በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ያህል መሥዋዕት ትከፍላለህ?

የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ያህል መሥዋዕት ትከፍላለህ?

የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ያህል መሥዋዕት ትከፍላለህ?

“ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?”—ማቴ. 16:26

1. ኢየሱስ፣ የጴጥሮስን ሐሳብ የተቃወመው ለምን ነበር?

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ የሚወደው መሪው ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተሠቃይቶ እንደሚሞት “በግልጽ” ሲናገር ሲሰማ ጆሮውን ማመን አልቻለም! “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” በማለት ኢየሱስን ይገሥጸው ጀመር፤ ጴጥሮስ ይህን ያለው ለጌታው በማሰብ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ግን ለጴጥሮስ ጀርባውን በመስጠት ሌሎቹን ደቀ መዛሙርት ዘወር ብሎ ተመለከታቸው። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት እንደ ጴጥሮስ የተሳሳተ አመለካከት ሳይኖራቸው አልቀረም። ኢየሱስ ይህንን ካስተዋለ በኋላ ጴጥሮስን “አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለ ሌለ መሰናክል ሆነህብኛል!” አለው።—ማር. 8:32, 33፤ ማቴ. 16:21-23

2. ኢየሱስ ከአንድ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ምን እንደሚጠበቅ የገለጸው እንዴት ነው?

2 ኢየሱስ ቀጥሎ የተናገረው ነገር፣ ጴጥሮስ ላቀረበው ሐሳብ ጠንከር ያለ ምላሽ የሰጠበትን ምክንያት ጴጥሮስ እንዲያስተውል ሳይረዳው አልቀረም። ኢየሱስ “ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ ‘ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም [“የራሱን የመከራ እንጨት፣” NW] ተሸክሞ ይከተለኝ፤ ነፍሱን ለማዳን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል።’” (ማር. 8:34, 35) እዚህ ላይ ኢየሱስ ‘ነፍስ’ የሚለውን ቃል የተጠቀመው “ሕይወትን” ለማመልከት ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት ለማድረግ የተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ ተከታዮቹም በአምላክ አገልግሎት ሕይወታቸውን መሥዋዕት ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸው ነበር። ይህን ካደረጉ ታላቅ በረከት ያገኛሉ።—ማቴዎስ 16:27ን አንብብ።

3. (ሀ) ኢየሱስ ለአድማጮቹ የትኞቹን ጥያቄዎች አቅርቦላቸዋል? (ለ) ኢየሱስ ያነሳው ሁለተኛ ጥያቄ አድማጮቹ ምን እንዲያስታውሱ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል?

3 በዚያው ወቅት ኢየሱስ ትኩረት የሚስቡ ሁለት ጥያቄዎችን አንስቷል፤ “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር። (ማቴ. 16:26) ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ የመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ግልጽ ነው። አንድ ሰው፣ ዓለም ሁሉ የእሱ ቢሆንና ሕይወቱን ወይም ነፍሱን ቢያጣ ምንም አይጠቀምም። አንድ ሰው ባሉት ነገሮች ሊደሰት የሚችለው በሕይወት ሲኖር ብቻ ነው። ኢየሱስ “ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?” በማለት ያነሳው ሁለተኛ ጥያቄ አድማጮቹ፣ “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” በማለት ሰይጣን በኢዮብ ዘመን የሰነዘረውን ክስ እንዲያስታውሱ አድርጓቸው ይሆናል። (ኢዮብ 2:4) ሰይጣን የሰነዘረው ሐሳብ ይሖዋን ከማያመልኩ አንዳንድ ሰዎች ጋር በተያያዘ እውነት ሊሆን ይችላል። ብዙዎች ሕይወታቸውን ላለማጣት ሲሉ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወይም የትኛውንም የሥነ ምግባር ሕግ ከመጣስ ወደኋላ አይሉም። ክርስቲያኖች ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት አላቸው።

4. ኢየሱስ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ለክርስቲያኖች ጥልቅ ትርጉም አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?

4 ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በዚህ ዓለም ውስጥ ጥሩ ጤንነትና ሀብት ሊሰጠን እንዲሁም ረጅም ዕድሜ መኖር እንድንችል ሊረዳን እንዳልሆነ እናውቃለን። ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር የምንችልበት አጋጣሚ ሊከፍትልን ሲሆን እኛም ይህን ተስፋ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። (ዮሐ. 3:16) አንድ ክርስቲያን፣ ኢየሱስ ያነሳው የመጀመሪያ ጥያቄ “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ፣ የዘላለም ሕይወት ተስፋውን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል?” ማለት እንደሆነ ይገነዘባል። የዚህ ጥያቄ መልስ ‘ምንም ጥቅም የለውም’ የሚል ነው። (1 ዮሐ. 2:15-17) ኢየሱስ ላነሳው ሁለተኛ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ‘በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሕይወት የማግኘት ተስፋዬ እውን እንዲሆን በአሁኑ ጊዜ ምን ያህል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ በአኗኗራችን የሚታይ ሲሆን ይህም ተስፋችን ምን ያህል እውን ሆኖ እንደሚታየን የሚጠቁም ነው።—ከዮሐንስ 12:25 ጋር አወዳድር።

5. የዘላለም ሕይወት ስጦታን ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

5 እርግጥ ነው፣ እዚህ ላይ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት በሥራችን የምናገኘው ነገር እንደሆነ መናገሩ አልነበረም። ሕይወት በአጠቃላይ ሌላው ቀርቶ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የምንኖረው አጭር ሕይወትም እንኳ ስጦታ ነው። ሕይወትን መግዛት አንችልም፤ እንዲሁም ሕይወት የሚገባን ነገር እንዲሆን ልናደርገው የምንችለው አንድም ነገር የለም። የዘላለም ሕይወት ስጦታን ማግኘት የምንችልበት ብቸኛው መንገድ “በኢየሱስ ክርስቶስ” እንዲሁም ‘ከልብ ለሚሹት ዋጋ በሚሰጠው’ በይሖዋ “በማመን” ነው። (ገላ. 2:16፤ ዕብ. 11:6) ያም ቢሆን ‘ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ’ ስለሆነ እምነታችን በሥራ መደገፍ አለበት። (ያዕ. 2:26) በመሆኑም ኢየሱስ ባነሳው ጥያቄ ላይ ይበልጥ ስናሰላስል፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ምን ያህል መሥዋዕት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆንን እንዲሁም እምነታችን ሕያው መሆኑን ለማሳየት በይሖዋ አገልግሎት ምን ለማድረግ ፈቃደኞች እንደሆንን በቁም ነገር ማሰባችን ተገቢ ይሆናል።

“ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘም”

6. ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ቅድሚያ የሰጠው ነገር ምንድን ነው?

6 ኢየሱስ በዘመኑ የነበረው ዓለም ሊሰጠው በሚችለው ነገር ላይ ሳይሆን አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጓል፤ እንዲሁም የተደላደለ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ ቁሳዊ ነገሮችን ከማሳደድ ተቆጥቧል። ለአምላክ ታዛዥ በመሆን በሕይወቱ ውስጥ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት አድርጓል። ክርስቶስ ራሱን ከማስደሰት ይልቅ “ምንጊዜም [አምላክን] የሚያስደስተውን” ነገር አድርጓል። (ዮሐ. 8:29) ኢየሱስ፣ አምላክን ለማስደሰት ሲል ምን ያህል መሥዋዕትነት ከፍሏል?

7, 8. (ሀ) ኢየሱስ ምን መሥዋዕትነት ከፍሏል? ምን ሽልማትስ አግኝቷል? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?

7 በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአል።” (ማቴ. 20:28) ከዚህ ቀደም ብሎ ኢየሱስ፣ ‘ነፍሱን እንደሚሰጥ’ ለተከታዮቹ ሲነግራቸው በራሱ ላይ እንዳይጨክን ጴጥሮስ ጠይቆት ነበር። ያም ቢሆን ኢየሱስ ከአቋሙ ወደኋላ አላለም። ነፍሱን ማለትም ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ሕይወቱን በፈቃደኝነት ለሰው ልጆች ሰጥቷል። ኢየሱስ እንዲህ ያለ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አካሄድ በመከተሉ የወደፊት ተስፋው አስተማማኝ ሆኗል። ትንሣኤ ያገኘ ከመሆኑም በላይ ወደ “እግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ” ተደርጓል። (ሥራ 2:32, 33) በዚህ መንገድ ለእኛ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል።

8 ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ‘ራሳቸውን ማስደሰት እንደሌለባቸው’ ምክር የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ “ክርስቶስ ራሱን ደስ አላሰኘም” ብሏቸዋል። (ሮሜ 15:1-3) እኛስ ሐዋርያው የሰጠውን ይህን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ልክ እንደ ኢየሱስ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች የምንሆነው እስከ ምን ድረስ ነው?

ይሖዋ ምርጣችንን እንድንሰጠው ይፈልጋል

9. አንድ ክርስቲያን ሕይወቱን ለአምላክ ሲወስን ምን ምርጫ ማድረጉ ነው?

9 በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ባሪያዎች የነበሩ ዕብራውያን በባርነት ማገልገል በጀመሩ በሰባተኛው ዓመት አሊያም በኢዮቤልዩ ዓመት ነፃ እንዲወጡ የሙሴ ሕግ ያዝዝ ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ባሪያዎች ሌላም ምርጫ ማድረግ ይችሉ ነበር። አንድ ባሪያ፣ ጌታውን የሚወደው ከሆነ ዕድሜ ልኩን በባርነት ለመቀጠል ሊመርጥ ይችላል። (ዘዳግም 15:12, 16, 17ን አንብብ።) እኛም ሕይወታችንን ለይሖዋ ስንወስን ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ምርጫ አድርገናል። የራሳችንን ፍላጎት ሳይሆን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በፈቃደኝነት ተስማምተናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋን ከልባችን እንደምንወደው እንዲሁም እሱን ለዘላለም ለማገልገል እንደምንፈልግ አሳይተናል።

10. የአምላክ ንብረቶች የሆንነው በምን መንገድ ነው? ይህ እውነታ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ምን ተጽዕኖ ማሳደር ይኖርበታል?

10 በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ፣ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ እየተካፈልክ እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እየተገኘህ ከሆነ ይህ የሚያስመሰግንህ ነው። በቅርቡ ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን እንደምትገፋፋና ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ “እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምን ነገር አለ?” በማለት ለፊልጶስ ያቀረበለት ዓይነት ጥያቄ እንደምትጠይቅ ተስፋ እናደርጋለን። (ሥራ 8:35, 36) እንዲህ ስታደርግ ጳውሎስ “እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ በዋጋ ተገዝታችኋል” በማለት የጻፈላቸው ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የነበራቸው ዓይነት ዝምድና ይኖርሃል። (1 ቆሮ. 6:19, 20) ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ይሁን በምድር ላይ መኖር፣ ራሳችንን ለይሖዋ ከወሰንን የእሱ ንብረቶች ነን። እንግዲያው የራስ ወዳድነት ምኞቶቻችንን መቆጣጠራችንና “የሰው ባሪያ” ላለመሆን መጣራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (1 ቆሮ. 7:23) ይሖዋ ደስ ባለው መንገድ የሚጠቀምብን ታማኝ ባሪያዎች መሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

11. ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ታዘዋል? በሙሴ ሕግ ውስጥ መሥዋዕት ስለማቅረብ ከተሰጠው መመሪያ አንጻር ይህ ምን ትርጉም አለው?

11 ጳውሎስ፣ የእምነት ባልንጀሮቹን ሲመክራቸው እንዲህ ብሏቸዋል:- “ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ]። . . . ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኮአችሁ ነው።” (ሮሜ 12:1) ይህ ሐሳብ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የኢየሱስ ተከታዮች ከመሆናቸው በፊት የአምልኳቸው ክፍል የነበረውን መሥዋዕት የማቅረብ ልማድ አስታውሷቸው ሊሆን ይችላል። በሙሴ ሕግ መሠረት አይሁዳውያን በይሖዋ መሠዊያ ላይ የሚያቀርቡት ካሏቸው እንስሳት ሁሉ ምርጡን መሆን እንዳለበት ያውቁ ነበር። እንከን ያለበት እንስሳ ተቀባይነት አልነበረውም። (ሚል. 1:8, 13) ሰውነታችንን “ሕያው መሥዋዕት” አድርገን ከማቅረብ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ለይሖዋ የምንሰጠው ምርጣችንን እንጂ የግል ፍላጎቶቻችንን ሁሉ ካሟላን በኋላ የሚተርፈንን መሆን የለበትም። ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ‘ነፍሳችንን’ ማለትም ሕይወታችንን ያለ ምንም ገደብ ለእሱ ሰጥተናል፤ ይህም ኃይላችንን፣ ቁሳዊ ሀብታችንን እንዲሁም ችሎታችንን ለእሱ መስጠትን ይጨምራል። (ቈላ. 3:23) ይህን መገንዘባችንን በሕይወታችን ውስጥ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ጊዜህን በጥበብ ተጠቀምበት

12, 13. ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

12 ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት የምንችልበት አንዱ መንገድ ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም ነው። (ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።) ይህ ደግሞ ራስን መግዛትን ይጠይቃል። ዓለም የሚያሳድርብን ተጽዕኖ እንዲሁም ፍጽምና የጎደለን መሆናችን፣ ጊዜያችንን የሚያስደስተንን ነገር በማድረግ ወይም የግል ጥቅማችንን በማሳደድ ብቻ የማሳለፍ ፍላጎት እንዲኖረን ሊያደርገን ይችላል። እርግጥ ነው፣ መዝናናትንና ሰብዓዊ ሥራ መሥራትን ጨምሮ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።” (መክ. 3:1) ያም ቢሆን ራሱን ለአምላክ የወሰነ አንድ ክርስቲያን በጊዜ አጠቃቀሙ ረገድ ሚዛናዊ መሆንና ጊዜውን በጥበብ መጠቀም ያስፈልገዋል።

13 ጳውሎስ አቴናን በጎበኘበት ወቅት እንዳስተዋለው “የአቴና ሰዎች በሙሉ እንዲሁም በዚያ የሚኖሩ የውጭ ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ስለ አዳዲስ ነገሮች በማውራትና በመስማት እንጂ በሌላ ጕዳይ አልነበረም።” (ሥራ 17:21) ዛሬም ብዙዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ጊዜያቸውን ያባክናሉ። በዘመናችን ጊዜያችንን ከሚሻሙብን ነገሮች መካከል ቴሌቪዥን መመልከት፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችን መጫወት እንዲሁም የተለያዩ ድረ ገጾችን መቃኘት ይገኙበታል። ትኩረታችንን የሚሰርቁና ጊዜያችንን እንድናባክን የሚያደርጉ ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል። በእነዚህ ነገሮች የምንጠመድ ከሆነ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ችላ ልንል እንችላለን። እንዲያውም “ከሁሉ የሚሻለውን” ነገር ማለትም ከይሖዋ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንኳ ለማከናወን ጊዜ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል።—ፊልጵ. 1:9, 10

14. የትኞቹን ጥያቄዎች በቁም ነገር ልናስብባቸው ይገባል?

14 ስለዚህ ሕይወትህን ለይሖዋ የወሰንክ የእሱ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ:- ‘በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ፣ ለማሰላሰል እንዲሁም ለመጸለይ ጊዜ እመድባለሁ?’ (መዝ. 77:12፤ 119:97፤ 1 ተሰ. 5:17) ‘ለጉባኤ ስብሰባዎች የምዘጋጅበት ፕሮግራም አለኝ? በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት ሌሎችን አንጻለሁ?’ (መዝ. 122:1፤ ዕብ. 2:12) የአምላክ ቃል፣ ጳውሎስና በርናባስ በይሖዋ ሥልጣን “በድፍረት እየተናገሩ ብዙ ጊዜ [እንደቈዩ]” ይናገራል። (ሥራ 14:3) አንተስ በስብከቱ ሥራ ይበልጥ ለመካፈል እንዲያውም በዚህ ሥራ “ብዙ ጊዜ” ለማሳለፍ ሁኔታዎችህን ማስተካከል ትችላለህ? በአቅኚነት ማገልገልስ ትችል ይሆን?—ዕብራውያን 13:15ን አንብብ።

15. ሽማግሌዎች ጊዜያቸውን በጥበብ የሚጠቀሙበት እንዴት ነው?

15 ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ በአንጾኪያ የሚገኘውን የክርስቲያን ጉባኤ በጎበኙበት ወቅት በዚያ ያሉትን “ደቀ መዛሙርት” ለማበረታታት ሲሉ ከእነሱ ጋር “ብዙ ጊዜ” ተቀምጠዋል። (ሥራ 14:28) በዛሬው ጊዜም በተመሳሳይ አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ሌሎችን ለማበረታታት ይጠቀሙበታል። ሽማግሌዎች በመስክ አገልግሎት ከመሳተፍ በተጨማሪ ለመንጋው እረኝነት ለማድረግ፣ የጠፉ በጎችን ለመፈለግ፣ የታመሙትን ለመርዳት እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሏቸውን ሌሎች በርካታ ኃላፊነቶች ለመወጣት ጠንክረው ይሠራሉ። የተጠመቅህ ወንድም ከሆንክ እንደነዚህ ያሉ ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶች ላይ ለመድረስ ሁኔታዎችህ ይፈቅዱልሃል?

16. ‘ለእምነት ቤተሰቦች መልካም ማድረግ’ ከምንችልባቸው መንገዶች ውስጥ አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

16 ብዙዎች፣ በሰው ሠራሽ አሊያም በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እርዳታ በመስጠት ደስታ ማግኘት ችለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ በቤቴል የሚያገለግሉ አንዲት እህት ለሌሎች እርዳታ በመስጠቱ ሥራ ለመካፈል ሲሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ሩቅ ቦታዎች በፈቃደኝነት ተጉዘዋል። እኚህ እህት የእረፍት ጊዜያቸውን ለዚህ ዓላማ ያዋሉት ለምንድን ነው? እንዲህ ብለዋል:- “የተለየ ችሎታ ባይኖረኝም አስፈላጊ የሆነውን ማንኛውንም ነገር መሥራት መቻሌን እንደ መብት እቆጥረዋለሁ። ብዙ ንብረት ያጡ ወንድሞቼና እህቶቼ ያላቸውን ጠንካራ እምነት ስመለከት በጣም እበረታታለሁ።” ከዚህም ሌላ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች የመንግሥት አዳራሾችንና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን በመገንባቱ ሥራ ይካፈላሉ። እኛም እንደዚህ ባሉት ሥራዎች በመካፈል ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ ‘ለእምነት ቤተሰቦች መልካም እናደርጋለን።’—ገላ. 6:10

“ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ”

17. የዘላለም ሕይወት ለማግኘት በግልህ ምን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ነህ?

17 ከአምላክ የራቀው ሰብዓዊ ማኅበረሰብ በቅርቡ ይጠፋል። ይህ የሚሆንበትን ትክክለኛ ጊዜ አናውቅም። ያም ቢሆን “ዘመኑ አጭር” መሆኑን እንዲሁም “የዚህ ዓለም መልክ ዐላፊ” እንደሆነ እናውቃለን። (1 ቆሮንቶስ 7:29-31ን አንብብ።) ይህንን ማወቃችን ኢየሱስ “ሰው በነፍሱ ምትክ ሊከፍለው የሚችለው ዋጋ ምንድን ነው?” በማለት ያነሳውን ጥያቄ ይበልጥ በቁም ነገር እንድናስብበት ሊያደርገን ይገባል። “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ለማግኘት ስንል ይሖዋ የሚጠይቀንን ማንኛውንም መሥዋዕት እንደምንከፍል ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ጢሞ. 6:19) በእርግጥም ኢየሱስ፣ ያለማቋረጥ ‘እንድንከተለው’ እንዲሁም ‘ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን እንድንሻ’ የሰጠንን ምክር ሰምተን ተግባራዊ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።—ማቴ. 6:31-33፤ 24:13

18. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ለምንስ?

18 ኢየሱስን መከተል ቀላል የማይሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ አይካድም፤ አንዳንዶች ይህን በማድረጋቸው ኢየሱስ እንደተናገረው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ያም ቢሆን በራሳችን ላይ እንዳንጨክን ለሚቀርብልን ፈተና ባለመሸነፍ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። ኢየሱስ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ቅቡዓን ተከታዮቹ በገባው ቃል ላይ እምነት አለን። (ማቴ. 28:20) እንግዲያው ጊዜያችንንና ችሎታችንን ምንም ሳንቆጥብ በቅዱስ አገልግሎት ለማዋል ጥረት እናድርግ። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ ከታላቁ መከራ እንደሚያድነን ወይም በአዲሱ ዓለም ውስጥ በትንሣኤ እንደሚያስነሳን እምነት እንዳለን እናረጋግጣለን። (ዕብ. 6:10) በዚህ መንገድ፣ ስጦታ የሆነውን ሕይወትን ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው እናሳያለን።

መልስህ ምንድን ነው?

• አምላክንና ሰዎችን በማገልገል ረገድ ኢየሱስ በምሳሌነት የሚጠቀስ የፈቃደኝነት መንፈስ ያሳየው እንዴት ነው?

• ራሳችንን መካድ የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህንንስ የምናደርገው እንዴት ነው?

• በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ተቀባይነት የሚያገኘው ምን ዓይነት መሥዋዕት ብቻ ነበር? ይህስ በዛሬው ጊዜ መመሪያ የሚሆነን እንዴት ነው?

• ጊዜያችንን በጥበብ መጠቀም የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ምንጊዜም አምላክን የሚያስደስተውን ነገር ያደርግ ነበር

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አድናቂ የሆኑ እስራኤላውያን እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ምርጣቸውን ይሰጡ ነበር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም አምላክን ማስደሰት እንችላለን