በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥንታዊው ኪዩኒፎርም እና መጽሐፍ ቅዱስ

ጥንታዊው ኪዩኒፎርም እና መጽሐፍ ቅዱስ

ጥንታዊው ኪዩኒፎርም እና መጽሐፍ ቅዱስ

የሰው ልጆች፣ ቋንቋቸው በባቤል ከተደበላለቀ በኋላ በርካታ የአጻጻፍ ስልቶችን ፈጠሩ። በመሰጴጦሚያ የሚኖሩ እንደ ሱሜሪያውያንና ባቢሎናውያን ያሉ ሕዝቦች በኪዩኒፎርም መጠቀም ጀመሩ። ኪዩኒፎርም የሚለው ቃል የመጣው “የሽብልቅ ቅርጽ” ከሚለው የላቲን ቃል ሲሆን ባልደረቀ ሸክላ ላይ የሚጻፈውን ሦስት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ምልክት ይወክላል።

የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎች፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለተጠቀሱ ሕዝቦችና ክንውኖች የሚገልጹ በኪዩኒፎርም ወይም የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉ ጽሑፎችን በቁፋሮ አግኝተዋል። ስለዚህ ጥንታዊ የአጻጻፍ ስልት ምን የሚታወቅ ነገር አለ? በዚህ የአጻጻፍ ስልት የተጻፉት ጽሑፎች፣ መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ይሰጣሉ?

ለረጅም ጊዜ የቆዩ መዛግብት

ምሑራን እንደሚያምኑት በመሰጴጦሚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት አንድን ቃል ወይም ሐሳብ የሚገልጹት በምልክት አሊያም በሥዕል ነበር። ለአብነት ያህል፣ በሬን ለማመልከት የበሬ ጭንቅላት ይስሉ ነበር። መረጃን በጽሑፍ ማስፈር ይበልጥ አስፈላጊ ሲመጣ ግን የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች መጠቀም ተጀመረ። “በዚህ ጊዜ ቃላትን ብቻ ሳይሆን ክፍለ ቃላትን (syllables) የሚወክሉ ምልክቶች ተፈጠሩ፤ እነዚህ ምልክቶችም አንድ ላይ በመሆን ቃላትን መግለጽ ቻሉ” ሲል ኤን አይ ቪ አርኪኦሎጂካል ስተዲ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ያብራራል። ውሎ አድሮ 200 የሚሆኑ የሽብልቅ ቅርጽ ያላቸው ምልክቶች በመፈጠራቸው በእነዚህ ምልክቶች በመጠቀም “ከባድ የሆኑ ቃላትን ያካተተውንና አስቸጋሪ የሰዋስው ሥርዓት የያዘውን ንግግር በጽሑፍ ማስፈር ተቻለ።”

አብርሃም በኖረበት ዘመን ማለትም በ2,000 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የመጻፍ ዘዴ በደንብ ዳብሮ ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት 2,000 ዓመታት 15 ቋንቋዎች ይህን የአጻጻፍ ስልት መከተል ጀመሩ። የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች ከተጻፉት በቁፋሮ የተገኙ ጽሑፎች መካከል ከ99 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከሸክላ በተሠሩ ጽላቶች ላይ የተቀረጹ ናቸው። ባለፉት ከ150 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ በርከት ያሉ እንዲህ ዓይነት ጽላቶች በዑር፣ በዩርክ፣ በባቢሎን፣ በኒምሩድ፣ በኒፑር፣ በአሹር፣ በነነዌ፣ በማሬ፣ በኤብላ፣ በኡጋሪት እንዲሁም በአሜርና ተገኝተዋል። አርኪኦሎጂ ኦደሲ የተባለው መጽሔት እንዲህ ብሏል፦ “ባለሞያዎች፣ እስካሁን ድረስ ከአንድ ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ጽላቶች በቁፋሮ እንደተገኙና በየዓመቱ ደግሞ ተጨማሪ 25,000 ያህል ጽላቶች እንደሚገኙ ይገምታሉ፤ በእነዚህ ጽላቶች ላይ [ያለው ሐሳብ] የተጻፈው የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች ነው።”

የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች ላይ ጥናት የሚያካሂዱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምሑራን እነዚህን ጽሑፎች ከመተርጎም ጋር በተያያዘ በጣም ሰፊና ከባድ የሆነ ሥራ ተደቅኖባቸዋል። በአንድ ግምታዊ መረጃ መሠረት “በአሁኑ ጊዜ ካሉት የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉ አሥር ጽሑፎች መካከል በዘመናችን አንድ ጊዜ እንኳ የተነበበው አንዱ ብቻ ነው።”

በሁለት ወይም በሦስት ቋንቋዎች የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉ ጽሑፎች መገኘታቸው በዚህ የአጻጻፍ ስልት የተጻፉትን ጽሑፎች ለመተርጎም ትልቅ እገዛ አድርጓል። ምሑራን የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉት እነዚህ መዛግብት በተለያዩ ቋንቋዎች ቢጻፉም ሁሉም የያዙት ጽሑፍ አንድ ዓይነት መሆኑን ማስተዋል ቻሉ። እነዚህ ምሑራን በተለያዩ ቋንቋዎች በተዘጋጁ ጽሑፎች ላይ የተጠቀሱት ስሞችና ማዕረጎች እንዲሁም የገዢዎች የዘር ሐረጎች አልፎ ተርፎም ራሳቸውን ለማወደስ የተጠቀሙባቸው አገላለጾች አብዛኛውን ጊዜ አንድ ዓይነት እንደሆኑ ማወቃቸው እነዚህን ቋንቋዎች ለመተርጎም ረድቷቸዋል።

በ1850ዎቹ ዓመታት ምሑራን፣ በጥንቱ መካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩ ሰዎች የሚግባቡበት የአካድ ቋንቋ በሚጠቀምባቸው የሽብልቅ ቅርጽ ያላቸው ምልክቶች የተጻፉ ጽሑፎችን ማንበብ ቻሉ። ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “የአካድን ቋንቋ መተርጎም ሲቻል [የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች] የተጻፉ ጽሑፎችን የአጻጻፍ ስልት መረዳት ተቻለ፤ በዚህ ስልት በመጠቀም የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉ ሌሎች ቋንቋዎችን መተርጎም ቻሉ።” እነዚህ ጽሑፎች ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው?

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ ማስረጃ

ኢየሩሳሌም በ1070 ከክርስቶስ ልደት በፊት አካባቢ በዳዊት ድል እስከተደረገችበት ጊዜ ድረስ በከነዓናውያን ነገሥታት ትተዳደር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ኢያሱ 10:1፤ 2 ሳሙ. 5:4-9) ሆኖም አንዳንድ ምሑራን የዚህን ዘገባ እውነተኝነት ይጠራጠራሉ። በ1887 በግብርና ሙያ የምትተዳደር አንዲት ሴት ከሸክላ የተሠራ አንድ ጽላት በአማርና፣ ግብጽ አገኘች። በዚህ ጽላት ላይ የሰፈሩት 380 የሚሆኑ ጽሑፎች ሲተረጎሙ ጽላቱ፣ የግብጽ ገዢዎች (አሜንሆቴፕ ሣልሳዊና አከናተን) እና የከነዓናውያን መንግሥታት የተጻጻፏቸውን ዲፕሎማሲያዊ ደብዳቤዎች የያዘ መሆኑ ታወቀ። ከእነዚህ ደብዳቤዎች መካከል ስድስቱን የጻፈው የኢየሩሳሌም ገዢ የነበረው አብዳይ ሄባ ነበር።

ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል፦ “በአማርና በተገኘው ጽላት ላይ ኢየሩሳሌም ይዞታ ሳትሆን ከተማ እንደሆነች ተደርጎ በግልጽ መጠቀሱ እንዲሁም አብዳይ ሄባ በኢየሩሳሌም መኖሪያ ቤትና 50 ግብጻውያን ወታደሮች ያሉት . . . ገዢ እንደሆነ መገለጹ ኢየሩሳሌም ኮረብታማ ቦታ ላይ የምትገኝ አነስተኛ አገር እንደሆነች ይጠቁማል።” ይኸው መጽሔት አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “በአማርና በተገኙት ደብዳቤዎች ላይ የሰፈረው ሐሳብ፣ [ኢየሩሳሌም] በወቅቱ ከነበሩት ከተሞች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጣት ከተማ እንደነበረች እርግጠኞች ለመሆን ያስችለናል።”

በአሦራውያንና በባቢሎናውያን መዛግብት ውስጥ የሚገኙ ስሞች

አሦራውያን፣ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ባቢሎናውያን በሸክላ ጽላቶች፣ ሞላላ ቅርጽ ባላቸው ድንጋዮች፣ በሐውልቶችና በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ታሪካቸውን ይጽፉ ነበር። በመሆኑም ምሑራን በአካድ ቋንቋ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉ ጽሑፎችን ሲተረጉሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም የተጠቀሱ ስሞችን አገኙ።

ዘ ባይብል ኢን ዘ ብሪቲሽ ሙዚየም የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ዶክተር ሳሙኤል በርች፣ አዲስ ለተቋቋመው ሶሳይቲ ኦቭ ቢብሊካል አርኪኦሎጂ የተባለ ማኅበር በ1870 ባቀረቡት ንግግር ላይ [የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች ከተጻፉት ጽሑፎች ውስጥ] የዕብራውያን ነገሥታት የሆኑትን ዖምሪ፣ አክዓብ፣ ኢዩ፣ ዓዛርያስ . . . ምናሔም፣ ፋቁሔ፣ ሆሴዕ፣ ሕዝቅያስና ምናሴ እንዲሁም የአሦር ነገሥታት የሆኑትን ቴልጌልቴልፌልሶር . . . [ሣልሳዊ]፣ ሳርጎን፣ ሰናክሬም፣ ኢሳር ሃዶን እና አሹርባናፓል፣ . . . በተጨማሪም ቤንሄዳድ፣ አዛሄልና ረአሶን የተባሉትን የሶርያውያን ነገሥታት ስሞች እንዳገኙ ገልጸው ነበር።”

ዘ ባይብል ኤንድ ራዲዮካርበን ዴቲንግ በተባለው መጽሐፍ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የእስራኤልና የይሁዳ ታሪክ፣ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች ከተጻፉ ጥንታዊ ጽሑፎች ጋር ተወዳድሯል። ውጤቱ ምን ሆነ? “በአጠቃላይ 15 ወይም 16 የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት በዚያ ዘመን በነበሩ ሌሎች አገሮች መዛግብት ውስጥ ተጠቅሰዋል፤ በእነዚህ መዛግብት ውስጥ የሰፈረው የነገሥታቱ ስምና የኖሩበት ዘመን [የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በአንደኛና በሁለተኛ] ነገሥት ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል። በአንደኛና በሁለተኛ ነገሥት ውስጥ ተጠቅሶ በእነዚህ መዛግብት ላይ ሳይጠቀስ የቀረ አንድም ንጉሥ የለም፤ እንዲሁም እነዚህ መዛግብት በአንደኛና በሁለተኛ ነገሥት ውስጥ ያልተጠቀሱ ነገሥታትን ስሞች አልያዙም።”

በ1879 በተገኘውና የቂሮስ ሲሊንደር በመባል በሚጠራው የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፈ ታዋቂ ጽሑፍ ላይ እንደተመዘገበው ቂሮስ በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎንን ከተቆጣጠረ በኋላ ቀደም ሲል ባወጣው ፖሊሲ መሠረት ምርኮኞቹን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቅዶላቸዋል። በዚህ ፖሊሲ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አይሁዳውያንም ይገኙበታል። (ዕዝራ 1:1-4) በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩ በርካታ ምሑራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው አዋጅ እውነተኛ መሆኑን ይጠራጠሩ ነበር። ይሁን እንጂ የቂሮስን ሲሊንደር ጨምሮ ፋርስ ኃያል በነበረችበት ዘመን የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉ መረጃዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ትክክል ስለመሆኑ አሳማኝ ማስረጃ ይሰጣሉ።

በ1883 በባቢሎን አቅራቢያ ባለችው በኒፑር፣ የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች የተጻፉ ከ700 በላይ ጽሑፎችን የያዘ መዝገብ ተገኘ። በዚህ መዝገብ ላይ ከተጠቀሱት 2,500 ስሞች መካከል 70 ያህሉ የአይሁዳውያን ስሞች ናቸው። ኤድዊን ያማዉቺ የተባሉት የታሪክ ምሑር እንደገለጹት “የአይሁዳውያኑ ስም በውሎች ላይ ተገኝቷል፤ ምሥክሮችም ሆነው ተጠቅሰዋል። በተጨማሪም ወኪሎች፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና የንጉሡ ባለሥልጣናት ሆነው ይሠሩ ነበር።” አይሁዳውያን በዚያ ዘመን በባቢሎን አቅራቢያ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች ማድረጋቸውን ቀጥለው እንደነበር የሚጠቁመው ማስረጃ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ ሐሳብ “የተረፉት” እስራኤላውያን ከአሦርና ከባቢሎን ግዞት ወደ ይሁዳ ሲመለሱ አብዛኞቹ እዚያው እንደቀሩ ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ይስማማል።—ኢሳ. 10:21, 22

ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበረው አንድ ሺህ ዓመት ውስጥ ሰዎች የሽብልቅ ቅርጽ ካላቸው ምልክቶች በተጨማሪ በሌሎች ፊደላትም ይጠቀሙ ነበር። ውሎ አድሮ ግን አሦራውያንና ባቢሎናውያን የሽብልቅ ቅርጽ ባላቸው ምልክቶች መጠቀማቸውን በመተው በፊደላት መጻፍ ጀመሩ።

በአሁኑ ጊዜ ገና ጥናት ያልተደረገባቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጽላቶች በሙዚየሞች ውስጥ ይገኛሉ። ባለሞያዎች እስካሁን የተረጎሟቸው ጽላቶች መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መጽሐፍ ለመሆኑ አሳማኝ ማስረጃ ሰጥተዋል። ገና ጥናት ያልተደረገባቸው ጽሑፎች ደግሞ ምን ዓይነት ተጨማሪ ማስረጃ እንደሚሰጡ ማን ያውቃል?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum