በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለነበር አልፈራንም

ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለነበር አልፈራንም

ይሖዋ ከእኛ ጋር ስለነበር አልፈራንም

ኤዪፕቲኣ ፔትሪዱ እንደተናገረችው

በ1972 በመላው ቆጵሮስ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ወንድም ናታን ኖር የሚሰጠውን ልዩ ንግግር ለማዳመጥ በኒኮሲያ ተሰበሰቡ፤ ይህ ወንድም የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑትን የስብከት ሥራ ለበርካታ ዓመታት በበላይነት ይከታተል ነበር። ወንድም ኖር ሲያየኝ ወዲያው ስላስታወሰኝ “በግብጽ ስላሉት ወንድሞች የሰማሽው ነገር አለ?” በማለት ጠየቀኝ። ከ20 ዓመታት በፊት በእስክንድርያ፣ ግብጽ ከወንድም ኖር ጋር ተገናኝተን ነበር።

የተወለድኩት ጥር 23, 1914 በእስክንድርያ ከተማ ሲሆን በቤተሰባችን ውስጥ ካሉት አራት ልጆች የመጀመሪያ ነኝ። ያደግነው በባሕሩ አቅራቢያ ነበር። በዚያን ጊዜ እስክንድርያ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ሰዎች የሚኖሩባትና ግሩም በሆኑ ሕንፃዎቿ እንዲሁም ታሪካዊ በመሆኗ የምትታወቅ ውብ ከተማ ነበረች። አውሮፓውያን ከአረቦች ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ ስለነበር እኔና ወንድሞቼ እንዲሁም እህቴ አረብኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ፈረንሳይኛ ብሎም የቤተሰባችን ቋንቋ የሆነውን ግሪክኛ መናገር ችለናል።

ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በአንድ የፈረንሳይ የልብስ ዲዛይን ማውጫ ሱቅ ውስጥ ሥራ አገኘሁ፤ እዚያም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሴቶች ለየት ባሉ ወቅቶች የሚለብሷቸውን ቀሚሶች ዲዛይን አወጣና እሰፋ ነበር። በተጨማሪም ሃይማኖተኛ ሰው በመሆኔ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ እወድ ነበር፤ በእርግጥ የማነበው ነገር ብዙም አይገባኝም ነበር።

በ1930ዎቹ ዓመታት አጋማሽ አካባቢ የቆጵሮስ ተወላጅ ከሆነ መልካም ጠባይ ያለው አንድ ወጣት ጋር ተዋወቅሁ። ቲኦዞቶስ ፔትሪዲስ የተባለው ይህ ወጣት በትግል ስፓርት ጎበዝ ቢሆንም ጣፋጭ ምግቦችን መሥራትም ተምሮ ነበር፤ ስለዚህ በአንድ የታወቀ የጣፋጭ ምግቦች መሸጫ ውስጥ ይሠራ ነበር። ቲኦዞቶስ ስለወደደኝ ብዙውን ጊዜ በመስኮቴ በኩል ሆኖ የግሪክ የፍቅር ዘፈኖችን ያዜምልኝ ነበር። ሰኔ 30, 1940 ከቲኦዞቶስ ጋር ተጋባን። ያ ጊዜ አስደሳች ነበር። እናቴ ባለችበት ሕንፃ ውስጥ እንኖር የነበረ ሲሆን በ1941 የመጀመሪያው ልጃችን ጆን ተወለደ።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መማር

ቲኦዞቶስ በሃይማኖታችን የማይደሰት ከመሆኑም በላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጥያቄዎችን ያነሳ ነበር። እኔ ሳላውቅ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሮ ነበር። አንድ ቀን ከልጃችን ጋር ቤት እያለሁ አንዲት ሴት መጣችና የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት የተጻፈበት ካርድ ሰጠችኝ። ሴትየዋን ላለማስቀየም ስል ካርዱን አነበብኩት። ከዚያም አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንድወስድ ጋበዘችኝ። የሚገርመው እነዚህ ጽሑፎች ቲኦዞቶስ ካመጣቸው መጻሕፍት ጋር አንድ ዓይነት ነበሩ!

ሴትየዋን “እነዚህ መጻሕፍትማ አሉኝ” ካልኳት በኋላ ወደ ቤት እንድትገባ ጋበዝኳት። ከዚያም እሌኒ ኒኮላ የተባለችውን ይህቺን የይሖዋ ምሥክር በጥያቄ አጣደፍኳት። እሷም በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም በትዕግሥት መልስ ሰጠችኝ። እንዲህ ማድረጓ ያስደሰተኝ ከመሆኑም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መረዳት ጀመርኩ። በውይይታችን መሃል እሌኒ የባለቤቴን ፎቶ ተመለከተችና “ይህን ሰው አውቀዋለሁ!” አለችኝ። የቲኦዞቶስ ምስጢር ገሃድ ወጣ፤ ሁኔታው በጣም አስገረመኝ። ለካስ ቲኦ፣ የት እንደሚሄድ እንኳ ሳይነግረኝ ብቻውን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኝ ነበር! የዚያን ዕለት ቲኦዞቶስ ወደ ቤት ሲመጣ “ባለፈው እሁድ የሄድክበት ቦታ በዚህ ሳምንት እኔም አብሬህ እሄዳለሁ!” አልኩት።

ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት ስብሰባ ላይ አሥር የሚያህሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የሚክያስ መጽሐፍ ላይ ውይይት ያደርጉ ነበር። የሚናገሩትን ሁሉ በጉጉት አዳመጥኩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጆርጅ እና ካቴሪኒ ፔትራኪ በየሳምንቱ ዓርብ ምሽት ላይ እየመጡ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑን ጀመር። አባቴ እንዲሁም ሁለቱ ወንድሞቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት በመጀመራችን ተቃወሙን፤ ታናሽ እህቴ ግን ወደ እውነት ባትመጣም አትቃወመንም ነበር። በሌላ በኩል እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበለች ሲሆን በ1942 እኔ፣ እናቴና ቲኦዞቶስ ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን ለማሳየት በእስክንድርያ አቅራቢያ ባለው ባሕር ውስጥ ተጠመቅን።

በሕይወታችን ውስጥ የተከሰቱ ለውጦች

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀመረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ጦርነቱ እየተባባሰ ሄደ። በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጀርመናዊው ጦር ጄኔራል ኤርቪን ሮመል የሚመራው ታንከኛ ሠራዊት በአቅራቢያችን ባለችው ኤላላሚን የሰፈረ ሲሆን እስክንድርያ ደግሞ በብሪታንያ የጦር ኃይል ተጥለቅልቃ ነበር። በዚህ ወቅት በርካታ ደረቅ ምግቦችን አከማቸን። ከጊዜ በኋላ የቲኦዞቶስ አሠሪ በስዊዝ አቅራቢያ በሚገኘው በፖርት ታውፊክ አዲስ የከፈተውን የጣፋጭ ምግቦች መሸጫ እንዲቆጣጠርለት ቲኦዞቶስን ስለጠየቀው ወደዚያ ተዛወርን። በዚያም የግሪክኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት እኛን ማፈላለግ ጀመሩ። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች አድራሻችንን ባያውቁትም እስኪያገኙን ድረስ ከቤት ወደ ቤት በማገልገል የምንኖርበትን ቦታ ማወቅ ችለዋል።

በፖርት ታውፊክ እያለን ስታቭሮስ እና ዩላ ኪፕራኦስ የተባሉትን ባልና ሚስት እንዲሁም ቶቶስ እና ዮርያ የሚባሉትን ልጆቻቸውን መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናቸው የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላም የቅርብ ወዳጆቻችን ሆኑ። ስታቭሮስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጣም ያስደስተው ስለነበር ወደ ቤታችን የምንሄድበት የመጨረሻው ባቡር እንዲያመልጠንና ከእነሱ ጋር እንድንቆይ ለማድረግ ሲል በቤቱ ውስጥ ያሉትን ሰዓቶች በሙሉ አንድ ሰዓት ወደኋላ ይመልሳቸው ነበር። በመሆኑም እስከ ሌሊት ድረስ እንወያይ ነበር።

በፖርት ታውፊክ አንድ ዓመት ከ6 ወር ከኖርን በኋላ እናቴ ስትታመም ወደ እስክንድርያ ተመለስን። እናቴ፣ ለይሖዋ ታማኝነቷን እንደጠበቀች በ1947 በሞት አንቀላፋች። በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ በመንፈሳዊ ጎልማሳ በሆኑ ክርስቲያን ወዳጆቻችን አማካኝነት አጽናንቶናል። ከዚህም በላይ የተለያዩ ሚስዮናውያን ወደተመደቡባቸው አገራት ሲጓዙ የተሳፈሩባቸው መርከቦች ለተወሰነ ጊዜ እስክንድርያ በሚቆሙበት ወቅት በእንግድነት ተቀብለን እናስተናግዳቸው ነበር።

አስደሳችና አሳዛኝ ክስተቶች

በ1952 ሁለተኛውን ልጃችንን ጄምስን ወለድኩ። በቤታችን ውስጥ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካሄዳቸው ለልጆቻችን ጠቃሚ መሆኑን ስለተገነዘብን በቤታችን ስብሰባ እንዲደረግ ፈቃደኞች ከመሆናችንም በላይ አዘውትረን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን እንጋብዝ ነበር። እንዲህ ማድረጋችን ትልቁ ልጃችን ጆን እውነትን እንዲወድ ስለረዳው በአሥራዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ እያለ አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በዚህ ወቅት ትምህርቱን ለማጠናቀቅ በማታው ክፍለ ጊዜ ይማር ነበር።

ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ቲኦዞቶስ ከባድ የልብ ችግር እንዳለበት ስለታወቀ ሐኪም ሥራውን እንዲያቆም መከረው። በዚያን ወቅት ልጃችን ጄምስ ገና አራት ዓመቱ ነበር። ታዲያ ምን ልንሆን ነው? ይሖዋ፣ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ” በማለት ቃል ገብቷል! (ኢሳ. 41:10) በ1956 በስዊዝ ቦይ አቅራቢያ በምትገኘው በኢዝሜሊያ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ስንመደብ ምን ያህል እንደተገረምንና እንደተደሰትን መገመት ትችላላችሁ! በቀጣዮቹ ዓመታት በግብጽ ሁከት በመንገሱ ወንድሞቻችን ማጽናኛ ያስፈልጋቸው ነበር።

በ1960 ሻንጣችንን ብቻ አንጠልጥለን ከግብጽ የወጣን ሲሆን የባለቤቴ የትውልድ ቦታ ወደሆነችው ወደ ቆጽሮስ ደሴት ሄድን። በዚህ ወቅት የቲኦዞቶስ ሕመም በጣም ተባብሶ ስለነበር ሥራ መሥራት አልቻለም። አንድ ደግ ወንድምና ባለቤቱ መኖሪያ ሰጡን። የሚያሳዝነው ከሁለት ዓመታት በኋላ ባለቤቴ በመሞቱ እኔና ጄምስ ብቻችንን ቀረን። አብሮን ወደ ቆጵሮስ የመጣው ልጄ ጆን ደግሞ አግብቶ ስለነበር የራሱን ቤተሰብ መንከባከብ ነበረበት።

አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት እንክብካቤ ማግኘት

ስታቭሮስና ዶራ ኬሪስ በቤታቸው እንድንኖር ጋበዙን። በዚህ ጊዜም ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ስላሟላልን ተንበርክኬ አመሰገንኩት። (መዝ. 145:16) ከጊዜ በኋላ ስታቭሮስና ዶራ ቤታቸውን ሸጠው ፎቅ ቤት ከገነቡ በኋላ ታችኛውን ክፍል የመንግሥት አዳራሽ እንዲሆን ሰጡት፤ በዚህ ወቅት ለእኔና ለጄምስም እዚያው ግቢ ውስጥ ሁለት ክፍል ያለው ቤት ሠሩልን።

ከጊዜ በኋላ ጄምስ ትዳር የመሠረተ ሲሆን እሱና ባለቤቱም የመጀመሪያ ልጃቸውን እስከወለዱበት ጊዜ ድረስ በአቅኚነት አገልግለዋል፤ ጄምስና ባለቤቱ አራት ልጆች አሏቸው። ወንድም ኖር የማይረሳ ጉብኝት ካደረገልን ከሁለት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1974 በቆጵሮስ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተቀሰቀሰ። * የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው በመሰደዳቸው በሌላ አካባቢ እንደ አዲስ ኑሮ መጀመር ነበረባቸው፤ እንዲህ ካደረጉት መካከል ልጄ ጆንም ይገኝበታል። ጆን ከሚስቱና ከሦስት ልጆቹ ጋር በካናዳ መኖር ጀመረ። ብዙዎች ቆጵሮስን ለቅቀው ቢሄዱም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር በመጨመሩ ተደስተናል።

ውሎ አድሮ የጡረታ አበሌን ማግኘት ስጀምር በአገልግሎት የበለጠ መካፈል ቻልኩ። ሆኖም ከጥቂት ዓመታት በፊት በጭንቅላቴ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ጤንነቴ ስለተቃወሰ ከጄምስና ከቤተሰቡ ጋር መኖር ጀመርኩ። ከዚያም ጤንነቴ እያሽቆለቆለ ሲሄድ ለበርካታ ሳምንታት ሆስፒታል ከተኛሁ በኋላ አረጋውያን እንክብካቤ ወደሚያገኙበት ተቋም ተዛወርኩ። የማያቋርጥ ሥቃይ ቢኖረኝም ለነርሶቹ፣ ለሕሙማኑ እንዲሁም እነሱን ለመጠየቅ ለሚመጡት ሰዎች እመሠክራለሁ። ከዚህም በላይ ለበርካታ ሰዓታት የግል ጥናት የማደርግ ሲሆን ደግ የሆኑት መንፈሳዊ ወንድሞቼ እርዳታ ስለሚያደርጉልኝ በአቅራቢያዬ በሚደረገው የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት ላይ መገኘት ችያለሁ።

በእርጅና ዘመኔ ያገኘሁት ማጽናኛ

እኔና ቲኦዞቶስ በመንፈሳዊ የረዳናቸው ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ መስማቴ ያጽናናኛል። ከእነዚህ ሰዎች ልጆችና የልጅ ልጆች መካከል አብዛኞቹ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ሲሆን አንዳንዶቹ በስዊዘርላንድ፣ በአውስትራሊያ፣ በእንግሊዝ፣ በካናዳና በግሪክ እያገለገሉ ነው። በአሁኑ ጊዜ ልጄ ጆንና ባለቤቱ ከወንድ ልጃቸው ጋር በካናዳ የሚኖሩ ሲሆን የመጀመሪያዋ ሴት ልጃቸውና ባለቤቷ አቅኚዎች ናቸው። ሊንዳ የተባለችው ሌላዋ ሴት ልጃቸውና ባለቤቷ ጆሹዋ ስናፕ በጊልያድ ትምህርት ቤት በ124ኛው ክፍል እንዲሠለጥኑ ተጋብዘዋል።

ጄምስ የተባለው ልጄና ባለቤቱ በአሁኑ ጊዜ በጀርመን ይኖራሉ። ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው በቤቴል (አንደኛው በአቴንስ፣ ግሪክ ሌላው ደግሞ በሴልተርስ፣ ጀርመን) እያገለገሉ ነው። ሦስተኛው ወንድ ልጃቸው እንዲሁም ሴት ልጃቸውና ባለቤቷ በጀርመን አቅኚ ሆነው ያገለግላሉ።

እናቴንና ውዱ ባለቤቴን ቲኦዞቶስን በትንሣኤ ስናገኛቸው የምንነግራቸው በጣም ብዙ ታሪኮች አሉ! ለቤተሰባቸው እንዴት ያለ ግሩም ቅርስ እንደተዉ ሲያውቁ ምን ያህል ይደሰቱ ይሆን! *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.21 የጥቅምት 22, 1974 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 12-15⁠ን ተመልከት።

^ አን.26 ይህ ርዕስ ለሕትመት በሚዘጋጅበት ወቅት እህት ፔትሪዱ በ93 ዓመታቸው አርፈዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በዚህ ጊዜም ቢሆን ይሖዋ በመንፈሳዊ ጎልማሳ በሆኑ ክርስቲያን ወዳጆቻችን አማካኝነት አጽናንቶናል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቆጵሮስ

ኒኮስያ

የሜድትራኒያን ባሕር

ግብጽ

ካይሮ

ኤላላሚን

እስክንድርያ

ኢዝሜሊያ

ስዊዝ

ፖርት ታውፊክ

የስዊዝ ቦይ

[ምንጭ]

Based on NASA/Visible Earth imagery

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1938 ከቲኦዞቶስ ጋር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጄ ጆን ከባለቤቱ ጋር

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጄ ጄምስ ከባለቤቱ ጋር