“መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ”
“መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ”
የኤሚልያ ፒደርሰን ታሪክ
ሩት ፓፓስ እንደተናገረችው
እናቴ ኤሚልያ ፒደርሰን የተወለደችው በ1878 ነበር። በመምህርነት ሙያ ላይ የተሰማራች ቢሆንም ትመኝ የነበረው ግን ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለመርዳት ነበር። በሚኒሶታ፣ ዩ ኤስ ኤ በምትገኘው ጃስፐር የተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ ባለው ቤታችን ውስጥ የተቀመጠው ትልቅ ሻንጣ እናቴ እንዲህ ያለ ፍላጎት እንደነበራት የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ሻንጣውን የገዛችው ዕቃዎቿን ጭና ወደ ቻይና በመሄድ ሚስዮናዊ ሆና ማገልገል ትፈልግ ስለነበር ነው። ሆኖም እናቷ ስትሞት ታናናሾቿን መንከባከብ ስለነበረባት እቅዷን ለመሰረዝ ተገደደች። በ1907 ቴዎዶር ሆሊን የተባለ ሰው አገባች። እኔ የተወለድኩት ታኅሣሥ 2, 1925 ሲሆን ወላጆቼ ካፈሯቸው ሰባት ልጆች የመጨረሻዋ ነኝ።
እናቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጥያቄዎች የነበሯት ሲሆን መልስ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ታደርግ ነበር። ጥያቄ ከፈጠሩባት ነገሮች አንዱ ሲኦል ክፉዎች የሚቀጡበት እሳታማ ሥፍራ እንደሆነ የሚገልጸው ትምህርት ነበር። በሉተራን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያለውን አንድ ቄስ ይህንን ትምህርት የሚደግፈው የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሆነ ጠየቀችው። ቄሱም መጽሐፍ ቅዱስ ምንም አለ ምን፣ ክፉዎች የሚቃጠሉበት እሳታማ ሲኦል እንዳለ ማስተማር አስፈላጊ መሆኑን የሚጠቁም ምላሽ ሰጣት።
እውነትን ለማወቅ የነበራትን ጥማት ማርካት ቻለች
በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የእናቴ እህት የሆነችው ኤማ ሙዚቃ ለመማር ወደ ኖርዝፊልድ፣ ሚኒሶታ ሄደች። አክስቴ ያረፈችው ሚልዩስ ክሪስቺያንሰን የተባለ አስተማሪዋ ዘንድ ሲሆን የዚህ ሰው ባለቤት በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ከሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች አንዷ ነበረች። ኤማም መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በጣም የምትወድ እህት እንዳለቻት ነገረቻቸው። ብዙም ሳይቆይ ሚስዝ ክሪስቺያንሰን ለእናቴ ደብዳቤ በመጻፍ ለጥያቄዎቿ መልስ ሰጠቻት።
አንድ ቀን ሎራ ኦትሃውት የተባለች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ስትል ከሱዝ ፎልስ፣ ሳውዝ ዳኮታ ተነስታ በባቡር ወደ ጃስፐር መጣች። እማማ፣ ሎራ የሰጠቻትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች አጠናቻቸው። ከዚያም በ1915 እነዚህን ጽሑፎች በማሰራጨት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች መናገር ጀመረች።
በ1916 እማማ በሱዝ ሲቲ፣ አይዋ በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ቻርልስ ቴዝ ራስል እንደሚኖር ስትሰማ በስብሰባው ላይ ለመገኘት ፈለገች። እማማ በዚህ ወቅት አምስት ልጆች የነበሯት ሲሆን ማርቪን የተባለው ትንሹ ልጅ ገና አምስት ወሩ ነበር። ያም ቢሆን ሁሉንም ልጆቿን ይዛ 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኘው ወደ ሱዝ ሲቲ በባቡር በመጓዝ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ተገኘች። በስብሰባው ላይ ወንድም ራስል የሰጠውን ንግግር ያዳመጠች ከመሆኑም በላይ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ስላይድ ፊልም ተመለከተች፤ እናቴ የተጠመቀችውም በዚህ ስብሰባ ላይ ነበር። ወደ ቤቷ ስትመለስ ስብሰባውን አስመልክታ የጻፈችው ሐሳብ ጃስፐር ጆርናል በተባለው መጽሔት ላይ ወጥቶ ነበር።
በ1922 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኙት 18,000 የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች መካከል አንዷ እማማ ነበረች። ከዚያ ስብሰባ ወዲህ ስለ አምላክ ኢሳ. 30:21
መንግሥት ከማወጅ ወደኋላ ብላ አታውቅም። እሷ የተወችልን ምሳሌ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ እንድናደርግ ረድቶናል።—የመንግሥቱ አገልግሎት ያስገኘው ፍሬ
በ1920ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ወላጆቼ ከጃስፐር ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ መኖር ጀመሩ። አባባ ጥሩ ገቢ በሚያስገኝለት ሥራው የተጠመደ ከመሆኑም ሌላ ብዙ አባላት ያሉትን ቤተሰባችንን ማስተዳደር ነበረበት። አባባ የእናታችንን ያህል መጽሐፍ ቅዱስን ባያጠናም የስብከቱን ሥራ በሙሉ ልቡ ይደግፍ ነበር፤ እንዲሁም በወቅቱ ፒልግሪም ተብለው የሚጠሩት ተጓዥ አገልጋዮች ቤታችን እንዲያርፉ ያደርግ ነበር። ከእነዚህ ተጓዥ አገልጋዮች አንዱ በቤታችን ንግግር ሲሰጥ አብዛኛውን ጊዜ ወደ መቶ የሚጠጉ ሰዎች በሳሎናችን፣ በምግብ ቤታችን እንዲሁም በመኝታ ቤታችን ውስጥ ሆነው ንግግሩን ያዳምጡ ነበር።
የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ለቲ የተባለችው አክስቴ፣ ጎረቤቶቿ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደሚፈልጉ ለወላጆቼ በስልክ ነገረቻቸው። የአክስቴ ጎረቤቶች የሆኑት ኤድ ላርሰንና ባለቤቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በደስታ ተቀበሉ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ የስምንት ልጆች እናት የሆነችውን ማርታ ቫን ዳለን የተባለች ጎረቤታቸውን አብራቸው እንድታጠና ጋበዟት። ማርታና መላው ቤተሰቧም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሆኑ። *
በዚሁ ጊዜ አካባቢ ከእኛ ቤት ጥቂት ራቅ ብሎ የሚኖር ጎርደን ካመሩድ የተባለ አንድ ወጣት ከአባቴ ጋር መሥራት ጀመረ። አንዳንድ ሰዎች ለጎርደን “የአለቃህ ሴቶች ልጆች ለየት ያለ ሃይማኖት ስላላቸው ከእነሱ ጋር እንዳትቀራረብ ተጠንቀቅ” ብለውት ነበር። ያም ቢሆን ጎርደን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረ ሲሆን እውነትን እንዳገኘ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደበትም። ይህ ወጣት ከሦስት ወራት በኋላ የተጠመቀ ሲሆን ወላጆቹም እውነትን ተቀበሉ። የእኛ፣ የካመሩድና የቫን ዳለን ቤተሰብ እያደር የቅርብ ወዳጆች ሆንን።
የአውራጃ ስብሰባዎች አጠናክረውናል
እማማ በሴዳር ፖይንት የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ በጣም ስላበረታታት ከዚያ በኋላ አንድም የአውራጃ ስብሰባ እንዲያመልጣት አትፈልግም ነበር። ልጅ እያለሁ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ረጅም ርቀት እንጓዝ እንደነበር አስታውሳለሁ። በ1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፤ ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራት የጀመርነው በዚህ ወቅት ነበር። (ኢሳ. 43:10-12) በተጨማሪም በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጹት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ወይም “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ማንነት የተብራራበት ታሪካዊ ንግግር የቀረበበትን በ1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ የተደረገውን የአውራጃ ስብሰባ በደንብ አስታውሰዋለሁ። (ራእይ 7:9፤ የ1954 ትርጉም) በስብሰባው ላይ ከተጠመቁት ከ800 የሚበልጡ ሰዎች መካከል ሊሊያን እና ዩኒስ የተባሉት እህቶቼ ይገኙበታል።
ቤተሰባችን በ1937 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ እንዲሁም በ1938 በሲያትል፣ ዋሽንግተን በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ተገኝቷል፤ በ1939 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ደግሞ ወደ ኒው ዮርክ ሲቲ ተጉዘን ነበር። በእነዚህ ወቅቶች የቫን ዳለንና የካመሩድ ቤተሰቦች እንዲሁም ሌሎች ወንድሞች አብረውን የተጓዙ ሲሆን በመንገድ ላይ ድንኳን ተክለን እናድር ነበር። ዩኒስ እና ሊዮ ቫን ዳለን በ1940 ከተጋቡ በኋላ አቅኚዎች ሆነው ማገልገል ጀመሩ። በዚያው ዓመት ሊሊያን እና ጎርደን ካመሩድ የተጋቡ ሲሆን እነሱም አቅኚዎች ሆኑ።
በ1941 በሴይንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ የተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ለየት ያለ ነበር። በስብሰባው ላይ ልጆች የተባለ መጽሐፍ የወጣ ሲሆን ይህ መጽሐፍ በዚያ ለነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ትናንሽ ልጆች ተሰጣቸው። ይህ ስብሰባ በሕይወቴ ላይ ለውጥ እንዳደርግ አነሳስቶኛል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ መስከረም 1, 1941 እኔ፣ ወንድሜ ማርቪንና ባለቤቱ ጆይስ አቅኚዎች ሆንን፤ በወቅቱ 15 ዓመቴ ነበር።
የምንኖረው በግብርና በሚተዳደር ማኅበረሰብ ውስጥ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት በሚደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚችሉት ሁሉም ወንድሞች አልነበሩም። በመሆኑም ከአውራጃ ስብሰባዎቹ ስንመለስ በስብሰባው ላይ ያልተገኙት ወንድሞች ከትምህርቱ ጥቅም እንዲያገኙ ሲባል በእኛ ግቢ ተሰባስበን ፕሮግራሙን እንከልስ ነበር። እነዚያ ስብሰባዎች እንዴት የሚያስደስቱ ነበሩ!
ጊልያድና የሚስዮናዊነት አገልግሎት
አቅኚዎችን ለሚስዮናዊነት አገልግሎት ለማሠልጠን ሲባል የካቲት 1943 የጊልያድ ትምህርት ቤት ተከፈተ። በዚህ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ሥልጠና ካገኙት መካከል ስድስት የቫን ዳለን ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል፤ እነሱም ወንድማማቾቹ ኤሚል፣ አርተር፣ ሆመርና ሊዮ፣ የአክስታቸው ልጅ ዶናልድ እንዲሁም የሊዮ ሚስት የሆነችው እህቴ ዩኒስ ናቸው። ወደ ጊልያድ ከሄዱ በኋላ እንደገና የምናገኛቸው መቼ እንደሆነ ስላላወቅን የተሰናበትናቸው ደስታና ሐዘን በተቀላቀለበት ስሜት ነበር። ከጊልያድ ከተመረቁ በኋላ ስድስቱም ፖርቶ ሪኮ ተመደቡ፤ በወቅቱ በዚያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።
ከአንድ ዓመት በኋላ ሊሊያንና ጎርደን እንዲሁም ማርቪንና ጆይስ በጊልያድ ትምህርት ቤት በሦስተኛው ክፍል እንዲሠለጥኑ ተጋበዙ። እነሱም ከተመረቁ በኋላ ፖርቶ ሪኮ ተመደቡ። እኔ ደግሞ በመስከረም ወር 1944 በአሥራ ስምንት ዓመቴ በጊልያድ ትምህርት ቤት በአራተኛው ክፍል ሠለጠንኩ። የካቲት 1945 ከተመረቅኩ በኋላ ወንድሜና እህቶቼ በሚያገለግሉበት በፖርቶ ሪኮ ተመደብኩ። በዚያ በርካታ አዳዲስ ነገሮች አጋጥመውኛል። ስፓንኛ መማር ተፈታታኝ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ አንዳንዶቻችን ከ20 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ጀመርን። ይሖዋ ሥራችንን ባርኮታል። በአሁኑ ጊዜ በፖርቶ ሪኮ 25,000 የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ!
ቤተሰባችን ሐዘን ደረሰበት
ሊዮና ዩኒስ በ1950 ማርክ የተባለውን ልጃቸውን ከወለዱ በኋላም በፖርቶ ሪኮ መኖራቸውን ቀጥለው ነበር። በ1952 ወደ አገራቸው ተመልሰው ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ስላሰቡ ሚያዝያ 11 ከፖርቶ ሪኮ ተነሱ። የሚያሳዝነው አውሮፕላኑ ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ውቅያኖስ ላይ ተከሰከሰ። በዚህ አደጋ ሊዮና ዩኒስ ሞቱ፤ የሁለት ዓመት ልጃቸው ማርክ ግን አንድ ሰው ሕይወት አድን ጀልባ ላይ አስቀምጦት ስለነበር አልሰመጠም። ማርክ መተንፈስ እንዲችል እርዳታ ስለተደረገለት በሕይወት መትረፍ ቻለ። *
ይህ ከሆነ ከአምስት ዓመት በኋላ መጋቢት 7, 1957 እማማና አባባ ወደ መንግሥት አዳራሽ እየሄዱ ሳለ የመኪናቸው ጎማ ተነፈሰባቸው። አባባ የመንገዱ ዳር ላይ መኪናዋን አቁሞ ጎማ ሲቀይር የሚያልፍ መኪና ገጨውና ወዲያውኑ ሞተ። በቀብር ንግግሩ ላይ 600 የሚያህሉ ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህም በአካባቢው ለሚገኙ ሰዎች ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል፤ አባባ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተከበረ ሰው ነበር።
አዲስ የአገልግሎት ምድብ
አባባ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በአርጀንቲና እንዳገለግል ተመድቤ ነበር። ነሐሴ 1957 በአንዲስ ተራራዎች ግርጌ ወደምትገኘው ሜንዶዛ የተባለች ከተማ ደረስኩ። በጊልያድ ትምህርት ቤት በ30ኛው ክፍል ላይ የሠለጠነው ጆርጅ ፓፓስ በ1958 በአርጀንቲና እንዲያገለግል ተመደበ። እኔና ጆርጅ ወዳጅነት የመሠረትን ሲሆን ሚያዝያ 1960 ተጋባን።
በ1961 እማማ በ83 ዓመቷ አረፈች። እማማ በእውነት መንገድ ላይ በታማኝነት የተመላለሰች ሲሆን ሌሎች በርካታ ሰዎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ረድታለች።እኔና ጆርጅ ለአሥር ዓመታት ያህል ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር በተለያዩ ቦታዎች አገልግለናል። ከዚያም ለሰባት ዓመታት በወረዳ ሥራ ተካፍለናል። የታመሙ የቤተሰባችንን አባላት ለመንከባከብ ስንል በ1975 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። በ1980 ባለቤቴ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ በስፓንኛ የሚመሩ ጉባኤዎችን እንዲጎበኝ ተጋበዘ። በዚያን ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወደ 600 የሚጠጉ በስፓንኛ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎች ነበሩ። ለ26 ዓመታት ከእነዚህ ጉባኤዎች መካከል አብዛኞቹን ጎብኝተናል፤ የጉባኤዎቹም ቁጥር ከ3,000 በላይ ሲሆን ተመልክተናል።
‘በመንገዱ’ ሄደዋል
እማማ ሌሎች የቤተሰቧ አባላትም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ሲካፈሉ ተመልክታለች። ለምሳሌ ያህል፣ የታላቅ እህቴ የኤስተር ልጅ የሆነችው ካሮል በ1953 አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ካሮል፣ ዴኒስ ትረምቦር የተባለ ወንድም ካገባች በኋላም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈላቸውን ቀጥለዋል። ሎይስ የተባለችው ሌላዋ የኤስተር ልጅ ደግሞ ዌንድል ጄንሰንን አገባች። እነሱም በጊልያድ ትምህርት ቤት በ41ኛው ክፍል ሥልጠና የወሰዱ ሲሆን ለ15 ዓመታት በናይጄሪያ ሚስዮናውያን ሆነው አገልግለዋል። የሊዮ እህት ሩት ላ ሎንድ እና ባለቤቷ ከርቲስ፣ ወላጆቹን በአውሮፕላን አደጋ ያጣውን ማርክን አሳደጉት። ማርክና ባለቤቱ ላቮን ለዓመታት በአቅኚነት ያገለገሉ ከመሆኑም ሌላ አራት ልጆቻቸውን በእውነተኛው ‘መንገድ’ አሳድገዋል።—ኢሳ. 30:21
ከቤተሰቤ አባላት መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚገኘው ኦርሊን የተባለው ወንድሜ ብቻ ሲሆን እሱም በ90ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ይገኛል። ኦርሊን አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገለ ነው። እኔና ጆርጅም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በደስታ መካፈላችንን ቀጥለናል።
እማማ የተወችልን ቅርስ
እማማ ትልቅ ቦታ ከምትሰጣቸው ዕቃዎቿ መካከል ጠረጴዛዋን ወርሻለሁ። ጠረጴዛው አባቴ ለሠርጋቸው የሰጣት ስጦታ ነበር። በአንዱ መሳቢያ ውስጥ ደብዳቤዎችንና እሷ የጻፈቻቸውን ርዕሶች የያዙ ጋዜጦችን ያስቀመጠችበት ማስታወሻ ደብተር ይገኛል። እነዚህ ርዕሶች ስለ አምላክ መንግሥት ጥሩ ምሥክርነት የሰጡ ሲሆን አንዳንዶቹ የተጻፉት በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነበር። እማማ በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉት ልጆቿ የጻፉላትን ደብዳቤዎች በጣም ትወዳቸዋለች፤ እነዚህ ደብዳቤዎችም በጠረጴዛው መሳቢያ ውስጥ ይገኛሉ። ደብዳቤዎቹን ደጋግሜ ማንበብ በጣም ያስደስተኛል! እማማ ሁልጊዜም ቢሆን አዎንታዊ የሆኑ ሐሳቦችን የያዙ የሚያበረታቱ ደብዳቤዎችን ትጽፍልን ነበር። እማማ ሚስዮናዊ የመሆን ምኞቷ ባይሳካም ቅንዓቷ ከእሷ በኋላ ያሉት ትውልዶች በዚህ አገልግሎት እንዲካፈሉ አነሳስቷቸዋል። ምድር ገነት በምትሆንበት ጊዜ ከእማማና ከአባባ እንዲሁም ከሌሎቹ የቤተሰባችን አባላት ጋር የምገናኝበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ!—ራእይ 21:3, 4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.13 የኤሚል ቫን ዳለን የሕይወት ታሪክ በሰኔ 15, 1983 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 27-30 ላይ ይገኛል።
^ አን.24 የ1987 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ ገጽ 93ን ተመልከት።
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤሚልያ ፒደርሰን
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1916 እማማና አባባ (ማርቪንን አቅፎ)፤ ከታች ከግራ ወደ ቀኝ:- ኦርሊን፣ ኤስተር፣ ሊሊያን፣ ሚልድሬድ
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሊዮ እና ዩኒስ ከመሞታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1950 ከግራ ወደ ቀኝ (ከላይ):- ኤስተር፣ ሚልድሬድ፣ ሊሊያን፣ ዩኒስ፣ ሩት፤ (ከታች):- ኦርሊን፣ እማማ፣ አባባና ማርቪን
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ2001 ጆርጅ እና ሩት ፓፓስ በወረዳ ሥራ ላይ እያሉ