በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የቆሮንቶስ ጉባኤ መንፈሳዊ ደኅንነት በጣም አሳስቦታል። በዚያ ባሉት ወንድሞች መካከል ክርክር እንዳለ ሰምቶ ነበር። በጉባኤው ውስጥ የሥነ ምግባር ብልግና ቢፈጸምም ጉዳዩ በቸልታ ታልፏል። ከዚህም በተጨማሪ በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ያሏቸውን ጥያቄዎች ለጳውሎስ ጽፈውለት ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ በ55 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በኤፌሶን ከተማ እያለ ለቆሮንቶስ ጉባኤ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ጻፈ።

ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላ እንደተጻፈ የሚገመተው ሁለተኛው ደብዳቤ ከመጀመሪያው የቀጠለ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤው ውጪ የነበሩት ሁኔታዎች በብዙ መንገዶች እኛ ካለንበት ዘመን ጋር የሚመሳሰሉ በመሆናቸው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ጉባኤ የላካቸው ደብዳቤዎች የያዙት መልእክት በእጅጉ ይጠቅመናል።—ዕብ. 4:12

‘ንቁ፤ ጽኑ፤ ጠንክሩ’

(1 ቆሮ. 1:1 እስከ 16:24)

ጳውሎስ ‘እርስ በርሳችሁ ተስማሙ’ የሚል ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 1:10) ክርስቲያናዊ ባሕርያት የሚታነጹበት ‘ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ መሠረት የለም።’ (1 ቆሮ. 3:11-13) ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ የሚገኘውን አመንዝራ የሆነ ግለሰብ በተመለከተ “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት” ብሏል። (1 ቆሮ. 5:13) “ሰውነት ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም” በማለት ተናግሯል።—1 ቆሮ. 6:13

ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ‘ለጻፉለት ጕዳይ’ ምላሽ በሰጠበት ወቅት ጋብቻንና ነጠላነትን በተመለከተ ግሩም ምክር ለግሷል። (1 ቆሮ. 7:1) ሐዋርያው ስለ ክርስቲያናዊው የራስነት ሥልጣን፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሥርዓታማ ስለመሆን እንዲሁም የትንሣኤ ተስፋ እርግጠኛ ስለመሆኑ ከጻፈ በኋላ “ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።—1 ቆሮ. 16:13

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

1:21—ይሖዋ የሚያምኑ ሰዎችን ለማዳን ሲል ‘ሞኝነትን’ ይጠቀማል? አይጠቀምም። ሆኖም “ዓለም በገዛ ጥበብዋ እግዚአብሔርን ማወቅ ስለ ተሳናት” አምላክ ሰዎችን ለማዳን የሚጠቀምበት መንገድ በዓለም ዘንድ እንደ ሞኝነት ይቆጠራል።—ዮሐ. 17:25

5:5—ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክፉ ድርጊት የፈጸመው ሰው “ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ [የጉባኤው መንፈስ፣” NW] . . . [ይድን] ዘንድ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ከባድ ኃጢአት እየሠራ ንስሐ የማይገባ ሰው ከክርስቲያን ጉባኤ ሲወገድ ዳግም የሰይጣን ክፉ ዓለም ክፍል ይሆናል። (1 ዮሐ. 5:19) በዚህም ምክንያት ለሰይጣን እንደተሰጠ ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። ግለሰቡ ከጉባኤው እንዲወገድ መደረጉ በጉባኤው ላይ የሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ እንዲጠፋ ወይም እንዲወገድ እንዲሁም የጉባኤው መንፈስ እንዲጠበቅ ያደርጋል።—2 ጢሞ. 4:22

7:33, 34—አንድ ያገባ ሰው እንደሚያሳስበው የተገለጸው ‘የዚህ ዓለም ነገር’ ምንድን ነው? እዚህ ላይ ጳውሎስ፣ ያገቡ ክርስቲያኖች ሊያሳስቧቸው የሚገቡ ከዕለት ተዕለት ኑሯቸው ጋር የተያያዙ ነገሮችን መጥቀሱ ነበር። እነዚህም ምግብን፣ ልብስንና መጠለያን የሚያካትቱ ቢሆንም ክርስቲያኖች የሚጸየፏቸውን በዚህ ዓለም ላይ ያሉ መጥፎ ነገሮች አያጠቃልሉም።—1 ዮሐ. 2:15-17

11:26—የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ መከበር ያለበት በየስንት “ጊዜ” ነው? ይህ በዓል መከበር ያለበትስ እስከ መቼ ድረስ ነው? ጳውሎስ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን በተካፈሉ ጊዜ ሁሉ (በዓመት አንድ ጊዜ ኒሳን 14 ቀን) ‘ሞቱን እንደሚናገሩ’ መግለጹ ነበር። ይህንንም የሚያደርጉት “ጌታ እስከሚመጣ ድረስ” ይኸውም ኢየሱስ በትንሣኤ አማካኝነት ወደ ሰማይ እስከሚወስዳቸው ድረስ ነው።—1 ተሰ. 4:14-17

13:13—ፍቅር ከእምነትና ከተስፋ የሚበልጠው በምን መንገድ ነው? “ተስፋ ያደረግነው ነገር” እውን ሲሆን እንዲሁም “እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት” ነገር ፍጻሜውን ሲያገኝ እምነትና ተስፋ ቀደም ሲል የነበራቸው ሚና ያበቃል። (ዕብ. 11:1) ፍቅር ግን ለዘላለም ጸንቶ ስለሚኖር ከእምነትና ከተስፋ ይበልጣል።

15:29—‘ለሞቱ ሰዎች ብሎ መጠመቅ’ የሚለው አባባል ምን ትርጉም አለው? ጳውሎስ በሕይወት ያሉ ሰዎች፣ ሳይጠመቁ ለሞቱት እንደሚጠመቁላቸው መግለጹ አልነበረም። እዚህ ላይ ጳውሎስ እስከሚሞቱ ድረስ ታማኝነታቸውን መጠበቅንና ትንሣኤ አግኝተው መንፈሳዊ ሕይወት መቀበልን የሚያካትተውን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች የሚጠመቁትን ጥምቀት መግለጹ ነበር።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:26-31፤ 3:3-9፤ 4:7በራሳችን ከመመካት ይልቅ ትሑት በመሆን በይሖዋ መመካታችን በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲኖር ያደርጋል።

2:3-5ጳውሎስ፣ የግሪክ ፍልስፍናና ትምህርት ማዕከል በሆነችው በቆሮንቶስ በሚሰብክበት ጊዜ አድማጮቹን በሚያሳምን መንገድ መናገር መቻሉ አሳስቦት ይሆናል። ሆኖም ድካምም ሆነ ፍርሃት አምላክ የሰጠውን አገልግሎት እንዳያከናውን እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም። እኛም በተመሳሳይ አስቸጋሪ ወይም እንግዳ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከማወጅ ወደኋላ ልንል አይገባም። ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም ይሖዋ እንደሚረዳን በመተማመን ወደ እሱ ዘወር ማለት እንችላለን።

2:16፦ ‘የክርስቶስን ልብ’ ወይም አስተሳሰብ ማዳበር ሲባል እሱ የሚያስብበትን መንገድና እንደዚያ እንዲያስብ ያደረገውን ምክንያት ማወቅ፣ እንደ እሱ ማሰብ፣ ባሕርያቱን ጠንቅቆ መረዳት እንዲሁም ምሳሌውን መከተል ማለት ነው። (1 ጴጥ. 2:21፤ 4:1) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ ያሳለፈውን ሕይወትና አገልግሎቱን በጥንቃቄ ማጥናታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

3:10-15፤ 4:17የማስተማርና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ችሎታችንን መመርመር እንዲሁም ማሻሻል አለብን። (ማቴ. 28:19, 20) ጥሩ የማስተማር ችሎታ ከሌለን መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች የሚያጋጥማቸውን የእምነት ፈተና መቋቋም ሊያቅታቸው ይችላል፤ በዚህ ምክንያት የሚደርስብን ጉዳት መዳናችን ‘በእሳት ውስጥ በጭንቅ የማለፍ’ ያህል እንዲሆንብን ያደርጋል።

6:18‘ከዝሙት መሸሽ’ ሲባል ፖርኒያ ከመፈጸም መራቅ ብቻ ሳይሆን የብልግና ምስሎችን ከመመልከት፣ ከሥነ ምግባር ርኩሰት፣ ስለ ብልግና ድርጊቶች ከማሰብ፣ ከማሽኮርመም በአጠቃላይ ወደ ዝሙት ከሚመሩ ነገሮች ሁሉ መራቅ ማለት ነው።—ማቴ. 5:28፤ ያዕ. 3:17

7:29የተጋቡ ሰዎች ስለ ትዳራቸው ብቻ በማሰብ ለመንግሥቱ ሥራ ሁለተኛ ቦታ እንዳይሰጡ መጠንቀቅ አለባቸው።

10:8-11እስራኤላውያን በሙሴና በአሮን ላይ ማጉረምረማቸው ይሖዋን እጅግ አስቆጥቶት ነበር። እኛም ማጉረምረም ልማድ እንዳይሆንብን መጠንቀቃችን የጥበብ አካሄድ ነው።

16:2በዓለም ዙሪያ ለሚከናወነው የስብከት ሥራ ስለምናደርገው የገንዘብ መዋጮ አስቀድመን አስበንበት እቅድ ማውጣታችን በቋሚነት አስተዋጽኦ ለማድረግ ያስችለናል።

‘መስተካከላችሁን ቀጥሉ’

(2 ቆሮ. 1:1 እስከ 13:14)

ጳውሎስ፣ ቀደም ሲል ተግሣጽ ተሰጥቶት የነበረው ኃጢአተኛ ንስሐ ከገባ በኋላ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‘ይቅር ሊሉትና ሊያጽናኑት’ እንደሚገባ ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ የጻፈላቸው የመጀመሪያ ደብዳቤ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ያሳዘናቸው ቢሆንም ‘ሐዘናቸው ንስሓ ለመግባት ስላበቃቸው’ ሐዋርያው መደሰቱን ገልጿል።—2 ቆሮ. 2:6, 7፤ 7:8, 9

ጳውሎስ፣ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ‘በሁሉ ነገር ልቀው እንደተገኙ’ ሁሉ ‘በቸርነት ሥራም ልቀው እንዲገኙ’ አበረታቷቸዋል። ሐዋርያው ለተቃዋሚዎች መልስ ከሰጠ በኋላ እንደሚከተለው በማለት ለሁሉም ሰው የሚሆን የመጨረሻ ምክር ሰጥቷል:- “መደሰታችሁን፣ መስተካከላችሁን፣ ማጽናኛ መቀበላችሁን፣ በሐሳብ መስማማታችሁንና በሰላም መኖራችሁን ቀጥሉ።”—2 ቆሮ. 8:7፤ 13:11 NW

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

2:15, 16—“የክርስቶስ መዐዛ” የሆንነው በምን መንገድ ነው? የክርስቶስ መዐዛ የሆንነው መጽሐፍ ቅዱስን ስለምንታዘዝ እንዲሁም መልእክቱን ስለምንሰብክ ነው። እንዲህ ያለው “ሽታ” ክፉ ለሆኑ ሰዎች የማያስደስት ሊሆን ቢችልም ለይሖዋ እና ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ግን መልካም መዓዛ ይሆንላቸዋል።

5:16 የ1954 ትርጉም—ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አያውቁም’ ሲባል ምን ማለት ነው? ሰዎችን በሥጋዊ ዓይን አይመለከቱም ይኸውም በሀብት፣ በዘር፣ በጎሣ ወይም በዜግነት አድሎ አያደርጉም ማለት ነው። ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ላላቸው መንፈሳዊ ግንኙነት ነው።

11:1, 16፤ 12:11—ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሞኝ ወይም ምክንያታዊነት የሚጎድለው ሰው ሆኖባቸው ነበር? በፍጹም አልሆነባቸውም። ሆኖም አንዳንዶች፣ ሐዋርያ መሆኑን ለማሳመን ሲል ያቀረበውን የመከላከያ ሐሳብ ሲያነቡ በራሱ እንደተመካ ወይም ምክንያታዊነት የሚጎድለው እንደሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል።

12:1-4—‘ወደ ገነት የተነጠቀው ሰው’ ማን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ራእይ ስለተመለከተ ሌላ ሰው አይገልጽም፤ ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ሐዋርያነቱን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ከሰጠ በኋላ በመሆኑ ራሱ ያጋጠመውን ነገር እየተረከ ሊሆን ይችላል። ሐዋርያው በራእይ የተመለከተው ‘በፍጻሜው ዘመን’ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚኖረውን መንፈሳዊ ገነት ሳይሆን አይቀርም።—ዳን. 12:4

ምን ትምህርት እናገኛለን?

3:5ይህ ጥቅስ ይሖዋ፣ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ እንዲሁም በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል አማካኝነት ክርስቲያኖች ለአገልግሎታቸው ብቃት እንዲኖራቸው እንደሚረዳቸው ይገልጽልናል። (ዮሐ. 16:7፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17) በመሆኑም የአምላክን ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በትጋት ማጥናታችን፣ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አዘውትረን መጸለያችን እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሳናሰልስ መገኘታችን ብሎም ተሳትፎ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው።—መዝ. 1:1-3፤ ሉቃስ 11:10-13፤ ዕብ. 10:24, 25

4:16ይሖዋ “ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት” እንዲታደስ ስለሚያደርግ እሱ ባደረጋቸው ዝግጅቶች አዘውትረን መጠቀም አለብን፤ በሌላ አባባል መንፈሳዊ ነገሮችን ሳናከናውን አንድም ቀን እንዲያልፍ መፍቀድ አይኖርብንም።

4:17, 18የሚደርስብን ‘መከራ ቀላልና ጊዜያዊ’ መሆኑን ማስታወሳችን ችግሮች ሲያጋጥሙን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል።

5:1-5ጳውሎስ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ የመኖር ተስፋቸውን በተመለከተ ምን እንደሚሰማቸው ግሩም በሆነ መንገድ ገልጿል!

10:13የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ እንድንሰብክ እስካልተመደብን ድረስ በጉባኤያችን የአገልግሎት ክልል ውስጥ ብቻ ማገልገል ይኖርብናል።

13:5‘በእምነት መሆናችንን ለማወቅ ራሳችንን ስንመረምር’ አኗኗራችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተማርነው ነገር ጋር የሚስማማ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። ‘ራሳችንን ለመፈተን’ ደግሞ ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነና ‘መልካሙን ከክፉው የመለየት’ ችሎታችን ምን ያህል እንደዳበረ መመዘን ይኖርብናል፤ እንዲሁም የምናከናውናቸውን የእምነት ሥራዎች ዓይነትና ብዛት መመርመር ያስፈልገናል። (ዕብ. 5:14፤ ያዕ. 1:22-25) ጳውሎስ የሰጠውን ጠቃሚ ምክር ተግባራዊ በማድረግ በእውነት ጎዳና ላይ መመላለሳችንን መቀጠል እንችላለን።

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ” የሚለው ጥቅስ ምን ትርጉም አለው?—1 ቆሮ. 11:26