በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በማንበብ ተጠቅመሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

• አንዳንድ ክርስቲያኖች ትዳር ከመሠረቱ በኋላ ምን ከባድ ችግር አጋጥሟቸዋል? በዚህ ጊዜ ምን ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል?

አንዳንድ ክርስቲያኖች የእነሱና የትዳር ጓደኛቸው ፍላጎት እንደማይጣጣም ይገነዘባሉ። እንዲህ ያለ ችግር የገጠማቸው ባለትዳሮች ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ ምክንያት መፋታት ለችግሩ መፍትሔ እንደማይሆን በመገንዘብ ትዳራቸው እንዳይፈርስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል።—4/15 ገጽ 17

• በመጦሪያ ተቋም ውስጥ የሚኖሩ አንድ አረጋዊ ክርስቲያን ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?

አንድ አረጋዊ ክርስቲያን ያሉበት የመጦሪያ ተቋም የሚገኘው በሌላ ጉባኤ ክልል ውስጥ ሊሆን ይችላል፤ እሳቸው ደግሞ በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኘውን ጉባኤ አያውቁት ይሆናል። በተቋሙ ውስጥ የሚኖሩት አብዛኞቹ ሰዎች ከእኚህ ወንድም የተለየ እምነት ይኖራቸው ይሆናል፤ እንዲሁም አረጋዊውን ወንድም በአንዳንድ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ ለማድረግ ይሞክሩ ይሆናል። ክርስቲያን የሆኑ የእኚህ ወንድም ዘመዶች እንዲሁም በአካባቢው ባለ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች እንዲህ ዓይነት ችግሮች መኖራቸውን ሊገነዘቡ እንዲሁም ድጋፍና እንክብካቤ ሊያደርጉላቸው ይገባል።—4/15 ገጽ 25-27

• የትዳር ጓደኛሞች ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ ሊረዷቸው የሚችሉት አራት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

በችግሩ ላይ ለመወያየት ጊዜ መድቡ። (መክ. 3:1, 7) ስሜታችሁን በሐቀኝነት እንዲሁም አክብሮት በተሞላበት መንገድ ተናገሩ። (ኤፌ. 4:25) የትዳር ጓደኞቻችሁን ለማዳመጥ እንዲሁም ስሜታቸውን ለመረዳት ሞክሩ። (ማቴ. 7:12) በመፍትሔ ሐሳብ ላይ ተስማሙ፤ እንዲሁም ተባብራችሁ ሥሩ። (መክ. 4:9, 10)—5/1 ገጽ 10-12

• የበላይ አካሉ አባላት በየትኞቹ ኮሚቴዎች ውስጥ ያገለግላሉ?

የአስተባባሪዎች ኮሚቴ፣ የፐርሶኔል ኮሚቴ፣ የኅትመት ኮሚቴ፣ የአገልግሎት ኮሚቴ፣ የትምህርት ኮሚቴና የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ።—5/15 ገጽ 29

• የኖኅ የጥፋት ውኃ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንደነበረው እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

ኢየሱስ የጥፋት ውኃ እንደተከሰተ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንደነበረው ያምን ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጹት ማስጠንቀቂያዎች ይህን የጥፋት ውኃ መሠረት በማድረግ የተነገሩ ናቸው።—6/1 ገጽ 8

በሮሜ 1:24-32 ላይ የተገለጸውን ድርጊት ይፈጽሙ የነበሩት አይሁዳውያን ናቸው ወይስ አሕዛብ?

ጥቅሱ ላይ የተገለጸውን ወራዳ ድርጊት የሚፈጽሙት ሁለቱም ወገኖች ሊሆኑ ቢችሉም ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረው ለበርካታ ዘመናት ሕጉን ይጥሱ ስለነበሩት ስለ ጥንቶቹ እስራኤላውያን ነበር። እነዚህ ሕዝቦች የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ቢያውቁም ሕግጋቱን አልተከተሉም።—6/15 ገጽ 29

• ቴል ዓራድ የምትገኘው የት ነው? በዚያ የተገኙ የአርኪኦሎጂ ግኝቶች ምን ጠቀሜታ አላቸው?

የጥንቷ የዓራድ ከተማ ትገኝበት የነበረውን ቦታ የሚያመለክተው ይህ የፍርስራሽ ክምር ከሙት ባሕር በስተ ምዕራብ ይገኛል። አርኪኦሎጂስቶች በዚህ አካባቢ ለመጻፊያነት ያገለግሉ የነበሩ የሸክላ ስብርባሪዎችን አግኝተዋል። ከእነዚህ ስብርባሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ስም እንዲሁም የአምላክን የግል ስም ይዘዋል።—7/1 ገጽ 23-24

• ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆናችን የበለጠ ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል የምንለው ለምንድን ነው?

የሚጠይቁብን መሥዋዕትነት ምንም ይሁን ምን ምክንያታዊነት እንደጎደለን የሚያሳዩ ግቦች የምናወጣ ከሆነ ራሳችንን አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ እንጨምራለን። ይህ ሲባል ግን አቅማችንን እንደሚገድቡብን የምናስባቸውን ነገሮች ሰበብ በማድረግ በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ እንዳንቀንስ መጠንቀቅ አለብን።—7/15 ገጽ 29

• ወላጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻቸው ጋር የሐሳብ ልውውጥ እንዳያደርጉ እንቅፋት የሚሆንባቸው ምን ሊሆን ይችላል?

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ዝምተኛና ዓይን አፋር መሆኑ እንዲሁም ራሱን ችሎ ለመኖርና ለብቻው ለመሆን መፈለጉ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዳይኖር እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ወላጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኝ ልጃቸው ጋር አብረው ጊዜ ማሳለፋቸውና ልጁ ከሚናገረው ሐሳብ በስተጀርባ ያለውን ነገር ለማስተዋል መሞከራቸው ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ይረዳቸው ይሆናል።—8/1 ገጽ 10-11