በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሰላም የሚገኝበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ’

‘ሰላም የሚገኝበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ’

‘ሰላም የሚገኝበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ’

አዲስ የተሠራ መንገድ ጠንካራና ፈጽሞ የማይበላሽ ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጂ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሊሰነጣጠቅና ሊቦረቦር ይችላል። አደጋ እንዳይከሰት ለመከላከልና የመንገዱን ዕድሜ ለማራዘም ጥገና ማድረግ አስፈላጊ ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ሊሻክር ብሎም ሊበላሽ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም በሚገኙ ክርስቲያኖች መካከል የአመለካከት ልዩነቶች እንደነበሩ ገልጿል። ክርስቲያን ባልንጀሮቹን “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችንም የምንተናነጽበትን ማንኛውንም ጥረት እናድርግ” ሲል መክሯቸዋል። (ሮሜ 14:13, 19) ‘ሰላም የሚገኝበትን ማንኛውንም ጥረት ማድረግ’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሰላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በድፍረትና በተሳካ መንገድ ጥረት ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

በአንድ መንገድ ላይ የሚፈጠሩ ትንንሽ ስንጥቆች ቶሎ ካልተጠገኑ አደጋ የሚያስከትሉ ጉድጓዶች ሊሆኑ ይችላሉ። የግል አለመግባባቶችም እልባት ሳያገኙ እንዲሁ ከተተዉ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ማንም፣ ‘እግዚአብሔርን እወደዋለሁ’ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና።” (1 ዮሐ. 4:20) መፍትሔ ሳያገኝ የቀረ አለመግባባት አንድን ክርስቲያን ቀስ በቀስ ወንድሙን ወደመጥላት ሊያደርሰው ይችላል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ከሌለን አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጿል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸዋል፦ “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ።” (ማቴ. 5:23, 24) አዎ፣ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት የምናደርግበት ዋናው ምክንያት ይሖዋ አምላክን ማስደሰት ስለምንፈልግ ነው። *

በፊልጵስዩስ ጉባኤ ተከስቶ የነበረ አንድ ሁኔታ ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነበትን ሌላ ምክንያት አጉልቶ ያሳያል። ኤዎድያንና ሲንጤኪን በተባሉት ሁለት ክርስቲያኖች መካከል ተከስቶ የነበረ በውል ያልተጠቀሰ አንድ ችግር ለመላው ጉባኤ ሰላም ስጋት ፈጥሮ ነበር። (ፊልጵ. 4:2, 3) መፍትሔ ያላገኙ የግል አለመግባባቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ሊታወቁ ይችላሉ። የጉባኤውን ፍቅርና አንድነት ለመጠበቅ ያለን ፍላጎት ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ሰላምን እንድንከታተል ይገፋፋናል።

ኢየሱስ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው” ብሏል። (ማቴ. 5:9) ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ ደስታና እርካታ ያስገኛል። ከዚህም በተጨማሪ “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት” ስለሚሰጥ፣ ሰላም ለጥሩ ጤንነት አስተዋጽኦ ያበረክታል። (ምሳሌ 14:30) በአንጻሩ ደግሞ ቂም ይዞ መቆየት ለጤና ቀውስ የመጋለጥ አጋጣሚን ከፍ ያደርጋል።

አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚቀበሉ ቢሆንም የግል አለመግባባቶችን መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚል ጥያቄ ይመጣብህ ይሆናል። በዚህ ረገድ ሊረዱን የሚችሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንመርምር።

በረጋ መንፈስ መወያየት ሰላም ያሰፍናል

አብዛኛውን ጊዜ፣ በአንድ መንገድ ላይ ትንንሽ ስንጥቆች ሲከሰቱ ጉዳት የደረሰበትን አካባቢ ከላይ በማልበስ መጠገን ይቻላል። ታዲያ የወንድሞቻችንን ጥቃቅን ጉድለቶች ሸፍነን ማለፍና ይቅር ማለት እንችላለን? ሐዋርያው ጴጥሮስ “ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናል” ብሎ ስለጻፈ አብዛኞቹ የግል አለመግባባቶች በዚህ መንገድ ሊፈቱ ይችላሉ።—1 ጴጥ. 4:8

አንዳንድ ጊዜ ግን ችግሩ ከባድ መስሎ ሊታየንና ችላ ብለን ማለፍ ሊቸግረን ይችላል። እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር ከወረሱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተከሰተውን ነገር ተመልከት። “የሮቤልና የጋድ ነገዶች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ” የዮርዳኖስን ወንዝ ከመሻገራቸው በፊት “ግዙፍ መሠዊያ ሠሩ።” ሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች መሠዊያው ለጣዖት አምልኮ የሚያገለግል ስለመሰላቸው ችግሩን በቸልታ ማለፍ አልቻሉም። በመሆኑም ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጁ።—ኢያሱ 22:9-12

አንዳንድ እስራኤላውያን ጥፋት ለመሠራቱ በቂ ማስረጃ እንዳለና ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘር ደግሞ ከራሳቸው ወገን ብዙ ሰው እንዳይሞት እንደሚያስችል አስበው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉት ነገዶች የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ከወንድሞቻቸው ጋር ለመወያየት ልዑካን ላኩ። እነሱም “በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ክህደት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው? እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ከመከተልስ እንዴት ወደ ኋላ ትላላችሁ?” ሲሉ ጠየቋቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መሠዊያውን የገነቡት ነገዶች ክህደት መፈጸማቸው አልነበረም። ይሁንና ለቀረበባቸው ክስ ምን ምላሽ ይሰጡ ይሆን? ክስ ባቀረቡባቸው ሰዎች ላይ ኃይለ ቃል ይናገሩ ወይም እነሱን ለማነጋገር እምቢ ይሉ ይሆን? ክስ የተሰነዘረባቸው ነገዶች መሠዊያውን የሠሩት ይሖዋን ለማገልገል ካላቸው ፍላጎት በመነሳሳት እንደሆነ በግልጽ በማስረዳት በገርነት መንፈስ ምላሽ ሰጡ። የሰጡት ምላሽ ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና እንዳይበላሽ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ አስችሏል። በረጋ መንፈስ መወያየታቸው ችግሩ እልባት እንዲያገኝና ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል።—ኢያሱ 22:13-34

ሌሎቹ የእስራኤል ነገዶች ከባድ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ከሮቤልና ከጋድ ነገዶች እንዲሁም ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ጋር ችግሩን አንስተው ተወያይተዋል። የአምላክ ቃል “የሞኞች ቍጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለ ሆነ፣ በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል” ይላል። (መክ. 7:9) ከበድ ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት የሚቻልበት ቅዱስ ጽሑፋዊ መንገድ ጉዳዩን አንስቶ በረጋ መንፈስ በግልጽ መወያየት ነው። በድሎናል ብለን በምናስበው ሰው ላይ ቂም ይዘንና ቀርበን ለማነጋገር ፈቃደኞች ሳንሆን ቀርተን እያለ በእርግጥ የይሖዋን በረከት እናገኛለን ብለን መጠበቅ እንችላለን?

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ክርስቲያን ባልንጀራችን እንደበደልነው ተሰምቶት ቀርቦ ቢያነጋግረን፣ ይባስ ብሎም በሐሰት ቢከሰን ምን እናደርጋለን? መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” ይላል። (ምሳሌ 15:1) ለቅሬታው መፈጠር ምክንያት የሆኑት የእስራኤል ነገዶች አቋማቸውን በገርነት ሆኖም በግልጽ አስረድተዋል፤ እንዲህ ማድረጋቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ወደ ተካረረ ጭቅጭቅ አስገብቷቸው የነበረው ጉዳይ እንዲረግብ አስችሏል። አንድን ችግር በተመለከተ ቅድሚያውን ወስደን ወንድማችንን ቀርበን ብናነጋግረው ወይም ደግሞ እሱ ቀርቦ ቢያነጋግረን ‘ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የሚረዳው ምን ዓይነት ቃላት ብናገር፣ እንዴት ያለ የድምፅ ቃና ብጠቀም እንዲሁም ምን ዓይነት ሁኔታ ባሳይ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው።

አንደበታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት

ይሖዋ ያሳሰቡንን ነገሮች አውጥተን መናገር እንደምንፈልግ ያውቃል። ከአንድ ሰው ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ሳንፈታው ከቀረን ጉዳዩን ለሌላ ሰው ለማውራት ልንፈተን እንችላለን። በውስጣችን ቂም ከያዝን ስለ ግለሰቡ ነቀፋ ያዘለ ነገር መናገር ሊቀናን ይችላል። ምሳሌ 11:11 አንደበትን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምን በተመለከተ ‘በክፉዎች አንደበት ከተማ ትጠፋለች’ ይላል። በተመሳሳይ ስለ ክርስቲያን ባልንጀራችን እንዳመጣልን የምንናገር ከሆነ በከተማ ሊመሰል የሚችለውን ጉባኤ ሰላም ልናደፈርስ እንችላለን።

ይሁን እንጂ የሰላምን ጎዳና መከተል ሲባል ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጭራሽ አናወራም ማለት አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ክፉ ንግግር ከከንፈሮቻችሁ አልፎ አይውጣ” ሲል መክሯቸዋል። ሆኖም አክሎ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሰዎች መስማት የሚፈልጉትንና በእርግጥ የሚጠቅማቸውን መልካም ነገር ብቻ ተናገሩ፤ . . . አንዳችሁ ለሌላው ደግነትና ርኅራኄ አሳዩ፤ እርስ በርሳችሁም ይቅር ተባባሉ።” (ኤፌ. 4:29-32 ዘ ኒው አሜሪካን ባይብል) ከዚህ በፊት ስለ አንተ ለሌሎች መልካም ነገር ይናገር የነበረ አንድ ወንድም በንግግርህ ወይም በአድራጎትህ እንደተጎዳ ተሰምቶት ቀርቦ ቢያነጋግርህ ይህን ወንድም ይቅርታ ለመጠየቅና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ አይቀልህም? በተመሳሳይም ስለ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን በምናወራበት ጊዜ የሚያንጹ ነገሮች የመናገር ልማድ ካለን አለመግባባቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ሰላማዊ ግንኙነታችንን እንደገና ለማደስ ቀላል ይሆንልናል።—ሉቃስ 6:31

አምላክን ‘ስምም ሆኖ ማገልገል’

ከወረስነው ኃጢአት የተነሳ ካስቀየሙን ሰዎች በመራቅ ራሳችንን ማግለል ይቀናናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ጥበብ የጎደለው ነው። (ምሳሌ 18:1) የይሖዋን ስም የምንጠራ አንድነት ያለን ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን አምላክን ‘ተስማምተን ለማገልገል’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።—ሶፎ. 3:9

ሌሎች የሚናገሩት ወይም የሚያደርጉት ተገቢ ያልሆነ ነገር ለንጹሕ አምልኮ ያለንን ቅንዓት ሊያዳክምብን አይገባም። የኢየሱስ መሥዋዕት በቤተ መቅደሱ ይቀርብ የነበረውን የእንስሳት መሥዋዕት ከመተካቱ ከጥቂት ቀናት በፊትና ኢየሱስ በወቅቱ የነበሩትን ጸሐፍት ክፉኛ ካወገዘ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አንዲት ድሃ መበለት “ያላትን መተዳደሪያ በሙሉ” በቤተ መቅደሱ መባ መሰብሰቢያ ውስጥ ስትጨምር ተመለከተ። ኢየሱስ ሊከለክላት ሞክሮ ነበር? በፍጹም! እንዲያውም በወቅቱ የነበረውን የይሖዋ ጉባኤ በታማኝነት በመደገፏ አመስግኗታል። (ሉቃስ 21:1-4) ሌሎች ይፈጽሙት የነበረው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት የይሖዋን አምልኮ በመደገፍ ረገድ ካለባት ግዴታ ነፃ አላደረጋትም።

ክርስቲያን ወንድማችን ወይም እህታችን ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዳደረጉብን፣ አልፎ ተርፎም በደል እንደፈጸሙብን ቢሰማን ምን እናደርጋለን? ይህ ሁኔታ ለይሖዋ በምናቀርበው የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር እንፈቅዳለን? ወይስ ዛሬ ባለው የአምላክ ጉባኤ ውስጥ የሚገኘው ውድ ሰላም እንዲጠበቅ ስንል ማንኛውም የግል አለመግባባት መፍትሔ እንዲያገኝ በድፍረት እርምጃ እንወስዳለን?

ቅዱሳን መጻሕፍት “ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚል ምክር ይሰጡናል። (ሮሜ 12:18) ይህን ምክር ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ እንዲህ በማድረግም በሕይወት ጎዳና ላይ በጽናት መጓዛችንን እንቀጥል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የሰጠውን ምክር በተመለከተ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የጥቅምት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 17-22⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤዎድያንና ሲንጤኪን ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርገው ምን ዓይነት ቃል፣ የድምፅ ቃና እና ሁኔታ ነው?