በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሮሜ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የሮሜ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የሮሜ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

በ56 ከክርስቶስ ልደት በኋላ አካባቢ ሐዋርያው ጳውሎስ ሦስተኛውን የሚስዮናዊ ጉዞውን ሲያደርግ ወደ ቆሮንቶስ ከተማ ሄደ። ጳውሎስ በዚያን ወቅት በሮም በሚገኙት አይሁዳውያንና አሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል የአመለካከት ልዩነት እንደተፈጠረ አውቆ ነበር። ሐዋርያው፣ እነዚህ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ፍጹም አንድነት እንዲኖራቸው ለመርዳት ስለፈለገ ደብዳቤ ጻፈላቸው።

ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሰው ልጆች ጻድቃን ተብለው ሊጠሩ የቻሉት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ጻድቃን ተብለው የተጠሩት ሰዎች አኗኗራቸው ምን ሊመስል እንደሚገባ አብራርቷል። ደብዳቤው ስለ አምላክና ስለ ቃሉ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል፤ የአምላክን ጸጋ እንዲሁም ክርስቶስ ከመዳናችን ጋር በተያያዘ የሚጫወተውን ሚና ጎላ አድርጎ ይገልጻል።—ዕብ. 4:12

ጻድቃን ተብለው የተጠሩት እንዴት ነው?

(ሮሜ 1:1 እስከ 11:36)

ጳውሎስ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” በማለት ጽፏል። አክሎም “በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል [“ጻድቃን ተብለው ተጠርተዋል፣” NW]” ብሏል። በተጨማሪም ጳውሎስ “ማንም ሰው ሕግን በመፈጸም ሳይሆን፣ በእምነት እንደሚጸድቅ” ወይም ጻድቅ ተብሎ እንደሚጠራ ተናግሯል። (ሮሜ 3:23, 24, 28) ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ‘የሌሎች በጎች’ አባላት የሆኑት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ‘ከበደል ነፃ በሚያደርግ አንድ ድርጊት’ በማመናቸው ‘ጻድቃን ተብለው መጠራት’ ችለዋል፤ በዚህም የተነሳ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዥዎች በመሆን በሰማይ የሚኖሩ ሲሆን እጅግ ብዙ ሕዝብ ደግሞ የአምላክ ወዳጆች በመሆን “ከታላቁ መከራ” የመትረፍ ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል።—ሮሜ 5:18 NW፤ ራእይ 7:9, 14፤ ዮሐ. 10:16፤ ያዕ. 2:21-24፤ ማቴ. 25:46

ጳውሎስ “ከሕግ በታች ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች በመሆናችን ኀጢአት እንሥራን?” ሲል ከጠየቀ በኋላ “በጭራሽ አይገባም!” በማለት መልሷል። አክሎም “ወደ ሞት ለሚወስደው ለኀጢአት ወይም ወደ ጽድቅ ለሚያደርሰው ለመታዘዝ ባሮች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?” ብሏል። (ሮሜ 6:15, 16) ጳውሎስ “ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ” በማለት ጽፏል።—ሮሜ 8:13

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:24-32—እዚህ ላይ የተገለጸውን ወራዳ ድርጊት የሚፈጽሙት አይሁዳውያን ነበሩ ወይስ አሕዛብ? ጥቅሱ ላይ የተገለጸውን ወራዳ ድርጊት የሚፈጽሙት ሁለቱም ወገኖች ሊሆኑ ቢችሉም ጳውሎስ የተናገረው ከሃዲ ስለሆኑት የጥንቶቹ እስራኤላውያን ነበር። እነዚህ ሕዝቦች የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ቢያውቁም ‘አምላክን ለማወቅ አልወደዱም።’ [የ1954 ትርጉም] በመሆኑም ሊወቀሱ ይገባቸው ነበር።

3:24, 25—‘በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነው ቤዛነት’፣ ሳይከፈል በፊት “ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት” ሊሸፍን የቻለው እንዴት ነው? በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው የመጀመሪያው መሲሐዊ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በሞተበት ወቅት ነበር። (ገላ. 3:13, 16) ሆኖም አምላክ ዓላማውን እንዳይፈጽም የሚያግደው ምንም ነገር ስለሌለ ይህን ትንቢት በተናገረበት ወቅት የቤዛውን ዋጋ እንደተከፈለ አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል። በመሆኑም ይሖዋ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደፊት የሚያቀርበውን መሥዋዕት መሠረት በማድረግ በዚህ ተስፋ ላይ እምነት የሚያሳድሩ የአዳም ዘሮችን ኃጢአት ይቅር ማለት ችሏል። እንዲሁም ቤዛው ከክርስትና በፊት የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ከፍቷል።—ሥራ 24:15

6:3-5—ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ለመሆን መጠመቅና ከሞቱ ጋር አንድ ለመሆን መጠመቅ የሚሉት አገላለጾች ምን ትርጉም አላቸው? ይሖዋ የክርስቶስን ተከታዮች በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባቸው ከኢየሱስ ጋር አንድ ከመሆናቸውም ሌላ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ አባላት ይሆናሉ፤ ይህ ጉባኤ የክርስቶስ አካል ሲሆን የአካሉ ራስ ደግሞ ኢየሱስ ነው። (1 ቆሮ. 12:12, 13, 27፤ ቈላ. 1:18) ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ለመሆን መጠመቅ የሚለው አገላለጽ ትርጉም ይህ ነው። በተጨማሪም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የመሥዋዕትነት ሕይወት ስለሚመሩና በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን ስለሚተዉ ‘[ከክርስቶስ] ሞት ጋር አንድ ለመሆን እንደሚጠመቁ’ ተገልጿል። በመሆኑም የቅቡዓኑ ሞት ቤዛዊ ጥቅም ባይኖረውም እንደ ኢየሱስ የመሥዋዕትነት ሞት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ከሞቱ በኋላ ወደ ሰማይ ለመሄድ ትንሣኤ ሲያገኙ ከክርስቶስ ሞት ጋር አንድ ለመሆን የሚጠመቁት ጥምቀት ይጠናቀቃል።

7:8-11—‘ኃጢአት ትእዛዙ ባስገኘው ዕድል የተጠቀመው’ እንዴት ነው? ሕጉ፣ ሰዎች የኃጢአትን ምንነት ሙሉ በሙሉ እንዲያውቁ ረድቷቸዋል፤ ይህም ኃጢአተኛ መሆናቸውን የበለጠ እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል። በዚህም ምክንያት በብዙ መንገዶች ኃጢአት እንደሠሩ ማወቅ የቻሉ ሲሆን በርካታ ሰዎችም ኃጢአተኞች መሆናቸውን ተገንዝበዋል። ኃጢአት ሕጉ ባስገኘው ዕድል እንደተጠቀመ የተገለጸው ለዚህ ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:14, 15:- ወንጌሉን በቅንዓት እንድንሰብክ የሚገፋፉን በርካታ ምክንያቶች አሉን። ከእነዚህ መካከል አንዱ በኢየሱስ ደም የተዋጁት ሰዎች ዕዳ ያለብን መሆኑ ነው፤ እነዚህን ሰዎች በመንፈሳዊ የመርዳት ግዴታ አለብን።

1:18-20:- የማይታዩት የአምላክ ባሕርያት በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ በግልጽ ስለሚታዩ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ክፉ ሰዎች ምንም “ማመካኛ” የላቸውም።

2:28፤ 3:1, 2፤ 7:6, 7:- ጳውሎስ፣ አይሁዳውያንን ቅር ሊያሰኙ የሚችሉ ጉዳዮችን አንስቶ ከተናገረ በኋላ ንግግሩን የሚያለዝብ ሐሳብ ሰጥቷል። ይህም አወዛጋቢ ጉዳዮችን እንዴት በዘዴ መግለጽ እንደምንችል የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል።

3:4:- የሰዎች ሐሳብ አምላክ በቃሉ ውስጥ ካሰፈረው ሐሳብ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው መልእክት ላይ እምነት በማሳደርና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ‘አምላክ እውነተኛ’ ሆኖ እንዲገኝ እናደርጋለን። ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈልም ሌሎች ሰዎች አምላክ እውነተኛ መሆኑን እንዲገነዘቡ እንረዳቸዋለን።

4:9-12:- የአብርሃም እምነት እንደ ጽድቅ የተቆጠረለት በ99 ዓመቱ ከመገረዙ ከረጅም ጊዜ በፊት ነበር። (ዘፍ. 12:4፤ 15:6፤ 16:3፤ 17:1, 9, 10) አምላክ እንዲህ በማድረጉ፣ በእሱ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖረን የሚያደርገን ምን እንደሆነ የሚያሳይ ጠንካራ ትምህርት ሰጥቷል።

4:18:- ለማመን ተስፋ በጣም አስፈላጊ ነው። እምነታችን የተመሠረተው በተስፋችን ላይ ነው።—ዕብ. 11:1

5:18, 19:- ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ከአዳም ጋር የሚመሳሰልበትን መንገድ በምክንያት በማስረዳት አንድ ሰው ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ መስጠት’ የሚችለው እንዴት እንደሆነ በጥቂት ቃላት ተጠቅሞ ቀለል ባለ መንገድ አብራርቷል። (ማቴ. 20:28) እንዲህ ያለው በምክንያት የማስረዳትና ቀለል ባለ መንገድ የማስተማር ዘዴ ልንኮርጀው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ነው።—1 ቆሮ. 4:17

7:23:- እንደ እጃችን፣ እግራችንና አንደበታችን ያሉት የአካላችን ክፍሎች ‘ለኀጢአት ሕግ እስረኛ ሊያደርጉን’ ስለሚችሉ ያላግባብ እንዳንጠቀምባቸው መጠንቀቅ አለብን።

8:26, 27:- ያጋጠሙን ሁኔታዎች በጣም ግራ የሚያጋቡ ከመሆናቸው የተነሳ ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን በማናውቅበት ጊዜ “መንፈስ . . . ለእኛ ይማልድልናል።” ‘ጸሎትን የሚሰማው’ ይሖዋም በቃሉ ላይ የሰፈሩ ከእኛ ሁኔታ ጋር የሚስማሙ ጸሎቶችን እኛ እንዳቀረብናቸው አድርጎ ይሰማል።—መዝ. 65:2

8:38, 39:- መከራም ሆነ ክፉ መንፈሳውያን ፍጥረታት እንዲሁም ሰብዓዊ መንግሥታት ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር እንዲጠፋ ሊያደርጉ አይችሉም፤ እኛም እነዚህ ነገሮች ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እንዲያጠፉብን መፍቀድ የለብንም።

9:22-28፤ 11:1, 5, 17-26:- ስለ እስራኤል መልሶ መቋቋም የተነገሩት በርካታ ትንቢቶች የተፈጸሙት በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ነው፤ የዚህ ጉባኤ አባላት ‘የተጠሩት ከአይሁድ ወገን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም’ ጭምር ነው።

10:10, 13, 14:- ለአምላክና ለሰዎች ካለን ፍቅር በተጨማሪ በይሖዋና በተስፋዎቹ ላይ ያለን ጠንካራ እምነት በክርስቲያናዊው አገልግሎት በቅንዓት እንድንካፈል ያነሳሳናል።

11:16-24, 33:- ‘የአምላክ ቸርነትና ጭካኔ’ ወይም ጥብቅነት እንዴት ሚዛኑን የጠበቀ ነው! አዎን፣ “እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው።”—ዘዳ. 32:4

ጻድቃን ተብሎ ከመጠራት ጋር ተስማምቶ መኖር

(ሮሜ 12:1 እስከ 16:27)

ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኀራኄ እለምናችኋለሁ።” (ሮሜ 12:1) ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ጻድቃን ተብለው ከመጠራታቸው አንጻር ጳውሎስ ቀጥሎ የተናገረው ነገር ስለ ራሳቸው፣ ስለ ሌሎችና ስለ መንግሥት ባለ ሥልጣናት በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለበት።

ጳውሎስ “ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ . . . እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ” ብሏል። እንዲሁም “ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል። (ሮሜ 12:3, 9) “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማም[ን]ት መገዛት ይገባዋል።” (ሮሜ 13:1) ጳውሎስ ለሕሊና በተተዉ ነገሮች ረገድ ክርስቲያኖች ‘አንዳቸው በሌላው ላይ ከመፍረድ እንዲቈጠቡ’ አበረታቷቸዋል።—ሮሜ 14:13

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

12:20—በጠላታችን ራስ ላይ ‘የእሳት ፍም የምንከምረው’ እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ያልተጣራ ብረት፣ ምድጃ ውስጥ ይከተትና ከላይም ከታችም ፍም ይደረግበት ነበር። ከላይ የተከመረበት ፍም የሙቀቱን መጠን ስለሚጨምረው ብረቱ ቀልጦ ከቆሻሻው እንዲለይ ያደርገዋል። በተመሳሳይም ለጠላታችን ደግነት የተሞላበት ነገር ስናደርግለት የእሳት ፍም በራሱ ላይ የምንከምርበት ሲሆን ይህም የልቡ ደንዳናነት ቀልጦ መልካም ባሕርያቱ እንዲወጡ ያደርጋል።

12:21—‘ክፉን በመልካም ማሸነፍ’ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን የምናደርግበት አንዱ መንገድ ይሖዋ የሰጠንን ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ ሥራ እሱ በቃ እስኪል ድረስ በድፍረት ማከናወናችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ነው።—ማር. 13:10

13:1—“ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” ሊባል የሚችለው በምን መንገድ ነው? ሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት “በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው” የሚባለው እንዲገዙ የፈቀደላቸው አምላክ በመሆኑ ነው፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ አምላክ ስለ አገዛዛቸው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ በርካታ ገዥዎች አስቀድሞ የተናገረው ትንቢት ይህንን ያረጋግጥልናል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

12:17, 19:- ለመበቀል መሞከር ይሖዋ ብቻ ሊወስደው የሚገባውን እርምጃ እኛ እንደመውሰድ ይሆንብናል። ‘ክፉን በክፉ መመለስ’ የትዕቢት አካሄድ ነው።

14:14, 15:- ለወንድማችን በምናቀርብለት ምግብ ወይም መጠጥ ልናሳዝነው ወይም ልናሰናክለው አይገባም።

14:17:- አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረቱ በዋነኝነት የተመካው አንድን ምግብ በመብላቱ ወይም ባለመብላቱ አሊያም አንድን መጠጥ በመጠጣቱ ወይም ባለመጠጣቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ፊት ሞገስ ማግኘቱ ከጽድቅ፣ ከሰላምና ከሐሤት ጋር የተያያዘ ነው።

15:7:- እውነትን ከልባቸው የሚፈልጉ ሰዎችን በሙሉ ያለ አድልዎ በጉባኤ ውስጥ መቀበል እንዲሁም ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ የመንግሥቱን መልእክት ማወጅ ይገባናል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤዛው ሳይከፈል በፊት ለተፈጸሙት ኃጢአቶች ይቅርታ ሊያስገኝ ይችላል?