በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ሥልጣን ተቀበሉ

የይሖዋን ሥልጣን ተቀበሉ

የይሖዋን ሥልጣን ተቀበሉ

“እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም።”—1 ዮሐ. 5:3

1, 2. (ሀ)በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች ለሥልጣን መገዛት የሚለው ሐሳብ የማይዋጥላቸው ለምንድን ነው? (ለ) የሌሎችን ሥልጣን መቀበል የሚከብዳቸው ሰዎች፣ በእርግጥ የሚመሩት በራሳቸው አመለካከት ነው? አብራራ።

“ሥልጣን” የሚለውን ቃል በዛሬው ጊዜ ብዙዎች አይወዱትም። በርካታ ሰዎች ለሌላ ሰው መገዛት የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። የሌሎችን ሥልጣን መቀበል የሚከብዳቸው ሰዎች “ማንም ሰው ምን ማድረግ እንዳለብኝ እንዲነግረኝ አልፈልግም” የሚል አመለካከት አላቸው። ይሁን እንጂ እንዲህ የሚሉ ሰዎች በእርግጥ የሚመሩት በራሳቸው አመለካከት ነው? አይደለም! ከእነዚህ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ፣ ‘ይህን ዓለም የሚመስሉ’ ግለሰቦች የሚያወጧቸውን መሥፈርቶች ይከተላሉ። (ሮሜ 12:2) እነዚህ ሰዎች በራሳቸው አመለካከት ከመመራት ይልቅ ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደገለጸው “የጥፋት ባሪያዎች” ሆነዋል። (2 ጴጥ. 2:19) ‘የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትለው፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነው’ ለሰይጣን ዲያብሎስ እየታዘዙ ይኖራሉ።—ኤፌ. 2:2

2 አንድ ደራሲ እንዲህ በማለት በኩራት ተናግረዋል:- “ወላጆቼም ሆኑ አንድ ቄስ ወይም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ . . . አሊያም መጽሐፍ ቅዱስ ለእኔ ትክክል የሆነውን ነገር እንዲወስኑልኝ አልፈልግም።” በእርግጥ አንዳንዶች ሥልጣናቸውን አላግባብ ስለሚጠቀሙበት ታዛዥነት የማይገባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ‘ምንም ዓይነት መመሪያ አያስፈልገንም’ የሚለው አመለካከት መፍትሔ ይሆናል? የጋዜጦችን ርዕሰ አንቀጽ ስንቃኝ የምንመለከተው አሳዛኝ ሁኔታ መመሪያ እንደሚያስፈልገን የሚያሳይ ነው። የሰው ልጅ መመሪያ በጣም በሚያስፈልገው በዚህ ዘመን አብዛኞቹ ሰዎች እንዲህ ያለውን መመሪያ ለመቀበል እምብዛም ፈቃደኞች አለመሆናቸው በጣም ያሳዝናል።

ለሥልጣን ያለን አመለካከት

3. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ለሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት የማይገዙባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ያሳዩት እንዴት ነበር?

3 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለሥልጣን ከመገዛት ጋር በተያያዘ ከዓለም የተለየ አቋም አለን። እንዲህ ሲባል ግን አድርጉ የተባልነውን ሁሉ እናደርጋለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎችም እንኳ ለመገዛት ፈቃደኛ የማንሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖችም እንዲህ አድርገው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያት መስበካቸውን እንዲያቆሙ በታዘዙበት ወቅት ሊቀ ካህናቱንም ሆነ በሥልጣን ላይ ያሉ ሌሎች የሳንሄድሪን አባላትን በመፍራት መስበካቸውን አላቆሙም። ለሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት ለመታዘዝ ብለው ትክክለኛውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ አላሉም።—የሐዋርያት ሥራ 5:27-29ን አንብብ።

4. በርካታ የአምላክ አገልጋዮች በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት የሌለውን አካሄድ እንደተከተሉ የሚያሳዩት በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የሚገኙት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

4 በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ በርካታ የአምላክ አገልጋዮችም ተመሳሳይ አቋም ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ “የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን” እምቢ በማለት “ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል” መርጧል፤ ሙሴ ያደረገው ውሳኔ “የንጉሡን ቊጣ” ቢያስከትልበትም ከአቋሙ ወደኋላ አላለም። (ዕብ. 11:24, 25, 27) ዮሴፍ፣ የጲጥፋራ ሚስት ከእሷ ጋር እንዲተኛ በተደጋጋሚ ስትጠይቀው ይህች ሴት እሱን ለመበቀልም ሆነ ለመጉዳት ኃይል እንዳላት ቢያውቅም ያለችውን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። (ዘፍ. 39:7-9) ዳንኤል ‘በንጉሡ ምግብ ላለመርከስ’ ያደረገውን ውሳኔ የጃንደረቦቹ አለቃ ለመቀበል እንደሚከብደው ቢያውቅም በአቋሙ ጸንቷል። (ዳን. 1:8-14) እነዚህ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት በታሪክ ዘመናት ሁሉ የአምላክ ሕዝቦች፣ ትክክል የሆነውን ማድረጋቸው የሚያስከትለው መዘዝ ምንም ይሁን ምን ይህንን በማድረግ በአቋማቸው ጸንተዋል። በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ እንዲያደርጉ የታዘዙትን ሁሉ አልፈጸሙም፤ እኛም ብንሆን እንዲህ ማድረግ የለብንም።

5. ስለ ሥልጣን ያለን አመለካከት ዓለም ካለው አመለካከት የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

5 ይሁን እንጂ በድፍረት የምንወስደው አቋም እንደ ግትርነት መታየት የለበትም፤ እንዲሁም በወቅቱ ካለው የፖለቲካ ሥርዓት ጋር አለመስማማታቸውን ለመግለጽ ከሚያምጹ ሰዎች የተለየን ነን። እንዲህ ዓይነት አቋም የምንወስደው፣ ከማንኛውም ሰብዓዊ ሥልጣን ይልቅ የይሖዋን ሥልጣን ለመቀበል ስለቆረጥን ነው። ሰዎች የሚያወጡት ሕግ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጋጭበት ጊዜ ምን እንደምናደርግ መወሰን አይከብደንም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ሐዋርያት እኛም ከሰው ይልቅ ለአምላክ እንታዘዛለን።

6. ምንጊዜም ቢሆን የይሖዋን መመሪያዎች መታዘዝ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

6 የአምላክን ሥልጣን እንድንቀበል የረዳን ምንድን ነው? በምሳሌ 3:5, 6 ላይ ከሚገኘው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር የምንስማማ በመሆኑ ነው:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” አምላክ እንድናደርገው ያዘዘን ማንኛውም ነገር ምንጊዜም ጥቅሙ ለራሳችን እንደሆነ እናምናለን። (ዘዳግም 10:12, 13ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ስለ ራሱ ለእስራኤላውያን ሲናገር “የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” ብሏል። አክሎም “ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” በማለት ተናግሯል። (ኢሳ. 48:17, 18) በዚህ ጥቅስ ላይ በተገለጸው ሐሳብ እንታመናለን። ምንጊዜም ቢሆን የአምላክን መመሪያዎች መታዘዛችን እንደሚጠቅመን ፍጹም እምነት አለን።

7. በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ አንድ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ባይገባን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

7 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ መመሪያዎች የተሰጡበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባንረዳም እንኳ የይሖዋን ሥልጣን እንቀበላለን እንዲሁም እንታዘዘዋለን። እንዲህ የምናደርገው በጭፍን እምነት ስለምንመራ ሳይሆን በአምላክ ላይ ስለምንተማመን ነው። ይህም ይሖዋ ለእኛ የሚበጀንን እንደሚያውቅ ከልባችን እንደምንተማመን የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም አምላክን መታዘዛችን እሱን እንደምንወደው ያሳያል፤ ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና” ብሏል። (1 ዮሐ. 5:3) ይሁንና ከመታዘዝ ጋር በተያያዘ ችላ ልንለው የማይገባ ሌላም ነጥብ አለ።

የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠን

8. የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠናችን የይሖዋን ሥልጣን ከመቀበል ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

8 መጽሐፍ ቅዱስ ‘መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳችንን ማስለመድ’ ወይም የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠን እንዳለብን ይነግረናል። (ዕብ. 5:14) ስለዚህ ዓላማችን የአምላክን ሕግጋት ሳናስብባቸው እንዲሁ በዘልማድ መታዘዝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በይሖዋ መሥፈርቶች መሠረት ‘መልካሙን ከክፉው የመለየት’ ችሎታ ማዳበር እንፈልጋለን። የይሖዋ መንገዶች ጥበብ የተንጸባረቀባቸው መሆናቸውን መገንዘብ እንሻለን፤ እንዲህ ካደረግን እንደ መዝሙራዊው “ሕግህም በልቤ ውስጥ አለ” ማለት እንችላለን።—መዝ. 40:8

9. ሕሊናችን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር እንዲስማማ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 እኛም እንደ መዝሙራዊው የአምላክ ሕግጋት ጠቃሚ መሆናቸውን ማስተዋል ከፈለግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባነበብናቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ለአብነት ያህል፣ ስለ አንድ የይሖዋ መመሪያ ስናነብ ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን:- ‘ይህ ትእዛዝ ወይም መሠረታዊ ሥርዓት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው እንድል የሚያደርገኝ ምንድን ነው? መታዘዜስ የሚጠቅመኝ እንዴት ነው? በዚህ ረገድ የአምላክን ምክር ችላ ያሉ ሰዎች ምን ችግሮች አጋጥመዋቸዋል?’ በዚህ መንገድ ሕሊናችንን ከይሖዋ መንገዶች ጋር እንዲስማማ ካደረግነው ከእሱ ፈቃድ ጋር የማይጋጩ ውሳኔዎች ማድረግ እንችላለን። ‘የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ማስተዋል’ እንዲሁም እሱን መታዘዝ እንችላለን። (ኤፌ. 5:17) ይህን ማድረግ ግን ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም።

ሰይጣን የአምላክን ሥልጣን ለማዳከም ይፈልጋል

10. ሰይጣን የአምላክን ሥልጣን ለማዳከም የሚጠቀምበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

10 ሰይጣን ከጥንት ጀምሮ የአምላክን ሥልጣን ለማዳከም ሲጥር ቆይቷል። እሱ የሚያስፋፋው በራስ የመመራት መንፈስ በበርካታ መንገዶች ይንጸባረቃል። አምላክ ላቋቋመው የጋብቻ ዝግጅት አክብሮት የማጣትን ዝንባሌ እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። አንዳንዶች ሳይጋቡ አብረው ለመኖር ሲመርጡ ሌሎች ደግሞ ጋብቻቸውን ለማፍረስ የሚያስችሏቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ። እነዚህ ሰዎች፣ “በአንድ ሰው ብቻ ተወስኖ መኖር ለሁለቱም ጾታዎች የማይቻል ነገር ነው” በማለት ከተናገረችው አንዲት ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ጋር ይስማማሉ። ይህቺ ሴት አክላም:- “ለትዳር ጓደኛው ታማኝ የሆነ ወይም መሆን የሚፈልግ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም” ብላለች። በተመሳሳይም አንድ ታዋቂ የፊልም ተዋናይ “በሕይወታችን ሙሉ ከአንድ ሰው ጋር ብቻ መኖር ተፈጥሯችን አይመስለኝም” ብሏል። እኛም ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል:- ‘ከጋብቻ ጋር በተያያዘ የይሖዋን ሥልጣን አከብራለሁ? ወይስ ልል የሆነው የዚህ ዓለም አመለካከት በአስተሳሰቤ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል?’

11, 12. (ሀ) ወጣቶች የይሖዋን ሥልጣን መቀበል ከባድ የሚሆንባቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የይሖዋን ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ችላ ማለት የሚያስከትለውን አሳዛኝ ውጤት የሚያሳይ ተሞክሮ ተናገር።

11 በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የምትገኝ ወጣት ከሆንክ ደግሞ ሰይጣን የይሖዋን ሥልጣን ለማዳከም በሚያደርገው ጥረት ዋነኛ ዒላማው ያደርግህ ይሆናል። ‘የወጣትነት ክፉ ምኞት’ እና የእኩዮችህ ተጽዕኖ የአምላክ ሕግጋት ሸክም እንደሆኑ እንዲሰማህ ሊያደርጉህ ይችላሉ። (2 ጢሞ. 2:22) እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳታዳብር ተጠንቀቅ። አምላክ ያወጣቸው መሥፈርቶች ጥበብ ያዘሉ መሆናቸውን ለመረዳት ጥረት አድርግ። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ከዝሙት ሽሹ” የሚል ምክር ይሰጣል። (1 ቆሮ. 6:18) እስቲ እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይህ ትእዛዝ ጥበብ ያዘለ ነው የምለው ለምንድን ነው? በዚህ ረገድ ታዛዥ መሆኔ የሚጠቅመኝ እንዴት ነው?’ የአምላክን ምክር ችላ ማለታቸው ከባድ መዘዝ ያስከተለባቸው አንዳንድ ሰዎች ታውቅ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች በአሁኑ ወቅት እውነተኛ ደስታ አላቸው? በይሖዋ ድርጅት ውስጥ እያሉ ከነበራቸው ይልቅ አሁን የተሻለ ሕይወት እየመሩ ነው? ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ያላስተዋሉትን ደስታ የሚያስገኝ ቁልፍ ማወቅ ችለዋል?—ኢሳይያስ 65:14ን አንብብ።

12 ሻረን የተባለች አንዲት ክርስቲያን ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰጠችውን ሐሳብ እንመልከት:- “የይሖዋን ሕግ ባለመታዘዜ ምክንያት ኤድስ በተባለው መድኃኒት የሌለው በሽታ ተይዣለሁ። ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸውን አስደሳች ዓመታት ብዙውን ጊዜ ወደኋላ መለስ ብዬ አስታውሳለሁ።” ይህች እህት የይሖዋን ሕግጋት አለመታዘዟ ሞኝነት እንደሆነና ትእዛዛቱን በጥልቅ ልታከብራቸው ይገባ እንደነበረ ተገንዝባለች። የይሖዋን ሕግጋት መታዘዛችን ጥበቃ ይሆንልናል። ሻረን ከላይ የሰፈረውን ሐሳብ ከጻፈች ከሰባት ሳምንታት በኋላ በሞት አንቀላፍታለች። ይህች እህት ያጋጠማት አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚያሳየው ሰይጣን የዚህ ክፉ ሥርዓት ክፍል ለሚሆኑ ሰዎች የሚሰጣቸው ምንም መልካም ነገር የለም። ሰይጣን ‘የሐሰት አባት’ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ተስፋዎችን ይሰጣል፤ ሆኖም ለሔዋን የገባውን ቃል እንዳልጠበቀ ሁሉ ዛሬም ከሚሰጣቸው ተስፋዎች አንዱንም አይፈጽምም። (ዮሐ. 8:44) በእርግጥም ምንጊዜም ቢሆን የይሖዋን ሥልጣን መቀበል ከሁሉ የተሻለ አካሄድ ነው።

በራስ የመመራት መንፈስ እንዳይኖራችሁ ተጠንቀቁ

13. በራስ የመመራት መንፈስ እንዳይኖረን መጠንቀቅ የሚገባን በምን ረገድ ነው?

13 የይሖዋን ሥልጣን ለመቀበል በምንጥርበት ወቅት በራስ የመመራት መንፈስ እንዳይኖረን መጠንቀቅ ይኖርብናል። የትዕቢት ዝንባሌ፣ የማንንም መመሪያ መቀበል እንደማያስፈልገን እንዲሰማን ሊያደርገን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያሉት በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ወንድሞች የሚሰጡንን ምክር ለመቀበል ፈቃደኞች ላንሆን እንችላለን። አምላክ፣ ታማኝና ልባም ባሪያ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያቀርብ ዝግጅት አድርጓል። (ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሕዝቦቹ የሚያስፈልጋቸውን የሚያቀርበው በዚህ መንገድ እንደሆነ በትሕትና መቀበል ይኖርብናል። በዚህ ረገድ የታማኞቹን ሐዋርያት ምሳሌ እንከተል። አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ቅር ተሰኝተው ኢየሱስን መከተል ባቆሙ ጊዜ ክርስቶስ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” በማለት ሐዋርያቱን ጠይቋቸው ነበር። ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት መልሶለታል።—ዮሐ. 6:66-68

14, 15. መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ምክር በትሕትና መቀበል ያለብን ለምንድን ነው?

14 የይሖዋን ሥልጣን መቀበል በቃሉ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጠን ተግባራዊ ማድረግንም ይጨምራል። ለምሳሌ፣ ታማኝና ልባም ባሪያ “እንንቃ፤ ራሳችንንም እንግዛ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እንድናደርግ ሲያሳስበን ቆይቷል። (1 ተሰ. 5:6) በርካታ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ [እንዲሁም] ገንዘብን የሚወዱ” በሆኑበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን ከላይ ያለው ምክር በጣም አስፈላጊ ነው። (2 ጢሞ. 3:1, 2) በብዙዎች ዘንድ ተስፋፍቶ የሚታየው ይህ ዓይነቱ አካሄድ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል? አዎን፣ መንፈሳዊ ያልሆኑ ግቦችን መከታተል በመንፈሳዊ እንድናንቀላፋ ወይም ቁሳዊ ሀብትን በማሳደድ ላይ እንድናተኩር ሊያደርገን ይችላል። (ሉቃስ 12:16-21) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር መቀበልና በሰይጣን ዓለም ውስጥ ተስፋፍቶ ከሚታየው የራስ ወዳድነት አኗኗር መራቅ ምንኛ ጥበብ ነው!—1 ዮሐ. 2:16

15 ታማኝና ልባም ባሪያ የሚያዘጋጀው መንፈሳዊ ምግብ ለጉባኤዎች የሚደርሰው በተሾሙ ሽማግሌዎች አማካኝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት መክሮናል:- “ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጉዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም።” (ዕብ. 13:17) ይህ ሲባል የጉባኤ ሽማግሌዎች ምንም ስሕተት አይሠሩም ማለት ነው? በፍጹም አይደለም! አምላክ፣ ከማናችንም ይበልጥ ጉድለቶቻቸው ቁልጭ ብለው ይታዩታል። ያም ሆኖ እንድንገዛላቸው ይጠብቅብናል። ሽማግሌዎች ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ከእነሱ ጋር መተባበራችን የይሖዋን ሥልጣን እንደምንቀበል ያሳያል።

የትሕትና አስፈላጊነት

16. የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ለሆነው ለኢየሱስ አክብሮት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 እውነተኛው የቤተ ክርስቲያን ራስ ኢየሱስ መሆኑን ምንጊዜም ማስታወስ አለብን። (ቈላ. 1:18) በጉባኤ ውስጥ የተሾሙትን ሽማግሌዎች ‘እጅግ በማክበር’ ለሚሰጡን መመሪያ በትሕትና እንድንገዛ የሚገፋፋን አንዱ ምክንያት ይህ ነው። (1 ተሰ. 5:12, 13) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች የራሳቸውን አመለካከት ሳይሆን የአምላክን ቃል ለጉባኤው በማስተማር እነሱም ተገዢ መሆናቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። የግላቸውን አመለካከት ለማስፋፋት ሲሉ ‘ከተጻፈው ማለፍ’ አይኖርባቸውም።—1 ቆሮ. 4:6

17. የራስን ክብር መሻት አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

17 ሁሉም የጉባኤ አባላት የራስን ክብር መሻት አደገኛ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። (ምሳሌ 25:27) ሐዋርያው ዮሐንስ የጠቀሰው አንድ ደቀ መዝሙር እንዲህ ያለው መንፈስ ወጥመድ ሆኖበት ነበር። ዮሐንስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “መሪ መሆን የሚወደው ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም። ስለዚህ እኔ ከመጣሁ እርሱ በክፉ ቃላት ስማችንን ለማጥፋት የሚያደርገውን ሁሉ ይፋ አወጣለሁ።” (3 ዮሐ. 9, 10) ይህ ጥቅስ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ለእኛም ትምህርት ይዟል። የራስን ክብር የመሻት መንፈስ በውስጣችን እንዳያቆጠቁጥ ለመከላከል እንድንጥር የሚገፋፋን በቂ ምክንያት አለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ትዕቢት ጥፋትን፣ የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” በማለት ይናገራል። የአምላክን ሥልጣን የሚቀበሉ ሁሉ ትዕቢትን ማስወገድ አለባቸው፤ ይህን አለማድረግ ውርደትን ያስከትላል።—ምሳሌ 11:2፤ 16:18

18. የይሖዋን ሥልጣን ለመቀበል ምን ሊረዳን ይችላል?

18 በእርግጥም፣ በዓለም ላይ ከሚታየው በራስ የመመራት መንፈስ የመራቅና የይሖዋን ሥልጣን የመቀበል ግብ ሊኖርህ ይገባል። ይሖዋን ለማገልገል ባገኘኸው ታላቅ መብት ላይ በየጊዜው አሰላስል። በአምላክ ሕዝቦች መካከል መሆንህ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንደሳበህ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ዮሐ. 6:44) ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና በፍጹም አቅልለህ አትመልከተው። በሁሉም የሕይወትህ ዘርፎች፣ በራስ ከመመራት መንፈስ በመራቅ የይሖዋን ሥልጣን እንደምትቀበል አሳይ።

ታስታውሳለህ?

• የይሖዋን ሥልጣን መቀበል የትኞቹን ነገሮች ይጨምራል?

• የማስተዋል ችሎታችንን ማሠልጠናችን የይሖዋን ሥልጣን ከመቀበል ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

• ሰይጣን የአምላክን ሥልጣን ለማዳከም የሚጥረው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• የይሖዋን ሥልጣን በመቀበል ረገድ ትሕትና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል”

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምንጊዜም ቢሆን አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች መከተል የጥበብ አካሄድ ነው