በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በታላቅ ጕጕት” ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጋችሁ ሂዱ

“በታላቅ ጕጕት” ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጋችሁ ሂዱ

“በታላቅ ጕጕት” ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጋችሁ ሂዱ

የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይሻሉ። እኛም እንዲህ ያለውን ተቀባይነት ለማግኘት ስለምንፈልግ እምነታችንን ለማጠናከርና በቅንዓት ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ የኖሩ አንዳንድ አይሁዳውያን የነበረባቸውን ከባድ ችግር አስመልክቶ የሰጠው ሐሳብ የእኛንም ትኩረት ይስባል፤ ጳውሎስ “ለእግዚአብሔር ቀናተኛ [ናቸው]፤ . . . ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 10:2) ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው በይሖዋ ላይ እምነት የምናሳድረውም ሆነ ለእሱ አምልኮ የምናቀርበው በስሜት ተገፋፍተን መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ ስለ ፈጣሪያችንና ስለ ፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት ሊኖረን ይገባል።

ጳውሎስ በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ላይ፣ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝ ምግባርን እውቀት ለማግኘት ከመጓጓት ጋር አያይዞ ገልጾታል። ሐዋርያው፣ የክርስቶስ ተከታዮች በአምላክ ፈቃድ ‘ትክክለኛ እውቀት እንዲሞሉ’ ጸልዮአል፤ እንዲህ ዓይነት እውቀት ማግኘታቸው ‘በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈሩና ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጉ ሲሄዱ ይሖዋን ሙሉ በሙሉ በማስደሰት ለእሱ በሚገባ ሁኔታ መመላለስ እንዲችሉ’ ይረዳቸዋል። (ቈላ. 1:9, 10 NW) “ትክክለኛ እውቀት” መቅሰማችን ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውን እውቀት በመቅሰም እያደግን መሄድ የሚኖርብንስ ለምንድን ነው?

እምነት ለማዳበር ቁልፍ የሆነው ነገር

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ የሚገልጸው ትክክለኛ እውቀት ለእምነታችን መሠረት ነው። እንዲህ ዓይነት ትክክለኛ እውቀት ከሌለን በይሖዋ ላይ ያለን እምነት በቀላሉ እንደሚፈርስ የእንቧይ ካብ ይሆናል። ጳውሎስ ‘የማሰብ ችሎታችንን በመጠቀም’ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንድናቀርብ እንዲሁም ‘አእምሯችንን በማደስ እንድንለወጥ’ ማበረታቻ ሰጥቶናል። (ሮሜ 12:1, 2 NW) መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማጥናታችን በዚህ ረገድ ሊረዳን ይችላል።

በፖላንድ የምትኖረው ኤቫ የተባለች የዘወትር አቅኚ እንዲህ ብላለች:- “የአምላክን ቃል አዘውትሬ ካላጠናሁ ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እድገት ማድረጌን አቆማለሁ። ብዙም ሳይቆይ ክርስቲያናዊ ማንነቴ መበላሸት የሚጀምር ከመሆኑም ሌላ በአምላክ ላይ ያለኝ እምነት ይዳከማል፤ ይህም ከአምላክ ጋር የመሠረትኩትን ዝምድና ወደማጣት ሊያደርሰኝ ይችላል።” ማናችንም እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ እንዲደርስብን አንፈልግም። ስለ ይሖዋ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደገ በመሄዱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ አንድ ሰው እስቲ እንመልከት።

“ሕግህን ምንኛ ወደድሁ!”

በመዝሙር 119 ላይ የሰፈረው ማራኪ መዝሙር፣ ይህን መዝሙር የጻፈው ሰው ስለ ይሖዋ ሕግ፣ ምሥክርነት፣ ሥርዓት፣ ትእዛዝና ፍርድ ያለውን አመለካከት ያሳያል። መዝሙራዊው “በሥርዐትህ ደስ ይለኛል፤ . . . ምስክርነትህ ለእኔ ደስታዬ ነው” በማለት ጽፏል። በተጨማሪም “ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ” ብሏል።—መዝ. 119:16, 24, 47, 48, 77, 97

“ደስ ይለኛል” እንዲሁም “አሰላስለዋለሁ” የሚሉት አገላለጾች መዝሙራዊው በአምላክ ቃል ላይ በማሰላሰል እንደሚደሰት ይጠቁማሉ። እነዚህ አገላለጾች፣ መዝሙራዊው መለኮታዊውን ሕግ ማጥናት በጣም ይወድ እንደነበር ጎላ አድርገው ያሳያሉ። መዝሙራዊው ለአምላክ ሕግ የነበረው ፍቅር ከስሜታዊነት የመነጨ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በሕጉ ላይ ‘ለማሰላሰልና’ ስለ ይሖዋ ቃል ጥልቅ ማስተዋል ለማግኘት ከፍተኛ ጕጕት ነበረው። ይህ መዝሙራዊ በተቻለው መጠን ስለ አምላክና ስለ ፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት የማግኘት ፍላጎት እንደነበረው ከጻፋቸው ነገሮች መረዳት እንችላለን።

መዝሙራዊው ለአምላክ ቃል የነበረው ፍቅር ከልብ የመነጨ እንደሆነ ግልጽ ነው። እኛም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ‘እኔስ የአምላክን ቃል ከልቤ እወዳለሁ? በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብኩት ነገር ላይ ምርምር ማድረግ ያስደስተኛል? የአምላክን ቃል ለማንበብ ትጋት የተሞላበት ጥረት አደርጋለሁ? ቃሉን ማንበብ ከመጀመሬ በፊትስ እጸልያለሁ?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች ‘አዎን’ ብለን መመለሳችን ‘ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደግን’ እንደሆነ ያሳያል።

ኤቫ እንዲህ ብላለች:- “ከግል ጥናቴ የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ሁልጊዜ ጥረት አደርጋለሁ። ‘መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ’ (እንግሊዝኛ) የተባለው ብሮሹር ከደረሰን ጀምሮ በእያንዳንዱ ጥናቴ ላይ እየተጠቀምኩበት ነው ማለት እችላለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍና በሌሎች ጽሑፎች ተጠቅሜ ምርምር ለማድረግ ከበፊቱ የበለጠ ጥረት አደርጋለሁ።”

በርከት ያሉ የቤተሰብ ኃላፊነቶች ያሉባቸውን ቮይቼክ እና ማዉጎዛታ የተባሉ ባልና ሚስት ሁኔታም እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፕሮግራማቸውን ያስተካከሉት እንዴት ነው? እንዲህ ብለዋል:- “በተቻለን መጠን የአምላክን ቃል በየግላችን ለማጥናት ጊዜ እንመድባለን። ከዚያም ትኩረታችንን የሳቡትን ወይም ለተግባር ያነሳሱንን ነጥቦች የቤተሰብ ጥናት በምናደርግበት ወቅት እንዲሁም በዕለታዊ ጭውውታችን ላይ እንወያይባቸዋለን።” እነዚህ ባልና ሚስት ጥልቀት ያለው የግል ጥናት ማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታ ያስገኘላቸው ከመሆኑም ሌላ ‘ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጉ እንዲሄዱ’ ረድቷቸዋል።

በምታጠኑበት ጊዜ የማወቅ ጕጕት ይኑራችሁ

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” እንደሆነ እናምናለን። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ይህ እውነታ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ያነበብነውን ነገር ‘ለማስተዋል’ ጥረት ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። (ማቴ. 15:10) የምናነበውን ነገር ለማስተዋል የሚረዳን አንዱ ነገር በጕጕት ማጥናት ነው። የጥንቶቹ የቤርያ ሰዎች እንደዚህ አድርገዋል፤ ጳውሎስ ምሥራቹን በነገራቸው ወቅት “ነገሩ እንደዚህ ይሆንን እያሉ መጻሕፍትን በየዕለቱ በመመርመር ቃሉን በታላቅ ጕጕት ተቀብለዋል።”—ሥራ 17:11

አንተስ የአምላክን ቃል በታላቅ ጕጕት በማጥናት የቤርያ ሰዎችን ምሳሌ ትከተላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ስታጠና አላስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ሐሳብህ እንዳይከፋፈል ጥረት ታደርጋለህ? አንድ ክርስቲያን ቀደም ሲል ማጥናት የማያስደስተው ቢሆንም የቤርያ ሰዎችን ምሳሌ ለመኮረጅ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የማንበብም ሆነ የማጥናት ፍላጎታቸው ይቀንሳል፤ ክርስቲያኖች ግን ይህ እንዲሆን መፍቀድ አይኖርባቸውም። አንድ ሰው በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ትኩረቱን የሚከፋፍሉ ነገሮችን ማስወገድ ይችላል። አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ካነበብካቸው ነገሮች ውስጥ ለሌሎች ልታካፍል የምትችለውን ሐሳብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ በምታጠናበት ወቅት ያገኘሃቸውን ሐሳቦች ለትዳር ጓደኛህ ወይም ክርስቲያን ለሆነ ወዳጅህ ለማካፈል የታሰበበት ጥረት ልታደርግ ትችል ይሆን? እንዲህ ማድረግህ ያነበብካቸው ሐሳቦች በአእምሮህና በልብህ ውስጥ እንዲቀረጹ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።

በጥናትህ ወቅት በጥንት ዘመን የነበረው ዕዝራ የተባለ የአምላክ አገልጋይ የተወውን ምሳሌ መከተልህ ጠቃሚ ነው፤ ዕዝራ የይሖዋን ‘ሕግ ይፈልግ ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።’ (ዕዝራ 7:10 የ1954 ትርጉም) አንተስ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ለጥናት አመቺ ሁኔታ እንዲኖር አድርግ። ከዚያም ይሖዋ መመሪያና ጥበብ እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቀው። (ያዕ. 1:5) ‘ከጥናቴ ምን ትምህርት አገኛለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በምታነብበት ጊዜ ቁልፍ የሆኑ ነጥቦችን ለማስተዋል ንቁ ሁን። እነዚህን ነጥቦች በማስታወሻህ ላይ ማስፈር ወይም ለማስታወስ በምትፈልጋቸው ሐሳቦች ላይ ምልክት ማድረግ ትችላለህ። ያነበብከውን ነገር፣ በአገልግሎት ላይ እንዲሁም ውሳኔ በምታደርግበት ጊዜ ወይም የእምነት ባልንጀሮችህን ለማበረታታት እንዴት ልትጠቀምበት እንደምትችል አስብ። ጥናትህን ወደማጠናቀቁ ስትቃረብ ያነበብካቸውን ነገሮች መለስ ብለህ ከልሳቸው። እንዲህ ማድረግህ የተማርከውን ነገር እንዳትረሳው ያስችልሃል።

ኤቫ ለጥናት የምትጠቀምበትን ዘዴ በተመለከተ እንዲህ ብላለች:- “መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ በኅዳጉ ላይ የሚገኙትን ማጣቀሻዎች፣ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫን (እንግሊዝኛ) እንዲሁም በሲዲ የተዘጋጀውን ዋችታወር ላይብረሪ እመለከታለሁ። ከዚያም በአገልግሎት ልጠቀምባቸው ያሰብኳቸውን ሐሳቦች በማስታወሻዬ ላይ አሰፍራቸዋለሁ።” *

አንዳንዶች ለበርካታ ዓመታት ጥልቀት ያለው ጥናት በማድረግ መንፈሳዊ ነገሮችን ሲማሩ ቆይተዋል። (ምሳሌ 2:1-5) ያም ቢሆን በዛ ያሉ ኃላፊነቶች ስላሉባቸው ለግል ጥናት ጊዜ መመደብ አስቸጋሪ እየሆነባቸው ነው። የአንተም ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ከሆነ በፕሮግራምህ ላይ ምን ማስተካከያዎች ማድረግ ትችላለህ?

ለጥናት የሚሆን ጊዜ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

የሚያስደስቱህን ነገሮች ለማከናወን ጊዜ ማግኘት ቀላል ነው ቢባል ትስማማ ይሆናል። ብዙዎች፣ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደማንበብ ያሉ ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች ማውጣታቸው ለግል ጥናት ትልቅ ቦታ ለመስጠት እንደሚረዳ ተገንዝበዋል። እርግጥ ነው፣ ረጃጅም የዘር ሐረግ ዝርዝሮችን እንዲሁም በጥንት ጊዜ ስለነበረው ቤተ መቅደስ በዝርዝር የሚገልጹ ሐሳቦችን ወይም በየዕለቱ ከሚያጋጥሙን ነገሮች ጋር ተዛምዶ የሌላቸው የሚመስሉ ውስብስብ ትንቢቶችን ማንበብ አሰልቺ ሊመስል ይችላል። እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ያወጣኸው ግብ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን እርምጃዎች ውሰድ። ለአብነት ያህል፣ አስቸጋሪ የሚመስል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መመርመር ከመጀመርህ በፊት ታሪኩ በተፈጸመበት ወቅት ስለነበሩት ሁኔታዎች ወይም ከትምህርቱ ስለምታገኘው ጥቅም አስቀድመህ ማንበብ ትችላለህ። እንዲህ ያለውን መረጃ ወደ 50 በሚጠጉ ቋንቋዎች ከተተረጎመው “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉና ጠቃሚ ናቸው” (እንግሊዝኛ) ከተባለው መጽሐፍ ወይም “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” ትክክለኛና ጠቃሚ ናቸው ከተባለው ብሮሹር ማግኘት ትችላለህ።

መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበት ጊዜ የምታነበውን ነገር በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት መሞከርህ ንባብህን አስደሳች ያደርግልሃል። እንዲህ ማድረግህ በታሪኩ ውስጥ ያሉትን ሰዎችና የተከናወኑትን ነገሮች በአእምሮህ ለመሳል ይረዳሃል። ከላይ የተመለከትናቸውን ሐሳቦች ብቻ እንኳ ተግባራዊ ማድረግህ የግል ጥናትህ አስደሳች ብሎም የሚክስ እንዲሆን ሊያደርግልህ ይችላል። ይህም ለግል ጥናት ጊዜ ለመመደብ የበለጠ እንድትጓጓ ያነሳሳሃል። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ ማዳበር ቀላል ይሆንልሃል።

ከላይ የቀረቡት ሐሳቦች በግለሰብ ደረጃ ሊረዱ ቢችሉም የተጣበበ ፕሮግራም ያለው ቤተሰብስ ምን ማድረግ ይችላል? የቤተሰብ ጥናት ማድረግ ያሉትን ጥቅሞች አንድ ላይ ሰብሰብ ብላችሁ ለምን አትወያዩም? እንደዚህ ዓይነት ውይይት ማድረጋችሁ ተግባራዊ ልታደርጓቸው የምትችሉ ሐሳቦችን እንድታስተውሉ ይረዳችሁ ይሆናል፤ ለምሳሌ በየዕለቱ ወይም በተወሰኑ ቀናት ጠዋት ላይ ከወትሮው ትንሽ ቀደም ብላችሁ በመነሳት መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ፕሮግራም ማውጣት ትችሉ ይሆናል። ወይም ደግሞ በቤተሰባችሁ ፕሮግራም ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባችሁ ልታስተውሉ ትችላላችሁ። ለአብነት ያህል፣ አንዳንድ ቤተሰቦች ምግብ ተመግበው ሲያበቁ በዕለቱ ጥቅስ ላይ ውይይት ማድረግ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አመቺ ሆኖ አግኝተውታል። የቤተሰቡ አባላት የተመገቡባቸውን ዕቃዎች ማነሳሳት ከመጀመራቸው ወይም ሌላ ሥራ ለማከናወን ከመሄዳቸው በፊት ለ10 ወይም ለ15 ደቂቃ ያህል በዕለቱ ጥቅስ ላይ ይወያያሉ፤ አሊያም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ፕሮግራም መሠረት የሳምንቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ያነባሉ። እንዲህ ማድረጉ መጀመሪያ አካባቢ በተወሰነ መጠን ከባድ ቢመስልም ብዙም ሳይቆይ የቤተሰቡ አባላት ይህን ዝግጅት ሊለምዱትና ፕሮግራሙ በጣም አስደሳች ሊሆንላቸው ይችላል።

ቮይቼክ እና ማዉጎዛታ፣ ቤተሰባቸውን የጠቀመው ምን እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ከዚህ በፊት፣ የማይረቡና እምብዛም ጠቃሚ ያልሆኑ ነገሮች ጊዜያችንን ይሻሙብን ነበር። [በመሆኑም] ኢ-ሜይል በመጻጻፍ የምናሳልፈውን ጊዜ ለመቀነስ ወሰንን። በመዝናኛ የምናሳልፈውን ጊዜም የቀነስን ሲሆን ጥልቀት ያለው ጥናት የምናደርግበት ቀንና ሰዓት መደብን።” ይህ ቤተሰብ እንዲህ ያለውን ማስተካከያ በማድረጉ እንደማይቆጭ ምንም ጥርጥር የለውም፤ እናንተም እንዲህ ብታደርጉ በውሳኔያችሁ አትቆጩም።

ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጉ መሄድ ይክሳል!

የአምላክን ቃል በጥልቀት ማጥናት “በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ” ለማፍራት ያስችላል። (ቈላ. 1:10) በመልካም ሥራ ፍሬ ስታፈራ ደግሞ ማደግህ ለሰው ሁሉ የሚታይ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት እውነቶች ጥልቀት ያለው እውቀት ያለህ መንፈሳዊ ሰው ትሆናለህ። የምታደርጋቸው ውሳኔዎች የበለጠ ሚዛናዊነት የሚንጸባረቅባቸው ይሆናሉ፤ እንዲሁም እውቀት የሌላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ እንደሚያደርጉት ጽንፈኛ ሳትሆን ሌሎችን በተሻለ መንገድ መርዳት ትችላለህ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ወደ ይሖዋ ይበልጥ ትቀርባለህ። ስለ ባሕርያቱ ጥልቅ የሆነ አድናቆት የሚያድርብህ ሲሆን ይህም ስለ እሱ ስትናገር በግልጽ ይታያል።—1 ጢሞ. 4:15፤ ያዕ. 4:8

በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ብትገኝ አሊያም ምንም ያህል ተሞክሮ ቢኖርህ በአምላክ ቃል ሁልጊዜ ለመደሰትና በጕጕት ጥልቅ የሆነ ጥናት ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርግ። ይሖዋ የምታደርገውን ጥረት እንደማይረሳ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ዕብ. 6:10) የተትረፈረፉ በረከቶችን በመስጠት ይክስሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.17 በታኅሣሥ 15 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የሚወጣውን የርዕስ ማውጫ መመልከትም ይቻላል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደግን ስንሄድ’ . . .

በአምላክ ላይ ያለን እምነት ይጠናከራል፤ እንዲሁም ለይሖዋ እንደሚገባ ሆነን እንኖራለን።—ቈላ. 1:9, 10

አስተዋይ እንሆናለን፤ እንዲሁም ማመዛዘን የታከለባቸው ውሳኔዎችን ማድረግ እንችላለን።መዝ. 119:99

ሌሎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ መርዳት ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል።ማቴ. 28:19, 20

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለጥናት አመቺ ሁኔታ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም እንዲህ ማድረጉ አስፈላጊ ነው

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ቤተሰቦች ምግብ ተመግበው ሲያበቁ መጽሐፍ ቅዱስን ያነባሉ