በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ይሖዋ ብርታቴ ነው’

‘ይሖዋ ብርታቴ ነው’

‘ይሖዋ ብርታቴ ነው’

ጆን ኮቪል እንደተናገረችው

ሐምሌ 1925 በሃደርስፊልድ፣ እንግሊዝ ውስጥ ተወለድኩ። ለወላጆቼ ብቸኛ ልጅ ነበርኩ። ጥሩ ጤንነት ስላልነበረኝ አባቴ “ነፋስ በነፈሰብሽ ቁጥር ትታመሚያለሽ” ይለኝ ነበር። ደግሞም የጤንነቴ ሁኔታ ሲታይ አባባሉ እውነት ይመስል ነበር!

ልጅ ሳለሁ ቀሳውስት ሰላም እንዲሰፍን አጥብቀው ይጸልዩ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት ወቅት ግን ድል እንዲገኝ መጸለይ ጀመሩ። ይህ ሁኔታ ግራ ያጋባኝ ከመሆኑም ሌላ ጥርጣሬ እንዲፈጠርብኝ አደረገ። በዚሁ ጊዜ አካባቢ አን ራትክሊፍ የተባለች የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን መጣች፤ በወቅቱ በአካባቢያችን የምትኖረው የይሖዋ ምሥክር እሷ ብቻ ነበረች።

እውነትን አወቅሁ

አን፣ ሳልቬሽን የተባለውን መጽሐፍ የሰጠችን ሲሆን ቤቷ በሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ላይ እንድትገኝ እናቴን ጋበዘቻት። * እናቴም አብሬያት እንድሄድ ጠየቀችኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁበት ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት እስከ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። ውይይቱ በቤዛው ዝግጅት ላይ ያተኮረ ቢሆንም አሰልቺ አልነበረም። ለነበሩኝ በርካታ ጥያቄዎች በውይይቱ ላይ መልስ አገኘሁ። በቀጣዩ ሳምንትም በዚህ ውይይት ላይ ተገኘን። በዚያ ዕለት ደግሞ ኢየሱስ ስለ መጨረሻው ዘመን ምልክት የተናገረው ትንቢት ተብራራ። በወቅቱ በዓለም ላይ ከነበሩት መጥፎ ሁኔታዎች አንጻር እኔና እማማ የተማርነው ነገር እውነት መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀብንም። ያን ቀን፣ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ግብዣ ቀረበልን።

በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ከአንዳንድ ወጣት አቅኚዎች ጋር የተዋወቅሁ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ጆይስ ባርበር (አሁን ጆይስ ኤሊስ ተብላለች) ትገኝበታለች፤ እህት ጆይስ በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቷ ከፒተር ጋር በለንደን ቤቴል እያገለገለች ነው። ሁሉም ሰው አቅኚ ሆኖ እንደሚያገለግል ስለተሰማኝ እኔም ገና ተማሪ የነበርኩ ቢሆንም በየወሩ 60 ሰዓት ማገልገል ጀመርኩ።

ከአምስት ወር በኋላ የካቲት 11, 1940 እኔና እናቴ በብራድፎርድ ከተማ በተደረገ የዞን ስብሰባ (አሁን የወረዳ ስብሰባ ይባላል) ላይ ተጠመቅን። አባቴ የምንከተለውን አዲስ ሃይማኖት ባይቃወምም የይሖዋ ምሥክር አልሆነም። እንደተጠመቅሁ አካባቢ መንገድ ላይ መመሥከር ተጀመረ። እኔም የመጽሔት ቦርሳዬንና ማስታወቂያ የተጻፈባቸውን ሠሌዳዎች አንግቤ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል ጀመርኩ። አንድ ቅዳሜ ዕለት፣ ሰው በሚበዛበት የገበያ ቦታ እንድቆም ተመደብኩ። የሰው ፍርሃት የነበረብኝ ሲሆን የዚያን ዕለት ደግሞ ልክ እንደፈራሁት አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች አብዛኞቹ በዚያ ሲያልፉ ተመለከቱኝ!

በ1940 ጉባኤያችን ለሁለት ተከፈለ። ጉባኤያችን ሲከፈል ከእኩዮቼ መካከል አብዛኞቹ በሌላኛው ጉባኤ ውስጥ ተመደቡ። ለሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ ይህን ስነግረው “ወጣት ጓደኞች ለማግኘት ከፈለግሽ ለወጣቶች ስበኪ” በማለት መለሰልኝ። እኔም እንዳለኝ ያደረግሁ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ከኤልሲ ኖብል ጋር ተገናኘሁ። ኤልሲ እውነትን ስለተቀበለች የዕድሜ ልክ ጓደኛሞች ሆንን።

የአቅኚነት አገልግሎትና ያገኘኋቸው በረከቶች

ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ አንድ የሒሳብ ባለሙያ ዘንድ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። ሆኖም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ምን ያህል ደስተኞች እንደሆኑ ስመለከት እኔም አቅኚ ሆኜ ይሖዋን የማገልገል ፍላጎቴ ጨመረ። ግንቦት 1945 ልዩ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ስጀምር በጣም ተደሰትኩ። አቅኚነቴን በጀመርኩበት ዕለት ቀኑን ሙሉ ኃይለኛ ዝናብ ጣለ። ቢሆንም አገልግሎት መውጣቴ በጣም ስላስደሰተኝ ዝናቡ ምንም አልመሰለኝም። እንዲያውም በየቀኑ በአገልግሎት ለመካፈል ስል ከቤት መውጣቴና አዘውትሬ በብስክሌት መንቀሳቀሴ ጤንነቴ እንዲሻሻል ረድቶኛል። በዕድሜዬ ሙሉ ክብደቴ ከ42 ኪሎ በላይ ሆኖ ባያውቅም የአቅኚነት አገልግሎቴን ለማቆም የተገደድኩበት ጊዜ የለም። ባለፉት ዓመታት ሁሉ ቃል በቃል ‘ይሖዋ ብርታቴ’ ሆኖልኛል።—መዝ. 28:7

ከጊዜ በኋላ አዳዲስ ጉባኤዎችን ለማቋቋም ስለተፈለገ የይሖዋ ምሥክሮች በሌሉባቸው ከተሞች ውስጥ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። መጀመሪያ ላይ በእንግሊዝ ለሦስት ዓመት ያገለገልኩ ሲሆን ከዚያም ወደ አየርላንድ ተዛውሬ ሦስት ዓመት ቆይቻለሁ። በሊዝበርን፣ አየርላንድ በአቅኚነት ሳገለግል የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ረዳት ፓስተር የሆነን አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ አስጠና ነበር። ይህ ሰው መሠረታዊ ስለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እውነቱን ሲያውቅ የተማረውን ነገር ለጉባኤው አባላት ማስተማር ጀመረ። ሆኖም አንዳንድ የጉባኤው አባላት ስለ ሁኔታው ለቤተ ክርስቲያኑ ኃላፊዎች ቅሬታቸውን በመግለጻቸው ግለሰቡ ለምን እንደዚህ ዓይነት ትምህርት እንዳስተማረ ተጠየቀ። እሱም ይህን ያደረገው ከዚህ ቀደም ለመንጋው ያስተማረው አብዛኛው ነገር የተሳሳተ እንደነበር የመናገር ክርስቲያናዊ ኃላፊነት እንዳለበት ስለተሰማው እንደሆነ ገለጸ። ይህ ሰው ቤተሰቦቹ አጥብቀው ቢቃወሙትም ሕይወቱን ለይሖዋ የወሰነ ከመሆኑም በላይ እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ በታማኝነት አገልግሏል።

በአቅኚነት አገልግሎት ሁለተኛ ምድቤ በሆነው በላርን፣ አየርላንድ ለስድስት ሳምንታት ለብቻዬ አገልግያለሁ፤ ይህም የሆነው አብራኝ የተመደበችው አቅኚ በ1950 በኒው ዮርክ በተደረገው “የቲኦክራሲው እድገት” የተባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሄዳ ስለነበረ ነው። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ጓጉቼ ስለነበር ይህ ወቅት ለእኔ በጣም ከባድ ነበር። ይሁንና በእነዚያ ሳምንታት በመስክ አገልግሎት በርካታ የሚያበረታቱ ተሞክሮዎችን አግኝቻለሁ። አንድ ቀን፣ ከ20 ዓመታት በፊት የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፍ ደርሷቸው የነበሩ በዕድሜ የገፉ ሰው አገኘሁ። በእነዚህ ዓመታት ጽሑፉን በተደጋጋሚ ስላነበቡት ሙሉውን በቃላቸው ያውቁታል ማለት ይቻላል። እኚህ ሰው፣ ወንድ ልጃቸው እንዲሁም ሴት ልጃቸው እውነትን ተቀበሉ።

በጊልያድ ትምህርት ቤት ሥልጠና ማግኘት

ከእንግሊዝ ከመጡ አሥር አቅኚዎች ጋር በመሆን በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት በ17ኛው ክፍል ገብቼ እንድሠለጥን በ1951 ተጋበዝኩ። በሥልጠና በቆየሁባቸው ወራት ያገኘሁት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዴት የሚያስደስት ነበር! በዚያን ወቅት እህቶች በጉባኤ ውስጥ የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሲመራ ክፍል አያቀርቡም፤ በጊልያድ ግን እህቶች ክፍል እንዲሁም ሪፖርት እንድናቀርብ እንመደብ ነበር። ይህንን ማድረግ በጣም ያስፈራን ነበር! የመጀመሪያ ክፍሌን ባቀረብኩበት ዕለት ማስታወሻዬን የያዝኩበት እጄ ክፍሉን አቅርቤ እስክጨርስ ድረስ ይንቀጠቀጥ ነበር። የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ወንድም ማክስዌል ፍሬንድ “ሁሉም ጥሩ ተናጋሪዎች መጀመሪያ ላይ ይፈራሉ፤ አንቺ ግን እስከ መጨረሻው ድረስ ፍርሃትሽ አልለቀቀሽም” በማለት በቀልድ መልክ ምክር ሰጠኝ። ይህ ሥልጠና ሁላችንም በሰው ፊት ሐሳባችንን የመግለጽ ችሎታችንን እንድናሻሽል ረድቶናል። ሥልጠናው ሳናስበው የተጠናቀቀ ሲሆን ከተመረቅን በኋላ ወደተለያዩ አገሮች ተላክን። እኔ የተመደብኩት ታይላንድ ነበር!

“ፈገግታ የማይለየው ሕዝብ”

በታይላንድ፣ አስትሪድ አንደርሰን ከተባለች እህት ጋር በሚስዮናዊነት እንዳገለግል መመደቤ የይሖዋ ስጦታ እንደሆነ እቆጥረዋለሁ። በጭነት መርከብ ተሳፍረን ታይላንድ ለመድረስ ሰባት ሳምንታት ፈጅቶብናል። በዋና ከተማዋ በባንኮክ የሚገኙት የገበያ ቦታዎች ግርግር የሚበዛባቸው ከመሆናቸው ሌላ በከተማዋ ውስጥ ሕዝቡ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው በጀልባ ነበር። በ1952 በባንኮክ የነበሩት የመንግሥቱ አስፋፊዎች 150 አይሞሉም።

በታይላንድ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጠበቂያ ግንብ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንመለከት ‘ይህንን ቋንቋ የምንለምደው እንዴት ይሆን?’ ብለን አሰብን። በተለይ ደግሞ ቃላትን በትክክለኛው መንገድ መጥራት ተፈታታኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ካኡዩ የሚለው ቃል ሲጠብቅና ሲላላ “ሩዝ” ወይም “ዜና” የሚል ትርጉም ይኖረዋል። በዚህም የተነሳ መጀመሪያ አካባቢ በአገልግሎት ስንካፈል ለሰዎች “ጥሩ ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ” በማለት ፈንታ “ጥሩ ሩዝ ይዤላችሁ መጥቻለሁ” እንላቸው ነበር! ብዙ የሚያስቁ ነገሮች ከተናገርን በኋላ ግን በጊዜ ሂደት ቋንቋውን ለመድነው።

የታይላንድ ሕዝብ በቀላሉ የሚቀረብ ነው። በመሆኑም የታይላንድ ሰዎች፣ “ፈገግታ የማይለየው ሕዝብ” መባላቸው ተገቢ ነው። መጀመሪያ የተመደብነው ኮራት (አሁን ናኮን ራቻሲማ ተብላ ትጠራለች) በተባለች ከተማ ሲሆን በዚያም ለሁለት ዓመታት አገልግለናል። ከዚያም ቺያንግ ማይ በተባለች ከተማ እንድናገለግል ተመደብን። አብዛኞቹ የታይላንድ ነዋሪዎች የቡድሂስት እምነት ተከታዮች ስለሆኑ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አያውቁም። በኮራት ከተማ በነበርንበት ጊዜ የፖስታ ቤቱን ኃላፊ መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናው ነበር። ከዚህ ሰው ጋር የእምነት አባት ስለሆነው ስለ አብርሃም ስንወያይ ሰውየው ይህንን ስም ከዚያ በፊት ስለሚያውቀው የምናገረው ነገር እንደገባው በሚገልጽ መንገድ ራሱን ይነቀንቅ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ሰውየው ስለየትኛው አብርሃም እንደምናገር እንዳልገባው ተገነዘብኩ። የፖስታ ቤቱ ኃላፊ ያሰበው የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ስለነበሩት ስለ አብርሃም ሊንከን ነበር!

ቅን ልብ ያላቸውን የታይላንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ያስደስተን ነበር፤ እነሱ ደግሞ ቀለል ያለ ሕይወት በመምራት እንዴት ደስተኛ መሆን እንደሚቻል አስተምረውናል። እንዲህ ያለ ትምህርት ማግኘታችን በጣም ጠቅሞናል፤ ምክንያቱም በኮራት የሚገኘው የመጀመሪያው የሚስዮናዊ ቤታችን የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ሆነ የቧንቧ ውኃ አልነበረውም። እንዲህ ባሉ አካባቢዎች በመኖራችን ‘አግኝቶም ሆነ አጥቶ የመኖርን ምስጢር ተምረናል።’ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም ‘ኀይልን በሚሰጠን በእሱ’ ብርታት አግኝተናል።—ፊልጵ. 4:12, 13

አዲስ የአገልግሎት ጓደኛና አዲስ ምድብ

በ1945 ወደ ለንደን ሄጄ ነበር። በዚያ ወቅት ከአንዳንድ አቅኚዎችና ቤቴላውያን ጋር በመሆን የብሪትሽ ሙዚየምን ጎበኘን። አብረውኝ ሙዚየሙን ከጎበኙት መካከል አለን ኮቪል ይገኝበታል፤ አለን፣ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በጊልያድ ትምህርት ቤት በ11ኛው ክፍል ሠልጥኗል። አለን መጀመሪያ በፈረንሳይ ከዚያም በቤልጅየም እንዲያገለግል ተመድቦ ነበር። * በታይላንድ በሚስዮናዊነት እያገለገልኩ እያለ አለን እንዳገባው የጠየቀኝ ሲሆን እኔም ተስማማሁ።

ሐምሌ 9, 1955 በብራስልስ፣ ቤልጅየም ተጋባን። ለጫጉላ ሽርሽር ወደ ፓሪስ ለመሄድ እመኝ ስለነበር አለን በቀጣዩ ሳምንት በዚያ በሚካሄደው ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ዝግጅት አደረገ። ይሁንና እዚያ እንደደረስን አለን ሙሉውን ስብሰባ እንዲያስተረጉም ተጠየቀ። በየቀኑ በጠዋት ተነስቶ መሄድ የነበረበት ሲሆን ወዳረፍንበት ቦታ የምንመለሰውም አምሽተን ነበር። እንደተመኘሁት የጫጉላ ሽርሽራችንን በፓሪስ ብናሳልፍም አብዛኛውን ጊዜ አለንን የማየው መድረክ ላይ ሆኖ ነበር! ያም ቢሆን ባለቤቴ፣ ወንድሞችንና እህቶችን ሲያገለግል በማየቴ ተደስቻለሁ፤ በትዳራችን ውስጥ ለይሖዋ የመጀመሪያውን ቦታ ከሰጠነው በጣም ደስተኞች እንደምንሆን ምንም ጥርጥር አልነበረኝም።

ሳገባ የአገልግሎት ክልሌም ወደ ቤልጅየም ተቀየረ። ስለ ቤልጅየም የማውቀው ነገር ቢኖር በአገሪቱ በርካታ ጦርነቶች መካሄዳቸውን ብቻ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ ግን አብዛኞቹ የቤልጅየም ዜጎች ሰላም ወዳዶች መሆናቸውን ተገነዘብኩ። በቤልጅየም መመደቤ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የሚነገረውን የፈረንሳይኛ ቋንቋ መማርን ጠይቆብኛል።

በ1955 በቤልጅየም 4,500 አስፋፊዎች ነበሩ። እኔና አለን ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት በቤቴልና በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ስናገለግል ቆይተናል። ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል በዝናብም ሆነ በፀሐይ በብስክሌት አቀበቱን እየወጣንና ቁልቁለቱን እየወረድን አገልግለናል። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከ2,000 በሚበልጡ ወንድሞች ቤት ውስጥ አድረናል! አቅመ ደካማ ቢሆኑም ባላቸው ኃይል ይሖዋን ለማገልገል ጥረት ከሚያደርጉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ብዙ ጊዜ እገናኝ ነበር። የእነሱ ምሳሌነት አገልግሎቴን እንዳላቋርጥ አበረታቶኛል። በየሳምንቱ አንድ ጉባኤ ጎብኝተን ስንጨርስ ሁልጊዜ እንደተበረታታን ይሰማን ነበር። (ሮሜ 1:11, 12) አለንም እውነተኛ አጋር ሆኖልኛል። በመክብብ 4:9,10 ላይ የሚገኘው “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል” የሚለው ሐሳብ ምንኛ ትክክል ነው!

በይሖዋ ብርታት’ በማገልገል ያገኘኋቸው በረከቶች

እኔና አለን አብረን ባሳለፍናቸው ዓመታት ሌሎች ሰዎች ይሖዋን እንዲያገለግሉ በመርዳት ብዙ አስደሳች ተሞክሮዎችን አግኝተናል። ለአብነት ያህል፣ በ1983 በአንትወርፕ የሚገኝን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ጉባኤ በምንጎበኝበት ወቅት አንድ ቤተሰብ በእንግድነት ተቀብሎን ነበር። ቤንጃሚን ባንዲዊላ የተባለ ከዛየር (አሁን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ተብላለች) የመጣ ወጣት ወንድምም እዚህ ቤተሰብ ዘንድ አርፎ ነበር። ቤንጃሚን ወደ ቤልጂየም የመጣው ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል ነበር። ይህ ወንድም “የእናንተ ሕይወት በጣም ያስቀናኛል፤ ሕይወታችሁ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ነው” በማለት ተናገረ። በዚህ ጊዜ አለን እንዲህ አለው፦ “በእኛ እንደምትቀና ገልጸህልናል፤ አንተ ግን በዚህ ዓለም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረግህ ነው። የተናገርከው ነገርና ድርጊትህ እርስ በርሱ የሚጋጭ አይመስልህም?” አለን የሰጠው ይህ ቀጥተኛ ምክር ቤንጃሚን ስለ ሕይወቱ ቆም ብሎ እንዲያስብ አደረገው። ከጊዜ በኋላ ወደ ዛየር ተመልሶ በአቅኚነት ማገልገል የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ነው።

በ1999 በምግብ መውረጃ ቧንቧዬ ላይ የተፈጠረውን ቁስለት ለማከም ቀዶ ጥገና ተደረገልኝ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ክብደቴ ከ30 ኪሎ በላይ ሆኖ አያውቅም። በእርግጥም በቀላሉ የምሰበር ‘የሸክላ ዕቃ’ ነኝ። ያም ቢሆን ይሖዋ “እጅግ ታላቅ ኀይል” ስለሰጠኝ አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ፣ ቀዶ ሕክምናው ከተደረገልኝ በኋላም ከአለን ጋር እንደገና በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ መካፈል እንድችል አበርትቶኛል። (2 ቆሮ. 4:7) መጋቢት 2004 አለን፣ እንቅልፍ ወስዶት እያለ ሕይወቱ አለፈ። እሱን በማጣቴ በጣም ባዝንም ይሖዋ ከሚያስባቸው ሰዎች መካከል መሆኑን ማወቄ ግን ያጽናናኛል።

በአሁኑ ጊዜ 83 ዓመቴ ሲሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ63 ዓመታት በላይ አሳልፌያለሁ። አሁንም ቢሆን ቤቴ ሆኜ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት እንዲሁም በየዕለቱ በማገኛቸው አጋጣሚዎች ተጠቅሜ ስለ ይሖዋ ድንቅ ዓላማ ለሰዎች በመናገር በአገልግሎት አዘውትሬ ለመካፈል ጥረት አደርጋለሁ። አንዳንድ ጊዜ ‘በ1945 በአቅኚነት ማገልገል ባልጀምር ኖሮ ምን ዓይነት ሕይወት ይኖረኝ ነበር?’ ብዬ አስባለሁ። ያን ጊዜ ጤንነቴ ጥሩ ስላልነበር በአቅኚነት ላለመካፈል በቂ ምክንያት ያለኝ ይመስል ነበር። ሆኖም በወጣትነቴ የአቅኚነት አገልግሎትን በመጀመሬ በጣም አመስጋኝ ነኝ! በሕይወታችን ውስጥ ለይሖዋ የመጀመሪያውን ቦታ ከሰጠን እሱ ብርታታችን እንደሚሆን ከራሴ ተሞክሮ ማየት ችያለሁ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 ሳልቬሽን በ1939 የታተመ መጽሐፍ ሲሆን አሁን መታተም አቁሟል።

^ አን.22 የወንድም ኮቪል የሕይወት ታሪክ በመጋቢት 15, 1961 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚስዮናዊነት አገልግሎት ጓደኛዬ ከሆነችው ከአስትሪድ አንደርሰን ጋር (በስተቀኝ ያለችው)

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1956 ከባለቤቴ ጋር በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ስናገለግል

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2000 ከአለን ጋር