ባልተከፋፈለ ልብ በታማኝነት መጽናት
ባልተከፋፈለ ልብ በታማኝነት መጽናት
“በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን እፈራ ዘንድ፣ ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ።”—መዝ. 86:11
1, 2. (ሀ) በመዝሙር 86:2, 11 ላይ እንደተገለጸው ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ለመጽናት የሚረዳን ምንድን ነው? (ለ) ከልብ የመነጨ ታማኝነት ማዳበር የሚገባን መቼ ነው?
እስራትም ሆነ ስደት ሳይበግራቸው ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት የጸኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከጊዜ በኋላ በፍቅረ ንዋይ የሚሸነፉት ለምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ከምሳሌያዊው ልባችን ማለትም ከውስጣዊ ማንነታችን ጋር የተያያዘ ነው። መዝሙር 86 ታማኝነትን ካልተከፋፈለ ወይም አንድ ከሆነ ልብ ጋር አያይዞ ገልጾታል። መዝሙራዊው ዳዊት “ለአንተ የተለየሁ [“ታማኝ፣” NW] ሰው ነኝና ነፍሴን ጠብቃት፤ አንተ አምላኬ ሆይ፤ በአንተ የታመነብህን ባሪያህን አድን” በማለት ጸልዮአል። ከዚህም በተጨማሪ ዳዊት “እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን እፈራ ዘንድ፣ ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” ሲል ጸልዮአል።—መዝ. 86:2, 11
2 በሙሉ ልባችን በይሖዋ የማንታመን ከሆነ ሌሎች ጉዳዮችና ለተለያዩ ነገሮች ያለን ፍቅር ለእውነተኛው አምላክ ያለንን ታማኝነት ሊያዳክሙብን ይችላሉ። ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸው ምኞቶች በመንገዳችን ላይ እንደተቀበሩ ፈንጂዎች ናቸው። ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ብንጸናም በሰይጣን ወጥመዶች ልንወድቅ እንችላለን። እንግዲያው ፈተናዎች እስኪያጋጥሙን ሳንጠብቅ አሁኑኑ ለይሖዋ ከልብ የመነጨ ታማኝነት ማዳበራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ” ይላል። (ምሳሌ 4:23) በዚህ ረገድ፣ የእስራኤል ንጉሥ ወደነበረው ወደ ኢዮርብዓም የተላከው የይሖዋ ነቢይ ካጋጠመው ነገር ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።
“ስጦታም አደርግልሃለሁ”
3. ኢዮርብዓም፣ የአምላክ ነቢይ የፍርድ መልእክት ሲነግረው ምን አደረገ?
3 እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል 1 ነገ. 13:1-6
ሞክር። አንድ የአምላክ ሰው፣ አሥሩን ነገዶች ባቀፈው በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የጥጃ አምልኮን ላቋቋመው ለንጉሥ ኢዮርብዓም ኃይለኛ መልእክት ተናግሮ ማብቃቱ ነው። ንጉሡ መልእክቱን ሲሰማ በጣም ስለተናደደ አገልጋዮቹ መልእክተኛውን እንዲይዙት ትእዛዝ ሰጠ። ሆኖም ይሖዋ፣ አገልጋዩን አልተወውም። ንጉሡ በንዴት የዘረጋው እጁ ወዲያው ደርቆ ቀረ፤ እንዲሁም ለሐሰት አምልኮ ያገለግል የነበረው መሠዊያ ተሰነጠቀ። በድንገት ኢዮርብዓም ጠባዩ ተለውጦ የአምላክን ሰው እንዲህ በማለት ይለማመጠው ጀመር:- “እጄ ወደ ቦታዋ እንድትመለስ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ለምንልኝ፤ ጸልይልኝም።” ነቢዩም ወደ ይሖዋ የጸለየ ሲሆን የንጉሡም እጅ ተፈወሰ።—4. (ሀ) ንጉሡ ለነቢዩ ያቀረበለት ግብዣ የነቢዩን ታማኝነት የሚፈትን ነበር የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ነቢዩ ምን ምላሽ ሰጠ?
4 ከዚያም ኢዮርብዓም የእውነተኛውን አምላክ ሰው “አብረኸኝ ወደ ቤት እንሂድ፤ አንድ ነገር ቅመስ፤ ስጦታም አደርግልሃለሁ” አለው። (1 ነገ. 13:7) ታዲያ ነቢዩ በዚህ ጊዜ ምን ያደርግ ይሆን? ንጉሡን የሚያወግዝ መልእክት ተናግሮ ሲያበቃ የንጉሡን ግብዣ መቀበል ይገባዋል? (መዝ. 119:113) ወይስ ንጉሡ የተጸጸተ ቢመስልም እንኳ ነቢዩ የንጉሡን ግብዣ ለመቀበል እንቢ ይበል? ኢዮርብዓም፣ ባለጠጋ በመሆኑ ለወዳጆቹ ውድ ስጦታዎች ሊሰጥ ይችል እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። የአምላክ ነቢይ በልቡ ቁሳዊ ነገሮችን ይመኝ ከነበረ የንጉሡ ግብዣ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንበት አይካድም። ሆኖም ይሖዋ፣ ነቢዩን “እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ” በማለት አዞታል። በመሆኑም ነቢዩ “ግማሽ ሀብትህን ብትሰጠኝ እንኳ፣ አብሬህ አልሄድም፤ እዚህ፣ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም” በማለት ቁርጥ ያለ መልስ ሰጠው። ከዚያም በሌላ አቅጣጫ ከቤቴል ወጥቶ ሄደ። (1 ነገ. 13:8-10) ይህ ነቢይ ያደረገው ውሳኔ ከልብ የመነጨ ታማኝነት በማሳየት ረገድ ምን ትምህርት ይሰጠናል?—ሮሜ 15:4
“ያ ይበቃናል”
5. ፍቅረ ንዋይ፣ ታማኝነታችንን የሚፈትነው እንዴት ነው?
5 ፍቅረ ንዋይ ከታማኝነት ጋር የሚያያዝ ነገር አይመስል ይሆናል፤ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው። ይሖዋ፣ የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች እንደሚሰጠን በገባው ቃል ላይ እምነት አለን? (ማቴ. 6:33፤ ዕብ. 13:5) “ጥሩ ኑሮ” እንዲኖረን የሚያስችሉንን ነገሮች ለመግዛት በአሁኑ ጊዜ አቅማችን ባይፈቅድልን፣ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከፍለን እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ይልቅ ያለ እነሱ ለመኖር ፈቃደኞች ነን? (ፊልጵስዩስ 4:11-13ን አንብብ።) በአሁኑ ጊዜ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለማግኘት ስንል ቲኦክራሲያዊ መብቶችን መሥዋዕት ለማድረግ እንፈተናለን? በሕይወታችን ውስጥ ቀዳሚውን ቦታ የሚይዘው ይሖዋን በታማኝነት ማገልገል ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ በአብዛኛው የሚመካው አምላክን የምናገለግለው በሙሉ ልባችን በመሆኑ ወይም ባለመሆኑ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እውነተኛ መንፈሳዊነት ባለን ነገር ከመርካት ጋር ትልቅ ትርፍ ነው። ምክንያቱም ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም። ነገር ግን ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል።”—1 ጢሞ. 6:6-8
6. ምን ዓይነት ‘ስጦታዎች’ ሊቀርቡልን ይችላሉ? እነዚህን ስጦታዎች መቀበል ይኖርብን እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰንስ ምን ሊረዳን ይችላል?
6 ለምሳሌ ያህል፣ አሠሪያችን የተሻለ ክፍያና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያስገኝ የሥራ እድገት ሊሰጠን እንዳሰበ ገለጸልን እንበል። አሊያም ደግሞ ሥራ ፍለጋ ወደ ሌላ አገር ወይም አካባቢ ብንሄድ ብዙ ገንዘብ እንደምናገኝ ይሰማን ይሆናል። መጀመሪያ ላይ እንደነዚህ ያሉት አጋጣሚዎች የይሖዋ በረከት እንደሆኑ እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት እንዲህ ለማድረግ የፈለግነው ለምን እንደሆነ ራሳችንን መመርመር አይገባንም? በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው “የማደርገው ውሳኔ ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና የሚነካው እንዴት ነው?” የሚለው ጉዳይ ነው።
7. ቁሳዊ ነገሮችን የመመኘት ዝንባሌን ሙሉ በሙሉ ማስወገዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 የሰይጣን ዓለም ምንጊዜም የሚያበረታታን ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ እንድንሰጥ ነው። (1 ዮሐንስ 2:15, 16ን አንብብ።) ዲያብሎስ ልባችንን መበከል ይፈልጋል። በመሆኑም በልባችን ውስጥ ቁሳዊ ነገሮችን የመመኘት ዝንባሌ መኖር አለመኖሩን ማጣራትና እንዲህ ያለውን ዝንባሌ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ንቁ መሆን አለብን። (ራእይ 3:15-17) ኢየሱስ፣ የዓለምን መንግሥታት በሙሉ እንደሚሰጠው ሰይጣን ያቀረበለትን ግብዣ ላለመቀበል ምንም አልተቸገረም። (ማቴ. 4:8-10) ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል:- “የሰው ሕይወቱ በሀብቱ ብዛት የተመሠረተ ስላልሆነ፣ ተጠንቀቁ፤ ከስግብግብነትም ሁሉ ራሳችሁንም ጠብቁ።” (ሉቃስ 12:15) ታማኝነት በራሳችን ሳይሆን በይሖዋ ላይ እንድንታመን ያደርገናል።
አንድ አረጋዊ ነቢይ ‘ዋሸው’
8. የአምላክ ነቢይ ታማኝነት የተፈተነው እንዴት ነበር?
8 የአምላክ ነቢይ ወደ አገሩ መጓዙን ቢቀጥል ኖሮ ጥሩ ይሆንለት ነበር። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ሌላ ፈተና አጋጠመው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “በቤቴል የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነቢይ ነበር፤ ልጆቹም መጥተው በዚያች ዕለት . . . [የተከናወነውን ሁሉ] ነገሩት።” ሽማግሌው ነቢይ ይህን ሲሰማ የአምላክን ነቢይ ለማግኘት ስለፈለገ ልጆቹ አህያውን እንዲጭኑለት ጠየቃቸው። ብዙም ሳይቆይ አረጋዊው ነቢይ፣ የአምላክን ሰው በአንድ የወርካ ዛፍ ሥር ተቀምጦ አገኘውና “አብረን ወደ ቤት እንሂድና ምግብ ብላ” አለው። የእውነተኛው አምላክ ሰው ግብዣውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ሲናገር ሽማግሌው ነቢይ “እኔም እኮ እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ አረጋዊው ነቢይ የተናገረው ‘ውሸት እንደነበር’ ይገልጻል።—1 ነገ. 13:11-18
9. ቅዱሳን መጻሕፍት ውሸታም ስለሆኑ ሰዎች ምን ይላሉ? እንደዚህ ያሉት ሰዎች የሚጎዱትን ማንን ነው?
9 አረጋዊው ነቢይ እንዲህ ያደረገበትን ምክንያት ባናውቅም የተናገረው ነገር ውሸት ነበር። ይህ አረጋዊ ሰው በአንድ ወቅት ታማኝ የይሖዋ ነቢይ የነበረ ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ግን ዋሽቷል። ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ያለውን ባሕርይ በጥብቅ ያወግዛሉ። (ምሳሌ 6:16, 17ን አንብብ።) እንደዚህ ነቢይ ያሉ ውሸታሞች ከይሖዋ ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚበላሽ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ይጎዳሉ።
ከአረጋዊው ጋር ‘አብሮ ተመለሰ’
10. የአምላክ ነቢይ፣ አረጋዊው ሰው ላቀረበለት ግብዣ ምን ምላሽ ሰጠ? ውጤቱስ ምን ሆነ?
10 ከይሁዳ የመጣው ነቢይ፣ በአረጋዊው ነቢይ ዘዴ ሊታለል አይገባም ነበር። ይህ ነቢይ፣ ‘ይሖዋ ለእኔ አዲስ መመሪያ ለመስጠት መልአኩን ወደ ሌላ ሰው መላክ ለምን አስፈለገው?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይችል ነበር። በተጨማሪም ነቢዩ፣ መመሪያውን ግልጽ እንዲያደርግለት ይሖዋን መጠየቅ ይችል ነበር፤ ሆኖም ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ ማድረጉን አይገልጹም። ከዚህ በተቃራኒ ይህ ነቢይ ከሽማግሌው ጋር ‘አብሮት ተመልሶ በቤቱ እንደበላና እንደጠጣ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ በዚህ ሁኔታ አልተደሰተም። የተታለለው ነቢይ ወደ ቤቱ ሲመለስ መንገድ ላይ አንበሳ አግኝቶ ገደለው። የነቢይነት ተልእኮው 1 ነገ. 13:19-25 *
በዚህ መንገድ መደምደሙ ምንኛ አሳዛኝ ነው!—11. አኪያ ምን ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል?
11 በሌላ በኩል ግን ኢዮርብዓምን ንጉሥ አድርጎ እንዲቀባው ተልኮ የነበረው ነቢዩ አኪያ በእርጅናው ዘመንም ቢሆን ታማኝ ነበር። አኪያ አርጅቶና ዓይኖቹ ታውረው በነበረበት ወቅት ኢዮርብዓም ስለታመመው ልጃቸው እንድትጠይቅ ሚስቱን ወደዚህ ነቢይ ልኳት ነበር። አኪያም የኢዮርብዓም ልጅ እንደሚሞት በድፍረት ተናግሯል። (1 ነገ. 14:1-18) አኪያ ካገኘው በረከት መካከል በመንፈስ አነሳሽነት ለተጻፈው የአምላክ ቃል አስተዋጽኦ የማድረግ መብት ማግኘቱ የሚጠቀስ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አኪያ የጻፋቸውን አንዳንድ ዘገባዎች ከጊዜ በኋላ ካህኑ ዕዝራ መጽሐፉን ባጠናቀረበት ወቅት ተጠቅሞባቸዋል።—2 ዜና 9:29 የ1980 ትርጉም
12-14. (ሀ) ወጣቱ ነቢይ ካጋጠመው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ሽማግሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው በሚሰጡት ምክር ላይ በቁም ነገር ማሰብ እንዲሁም ጉዳዩን አስመልክቶ መጸለይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።
12 ወጣቱ ነቢይ ወደኋላ ተመልሶ ከሽማግሌው ነቢይ ጋር ከመብላቱና ከመጠጣቱ በፊት ይሖዋን ለምን እንዳላማከረ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ምናልባት ሽማግሌው ነቢይ የተናገረው፣ ወጣቱ ነቢይ መስማት ይፈልግ የነበረውን ነገር ይሆን? ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? የይሖዋ መመሪያዎች ትክክለኛ ስለመሆናቸው ሙሉ እምነት ሊኖረን ይገባል። እንዲሁም ምንም ነገር ቢመጣ እነዚህን መመሪያዎች ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።
13 አንዳንዶች ምክር በሚሰጣቸው ወቅት የሚሰሙት፣ መስማት የሚፈልጉትን ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አስፋፊ ከቤተሰቡ ጋር እንዲሁም ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን የሚያሳልፈውን ጊዜ የሚሻማበት ሥራ አገኘ እንበል። ይህ ወንድም ምክር እንዲሰጠው አንድን ሽማግሌ ይጠይቅ ይሆናል። ሽማግሌው በውይይቱ መጀመሪያ ላይ፣ ወንድም ቤተሰቡን እንዴት መርዳት እንዳለበት መናገር የእሱ ቦታ እንዳልሆነ ይገልጽ ይሆናል። ከዚያም ሽማግሌው፣ ይህ ወንድም የቀረበለትን ሥራ መቀበሉ የሚያስከትላቸውን መንፈሳዊ አደጋዎች አንስቶ ያወያየው ይሆናል። ይህ ወንድም የሚያስታውሰው ሽማግሌው መጀመሪያ ላይ የሰጠውን ሐሳብ ብቻ ነው ወይስ ከዚያ ቀጥሎ የተወያዩባቸውን ነጥቦች በቁም ነገር ይመለከታቸዋል? ወንድም በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚጠቅመውን አገናዝቦ መወሰን እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው።
14 ሌላ ሁኔታ ደግሞ እንመልከት። አንዲት እህት የይሖዋ ምሥክር ካልሆነው ባሏ ጋር መለያየት ይኖርባት እንደሆነ አንድን ሽማግሌ ትጠይቀው ይሆናል። ሽማግሌው፣ ከባሏ ለመለያየት ወይም ላለመለያየት ውሳኔ ማድረግ ያለባት 1 ቆሮ. 7:10-16) ይህቺ እህት፣ ሽማግሌው ለሰጣት ሐሳብ ትኩረት ትሰጠው ይሆን? ወይስ ቀድሞውንም ቢሆን ከባሏ ጋር ለመለያየት ወስናለች? ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ሽማግሌው በሰጣት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ላይ በቁም ነገር ማሰቧ የጥበብ አካሄድ ነው።
ራሷ መሆኗን እንደሚገልጽላት ጥርጥር የለውም። አክሎም መለያየትን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በመጥቀስ ያወያያት ይሆናል። (ትሑት ሁኑ
15. የአምላክ ነቢይ ከሠራው ስህተት ምን ትምህርት እናገኛለን?
15 ከይሁዳ የመጣው ነቢይ ከሠራው ስህተት ምን ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን? ምሳሌ 3:5 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” ይላል። ከይሁዳ የመጣው ነቢይ፣ ከዚያ ቀደም ያደርገው እንደነበረው በይሖዋ ከመታመን ይልቅ በዚህ ወቅት በራሱ ማስተዋል ታምኗል። የሠራው ስህተት ሕይወቱን እንዲሁም በአምላክ ዘንድ የነበረውን መልካም ስም እንዲያጣ አድርጎታል። በዚህ ነቢይ ላይ የደረሰው ነገር ይሖዋን በትሕትና እንዲሁም በታማኝነት የማገልገልን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው!
16, 17. ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?
16 ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት የልባችን ዝንባሌ በተሳሳተ መንገድ ሊመራን ይችላል። “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም።” (ኤር. 17:9) ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ለመቀጠል እንድንችል የኩራትና በራስ የመመራት ዝንባሌ እንዲኖረን የሚገፋፋንን አሮጌውን ሰው አውልቀን ለመጣል የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና [“ታማኝነት፣” NW] እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” መልበስ ይገባናል።—ኤፌሶን 4:22-24ን አንብብ።
17 ምሳሌ 11:2 “በትሑት ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። ትሑት በመሆን በይሖዋ ላይ መታመናችን ከባድ ስህተቶችን እንዳንሠራ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ተስፋ መቁረጥ የማመዛዘን ችሎታችን በቀላሉ እንዲዛባ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 24:10 NW) በአንድ የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ መሳተፍ ሊሰለቸንና ባለፉት ዓመታት የሠራነው በቂ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል፤ ምናልባትም ሸክሙን ሌሎች ሊሸከሙት እንደሚገባ እናስብ ይሆናል። አሊያም ደግሞ “እንደ ሌሎች ሰዎች” ለመኖር እንመኝ ይሆናል። ይሁን እንጂ ‘ተጋድሎ ማድረጋችን’ እንዲሁም ‘ለጌታ ሥራ ዘወትር መትጋታችን’ ልባችንን ለመጠበቅ ይረዳናል።—ሉቃስ 13:24 የ1954 ትርጉም፤ 1 ቆሮ. 15:58
18. ውሳኔ ለማድረግ በምንቸገርበት ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን?
18 አንዳንድ ጊዜ ውሳኔ የሚጠይቁ ከበድ ያሉ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ልንወስደው የሚገባው ትክክለኛ እርምጃ ምን እንደሆነ ግልጽ ላይሆንልን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ለራሳችን ትክክል መስሎ በታየን መንገድ ችግሩን ለመፍታት እንፈተናለን? በዚህ ወቅት የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት መጸለያችን የጥበብ እርምጃ ነው። ያዕቆብ 1:5 “ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ . . . በልግስና ለሁሉም የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን” ይላል። በሰማይ ያለው አባታችን ትክክለኛ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ቅዱስ መንፈሱን ይሰጠናል። —ሉቃስ 11:9, 13ን አንብብ።
በታማኝነት ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ
19, 20. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል?
19 ሰሎሞን እውነተኛውን አምልኮ ከተወ በኋላ በነበሩት ሁከት የነገሠባቸው ዓመታት የአምላክ አገልጋዮች ታማኝነታቸውን በእጅጉ የሚፈታተን ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። በዚያ ወቅት ከእስራኤላውያን መካከል ብዙዎቹ ታማኝነታቸውን ማጉደላቸው የማይካድ ቢሆንም አንዳንዶች ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ጸንተዋል።
20 እኛም ታማኝነታችንን የሚፈታተኑ ምርጫዎችና ውሳኔዎች በየዕለቱ ያጋጥሙናል። ያም ቢሆን በታማኝነት መጽናት እንችላለን። ይሖዋ ታማኞቹን መባረኩን እንደሚቀጥል ሙሉ በሙሉ በመተማመን ልባችን ሳይከፋፈል ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ እንሁን።—2 ሳሙ. 22:26
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.10 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አረጋዊውን ነቢይ ይሖዋ በሞት ቀጥቶት ይሁን አይሁን የሚገልጸው ነገር የለም።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ቁሳዊ ነገሮችን የመመኘት ዝንባሌን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
• ለይሖዋ ታማኝ ሆነን ለመጽናት ምን ሊረዳን ይችላል?
• ትሕትና ለይሖዋ ታማኝ ሆነን እንድንጸና ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈተናዎችን መቋቋም ያስቸግርሃል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ሲሰጥህ ጉዳዩን በጸሎት ታስብበታለህ?