በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ ትመላለሳለህ?

ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ ትመላለሳለህ?

ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ ትመላለሳለህ?

“እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም።”—ኢዮብ 27:5 NW

1, 2. ምን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል? የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

የአንድን ቤት ፕላን እየተመለከትክ ነው እንበል። ቤቱ ለመኖሪያ ምን ያህል አመቺ እንደሚሆን በማሰብ ትገረማለህ። ይህ ቤት ሲሠራ አንተንም ሆነ ቤተሰብህን እንዴት ሊጠቅማችሁ እንደሚችል ስታስብ ትደሰታለህ። ይሁን እንጂ ቤቱን ሠርተህ በውስጡ መኖር ካልጀመርክ እንዲሁም በየጊዜው እድሳት ካላደረግህለት ፕላኑም ሆነ ከቤቱ ጋር በተያያዘ ያሰብካቸው ነገሮች በሙሉ ብዙም ጥቅም አይኖራቸውም ቢባል አትስማማም?

2 በተመሳሳይም ንጹሕ አቋም፣ እኛንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች በእጅጉ የሚጠቅም በጣም አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ እናስብ ይሆናል። ሆኖም ክርስቲያናዊ ንጹሕ አቋም ካልያዝንና ይህን አቋማችንን ጠብቀን ካልተመላለስን ይህንን ባሕርይ ማድነቃችን ብቻ ብዙም ጠቀሜታ አይኖረውም። በዛሬው ጊዜ የግንባታ ሥራ በአብዛኛው ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። (ሉቃስ 14:28, 29) በተመሳሳይም ንጹሕ አቋም መያዝ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል፤ ያም ቢሆን ግን የሚያስገኘው ጥቅም የሚክስ ነው። ከዚህ አንጻር እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመርምር፦ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው? ክርስቲያናዊ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ማድረግ እንችላለን? አንድ ሰው በሆነ ወቅት ላይ ንጹሕ አቋሙን ቢያጎድፍ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

3, 4. (ሀ) ይሖዋ ንጹሕ አቋም እንድንይዝ የሚረዳን በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) በኢየሱስ ሕይወት እንደታየው ንጹሕ አቋም መያዝ የምንችለው እንዴት ነው?

3 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ፣ ንጹሕ አቋማችንን በመጠበቅ ረገድ የራሳችንን ምርጫ እንድናደርግ አጋጣሚውን በመስጠት አክብሮናል። ደስ የሚለው ግን ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ በምናደርገው ጥረት ብቻችንን አልተወንም። ይሖዋ፣ ንጹሕ አቋም መያዝ የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያስተምረን ከመሆኑም በላይ ያስተማረንን ነገሮች በተግባር ለማዋል እንድንችል የሚረዳንን ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:13) ከዚህም ባሻገር ያለ ነቀፋ ወይም ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው ለመመላለስ ለሚጥሩ ሁሉ መንፈሳዊ ጥበቃ ያደርግላቸዋል።—ምሳሌ 2:7

4 ይሖዋ፣ ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ ያስተማረን እንዴት ነው? ዋነኛው መንገድ ልጁን ኢየሱስን ወደ ምድር በመላክ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በኖረበት ዘመን በሙሉ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ ታዟል። “እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ” ነበር። (ፊልጵ. 2:8) ኢየሱስ ባከናወናቸው ነገሮች ሁሉ በሰማይ የሚኖረውን አባቱን ታዟል፤ ሌላው ቀርቶ መታዘዝ በጣም አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ታዛዥነት አሳይቷል። ኢየሱስ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም” ብሏል። (ሉቃስ 22:42) ሁላችንም ‘እኔስ እንዲህ ዓይነት የታዛዥነት መንፈስ አለኝ?’ በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። በትክክለኛ ዝንባሌ ተነሳስተን ታዛዥ ሆነን በመኖር ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንችላለን። ታዛዥነት ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆንባቸውን አንዳንድ የሕይወት ዘርፎች እስቲ እንመልከት።

5, 6. (ሀ) ዳዊት ሌሎች ሰዎች በማያዩን ጊዜም እንኳ ንጹሕ አቋምን መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ ፈተና የሚሆኑባቸው ምን ነገሮች ያጋጥሟቸዋል?

5 ብቻችንን እንደሆንን በምናስብበት ጊዜም ጭምር ይሖዋን መታዘዝ ይኖርብናል። መዝሙራዊው ዳዊት ብቻውን በሚሆንበት ጊዜም እንኳ በንጹሕ ልብ ወይም አቋም የመመላለስን አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። (መዝሙር 101:2ን አንብብ።) ዳዊት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ከሰዎች ጋር ነበር። በመቶዎች አልፎ ተርፎም በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች መሃል የተገኘባቸው በርካታ አጋጣሚዎች እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም። (ከመዝሙር 26:12 ጋር አወዳድር።) ንጉሡ ለሕዝቡ ጥሩ ምሳሌ እንዲሆን ስለሚጠበቅበት ከሰዎች ጋር በሚሆንበት ጊዜ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ አስፈላጊ ነበር። (ዘዳ. 17:18, 19) ሆኖም ዳዊት በእነዚህ ወቅቶች ብቻ ሳይሆን ‘በቤቱ ውስጥ’ ብቻውን በሚሆንበት ጊዜም ጭምር በንጹሕ አቋም መመላለስ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። እኛስ እንደዚህ ይሰማናል?

6 ዳዊት በመዝሙር 101:3 ላይ “በዐይኔ ፊት፣ ክፉ ነገር አላኖርም” በማለት ተናግሯል። በዛሬው ጊዜ በተለይ ደግሞ ብቻችንን ስንሆን ክፉ ወይም ከንቱ ነገሮችን ለመመልከት የምንፈተንባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። በዚህ ረገድ ኢንተርኔት ለብዙዎች ፈተና ሆኖባቸዋል። በኢንተርኔት አማካኝነት ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን አልፎ ተርፎም የብልግና ምስሎችን በቀላሉ መመልከት ይቻላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ ዳዊት ቀደም ሲል የጠቀሰውን ሐሳብ ላስጻፈው አምላክ መታዘዝ ሊሆን ይችላል? የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ነገሮች ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸውና መጥፎ የሆኑ ምኞቶችን ይቀሰቅሳሉ፤ ሕሊናን ያቆሽሻሉ እንዲሁም የጋብቻን መሠረት ይሸረሽራሉ። ከዚህም በላይ እንዲህ ያሉት ነገሮች፣ የሚያዘጋጇቸውንም ሆነ የሚመለከቷቸውን ወይም የሚያነቧቸውን ሰዎች ያዋርዳሉ።—ምሳሌ 4:23፤ 2 ቆሮ. 7:1፤ 1 ተሰ. 4:3-5

7. ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚረዳን የትኛውን ጥቅስ ማስታወሳችን ነው?

7 እርግጥ ነው፣ የትኛውም የይሖዋ አገልጋይ መቼም ቢሆን ብቻውን ነው ሊባል አይችልም። በሰማይ የሚኖረው አባታችን በፍቅር ተነሳስቶ ይመለከተናል። (መዝሙር 11:4ን አንብብ።) ይሖዋ፣ ፈተናዎችን ስትቋቋም ሲመለከት ምን ያህል ይደሰት ይሆን! የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች ስትቋቋም ኢየሱስ በማቴዎስ 5:28 ላይ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ እያደረግህ ነው። መጥፎ ነገር እንድታደርግ የሚያነሳሱህን ምስሎች በምንም ዓይነት ላለመመልከት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። የብልግና ምስሎችን በማየት አሊያም እንዲህ ያሉ ጽሑፎችን በማንበብ ውድ የሆነውን ንጹሕ አቋምህን ርካሽ በሆነ ነገር አትለውጠው!

8, 9. (ሀ) ዳንኤልና ጓደኞቹ ንጹሕ አቋምን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ምን ፈተና ገጥሟቸው ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወጣት ክርስቲያኖች ይሖዋንም ሆነ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ማስደሰት የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ከዚህም በተጨማሪ አማኝ ካልሆኑ ሰዎች ጋር በምንሆንበት ጊዜ ይሖዋን በመታዘዝ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅ እንችላለን። የዳንኤልንና የሦስቱን ጓደኞቹን ሁኔታ አስታውስ። ወደ ባቢሎን ተማርከው የተወሰዱት ገና በወጣትነታቸው ሲሆን ባቢሎናውያኑ ደግሞ ስለ ይሖዋ ምንም አያውቁም አሊያም ያላቸው እውቀት ውስን ነበር፤ በእነዚህ የማያምኑ ሰዎች መካከል የነበሩት አራት ዕብራውያን ወጣቶች የአምላክ ሕግ የሚከለክላቸውን ምግቦች እንዲመገቡ ጫና ተደረገባቸው። እነዚህ ወጣቶች የአምላክን ሕግ ለመጣስ ቢፈልጉ ሰበብ መፍጠር ይችሉ ነበር። ወላጆቻቸውም ሆኑ የእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲሁም ካህናቱ አራቱ ወጣቶች የሚያደርጉትን ነገር ሊያዩ አይችሉም። ሆኖም ማን ሊያያቸው ይችላል? ይሖዋ የሚያደርጉትን ነገር ያያል። ስለዚህ እነዚህ ወጣቶች ውሳኔያቸው ችግር እንደሚያስከትልባቸው ቢያውቁም የሚደረግባቸውን ጫና ተቋቁመው በአቋማቸው በመጽናት ይሖዋን ታዝዘዋል።—ዳን. 1:3-9

9 በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮችም አምላክ ለክርስቲያኖች ያወጣቸውን መመሪያዎች በመታዘዝና እኩዮቻቸው በሚያሳድሩባቸው ጎጂ ተጽዕኖ ባለመሸነፍ ከአራቱ ዕብራውያን ወጣቶች ጋር የሚመሳሰል እርምጃ እየወሰዱ ነው። እናንት ወጣቶች፣ አደገኛ ዕጾችን እንድትወስዱና በዓመጽ እንድትካፈሉ፣ እንድትሳደቡ፣ የጾታ ብልግና እንዲሁም ሌሎች መጥፎ ድርጊቶችን እንድትፈጽሙ የሚደረግባችሁን ጫና ስትቋቋሙ ይሖዋን እየታዘዛችሁት ነው። ይሖዋን ስትታዘዙ ደግሞ ንጹሕ አቋማችሁን መጠበቃችሁ ነው። እንዲህ ስታደርጉ ራሳችሁን የምትጠቅሙ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋንና የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ታስደስታላችሁ!—መዝ. 110:3

10. (ሀ) አንዳንድ ወጣቶች ንጹሕ አቋማቸውን እንዲያጎድፉ ያደረጋቸው ስለ ዝሙት ምን የተሳሳተ አመለካከት ማዳበራቸው ነው? (ለ) ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያለን ፍላጎት ወደ ዝሙት ሊመሩ ከሚችሉ ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል?

10 ከዚህም በላይ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ታዛዥ መሆን ይጠበቅብናል። የአምላክ ቃል ዝሙትን እንደሚያወግዝ እናውቃለን። ያም ሆኖ ግን ቀስ በቀስ ከታዛዥነት በመራቅ ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን የማድረግ አዝማሚያ ልናሳይ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ወጣቶች በአፍ ወይም በፊንጢጣ የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ አሊያም አንዳቸው የሌላውን ብልት ያሻሻሉ፤ እነዚህ ወጣቶች እንዲህ ያሉት ድርጊቶች ቃል በቃል “የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም” የተለዩ እንደሆኑ ስለሚያስቡ ያን ያህል መጥፎ አይደሉም የሚል ሰበብ ያቀርባሉ። እንደዚህ የሚያደርጉ ወጣቶች ዝሙት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እነዚህን ድርጊቶች በሙሉ እንደሚያጠቃልል ይዘነጋሉ፤ አሊያም ድርጊታቸው ዝሙት እንደሆነ ቢያውቁም ይህን ከማድረግ አይርቁም። እንደነዚህ ያሉ መጥፎ ድርጊቶችን የሚፈጽም ሰው ሊወገድ ይችላል። * ከዚህ የከፋው ደግሞ እነዚህ ወጣቶች ንጹሕ አቋማቸውን የመጠበቅን አስፈላጊነት ችላ ማለታቸው ነው። ክርስቲያኖች፣ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ጥረት ስለምናደርግ መጥፎ ነገሮችን ለመፈጸም የሚያስችለን ሰበብ አንፈላልግም። ለቅጣት እስካላጋለጠን ድረስ የቻልነውን ያህል ወደ ኃጢአት ድንበር ለመቅረብ አንሞክርም። መጥፎ ድርጊት መፈጸም ሊያስከትል በሚችለው የፍርድ እርምጃ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ይሖዋን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግና ስሜቱን ላለመጉዳት እንጥራለን። ወደ ኃጢአት ድንበር ምን ያህል መቅረብ እንደምንችል ለማየት ከመሞከር ይልቅ ከኃጢአት በመራቅ ‘ከዝሙት እንሸሻለን።’ (1 ቆሮ. 6:18) በዚህ መንገድ ከልባችን ንጹሕ አቋማችንን የምንጠብቅ ሰዎች መሆናችንን እናሳያለን።

ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ምን ማድረግ እንችላለን?

11. በእያንዳንዱ ሁኔታ ታዛዥ መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

11 ንጹሕ አቋም መያዝ የምንችለው ታዛዥ በመሆን ነው፤ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ደግሞ ታዛዦች ሆነን መኖር ያስፈልገናል። አንድን ትእዛዝ ማክበር ቀላል ነገር ይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ስንሆን የምናሳየው ታዛዥነት በጊዜ ሂደት አንድ ላይ ተዳምሮ ንጹሕ አቋም በማሳየት ረገድ ጥሩ ስም እንድናተርፍ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ጡብ ብቻውን ብዙም የሚጠቅም ላይመስል ይችላል፤ ሆኖም በርከት ያሉ ጡቦችን አንዱን በአንዱ ላይ መልክ ባለው መንገድ በማደራረብ የሚያምር ቤት መሥራት ይቻላል። እኛም ታዛዥ ሆነን በመቀጠል ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን።—ሉቃስ 16:10

12. ዳዊት ፍትሕ የጎደለው ድርጊትና በደል ቢፈጸምበትም ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ በመቀጠል ምን ምሳሌ ትቷል?

12 በተለይ ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን፣ በደል ሲደርስብን ወይም ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ሲፈጸምብን በመጽናት ንጹሕ አቋማችንን መጠበቃችንን እናሳያለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት ወጣት እያለ፣ የይሖዋን ሥልጣን እንደሚወክል ተደርጎ ይታይ የነበረው ንጉሥ የሚያደርስበትን ስደት መቋቋም አስፈልጎት ነበር። በወቅቱ ንጉሥ ሳኦል የይሖዋን ሞገስ ያጣ ሲሆን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በነበረው በዳዊት በጣም ይቀና ነበር። ያም ሆኖ ሳኦል ለተወሰነ ጊዜ በሥልጣኑ ላይ የቆየ ከመሆኑም በላይ ዳዊትን ለማሳደድ በእስራኤል ሠራዊት ይጠቀም ነበር። ይሖዋም እንዲህ ያለው ፍትሕ የጎደለው ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እንዲቀጥል ፈቅዶ ነበር። ታዲያ ዳዊት አምላክን አማረረ? መጽናቱ ምንም ጥቅም እንደሌለው አድርጎ አስቦ ይሆን? በጭራሽ እንዲህ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ሳኦልን ለመበቀል የሚያስችል አጋጣሚ ቢያገኝም እንዲህ ከማድረግ በመቆጠብ በአምላክ የተቀባው ንጉሥ ለነበረው ሥልጣን ጥልቅ አክብሮት ማሳየቱን ቀጥሏል።—1 ሳሙ. 24:2-7

13. አንድ ሰው ቢበድለን ወይም ቅር ቢያሰኘን ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

13 ዳዊት በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የሚገኙበት የዓለም አቀፉ ጉባኤ አባላት በመሆናችን ከወንድሞቻችን መካከል አንዱ ሊበድለን ይችላል፤ ወይም እውነትን ይተው ይሆናል። እርግጥ ነው፣ በቡድን ደረጃ የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ አቋማቸው ሊበላሽ በማይችልበት ዘመን ላይ በመገኘታችን ተባርከናል። (ኢሳ. 54:17) ያም ሆኖ አንድ ሰው ቢያሳዝነን ወይም ስሜታችንን ቢጎዳው ምን ማድረግ ይኖርብናል? በእምነት ባልንጀራችን ላይ ቂም የምንይዝ ወይም ምሬት ልባችንን እንዲመርዘው የምንፈቅድ ከሆነ ንጹሕ አቋማችንን እናጎድፋለን። ሌሎች የሚያደርጉት ነገር በአምላክ ላይ እንድናማርር ወይም ታማኝነታችንን እንድናጎድል ፈጽሞ ሰበብ ሊሆነን አይችልም። (መዝ. 119:165) ችግሮች እያጋጠሙንም እንኳ መጽናታችን ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል።

14. ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ከድርጅታዊ አሠራርና ከመሠረተ ትምህርት ጋር የተያያዙ ለውጦች ሲደረጉ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?

14 በተጨማሪም ስህተት ፈላጊዎች ወይም ነቃፊዎች ከመሆን በመቆጠብ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን። ይህን ስናደርግ ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን እናሳያለን። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት ይሖዋ ሕዝቦቹን እየባረካቸው ነው። እውነተኛው አምልኮ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍ ብሏል። (ኢሳ. 2:2-4) ስለ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በተሰጠው ማብራሪያ ወይም ነገሮች በሚከናወኑበት መንገድ ላይ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ያለማንገራገር ልንቀበላቸው እንፈልጋለን። መንፈሳዊው ብርሃን አሁንም እየጨመረ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማየታችን ያስደስተናል። (ምሳሌ 4:18) አንድ ማስተካከያ የተደረገበትን ምክንያት መረዳት ከከበደን ይሖዋ ነጥቡን መገንዘብ እንድንችል ይረዳን ዘንድ እንጸልያለን። እስከዚያው ድረስ ግን ታዛዥ ሆነን በመቀጠል ንጹሕ አቋማችንን እንጠብቃለን።

አንድ ሰው ንጹሕ አቋሙን ቢያጎድፍ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

15. ንጹሕ አቋምህን ሊያጎድፍብህ የሚችለው ማን ብቻ ነው?

15 ይህ በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጥያቄ ነው ቢባል አትስማማም? ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ንጹሕ አቋም በጣም አስፈላጊ ባሕርይ ነው። ንጹሕ አቋማችንን ካልጠበቅን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነው ዝምድና ይበላሻል፤ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ አይኖረንም። ልትዘነጋው የማይገባ አንድ ነገር አለ፦ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ንጹሕ አቋምህን ሊያጎድፍብህ የሚችለው አንድ ግለሰብ ብቻ ነው። ይህ ግለሰብ አንተው ራስህ ነህ። ኢዮብ ይህንን እውነታ በሚገባ ስለተገነዘበ “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5 NW) አንተም እንዲህ ያለ አቋም ካለህ እንዲሁም ይሖዋን የሙጥኝ ብለህ የምትኖር ከሆነ ንጹሕ አቋምህን እንዳትጠብቅ የሚያግድህ ነገር አይኖርም።—ያዕ. 4:8

16, 17. (ሀ) አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ከሠራ የትኛውን አካሄድ መከተሉ ስህተት ነው? (ለ) ሊወስደው የሚገባው ትክክለኛ እርምጃ ምንድን ነው?

16 ያም ሆኖ አንዳንዶች ንጹሕ አቋማቸውን ያጎድፋሉ። ሐዋርያት በሕይወት በነበሩበት ዘመን እንደሆነው ሁሉ ዛሬም አንዳንዶች ከባድ ኃጢአት መሥራት ልማድ ሆኖባቸዋል። አንተም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ ምንም ተስፋ የለህም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እስቲ በቅድሚያ ማድረግ የሌለብህን ነገር እንመልከት። ሰው ስለሆንን፣ የሠራናቸውን ኃጢአቶች ከወላጆቻችን ወይም ከእምነት ባልንጀሮቻችን አሊያም ከሽማግሌዎች መደበቅ ይቀናናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ግን ምሕረትን ያገኛል” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል። (ምሳሌ 28:13) ከአምላክ ሊሰወር የሚችል ምንም ነገር ስለሌለ ኃጢአትን ለመደበቅ መሞከር ከባድ ስህተት ነው። (ዕብራውያን 4:13ን አንብብ።) አንዳንዶች በአንድ በኩል ከባድ ኃጢአቶችን እየፈጸሙ በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋን በማገልገል ሁለት ዓይነት ሕይወት ለመምራት ይሞክራሉ። እንዲህ ዓይነት ሕይወት የሚመራ ሰው ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል ሊባል አይችልም፤ ይህ ሰው ንጹሕ አቋሙን አጉድፏል። ይሖዋ የሠሩትን ከባድ ኃጢአት የሚደብቁ ሰዎች በሚያቀርቡት አምልኮ አይደሰትም። እንዲያውም እንዲህ ያለው ግብዝነት ያስቆጣዋል።—ምሳሌ 21:27፤ ኢሳ. 1:11-16

17 አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ ሊወስደው የሚገባው ትክክለኛ እርምጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል። በዚህ ወቅት የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ መጠየቅ አለበት። ይሖዋ ከባድ መንፈሳዊ ሕመም ያጋጠማቸውን ሰዎች ለመርዳት ዝግጅት አድርጓል። (ያዕቆብ 5:14ን አንብብ።) ተግሣጽ ወይም እርማት ሊሰጥህ እንደሚችል በመፍራት መንፈሳዊ ጤንነትህን ለማሻሻል የሚረዳህን እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አትበል። ደግሞስ አንድ ሰው ለሕይወቱ የሚያሠጋ የጤና ችግር ቢኖርበት፣ መርፌ መወጋት ወይም ቀዶ ሕክምና ማድረግ የሚያስከትልበትን ጊዜያዊ ሥቃይ በመፍራት ችግሩን ከማስተካከል ወደኋላ ማለቱ ብልህነት ነው?—ዕብ. 12:11

18, 19. (ሀ) የዳዊት ሕይወት፣ አንድ ሰው ንጹሕ አቋሙን ካጎደፈ ይህን አቋሙን መልሶ ማግኘት እንደሚችል የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ንጹሕ አቋምን በመጠበቅ ረገድ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

18 ከባድ ኃጢአት የፈጸመ ሰው አቋሙን ሙሉ በሙሉ ማስተካከል ይችላል? ንጹሕ አቋም አንድ ጊዜ ከጎደፈ እንደገና ሊስተካከል ይችላል? አሁንም የዳዊትን ምሳሌ እንመልከት። ዳዊት ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ ነበር። የሌላ ሰው ሚስት ከመመኘቱና ከእሷ ጋር ምንዝር ከመፈጸሙም በላይ ምንም ጥፋት የሌለበትን የሴትየዋን ባል አስገደለው። በዚያን ወቅት ዳዊትን ንጹሕ አቋሙን እንደሚጠብቅ ሰው አድርጎ ማሰብ እንደሚከብድ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ዳዊት ሁኔታውን ማስተካከል አይችልም ማለት ነው? ዳዊት ጠንከር ያለ ተግሣጽ ያስፈለገው ሲሆን እሱም ተግሣጹን ተቀብሏል። ከልቡ ንስሐ በመግባቱ ይሖዋ ምሕረት አድርጎለታል። ዳዊት ከተሰጠው ተግሣጽ ትምህርት የወሰደ ሲሆን በቀሪው የሕይወት ዘመኑ አምላክን መታዘዙን በመቀጠል ንጹሕ አቋሙን መልሶ ማግኘት ችሏል። በምሳሌ 24:16 ላይ የሚገኘው “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” የሚለው ሐሳብ እውነተኝነት በዳዊት ሕይወት ላይ ታይቷል። ይህ የአምላክ አገልጋይ እንዲህ ያለ አካሄድ በመከተሉ ምን ዓይነት ስም ማትረፍ ችሏል? ይሖዋ፣ ዳዊት ከሞተ በኋላ ስለ እሱ ምን ብሎ እንደተናገረ ልብ በል። (1 ነገሥት 9:4ን አንብብ።) አምላክ፣ ዳዊትን ልበ ቅን እንደሆነ ወይም ንጹሕ አቋሙን እንደጠበቀ ሰው አድርጎ ተመልክቶታል። በእርግጥም ይሖዋ ከባድ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችን እንኳ ንስሐ ከገቡ ሊያነጻቸው ይችላል።—ኢሳ. 1:18

19 አንተም በፍቅር ተነሳስተህ አምላክን በመታዘዝ ንጹሕ አቋምህን መጠበቅ ትችላለህ። በታማኝነት ለመጽናት ጥረት አድርግ፤ ከባድ ኃጢአት ከፈጸምክ ደግሞ ከልብህ ንስሐ ግባ። ንጹሕ አቋም እንደ ዕንቁ ውድ የሆነ ባሕርይ ነው! ሁላችንም እንደሚከተለው ብሎ እንደተናገረው እንደ ዳዊት ያለ አቋም ይኑረን፦ “እኔ ግን ንጹሕ አቋሜን ጠብቄ እመላለሳለሁ።”—መዝ. 26:11 NW

[የግርጌ ማስታወሻ]

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ንጹሕ አቋምህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

• ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ መኖር የምትችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• አንድ ሰው ንጹሕ አቋሙን ቢያጎድፍ ይህን አቋሙን መልሶ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

‘እንዴት ያለ ደግነት ነው’

ይህን ሐሳብ የተናገረችው የአምስት ወር እርጉዝ የሆነች አንዲት ሴት ስትሆን እንዲህ እንድትል ያነሳሳትም አንዲት የማታውቃት ሴት ንጹሕ አቋሟን በመጠበቅ ያሳየቻት ደግነት ነው። ሴትየዋ አንድ ምግብ ቤት ገብታ ነበር፤ ከምግብ ቤቱ ከወጣች ከተወሰነ ሰዓት በኋላ የገንዘብ ቦርሳዋን እንደረሳችው አወቀች። በቦርሳው ውስጥ ወደ 20,000 ብር የሚጠጋ ገንዘብ የነበረ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ይህን ያህል ብዛት ያለው ገንዘብ ይዛ አትንቀሳቀስም። ቦርሳው መጥፋቱን ስታውቅ ምን እንደተሰማት ለአንድ ጋዜጣ አዘጋጅ ስትናገር “በጣም ደንግጬ ነበር” ብላለች። ሆኖም አንዲት ወጣት ቦርሳውን ያገኘችው ሲሆን ወዲያውኑም ባለቤቱን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጀመረች። ወጣቷ ያደረገችው ጥረት ስላልተሳካላት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደች፤ በመጨረሻም ፖሊሶች ነፍሰጡሯን ሴት አገኟት። ቦርሳዋ ጠፍቶባት የነበረችው ይህች ሴት ‘እንዴት ያለ ደግነት ነው’ በማለት ምስጋናዋን ገልጻለች። ቦርሳውን ያገኘችው ወጣት ገንዘቡን ለመመለስ ይህን ያህል የደከመችው ለምን ነበር? የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ይህች ወጣት “ንጹሕ አቋሟን የጠበቀችው በሃይማኖቷ ምክንያት እንደሆነ” ጋዜጣው ገልጿል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቶች ፈተና ቢያጋጥማቸውም ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ ይችላሉ

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳዊት በአንድ ወቅት ንጹሕ አቋሙን ቢያጎድፍም ይህን አቋሙን መልሶ ማግኘት ችሏል