“የባሕር መዝሙር”—ክፍተቱ እንዲደፈን ያደረገ ጥንታዊ ቅጂ
“የባሕር መዝሙር”—ክፍተቱ እንዲደፈን ያደረገ ጥንታዊ ቅጂ
ግንቦት 22, 2007፣ በሰባተኛው ወይም በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተዘጋጀ የዕብራይስጥ ጥቅልል ቁራጭ ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው የእስራኤል ሙዚየም ለእይታ ቀርቦ ነበር። ይህ ቁራጭ ከዘፀአት 13:19 እስከ 16:1 ያሉትን ጥቅሶች የያዘ ነው። በዚህ ውስጥ “የባሕር መዝሙር” በመባል የሚታወቀው እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን በተአምራዊ ሁኔታ ካቋረጡ በኋላ የዘመሩት የድል መዝሙር ይገኛል። የዚህ ጥቅልል ቁራጭ ለእይታ መቅረቡ ያን ያህል ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?
የዚህ ጥያቄ መልስ ይህ ጽሑፍ ካስመዘገበው ዕድሜ ጋር የተያያዘ ነው። የሙት ባሕር ጥቅልሎች የተጻፉት ከሦስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ መጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። የሙት ባሕር ጥቅልሎች ከመገኘታቸው ከ60 ዓመታት ገደማ በፊት እጅግ በጣም የቆየ የሚባለው የዕብራይስጥ ጽሑፍ በ930 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተዘጋጀው አሌፖ ኮዴክስ በመባል የሚታወቀው ቅጂ ነበር። ከጥቂት ቁርጥራጮች በስተቀር በመሃል ባሉት በርካታ መቶ ዓመታት ውስጥ የተጻፈ ምንም የዕብራይስጥ ጽሑፍ ቅጂ አልተገኘም ነበር።
የእስራኤል ሙዚየም ዳይሬክተር የሆኑት ጄምስ ኤስ ስናይደር “የባሕር መዝሙር ጥንታዊ ቅጂ በሙት ባሕር ጥቅልሎች . . . እና በአሌፖ ኮዴክስ መካከል ባለው የታሪክ ዘመን የተፈጠረውን ክፍተት የሚደፍን ነው” ሲሉ ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት ከሌሎች ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በተጨማሪ ይህ በእጅ የተጻፈ ጥንታዊ ቅጂ “በጽሑፉ ላይ ምንም ለውጥ እንዳልተደረገ የሚያሳይ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ማስረጃ ነው።”
ይህ ቁራጭ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በግብፅ፣ ካይሮ በአንድ ምኩራብ ውስጥ ከተገኙት በርካታ ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታመናል። ይሁን እንጂ ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅጂዎችን በግሉ የሚሰበስብ አንድ ሰው በ1970ዎቹ መገባደጃ ላይ አንድን ባለሙያ እስካማከረበት ጊዜ ድረስ የዚህን ጥንታዊ ቅጂ ዋጋማነት አልተረዳም ነበር። በዚያን ወቅት የቁራጩ ዕድሜ ካርቦን-ዴቲንግ በሚባለው ዘዴ ከታወቀ በኋላ በእስራኤል ሙዚየም ለእይታ እስከቀረበበት ጊዜ ድረስ በቅርስነት ተጠብቆ እንዲቆይ ተደረገ።
በእስራኤል ሙዚየም ውስጥ የሚገኘው ሽራይን ኦቭ ዘ ቡክ ተብሎ የሚጠራው ክፍል ዋና ኃላፊና የሙት ባሕር ጥቅልሎች ጠባቂ የሆኑት አዶልፎ ሮይትመን የጥቅልሉ ቁራጭ ያለውን ፋይዳ በተመለከተ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፦ “የባሕር መዝሙር ጥንታዊ ቅጂ፣ የማሶራውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ለበርካታ መቶ ዓመታት አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በትክክል ሲተላለፍ እንደቆየ ያሳያል። በዛሬው ጊዜም ያለው የባሕር መዝሙር የሰባተኛውን ወይም የስምንተኛውን መቶ ዘመን ለየት ያለ የአጻጻፍ ዘይቤ እንደጠበቀ መገኘቱ በጣም ያስገርማል።”
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ መሪነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው፤ በመሆኑም መጽሐፉ ተጠብቆ እንዲቆይ የማድረጉን ጉዳይ በዋነኝነት የሚከታተለው ይሖዋ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቅዱሳን መጻሕፍትን የገለበጡት ሰዎች ይህን ሥራ ያከናወኑት በከፍተኛ ጥንቃቄ ነበር። ስለዚህ ዛሬ የምናነበው መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ አስተማማኝ ነው።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of Israel Museum, Jerusalem