በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኮሪያ የአምላክ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ተመልክቻለሁ

በኮሪያ የአምላክ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ተመልክቻለሁ

በኮሪያ የአምላክ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ተመልክቻለሁ

ሚልተን ሃሚልተን እንደተናገረው

“የኮሪያ ሪፑብሊክ መንግሥት፣ ሚስዮናውያን ለሆናችሁት ለሁላችሁም ቪዛ ሊሰጣችሁ ፈቃደኛ አለመሆኑንና ወደ አገሪቱ እንድትገቡ እንደማይፈልግ መግለጹን ስንነግራችሁ በጣም እናዝናለን።  . . . በዚህም ምክንያት ለጊዜው ጃፓን ተመድባችኋል።”

በ1954 መገባደጃ አካባቢ ከላይ የተገለጸው መልእክት ከብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ ለእኔና ለባለቤቴ ደረሰን። በዚሁ ዓመት ኒው ዮርክ ከሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት 23ኛ ክፍል ተመርቀን ነበር። ደብዳቤው ሲደርሰን ኢንዲያናፓሊስ፣ ኢንዲያና ውስጥ በጊዜያዊነት እንድናገለግል ተመድበን ነበር።

እኔና ባለቤቴ ሊዝ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለን አንድ ክፍል ነበርን። በኋላም በ1948 ትዳር መሠረትን። ሊዝ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ብትወደውም ከዩናይትድ ስቴትስ ውጭ በሌላ አገር ማገልገል ያስፈራት ነበር። ታዲያ አመለካከቷን እንድትቀይር የረዳት ምንድን ነው?

በ1953 ሞቃት ወቅት ኒው ዮርክ በሚገኘው ያንኪ ስታዲየም ብሔራት አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፤ በዚህ ስብሰባ ላይ ከጊልያድ አመልካቾች ጋር ስብሰባ ተደርጎ የነበረ ሲሆን ሊዝም በስብሰባው ላይ አብራኝ ለመገኘት ተስማማች። አበረታች በነበረው በዚያ ስብሰባ ላይ ከተገኘን በኋላ ለጊልያድ አመልካቾች የተዘጋጀውን ቅጽ ሞላን። የሚገርመው፣ የካቲት 1954 በሚጀምረው ቀጣዩ ሥልጠና ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን።

ከዚያም በኮሪያ እንድናገለግል ተመደብን። በኮሪያ ለሦስት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት ያበቃው በ1953 ሲሆን ጦርነቱ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ውድመት አስከትሎ ነበር። መግቢያዬ ላይ በጠቀስኩት ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው መጀመሪያ ወደ ጃፓን አቀናን። በኮሪያ እንዲያገለግሉ ተመድበው ከነበሩ ሌሎች ስድስት ሚስዮናውያን ጋር በመሆን ለ20 ቀናት ያህል በውቅያኖስ ላይ ከተጓዝን በኋላ ጥር 1955 ጃፓን ደረስን። በወቅቱ የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ የበላይ ተመልካች የነበረው ወንድም ሎይድ ባሪ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ወደብ ድረስ መጥቶ ተቀበለን። ከዚያም ዮኮሃማ ወደሚገኘው የሚስዮናውያን መኖሪያ የተጓዝን ሲሆን የዚያኑ ቀን አገልግሎት ወጣን።

ወደ ኮሪያ መግባት ቻልን

ከጊዜ በኋላ ወደ ኮሪያ ሪፑብሊክ ለመግባት የሚያስችለን ቪዛ ተሰጠን። መጋቢት 7, 1955 ቶኪዮ ከሚገኘው ሃኔዳ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተን ለሦስት ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ ሴኡል ወደሚገኘው ዮኢዶ አውሮፕላን ማረፊያ ደረስን። እዚያ ስንደርስ ከ200 የሚበልጡ ኮሪያውያን የይሖዋ ምሥክሮች ተቀበሉን። በጣም ተደስተን ስለነበር እንባችንን መቆጣጠር አልቻልንም። በወቅቱ በመላው ኮሪያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች 1,000 ብቻ ነበሩ። እንደ ሌሎች በርካታ ምዕራባውያን ሁሉ እኛም የሩቅ ምሥራቅ ሰዎች የየትኛውም አገር ዜጋ ቢሆኑ መልካቸውም ሆነ ነገረ ሥራቸው ተመሳሳይ እንደሆነ እናስብ ነበር። ሆኖም እንደዚያ አለመሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልወሰደብንም። ኮሪያውያን የራሳቸው የሆነ ቋንቋና ፊደል ብቻ ሳይሆን ለየት ያለ የምግብ አሠራር ዘዴና ባሕላዊ ልብስ አላቸው፤ መልካቸውም ቢሆን ከሌሎች የተለየ ነው። እንዲሁም የሕንፃዎቻቸውን ንድፍ የመሳሰሉ ነገሮች ከሌሎች የተለዩ ያደርጓቸዋል።

መጀመሪያ ላይ በጣም ፈታኝ የሆነብን ቋንቋቸውን መማር ነበር። በወቅቱ የኮሪያን ቋንቋ ለመማር የሚረዱን መጻሕፍት አልነበሩንም። ብዙም ሳይቆይ የእንግሊዝኛ ቃላትን ድምፅ በመጠቀም የኮሪያ ቃላትን በትክክል መጥራት እንደማንችል ተረዳን። አንድ ሰው በኮሪያ ቋንቋ ቃላትን በትክክል መጥራት የሚችለው የኮሪያን ፊደላት ሲማር ብቻ ነው።

የኮሪያን ቋንቋ ስንናገር አንዳንድ ስሕተቶችን እንሠራ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሊዝ ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል አንዲትን ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ይኖራት እንደሆነ ጠየቀቻት። የቤቱ ባለቤት በዚህ ጥያቄ ግራ እንደተጋባች ፊቷ ላይ ቢታይም እንደተባለችው ክብሪት ይዛላት መጣች። ለካስ ሊዝ የጠየቀቻት ሱንኪዩንግ (መጽሐፍ ቅዱስ) ሳይሆን ሱንግያንግ (ክብሪት) ነበር።

ከጥቂት ወራት በኋላ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ፉሳን የተባለች የወደብ ከተማ የሚስዮናውያን ቤት እንድናቋቁም ተላክን። ለእኔና ለባለቤቴ እንዲሁም አብረውን ለተመደቡት ሁለት እህቶች መኖሪያ የሚሆን ሦስት ክፍሎች ያሉት ቤት ተከራየን። እነዚህ ሦስት ትንንሽ ክፍሎች ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚገኙ ሲሆን የቧንቧ ውኃም ሆነ መጸዳጃ ቤት አልነበራቸውም። ውኃው ሁለተኛው ፎቅ ላይ የሚደርሰው በፕላስቲክ ቱቦ አማካኝነት ሲሆን እዚያ ለመድረስ የሚያስችል ኃይል የሚኖረው ምሽት ላይ ብቻ ነበር። በመሆኑም በየተራ በሌሊት እየተነሳን ውኃ እናጠራቅም ነበር። ውኃውን ለመጠጣት ማፍላት አሊያም ክሎሪን መጨመር ነበረብን።

ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም ነበሩ። የኤሌክትሪክ ኃይል እንደልብ ስለማይገኝ የልብስ ማጠቢያ ማሽንም ሆነ ካውያ መጠቀም አንችልም ነበር። ምግብ የምናበስለው ኮሪደር ላይ ሲሆን የምንጠቀመውም በነጭ ጋዝ በሚሠራ ምድጃ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እያንዳንዳችን በተመደብንበት ቀን ምግብ ማዘጋጀት ለመድን። ወደዚህ አካባቢ ከመጣን ከሦስት ዓመት በኋላ እኔና ሊዝ ሄፒታይተስ የተባለ በሽታ ያዘን። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሚስዮናውያን በዚህ በሽታ ተይዘው ነበር። ከዚህ በሽታ ያገገምነው ከወራት በኋላ ሲሆን ሌሎች የጤና ችግሮችም አጋጥመውናል።

ወንድሞች ችግሮችን እንዲቋቋሙ ረድተናቸዋል

ባለፉት 55 ዓመታት በኮሪያ ባሕረ ገብ መሬት የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ የተረጋጋ አልነበረም። ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ የሆነው ክልል የኮሪያን ባሕረ ገብ መሬት ለሁለት ከፍሎታል። ይህ ክልል የሚገኘው የኮሪያ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ከሆነችው ከሴኡል በስተ ሰሜን 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ብሩክሊን በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት የሚያገለግለው ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ በ1971 ሊጎበኘን መጥቶ ነበር። እኔም ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ ወደሆነው ክልል አብሬው ሄድኩ፤ ይህ አካባቢ በምድር ላይ ካሉት ድንበሮች ሁሉ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ነው። ባለፉት ዓመታት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ከሁለቱ መንግሥታት ተወካዮች ጋር በዚህ ቦታ በተደጋጋሚ ውይይት አድርገዋል።

በኮሪያ ባሕረ ገብ መሬት አካባቢ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም የፓለቲካ ጉዳዮች ገለልተኞች እንደሆንን የታወቀ ነው። (ዮሐ. 17:14) ከ13,000 በላይ የሚሆኑ ኮሪያውያን የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነት ለመካፈል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በድምሩ 26,000 ለሚያክሉ ዓመታት ታስረዋል። (2 ቆሮ. 10:3, 4) በዚህች አገር የሚገኙ ወጣት ወንድሞች በሙሉ የገለልተኝነት አቋማቸውን መጠበቃቸው ችግር ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ቢያውቁም በፍርሃት ተሸንፈው ወደኋላ አላሉም። መንግሥት፣ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋምን መጠበቅን እንደ “ወንጀል” በመቁጠር ክርስቲያን አገልጋዮችን “ወንጀለኞች” እንደሆኑ አድርጎ መግለጹ የሚያሳዝን ነው።

እኔም በ1944 በሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወቅት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኔ ሊውዝበርግ፣ ፔንስልቬንያ በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ወህኒ ቤት ለሁለት ዓመት ተኩል ታስሬ ነበር። ምንም እንኳ በኮሪያ ወህኒ ቤት ውስጥ ያለው ሁኔታ ለወንድሞቻችን ይበልጥ አስቸጋሪ ቢሆንም እነዚህ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ችግሮችን መቋቋም እንደሚያስፈልጋቸው እረዳለሁ። ብዙ ወንድሞች በኮሪያ ከነበርነው ሚስዮናውያን መካከል አንዳንዶቻችን ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥመውን እንደነበረ ማወቃቸው አበረታቷቸዋል።—ኢሳ. 2:4

ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጠሙን

በ1977 ተከስቶ ከነበረው ችግር ጋር በተያያዘ እኛም የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ አስፈልጎን ነበር። ባለሥልጣናቱ፣ ወጣት ኮሪያውያን ወታደራዊ አገልግሎት እንዳይሰጡና የጦር መሣሪያ እንዳይታጠቁ ተጽዕኖ እያደረግንባቸው እንደሆነ ተሰማቸው። በመሆኑም መንግሥት በማንኛውም ምክንያት አገሪቱን ለቅቆ የወጣ ሚስዮናዊ ተመልሶ ወደ አገሪቱ እንዳይገባ ውሳኔ አስተላለፈ። ይህ እገዳ ከ1977 እስከ 1987 ድረስ የዘለቀ ነበር። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከኮሪያ ከወጣን ተመልሰን እንድንገባ አይፈቀድልንም ነበር። በመሆኑም በእነዚህ ጊዜያት ቤተሰባችንን ለመጠየቅ እንኳ ወደ አገራችን አልሄድንም።

የክርስቶስ ተከታዮች እንደ መሆናችን መጠን ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኞች መሆናችንን ለመንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ጊዜያት ነግረናቸዋል። ከጊዜ በኋላ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ፈርተን ከአቋማችን ወደኋላ እንደማንል ስለተገነዘቡ የተጣለብን እገዳ ከአሥር ዓመት በኋላ ተነሳልን። እገዳው በነበረባቸው ዓመታት ጥቂት ሚስዮናውያን የጤና ችግርን በመሳሰሉ አንዳንድ ሁኔታዎች አገሪቱን ለቀው መሄድ ግድ ሆኖባቸው ነበር፤ ሆኖም ሌሎቻችን እዚያው በመቆየታችን ደስተኞች ነን።

በ1980ዎቹ ዓመታት አጋማሽ አካባቢ ተቃዋሚዎች በወቅቱ በኮሪያ ያለውን ሕጋዊ ኮርፖሬሽን በበላይነት የሚመሩትን ወንድሞች በሐሰት ወነጀሏቸው። እነዚህ ወንድሞች የተከሰሱት ወጣት ወንዶች በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዳይካፈሉ ያስተምራሉ ተብለው ነበር። በመሆኑም መንግሥት እያንዳንዳችንን ጠርቶ አነጋገረን። ጥር 22, 1987 የአቃቤ ሕግ ቢሮ የተመሠረቱብን ክሶች በሙሉ መሠረተ ቢስ መሆናቸውን አረጋገጠ። ይህ ውሳኔ ወደፊት እኛን በተመለከተ ሊኖር የሚችለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስተካከል ይረዳል።

አምላክ ሥራችንን ባርኮልናል

የገለልተኝነት አቋማችንን በመጠበቃችን በኮሪያ በስብከት ሥራችን ላይ የሚሰነዘረው ተቃውሞ እየበረታ ሄደ። በመሆኑም ትላልቅ ስብሰባዎች የምናደርግባቸውን ተስማሚ ቦታዎች ማግኘት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስቸጋሪ ሆነ። በዚህም የተነሳ በአካባቢው የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች ትላልቅ ስብሰባዎች የሚደረጉበት አንድ አዳራሽ በፉሳን የገነቡ ሲሆን ይህም በሩቅ ምሥራቅ አገሮች ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያ አዳራሽ ነው። ሚያዝያ 5, 1976 በአዳራሹ ውስጥ ተገኝተው በነበሩት 1,300 ሰዎች ፊት የውሰናውን ንግግር የመስጠት መብት በማግኘቴ ተደስቻለሁ።

ከ1950 አንስቶ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በኮሪያ ለተወሰነ ጊዜ እንዲያገለግሉ ይመደቡ ነበር። ከእነዚህ ወታደሮች መካከል ብዙዎች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሲመለሱ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። አብዛኛውን ጊዜ ከእነዚህ ወንድሞች ደብዳቤ የሚደርሰን ሲሆን ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ እነሱን መርዳት በመቻላችን እንደተባረክን ይሰማናል።

መስከረም 26, 2006 ተወዳጇን የትዳር ጓደኛዬን ሊዝን በሞት በመነጠቄ አዝኛለሁ። እሷን ከጎኔ ማጣቴ በጣም ይሰማኛል። ኮሪያ ውስጥ በቆየችባቸው 51 ዓመታት የተሰጠንን የትኛውንም ምድብ ያለ ማጉረምረም በደስታ ትቀበል ነበር። በአንድ ወቅት ፈጽሞ ከዩናይትድ ስቴስት የመውጣት ሐሳብ ያልነበራት ሊዝ እዚህ ከመጣን በኋላ ወደዚያ ለመመለስ ሐሳብ አቅርባ ሌላው ቀርቶ የመመለስ ፍላጎት እንዳላት የሚጠቁም ፍንጭ እንኳ አሳይታ አታውቅም!

በአሁኑ ወቅት የኮሪያ ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆኜ አገለግላለሁ። ቀደም ባሉት ዓመታት በጣት የሚቆጠሩ የነበሩት የቤተሰቡ አባላት በአሁኑ ጊዜ ወደ 250 ደርሰዋል። እኔም በኮሪያ የሚካሄደውን ሥራ በበላይነት ከሚከታተሉት ሰባት የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የመሆን መብት አግኝቻለሁ።

ወደ ኮሪያ ስንመጣ አገሪቱ በከፋ ድህነት ውስጥ የነበረች ሲሆን በዛሬው ጊዜ ግን በዓለም ላይ ከሚገኙት የሠለጠኑ አገሮች አንዷ ሆናለች። በአሁኑ ጊዜ በኮሪያ ከ95,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ወደ 40 በመቶ የሚሆኑት የዘወትር አሊያም ረዳት አቅኚ በመሆን ያገለግላሉ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች አምላክን በኮሪያ በማገልገልና የአምላክ ሕዝቦች ቁጥር እያደገ ሲሄድ በማየት ያገኘሁት ደስታ እጥፍ ድርብ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብረውን ከተመደቡት ሚስዮናውያን ጋር ኮሪያ ስንደርስ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በፉሳን ስናገለግል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1971 ከወንድም ፍራንዝ ጋር፣ ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ በሆነው ክልል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሊዝ ጋር፣ ከመሞቷ ጥቂት ቀደም ብሎ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቤቴል ቤተሰብ አባል በመሆን የማገለግልበት የኮሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ