ ነኝ” በማለት ተናገረች።

ሱሳና ለ20 ደቂቃ የተዘጋጀችው ንግግር በአጠቃላይ ሦስት ሰዓት ወሰደ። ከሳምንት በኋላ ሌሎች ተማሪዎችም ስለ እምነታቸው ንግግር አቀረቡ። ንግግራቸውን ከጨረሱ በኋላ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ተማሪዎቹ ስለ እምነታቸው ማስረዳት አልቻሉም። አስተማሪዋ “የይሖዋ ምሥክር እንደሆነችው የክፍላችሁ ልጅ እናንተም ስለ እምነታችሁ ማስረዳት ያልቻላችሁት ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀቻቸው።

ተማሪዎቹም “እነሱ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ያጠናሉ፤ እኛ ግን እንዲህ አናደርግም” አሉ።

አስተማሪዋ ሱሳናን እንዲህ አለቻት:- “በእርግጥም እናንተ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ታጠናላችሁ፤ እንዲሁም ቃሉን ተግባራዊ ለማድረግ ትጥራላችሁ። ልትመሰገኑ ይገባችኋል።”

ሱሳና ዝም ማለት ትችል ነበር። እሷ ግን ስለ እምነቷ ለክፍሏ ተማሪዎች በመናገር፣ በጥንት ጊዜ በምርኮ ወደ ሶርያ የተወሰደችውን ስሟ ያልተጠቀሰ እስራኤላዊት ልጃገረድ ግሩም ምሳሌ ተከትላለች። ይህች ልጅ፣ ንዕማን በተባለው የሶርያ ጦር አዛዥ ቤት ውስጥ ታገለግል ነበር፤ ንዕማን አስከፊ የቆዳ በሽታ ነበረበት። እስራኤላዊቷ ልጃገረድ እመቤቷን “ጌታዬ በሰማርያ ያለውን ነቢይ ሄዶ ቢያገኘው እኮ ከዚህ ለምጹ ይፈውሰው ነበር” አለቻት። ልጅቷ ስለ እውነተኛው አምላክ መመሥከር እንዳለባት ተሰምቷት ነበር። በዚህም የተነሳ ጌታዋ ንዕማን የይሖዋ አምላኪ ሊሆን ችሏል።—2 ነገ. 5:3, 17

በተመሳሳይም ሱሳና ስለ ይሖዋና ስለ ሕዝቦቹ መመሥከር እንዳለባት ተሰምቷታል። ስለ እምነቷ ጥያቄ ሲነሳ መልስ በመስጠቷ የሚከተለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ታዝዛለች:- “ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት።” (1 ጴጥ. 3:15) አንተስ ስለ እምነትህ ለማስረዳት ዝግጁ ነህ? ጥያቄ ሲነሳ ለመመለስ ፈቃደኛ ነህ?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እነዚህ መሣሪያዎች ስለ እምነትህ ለማስረዳት ያግዙሃል