በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቲቶና ለፊልሞና እንዲሁም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

ለቲቶና ለፊልሞና እንዲሁም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

ለቲቶና ለፊልሞና እንዲሁም ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የተጻፉት ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከእስር ከተፈታ ብዙም ሳይቆይ ወደ ቀርጤስ ደሴት ሄዶ ነበር። ጳውሎስ በቀርጤስ የሚገኙትን ጉባኤዎች መንፈሳዊ ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ ቲቶ በዚያ ቆይቶ እንዲረዳቸው አደረገ። ቆየት ብሎም ጳውሎስ፣ ቲቶ ማከናወን ያለበትን ሥራ የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈለት፤ ቲቶ ይህን ሥራ እንዲያከናውን ሥልጣን የሰጠው ሐዋርያው ጳውሎስ መሆኑም በደብዳቤው ላይ ተገልጿል። ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው መቄዶንያ በነበረበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም።

ሐዋርያው ጳውሎስ በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከመጀመሪያው እስር ከመለቀቁ ጥቂት ቀደም ብሎ በቈላስይስ ይኖር ለነበረ ፊልሞና የተባለ ክርስቲያን ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ይህ ደብዳቤ ጳውሎስ አንድ ወዳጁን በተመለከተ ያቀረበውን ልመና ይዟል።

በተጨማሪም በ61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ጳውሎስ በይሁዳ ለሚኖሩት ዕብራውያን አማኞች ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን በደብዳቤው ላይ ክርስትና ከአይሁድ ሥርዓት ብልጫ እንዳለው ገልጿል። ሦስቱም ደብዳቤዎች ለእኛ ጠቃሚ ምክር ይዘውልናል።—ዕብ. 4:12

ትክክለኛ እምነት ይዞ መኖር

(ቲቶ 1:1 እስከ 3:15)

ጳውሎስ ‘በየከተማው ሽማግሌዎችን እንዲሾም’ ለቲቶ መመሪያ ሰጥቶታል፤ እንዲሁም “ትክክለኛ እምነት እንዲኖራቸው” ዐመፀኞችን “አጥብቀህ ገሥጻቸው” በማለት መክሮታል። አክሎም በቀርጤስ በሚገኙት ጉባኤዎች ያሉት ክርስቲያኖች በሙሉ ‘አምላካዊ ያልሆነ ምግባርን ክደው ጤናማ አስተሳሰብ በመያዝ እንዲኖሩ’ አሳስቧቸዋል።—ቲቶ 1:5, 10-13፤ 2:12 NW

ጳውሎስ በቀርጤስ ያሉት ወንድሞች በመንፈሳዊ ጤናማ ሆነው እንዲኖሩ የሚረዳቸው ተጨማሪ ምክር ሰጥቷቸዋል። ቲቶንም “ከንቱ ከሆነ ክርክርና . . . ስለ ሕግ ከሚነሣ ጠብ ራቅ” በማለት መክሮታል።—ቲቶ 3:9

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

1:15“ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኵሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም” ሲባል ምን ማለት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ ጳውሎስ “ሁሉም ነገር” ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ጳውሎስ የተናገረው በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል ውስጥ በቀጥታ ስለተወገዙት ነገሮች ሳይሆን አንድ አማኝ በሕሊናው ተመርቶ ውሳኔ ማድረግ ስለሚችልባቸው ጉዳዮች ነው። ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ አስተሳሰብ ላለው ሰው፣ አምላክ በቀጥታ ያላወገዛቸው ነገሮች ሁሉ ንጹሕ ናቸው። አስተሳሰቡ ለተዛባና ሕሊናው ለረከሰ ሰው ግን እንዲህ ያሉት ነገሮች ንጹሕ አይደሉም። *

3:5—ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በመታጠብ የዳኑት’ እንዲሁም ‘በመንፈስ ቅዱስ የታደሱት’ እንዴት ነው? ‘በመታጠብ ድነዋል’ የሚባለው አምላክ በቤዛዊው መሥዋዕት አማካኝነት በኢየሱስ ደም ስላጠባቸው ወይም ስላነጻቸው ነው። ‘በመንፈስ ቅዱስ ታድሰዋል’ ሊባሉ የሚችሉት ደግሞ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በመሆን “አዲስ ፍጥረት” ስለሆኑ ነው።—2 ቆሮ. 5:17

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:10-13፤ 2:15:- ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በጉባኤ ውስጥ የሚታዩ ስሕተቶችን ለማረም ደፋሮች መሆን ይኖርባቸዋል።

2:3-5:- በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ጎልማሳ እህቶችም “በአኗኗራቸው የተከበሩ” መሆን ይኖርባቸዋል፤ በተጨማሪም “በጎ የሆነውን የሚያስተምሩ እንጂ የሰው ስም የሚያጠፉ ወይም በወይን ጠጅ ሱስ የተጠመዱ” ሊሆኑ አይገባም። እንዲህ ያሉ እህቶች በጉባኤ ውስጥ ያሉ ‘ወጣት ሴቶችን’ በግል በማስተማር ረገድ ውጤታማ መሆን ይችላሉ።

3:8, 14 NW:- አእምሯችንን “ሁልጊዜ በመልካም ሥራዎች ማስጠመድ” በአምላክ አገልግሎት ፍሬያማ ለመሆን እንዲሁም ከዚህ ክፉ ዓለም የተለየን ሆነን ለመኖር ስለሚያስችለን ‘መልካምና ጠቃሚ’ ነው።

“በፍቅር” አጥብቆ መምከር

(ፊል. 1-25)

ፊልሞና ‘በእምነትና በፍቅር’ ምሳሌ በመሆኑ ተመስግኗል። እንዲሁም ለእምነት ባልንጀሮቹ የብርታት ምንጭ መሆኑ ለጳውሎስ “ታላቅ ደስታና መጽናናት” አስገኝቶለታል።—ፊል. 4, 5, 7

በፊልሞና እና በአናሲሞስ መካከል የተፈጠረውን ከበድ ያለ ጉዳይ በተመለከተ ጳውሎስ ለፊልሞና ትእዛዝ ከመስጠት ይልቅ “በፍቅር” ላይ የተመሠረተ ምክር በመለገስ ለሁሉም የበላይ ተመልካቾች ግሩም ምሳሌ ትቷል። ጳውሎስ ፊልሞናን “ታዛዥ መሆንህን በመተማመን፣ ከምጠይቀውም በላይ እንደምታደርግ በማወቅ እጽፍልሃለሁ” ብሎታል።—ፊል. 8, 9, 21

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

10, 11, 18—አስቀድሞ ‘የሚጠቅም ያልነበረው’ አናሲሞስ “የሚጠቅም ሰው” የሆነው እንዴት ነው? አናሲሞስ፣ በቈላስይስ ከሚገኘው ከፊልሞና ቤት ጠፍቶ ወደ ሮም የሸሸ ታዛዥ ያልሆነ ባሪያ ነበር። አናሲሞስ 1,400 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ጉዞ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከጌታው ሳይሰርቅ አልቀረም። በእርግጥም አናሲሞስ ለፊልሞና የሚጠቅም ሰው አልነበረም። ሆኖም አናሲሞስ ሮም ከደረሰ በኋላ ከጳውሎስ ጋር ስለተገናኘ ክርስቲያን ሆኖ ነበር። ቀደም ሲል ‘የሚጠቅም ያልነበረው’ ይህ ባሪያ ክርስቲያን በመሆኑ “የሚጠቅም ሰው” መሆን ችሏል።

15, 16—ጳውሎስ፣ አናሲሞስን ነፃ እንዲለቀው ፊልሞናን ያልጠየቀው ለምን ነበር? ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔርን መንግሥት ከመስበክና ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከማስተማር’ ተልእኮው ውጪ በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ መግባት አልፈለገም። በመሆኑም ከባርነት ጋር የተያያዙ ሁኔታዎችን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላለመጠላለፍ መርጧል።—ሥራ 28:31

ምን ትምህርት እናገኛለን?

2:- ፊልሞና በቤቱ ውስጥ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ፈቅዶ ነበር። እኛም በቤታችን ውስጥ የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ የሚደረግ ከሆነ ትልቅ መብት አግኝተናል።—ሮሜ 16:5፤ ቈላ. 4:15

4-7:- በእምነትና በፍቅር ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን ማመስገን ይኖርብናል።

15, 16:- በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከልክ በላይ እንድንጨነቅ ሊያደርጉን አይገባም። ከአናሲሞስ ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ሁኔታ መመልከት እንደምንችለው ያጋጠሙን ነገሮች የኋላ ኋላ መልካም ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ።

21:- ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር እንደሚለው ጳውሎስ ተማምኖ ነበር። እኛም በተመሳሳይ ያስቀየመን ወንድም ካለ ይቅር እንድንለው ይጠበቅብናል።—ማቴ. 6:14

“ወደ ብስለት እንሂድ”

(ዕብ. 1:1 እስከ 13:25)

ጳውሎስ፣ በኢየሱስ ቤዛ ላይ እምነት ማሳደር ሕግን ከመጠበቅ እንደሚልቅ ለማሳየት ሲል የክርስትና መሥራች፣ የክህነት አገልግሎቱ፣ መሥዋዕቱ እንዲሁም አዲሱ ቃል ኪዳን ከሁሉ እንደሚበልጡ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዕብ. 3:1-3፤ 7:1-3, 22፤ 8:6፤ 9:11-14, 25, 26) የዕብራውያን ክርስቲያኖች ይህንን ማወቃቸው አይሁዳውያን ያደረሱባቸውን ስደት መቋቋም እንዲችሉ እንደረዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች “ወደ ብስለት እንሂድ” በማለት አሳስቧቸዋል።—ዕብ. 6:1

በክርስትና ውስጥ እምነት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ጳውሎስ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም” በማለት ጽፏል። እንዲሁም የዕብራውያን ክርስቲያኖችን “በፊታችን ያለውን ሩጫ በጽናት እንሩጥ” ሲል አበረታቷቸዋል፤ ይህ ደግሞ እምነት ማዳበርን ይጠይቃል።—ዕብ. 11:6፤ 12:1

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው:-

2:14, 15—ሰይጣን “በሞት ላይ ኀይል” እንዳለው መገለጹ የፈለገውን ሰው ሁሉ መግደል እንደሚችል የሚያሳይ ነው? አይደለም። ሆኖም ሰይጣን በኤደን የክፋት አካሄዱን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተናገራቸው ውሸቶች የሰው ልጆችን ለሞት ዳርገዋል፤ ይህም የሆነው አዳም ኃጢአት በመሥራቱና ለሰብዓዊው ቤተሰብ ኃጢአትንና ሞትን በማውረሱ ነው። (ሮሜ 5:12) ከዚህም በተጨማሪ የሰይጣንን ዓላማ የሚያራምዱ ሰዎች በኢየሱስ ላይ እንዳደረጉት የአምላክ አገልጋዮችን እስከ ሞት ድረስ አሳደዋቸዋል። ይህ መሆኑ ግን ሰይጣን የፈለገውን ሁሉ ለመግደል የሚያስችል ኃይል እንዳለው አያመለክትም። ሰይጣን እንዲህ ዓይነት ኃይል ቢኖረው ኖሮ የይሖዋን አምላኪዎች በሙሉ ከረጅም ጊዜ በፊት ባጠፋቸው ነበር። ይሖዋ፣ ለሕዝቦቹ በቡድን ደረጃ ጥበቃ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ሰይጣን ከምድር ገጽ እንዲያጠፋቸው አይፈቅድለትም። አምላክ፣ አንዳንዶቻችን በሰይጣን ጥቃት ሕይወታችንን እንድናጣ ቢፈቅድም እንኳ ያጣነውን ማንኛውንም ነገር መልሶ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

4:9-11—ወደ አምላክ “ዕረፍት ለመግባት” የምንችለው እንዴት ነው? አምላክ በስድስቱ የፍጥረት ቀናት መጨረሻ ላይ ከፍጥረት ሥራው አርፏል፤ ይህን ያደረገው ከምድርና ከሰው ዘር ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ እንደሚፈጸም እርግጠኛ በመሆን ነበር። (ዘፍ. 1:28፤ 2:2, 3) “ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት” በሥራችን ራሳችንን ለማጽደቅ ጥረት ከማድረግ መራቅ እንዲሁም አምላክ መዳን እንድናገኝ ያደረገውን ዝግጅት መቀበል ይኖርብናል። የራሳችንን ጥቅም ከማሳደድ ይልቅ በይሖዋ ላይ እምነት የምናሳድር እንዲሁም በታዛዥነት ልጁን የምንከተል ከሆነ በየዕለቱ መንፈስን የሚያድስና እረፍት የሚሰጥ በረከት እናገኛለን።—ማቴ. 11:28-30

9:16 NW—ከአዲሱ ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ “ቃል ኪዳኑን የገባው ሰው” የተባለው ማን ነው? አዲሱን ቃል ኪዳን ያዘጋጀው ይሖዋ ሲሆን “ቃል ኪዳኑን የገባው ሰው” የተባለው ደግሞ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ የዚህ ቃል ኪዳን አስታራቂ ሲሆን በሞቱም ይህ ቃል ኪዳን የጸና እንዲሆን የሚያስፈልገውን መሥዋዕት አቅርቧል።—ሉቃስ 22:20፤ ዕብ. 9:15

11:10, 13-16—አብርሃም የሚጠባበቀው የትኛዋን “ከተማ” ነበር? ይህች ከተማ ምሳሌያዊ እንጂ እውነተኛ ከተማ አልነበረችም። አብርሃም ይጠባበቅ የነበረው በክርስቶስ ኢየሱስና አብረውት በሚገዙት 144,000 ሰዎች የተዋቀረችውን “ሰማያዊት ኢየሩሳሌም” ነው። ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙት ሰዎች በሰማይ ክብር ከተጎናጸፉ በኋላ “ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ተብለውም ተጠርተዋል። (ዕብ. 12:22፤ ራእይ 14:1፤ 21:2) አብርሃም በጉጉት ይጠባበቅ የነበረው በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር የሚያገኘውን ሕይወት ነው።

12:2 NW—ኢየሱስ ‘በመከራ እንጨት ላይ እስከመሞት ድረስ እንዲጸና’ የረዳው ‘ከፊቱ ይጠብቀው የነበረው ደስታ’ ምንድን ነው? ኢየሱስ የይሖዋ ስም እንዲቀደስና ሉዓላዊነቱ እንዲረጋገጥ ማድረጉን እንዲሁም የሰውን ዘር ከሞት መቤዠቱን ጨምሮ በአገልግሎቱ ያከናወናቸውን ነገሮች በማየት የሚያገኘው ደስታ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ንጉሥና ሊቀ ካህናት በመሆን የሰው ዘርን የሚጠቅምበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቅ ነበር።

13:20—አዲሱ ቃል ኪዳን ‘የዘላለም’ ኪዳን እንደሆነ የተገለጸው ለምንድን ነው? በሦስት ምክንያቶች የተነሳ ነው፦ (1) በሌላ ቃል ኪዳን ስለማይተካ፣ (2) የሚያከናውናቸው ነገሮች ዘላቂ ስለሆኑ እንዲሁም (3) “ሌሎች በጎች” ከአርማጌዶን በኋላም በአዲሱ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ መሆናቸውን ስለሚቀጥሉ ነው።—ዮሐ. 10:16

ምን ትምህርት እናገኛለን?

5:14 NW:- የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት እንዲሁም የተማርናቸውን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የማስተዋል ችሎታችንን’ ማሠልጠን የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።—1 ቆሮ. 2:10

6:17-19:- ተስፋችን አምላክ በገባው ቃል እንዲሁም በመሐላው ላይ የተመሠረተ መሆኑ ከእውነት መንገድ እንዳንወጣ ይረዳናል።

12:3, 4:- ቀላል የሆኑ ፈተናዎች ወይም ተቃውሞዎች ሲያጋጥሙን ‘ዝለን ተስፋ ከመቁረጥ’ ይልቅ ወደ ጉልምስና ማደግ እንዲሁም ፈተናዎችን የመቋቋም ችሎታችንን ማጠናከር ይኖርብናል። ‘ደማችንን እስከ ማፍሰስ ድረስ ለመቃወም’ ማለትም እስከ ሞት ድረስ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።—ዕብ. 10:36-39

12:13-15:- “መራራ ሥር” ወይም በጉባኤ ውስጥ ነገሮች በሚከናወኑበት መንገድ ላይ ስሕተት የሚፈላልግ ማንኛውም ሰው፣ ‘ለእግራችን ቀና መንገድ ከማበጀት’ እንዲያግደን መፍቀድ አይኖርብንም።

12:26-28:- በአምላክ ሳይሆን በሌሎች “የተፈጠሩት” ነገሮች ይኸውም በአሁኑ ጊዜ ያለው ሥርዓትና ክፉ የሆኑት “ሰማያት” በሙሉ ይናወጣሉ ማለትም ድምጥማጣቸው ይጠፋል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጸንተው የሚኖሩት “የማይናወጡት” ነገሮች ማለትም የአምላክ መንግሥትና ደጋፊዎቹ ብቻ ናቸው። እንግዲያው ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት ማወጃችንና በዚህ መንግሥት መመሪያዎች መሠረት መኖራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

13:7, 17:- በጉባኤ ውስጥ ላሉት የበላይ ተመልካቾች እንድንታዘዝና እንድንገዛ የተሰጠንን ይህንን ምክር መከተላችን የትብብር መንፈስ እንድናሳይ ይረዳናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]