በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የሚያሳድገው አምላክ’ ነው!

‘የሚያሳድገው አምላክ’ ነው!

‘የሚያሳድገው አምላክ’ ነው!

‘የሚያሳድገው አምላክ እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም።’—1 ቆሮ. 3:7

1. ‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራው’ የትኛውን ሥራ ነው?

‘ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።’ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሁላችንም ልናከናውነው የምንችለውን ልዩ ሥራ የገለጸው በዚህ መንገድ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 3:5-9ን አንብብ።) እዚህ ላይ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ደቀ መዛሙርት ስለማድረጉ ሥራ ነው። ይህንን ሥራ ዘር ከመዝራትና ውኃ ከማጠጣት ጋር አመሳስሎታል። እጅግ አስፈላጊ በሆነው በዚህ ሥራ ውጤታማ ለመሆን የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። ጳውሎስም ‘የሚያሳድገው አምላክ’ መሆኑን አስገንዝቦናል።

2. ‘የሚያሳድገው አምላክ’ መሆኑን መገንዘባችን ለአገልግሎታችን ተገቢ አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን እንዴት ነው?

2 ይህንን እውነታ መገንዘባችን ትሑት በመሆን ለአገልግሎታችን ተገቢ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል። በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በትጋት ብንካፈልም ለሚገኘው እድገት ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ማናችንም የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ፣ አንድ ሰው እድገት የሚያደርግበትን መንገድ ሙሉ በሙሉ ልንረዳው አንችልም፤ ስለዚህ ሁኔታው ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን “ሁሉን ሠሪ የሆነውን፣ የእግዚአብሔርን ሥራ ማስተዋል አትችልም” በማለት በጻፈ ጊዜ ሁኔታውን በትክክል ገልጾታል።—መክ. 11:5

3. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራና ቃል በቃል ዘር በመዝራት መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

3 ታዲያ አንድ ሰው እድገት የሚያደርግበትን መንገድ መረዳት አለመቻላችን ሥራችን ተስፋ አስቆራጭ እንዲሆንብን ያደርጋል? በፍጹም። እንዲያውም ይህ ሁኔታ ሥራችንን አስደሳችና ትኩረት የሚስብ ያደርገዋል። ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ብሏል:- “ጠዋት ላይ ዘርህን ዝራ፤ ማታም ላይ እጅህ ሥራ አይፍታ፤ ይህ ወይም ያ፣ ወይም ሁለቱ መልካም ይሁኑ፣ የቱ እንደሚያፈራ አታውቅምና።” (መክ. 11:6) ቃል በቃል ዘር ከመዝራት ጋር በተያያዘ፣ ዘሩ ማፍራት አለማፍራቱን ወይም የት ቦታ ላይ እንደሚያፈራ ማወቅ አንችልም። ልንቆጣጠራቸው የማንችላቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ በሚመለከትም ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። ኢየሱስ፣ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 4 ላይ ተመዝግበው በሚገኙ ሁለት ምሳሌዎች ላይ ይህንን እውነታ ጎላ አድርጎ ገልጿል። እስቲ ከእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመልከት።

የተለያዩ የአፈር ዓይነቶች

4, 5. ኢየሱስ ስለ ዘሪው የተናገረውን ምሳሌ በአጭሩ ግለጽ።

4 በማርቆስ 4:1-9 ላይ ኢየሱስ ስለ አንድ ዘሪ የተናገረ ሲሆን የተዘራው ዘር በተለያዩ ቦታዎች እንደወደቀ ገልጿል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ስሙ፤ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ ወጣ። ዘሩን በሚዘራበትም ጊዜ አንዳንዱ መንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። ሌላው በቂ ዐፈር በሌለበት በጭንጫ ቦታ ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አድጎ የዘሩን ተክል ስላነቀው ፍሬ አላፈራም። ሌላው ዘር ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ስለ ወደቀ በቅሎ አደገ፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱ ሠላሣ፣ አንዱ ሥልሳ፣ ሌላውም መቶ ፍሬ አፈራ።”

5 በአንዳንድ አገሮች በአብዛኛው ዘር የሚዘራው ዘሩን በእጅ በመበተን ነው። ዘሪው፣ በልብሱ ወይም በዕቃ ዘሩን በመያዝ በእጁ እየዘገነ ይበትነዋል። ስለዚህ በዚህ ምሳሌ ላይ የተገለጸው ዘሪ፣ ዘሩን በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ የዘራው ሆን ብሎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘሩን ሲበትነው በተለያየ ቦታ ላይ ይወድቃል።

6. ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ ያብራራው እንዴት ነው?

6 የዚህን ምሳሌ ትርጉም መገመት አያስፈልገንም። ኢየሱስ በማርቆስ 4:14-20 ላይ የምሳሌውን ትርጉም ሲያብራራ እንዲህ ብሏል:- “ዘሪው ቃሉን ይዘራል። አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል። እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ ቦታ ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ ነገር ግን ሥር የሌላቸው ስለሆኑ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን አንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ሥልሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”

7. ዘሩም ሆነ የተለያዩት የአፈር ዓይነቶች ምን ያመለክታሉ?

7 ኢየሱስ፣ ዘሪው የተለያየ ዓይነት ዘር እንደተጠቀመ አለመግለጹን ልብ በል። ከዚህ ይልቅ አንድ ዓይነት ዘር፣ በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ እንደወደቀና የተለያየ ውጤት እንደተገኘ ገልጿል። የመጀመሪያው የአፈር ዓይነት የደደረ ሲሆን ሁለተኛው ጥልቀት የሌለው አፈር ነው፤ ሦስተኛውን መሬት እሾህ ወርሶታል፤ አራተኛው ግን ጥሩ ምርት የሚያስገኝ መልካም መሬት ነው። (ሉቃስ 8:8) ዘሩ ምን ያመለክታል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገር መልእክት ያመለክታል። (ማቴ. 13:19) የተለያዩት የአፈር ዓይነቶችስ ምን ትርጉም አላቸው? የተለያየ የልብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታሉ።—ሉቃስ 8:12, 15ን አንብብ።

8. (ሀ) በዘሪው የተመሰሉት እነማን ናቸው? (ለ) ሰዎች ለስብከቱ ሥራ የተለያየ ምላሽ የሚሰጡት ለምንድን ነው?

8 በዘሪው የተመሰሉት እነማን ናቸው? ዘሪው፣ ከአምላክ ጋር አብረው የሚሠሩትን የመንግሥቱ ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች ይወክላል። እነዚህ ሰዎች እንደ ጳውሎስና እንደ አጵሎስ ይተክላሉ እንዲሁም ውኃ ያጠጣሉ። ሆኖም ጠንክረው ቢሠሩም እንኳ የሚያገኙት ውጤት የተለያየ ነው። ለምን? መልእክቱን የሚሰሙት ሰዎች የልባቸው ሁኔታ የተለያየ ስለሆነ ነው። በምሳሌው ላይ የተገለጸው ዘሪ የሚያገኘው ውጤት እሱ በሚያደርገው ጥረት ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ይህን ማወቃችን እንዴት የሚያጽናና ነው! በተለይ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት፣ አንዳንድ ጊዜም ለአሥርተ ዓመታት ብዙም ውጤት ሳያገኙ ሲያገለግሉ ለቆዩ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ይህ በጣም የሚያጽናና ነው! * እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

9. ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ኢየሱስ የትኛውን የሚያጽናና እውነት ጎላ አድርገው ተናግረዋል?

9 የዘሪው ታማኝነት የሚለካው በሥራው በሚያገኘው ውጤት አይደለም። ጳውሎስ “እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል” ብሎ ሲናገር ይህን ነጥብ በተዘዋዋሪ መግለጹ ነበር። (1 ቆሮ. 3:8) ግለሰቡ ሽልማት የሚያገኘው እንደ ሥራው መጠን እንጂ ሥራው እንዳስገኘው ውጤት መጠን አይደለም። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ከስብከት ሥራቸው ተመልሰው ያገኙትን ውጤት ሲነግሩት ከላይ የተገለጸውን ነጥብ የሚያጎላ ሐሳብ ተናግሯል። ደቀ መዛሙርቱ፣ በኢየሱስ ስም አጋንንት ስለተገዙላቸው በጣም ተደስተው ነበር። ይህ የቱንም ያህል አስደሳች ቢሆንም ኢየሱስ “መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚያ ደስ አይበላችሁ፤ ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 10:17-20) አንድ ዘሪ የሚያከናውነው ሥራ ብዙ ጭማሪ ባያስገኝም ይህ ዘሪው፣ እንደ ሌሎች በትጋት ወይም በታማኝነት ሥራውን እንዳላከናወነ የሚጠቁም አይደለም። የሚገኘው ውጤት በአብዛኛው የተመካው ምሥራቹን በሚሰሙት ሰዎች የልብ ሁኔታ ላይ ነው። ዞሮ ዞሮ ግን የሚያሳድገው አምላክ ነው!

ቃሉን የሚሰሙት ሰዎች ያለባቸው ኃላፊነት

10. ቃሉን የሚሰማ አንድ ግለሰብ እንደ መልካሙ መሬት መሆን አለመሆኑ በምን ላይ የተመካ ነው?

10 ቃሉን ስለሚሰሙት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ አስቀድሞ ተወስኗል? በፍጹም። ሰዎቹ እንደ መልካሙ መሬት መሆን አለመሆናቸው የራሳቸው ምርጫ ነው። እርግጥ ነው፣ የአንድ ሰው የልብ ዝንባሌ ሊሻሻል ወይም መጥፎ ሊሆን ይችላል። (ሮሜ 6:17) በምሳሌው ላይ ኢየሱስ፣ አንዳንዶች “ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ” በውስጣቸው የተዘራውን ቃል እንደሚወስደው ተናግሯል። ይሁን እንጂ ይህ እንዳይሆን መከላከል ይቻላል። በያዕቆብ 4:7 ላይ ክርስቲያኖች “ዲያብሎስን ተቃወሙት” የሚል ማበረታቻ የተሰጣቸው ሲሆን እንዲህ ካደረጉ ሰይጣን ከእነሱ ይሸሻል። ሌሎች ደግሞ፣ መጀመሪያ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ በደስታ እንደተቀበሉት ሆኖም “ሥር የሌላቸው ስለሆኑ” እንደተሰናከሉ ኢየሱስ ተናግሯል። የአምላክ አገልጋዮች ግን ‘ሥር እንዲሰዱ’ እንዲሁም በመሠረቱ ላይ እንዲታነጹ ተመክረዋል፤ እንዲህ ማድረጋቸው “የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ . . . [እንዲሁም] ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር” ለመረዳት ያስችላቸዋል።—ኤፌ. 3:17-19፤ ቈላ. 2:6, 7

11. የዚህ ዓለም ውጣ ውረድና የሀብት አጓጊነት ቃሉን እንዳያንቀው መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ቃሉን ስለሰሙት ስለ ሌሎቹ ሰዎች ሲናገር “የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ [እና] የሀብት አጓጊነት” ወደ ልባቸው ሰርጎ በመግባት ቃሉን አንቆ እንደሚይዘው ገልጿል። (1 ጢሞ. 6:9, 10) ሰዎቹ ይህ እንዳይሆን ምን ማድረግ ይችላሉ? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት መልሱን ሰጥቶናል:- “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ ‘ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም’ ብሎአል።”—ዕብ. 13:5

12. በመልካም መሬት የተመሰሉት ሰዎች የሚያፈሩት ፍሬ መጠኑ የተለያየ የሆነው ለምንድን ነው?

12 በመጨረሻም ኢየሱስ በመልካም መሬት ላይ በተዘራው ዘር የተመሰሉት ሰዎች ‘ሠላሳ፣ ሥልሳ፣ መቶም ፍሬ እንዳፈሩ’ ገልጿል። ቃሉን የሚሰሙ አንዳንዶች ጥሩ የልብ ዝንባሌ ኖሯቸው ፍሬ ቢያፈሩም ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ሊያከናውኑት የሚችሉት ነገር እንደ ሁኔታቸው ይለያያል። ለምሳሌ፣ የዕድሜ መግፋት አሊያም አቅም የሚያሳጣ ሕመም አንዳንዶች በስብከቱ ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ሊገድብባቸው ይችላል። (ከማርቆስ 12:43, 44 ጋር አወዳድር።) በዚህም ረገድ ቢሆን ዘሪው ሊያደርገው የሚችለው ነገር ውስን ነው ወይም ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ ሆኖም ይሖዋ ዘሩን እንዳሳደገው ሲመለከት ይደሰታል።—መዝሙር 126:5, 6ን አንብብ።

የሚተኛው ዘሪ

13, 14. (ሀ) ኢየሱስ ዘር ስለሚዘራው ሰው የተናገረውን ምሳሌ በአጭሩ ግለጽ። (ለ) በዘሪው የተመሰሉት እነማን ናቸው? ዘሩስ ምን ያመለክታል?

13 በማርቆስ 4:26-29 ላይ ደግሞ ስለ ሌላ ዘሪ የሚናገር ምሳሌ እናገኛለን። ምሳሌው እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ ምድርም ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ አጨዳ ይጀምራል።”

14 በዚህ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ዘሪ ማን ነው? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ሰዎች ይህ ዘሪ ኢየሱስን እንደሚያመለክት ያምናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ‘እንደሚተኛና እሱ ሳያውቅ ዘሩ እንደሚበቅል’ መናገር ይቻላል? ኢየሱስ ዘሩ እድገት የሚያደርግበትን መንገድ እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም! በመጀመሪያው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ዘሪ ሁሉ ይሄኛውም ዘሪ፣ የመንግሥቱን ዘር በቅንዓት የሚሰብኩትን የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ያመለክታል። መሬት ላይ የተዘራው ዘር ደግሞ የሚሰብኩትን ቃል የሚያመለክት ነው። *

15, 16. ኢየሱስ፣ አንድ ዘር ቃል በቃል ስለማደጉም ሆነ መንፈሳዊ እድገት ስለማድረግ የትኛውን እውነታ ጎላ አድርጎ ገልጿል?

15 ኢየሱስ፣ ዘሪው “ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል” ብሏል። ዘሪው እንዲህ ማድረጉ ግዴለሽ መሆኑን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአብዛኞቹን ሰዎች የተለመደ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያሳይ አገላለጽ ነው። ሐሳቡ የተገለጸበት መንገድ፣ ቀጣይነት ያለውን ሂደት ይኸውም ዘሪው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቀን እየሠራ ማታ ይተኛ እንደነበር የሚጠቁም ነው። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ ውስጥ የተከናወነውን ነገር ሲገልጽ “ያ ዘር በቅሎ ያድጋል” ብሏል። አክሎም ይህ ሁኔታ የተከናወነው ዘሪው “ሳያውቅ” መሆኑን ገልጿል። እዚህ ላይ ሊጎላ የተፈለገው ነገር እድገቱ የተካሄደው ‘በራሱ’ መሆኑ ነው። *

16 ኢየሱስ እዚህ ላይ ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? የተዘራው ዘሩ በማደጉና ሂደቱም የተከናወነው ቀስ በቀስ በመሆኑ ላይ ትኩረት እንዳደረገ ልብ በል። “ምድርም ራስዋ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች።” (ማር. 4:28) ይህ እድገት የሚከናወነው ቀስ በቀስ እንዲሁም ደረጃ በደረጃ ነው። እድገቱን ማፋጠን አይቻልም። መንፈሳዊ እድገትንም በተመለከተ ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ባለው ግለሰብ ልብ ውስጥ እውነት የሚያድገው ይሖዋ በፈቀደው ጊዜ ደረጃ በደረጃ ነው።—ሥራ 13:48፤ ዕብ. 6:1

17. የእውነት ዘር ፍሬ ሲያፈራ የሚደሰቱት እነማን ናቸው?

17 ዘሪው “ፍሬው እንደ በሰለ” በአጨዳው የሚካፈለው እንዴት ነው? ይሖዋ፣ የመንግሥቱ እውነት በአዳዲስ ደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ እንዲያድግ ሲያደርግ እነዚህ ደቀ መዛሙርት ቀስ በቀስ እድገት በማድረግ ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ሕይወታቸውን ለእሱ ይወስናሉ። ከዚያም ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት በውኃ ይጠመቃሉ። ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለመድረስ ጥረት የሚያደርጉ ወንድሞች፣ ቀስ በቀስ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን መቀበል ይችላሉ። አንድን ደቀ መዝሙር ያስገኘውን ዘር መጀመሪያ የዘራው ሰውም ሆነ በዚህ ሥራ በቀጥታ ያልተካፈሉት ሌሎች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የመንግሥቱን ዘር ያጭዳሉ። (ዮሐንስ 4:36-38ን አንብብ።) በእርግጥም ‘ዘሪውና አጫጁ በጋራ ደስ ይላቸዋል።’

በአሁኑ ጊዜ የምናገኘው ትምህርት

18, 19. (ሀ) አንተ በግልህ ኢየሱስ በተናገራቸው ምሳሌዎች ላይ ባደረግነው ምርምር የተበረታታኸው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ለየትኛው ጥያቄ መልስ እናገኛለን?

18 በማርቆስ ምዕራፍ 4 ላይ ተመዝግበው በሚገኙት በእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች ላይ ካደረግነው ምርምር ምን ትምህርት አግኝተናል? በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው ዘር የመዝራት ሥራ ተሰጥቶናል። አንዳንድ ችግሮች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ በማሰብና ሰበብ በመፍጠር ይህን ሥራ ከማከናወን ወደኋላ ማለት አይኖርብንም። (መክ. 11:4) በሌላ በኩል ደግሞ ከአምላክ ጋር የመሥራት ታላቅ መብት እንዳለን እንገነዘባለን። የእኛንም ሆነ መልእክቱን የሚቀበሉትን ሰዎች ጥረት በመባረክ መንፈሳዊ እድገት እንዲኖር የሚያደርገው ይሖዋ ነው። ማንም ሰው መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ልናስገድደው እንደማንችል እንገነዘባለን። እንዲሁም በስብከቱ ሥራ የምናገኘው እድገት አዝጋሚ ቢሆን ወይም እድገት ባይኖርም ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። በሥራችን ውጤታማ መሆናችን፣ ለይሖዋ እንዲሁም ‘የመንግሥቱን ወንጌል ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን’ እንድንሰብክ ለሰጠን መብት ታማኝ በመሆናችን ላይ የተመካ መሆኑ እንዴት የሚያጽናና ነው!—ማቴ. 24:14

19 ኢየሱስ፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ስለሚያደርጉት እድገትና ስለ መንግሥቱ ስብከቱ ሥራ ምን ተጨማሪ ትምህርት ሰጥቷል? የዚህ ጥያቄ መልስ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙ ሌሎች ምሳሌዎች ላይ ተገልጿል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 210, 211 (እንግሊዝኛ) ላይ የሚገኘውን ወንድም ጌኦርግ ፊዩልኒር ሊንዳል በአይስላንድ ስላከናወኑት አገልግሎት የሚገልጸውን ተሞክሮ እንዲሁም በ1988 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 82-99 (እንግሊዝኛ) ላይ የሚገኘውን ለበርካታ ዓመታት ውጤት ሳያገኙ በአይስላንድ ያገለገሉትን ታማኝ ወንድሞች ተሞክሮ ተመልከት።

^ አን.14 ከዚህ ቀደም በወጣ መጠበቂያ ግንብ ላይ፣ ዘሩ ወደ ጉልምስና ማደግ የሚያስፈልጋቸውን የግለሰብ ክርስቲያኖች ባሕርያት እንደሚያመለክት እንዲሁም በአካባቢያቸው ያሉ የተለያዩ ነገሮች በክርስቲያኖች ባሕርይ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርጉ ተገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ዘሩ እንደተበላሸ ወይም ፍሬው እንደበሰበሰ አለመገለጹን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ይልቅ ዘሩ ምንም ሳይሆን ወደ ጉልምስና ያድጋል።—የሰኔ 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-19 (እንግሊዝኛ) እንዲሁም “መንግሥትህ ትምጣ” የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 96-99 ተመልከት።

^ አን.15 ከማርቆስ ወንጌል ሌላ ይህ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በሐዋርያት ሥራ 12:10 ላይ ብቻ ሲሆን ጥቅሱም የብረቱ መዝጊያ “ራሱ ዐውቆ” እንደተከፈተ ይገልጻል።

ታስታውሳለህ?

• ቃል በቃል ዘር መዝራትና የመንግሥቱን መልእክት ማወጅ የሚያመሳስሏቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

• ይሖዋ፣ የአንድን የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪ ታማኝነት የሚለካው በምንድን ነው?

• ኢየሱስ፣ አንድ ዘር ቃል በቃል በሚያደርገው እድገትና በመንፈሳዊ እድገት መካከል ምን ተመሳሳይነት እንዳለ አጉልቷል?

• ‘ዘሪውና አጫጁ በጋራ ደስ የሚላቸው’ እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚሰብክ ግለሰብን ዘር ከሚዘራ ሰው ጋር ያመሳሰለው ለምን ነበር?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመልካም መሬት የተመሰሉት ሰዎች በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ሁኔታቸው በፈቀደላቸው መጠን በሙሉ ልባቸው ይካፈላሉ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማደጉን እንዲቀጥል የሚያደርገው አምላክ ነው