በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድንቅ ብልሃት

ድንቅ ብልሃት

ድንቅ ብልሃት

በመካከለኛው አፍሪካ የሚኖሩ ሦስት ወጣቶች ከሚኖሩበት ቦታ ራቅ ብሎ በሚገኝ አካባቢ በሚደረግ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ፈለጉ። ታዲያ ወደዚያ ቦታ መድረስ የሚችሉት እንዴት ነው? ስብሰባው የሚደረገው እነሱ ካሉበት አካባቢ 90 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ሲሆን መንገዱም ኮረኮንችና አቧራማ ነው፤ በዚያ ላይ ምንም መጓጓዣ አልነበራቸውም። በመሆኑም እነዚህ ወንድሞች ሦስት ብስክሌቶችን ለመዋስ ወሰኑ፤ ይሁን እንጂ ለዚህ ጉዞ የሚሆኑ ብስክሌቶች ማግኘት አልቻሉም።

በአካባቢያቸው በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ችግራቸውን ከተመለከተ በኋላ የራሱን ብስክሌት ሰጣቸው፤ ብስክሌቱ ያረጀ ቢሆንም ይሠራ ነበር። ይህ ወንድም ከዚህ በፊት እሱና ሌሎች ወንድሞች ወደ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ለመሄድ ምን እንዳደረጉ ነገራቸው። ሽማግሌው ሦስቱም በአንድ ብስክሌት እንዲጠቀሙ ሐሳብ አቀረበላቸው። ቀላል ሆኖም ጥሩ ቅንጅት የሚጠይቅ የመፍትሔ ሐሳብ ነበር። ሦስት ሰዎች በአንድ ብስክሌት ተጠቅመው እንዴት መጓዝ ይችላሉ?

እነዚህ ወጣት ወንድሞች በጠራራ ፀሐይ ላለመጓዝ ሲሉ በማለዳ ተገናኙና ጓዛቸውን በብስክሌቱ ላይ ጫኑ። አንደኛው ወንድም ብስክሌቱን እየነዳ ሲሄድ ሁለቱ ደግሞ ቶሎ ቶሎ እየተራመዱ ይከተሉት ጀመር። በብስክሌት የሚጓዘው ወንድም 500 ሜትር ያህል ከተጓዘ በኋላ ዕቃ የጫነውን ብስክሌት አንድ ዛፍ ሥር አስደግፎ አቆመው። እርግጥ ሌቦች እንዳይሰርቁት ብስክሌቱን ያቆመው ሁለቱ ወንድሞች ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ነው። ከዚያም ብስክሌቱን ሲነዳ የነበረው ወንድም ጉዞውን በእግሩ ቀጠለ።

ሁለቱ ወንድሞች ብስክሌቱ ጋር ሲደርሱ አንደኛው ብስክሌቱን መንዳት ጀመረ፤ ሌላኛው ወንድም ደግሞ ተራው እስኪደርስ ድረስ ቀጣዩን 500 ሜትር ያህል በእግር መጓዙን ቀጠለ። እነዚህ ሦስት ወንድሞች ጥሩ እቅድ በማውጣትና ቆራጥ በመሆን በእግር ሊጓዙ የነበረውን 90 ኪሎ ሜትር ወደ 60 ኪሎ ሜትር ገደማ መቀነስ ችለዋል። ያደረጉት ጥረትም የሚያስቆጭ አልነበረም። በአውራጃ ስብሰባው ላይ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር የተገናኙ ሲሆን በዚያ በቀረበው መንፈሳዊ ግብዣም ተደስተዋል። (ዘዳ. 31:12) አንተስ በዚህ ዓመት በአካባቢህ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የምትችለውን ሁሉ ታደርጋለህ?