በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዘሌዋውያን 3:17 ላይ የሚገኘው ሕግ ‘ስብ ከቶ አትብሉ’ የሚል ቢሆንም በነህምያ 8:10 (የ1954 ትርጉም) ላይ አይሁዳውያን ‘የሰባውን ብሉ’ ተብለዋል። እነዚህን ጥቅሶች ማስማማት የምንችለው እንዴት ነው?

በነህምያ 8:10 (የ1954 ትርጉም) ላይ ‘የሰባ’ ተብሎ የተተረጎመው ቃልና በዘሌዋውያን 3:17 ላይ ‘ስብ’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል በበኩረ ጽሑፉ ልዩነት አላቸው። በዘሌዋውያን 3:17 ላይ ‘ስብ’ ተብሎ የተተረጎመው ኬሌቭ የተባለው የዕብራይስጥ ቃል የእንስሳትን ወይም የሰዎችን ስብ ያመለክታል። (ዘሌ. 3:3፤ መሳ. 3:22 የ1954 ትርጉም) በቁጥር 17 ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያመለክተው ‘ስብ ሁሉ የይሖዋ በመሆኑ’ እስራኤላውያን በመሥዋዕትነት የሚያቀርቡትን እንስሳ የሆድ ዕቃ የሚሸፍነውን ስብ እንዲሁም በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ስብ እንዳይበሉ ታዘው ነበር። (ዘሌ. 3:14-16) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው እስራኤላውያን ለይሖዋ በመሥዋዕትነት የሚቀርቡ እንስሳትን ስብ መብላት አልነበረባቸውም።

በሌላ በኩል ግን በነህምያ 8:10 ላይ ‘የሰባ’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል ማሽማኒም ሲሆን ይህ ቃል በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው እዚህ ጥቅስ ላይ ብቻ ነው። ይህ ቃል ሻሚን ከሚለው ግስ የመጣ ሲሆን “መስባት፣ የሰባ መሆን” የሚል ትርጉም አለው። ከዚህ ግስ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ቃላት የሚያስተላልፉት መሠረታዊ ሐሳብ ብልጽግናን እንዲሁም ደኅንነትን የሚያመለክት ይመስላል። (ከኢሳይያስ 25:6 የ1954 ትርጉም ጋር አወዳድር።) ከዚህ ግስ ከመጡት ቃላት መካከል ብዙ ጊዜ የሚሠራበት ሸሚን የተባለው ስም ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ “ዘይት” ተብሎ ተተርጉሟል። (ዘዳ. 8:8፤ ዘሌ. 24: 2) ማሽማኒም የሚለው ቃል በነህምያ 8:10 ላይ የተሠራበት በዛ ያለ ዘይት ተጨምሮበት የተዘጋጀ ምግብን ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም፤ ይህ ቃል ሙሉ በሙሉ ስብ ያልሆነን ሆኖም የተወሰነ ስብ ያለውን ሥጋም ያመለክት ይሆናል።

እስራኤላውያን የእንስሳት ስብ እንዳይበሉ ቢከለከሉም ቅባት የበዛባቸውንና ጣፋጭ የሆኑ ምግቦችን መመገብ ይችሉ ነበር። ከዱቄት የሚሠሩ የተጠበሱ ምግቦችን የመሳሰሉ አንዳንድ ነገሮች የሚበስሉት በእንስሳት ስብ ሳይሆን በአትክልት ዘይት አብዛኛውን ጊዜም በወይራ ዘይት ነበር። (ዘሌ. 2:7) በመሆኑም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው በነህምያ 8:10 ላይ የተጠቀሰው ‘የሰባ’ ነገር “የበለጸገውን ክፍል፣ ከሲታ ወይም ኮስማና ያልሆነውን ከዚህ ይልቅ በአትክልት ዘይት የተዘጋጁትን ጥሩ ጣዕም ያላቸው ምግቦች ጨምሮ ለመብላት የሚያስጎመጀውን ሁሉ ያመለክታል።”

እርግጥ ክርስቲያኖች፣ ስብ መብላትን የሚከለክለው መመሪያ የሙሴ ሕግ ክፍል እንደነበር አይዘነጉም። በመሆኑም ክርስቲያኖች፣ ከእንስሳት መሥዋዕት ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን ጨምሮ ሕጉን ማክበር አይጠበቅባቸውም።—ሮሜ 3:20፤ 7:4, 6፤ 10:4፤ ቈላ. 2:16, 17