በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የቀድሞው ፍቅርህ’ እንዳይቀዘቅዝ ተጠንቀቅ

‘የቀድሞው ፍቅርህ’ እንዳይቀዘቅዝ ተጠንቀቅ

‘የቀድሞው ፍቅርህ’ እንዳይቀዘቅዝ ተጠንቀቅ

“ያለህን አጥብቀህ ያዝ።”—ራእይ 3:11

1, 2. ስለ ይሖዋ የተማርከው ነገር እውነት መሆኑን ስታምንበት ምን ተሰምቶህ ነበር?

ይሖዋ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ስላዘጋጀው ግሩም ተስፋ መጀመሪያ የሰማህበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? ከዚያ በፊት የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ከነበርክ የአምላክ ዓላማ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሲብራራልህ ወይም ቀደም ሲል ለመረዳት ይከብዱህ የነበሩ ትምህርቶች ግልጽ ሲሆኑልህ ምን ተሰማህ? ስለ አምላክ ትክክለኛውን ነገር እንዳልተማርክ ተገንዝበህ ይሆናል። እውነትን በማወቅህ ግን በጣም ተደስተሃል! በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆችህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆኑ፣ ስለ ይሖዋ የተማርካቸው ነገሮች እውነት እንደሆኑ ስታምንባቸውና ከተማርካቸው ነገሮች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ስትወስን ምን ተሰምቶህ እንደነበር ታስታውሳለህ?—ሮሜ 12:2

2 አብዛኞቹ መንፈሳዊ ወንድሞችህ እውነትን ሲያውቁ በጣም ተደስተው እንደነበረ፣ ወደ ይሖዋ እንደቀረቡ እንደተሰማቸው እንዲሁም ወደ ራሱ ስለሳባቸው አመስጋኞች እንደነበሩ ይነግሩሃል። (ዮሐ. 6:44) ደስታቸው በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ አነሳስቷቸዋል። እነዚህ ወንድሞች በጣም ከመደሰታቸው የተነሳ የተማሩትን ነገር ለሁሉም ሰው ለማካፈል ይፈልጉ ነበር። አንተስ እንደዚህ ተሰምቶህ ነበር?

3. ኢየሱስ ለኤፌሶን ጉባኤ መልእክት በላከበት ወቅት ጉባኤው የነበረበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

3 ኢየሱስ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ በላከው መልእክት ላይ ጉባኤው ‘ቀድሞ ስለነበረው ፍቅር’ ጠቅሶ ነበር። የኤፌሶን ክርስቲያኖች በርካታ መልካም ባሕርያት ቢኖሯቸውም በአንድ ወቅት ለይሖዋ የነበራቸው ፍቅር ቀዝቅዞ ነበር። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “ሥራህን፣ ጥረትህንና ትዕግሥትህን ዐውቃለሁ። ክፉዎችንም ችላ ብለህ እንዳላለፍሃቸው፣ ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትንም መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ። ደግሞም በትዕግሥት መጽናትህንና ስለ ስሜም መከራን መቀበልህን ዐውቃለሁ፤ በዚህ ሁሉ አልታከትህም። ይሁን እንጂ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል።”—ራእይ 2:2-4

4. ኢየሱስ ለኤፌሶን ጉባኤ የላከው መልእክት በዛሬው ጊዜ ጠቃሚ የሆነው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ለኤፌሶን ጉባኤም ሆነ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ለተጠቀሱት ሌሎች ጉባኤዎች የሰጠው ምክር ከ1914 ጀምሮ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለነበሩበት ሁኔታ ተስማሚ ነበር። (ራእይ 1:10) በአሁኑ ጊዜም ቢሆን አንዳንድ ክርስቲያኖች ለይሖዋም ሆነ ለክርስትና እውነት ‘ቀድሞ የነበራቸው ፍቅር’ ሊቀዘቅዝ ይችላል። ይህንን በአእምሯችን በመያዝ፣ አንተ በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህን ነገሮች ማስታወስህ እንዲሁም በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰልህ ለአምላክም ሆነ ለእውነት መጀመሪያ የነበረህ ፍቅርና ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ፣ እንዲታደስና እያደገ እንዲሄድ ለማድረግ እንዴት እንደሚረዳህ እንመልከት።

የተማርከው ነገር እውነት መሆኑን እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

5, 6. (ሀ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ምን ማወቅ አለበት? (ለ) አንተ በግልህ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት ነገር እውነት መሆኑን ያሳመነህ ምንድን ነው? (ሐ) አንድ ሰው ቀድሞ የነበረውን ፍቅር ለማደስ ምን ሊረዳው ይችላል?

5 ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ማንኛውም ክርስቲያን እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ከማድረጉ በፊት፣ ‘መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ’ ምን እንደ ሆነ ‘ፈትኖ አውቋል።’ (ሮሜ 12:1, 2) ይህን ለማድረግ ከረዱት ነገሮች አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማሩ ነው። አንድ ሰው፣ የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንደሚያስተምሩ እንዲያምን የሚያደርገው ነገር ሌላውን ሰው ከሚያሳምነው ነገር የተለየ ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች አመለካከታቸው የተለወጠው የአምላክን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲያነቡ ወይም ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እውነቱን ሲያውቁ እንደሆነ ያስታውሳሉ። (መዝ. 83:18፤ መክ. 9:5, 10) ሌሎች ደግሞ የማረካቸው በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የተመለከቱት ፍቅር ነው። (ዮሐ. 13:34, 35) አንዳንዶች የዓለም ክፍል አለመሆን ምን ትርጉም እንዳለው መረዳታቸው ልባቸውን ነክቶታል። እነዚህ ግለሰቦች እውነተኛ ክርስቲያኖች በማንኛውም አገር ፖለቲካዊ ውዝግብም ሆነ ጦርነት ውስጥ መካፈል እንደሌለባቸው ተገንዝበው ነበር።—ኢሳ. 2:4፤ ዮሐ. 6:15፤ 17:14-16

6 በርካታ ሰዎች፣ መጀመሪያ ላይ አምላክን እንዲወዱት ያደረጓቸው እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ነበሩ። እስቲ አንተም የተማርከው ነገር እውነት መሆኑን እንድታምን ያደረግህ ምን እንደነበረ ለማስታወስ ሞክር። የእያንዳንዱ ሰው ባሕርይና በሕይወቱ ውስጥ የሚያጋጥሙት ሁኔታዎች የተለያዩ በመሆናቸው አንተም ይሖዋን እንድትወደውና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንዲኖርህ ያደረጉህ ምክንያቶች ከሌሎች ሰዎች የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ምክንያቶች፣ መጀመሪያ እውነትን ስትሰማ አሳማኝ እንደሆኑልህ ሁሉ ዛሬም እውነትን እንደያዝክ እንደሚያሳምኑህ አያጠራጥርም። እውነት ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። ስለዚህ እነዚያን ትምህርቶች መለስ ብለህ ማሰብህና በዚያን ጊዜ ምን ተሰምቶህ እንደነበረ ማስታወስህ ለእውነት የነበረህን የቀድሞ ፍቅር ለማደስ ይረዳሃል።—መዝሙር 119:151, 152⁠ን እና 143:5ን አንብብ።

መሠረትህን አጠናክረው

7. መጀመሪያ ላይ ለእውነት የነበረን ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

7 ራስህን ለይሖዋ ከወሰንክ በኋላ ባለፉት ዓመታት በሕይወትህ ውስጥ በርካታ ለውጦች አጋጥመውህ ይሆናል። ለእውነት የነበረህ የቀድሞ ፍቅር አስፈላጊ ቢሆንም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ያጋጠሙህን እምነትህን የሚፈታተኑ አዳዲስ ነገሮች ለመቋቋም እንድትችል ፍቅርህን ማጠናከር አስፈልጎሃል። ይሖዋም በዚህ ጊዜ ረድቶሃል። (1 ቆሮ. 10:13) በመሆኑም ባለፉት ዓመታት ያካበትካቸው ተሞክሮዎችም በጣም ይጠቅሙሃል። እነዚህ ተሞክሮዎች የቀድሞ ፍቅርህ እያደገ እንዲሄድ የረዱህ ከመሆኑም ሌላ መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ ፈትነህ ለማወቅ ከሚያስችሉህ መንገዶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።—ኢያሱ 23:14፤ መዝ. 34:8

8. ይሖዋ ራሱን ለሙሴ ሲገልጽለት ምን ብሎት ነበር? እስራኤላውያን አምላክን የበለጠ ማወቅ የቻሉት እንዴት ነበር?

8 ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት ዓላማ እንዳለው ከገለጸላቸው በኋላ የተከናወኑትን ነገሮች እንመልከት። አምላክ “መሆን የሚያስፈልገኝን ሁሉ እሆናለሁ” (NW) በማለት ለሙሴ ራሱን ገልጦለታል። (ዘፀ. 3:7, 8, 13, 14) በሌላ አባባል ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን ነፃ ለማውጣት ሲል የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን መግለጹ ነበር። ከዚያ በኋላ የተከናወኑት ሁኔታዎች እንዲሁም አምላክ በወቅቱ አስፈላጊ የነበሩትን ነገሮች ለማሟላት የወሰዳቸው እርምጃዎች ይሖዋ፣ ዳኛና መሪ እንዲሁም ነፃ አውጪ፣ ተዋጊ፣ ተንከባካቢና ሁሉን ቻይ አምላክ መሆን እንደሚችል ለእስራኤላውያን አሳይተዋቸዋል።—ዘፀ. 12:12፤ 13:21፤ 14:24-31፤ 16:4፤ ነህ. 9:9-15

9, 10. አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ያጋጠመው ምን ዓይነት ሁኔታ አምላክን የበለጠ ለማወቅ ሊረዳው ይችላል? እነዚህን አጋጣሚዎች ማስታወሱ ጠቃሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?

9 እርግጥ ነው፣ የአንተ ሁኔታ ከጥንቶቹ እስራኤላውያን የተለየ ነው። ያም ቢሆን አምላክ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ እንድታምን ያደረጉህ ሁኔታዎች በሕይወትህ ውስጥ አጋጥመውህ ይሆናል፤ እነዚህ ሁኔታዎችም እምነትህን አጠናክረውልሃል። ምናልባትም ይሖዋ ተንከባካቢ፣ አጽናኝ ወይም አስተማሪ ሆኖልህ ሊሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 30:20ለ, 21ን አንብብ።) ወይም ላቀረብከው ጸሎት ቀጥተኛ መልስ አግኝተህ ይሆናል። አሊያም ደግሞ አንድ ፈታኝ ሁኔታ ባጋጠመህ ወቅት የእምነት ባልንጀራህ ረድቶህ ሊሆን ይችላል። ወይም የግል ጥናት ስታደርግ አንተ ካለህበት ሁኔታ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ጥቅሶችን አግኝተህ ይሆናል።

10 ይሖዋ ያደረገልህ እንደነዚህ ያሉት ነገሮች ተዓምር ባለመሆናቸው ለሌሎች ሰዎች ስትነግራቸው የአንተን ያህል ልባቸው ላይነካ ይችላል። ለአንተ ግን ትልቅ ትርጉም አላቸው። አዎን፣ ይሖዋ ለአንተ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ሆኖልሃል። እስቲ በእውነት ውስጥ ያሳለፍካቸውን ዓመታት መለስ ብለህ አስብ። በሕይወትህ ውስጥ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህ የተመለከትክባቸውን አጋጣሚዎች ማስታወስ ትችላለህ? ከሆነ እነዚህን አጋጣሚዎችና በወቅቱ ያሳደሩብህን ስሜት ማስታወስህ በዚያን ጊዜ ስለ ይሖዋ ተሰምቶህ የነበረው ዓይነት ፍቅር እንዲሰማህ ሊያደርግህ ይችላል። እነዚህን አጋጣሚዎች ከፍ አድርገህ ተመልከታቸው፤ እንዲሁም አሰላስልባቸው። እነዚህ ነገሮች ይሖዋ፣ በግለሰብ ደረጃ ለአንተ እንደሚያስብልህ እንድታምን የሚያደርጉ ማስረጃዎች ናቸው፤ ማንም ይህንን እምነትህን ሊያዳክምብህ አይችልም።

ራስህን መርምር

11, 12. አንድ ክርስቲያን ለእውነት ያለው ፍቅር ከቀዘቀዘ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ ምን ምክር ሰጥቷል?

11 ለአምላክም ሆነ ለእውነት የነበረህ ፍቅር እንደቀዘቀዘ ከተሰማህ እንዲህ ዓይነት ስሜት ያደረብህ ይሖዋ ስለተለወጠ አይደለም። ይሖዋ ፈጽሞ አይለወጥም። (ሚል. 3:6፤ ያዕ. 1:17) እሱ እንደ በፊቱ ሁሉ አሁንም ስለ አንተ ያስባል። ከይሖዋ ጋር ያለህ ግንኙነት እንደ በፊቱ ካልሆነ ለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን? የኑሮ ውጣ ውረድ ከቀድሞው ይበልጥ እንድትጨነቅና ውጥረት እንዲበዛብህ አድርጎህ ይሆን? ምናልባትም ከዚህ በፊት አጥብቀህ የመጸለይ፣ በትጋት የማጥናት እንዲሁም አዘውትረህ የማሰላሰል ልማድ ይኖርህ ይሆናል። ከዚህ ቀደም አሁን ከምታደርገው ይበልጥ በአገልግሎት በቅንዓት ትካፈል እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረህ ትገኝ ነበር?—2 ቆሮ. 13:5

12 ራስህን ከመረመህ በኋላ ምንም የተለወጠ ነገር እንደሌለ ይሰማህ ይሆናል፤ ለውጥ እንዳለ ካስተዋልክ ግን መንስኤው ምን ሊሆን ይችላል? ለቤተሰብህ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማሟላት ወይም ጤንነትህን ለመጠበቅ የምታደርገው ጥረት አሊያም እንደነዚህ ያሉ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የይሖዋ ቀን መቅረቡን እንድትዘነጋና የጥድፊያ ስሜትህን እንድታጣ አድርገውህ ይሆን? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸዋል:- “በገደብ የለሽ ሕይወት፣ በመጠጥ ብዛትና ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ እንዳይዝልና ያ ቀን እንደ ወጥመድ ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ይህ በመላው ምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ይደርሳልና። ስለዚህ ከሚመጣው ሁሉ እንድታመልጡ . . . ሁልጊዜ ተግታችሁ ጸልዩ።”—ሉቃስ 21:34-36

13. ያዕቆብ የአምላክን ቃል ከምን ጋር አመሳስሎታል?

13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ያዕቆብ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ በአምላክ ቃል በመጠቀም ራሳቸውን በሐቀኝነት እንዲመረምሩ አሳስቧቸዋል። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቃሉ የሚናገረውን አድርጉ እንጂ ሰሚዎች ብቻ ሆናችሁ ራሳችሁን አታታልሉ። ቃሉን የሚሰማ፣ ነገር ግን የሚለውን የማይፈጽም ሰው ፊቱን በመስተዋት እንደሚያይ ሰው ነው፤ ራሱንም አይቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም ምን እንደሚመስል ይረሳል፤ ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹም ሕግ ተመልክቶ የሚጸና፣ የሰማውን የሚያደርግና የማይረሳ ሰው በሥራው የተባረከ ይሆናል።”—ያዕ. 1:22-25

14, 15. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ አቋምህን ለማሻሻል የሚረዳህ እንዴት ነው? (ለ) በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ ልታሰላስል ትችላለህ?

14 አንድ ሰው አለባበሱና ሁሉ ነገሩ መስተካከሉን ለማረጋገጥ መስተዋት ይመለከታል። ለምሳሌ ያህል፣ ወንዶች ክራባታቸው እንደተዛነፈ ከተመለከቱ ያስተካክሉታል። ሴቶች ደግሞ ጸጉራቸው መስተካከል እንደሚያስፈልገው ካዩ መልክ ያስይዙታል። በተመሳሳይም ቅዱሳን መጻሕፍት ራሳችንን እንድንመረምር ይረዱናል። በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት ከሚጠበቅብን ነገር ጋር ራሳችንን ስናወዳድር መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መስተዋት እየተጠቀምንበት ነው። ይሁን እንጂ በራሳችን ላይ የተመለከትነውን ጉድለት የማናስተካክለው ከሆነ መስተዋት ማየታችን ምን ጥቅም አለው? በአምላክ “ፍጹም ሕግ” ውስጥ ከተመለከትነው ነገር ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ቃሉን ‘ማድረግ’ የጥበብ አካሄድ ነው። እንግዲያው ለይሖዋም ሆነ ለእውነት ቀድሞ የነበረው ፍቅር እንደቀዘቀዘ የተገነዘበ ማንኛውም ሰው በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰሉ ተገቢ ነው:- ‘በሕይወቴ ውስጥ ምን የሚያስጨንቁ ሁኔታዎች ገጥመውኛል? እነዚህን ሁኔታዎች ለመቋቋም ምን እያደረግሁ ነው? ከዚህ በፊት እንደነዚህ ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ ምን አድርጌ ነበር? አሁን የተለወጠ ነገር አለ?’ በዚህ መልኩ ራስህን ስትመረምር አንዳንድ ድክመቶች እንዳሉህ ካስተዋልክ ችላ አትበላቸው። ለውጥ ማድረግ የሚያስፈልግህ ከሆነ ሳትውል ሳታድር ማስተካከያ አድርግ።—ዕብ. 12:12, 13

15 በዚህ መንገድ ማሰላሰልህ በመንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚያግዙህ ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦችን ለማውጣትም ሊረዳህ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባው ለሆነው ለጢሞቴዎስ በአገልግሎቱ ማሻሻያ ለማድረግ የሚያስችለው ምክር ሰጥቶታል። ጳውሎስ በዕድሜ ከእሱ የሚያንሰውን ጢሞቴዎስን “ሰው ሁሉ ማደግህን ያይ ዘንድ በእነዚህ ነገሮች ላይ አትኵር፤ በትጋትም ፈጽማቸው” በማለት አሳስቦታል። እኛም በምን ረገድ እድገት ማድረግ እንደምንችል ለማወቅ በአምላክ ቃል ተጠቅመን ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው።—1 ጢሞ. 4:15

16. በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅመህ ራስህን ስትመረምር የትኛውን አደገኛ አመለካከት እንዳታዳብር መጠንቀቅ ይኖርብሃል?

16 በሐቀኝነት ራስህን ስትመረምር አንዳንድ ድክመቶች እንዳሉህ መገንዘብህ አይቀርም። ይህ ተስፋ ሊያስቆርጥህ የሚችል ቢሆንም ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጥ። ራስህን የምትመረምረው በየትኞቹ ነገሮች ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ለማወቅ መሆኑን አትዘንጋ። የሰይጣን ፍላጎት አንድ ክርስቲያን ያሉትን ጉድለቶች በማሰብ ከንቱ እንደሆነ እንዲሰማው ማድረግ ነው። አምላክ እሱን ለማገልገል የሚደረገውን ጥረት ከቁብ እንደማይቆጥረው የሚገልጽ ክስ ተሰንዝሯል። (ኢዮብ 15:15, 16፤ 22:3) ኢየሱስ ግን ይህ ዓይነቱ አመለካከት ውሸት መሆኑን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ሰጥቶናል፤ አምላክ እያንዳንዳችንን ከፍ አድርጎ ይመለከተናል። (ማቴዎስ 10:29-31ን አንብብ።) ድክመቶችህን ማወቅህ ትሑት በመሆን በይሖዋ እርዳታ ራስህን ለማስተካከል ቁርጥ ውሳኔ እንድታደርግ ሊያነሳሳህ ይገባል። (2 ቆሮ. 12:7-10) ሕመም ወይም የዕድሜ መግፋት አቅምህን ከገደበብህ ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦችን አውጣ፤ ሆኖም ተስፋ አትቁረጥ ወይም ፍቅርህ እንዲቀዘቅዝ አትፍቀድ።

አመስጋኝ እንድትሆን የሚገፋፉህ ምክንያቶች

17, 18. ቀድሞ የነበረህ ፍቅር እንዲጠናከር ማድረግህ ምን ጥቅሞች ያስገኝልሃል?

17 ቀድሞ የነበረህ ፍቅር እንዲጠናከር ማድረግህ በርካታ ጥቅሞች አሉት። ስለ አምላክ ያለህ እውቀት እንዲሁም በፍቅር ተነሳስቶ ለሚሰጥህ መመሪያ ያለህ አድናቆት እንዲያድግ ማድረግ ትችላለህ። (ምሳሌ 2:1-9⁠ን እና 3:5, 6ን አንብብ።) መዝሙራዊው የይሖዋን ፍርድ “መጠበቅ ወሮታ አለው” ብሏል። “የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤ አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።” ከዚህም በላይ “መንገዳቸው ነቀፋ የሌለበት፣ በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ የተባረኩ ናቸው።”—መዝ. 19:7, 11፤ 119:1

18 አመስጋኝ እንድትሆን የሚገፋፉህ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን እንደምትቀበል የታወቀ ነው። በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ሁኔታዎች መንስዔ ምን እንደሆነ ታውቃለህ። በዚህ ዘመን አምላክ ለሕዝቦቹ ከሚያደርግላቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሁሉ ጥቅም እያገኘህ ነው። ይሖዋ ወደ ዓለም አቀፋዊው ጉባኤ ስለሳበህ እንዲሁም ከምሥክሮቹ አንዱ የመሆን መብት ስለሰጠህ አመስጋኝ እንደምትሆን አያጠራጥርም። ስላገኘሃቸው በረከቶች አስብ! እነዚህን በረከቶች በዝርዝር ላስፍራቸው ብትል ብዙ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው። ስላገኘሃቸው በረከቶች በየጊዜው ማሰላሰልህ “ያለህን አጥብቀህ ያዝ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳሃል።—ራእይ 3:11

19. ከአምላክ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ከማሰላሰል በተጨማሪ በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነህ ለመኖር የሚረዱህ ምን ነገሮች አሉ?

19 ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እምነትህ እንዴት እንደተጠናከረ ማሰላሰልህ ያለህን አጥብቀህ ለመያዝ ከሚረዱህ ነገሮች አንዱ ነው። መንፈሳዊ ጤንነትህን ለመጠበቅ የሚረዱ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች በተደጋጋሚ ጊዜ በዚህ መጽሔት ላይ ወጥተዋል። ከእነዚህም መካከል ጸሎት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ተሳትፎ ማድረግ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ በቅንዓት መካፈል ይገኙበታል። እነዚህ ነገሮች የቀድሞ ፍቅርህ እንዳይቀዘቅዝ፣ እንዲታደስና እያደገ እንዲሄድ ይረዱሃል።—ኤፌ. 5:10፤ 1 ጴጥ. 3:15፤ ይሁዳ 20, 21

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• መጀመሪያ ላይ ይሖዋን እንድትወደው ያደረጉህ ምክንያቶች አሁንም የብርታት ምንጭ ሊሆኑልህ የሚችሉት እንዴት ነው?

• ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙህን ነገሮች መለስ ብለህ ማሰብህ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል?

• ለአምላክ ያለህን ፍቅር በተመለከተ ራስህን መመርመር የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እውነትን ስትማር የሳበህና የተማርከው ነገር እውነት መሆኑን እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልታስተካክላቸው የሚገቡ ነገሮች ይታዩሃል?