በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ አረጋዊ ለሆኑ አገልጋዮቹ በጥልቅ ያስባል

ይሖዋ አረጋዊ ለሆኑ አገልጋዮቹ በጥልቅ ያስባል

ይሖዋ አረጋዊ ለሆኑ አገልጋዮቹ በጥልቅ ያስባል

‘አምላክ ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም።’—ዕብ. 6:10

1, 2. (ሀ) ጠጉሩ የሸበተ ሰው ስትመለከት ምን ትዝ ይልሃል? (ለ) ይሖዋ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖችን የሚመለከታቸው እንዴት ነው?

በጉባኤ ውስጥ ጠጕራቸው የሸበተ አረጋውያንን ስትመለከት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው የዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ ታስታውስ ይሆናል። ዳንኤል በተመለከተው ራእይ ላይ ይሖዋ አምላክ ጠጕሩ ነጭ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ዳንኤል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኔም ስመለከት፣ ዙፋኖች ተዘረጉ፤ ጥንታዌ ጥንቱም [“በዘመናት የሸመገለውም፣ የ1954 ትርጉም] ተቀመጠ፤ ልብሱ እንደ በረዶ ነጭ ነበረ፤ የራሱም ጠጕር እንደ ጥጥ ነጭ ነበረ።”—ዳን. 7:9

2 አምላክ ‘ጠጕሩ እንደ ጥጥ ነጭ’ እንደሆነ መገለጹና ‘በዘመናት የሸመገለው’ ተብሎ መጠራቱ ዘላለማዊ እንደሆነና ታላቅ ጥበብ እንዳለው የሚያመለክት ሲሆን ይህም በጥልቅ ልናከብረው እንደሚገባ ያሳያል። ታዲያ በዘመናት የሸመገለ የተባለው ይሖዋ በዕድሜ የገፉ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን እንዴት ይመለከታቸዋል? የአምላክ ቃል “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” ይላል። (ምሳሌ 16:31) አዎን፣ አንድ ታማኝ ክርስቲያን ጠጉሩ ሲሸብት ወይም እንደ ጥጥ ነጭ ሲሆን ግለሰቡ የጎለመሰ መሆኑን የሚያሳየውን ይህንን ሁኔታ አምላክ ውብ እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። አንተስ ይሖዋ፣ አረጋውያን ለሆኑ ወንድሞችና እህቶች ያለው ዓይነት አመለካከት አለህ?

ውድ እንደሆኑ አድርገን የምንመለከታቸው ለምንድን ነው?

3. በዕድሜ የገፉ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ውድ እንደሆኑ አድርገን የምንመለከታቸው ለምንድን ነው?

3 ከእነዚህ ውድ የሆኑ በዕድሜ የገፉ የአምላክ አገልጋዮች መካከል የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባላት፣ በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ጨምሮ የቀድሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ በቅንዓት የሚያገለግሉ አቅኚዎች እንዲሁም በጉባኤያችን ውስጥ በታማኝነት የሚያገለግሉ ጎልማሳ የሆኑ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይገኙበታል። አንተም ለአሥርተ ዓመታት ምሥራቹን በቅንዓት ሲሰብኩ የቆዩ እንዲሁም በመልካም ምሳሌነታቸው በወጣቶች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩና ለሥራ እንዲነሣሡ ያደረጉ አንዳንድ አረጋውያንን ታውቅ ይሆናል። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ የእምነት ባልንጀሮቻችን ከባድ ኃላፊነቶችን የተሸከሙ ከመሆኑም በላይ በምሥራቹ የተነሳ የደረሰባቸውን ስደት ተቋቁመው ጸንተዋል። ይሖዋም ሆነ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እነዚህ አረጋውያን ከመንግሥቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ያደረጉትንና አሁን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ከልብ ያደንቃሉ።—ማቴ. 24:45 የ1954 ትርጉም

4. በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖችን ልናከብራቸውና ልንጸልይላቸው የሚገባው ለምንድን ነው?

4 ሌሎች የይሖዋ አምላክ አገልጋዮችም፣ አረጋዊ የሆኑትን እነዚህን ታማኝ ወንድሞችና እህቶች ሊያደንቋቸውና ሊያከብሯቸው ይገባል። አምላክ በሙሴ በኩል የሰጠው ሕግ ለአረጋውያን አሳቢነትና አክብሮት ማሳየትን ይሖዋን ከመፍራት ጋር አያይዞ ገልጾታል። (ዘሌ. 19:32) ለእነዚህ ታማኞች አዘውትረን ልንጸልይና በፍቅር ተነሳስተው ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች አምላክን ልናመሰግን ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣትም ሆነ አረጋዊ ለሆኑ የተወደዱ የሥራ ባልደረቦቹ ጸልዮ ነበር።—1 ተሰሎንቄ 1:2, 3ን አንብብ።

5. በዕድሜ ከገፉ የይሖዋ አምላኪዎች ጋር ጊዜ ማሳለፋችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

5 ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም የጉባኤ አባላት ከአረጋውያን ክርስቲያኖች ጋር አብረው ጊዜ በማሳለፋቸው ይጠቀማሉ። በዕድሜ የገፉ ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች ካነበቧቸውና ከተመለከቷቸው ነገሮች እንዲሁም ካካበቱት ተሞክሮ በዋጋ ሊተመን የማይችል እውቀት አግኝተዋል። እነዚህ አረጋውያን ታጋሽ መሆንንና የሌሎችን ችግር እንደ ራሳቸው አድርገው መመልከትን ተምረዋል፤ የተማሯቸውን ነገሮች ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍም ታላቅ ደስታና እርካታ ያስገኝላቸዋል። (መዝ. 71:18) እናንት ወጣቶች፣ ጥልቅ ከሆነ ጉድጓድ ውኃ እንደሚቀዳ ሁሉ አረጋውያን ካላቸው የእውቀት ክምችት ቀድታችሁ በመጠቀም ጥበበኞች መሆናችሁን አሳዩ።—ምሳሌ 20:5

6. አረጋውያንን ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቷቸው እንዴት ማሳየት ትችላላችሁ?

6 ይሖዋ ለአረጋውያን ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጣቸው ሁሉ እናንተም ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቷቸው እንዲያውቁ ታደርጋላችሁ? ይህን ማድረግ የምትችሉበት አንዱ መንገድ ታማኝ በመሆናቸው ምን ያህል እንደምትወዷቸውና ለሚሰጡት አስተያየት ትልቅ ቦታ እንደምትሰጡት በመግለጽ ነው። ከዚህም በላይ የሰጧችሁን ምክሮች ወይም ሐሳቦች ተግባራዊ በማድረግ ከልባችሁ እንደምታከብሯቸው ታሳያላችሁ። በዕድሜ የገፉ በርካታ ክርስቲያኖች፣ ወጣት በነበሩበት ወቅት ታማኝ የሆኑ አረጋውያን ጥበብ ያዘለ ምክር እንደሰጧቸው እንዲሁም ምክሩን በሥራ ላይ በማዋላቸው በሕይወታቸው ሙሉ እንደተጠቀሙ ያስታውሳሉ። *

አሳቢነታችሁን በተግባር አሳዩ

7. ይሖዋ፣ አረጋውያንን የመንከባከቡን ኃላፊነት በዋነኝነት የሰጠው ለማን ነው?

7 አምላክ፣ አረጋውያን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች የማሟላቱን ኃላፊነት በዋነኝነት የሰጠው ለቤተሰቦቻቸው ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8ን አንብብ።) የአረጋውያን ቤተሰቦች እነዚህን ዘመዶቻቸውን በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ይሖዋ ይደሰታል፤ በዚህ መንገድ አረጋውያንን ልክ እንደ ይሖዋ እንደሚንከባከቧቸው ያሳያሉ። አምላክ እንዲህ የሚያደርጉ ቤተሰቦችን የሚደግፍ ከመሆኑም በላይ ለሚያደርጉት ጥረትም ሆነ ለሚከፍሏቸው መሥዋዕቶች ሁሉ ይባርካቸዋል። *

8. ጉባኤዎች፣ በዕድሜ ለገፉ ክርስቲያኖች እንደሚያስቡላቸው ማሳየት ያለባቸው ለምንድን ነው?

8 በተጨማሪም እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ታማኝ አረጋውያን፣ የቤተሰባቸው አባላት የማያምኑ ከሆኑ አሊያም ሊረዷቸው ፈቃደኛ ካልሆኑ ጉባኤዎች ሲረዷቸው ይሖዋ ይደሰታል። (1 ጢሞ. 5:3, 5, 9, 10) ጉባኤዎች እንዲህ በማድረግ “እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆች . . . ሁኑ” የሚለውን ምክር ከአረጋውያን ጋር በተያያዘ በተግባር እንዳዋሉት ያሳያሉ። (1 ጴጥ. 3:8) ጳውሎስ አንዱ የሰውነት ክፍል ሲሠቃይ ‘ብልቶች ሁሉ አብረው እንደሚሠቃዩ’ የተናገረው ሐሳብ ጉባኤው በዕድሜ ለገፉ ወንድሞችና እህቶች ያለውን አሳቢነት ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። (1 ቆሮ. 12:26) አረጋውያን ወንድሞቻችንን የሚጠቅሟቸውን ነገሮች ርኅራኄ በተሞላበት መንገድ ማከናወናችን “አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህም ሁኔታ የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ” ከሚለው የጳውሎስ ምክር በስተጀርባ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት እንደሠራንበት ያሳያል።—ገላ. 6:2

9. የዕድሜ መግፋት ምን ዓይነት ሸክም ሊያስከትል ይችላል?

9 አረጋውያን ያለባቸው ሸክም ምንድን ነው? ብዙዎቹ ቶሎ ይደክማቸዋል። ሐኪም ቤት መሄድ፣ የተለያዩ ጉዳዮችን ማስፈጸም፣ ቤት ማጽዳትና ምግብ ማዘጋጀት የመሳሰሉትን መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች ማከናወን እንኳ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ብዙውን ጊዜ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የምግብ ፍላጎታቸው ስለሚቀንስ ሰውነታቸው የሚያስፈልገውን ያህል መብላት ወይም መጠጣት እንዳለባቸው አይሰማቸው ይሆናል። መንፈሳዊ ምግብ በመመገብ ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ዓይናቸውና ጆሯቸው መድከሙ ማንበብና መንፈሳዊ ፕሮግራሞችን ማዳመጥ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ሊያደርግ ይችላል፤ ሌላው ቀርቶ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ለመሄድ የሚያስፈልጓቸውን ዝግጅቶች ማድረግ እንኳ አድካሚ ሊሆንባቸው ይችላል። ታዲያ እንደነዚህ ያሉትን አረጋውያን ለመርዳት ሌሎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

10. ሽማግሌዎች፣ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዲሟሉላቸው ምን ማድረግ ይችላሉ?

10 ብዙ ጉባኤዎች ለአረጋውያን እንክብካቤ የሚያደርጉበት መንገድ አርዓያ የሚሆን ነው። አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች፣ አረጋውያን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በመግዛትና ምግብ በማብሰል እንዲሁም ከጽዳት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በማከናወን በዕድሜ የገፉትን ክርስቲያኖች ያግዟቸዋል። በዕድሜ የገፉት ክርስቲያኖች፣ ስብሰባ ለመሄድ የሚያስፈልጋቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉና በአገልግሎታቸው አዘውታሪ እንዲሆኑም ይረዷቸዋል፤ እንዲሁም አብረዋቸው ያጠናሉ። ከአረጋውያኑ በዕድሜ የሚያንሱ የይሖዋ ምሥክሮች አረጋውያኑ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መሄድ ሲፈልጉ አብረዋቸው ይሄዳሉ፤ እንዲሁም መጓጓዣ ማግኘት የሚችሉበት ዝግጅት ያደርጉላቸዋል። በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ከቤት መውጣት የማይችሉ ከሆነ ስብሰባውን በስልክ የሚከታተሉበት ዝግጅት ይደረጋል አሊያም ፕሮግራሙ ይቀዳላቸዋል። ሽማግሌዎች፣ በጉባኤ ውስጥ ያሉ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በተቻለ መጠን ለማሟላት ዝግጅቶች እንዲደረጉ ጥረት ያደርጋሉ። *

11. የአንድ ቤተሰብ አባላት በዕድሜ የገፉ አንድ ወንድምን እንዴት እንደረዷቸው ግለጽ።

11 ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ማሳየትና ልግስና ማድረግ ይችላሉ። አንድ አረጋዊ ወንድም፣ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ሲያጡ የባለቤታቸው የጡረታ አበል በመቋረጡ የቤት ኪራይ መክፈል አስቸጋሪ ሆነባቸው። በአንድ ወቅት እኚህ ወንድምና ባለቤታቸው ሁለት ሴቶች ልጆች ያሏቸውን አንድ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠኑ ነበር፤ ቤተሰቡ ትልቅ ቤት ስለነበረው አረጋዊው ወንድም በተቸገሩበት ወቅት ሁለት ክፍል ሰጣቸው። አረጋዊው ወንድምና የዚህ ቤተሰብ አባላት ለ15 ዓመታት ያህል በፍቅር አብረው የኖሩ ሲሆን ብዙ አስደሳች ትዝታዎችንም አሳልፈዋል፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ አረጋዊው ወንድም የሚመገቡት ከቤተሰቡ ጋር ነበር። የቤተሰቡ አባላት ከአረጋዊው ወንድም እምነትና ካካበቱት ተሞክሮ ብዙ ጥቅም ያገኙ ሲሆን እኚህ ወንድምም ከዚህ ቤተሰብ ጋር አብረው በመኖራቸው ይደሰቱ ነበር። ወንድም በ89 ዓመታቸው እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ ከዚህ ቤተሰብ ጋር ኖረዋል። ቤተሰቡ ከአረጋዊው ወንድም ጋር አብረው በመኖራቸው ላገኟቸው ብዙ በረከቶች አሁንም ድረስ አምላክን ያመሰግናሉ። የዚህ ቤተሰብ አባላት እንደ እነሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነውን ወንድማቸውን በመርዳታቸው ‘ዋጋቸውን አላጡም።’—ማቴ. 10:42 *

12. በዕድሜ ለገፉ ወንድሞችና እህቶች በጥልቅ እንደምታስቡላቸው ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው?

12 ከላይ የተገለጸው ቤተሰብ በዕድሜ ለገፉት ወንድም እርዳታ ባደረገበት መንገድ አንድን አረጋዊ ወንድም ወይም እህት መርዳት አትችሉ ይሆናል። ይሁንና በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖችን ወደ ስብሰባዎች ልትወስዷቸውና አብራችኋቸው አገልግሎት ልትወጡ ትችላላችሁ። በተጨማሪም ቤታችሁ ልትጋብዟቸውና ለሽርሽር ወጣ ስትሉ አብረዋችሁ እንዲሄዱ ልታደርጉ ትችላላችሁ። በተለይ በሚታመሙበት ወይም ከቤት መውጣት በማይችሉበት ወቅት ቤታቸው ሄዳችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ። ከዚህም በላይ ምንጊዜም ቢሆን እንደ አንድ ጎልማሳ ሰው አድርጋችሁ ልትመለከቷቸው ይገባል እንጂ እነሱን እንደ ልጅ ማየት ተገቢ አይደለም። በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በትክክል ማሰብ እስከቻሉ ድረስ ከእነሱ ጋር በተያያዘ በሚደረገው በማንኛውም ውሳኔ ውስጥ እንዲካፈሉ ልታደርጉ ይገባል። የማመዛዘን ችሎታቸው በጣም የደከመ አረጋውያንም እንኳ ሌሎች እንደሚያከብሯቸውና እንደማያከብሯቸው ማወቅ ይችላሉ።

ይሖዋ ሥራችሁን አይረሳም

13. ለአረጋውያን ክርስቲያኖች ስሜት ማሰብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ለአረጋውያን ስሜት ማሰብ አስፈላጊ ነው። በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ወጣትና ጤናማ በነበሩበት ጊዜ ያከናውኑት የነበሩትን ሁሉ አሁን ማድረግ ባለመቻላቸው ብዙውን ጊዜ ሲያዝኑና ሲበሳጩ ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት ይሖዋን በቅንዓት ሲያገለግሉ የቆዩና የዘወትር አቅኚ የነበሩ አንዲት እህት አቅም በሚያሳጣ በሽታ በመያዛቸው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም ያስቸግራቸው ነበር። እኚህ እህት ከዚህ ቀደም ያከናውኑት የነበረውን አገልግሎት ሲያስታውሱና አሁን አቅማቸው ምን ያህል የተገደበ እንደሆነ ሲያስቡ ያለቅሳሉ። አንገታቸውን አቀርቅረው እያነቡ “ከእንግዲህ ምንም መሥራት አልችልም” በማለት ይናገራሉ።

14. የመዝሙር መጽሐፍ በዕድሜ ለገፉ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ማበረታቻ ይሰጣል?

14 እርስዎም እንዲህ ያለ መንፈስዎን የሚረብሽ ሐሳብ ይመጣብዎታል? ወይም ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ እንደተዎት ይሰማዎታል? መዝሙራዊው በእርጅና ዘመኑ እንደዚህ ሳይሰማው አልቀረም፤ እንደሚከተለው በማለት ይሖዋን የለመነውም ለዚህ ሊሆን ይችላል:- “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጕልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ። . . . አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ።” (መዝ. 71:9, 18) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ይህን መዝሙር ያቀናበረውን ሰው አልተወውም፤ ስለዚህ እርስዎንም አይተዎትም። በሌላ መዝሙር ላይ ዳዊት በአምላክ እርዳታ እንደሚተማመን ገልጿል። (መዝሙር 68:19ን አንብብ።) እርስዎም ታማኝ የሆኑ አረጋዊ ክርስቲያን ከሆኑ ይሖዋ እንደማይተዎትና በየዕለቱ እንደሚደግፍዎት እርግጠኛ መሆን ይችላሉ።

15. አረጋውያን አዎንታዊ አመለካከት ይዘው እንዲቀጥሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

15 እናንት አረጋውያን፣ ይሖዋ እሱን ለማስከበር ስትሉ ያደረጋችሁትንም ሆነ አሁን እያደረጋችሁ ያላችሁትን ሁሉ በፍጹም አይረሳም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም . . . ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም” ይላል። (ዕብ. 6:10) ስለዚህ ‘ዕድሜዬ በመግፋቱ ለይሖዋ አላስፈልገውም’ የሚል የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራችሁ አትፍቀዱ። ተስፋ አስቆራጭና አሉታዊ የሆኑ ሐሳቦችን አስወግዳችሁ አዎንታዊ አመለካከት ለማዳበር ጣሩ። አሁን ባሏችሁ በረከቶችና በወደፊት ተስፋችሁ ደስ ይበላችሁ! ከሁሉ የላቀ “ተስፋ” ያለን ሲሆን ይህም እንደሚፈጸም ፈጣሪያችን ዋስትና ሰጥቶናል። (ኤር. 29:11, 12፤ ሥራ 17:31፤ 1 ጢሞ. 6:19) በተስፋችሁ ላይ አሰላስሉ። ልባችሁ እንዲያረጅ አትፍቀዱ፤ በአስተሳሰባችሁ ወጣት እንደሆናችሁ ለመቀጠል ጥረት አድርጉ። እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ መኖራችሁ ያለውን ጠቀሜታ ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱት! *

16. በዕድሜ የገፉ አንድ ወንድም በሽምግልና ማገልገላቸውን ማቆም እንዳለባቸው የተሰማቸው ለምን ነበር? የጉባኤያቸው የሽማግሌዎች አካላትስ እኚህን ወንድም ያበረታቷቸው እንዴት ነው?

16 ዮሃን የተባሉትን የ80 ዓመት አዛውንት እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እኚህ ወንድም፣ ታማሚ የሆኑትንና የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሳኒ የተባሉ ታማኝ ባለቤታቸውን በመንከባከብ ሙሉ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። * ወንድም ዮሃን ወደ ስብሰባዎች መሄድና አገልግሎት መውጣት እንዲችሉ እህቶች ተራ ገብተው እህት ሳኒን ይንከባከባሉ። በቅርቡ ግን ወንድም ዮሃን ኃይላቸው እንደተሟጠጠ ስለተሰማቸው የጉባኤ ሽማግሌ ሆነው ማገልገል እንደማይችሉ ማሰብ ጀምረው ነበር። ዓይናቸው እንባ አቅርሮ እንዲህ አሉ:- “በጉባኤ ውስጥ ምንም የሚጠቅም ነገር አልሠራም። ታዲያ የእኔ ሽማግሌ መሆን ምን ትርጉም አለው?” አብረዋቸው በሽምግልና የሚያገለግሉት ሌሎች ወንድሞች ግን የእሳቸው ተሞክሮና የማስተዋል ችሎታ በዋጋ ሊተመን የማይችል እንደሆነ ገለጹላቸው። እነዚህ ሽማግሌዎች፣ ወንድም ዮሃን የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ውስን ቢሆንም በሽምግልና ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸው። ወንድም ዮሃን በጣም ስለተበረታቱ በሽምግልና ማገልገላቸውን የቀጠሉ ሲሆን እንዲህ በማድረጋቸውም ለጉባኤው በረከት ሆነዋል።

ይሖዋ በእርግጥም ያስብላቸዋል

17. መጽሐፍ ቅዱስ በዕድሜ ለገፉ ክርስቲያኖች ምን ዋስትና ይሰጣቸዋል?

17 አረጋውያን፣ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ቢኖሩባቸውም በይሖዋ አገልግሎት ፍሬ ማፍራታቸውን መቀጠል እንደሚችሉ ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ ያሳያሉ። መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “በእግዚአብሔር ቤት ተተክለዋል፤ . . . ባረጁ ጊዜ እንኳ ያፈራሉ፤ እንደ ለመለሙና እንደ ጠነከሩም ይኖራሉ።” (መዝ. 92:13, 14) አካላዊ ሕመም እንደነበረበት የሚታሰበው ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ውጫዊው ሰውነቱ እየጠፋ ቢሄድም እንኳ ተስፋ አልቈረጠም።’—2 ቆሮንቶስ 4:16-18ን አንብብ።

18. በዕድሜ የገፉ የእምነት ባልንጀሮቻችንም ሆኑ እነሱን የሚንከባከቧቸው ሰዎች የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

18 በርካታ ዘመናዊ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች ፍሬ ‘ማፍራታቸውን’ ሊቀጥሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ሕመምና የዕድሜ መግፋት የሚያስከትሏቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች፣ ተንከባካቢና ሁልጊዜ ከጎናቸው የሚሆኑ ቤተሰቦች ያሏቸውን አረጋውያንም እንኳ ተስፋ ሊያስቆርጧቸው ይችላሉ። አረጋውያንን የሚንከባከቧቸው ሰዎችም ሊዝሉ ይችላሉ። የጉባኤው አባላት በዕድሜ ለገፉት ክርስቲያኖችም ሆነ እነሱን ለሚንከባከቡት ሰዎች ያላቸውን ፍቅር በተግባር የማሳየት መብትና ኃላፊነት አለባቸው። (ገላ. 6:10) እንዲህ የማናደርግ ከሆነ እነዚህን ሰዎች በሚጠቅማቸው መንገድ ሳንረዳቸው “አይብረዳችሁ፤ ጥገቡ” የምንላቸው ያህል ነው።—ያዕ. 2:15-17

19. በዕድሜ የገፉ ታማኝ ክርስቲያኖች የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የሚችሉት ለምንድን ነው?

19 አንድ ክርስቲያን ዕድሜው መግፋቱ የሚያደርጋቸውን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች በተወሰነ መጠን እንዲቀንስ ያደርገው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የጊዜ ማለፍ ይሖዋ ታማኝ ለሆኑ አረጋውያን አገልጋዮቹ ያለው ፍቅር እንዲቀንስ አያደርግም። ከዚህ በተቃራኒ እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች በሙሉ በእሱ ፊት ውድ ናቸው፤ እንዲሁም ፈጽሞ አይጥላቸውም። (መዝ. 37:28፤ ኢሳ. 46:4) ይሖዋ በእርጅና ዘመናቸው በሙሉ ይንከባከባቸዋል እንዲሁም ይመራቸዋል።—መዝ. 48:14

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ “አረጋውያን ወላጆቻችንን ማክበር” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 15⁠ን ተመልከት።

^ አን.10 ይህ፣ በአንዳንድ አገሮች መንግሥት ካደረገው ዝግጅት እንዲጠቀሙ አረጋውያኑን መርዳትንም ሊጨምር ይችላል። በሰኔ 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አምላክ ለአረጋውያን ያስባል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.15 በመጋቢት 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የሽበት ግርማ ሞገስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.16 ስሞቹ ተቀይረዋል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• በዕድሜ የገፉ ታማኝ ክርስቲያኖችን ውድ እንደሆኑ አድርገህ የምትመለከታቸው ለምንድን ነው?

• በዕድሜ ለገፉ የእምነት ባልንጀሮቻችን በጥልቅ እንደምናስብላቸው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• በዕድሜ የገፉ የይሖዋ አገልጋዮች አዎንታዊ አመለካከት ይዘው እንዲቀጥሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጉባኤው አባላት ለአረጋውያን ትልቅ ቦታ ይሰጧቸዋል