በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ድክመቶች ቢኖሩንም ብርቱዎች መሆን

ድክመቶች ቢኖሩንም ብርቱዎች መሆን

ድክመቶች ቢኖሩንም ብርቱዎች መሆን

አንዳንድ ጊዜ ድክመቶችህ ከአቅምህ በላይ ሊሆኑብህ ይችላሉ። እንደ መዥገር ተጣብቀው እንደማይለቁህ ይሰማህ ይሆናል። እነዚህን ድክመቶችህን መቼም ቢሆን ማሸነፍ እንደማትችል ታስብ ይሆናል፤ ወይም ራስህን ከሌሎች ጋር በማወዳደርና ሌሎች ከአንተ እንደሚሻሉ በመቁጠር ከንቱ እንደሆንክ ልታስብ ትችላለህ። በሌላ በኩል ደግሞ ኃይልህን ከሚያሟጥጥና ሕይወት እንዲያስጠላህ ከሚያደርግ አቅም የሚያሳጣ በሽታ ጋር እየታገልህ ይሆናል። እንድትደክም ያደረገህ ነገር ምንም ይሁን ምን ከዚህ ሁኔታ መገላገል የምትችልበት መንገድ እንደሌለ ታስብ ይሆናል። “ምነው መቃብር ውስጥ በሰወርኸኝ! ቍጣህም እስከሚያልፍ በሸሸግኸኝ! ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ፣ ከዚያ በኋላ ባስታወስኸኝ!” በማለት ለአምላክ እንደተናገረው እንደ ኢዮብ ሊሰማህ ይችላል።—ኢዮብ 14:13

እንዲህ ካለው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ መገላገል የምትችለው እንዴት ነው? ችግሮችህን መርሳት ቀላል ባይሆንም ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንዲህ ማድረግ ያስፈልግሃል። ለምሳሌ፣ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዩ ለኢዮብ ባቀረባቸው በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል ትችላለህ:- “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? በእርግጥ የምታስተውል ከሆንህ፣ ንገረኝ። ካወቅህ፣ መጠኗን ለይቶ ማን ወሰነ? በላይዋስ መለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው?” (ኢዮብ 38:4, 5) እነዚህ ጥያቄዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው ስናሰላስል ይሖዋ የላቀ ጥበብና ኃይል ምንጭ እንደሆነ አምነን ለመቀበል እንገፋፋለን። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ እንዲቀጥል የፈቀደበት በቂ ምክንያት አለው።

‘የሥጋ መውጊያ’

አንድ ሌላ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ደግሞ ‘የሥጋ መውጊያ’ የሆነበትን የማያቋርጥ ችግር እንዲያስወግድለት ይሖዋን ጠይቆት ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ችግር እንዲወገድለት አምላክን ሦስት ጊዜ ለምኖታል። የጳውሎስ ችግር ምንም ይሁን ምን እንደ እሾህ እረፍት ይነሳው ስለነበር በይሖዋ አገልግሎት የሚያገኘውን ደስታ እንዲያጣ አድርጎት ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ይህንን ችግር፣ ማቆሚያ ከሌለው ሥቃይ ወይም ዘወትር በጥፊ ከመመታት ጋር አመሳስሎታል። ይሖዋ ለጳውሎስ ምን መልስ ሰጠው? “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” ብሎታል። ይሖዋ የጳውሎስን የሥጋ መውጊያ አላስወገደለትም። ጳውሎስ ከዚህ ችግር ጋር መታገል የነበረበት ቢሆንም “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” ብሏል። (2 ቆሮ. 12:7-10) ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር?

የጳውሎስ ችግር በተዓምራዊ ሁኔታ አልተወገደም። ያም ቢሆን፣ ሐዋርያው የነበረበት ችግር በይሖዋ አገልግሎት አስደናቂ ሥራዎችን እንዳያከናውን አላገደውም። ጳውሎስ፣ ይሖዋ በሚሰጠው ድጋፍ ይተማመን የነበረ ከመሆኑም ባሻገር የእሱን እርዳታ አዘውትሮ ይጠይቅ ነበር። (ፊልጵ. 4:6, 7) ጳውሎስ በምድራዊ ሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ “መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫውን ጨርሻለሁ፤ ሃይማኖትንም ጠብቄአለሁ” በማለት መናገር ችሏል።—2 ጢሞ. 4:7

ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ጉድለቶችና ችግሮች ቢኖሩባቸውም ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም በእነሱ ይጠቀማል፤ በመሆኑም ክብር ሊሰጠው የሚገባው እሱ ነው። ይሖዋ፣ እነዚህ ሰዎች ያሉባቸውን ችግሮች እንዲቋቋሙና ደስተኛ ሆነው እሱን ማገልገል እንዲችሉ የሚያስፈልጋቸውን መመሪያና ጥበብ ይሰጣቸዋል። አዎን፣ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ድክመቶች ቢኖሩባቸውም አምላክ በእነሱ ተጠቅሞ ታላላቅ ሥራዎችን ሊያከናውን ይችላል።

ጳውሎስ፣ አምላክ የሥጋ መውጊያውን ያላስወገደለት ‘እንዳይታበይ’ ሲል እንደሆነ ገልጿል። (2 ቆሮ. 12:7) የጳውሎስ “መውጊያ” አቅሙ ውስን እንደሆነ ያስታውሰው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ትሑት እንዲሆን ረድቶታል። ይህም “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ይዋረዳል፣ ራሱን የሚያዋርድ ግን ይከበራል” ከሚለው የኢየሱስ ትምህርት ጋር ይስማማል። (ማቴ. 23:12) ችግሮች የአምላክ አገልጋዮች ትሕትናን እንዲማሩ የሚያደርጓቸው ከመሆኑም ሌላ በታማኝነት ለመጽናት በይሖዋ መታመን እንደሚያስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ ይረዷቸዋል። በዚህ መንገድ እንደ ሐዋርያው እነሱም ‘በይሖዋ መመካት’ ይችላሉ።—1 ቆሮ. 1:31

ስውር ድክመቶች

አንዳንዶች እነሱ ራሳቸው የማያስተውሉት ድክመት ሊኖራቸው ይችላል፤ አሊያም ድክመት እንዳለባቸው መቀበል አይፈልጉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው በችሎታው በመመካት ከሚገባው በላይ በራሱ የመተማመን ችግር ይኖርበት ይሆናል። (1 ቆሮ. 10:12) ፍጽምና በጎደላቸው የሰው ልጆች ላይ ብዙውን ጊዜ የሚስተዋለው ሌላው ድክመት ደግሞ ከፍ ብሎ የመታየት ፍላጎት ነው።

የንጉሥ ዳዊት የጦር አዛዥ የሆነው ኢዮአብ ደፋር፣ ቆራጥና ችግሮችን የመፍታት ችሎታ ያለው ሰው ነበር። ሆኖም ትዕቢተኛና ከፍ ብሎ የመታየት ፍላጎት የነበረው ሰው መሆኑን የሚጠቁሙ ከባድ ጥፋቶችን ሠርቷል። ሁለት የጦር አዛዦችን በጭካኔ ገድሏል። መጀመሪያ በበቀል ስሜት ተነሳስቶ አበኔርን ገድሎታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የአክስቱ ልጅ የነበረውን አሜሳይን የሚስመው መስሎ በቀኝ እጁ ጢሙን በመያዝ በግራ እጁ የያዘውን ሰይፍ ሆዱ ላይ ሻጠበት። (2 ሳሙ. 17:25፤ 20:8-10) አሜሳይ በኢዮአብ ምትክ የጦር አዛዥ ተደርጎ ስለነበር ኢዮአብ በዚህ መንገድ ተፎካካሪውን አስወገደው፤ እንዲህ ያደረገው በድጋሚ በጦር አዛዥነት እንደሚሾም አስቦ ይሆናል። ኢዮአብ ራስ ወዳድነትን ጨምሮ ሌሎች ዝንባሌዎቹን እንዳልተቆጣጠረ ከዚህ መመልከት ይቻላል። የጭካኔ ድርጊት ከመፈጸሙም በላይ እንደተጸጸተ የሚያሳይ ምንም ነገር አላደረገም። ንጉሥ ዳዊት ወደ ሕይወቱ መገባደጃ ሲቃረብ ሰሎሞን፣ ኢዮአብን ለፈጸማቸው ክፉ ድርጊቶች እንዲቀጣው ነግሮታል።—1 ነገ. 2:5, 6, 29-35

እኛም በመጥፎ ምኞቶች እንዳንሸነፍ መጠንቀቅ እንዳለብን ግልጽ ነው። ድክመቶቻችንን ማሸነፍ እንችላለን። መጀመሪያ ግን ድክመቶቻችንን ለይተን ማወቅና ድክመቶች እንዳሉብን አምነን መቀበል ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ እርምጃ መውሰድ እንችላለን። በዚህ ረገድ ይሖዋ እንዲረዳን አዘውትረን መጸለይ እንዲሁም ምኞቶቻችንን ለመቆጣጠር የሚያስችሉንን መንገዶች ለማግኘት ቃሉን በትጋት ማጥናት እንችላለን። (ዕብ. 4:12) ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ ያልተቋረጠ ጥረት ማድረግ ቢኖርብንም ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ምናልባትም የምናደርገውን ትግል ፍጽምና ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ መቀጠል ይኖርብን ይሆናል። ጳውሎስ “ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁ” ብሎ መጻፉ ይህ እውነት መሆኑን ያሳያል። ይሁን እንጂ ሁላችንም እንደምናውቀው ጳውሎስ ድርጊቶቹን መቆጣጠር እንደማይችል በማሰብ ለድክመቶቹ እጅ አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በሚሰጠው እርዳታ በመታመን ድክመቶቹን ለማሸነፍ ትግል ማድረጉን ቀጥሏል። (ሮሜ 7:15-25) ጳውሎስ በሌላ ጥቅስ ላይ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ ውድቅ ሆኜ እንዳልቀር፣ ሰውነቴን እየጐሰምሁ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” ብሏል።—1 ቆሮ. 9:27

የሰው ልጆች ለድክመቶቻቸው ሰበብ መፍጠር ይቀናቸዋል። የይሖዋ ዓይነት አመለካከት በማዳበር እንዲሁም ጳውሎስ “ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ፤ በጎ ከሆነው ነገር ጋር ተቈራኙ” በማለት ለክርስቲያኖች የሰጠውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ይህን ችግር ማስወገድ እንችላለን። (ሮሜ 12:9) ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል ሐቀኛና ቆራጥ መሆን እንዲሁም ራሳችንን መገሠጽ ያስፈልገናል። ዳዊት፣ “ልቤንና ውስጤን መርምር” በማለት ይሖዋን ጠይቆ ነበር። (መዝ. 26:2) አምላክ ውስጣዊ ዝንባሌያችንን በትክክል መመርመርና እርዳታ ሲያስፈልገን መስጠት እንደሚችል ዳዊት ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት የሚሰጠንን መመሪያ ከተከተልን ድክመቶቻችንን ቀስ በቀስ ማሸነፍ እንችላለን።

አንዳንዶች ያሉባቸውን ችግሮች ለብቻቸው መወጣት እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆናል። የጉባኤ ሽማግሌዎች ፍቅራዊ እርዳታና ማበረታቻ ሊሰጧቸው እንደሚችሉ ምንም ጥርጥር የለውም። (ኢሳ. 32:1, 2) ያም ሆኖ በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆናችን የጥበብ አካሄድ ነው። አንዳንድ ችግሮች በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ማግኘት አይችሉም። ያም ቢሆን በርካታ ሰዎች ችግሮቻቸውን ተቋቁመው መኖርን ተምረዋል፤ ይህ ደግሞ በሕይወታቸው እንዲረኩ ረድቷቸዋል።

ይሖዋ እንደሚደግፈን የሚያሳይ ማረጋገጫ

በዚህ አስቸጋሪ ዘመን ምንም ዓይነት ችግሮች ቢያጋጥሙን ይሖዋ መመሪያ እንደሚሰጠንና እንደሚንከባከበን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያሳስበናል:- “እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥ. 5:6, 7

ለበርካታ ዓመታት በቤቴል ስታገለግል የቆየችው ካቲ፣ ባለቤቷ ኦልዛይመርስ በተባለው በሽታ መያዙን ስታውቅ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡትን ፈታኝ ሁኔታዎች መቋቋም እንደማትችል ተሰምቷት ነበር። ይሖዋ፣ ጥበብና ውስጣዊ ጥንካሬ እንዲሰጣት በየዕለቱ መጸለይ አስፈልጓት ነበር። የባለቤቷ ጤንነት ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ ሲሄድ አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞች ስለ በሽታው ለማወቅ ጥረት ያደርጉ፣ አሳቢ የሆኑ እህቶች ደግሞ ያበረታቷት ነበር። ይሖዋ ካቲን ለማበርታት ከተጠቀመባቸው መንገዶች መካከል የእነዚህ ክርስቲያኖች እርዳታ የሚጠቀስ ነው፤ ካቲም ባለቤቷ ከ11 ዓመታት በኋላ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ልትንከባከበው ችላለች። ካቲ እንዲህ ብላለች:- “ይሖዋን ላደረገልኝ እርዳታ ሁሉ እያነባሁ ከልቤ አመሰገንኩት፤ በእሱ እርዳታ ባለቤቴን እየተንከባከብኩ መቀጠል ችያለሁ። በጣም እንደዛልኩ እየተሰማኝም እንኳ ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት የሚጠበቅብኝን እያደረግኩ መቀጠል እንደሚቻል አላውቅም ነበር!”

ስውር ድክመቶችን ለማሸነፍ የሚያስችል እርዳታ

የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማቸው ሰዎች፣ በተጨነቁበት ወቅት እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሖዋ እንደማይሰማ ያስቡ ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከቤርሳቤህ ጋር ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ በኋላ የጸጸት ስሜት ያደረበት ዳዊት በተናገረው ሐሳብ ላይ ማሰላሰላቸው ጠቃሚ ነው፤ ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም” ብሎ ነበር። (መዝ. 51:17) ይህ የአምላክ አገልጋይ ከልቡ ንስሐ ገብቶ ነበር፤ በመሆኑም ወደ አምላክ በጸሎት መቅረብ እንደሚችል እንዲሁም አምላክ ይቅር እንደሚለው እርግጠኛ ነበር። ኢየሱስም እንደ ይሖዋ አሳቢነት አሳይቷል። የወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ “የተቀጠቀጠውን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም” የሚለው የኢሳይያስ ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ ገልጿል። (ማቴ. 12:20፤ ኢሳ. 42:3) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ዝቅ ተደርገው ለሚታዩና ለተጨቆኑ ሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። በምሳሌያዊ አነጋገር ሊጠፋ እንደተቃረበ የጧፍ ክር የሆኑ ሰዎችን የመኖር ተስፋ አላጨለመባቸውም። ከዚህ ይልቅ በችግር ለሚሠቃዩ ሰዎች ርኅራኄ በማሳየት የመኖር ተስፋቸው እንዲለመልም አድርጓል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እንደዚህ ዓይነት ሰው ነበር። ኢየሱስ አሁንም ቢሆን እንዳልተለወጠና ድክመቶችህን እንደሚረዳልህ ታምናለህ? በዕብራውያን 4:15 ላይ ያለውን ክርስቶስ ‘በድካማችን እንደሚራራልን’ የሚገልጸውን ሐሳብ ልብ በል።

ጳውሎስ ስለ ‘ሥጋው መውጊያ’ ሲጽፍ ክርስቶስ የሚሰጠው ኃይል በእሱ ላይ እንደ ድንኳን ‘እንደሚያድር’ ገልጾ ነበር። (2 ቆሮ. 12:7-9) በድንኳን ውስጥ ያለ ሰው አስቸጋሪ ከሆነ የአየር ሁኔታ ከለላ እንደሚያገኝ ሁሉ ጳውሎስም፣ አምላክ በክርስቶስ በኩል ጥበቃ እንደሚያደርግለት ተሰምቶት ነበር። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ድክመቶቻችንና የሚያጋጥሙን ችግሮች እንዲያሸንፉን መፍቀድ የለብንም። በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን መቀጠል እንድንችል ይሖዋ በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል በኩል በሚያቀርብልን ዝግጅቶች በሙሉ መጠቀም ይኖርብናል። አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን በኋላ ይሖዋ አካሄዳችንን እንደሚመራልን ሙሉ በሙሉ በመተማመን እሱን መጠበቅ አለብን። የአምላክ ኃይል ድክመቶቻችንን እንድናሸንፍ እንዴት እንደረዳን ስንመለከት እኛም እንደ ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” ማለት እንችላለን።—2 ቆሮ. 12:10

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ አገልግሎቱን ለማከናወን የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት አዘውትሮ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጉሥ ዳዊት ኢዮአብን የሠራዊቱ አዛዥ እንዲሆን ሾሞት ነበር

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮአብ ተፎካካሪውን አሜሳይን ገድሎታል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አፍቃሪ የሆኑት ሽማግሌዎች ችግሮቻችንን ለመቋቋም የሚረዳን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ይሰጡናል