በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ንጹሑን ቋንቋ’ አጥርተህ ትናገራለህ?

‘ንጹሑን ቋንቋ’ አጥርተህ ትናገራለህ?

‘ንጹሑን ቋንቋ’ አጥርተህ ትናገራለህ?

“ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩ . . . ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።”—ሶፎ. 3:9 NW

1. ይሖዋ ምን ታላቅ ስጦታ ሰጥቶናል?

ቋንቋ፣ ሰዎች የፈጠሩት ነገር ሳይሆን የሰው ዘር ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ የተገኘ ስጦታ ነው። (ዘፀ. 4:11, 12) ይሖዋ፣ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም የመናገር ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ቃላትን የመፍጠር ችሎታም ሰጥቶት ነበር፤ ይህም አዳም የሚያውቃቸው ቃላት ብዛት እየጨመረ እንዲሄድ አድርጓል። (ዘፍ. 2:19, 20, 23) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ስጦታ ነው! ይህ ስጦታ የሰው ልጆች በሰማይ ከሚኖረው አባታቸው ጋር ለመነጋገር እንዲሁም የይሖዋን ታላቅ ስም ለማወደስ አስችሏቸዋል።

2. የሰው ልጆች አንድ ቋንቋ መናገር ያቆሙት ለምንድን ነው?

2 የሰው ልጅ ከተፈጠረ በኋላ በነበሩት 1,700 ዓመታት ውስጥ ሁሉም ሰው የሚናገረው አንድ ቋንቋ ነበር። (ዘፍ. 11:1) ከዚያም በናምሩድ ዘመን ሰዎች ዓመፁ። ታዛዥ ያልሆኑ የሰው ልጆች፣ ይሖዋ የሰጣቸውን መመሪያ በመቃረን በምድር ላይ ሳይበተኑ በአንድ ቦታ ላይ ተወስነው ለመኖር ስለፈለጉ ከጊዜ በኋላ ባቤል ተብሎ በተጠራው ቦታ ላይ ተሰባሰቡ። በዚያም አንድ ግዙፍ ግንብ መሥራት ጀመሩ፤ ይህንንም ያደረጉት ለይሖዋ ክብር ለመስጠት ሳይሆን ‘ለስማቸው መጠሪያ እንዲሆን’ ነበር። በዚህም ምክንያት ይሖዋ እነዚህ ዓመፀኞች የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲናገሩ አደረጋቸው። ሰዎቹ ቋንቋቸው ስለተደበላለቀባቸው በምድር ሁሉ ላይ ተበተኑ።—ዘፍጥረት 11:4-8ን አንብብ።

3. ይሖዋ፣ በባቤል የነበሩትን ዓመፀኞች ቋንቋ በደበላለቀበት ወቅት ምን ተፈጠረ?

3 በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ አንዳንዶች በዓለም ላይ ያሉት ቋንቋዎች ከ6,800 እንደሚበልጡ ይገምታሉ። እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩት ሰዎች የሚያስቡበት መንገድ የተለያየ ነው። ከዚህ ለመረዳት እንደምንችለው ይሖዋ የእነዚያን ዓመፀኞች ቋንቋ በደበላለቀበት ወቅት ከዚያ በፊት ይናገሩት የነበረውን ቋንቋ ሙሉ በሙሉ እንዲረሱት ያደረጋቸው ይመስላል። ይሖዋ፣ እነዚህ ሰዎች አዳዲስ ቃላትን እንዲያውቁ ከማድረጉም በላይ የሚያስቡበት መንገድ እንዲቀየርና አዲስ የቋንቋ ሰዋስው እንዲኖራቸው አድርጓል። በእርግጥም ግንቡ የተሠራበት ቦታ “መደባለቅ” ወይም ባቤል ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስገርምም! (ዘፍ. 11:9 የ1980 ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ለሚነገሩት በርካታ ቋንቋዎች መፈጠር ምክንያቱ ምን እንደሆነ አጥጋቢ በሆነ መንገድ መልስ የሚሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።

አዲስ የሆነ ንጹሕ ቋንቋ

4. ይሖዋ በዘመናችን ምን እንደሚከናወን ትንቢት አስነግሯል?

4 አምላክ በባቤል ጣልቃ ገብቶ ስለወሰደው እርምጃ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አስገራሚ ቢሆንም በዘመናችን ከዚያ ይበልጥ ትኩረት የሚስብና በጣም ጠቃሚ የሆነ ክንውን ተፈጽሟል። ይሖዋ በነቢዩ ሶፎንያስ አማካኝነት እንዲህ የሚል ትንቢት አስነግሯል:- “በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩና አንድ ሆነው እንዲያገለግሉት ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።” (ሶፎ. 3:9 NW) ይህ “ንጹሕ ቋንቋ” ምንድን ነው? ይህን ቋንቋ አጥርተን መናገር የምንችለውስ እንዴት ነው?

5. ንጹሕ ቋንቋ የተባለው ምንድን ነው? ይህ የቋንቋ ለውጥ ምን ውጤት አምጥቷል?

5 ንጹሕ ቋንቋ፣ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውና ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲሁም ስለ ዓላማዎቹ የሚናገረው እውነት ነው። ይህ “ቋንቋ” ስለ አምላክ መንግሥት እንዲሁም ይህ መንግሥት የይሖዋን ስም የሚያስቀድሰው፣ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጠውና ታማኝ ለሆኑ የሰው ልጆች ዘላለማዊ በረከት የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ የሚገልጸውን ትክክለኛ እውቀት ያጠቃልላል። ሰዎች ቋንቋቸው በዚህ መንገድ መለወጡ ምን ውጤት ያስገኛል? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ‘የይሖዋን ስም እንደሚጠሩ’ እንዲሁም ‘አንድ ሆነው እንደሚያገለግሉት’ ይነግረናል። በባቤል ከተከሰተው ሁኔታ በተቃራኒ ሰዎች ቋንቋቸው ወደ ንጹሕ ቋንቋ መለወጡ፣ የይሖዋ ስም እንዲቀደስ እንዲሁም በሕዝቦቹ መካከል አንድነት እንዲኖር አድርጓል።

ንጹሑን ቋንቋ መማር

6, 7. (ሀ) አዲስ ቋንቋ መማር ምን ማድረግን ይጠይቃል? ንጹሑን ቋንቋ ከመማር ጋር በተያያዘ ይህ የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እየተመለከትን እንሄዳለን?

6 አንድ ሰው አዲስ ቋንቋ መማር ከፈለገ አዳዲስ ቃላትን ከማጥናት የበለጠ ነገር ማድረግ ይኖርበታል። አዲስ ቋንቋ ለመማር፣ ከቀድሞ በተለየ መንገድ ማሰብን መልመድ ያስፈልጋል። ሰዎች ሐሳባቸውን የሚገልጹበትና ቀልድ የሚናገሩበት መንገድ እንደየቋንቋው ይለያያል። አዳዲስ ድምጾች ለማውጣት ምላስን ጨምሮ ሌሎች የአንደበታችንን ክፍሎችን በተለየ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል። ንጹሕ ቋንቋ የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መማር ስንጀምርም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንዲህ ማድረግ መሠረታዊ የሆኑ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ከማወቅ የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ይህን አዲስ ቋንቋ ጠንቅቀን ለማወቅ በአስተሳሰባችን ላይ ለውጥ ማድረግ እንዲሁም በአእምሯችን መታደስ ይኖርብናል።—ሮሜ 12:2ን እና ኤፌሶን 4:23ን አንብብ።

7 ንጹሑን ቋንቋ ከመረዳትም አልፈን አጥርተን ለመናገር እንድንችል ምን ሊረዳን ይችላል? ማንኛውንም ቋንቋ ለመማር የሚረዱ አንዳንድ ዘዴዎች እንዳሉ ሁሉ ንጹሕ ቋንቋ የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አጥርቶ ለመናገርም የሚረዱን መሠረታዊ የሆኑ ዘዴዎች አሉ። ሌላ ቋንቋ የሚማሩ ሰዎች የሚጠቀሙባቸውን አንዳንድ መሠረታዊ ዘዴዎች በመመርመር እነዚህ ዘዴዎች ይህንን ምሳሌያዊ የሆነ አዲስ ቋንቋ ለመማር እንዴት እንደሚረዱን እስቲ እንመልከት።

ንጹሑን ቋንቋ አጥርቶ መናገር

8, 9. ንጹሑን ቋንቋ ለመማር ከፈለግን ምን ማድረግ አለብን? ይህን ማድረጋችንስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 በጥሞና አዳምጥ። አንድ ሰው ከዚህ ቀደም ሰምቶት የማያውቀውን ቋንቋ በሚሰማበት ጊዜ ፈጽሞ የማይገባ ነገር ይመስለው ይሆናል። (ኢሳ. 33:19) ይሁንና ግለሰቡ በሚሰማው ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ እየለመደ ሲመጣ አንዳንድ ቃላትን መረዳት እንዲሁም የተናጋሪዎቹን የአነጋገር ዘዬ ልብ ማለት ይጀምራል። በተመሳሳይ እኛም “ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ [‘ከወትሮው የተለየ ትኩረት ልንሰጥ፣’ NW] ይገባናል” የሚል ምክር ተሰጥቶናል። (ዕብ. 2:1) ኢየሱስ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” በማለት ተከታዮቹን በተደጋጋሚ ጊዜያት አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 11:15፤ 13:43፤ ማር. 4:23፤ ሉቃስ 14:35) በእርግጥም፣ ስለ ንጹሑ ቋንቋ ያለን ግንዛቤ እየሰፋ እንዲሄድ ‘መስማት’ እንዲሁም የሰማነውን ነገር ‘ማስተዋል’ ይኖርብናል።—ማቴ. 15:10፤ ማር. 7:14

9 ማዳመጥ፣ ትኩረት ማድረግን የሚጠይቅ ነገር ቢሆንም በዚህ ረገድ ጥረት ማድረጉ የሚክስ ነው። (ሉቃስ 8:18 NW) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በምንገኝበት ጊዜ እየተብራራ ያለውን ትምህርት በትኩረት እናዳምጣለን ወይስ ሐሳባችን ይከፋፈላል? የሚቀርበውን ትምህርት በትኩረት ለመከታተል የተቻለንን ሁሉ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ የማናደርግ ከሆነ ጆሮዎቻችን ሊፈዝዙ ይችላሉ።—ዕብ. 5:11 የ1954 ትርጉም

10, 11. (ሀ) በጥሞና ከማዳመጥ በተጨማሪ ምን ማድረግ አለብን? (ለ) ንጹሑን ቋንቋ መናገር ምን ነገሮችን ይጨምራል?

10 ቋንቋውን አጥርተው የሚናገሩ ሰዎችን ኮርጅ። አዲስ ቋንቋ የሚማሩ ሰዎች በጥሞና እንዲያዳምጡ ብቻ ሳይሆን ቋንቋውን አጥርተው የሚናገሩ ሰዎች ቃላትን የሚጠሩበትን መንገድ እንዲሁም የሰዎቹን የአነጋገር ዘዬ እንዲኮርጁ ይበረታታሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ከጊዜ በኋላ ተማሪዎቹ ቋንቋውን በሚናገሩበት ወቅት ከሌሎች ጋር ለመግባባት እንቅፋት የሚሆንባቸውን ቃላትን በተሳሳተ መንገድ የመጥራት ልማድ እንዳያዳብሩ ይረዳቸዋል። እኛም በተመሳሳይ አዲሱን ቋንቋ “በማስተማር” ረገድ ውጤታማ ከሆኑ ሰዎች ለመማር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 4:2) እንዲህ ያሉ ሰዎች እንዲረዱህ ጠይቅ። ስሕተት ስትሠራ የሚሰጥህን እርማት ለመቀበል ፈቃደኛ ሁን።—ዕብራውያን 12:5, 6, 11ን አንብብ።

11 ንጹሑን ቋንቋ መናገር፣ እውነትን አምኖ መቀበልንና ይህንንም እውነት ለሌሎች ማስተማርን ብቻ ሳይሆን አኗኗራችንን ከአምላክ ሕግና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ማስማማትንም ይጨምራል። ይህን ለማድረግ የሌሎችን መልካም አኗኗር ልብ ብለን ማየትና መኮረጅ ይኖርብናል። ይህም በእምነታቸውና በቅንዓታቸው እነሱን መምሰልን ይጨምራል፤ ከዚህም በላይ ኢየሱስ በሕይወቱ ሙሉ የተከተለውን አካሄድ መኮረጅን ያጠቃልላል። (1 ቆሮ. 11:1፤ ዕብ. 12:2፤ 13:7) እንዲህ ማድረጋችንን መቀጠላችን በአምላክ ሕዝቦች መካከል አንድነት እንዲኖር ከማድረጉም በላይ ንጹሑን ቋንቋ በአንድ ዓይነት መንገድ ለመናገር ያስችላል።—1 ቆሮ. 4:16, 17

12. አንዳንድ ነገሮችን በቃል ማጥናት አዲስ ቋንቋን በመማር ረገድ ምን ሚና አለው?

12 በቃልህ አጥና። ቋንቋ የሚማሩ ሰዎች በርካታ አዳዲስ ነገሮችን በአእምሯቸው መያዝ ይኖርባቸዋል። ይህም አዳዲስ ቃላትንና አገላለጾችን በቃላቸው ማጥናትን ይጨምራል። ክርስቲያኖችም አንዳንድ ነገሮችን በቃላቸው ማጥናታቸው ንጹሑን ቋንቋ አጥርተው መናገር እንዲችሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ስሞች በቅደም ተከተላቸው በቃላችን ለመያዝ መጣራችን ጠቃሚ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንዶች፣ የተወሰኑ ጥቅሶችን ሐሳብ ወይም የአንዳንድ ጥቅሶችን ምዕራፍና ቁጥር በአእምሯቸው የመያዝ ግብ አውጥተዋል። ሌሎች ደግሞ የእስራኤልን ነገዶችና የ12ቱን ሐዋርያት ስም፣ የመንግሥቱን መዝሙሮች እንዲሁም በመንፈስ ፍሬ ውስጥ የሚካተቱትን ባሕርያት በቃላቸው ማጥናት ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በጥንት ጊዜ ብዙ እስራኤላውያን በርካታ መዝሙራትን በቃላቸው ያጠኑ ነበር። በዘመናችን ደግሞ አንድ ትንሽ ልጅ ገና በስድስት ዓመቱ ከ80 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃሉ መያዝ ችሏል። ታዲያ እኛስ ይህንን ጠቃሚ የሆነ ችሎታ በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት እንችላለን?

13. መደጋገም በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 መደጋገም ነገሮችን ለማስታወስ ይረዳል፤ ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር በተያያዘም ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ መሰጠቱ በጣም አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች ብታውቋቸውና በያዛችሁት እውነት ብትጸኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች እናንተን ዘወትር ከማሳሰብ ቸል አልልም።” (2 ጴጥ. 1:12) ማሳሰቢያዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው? ጥልቀት ያለው እውቀት እንዲኖረንና አመለካከታችን እንዲሰፋ እንዲሁም ይሖዋን ለመታዘዝ ያደረግነው ቁርጥ ውሳኔ እንዲጠናከር ስለሚረዱን ነው። (መዝ. 119:129) አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች በየጊዜው መከለሳችን ራሳችንን ለመመርመር እንዲሁም ‘ሰምቶ የመርሳትን’ ዝንባሌ ለማስወገድ ይረዳናል። (ያዕ. 1:22-25) ስለ እውነት ዘወትር የማናስብ ከሆነ ሌሎች ነገሮች በአስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ ስለሚያደርጉ ንጹሑን ቋንቋ አጥርተን መናገር ሊያቅተን ይችላል።

14. ንጹሑን ቋንቋ በምናጠናበት ጊዜ ምን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው?

14 ጮክ ብለህ አንብብ። (ራእይ 1:3 NW) አዲስ ቋንቋ የሚማሩ አንዳንድ ሰዎች ድምጻቸውን ሳያሰሙ ለማጥናት ይሞክራሉ። ይህ ግን ጥሩ ውጤት አያስገኝም። ከዚህ በተለየ መልኩ ንጹሑን ቋንቋ በምናጠናበት ወቅት ትኩረታችን እንዳይሰረቅ አንዳንድ ጊዜ ‘ድምጻችንን አውጥተን ማንበብ’ ይኖርብን ይሆናል። (መዝሙር 1:1, 2 NWን አንብብ። *) እንዲህ ማድረጋችን የምናነበው ነገር ከአእምሯችን ውስጥ በማይጠፋ መንገድ እንዲቀረጽ ይረዳናል። በዕብራይስጥ ‘ድምጽን አውጥቶ ማንበብ’ የሚለው አገላለጽ ከማሰላሰል ጋር ተቀራራቢ ትርጉም አለው። ከምንመገበው ምግብ ሙሉ ጥቅም ማግኘት እንድንችል ምግቡ መፈጨትና ከሰውነታችን ጋር መዋሐድ እንደሚያስፈልገው ሁሉ የምናነበውን ነገር ሙሉ በሙሉ ለመረዳትም ማሰላሰል አስፈላጊ ነው። ታዲያ ባጠናነው ነገር ላይ ለማሰላሰል በቂ ጊዜ እንመድባለን? መጽሐፍ ቅዱስን ካነበብን በኋላ ስላነበብነው ነገር በጥልቅ ልናስብ ይገባል።

15. የንጹሑን ቋንቋ “ሰዋስው” ማጥናት የምንችለው እንዴት ነው?

15 የቋንቋውን ሰዋስው አጥና። አዲስ ቋንቋ በመማር ረገድ እድገት እያደረግን ስንሄድ የቋንቋውን ሰዋስው ወይም ዓረፍተ ነገሮች የሚዋቀሩበትን መንገድ ማጥናት ጠቃሚ ነው። እንዲህ ማድረጋችን የቋንቋውን ሥርዓት ለመረዳትና ቋንቋውን በተገቢው መንገድ ለመናገር ያስችለናል። በአንድ ቋንቋ ውስጥ ዓረፍተ ነገሮች የሚዋቀሩበት ሥርዓት እንዳለ ሁሉ ንጹሕ ቋንቋ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትም ‘የጤናማ ቃላት ንድፍ’ ወይም ሥርዓት አለው። (2 ጢሞ. 1:13 NW) ይህንን “ንድፍ” ወይም ሥርዓት መኮረጅ አለብን።

16. የትኛውን አዝማሚያ ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

16 እድገት ማድረግህን ቀጥል። አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ለመግባባት በሚያስችለው መጠን አንድን ቋንቋ ከተማረ በኋላ እድገት ማድረጉን ሊያቆም ይችላል። ንጹሑን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎችም እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ። (ዕብራውያን 5:11-14ን አንብብ።) የዚህ ዓይነቱን አዝማሚያ ለማሸነፍ ምን ሊረዳን ይችላል? ይህንን ቋንቋ መማርህን ለመቀጠል የሚያስፈልገውን ጥረት ከማድረግ ወደኋላ አትበል። “ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ወደ ብስለት እንሂድ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ ስለ መግባትና በእግዚአብሔር ስለ ማመን እንደ ገና መሠረትን አንጣል፤ እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣ ስለ ሙታን ትንሣኤና ስለ ዘላለም ፍርድ ትምህርት እንደ ገና አንመሥርት።”—ዕብ. 6:1, 2

17. ቋሚ የጥናት ልማድ ማዳበር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

17 ቋሚ የጥናት ጊዜ መድብ። አልፎ አልፎ ረዘም ላለ ሰዓት ከማጥናት ይልቅ ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ቋሚ በሆነ መንገድ ማጥናት የተሻለ ነው። ንቁ በምትሆንበትና ሐሳብህ በቀላሉ በማይከፋፈልበት ጊዜ ላይ አጥና። አዲስ ቋንቋ መማር በጫካ ውስጥ መንገድ እንደማውጣት ነው። ሰዎች አዘውትረው የሚሄዱበት ከሆነ መንገዱ ቶሎ ስለማይጠፋ በዚያ መሄድ ቀላል ይሆናል። መንገዱን ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሰዎች ካልተጠቀሙበት ግን ብዙም ሳይቆይ ጥሻ ይወርሰዋል። አዲስ ቋንቋ በመማር ረገድም ቆራጥ በመሆን ሁልጊዜ ማጥናት አስፈላጊ ነው! (ዳን. 6:16, 20) ንጹሕ ቋንቋ የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከመናገር ጋር በተያያዘም ‘ዘወትር ንቁ በመሆን’ ጸሎት የታከለበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።—ኤፌ. 6:18 NW

18. ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በንጹሑ ቋንቋ መናገር ያለብን ለምንድን ነው?

18 አዘውትረህ ተናገር! አዲስ ቋንቋ የሚማሩ አንዳንድ ሰዎች ስለሚያፍሩ ወይም እንዳይሳሳቱ ስለሚፈሩ ከመናገር ወደኋላ ይላሉ። ይህ ደግሞ እድገት እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። ቋንቋን በመማር ረገድ ልምምድ ማድረግ ጥሩ ውጤት ለማግኘት ይረዳል። አዲስ ቋንቋ የሚማር አንድ ሰው አዘውትሮ በተናገረ መጠን በቋንቋው መጠቀም ቀላል ይሆንለታል። እኛም ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በንጹሑ ቋንቋ መናገር ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ “የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ [“በይፋ፣” NW] መስክረህ ነው” ይላል። (ሮሜ 10:10) ‘በይፋ የምንመሰክረው’ ስንጠመቅ ብቻ ሳይሆን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ስለ ይሖዋ ስንናገር ነው፤ ይህ በአገልግሎት መካፈልንም ይጨምራል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ዕብ. 13:15) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን በንጹሑ ቋንቋ በመጠቀም ግልጽ በሆነና ባልተንዛዛ መንገድ ሐሳባችንን ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጡናል።—ዕብራውያን 10:23-25ን አንብብ።

ይሖዋን ለማወደስ ንጹሑን ቋንቋ በአንድነት ተጠቀሙበት

19, 20. (ሀ) በዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮች ምን አስገራሚ ነገር እያከናወኑ ነው? (ለ) ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

19 ሲቫን 6, 33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እሁድ ጠዋት ላይ በኢየሩሳሌም መገኘት ቢቻል ኖሮ እንዴት የሚያስደስት ይሆን ነበር! የዚያን ቀን ጠዋት ሦስት ሰዓት ገደማ በአንድ ቤት ሰገነት ላይ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ “በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር።” (ሥራ 2:4) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች በልሳን ወይም በሌላ ቋንቋ የመናገር ስጦታ የላቸውም። (1 ቆሮ. 13:8) ያም ቢሆን የይሖዋ ምሥክሮች ከ430 በሚበልጡ ቋንቋዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ይሰብካሉ።

20 በዕለታዊ ሕይወታችን የምንናገረው ቋንቋ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ንጹሕ ቋንቋ የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በአንድነት መናገር በመቻላችን በጣም አመስጋኞች ነን! ይህ ሁኔታ በባቤል ከተከሰተው ምንኛ የተለየ ነው! የይሖዋ ሕዝቦች ልክ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ያህል አንድ ሆነው ስሙን ያወድሳሉ። (1 ቆሮ. 1:10) በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ለይሖዋ ክብር በሚያመጣ መንገድ ይህንን አንድ ቋንቋ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አጥርተን መናገርን በመማር በምድር ዙሪያ ከሚገኙት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ‘አንድ ሆነን’ ማገልገላችንን መቀጠል ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።—መዝሙር 150:1-6ን አንብብ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 መዝሙር 1:1, 2 (NW):- “በክፉዎች ምክር ያልሄደ፣ በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ፣ በፌዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ ሰው ደስተኛ ነው። . . . የሚደሰተው በይሖዋ ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ድምጹን አውጥቶ ያነባል።”

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ንጹሕ ቋንቋ የተባለው ምንድን ነው?

• ንጹሑን ቋንቋ መናገር ምን ነገሮችን ያጠቃልላል?

• ንጹሑን ቋንቋ አጥርተን ለመናገር ምን ሊረዳን ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ንጹሑን ቋንቋ አጥርተህ የመናገር ችሎታህን ለማሻሻል:-

በጥሞና አዳምጥ።

ሉቃስ 8:18፤ ዕብ. 2:1

ቋንቋውን አጥርተው የሚናገሩ ሰዎችን ኮርጅ።

1 ቆሮ. 11:1፤ ዕብ. 13:7

በቃል ማጥናትና መደጋገም።

ያዕ. 1:22-25፤ 2 ጴጥ. 1:12

ጮክ ብለህ አንብብ።

መዝ. 1:1, 2 NW፤ ራእይ 1:3 NW

የቋንቋውን “ሰዋስው” አጥና።

2 ጢሞ. 1:13 NW

እድገት ማድረግህን ቀጥል።

ዕብ. 5:11-14፤ 6:1, 2

ቋሚ የጥናት ጊዜ መድብ።

ዳን. 6:16, 20፤ ኤፌ. 6:18 NW

አዘውትረህ ተናገር!

ሮሜ 10:10፤ ዕብ. 10:23-25

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ሕዝቦች ንጹሑን ቋንቋ በአንድነት ይናገራሉ