በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሚስዮናውያን ከአንበጣ ጋር ተመሳስለዋል

ሚስዮናውያን ከአንበጣ ጋር ተመሳስለዋል

124ኛው የጊልያድ ምረቃ

ሚስዮናውያን ከአንበጣ ጋር ተመሳስለዋል

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በየስድስት ወሩ ተማሪዎችን የሚያስመርቅ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል አባላት በሙሉ ይጋበዛሉ። መጋቢት 8, 2008 በተካሄደው የ124ኛው ክፍል የጊልያድ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከቤቴል ቤተሰብ አባላት በተጨማሪ ከ30 ከሚበልጡ አገሮች የመጡ እንግዶች ተገኝተው ነበር። ተማሪዎቹ ልዩ ትኩረት በሚሰጡት በዚህ ቀን 6,411 የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት የደስታቸው ተካፋይ ሆነዋል።

የበላይ አካል አባልና የዕለቱ ፕሮግራም ሊቀ መንበር የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት “ከይሖዋ ምሳሌያዊ አንበጦች ጋር አብራችሁ ተጓዙ” በሚል ርዕስ የመክፈቻውን ንግግር አቀረበ። በራዕይ 9:1-4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ፣ በ1919 በመንፈሳዊ ሁኔታ ያንሰራሩትን አነስተኛ ቁጥር የነበራቸው ቅቡዓን ክርስቲያኖች በድንገት እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረ የአንበጣ መንጋ ጋር ያመሳስላቸዋል። ተማሪዎቹም ‘የሌሎች በጎች’ አባላት እንደመሆናቸው መጠን ከዚህ ምሳሌያዊ የአንበጣ መንጋ ጋር ለመተባበር ራሳቸውን ማቅረባቸውን እንዲያስታውሱ ተናጋሪው አበረታቷቸዋል።—ዮሐ. 10:16

ቀጥሎ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሎን ሺሊንግ “እርስ በርስ የምትደጋገፉ ሁኑ” የሚል ንግግር አቀረበ። ንግግሩ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ በነበሩት አቂላና ጵርስቅላ የተባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስት ምሳሌ ላይ የተመሠረተ ነበር። (ሮሜ 16:3, 4) በ124ኛው ክፍል ውስጥ 28 ጥንዶች የነበሩ ሲሆን እነሱም በሚስዮናዊነት አገልግሎታቸው ስኬታማ መሆን እንዲችሉ የጋብቻ ጥምረታቸው ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አቂላና ሚስቱ ጵርስቅላ ሁልጊዜ የሚጠቀሱት አንድ ላይ ነው። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ጉባኤው እነዚህን ባልና ሚስት እንደ አንድ አካል አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉ ባልና ሚስት አብረው መሥራት፣ አብረው ይሖዋን ማምለክ እንዲሁም በሌላ አገር ተመድበው ሲያገለግሉ የሚያጋጥሟቸውን ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አብረው ማሸነፍ ይኖርባቸዋል፤ በዚህ መንገድ አንዳቸው ለሌላው ረዳት መሆን ወይም እርስ በርስ መደጋገፍ ይችላሉ።—ዘፍ. 2:18

“ለይሖዋ ጥሩነት ምላሽ ስጡ” የሚለውን ቀጣዩን ንግግር ያቀረበው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጋይ ፒርስ ነበር። ወንድም ፒርስ፣ ጥሩ ሰው መሆን ሲባል መጥፎ ነገር ከማድረግ መቆጠብ ማለት ብቻ አለመሆኑን አብራርቷል። ጥሩ ሰው፣ ሌሎችን የሚጠቅሙ ጥሩ ነገሮችን ያደርጋል። ይሖዋ አምላክ፣ በበጎነቱ ወይም በጥሩነቱ አቻ አይገኝለትም። (ዘካ. 9:16, 17 የ1954 ትርጉም) የአምላክ ጥሩነትና ፍቅር እኛም ለሌሎች ጥሩ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል። ወንድም ፒርስ ንግግሩን ሲደመድም ተማሪዎቹን እንዲህ በማለት አመስግኗቸዋል:- “እስካሁን ጥሩ ነገር ስታደርጉ ቆይታችኋል። ወደፊትም ይሖዋ አምላክ በሚሰጣችሁ በየትኛውም የአገልግሎት ምድብ ጥሩ ነገር በማከናወን ለአምላክ ጥሩነት ምላሽ መስጠታችሁን እንደምትቀጥሉ እርግጠኞች ነን።”

በመቀጠልም ከዚህ ቀደም በሚስዮናዊነት ያገለግል የነበረውና በቅርቡ የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማይክል በርኔት “በግንባራችሁ ላይ እንደ ምልክት ይሁን” የሚል ርዕስ ያለው ንግግር አቀረበ። እስራኤላውያን በግንባራቸው ላይ ምልክት ያለ ያህል ይሖዋ ተዓምራዊ በሆነ መንገድ እንዴት ከግብጽ እንዳወጣቸው ማስታወስ ነበረባቸው። (ዘፀ. 13:16) ተማሪዎቹም፣ በግንባራቸው ላይ ምልክት ያለ ያህል በጊልያድ ትምህርት ቤት ያገኟቸውን በርካታ ትምህርቶች እንዲያስታውሱ ተመክረዋል። ወንድም በርኔት፣ ተመራቂዎቹ አብረዋቸው ከሚያገለግሉ ሚስዮናውያንም ሆነ ከሌሎች ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሚፈቱበት ወቅት ትሑት መሆንና ልክን ማወቅ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል።—ማቴ. 5:23, 24

የጊልያድ አስተማሪ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለው ወንድም ማርክ ኑሜር፣ “ለእናንተስ ምን ዓይነት መዝሙር ይዘመርላችሁ ይሆን?” የሚል ንግግር አቅርቧል። በጥንት ዘመን በጦርነት ድል ሲገኝ ደስታን በመዝሙር መግለጽ የተለመደ ነበር። እንደነዚህ ካሉት መዝሙሮች መካከል አንዱ፣ የሮቤልና የዳን እንዲሁም የአሴር ነገዶች ራሳቸውን በፈቃደኝነት አለማቅረባቸውን የሚያጋልጥ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የራሱን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በማሳየቱ የዛብሎንን ነገድ አወድሶታል። (መሳ. 5:16-18) በአንድ መዝሙር ውስጥ እንዳሉ ስንኞች ሁሉ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ድርጊትም ውሎ አድሮ በሌሎች ዘንድ መታወቁ አይቀርም። አንድ ሰው አምላክ የሰጠውን ሥራ በቅንዓት የሚያከናውን እንዲሁም ቲኦክራሲያዊ መመሪያዎችን በታማኝነት የሚከተል ከሆነ በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም የሚያተርፍ ከመሆኑም ሌላ ለወንድሞቹ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች በድርጊታችን አማካኝነት የተጻፈውን ምሳሌያዊ መዝሙር ሲያዳምጡ ይህንን መልካም ምግባራችንን ለመኮረጅ ይነሳሳሉ።

የመስክ አገልግሎት፣ በጊልያድ የሚሰጠው ሥልጠና ክፍል እንደመሆኑ መጠን የ124ኛው ክፍል ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ በነበራቸው ቆይታ በድምሩ ወደ 3,000 የሚጠጋ ሰዓት በስብከቱ ሥራ አሳልፈዋል። ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን በሚከታተለው ክፍል ውስጥ የሚሠራው ወንድም ሳም ሮበርሰን “መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ መከተል” በሚል ጭብጥ ባቀረበው ክፍል ላይ ተማሪዎቹ ከመስክ አገልግሎት ያገኟቸውን ተሞክሮዎች የተናገሩ ሲሆን አንዳንዶቹንም በሠርቶ ማሳያ መልክ አቅርበዋቸዋል። እነዚህ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች ከተሰሙ በኋላ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፓትሪክ ላፍራንካ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚያገለግሉ የጊልያድ ምሩቃን ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ። ተማሪዎቹ እነዚህ ወንድሞች ለሰጧቸው ጠቃሚ ምክሮች ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ደግሞ “የሚታዩት ነገሮች ጊዜያዊ መሆናቸውን አስታውሱ” በሚል ጭብጥ የመጨረሻውን ንግግር አቀረበ። ቅዱሳን መጻሕፍት ዛሬ በሚደርሱብን ጊዜያዊ መከራዎች ላይ ሳይሆን ይሖዋ ወደፊት በሚሰጠን በረከቶች ላይ እንድናተኩር ይመክሩናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) ሥር የሰደደ ድህነት፣ የፍትሕ መጓደል፣ ጭቆና፣ ሕመም እንዲሁም ሞት በዛሬው ጊዜ በየቦታው የሚታዩ ነገሮች ናቸው። ሚስዮናውያንም ከእነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች መካከል አንዳንዶቹ ሊደርሱባቸው ይችላሉ። ይሁንና እነዚህ ነገሮች ጊዜያዊ መሆናቸውን ማስታወሳችን መንፈሳዊ ሚዛናችንን ጠብቀን በተስፋ እንድንኖር ይረዳናል።

በፕሮግራሙ መደምደሚያ ላይ ተመራቂዎቹ በሙሉ መድረኩ ላይ ወጥተው ከተቀመጡ በኋላ ወንድም ሌት የመጨረሻ ምክር ሰጣቸው። ወንድም ሌት፣ ተስፋ እንዳይቆርጡ ካበረታታቸው በኋላ “ይሖዋ ከጎናችን እስካለ ድረስ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን በአቋማችን መጽናት እንችላለን” አላቸው። አዲሶቹ ሚስዮናውያን ይሖዋን በማገልገል ወደፊት እንዲገፉ እንዲሁም ለዘላለም ቀናተኞች፣ ታማኞችና ታዛዦች በመሆን እንደ አንበጦች እንዲሆኑ ተበረታተዋል።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ

ተማሪዎቹ የተውጣጡባቸው አገሮች ብዛት:- 7

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 16

የተማሪዎቹ ብዛት:- 56

አማካይ ዕድሜ:- 33.8

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 18.2

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 13.8

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 124ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) ታንያ ኒኮልሰን፣ ሄዘር ሜን፣ ዮኮ ሴንጌ፣ ሊንዳ ስኔፕ፣ ክሎዲያ ቫኔጋስ፣ ሊቲሻ ፖ (2) ሳንድራ ሳንታና፣ ክሪስተን ኦ፣ ክሪስቲን ለሜትረ፣ ኑሪያ ዊልያምዝ፣ ሊሳ አሊግዛንደር (3) ብሬንዳ ዉድዝ፣ ሊያ ስቴንተን፣ ኤምሊ ሀንትሊ፣ ግሎሪያ አልቫሬዝ፣ ጂልያን ክሩስ፣ ጆኣና ቤኔት (4) አዠር ዊልያምሰን፣ ኖኤሚ ጎንሳሌስ፣ ጄኒፈር ዙሮስኪ፣ ኢዛቤል ድሃንድ፣ ጄሲካ ሜይ፣ ስቺንትሲያ ዲየሚ፣ ሎረን ታቭነር (5) ዊልያም ለሜትረ፣ አሊሻ ሃሪስ፣ ሲንቲያ ዌልዝ፣ ሤራ ራጀርዝ፣ ማንዲ ዱራንት፣ ጁን ሴንጌ (6) ትሬቨር ሀንትሊ፣ አለን ቫኔጋስ፣ አንቶንዮ ፖ፣ ሞይሴስ ሳንታና፣ ቮን ቤኔት፣ ዴቪድ ታቭነር፣ ማይክል ኦ (7) ሚክ ዙሮስኪ፣ ጎርደን ራጀርዝ፣ ዳንኤል ዲየሚ፣ ሊ ኒኮልሰን፣ ካርሎስ አልቫሬዝ፣ ጃሽዋ ስኔፕ (8) ማት ሃሪስ፣ ፔትሮ ጎንሳሌስ፣ ሾን ሜን፣ ስቴፋንክ ዉድዝ፣ ብሬንት ስቴንተን፣ ድዌን ዊልያምሰን፣ ጃን ዱራንት (9) ፖል ክሩስ፣ ብሬክት ድሃንድ፣ ዳነልድ ዊልያምዝ፣ ሳይመን ዌልዝ፣ ዳን አሊግዛንደር፣ ማይካ ሜይ

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ ትምህርት ቤት በመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ውስጥ ይገኛል