በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ልዩ ሚና ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ልዩ ሚና ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ልዩ ሚና ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

“መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።”—ዮሐ. 14:6

1, 2. ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተው ልዩ ሚና ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

ባለፉት ዘመናት ሁሉ ብዙዎች ከሌሎች ለየት ብለው ለመታየት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በዚህ ረገድ የተሳካላቸው ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር በማከናወን ረገድ ከሌሎች የተለዩ እንደሆኑ አፋቸውን ሞልተው መናገር የሚችሉት ደግሞ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በብዙ መንገዶች ልዩ ነው።

2 ኢየሱስ የሚጫወተው ልዩ ሚና ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? በሰማይ ከሚኖረው አባታችን ከይሖዋ ጋር ከመሠረትነው ዝምድና ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው! ኢየሱስ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” ብሏል። (ዮሐ. 14:6፤ 17:3) ኢየሱስ ልዩ የሆነባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመርምር። እንዲህ ማድረጋችን በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ከፍ አድርገን እንድንመለከት ይረዳናል።

‘የአምላክ አንድያ ልጅ’

3, 4. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅ የተባለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ከፍጥረት ጋር በተያያዘ የተጫወተው ሚና ልዩ የሆነው እንዴት ነው?

3 ሰይጣን፣ ኢየሱስን በፈተነው ወቅት “የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት ጠርቶት ነበር። (ማቴ. 4:3, 6) ኢየሱስ ግን “የእግዚአብሔር ልጅ” ብቻ ሳይሆን ‘የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ’ ነው። (ዮሐ. 3:16, 18) “አንድያ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ፣ አንድ ብቻ” ወይም “ቀዳሚና ተከታይ የሌለው” አሊያም “ልዩ” የሚል ፍቺ አለው። ይሖዋ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ልጆች አሉት። ታዲያ ኢየሱስ “ቀዳሚና ተከታይ የሌለው” ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?

4 ኢየሱስ፣ ልዩ የሆነው በአባቱ በቀጥታ የተፈጠረው እሱ ብቻ በመሆኑ ነው። እሱ የበኩር ልጅ ነው። እንዲያውም “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው።” (ቈላ. 1:15) ኢየሱስ “ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ” ነው። (ራእይ 3:14 NW) ይህ አንድያ ልጅ ከፍጥረት ጋር በተያያዘ የተጫወተው ሚናም ልዩ ነው። ኢየሱስ፣ ፈጣሪ ወይም የፍጥረት ምንጭ አይደለም። ሆኖም ይሖዋ ሌሎች ነገሮችን በሙሉ የፈጠረው በእሱ ተጠቅሞ ነው። (ዮሐንስ 1:3ን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከእርሱ የሆነ፣ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በእርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በእርሱ አማካይነት የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።”—1 ቆሮ. 8:6

5. ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ኢየሱስ ልዩ የሆነባቸውን ሌሎች መንገዶች ጎላ አድርገው የሚገልጹት እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ ልዩ የሆነባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ቅዱሳን መጻሕፍት ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ልዩ ሚና ጎላ አድርገው የሚገልጹ በርካታ ስሞችን ይጠቀማሉ። ከእነዚህ መካከል በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለኢየሱስ የተሰጡትን ሌሎች አምስት ስሞች እንመርምር።

“ቃል”

6. ኢየሱስ “ቃል” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 ዮሐንስ 1:14ን አንብብ። ኢየሱስ “ቃል” ወይም ሎጎስ ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? ይህ ስያሜ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሌሎች ፍጥረታት ወደ ሕልውና ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ እያከናወነ ያለውን ሥራ የሚያመለክት ነው። ይሖዋ በምድር ላይ ለሚኖሩ የሰው ልጆች መልእክቱን ለማስተላለፍ በልጁ እንደተጠቀመ ሁሉ ለሌሎቹ መንፈሳዊ ልጆቹም መረጃና መመሪያዎችን ለመስጠት በዚህ ልጁ ተጠቅሟል። ኢየሱስ ያዳምጡት ለነበሩት አይሁዳውያን የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ፣ ቃል ወይም የአምላክ ቃል አቀባይ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፤ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የማስተምረው ትምህርት ከራሴ ሳይሆን፣ ከላከኝ የመጣ ነው። ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ፣ የእኔ ትምህርት ከእግዚአብሔር ወይም ከራሴ የመጣ መሆኑን ለይቶ ያውቃል።” (ዮሐ. 7:16, 17) ኢየሱስ፣ ወደ ሰማይ ተመልሶ ክብር ከተጎናጸፈ በኋላም “የእግዚአብሔር ቃል” በሚለው ስም መጠራቱን ቀጥሏል።—ራእይ 19:11, 13, 16

7. ኢየሱስ “ቃል” በመሆን ሥራውን ሲያከናውን የሚያሳየውን ትሕትና መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

7 ይህ ስያሜ ምን እንደሚያመለክት እስቲ ቆም ብለህ አስብ። ኢየሱስ ከይሖዋ ፍጥረታት ሁሉ በጥበቡ የሚተካከለው ባይኖርም በራሱ ጥበብ አልተማመነም። የሚናገረው አባቱ ያስተማረውን ብቻ ነው። የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ከመሳብ ይልቅ ምንጊዜም ሰዎች በይሖዋ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ያበረታታል። (ዮሐ. 12:50) ልንኮርጀው የሚገባ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! እኛም “የምሥራች” የመናገር ክቡር ሥራ ተሰጥቶናል። (ሮሜ 10:15) ትሕትና በማሳየት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መገንዘባችን የራሳችንን አመለካከት ከመናገር እንድንቆጠብ ሊገፋፋን ይገባል። በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት አድን መልእክት ለሌሎች ስንናገር “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን መመሪያ መከተል እንፈልጋለን።—1 ቆሮ. 4:6

“አሜን”

8, 9. (ሀ) “አሜን” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? ኢየሱስ “አሜን” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ “አሜን” በመሆን የተሰጠውን ሚና የተወጣው እንዴት ነው?

8 ራእይ 3:14ን አንብብ። ኢየሱስ “አሜን” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? “አሜን” የሚለው ቃል በቀጥታ ከዕብራይስጥ የተወሰደ ሲሆን “ይሁን” ወይም “በእርግጥ” የሚል ትርጉም አለው። ይህ ቃል “ታማኝ” ወይም “እምነት የሚጣልበት” መሆን የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። ይኸው ቃል የይሖዋን ታማኝነት ለማመልከት ተሠርቶበታል። (ዘዳ. 7:9፤ ኢሳ. 49:7) ታዲያ ኢየሱስ “አሜን” ተብሎ መጠራቱ ልዩ የሚያደርገው በምን መንገድ ነው? ሁለተኛ ቆሮንቶስ 1:19, 20 ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ እንመልከት፦ “እኛ የሰበክንላችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አዎን’ እና ‘አይደለም’ አልነበረም፤ ነገር ግን በእርሱ ዘወትር፣ ‘አዎን’ ነው። በእግዚአብሔር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ፣ ‘አዎን’ የሚሆኑት በእርሱ ነውና፤ እኛም በእርሱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ክብር፣ ‘አሜን’ የምንለው በዚህ ምክንያት ነው።”

9 አምላክ ቃል የገባቸው ተስፋዎች በሙሉ “አሜን” የሚሆኑት በኢየሱስ በኩል ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መመላለሱና መሥዋዕት ሆኖ መሞቱ ይሖዋ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ አረጋግጧል፤ እንዲሁም እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አስችሏል። በተጨማሪም ኢየሱስ በታማኝነት በመጽናቱ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የሰይጣን ክስ ውሸት መሆኑን አረጋግጧል። ሰይጣን፣ የአምላክ አገልጋዮች ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን መሠረታዊ ነገሮች ሲያጡ፣ መከራ ሲደርስባቸው ወይም ፈተና ሲያጋጥማቸው አምላክን እንደሚክዱት ገልጾ ነበር። (ኢዮብ 1:6-12፤ 2:2-7) ከአምላክ ፍጥረታት በሙሉ ለዚህ ክስ የማያሻማ መልስ መስጠት የሚችለው የአምላክ የበኩር ልጅ ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ የመግዛት መብት ላይ ከተነሳው ጥያቄ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ከአባቱ ጎን በመቆም ሉዓላዊነቱን እንደሚደግፍ አሳይቷል።

10. ኢየሱስ “አሜን” በመሆን የሚጫወተውን ልዩ ሚና መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

10 ኢየሱስ “አሜን” በመሆን የሚጫወተውን ልዩ ሚና መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው? ለይሖዋ ታማኝ ሆነን በመኖርና የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን በመደገፍ ነው። እንዲህ ስናደርግ በምሳሌ 27:11 (የ1954 ትርጉም) ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚለውን ሐሳብ እንደምንታዘዝ እናሳያለን።

“የአዲስ ኪዳን መካከለኛ”

11, 12. ኢየሱስ መካከለኛ በመሆን የሚጫወተው ሚና ልዩ የሆነው እንዴት ነው?

11 አንደኛ ጢሞቴዎስ 2:5, 6ን አንብብ። “በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል” ያለው “አንድ አስታራቂ” ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ “የአዲስ ኪዳን መካከለኛ” ነው። (ዕብ. 9:15፤ 12:24) ይሁን እንጂ ሙሴም የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ እንደሆነ ተገልጿል። (ገላ. 3:19) ታዲያ ኢየሱስ መካከለኛ በመሆን የሚጫወተው ሚና ልዩ የሆነው እንዴት ነው?

12 በበኩረ ጽሑፉ “መካከለኛ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ከሕግ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚሠራበት ነው። ይህ ቃል፣ ኢየሱስ ለአዲሱ ቃል ኪዳን ሕጋዊ መካከለኛ (ጠበቃ እንደማለት ነው) መሆኑን ይገልጻል፤ ይህ ቃል ኪዳን አዲስ ብሔር ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ እንዲወለድ አስችሏል። (ገላ. 6:16) ይህ ብሔር በሰማይ “የንጉሥ ካህናት” የሚሆኑትን በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። (1 ጴጥ. 2:9፤ ዘፀ. 19:6) ሙሴ መካከለኛ ሆኖ ያገለገለበት የሕጉ ቃል ኪዳን እንዲህ ያለ ብሔር ማስገኘት አልቻለም።

13. ኢየሱስ መካከለኛ በመሆን የሚጫወተው ሚና ምን ነገሮችን ያካትታል?

13 ኢየሱስ መካከለኛ በመሆን የሚጫወተው ሚና ምን ነገሮችን ያካትታል? ይሖዋ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሰዎች የኢየሱስ ደም ካስገኘው ውጤት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይሖዋ እንዲህ በማድረግ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እነዚህን ሰዎች ጻድቃን አድርጎ ይቆጥራቸዋል። (ሮሜ 3:24፤ ዕብ. 9:15) ይህም በመሆኑ አምላክ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ለመታቀፍ ብቁ እንደሆኑ አድርጎ ሊመለከታቸው ይችላል፤ በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ በመታቀፋቸው በሰማይ ነገሥታትና ካህናት የመሆን ተስፋ ይኖራቸዋል! ኢየሱስ መካከለኛ በመሆኑ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው እንዲመላለሱ ይረዳቸዋል።—ዕብ. 2:16

14. ሁሉም ክርስቲያኖች ተስፋቸው ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ መካከለኛ በመሆን የሚጫወተውን ሚና ከፍ አድርገው መመልከት ያለባቸው ለምንድን ነው?

14 በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የማይታቀፉትንና በሰማይ ሳይሆን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ባይካተቱም ከዚህ ቃል ኪዳን ይጠቀማሉ። የኃጢአት ይቅርታ ከማግኘታቸውም ሌላ እንደ ጻድቅ በመቆጠር የአምላክ ወዳጅ ሆነዋል። (ያዕ. 2:23፤ 1 ዮሐ. 2:1, 2) ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ይሁን በምድር ላይ መኖር እያንዳንዳችን ኢየሱስ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ በመሆን የሚጫወተውን ሚና ከፍ አድርገን እንድንመለከት የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን።

“ሊቀ ካህናት”

15. ኢየሱስ ሊቀ ካህናት በመሆን የሚጫወተው ሚና ቀደም ሲል ሊቀ ካህናት በመሆን ካገለገሉት ወንዶች ሁሉ የተለየ የሆነው በምን መንገድ ነው?

15 በጥንት ጊዜያት በርካታ ወንዶች ሊቀ ካህናት ሆነው ያገለገሉ ቢሆንም ኢየሱስ ሊቀ ካህናት በመሆን የሚጫወተው ሚና ልዩ ነው። እንዴት? ጳውሎስ እንዲህ ሲል መልሱን ሰጥቶናል፦ “እርሱም እንደ ሌሎቹ ሊቃነ ካህናት፣ መጀመሪያ ስለራሱ ኀጢአት ከዚያም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን በሰጠ ጊዜ፣ ስለ ኀጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት አቅርቦአልና። ሕጉ ደካማ የሆኑትን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣው መሐላ ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ሾሞአል።”—ዕብ. 7:27, 28 *

16. የኢየሱስ መሥዋዕት ልዩ የሆነው ለምንድን ነው?

16 ኢየሱስ ፍጹም ሰው ነበር፤ ይህም ሲባል አዳም ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት የነበረው ዓይነት ፍጹም ሕይወት ነበረው ማለት ነው። (1 ቆሮ. 15:45) በመሆኑም ፍጹምና የተሟላ መሥዋዕት ማለትም በድጋሚ መቅረብ የማያስፈልገው መሥዋዕት ለማቅረብ የሚያስችል ብቃት የነበረው ሰው ኢየሱስ ብቻ ነው። የሙሴ ሕግ በየቀኑ መሥዋዕቶች እንዲቀርቡ ያዝዝ ነበር። ሆኖም እነዚህ ሁሉ መሥዋዕቶች እንዲሁም የክህነት አገልግሎቱ ኢየሱስ ለሚያከናውነው ነገር ጥላ ነበሩ። (ዕብ. 8:5፤ 10:1) ኢየሱስ ከሌሎቹ ሊቀ ካህናት የበለጠ ነገር በማከናወኑና ሊቀ ካህናት በመሆን የሚያቀርበው አገልግሎት ዘላቂ በመሆኑ በዚህ ረገድ የሚጫወተው ሚና በእርግጥም ልዩ ነው።

17. ኢየሱስ፣ ሊቀ ካህናት በመሆን የሚጫወተውን ሚና ከፍ አድርገን መመልከት የሚኖርብን ለምንድን ነው? ይህንንስ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ ሊቀ ካህናት በመሆን የሚያከናውነው አገልግሎት በአምላክ ፊት ትክክለኛ አቋም እንዲኖረን ይረዳናል። እንዴት ያለ ድንቅ ሊቀ ካህናት አለን! ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በድካማችን የማይራራልን ሊቀ ካህናት የለንምና፤ ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ሊቀ ካህናት አለን፤ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም።” (ዕብ. 4:15) ይህን እውነታ መገንዘባችን ‘ለሞተልን እንጂ ከእንግዲህ ለራሳችን እንዳንኖር’ ሊያነሳሳን ይገባል።—2 ቆሮ. 5:14, 15፤ ሉቃስ 9:23

አስቀድሞ የተነገረለት “ዘር”

18. አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ምን ትንቢት ተነገረ? ይህን ትንቢት በተመለከተ ከጊዜ በኋላ ምን ነገር ታወቀ?

18 በኤደን ውስጥ የሰው ልጅ ሁሉንም ነገር ማለትም በአምላክ ፊት የነበረውን ንጹሕ አቋም፣ የዘላለም ሕይወትን፣ ደስታን እንዲሁም በገነት የመኖር አጋጣሚን ጨርሶ ያጣ ይመስል በነበረበት ወቅት ይሖዋ አምላክ አዳኝ እንደሚያስነሳ ትንቢት ተናገረ። ይህ አዳኝ ‘ዘር’ ተብሎ ተጠርቷል። (ዘፍ. 3:15) ባለፉት ዘመናት የተነገሩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጭብጥ ማንነቱ ባልተገለጸው በዚህ ዘር ላይ ያተኮረ ነበረ። ይህ ዘር ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ እንዲሁም ከንጉሥ ዳዊት የትውልድ ሐረግ እንደሚመጣ ተነግሮ ነበር።—ዘፍ. 21:12፤ 22:16-18፤ 28:14፤ 2 ሳሙ. 7:12-16

19, 20. (ሀ) ተስፋ የተደረገበት ዘር ማን ነው? (ለ) ተስፋ የተደረገበት ዘር ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይጨምራል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

19 ተስፋ የተደረገበት ይህ ዘር ማን ነበር? ገላትያ 3:16 ለዚህ ጥያቄ መልሱን ይሰጠናል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚሁ ምዕራፍ ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።” (ገላ. 3:29) ቅቡዓን ክርስቲያኖችም የአብርሃም ዘር ተብለው ከተጠሩ ተስፋ የተደረገበት ዘር ክርስቶስ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?

20 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአብርሃም ዝርያዎች እንደሆኑ የሚናገሩ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶች ነቢያት እንደሆኑ ይገልጻሉ። አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ ነቢያቶቻቸው የአብርሃም ዘሮች እንደሆኑ የሚገልጹ ሲሆን ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ቦታ ይሰጡታል። ይሁንና እነዚህ ሁሉ ሰዎች ተስፋ የተደረገው ዘር ናቸው? አይደሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ እንደጻፈው ከአብርሃም ዝርያዎች መካከል ተስፋ የተደረገበት ዘር እንደሆኑ መናገር የሚችሉት ሁሉም አይደሉም። የሰው ልጆች የሚባረኩት በይስሐቅ ዘር ብቻ እንጂ በሌሎቹ የአብርሃም ልጆች በኩል አይደለም። (ዕብ. 11:18) አስቀድሞ የተነገረለት የዚህ ዘር ዋነኛ ክፍል አንድ ሰው ብቻ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ከአብርሃም ጀምሮ ያለው የትውልድ ሐረጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቧል። * ከጊዜ በኋላ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል የሆኑት ሌሎች ሰዎች በሙሉ የዚህ ዘር ክፍል ሊሆኑ የቻሉት ‘የክርስቶስ በመሆናቸው’ ነው። በእርግጥም ኢየሱስ በዚህ ትንቢት አፈጻጸም ረገድ የተጫወተው ሚና ልዩ ነው።

21. ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለውን ልዩ ሚና ከተወጣበት መንገድ አንተን ይበልጥ የሚማርክህ የትኛው ነው?

21 ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ልዩ ሚና በአጭሩ መመልከታችን ምን ትምህርት ለማግኘት አስችሎናል? የአምላክ አንድያ ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በእርግጥም ልዩ መሆኑን ተመልክተናል። ያም ቢሆን በኋላ ላይ ኢየሱስ የተባለው ይህ ልዩ የሆነ የአምላክ ልጅ ፈጽሞ ለራሱ ክብር ሳይሻ ምንጊዜም ከአባቱ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እሱን በትሕትና አገልግሏል። (ዮሐ. 5:41፤ 8:50) ይህ በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው ክርስቲያኖች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ልክ እንደ ኢየሱስ እኛም “ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር [የማድረግ]” ግብ ይኑረን።—1 ቆሮ. 10:31

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.15 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንደተናገሩት “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ይገልጻል፤ ይህ ቃል “የክርስቶስ ሞት የማይደገም፣ ልዩ ወይም በዓይነቱ ብቸኛ መሆኑን ያመለክታል።”

^ አን.20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የነበሩት አይሁዳውያን የአብርሃም ዝርያዎች በመሆናቸው የአምላክን ሞገስ እንደሚያገኙ ቢያስቡም እንኳ መሲሕ ወይም ክርስቶስ ሆኖ እንደሚመጣ የሚጠብቁት ግን አንድ ሰው ብቻ ነበር።—ዮሐ. 1:25፤ 7:41, 42፤ 8:39-41

ታስታውሳለህ?

• ለኢየሱስ የተሰጡት ስሞች ይህ የአምላክ ልጅ የሚጫወተውን ልዩ ሚና በተመለከተ ምን ግንዛቤ እንዲኖርህ ረድተውሃል? (ሣጥኑን ተመልከት።)

• የይሖዋ ልዩ ልጅ የሆነው ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መኮረጅ የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ልዩ ሚና የሚያመለክቱ አንዳንድ ስሞች

አንድያ ልጅ። (ዮሐ. 1:3) በአባቱ በቀጥታ የተፈጠረው ኢየሱስ ብቻ ነው።

ቃል። (ዮሐ. 1:14) ይሖዋ ለሌሎች ፍጥረታቱ መረጃና መመሪያዎችን ለመስጠት ልጁን እንደ ቃል አቀባይ ይጠቀምበታል።

አሜን። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ በምድር ላይ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ መመላለሱና መሥዋዕት ሆኖ መሞቱ ይሖዋ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ አረጋግጧል፤ እንዲሁም እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አስችሏል።

የአዲስ ኪዳን መካከለኛ። (1 ጢሞ. 2:5, 6) ኢየሱስ ለአዲሱ ቃል ኪዳን ሕጋዊ መካከለኛ በመሆን አዲስ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤል’ እንዲወለድ አስችሏል። ይህ ብሔር በሰማይ “የንጉሥ ካህናት” የሚሆኑትን ክርስቲያኖች ያቀፈ ነው። —ገላ. 6:16፤ 1 ጴጥ. 2:9

ሊቀ ካህናት። (ዕብ. 7:27, 28) ፍጹም የሆነ ማለትም በድጋሚ መቅረብ የማያስፈልገው መሥዋዕት ለማቅረብ የሚያስችል ብቃት የነበረው ሰው ኢየሱስ ብቻ ነው። ኢየሱስ ከኃጢአት ሊያነጻንና የኃጢአት ውጤት ከሆነው ከሞት ሊታደገን ይችላል።

ተስፋ የተደረገበት ዘር። (ዘፍ. 3:15) አስቀድሞ የተነገረለት የዚህ ዘር ዋነኛ ክፍል አንድ ሰው ብቻ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከጊዜ በኋላ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል የሆኑት ሌሎች ሰዎች በሙሉ ‘የክርስቶስ ናቸው።’—ገላ. 3:29