በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምን ዓይነት ሰው መሆን ትፈልጋለህ?

ምን ዓይነት ሰው መሆን ትፈልጋለህ?

ምን ዓይነት ሰው መሆን ትፈልጋለህ?

በፊሊፒንስ በሚገኝ አንድ ከተማ ውስጥ የሚኖር የፖሊስ አዛዥ “ይህ ሰው እንዲህ ዓይነት የባሕርይ ለውጥ እንዲያሳይ ልታደርጊ የቻልሽው እንዴት ነው?” ሲል አንዲትን አቅኚ ጠየቃት። ከዚያም ጠረጴዛው ላይ ወደተከመረው ወረቀት እያመለከተ “እነዚህ ሁሉ ቀደም ባሉት ጊዜያት በእሱ ላይ የቀረቡበትን ክሶች የያዙ መዝገቦች መሆናቸውን ታውቂያለሽ? በዚህ ከተማ ውስጥ ራስ ምታት ከሆኑብን ችግሮች መካከል ከአንዱ አሳርፈሽናል” አላት። የፖሊስ አዛዡ የጠቀሰው ግለሰብ ሁልጊዜ እየሰከረ ረብሻ በመፍጠር የሚታወቅ ነበር። በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምንድን ነው? በመንፈስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት ነው።

ብዙ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ቀድሞ በነበሩበት ሕይወት የለበሱትን አሮጌውን ሰውነት አውልቀው አምላክን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንዲለብሱ’ የሰጠውን ምክር በቁም ነገር ተመልክተውታል። (ኤፌ. 4:22-24) በሕይወታችን ውስጥ ልናደርጋቸው የሚገቡ ለውጦች ትንሽም ይሁኑ ትልቅ አዲሱን ሰው መልበስ ክርስቲያን መሆናችንን የምናሳይበት አንዱ ገጽታ ነው።

በሕይወታችን ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን በማድረግ እስከ መጠመቅ ደረጃ የደረስን ቢሆንም ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ብቻ ነው። በውኃ ለመጠመቅ ራሳችንን ባቀረብንበት ጊዜ የነበረን ሁኔታ የተወሰነ ቅርጽ ከወጣለት አንድ እንጨት ጋር ይመሳሰላል። ይህ እንጨት በመጨረሻ ምን ዓይነት ዕቃ እንደሚወጣው ማወቅ ቢቻልም ገና ብዙ ሥራ ይቀራል። ቅርጽ አውጪው ዕቃውን ለማሳመር ተጨማሪ ጥቃቅን ሥራዎች መሥራት ይኖርበታል። በምንጠመቅበት ጊዜ አንድ የአምላክ አገልጋይ ሊያሟላቸው የሚገቡ መሠረታዊ ባሕርያትን አዳብረን ነበር። ይሁን እንጂ አዲሱን ሰውነት ይበልጥ ማጎልበት እንዲሁም አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ እየተሻሻለ እንዲሄድ ማድረግ ይኖርብናል።

ጳውሎስም እንኳ ማስተካከያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። “በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ” ሲል በግልጽ ተናግሯል። (ሮሜ 7:21) ጳውሎስ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነና እንዴት ዓይነት ሰው መሆን እንደሚፈልግ በሚገባ ያውቅ ነበር። እኛስ? እኛም ራሳችንን ‘ከእኔ ጋር ያለው ምንድን ነው? እኔ ምን ዓይነት ሰው ነኝ? ምን ዓይነት ሰውስ መሆን እፈልጋለሁ?’ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል።

‘ከእኔ ጋር ያለው’ ምንድን ነው?

አንድን ያረጀ ቤት በምናድስበት ጊዜ ውስጥ ያሉት ምሰሶዎች በስብሰው እያሉ ውጪውን ቀለም መቀባት በቂ አይደለም። የአንድን ቤት መዋቅራዊ ችግሮች ችላ ማለት የኋላ ኋላ ለከፋ ችግር ይዳርጋል። በተመሳሳይም እንዲሁ ከላይ ብቻ ጻድቅ መስሎ መታየት በቂ አይደለም። ትክክለኛ ማንነታችንን መመርመርና ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ችግሮች ለይተን ማወቅ ይኖርብናል። ይህ ካልሆነ ግን የአሮጌው ሰው ባሕርያት እንደገና ሊያገረሹብን ይችላሉ። በመሆኑም ራስን በሚገባ መመርመር የግድ አስፈላጊ ነው። (2 ቆሮ. 13:5) መጥፎ ባሕርያችንን ለይተን ማወቅና ማረም ይኖርብናል። ይሖዋ ይህን ለማድረግ የሚያስችለንን እርዳታ አዘጋጅቶልናል።

ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን [“መቅኒን፣” NW] እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።” (ዕብ. 4:12) በጽሑፍ በሰፈረው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት በሕይወታችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ቃሉ ውስጥ ድረስ ዘልቆ የሚወጋ ሲሆን በምሳሌያዊ አነጋገር በአጥንታችን ውስጥ እስከሚገኘው መቅኒ ድረስ ይገባል። አስተሳሰባችንና የልባችን ግፊት ይፋ እንዲወጣ በማድረግ ከውጭ መስለን ከምንታየው ወይም እኛ ስለራሳችን ካለን ግምት በተለየ ትክክለኛ ውስጣዊ ማንነታችን በግልጽ እንዲታይ ያደርጋል። የአምላክ ቃል ያሉብንን ችግሮች እንድንገነዘብ የሚያስችል ትልቅ መሣሪያ ነው!

አንድን ያረጀ ቤት ስንጠግን የተበላሹ ዕቃዎችን መቀየር ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። የችግሮቹን መንስኤ ማወቃችን እንደገና ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት የሚያደርጉ እርምጃዎች እንድንወስድ ያስችለናል። በተመሳሳይም ምን ዓይነት መጥፎ ባሕርያት እንዳሉን ብቻ ሳይሆን እነዚህን ባሕርያት እንድናፈራ ምክንያት የሆኑትን ወይም አስተዋጽኦ ያደረጉትን ነገሮች ለይተን ማወቃችን ድክመቶቻችንን ማሸነፍ እንድንችል ይረዳናል። የእኛን ማንነት የሚቀርጹ ብዙ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለን ቦታ፣ የኑሮ ደረጃችን፣ የምንኖርበት አካባቢ፣ ባሕላችን፣ ወላጆቻችን፣ ጓደኞቻችንና የምንከተለው ሃይማኖት ይገኙበታል። ሌላው ቀርቶ የምንመለከታቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች እንዲሁም ሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች በእኛ ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ይኖራል። በባሕርያችን ላይ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብንን ነገሮች ማወቃችን ተጽዕኗቸው እንዲቀንስ ለማድረግ ያስችለናል።

ራሳችንን ከመረመርን በኋላ ‘በቃ ይህ ተፈጥሮዬ ነው’ ለማለት ይዳዳን ይሆናል። እንዲህ ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ጳውሎስ ከዚህ ቀደም አመንዝሮች፣ ግብረ ሰዶማውያንና ሰካራሞች የነበሩትን እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ድርጊቶች ይፈጽሙ የነበሩትን በቆሮንቶስ ጉባኤ ያሉ ክርስቲያኖች በተመለከተ “ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን . . . በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል” ብሏል። (1 ቆሮ. 6:9-11) እኛም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ አስፈላጊ ለውጦችን ማድረግ እንችላለን።

በፊሊፒንስ የሚኖረውን ማርኮስ * የተባለውን ሰው ሁኔታ እንመልከት። ማርኮስ አስተዳደጉን በተመለከተ “ወላጆቼ ነጋ ጠባ ይጨቃጨቁ ነበር። በመሆኑም የ19 ዓመት ልጅ ሳለሁ ዓመጽኩ” ሲል ተናግሯል። ማርኮስ የታወቀ ቁማርተኛ፣ ሌባና ዘራፊ ሆነ። ምንም እንኳ ያሰቡት ሳይሳካ ቢቀርም እሱና ሌሎች ሰዎች አንድ ላይ በመሆን አውሮፕላን ለመጥለፍ አስበው ነበር። ማርኮስ ካገባም በኋላ መጥፎ ድርጊቱን አልተወም። በመጨረሻም በቁማር የተነሳ ያለውን ሁሉ አጣ። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና ከነበረችው ሚስቱ ጋር በመሆን ማጥናት ጀመረ። መጀመሪያ ላይ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እንደማይበቃ ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ የተማረውን ነገር በሥራ ላይ ማዋሉና በስብሰባዎች ላይ መገኘቱ የቀድሞ አኗኗሩን እርግፍ አድርጎ እንዲተው ረዳው። በአሁኑ ጊዜ ማርኮስ የተጠመቀ ክርስቲያን ከመሆኑም በተጨማሪ ሌሎችም ለውጥ ማድረግ እንዲችሉ በማስተማሩ ሥራ ዘወትር ይሳተፋል።

ምን ዓይነት ሰው መሆን ትፈልጋለህ?

ክርስቲያናዊ ባሕርያችንን ለማሻሻል ምን ዓይነት ለውጦች ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል? ጳውሎስ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል መክሯል፦ “ቍጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን፣ ሐሜትንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ [ጣሉ፤] እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ።” ሐዋርያው በመቀጠል ‘የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ልበሱ’ ብሏል።—ቈላ. 3:8-10

ስለዚህ ዋናው ግባችን አሮጌውን ሰውነት አውልቀን አዲሱን ሰው መልበስ ነው። በዚህ ረገድ የሚረዳን የትኞቹን ባሕርያት ማዳበራችን ነው? ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ። በእነዚህ ሁሉ ላይ ሁሉን በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን ልበሱት።” (ቈላ. 3:12-14) እነዚህን ባሕርያት ለማዳበር የታሰበበት ጥረት ማድረጋችን “በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ” እንድናገኝ ይረዳናል። (1 ሳሙ. 2:26 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ አምላካዊ ባሕርያትን በላቀ ደረጃ አንጸባርቋል። ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ በማጥናትና በመኮረጅ ልክ እንደ እሱ ‘አምላክን መምሰል’ እንችላለን።—ኤፌ. 5:1, 2

በሕይወታችን ውስጥ ምን ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልገን ማወቅ የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ባሕርያት ማጥናት ይኸውም ጥሩና መጥፎ ጎናቸውን መመርመር ነው። የእምነት አባት የሆነውን የያዕቆብን ልጅ ዮሴፍን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዮሴፍ ፍትሐዊ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጸምበትም አዎንታዊ አመለካከቱንና ውስጣዊ ውበቱን ጠብቆ ኖሯል። (ዘፍ. 45:1-15) በአንጻሩ ደግሞ የንጉሥ ዳዊት ልጅ የሆነው አቤሴሎም ለሕዝቡ አሳቢ መስሎ የቀረበ ሲሆን በውበቱም የተደነቀ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከሃዲና ነፍሰ ገዳይ ነበር። (2 ሳሙ. 13:28, 29፤ 14:25፤ 15:1-12) እንዲያው ጥሩ መስሎ መታየትና ውጫዊ ውበት አንድን ሰው ተወዳጅ አያደርጉትም።

ሊሳካልን ይችላል

ባሕርያችንን ለማሻሻልና በአምላክ ፊት ያማርን ለመሆን ለውስጣዊ ማንነታችን ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል። (1 ጴጥ. 3:3, 4) የባሕርይ ለውጥ ለማድረግ መጥፎ ባሕርይዎቻችንንና ለዚያ መንስኤ የሆኑትን ወይም አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ነገሮች ለይተን ማወቅ እንዲሁም አምላካዊ ባሕርያትን መኮትኮት ይጠይቃል። እንዲህ ዓይነት ለውጥ ለማድረግ የምናደርገው ጥረት እንደሚሳካ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

አዎ፣ በይሖዋ እርዳታ አስፈላጊዎቹን ለውጦች ማድረግ እንችላለን። ልክ እንደ መዝሙራዊው እኛም “አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” ብለን መጸለይ እንችላለን። (መዝ. 51:10) ሕይወታችን ከአምላክ ፈቃድ ጋር ይበልጥ የተስማማ እንዲሆን ለማድረግ ያለንን ፍላጎት እንዲያሳድግልን የአምላክ መንፈስ በውስጣችን እንዲሠራ መለመን እንችላለን። በእርግጥም፣ በይሖዋ ፊት ይበልጥ ያማርን ሆነን በመታየት ረገድ ሊሳካልን ይችላል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 ትክክለኛ ስሙ አይደለም።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህን በማዕበል የተመታ ቤት ውጪውን ቀለም መቀባት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ አዳብረሃል?