በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መጥተህ ተከታዬ ሁን’

‘መጥተህ ተከታዬ ሁን’

‘መጥተህ ተከታዬ ሁን’

“ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ፣ የራሱን የመከራ እንጨት በየዕለቱ ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።”—ሉቃስ 9:23

1, 2. (ሀ)ኢየሱስ ደግነት የተንጸባረቀበት ምን ግብዣ አቅርቧል? (ለ) ኢየሱስ ላቀረበው ግብዣ ምን ምላሽ ሰጥተሃል?

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ መገባደጃ አካባቢ በሰሜን ምሥራቅ ይሁዳ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በሚገኘው በፔሪያ ምሥራቹን እየሰበከ ነበር። በዚህ ወቅት፣ ባለጠጋ የሆነ አንድ ወጣት ወደ እሱ መጣና የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ እንደሚኖርበት ጠየቀው። ኢየሱስ፣ ይህ ወጣት የሙሴን ሕግ በጥብቅ እንደሚከተል ከተገነዘበ በኋላ አንድ ታላቅ ግብዣ አቀረበለት። “ሂድና ያለህን ነገር ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ስጥ፤ በሰማይም ውድ ሀብት ታገኛለህ፤ መጥተህም ተከታዬ ሁን” አለው። (ማር. 10:21) እስቲ አስበው፣ ይህ ሰው የልዑሉ አምላክ አንድያ ልጅ የሆነውን ኢየሱስን እንዲከተል ግብዣ ቀርቦለታል!

2 ይህ ወጣት የቀረበለትን ግብዣ ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆንም ሌሎች ግን የኢየሱስን ግብዣ ተቀብለውታል። ከዚያ ቀደም ኢየሱስ፣ ፊልጶስን “ተከታዬ ሁን” ብሎት ነበር። (ዮሐ. 1:43) ፊልጶስ ግብዣውን የተቀበለ ሲሆን ከጊዜ በኋላም የኢየሱስ ሐዋርያ ሆኗል። ኢየሱስ ይህንኑ ግብዣ ለማቴዎስ ያቀረበለት ሲሆን እሱም ግብዣውን ተቀብሏል። (ማቴ. 9:9፤ 10:2-4) ኢየሱስ “ሊከተለኝ የሚፈልግ ካለ ራሱን ይካድ፣ የራሱን የመከራ እንጨት በየዕለቱ ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ” በማለት ሲናገር ጽድቅን ለሚወዱ ሁሉ ተመሳሳይ ግብዣ ማቅረቡ ነበር። (ሉቃስ 9:23) በመሆኑም ማንኛውም ሰው የኢየሱስ ተከታይ መሆን ከፈለገ ይህን ማድረግ ይችላል። አንተስ የኢየሱስ ተከታይ የመሆን ፍላጎት አለህ? አብዛኞቻችን ኢየሱስ በደግነት ያቀረበውን ግብዣ የተቀበልን ከመሆኑም በላይ በመስክ አገልግሎት ለምናገኛቸው ሰዎች ተመሳሳይ ግብዣ እናቀርብላቸዋለን።

3. ኢየሱስን ከመከተል ቀስ በቀስ እየራቅን እንዳንሄድ ምን ማድረግ እንችላለን?

3 የሚያሳዝነው ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያሳዩ አንዳንድ ሰዎች በጥናታቸው አይቀጥሉም። እነዚህ ሰዎች ለእውነት ያላቸው ፍላጎት ይቀንስና ኢየሱስን ከመከተል ‘ቀስ በቀስ እየራቁ’ ይሄዳሉ። (ዕብ. 2:1) እኛስ እንደዚህ ባለው ወጥመድ እንዳንወድቅ ምን ማድረግ እንችላለን? እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው:- ‘መጀመሪያውኑም ኢየሱስን ለመከተል የመረጥኩት ለምን ነበር? ኢየሱስን መከተል ሲባልስ ምን ማለት ነው?’ ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች በምንሰጠው መልስ ላይ ማሰላሰላችን በመረጥነው ትክክለኛ ጎዳና ጸንተን ለመቀጠል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። ከዚህም በላይ ሌሎች ሰዎች ኢየሱስን እንዲከተሉ ለማበረታታት ያስችለናል።

ኢየሱስን የምንከተለው ለምንድን ነው?

4, 5. ኢየሱስ መሪ ለመሆን ብቃቱ አለው የምንለው ለምንድን ነው?

4 ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ።” (ኤር. 10:23) ኤርምያስ የተናገረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ታሪክ ያረጋግጣል። ፍጹም ያልሆኑ የሰው ልጆች ራሳቸውን ለመምራት የሚያደርጉት ሙከራ እንደማይሳካላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ኢየሱስ ከማንኛውም የሰው ዘር በተሻለ መሪያችን የመሆን ብቃት እንዳለው በመገንዘባችን እንድንከተለው ያቀረበልንን ግብዣ ተቀብለናል። ኢየሱስ ካሉት ብቃቶች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

5 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢየሱስን መሪ እንዲሆን የቀባው ይሖዋ ራሱ ነው። ለእኛ የሚበጀንን መሪ ከፈጣሪያችን በላይ ማን ሊያውቅ ይችላል? ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ልናደንቃቸውና ልንኮርጃቸው የምንችላቸው ግሩም ባሕርያት አሉት። (ኢሳይያስ 11:2, 3ን አንብብ።) ኢየሱስ ፍጹም የሆነ ምሳሌ ነው። (1 ጴጥ. 2:21) ሦስተኛ፣ ኢየሱስ እሱን ለሚከተሉ ሁሉ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት በጥልቅ እንደሚያስብላቸው አሳይቷል። (ዮሐንስ 10:14, 15ን አንብብ።) በአሁኑ ጊዜ ደስታ፣ ወደፊት ደግሞ አስደናቂ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ወደሚያስገኝልን የተሻለ ሕይወት በመምራት አሳቢ እረኛ መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐ. 10:10, 11፤ ራእይ 7:16, 17) በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ኢየሱስ እንድንከተለው ያቀረበልንን ግብዣ መቀበላችን ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ነው። ይሁን እንጂ ኢየሱስን መከተል ምን ነገሮችን ይጨምራል?

6. ኢየሱስን መከተል ምን ነገሮችን ይጨምራል?

6 የክርስቶስ ተከታይ መሆን ክርስቲያን ነኝ ብሎ ከመናገር ያለፈ ነገርን ይጨምራል። በዛሬው ጊዜ ወደ ሁለት ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ክርስቲያኖች እንደሆኑ ቢናገሩም ድርጊታቸው ግን “ዓመፀኞች” መሆናቸውን ያሳያል። (ማቴዎስ 7:21-23ን አንብብ።) ሰዎች ኢየሱስን እንዲከተሉ የቀረበላቸውን ግብዣ ለመቀበል ፍላጎት እንዳላቸው ስንመለከት፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች መላ አኗኗራቸውን ከኢየሱስ ትምህርቶችና እሱ ከተወው ምሳሌ ጋር ዘወትር ማስማማት እንደሚኖርባቸው እንገልጽላቸዋለን። ኢየሱስን መኮረጅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለመረዳት ስለ እሱ የምናውቃቸውን አንዳንድ ነገሮች እስቲ እንመልከት።

ጥበበኛ በመሆን ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ ኮርጅ

7, 8. (ሀ) ጥበብ ምንድን ነው? ኢየሱስ የላቀ ጥበብ ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ጥበበኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ እንዴት ልንኮርጀው እንችላለን?

7 ኢየሱስ ወደር የማይገኝላቸው በርካታ ባሕርያት አሉት፤ አሁን ግን በአራቱ ይኸውም በጥበቡ፣ በትሕትናው፣ በቅንዓቱና በፍቅሩ ላይ እናተኩራለን። በቅድሚያ ጥበቡን ማለትም እውቀትንና ማስተዋልን በተግባር የማዋል ችሎታውን እንመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስ “የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ በሚገባ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ውስጥ ነው” ሲል ጽፏል። (ቆላ. 2:3) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ጥበብ ያገኘው ከየት ነው? እሱ ራሱ “እነዚህን ነገሮች የምናገረው ልክ አብ እንዳስተማረኝ [ነው]” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 8:28) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ጥበብ ያገኘው ከይሖዋ በመሆኑ ባደረጋቸው ነገሮች ከፍተኛ የሆነ የማመዛዘን ችሎታ ማንጸባረቁ ሊያስደንቀን አይገባም።

8 ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ የሚከተለውን ጎዳና በመምረጥ ረገድ ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ አድርጓል። ኢየሱስ በአንድ ነገር ላይ ብቻ ማለትም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ በማተኮር ኑሮውን ቀላል ለማድረግ ወስኗል። ጊዜውንና ጉልበቱን ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወን በጥበብ ተጠቅሞባቸዋል። እኛም ‘አጥርቶ የሚያይ ዓይን’ እንዲኖረን ጥረት በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። እንዲህ ማድረጋችን ጉልበታችንን የሚያሟጥጡና ትኩረታችንን የሚሰርቁ አላስፈላጊ ነገሮችን በማድረግ በራሳችን ላይ ሸክም ከመጫን ይጠብቀናል። (ማቴ. 6:22) በርካታ ክርስቲያኖች በአገልግሎት የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል ለማድረግ የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች ወስደዋል። አንዳንዶች በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል ችለዋል። አንተም እንዲህ አድርገህ ከሆነ በጣም ልትመሰገን ይገባሃል። ‘አስቀድሞ የአምላክን መንግሥት መፈለግ’ ከፍተኛ ደስታና እርካታ ያስገኛል።—ማቴ. 6:33

እንደ ኢየሱስ ትሑት ሁን

9, 10. ኢየሱስ ትሑት መሆኑን ያሳየው እንዴት ነበር?

9 ከኢየሱስ ባሕርያት መካከል ቀጥለን የምንመለከተው ደግሞ ትሕትናውን ነው። ብዙውን ጊዜ፣ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ሥልጣን ሲሰጣቸው ራሳቸውን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። ኢየሱስ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ አመለካከት አለው! በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ቁልፍ የሆነ ቦታ ቢኖረውም ቅንጣት ታክል የኩራት መንፈስ አልታየበትም። እኛም በዚህ ረገድ የተወውን ምሳሌ እንድንኮርጅ ተበረታትተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር፤ እሱ በአምላክ መልክ ይኖር የነበረ ቢሆንም ከአምላክ ጋር እኩል መሆንን ነጥቆ ሊወስደው እንደሚገባ ነገር አድርጎ አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ራሱን ባዶ አደረገ፤ እንደ ባሪያ ሆኖም በሰው አምሳል መጣ።” (ፊልጵ. 2:5-7) ኢየሱስ ይህን ለማድረግ ምን ጠይቆበት ነበር?

10 ኢየሱስ በሰማይ ከአባቱ ጋር የመኖር አስደናቂ መብት የነበረው ቢሆንም በፈቃደኝነት “ራሱን ባዶ [አድርጓል]።” የኢየሱስ ሕይወት ወደ አንዲት አይሁዳዊት ድንግል ማሕጸን ተዛወረ፤ ከዚያም በማርያም ማሕጸን ውስጥ ለዘጠኝ ወራት ከቆየ በኋላ በአናጢነት በሚተዳደር ምስኪን ቤተሰብ ውስጥ ተወለደ። በዚህ ወቅት ኢየሱስ የሌሎች እንክብካቤ የሚያስፈልገው ሕጻን ነበር። ከዚያም በዮሴፍ ቤት ውስጥ ድክ ድክ ማለት ጀመረ፤ ቀስ በቀስም እያደገ ሄደና ወጣት ሆነ። ኢየሱስ ፍጹም ሰው ቢሆንም ኃጢአተኞች ለነበሩት ሰብዓዊ ወላጆቹ በወጣትነት ዕድሜው በሙሉ ታዝዟል። (ሉቃስ 2:51, 52) ኢየሱስ እንዴት ያለ የሚያስደንቅ ትሕትና አሳይቷል!

11. የኢየሱስን ትሕትና መኮረጅ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

11 እኛም ዝቅተኛ እንደሆነ ተደርጎ የሚታይ ሥራ ሲሰጠን ለመሥራት ፈቃደኞች በመሆን የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። ምሥራቹን የመስበክ ሥራችንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በተለይ ሰዎች ግዴለሽና ፌዘኛ በሚሆኑበት አሊያም ለእኛ ጥላቻ በሚኖራቸው ጊዜ የመስበክ ተልዕኳችን እንደ ዝቅተኛ ሥራ ይታይ ይሆናል። ይሁን እንጂ በስብከቱ ሥራ ስንጸና ሰዎች ኢየሱስን እንዲከተሉ የቀረበላቸውን ግብዣ እንዲቀበሉ እንረዳቸዋለን። ግብዣውን መቀበላቸው ደግሞ ለመዳን ያስችላቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 4:1-5ን አንብብ።) ሌላው ምሳሌ ደግሞ የመንግሥት አዳራሻችንን ንጽሕና መጠበቅና የተለያዩ የጥገና ሥራዎችን ማከናወን ነው። ይህም ቆሻሻ እንደ መድፋት፣ ወለል እንደ መወልወልና መጸዳጃ ቤቶችን እንደ ማጽዳት ያሉ ሥራዎችን ማከናወንን ይጨምራል፤ እነዚህ ሁሉ በሰዎች ዘንድ ዝቅተኛ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎች ናቸው! ያም ቢሆን በአካባቢያችን የንጹሕ አምልኮ ማዕከል የሆነውን የመንግሥት አዳራሻችንን ንጽሕና መጠበቅና የተለያዩ የጥገና ሥራዎችን ማከናወን የቅዱስ አገልግሎታችን ክፍል እንደሆነ እንገነዘባለን። ዝቅተኛ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን በፈቃደኝነት በመሥራት ትሑት መሆናችንን የምናሳይ ከመሆኑም ሌላ የክርስቶስን ፈለግ እንከተላለን።

የኢየሱስ ዓይነት ቅንዓት ይኑርህ

12, 13. (ሀ) ኢየሱስ በአገልግሎቱ ቅንዓት ያሳየው እንዴት ነው? እንዲህ እንዲያደርግ ያነሳሳውስ ምን ነበር? (ለ)  እኛም በአገልግሎታችን በቅንዓት እንድንካፈል ምን ሊያነሳሳን ይችላል?

12 ኢየሱስ በአገልግሎቱ ያሳየውን ቅንዓት ደግሞ እንመልከት። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ብዙ ነገሮችን አከናውኗል። በወጣትነት ዕድሜው ከአሳዳጊ አባቱ ከዮሴፍ ጋር አናጺ ሆኖ ሳይሠራ አልቀረም። በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ዓመታት ሕመምተኞችን መፈወስንና ሙታንን ማስነሳትን ጨምሮ በርካታ ተአምራትን ፈጽሟል። ዋነኛ ሥራው ግን ምሥራቹን መስበክና ለመስማት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ማስተማር ነበር። (ማቴ. 4:23) እኛም ተከታዮቹ እንደመሆናችን መጠን ተመሳሳይ ሥራ ተሰጥቶናል። ታዲያ ይህን ሥራ ስናከናውን ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ፣ ኢየሱስ ይህንን ሥራ እንዲያከናውን ያነሳሳውን ዝንባሌ በመኮረጅ ነው።

13 ኢየሱስ እንዲሰብክና እንዲያስተምር ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ለአምላክ ያለው ፍቅር ነው። በተጨማሪም የሚያስተምረውን እውነት ይወደው ነበር። ይህንን እውነት በዋጋ ሊተመን እንደማይችል ውድ ሀብት አድርጎ ይመለከተው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለሰዎች የማካፈል ጉጉት ነበረው። እኛም “የሕዝብ አስተማሪዎች” እንደመሆናችን መጠን ተመሳሳይ ስሜት አለን። ከአምላክ ቃል የተማርናቸውን አንዳንድ ውድ እውነቶች እስቲ አስብ! ከአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ጥያቄ እንዲሁም ይህ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ እናውቃለን። ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩት በረከቶች ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን ትምህርት በሚገባ እናውቃለን። እንደነዚህ ያሉትን እውነቶች የተማርነው በቅርቡም ይሁን ከረጅም ዓመታት በፊት እነዚህ እውነቶች አሁንም ውድ ናቸው። እነዚህ እውነቶች አሮጌም ሆኑ አዲስ በዋጋ ሊተመን የማይችል ውድ ሀብት ናቸው። (ማቴዎስ 13:52ን አንብብ።) ከልብ በመነጨ ስሜት በመስበክ ሌሎችም እንደ እኛ ይሖዋ ላስተማረን ነገሮች ፍቅር እንዲያድርባቸው እናደርጋለን።

14. ኢየሱስ ያስተማረበትን መንገድ መኮረጅ የምንችለው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ እንዴት እንዳስተማረም ልብ በል። በተደጋጋሚ ጊዜ ከቅዱሳን መጻሕፍት በመጥቀስ አድማጮቹ በአምላክ ቃል ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓል። አንድ አስፈላጊ ነጥብ ሲናገር ብዙውን ጊዜ “ተብሎ ተጽፏል” በማለት ይደመድም ነበር። (ማቴ. 4:4፤ 21:13) በጽሑፍ ከሰፈሩት ኢየሱስ የተናገራቸው ሐሳቦች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተጠቀሱ ናቸው። እኛም እንደ ኢየሱስ በአገልግሎት ስንካፈል ምንጊዜም ቢሆን ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሰን የምናስተምር ከመሆኑም በላይ ሁኔታው አመቺ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን አውጥተን ለማንበብ እንጥራለን። በዚህ መንገድ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የራሳችንን ሳይሆን የአምላክን ሐሳቦች እንደምናስተምር እንዲገነዘቡ እንረዳቸዋለን። አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን አውጥተን እንድናነብለት እንዲሁም የአምላክ ቃል ስላለው ጥቅምና ትርጉም እንድናወያየው ፈቃደኛ ሲሆን እንዴት ያስደስታል! እንዲህ ያለው ሰው ኢየሱስን እንዲከተል የቀረበለትን ግብዣ ሲቀበል ደግሞ ደስታችን ወደር አይኖረውም።

ኢየሱስን መከተል ሌሎችን መውደድን ይጨምራል

15. ኢየሱስ ካሉት ባሕርያት ሁሉ የላቀው የትኛው ነው? በዚህ ባሕርይ ላይ ማሰላሰላችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል?

15 በመጨረሻ የምንወያይበት የኢየሱስ ባሕርይ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ሲሆን ይህም ከባሕርያቱ ሁሉ ይበልጥ ልብ የሚነካ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮ. 5:14) ኢየሱስ ለመላው የሰው ዘርና በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዳችን ስላለው ፍቅር ስናስብ ልባችን ስለሚነካ የእሱን አርዓያ ለመከተል እንገፋፋለን።

16, 17. ኢየሱስ ለሌሎች ያለውን ፍቅር ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

16 ኢየሱስ ለሌሎች ፍቅር እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? ለሰው ዘር ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ በመሆን ፈጽሞ ተወዳዳሪ የሌለው ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። (ዮሐ. 15:13) ይሁን እንጂ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት በሌሎች መንገዶችም ፍቅሩን አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በሰዎች ላይ የደረሰው ችግር በራሱ ላይ እንደደረሰ ያህል ሆኖ ይሰማው ነበር። ማርያምና አብረዋት የነበሩት ሰዎች በአልዓዛር ሞት ምክንያት ሲያለቅሱ በተመለከተ ጊዜ ሐዘናቸው በጥልቅ ተሰምቶት ነበር። ኢየሱስ አልዓዛርን እንደሚያስነሳው ቢያውቅም በጣም ከመረበሹ የተነሳ ‘እንባውን አፍስሷል።’—ዮሐ. 11:32-35

17 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት፣ የሥጋ ደዌ በሽታ የነበረበት አንድ ሰው ወደ እሱ ቀርቦ “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎት ነበር። ኢየሱስ ምን ተሰማው? ዘገባው “በጣም አዘነለት” በማለት ይናገራል። ቀጥሎም አስደናቂ የሆነ ነገር እንዳደረገለት ይገልጻል። “እጁን ዘርግቶ ዳሰሰው፤ ከዚያም ‘እፈልጋለሁ፣ ንጻ’ አለው። ወዲያውም የሥጋ ደዌው ለቀቀውና ነጻ።” በሙሴ ሕግ መሠረት የሥጋ ደዌ ያለባቸው ሰዎች ርኩስ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ይህን ሰው መንካት ሳያስፈልገው ሊፈውሰው ይችል ነበር። ይሁንና ኢየሱስ፣ ግለሰቡ ሌላ ሰው ሲነካው የሚፈጠርበትን ልዩ ስሜት ግምት ውስጥ በማስገባት በእጁ ዳስሶታል፤ ምናልባትም ይህ ሰው ሌሎች ሳይነኩት በርካታ ዓመታት አልፈው ሊሆን ይችላል። እንዴት ያለ ታላቅ ርኅራኄ ነው!—ማር. 1:40-42

18. ‘የሌላውን ስሜት እንደምንረዳ’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 እኛም የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ‘የሌላውን ስሜት በመረዳት’ ፍቅራችንን እንድናሳይ ተመክረናል። (1 ጴጥ. 3:8) ሥር የሰደደ ሕመም ወይም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት የሚያሠቃየውን የእምነት ባልንጀራችንን ስሜት መረዳት ቀላል ላይሆን ይችላል፤ በተለይ ደግሞ እንዲህ ያሉት ነገሮች ደርሰውብን የማያውቁ ከሆነ የዚህን ሰው ስሜት መረዳት ሊከብደን ይችላል። ኢየሱስ ታሞ የማያውቅ ቢሆንም የታመሙ ሰዎች ሥቃይ ይሰማው ነበር። እኛስ እንዲህ ያለ ባሕርይ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? መከራ የደረሰባቸው ሰዎች የልባቸውን አውጥተው ሲነግሩን በትዕግሥት በማዳመጥ ነው። በተጨማሪም ‘እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን ይሰማኝ ነበር?’ እያልን ራሳችንን እንጠይቅ። የሌሎችን ስሜት የምንረዳ ከሆነ “የተጨነቁትን ነፍሳት” በተሻለ ሁኔታ ‘ማጽናናት’ እንችላለን። (1 ተሰ. 5:14) በዚህ መንገድ የኢየሱስን ፈለግ እንከተላለን።

19. ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

19 ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች በማጥናት እንዴት ያለ አስደናቂ ትምህርት አግኝተናል! ስለ እሱ ይበልጥ ባወቅን መጠን እሱን የመምሰል ከፍተኛ ፍላጎት ያድርብናል፤ በዚያው መጠን ደግሞ ሌሎች ሰዎች እሱን እንዲመስሉ ለመርዳት እንገፋፋለን። እንግዲያው አሁንም ሆነ ለዘላለም መሲሐዊውን ንጉሥ በመከተል እንደሰት!

ልታብራራ ትችላለህ?

• እንደ ኢየሱስ ጥበበኛ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• ትሕትናን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• በአገልግሎታችን በቅንዓት እንድንካፈል ምን ሊያነሳሳን ይችላል?

• ለሌሎች ፍቅር በማሳየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ክርስቶስን ለመምሰል የሚረዳን መጽሐፍ

በ2007 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ‘መጥተህ ተከታዬ ሁን ’ የተባለ ባለ 192 ገጽ መጽሐፍ ወጥቶ ነበር። ይህ መጽሐፍ ክርስቲያኖች በኢየሱስ በተለይም በባሕርያቱና ባደረጋቸው ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች የመግቢያ ሐሳቦችን ይዘዋል፤ ከዚያም ክፍል አንድ ስለ ኢየሱስ ዋና ዋና ባሕርያት ይኸውም ስለ ትሕትናው፣ ስለ ድፍረቱ፣ ስለ ጥበቡ፣ ስለ ታዛዥነቱና ስለ ጽናቱ ያብራራል።

ቀጥሎም፣ ኢየሱስ የምሥራቹ አስተማሪና ሰባኪ በመሆን ስላከናወናቸው ነገሮች እንዲሁም ታላቅ ፍቅሩን ስላሳየባቸው አንዳንድ መንገዶች የሚያብራሩ ክፍሎች አሉ። በመጽሐፉ ውስጥ የቀረቡት ሐሳቦች ክርስቲያኖች ኢየሱስን እንዲመስሉ ለመርዳት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው።

ይህ መጽሐፍ ሁላችንም ‘በእርግጥ ኢየሱስን እየተከተልኩት ነው? ከበፊቱ ይበልጥ በጥብቅ ልከተለው የምችለው እንዴት ነው?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን እያነሳን ራሳችንን እንድንመረምር እንደሚገፋፋን እምነት አለን። ከዚህም በተጨማሪ “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሁሉ የኢየሱስ ተከታዮች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።—ሥራ 13:48

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ወደ ምድር መጥቶ ሰው ሆኖ ለመወለድ ፈቃደኛ ሆኗል። እንዲህ ለማድረግ የትኛው ባሕርይ አስፈልጎት ነበር?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአገልግሎታችን በቅንዓት እንድንካፈል ምን ሊያነሳሳን ይችላል?