በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ስለ መተላለፋችን የተወጋው’ የይሖዋ አገልጋይ

‘ስለ መተላለፋችን የተወጋው’ የይሖዋ አገልጋይ

‘ስለ መተላለፋችን የተወጋው’ የይሖዋ አገልጋይ

“እርሱ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ . . . በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።”—ኢሳ. 53:5

1. የመታሰቢያውን በዓል በምናከብርበት ወቅት የትኞቹን ነገሮች ልናስታውስ ይገባል? ይህን ለማድረግ የሚረዳን የትኛው ትንቢት ነው?

የመታሰቢያውን በዓል የምናከብረው የክርስቶስን ሞት እንዲሁም የእሱ ሞትና ትንሣኤው ያስገኛቸውን ነገሮች ሁሉ ለማስታወስ ነው። የመታሰቢያው በዓል ስለ ይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥ፣ ስለ ስሙ መቀደስ እንዲሁም የሰው ልጆችን መዳን ስለሚጨምረው የአምላክ ዓላማ መፈጸም እንድናስብ ያደርገናል። ክርስቶስ መሥዋዕት ስለ መሆኑ እንዲሁም መሥዋዕቱ ስላከናወነው ነገር፣ በ⁠ኢሳይያስ 53:3-12 ላይ ከተነገረው ትንቢት በተሻለ የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የለም ማለት ይቻላል። ኢሳይያስ፣ የአምላክ አገልጋይ ስለሚደርስበት ሥቃይ አስቀድሞ የተነበየ ከመሆኑም ሌላ ስለ ክርስቶስ አሟሟት እንዲሁም ሞቱ ለቅቡዓን ወንድሞቹና ‘ለሌሎቹ በጎቹ’ ስለሚያስገኛቸው በረከቶች በዝርዝር ተናግሯል።—ዮሐ. 10:16

2. ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት ምን ይጠቁማል? ይህን ትንቢት መመርመራችንስ ምን ጥቅም አለው?

2 ይሖዋ፣ የመረጠው አገልጋዩ እስከ ሞት ድረስ ቢፈተንም በታማኝነት እንደሚጸና ኢየሱስ ከመወለዱ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት በኢሳይያስ በኩል ትንቢት አስነግሮ ነበር። ይሖዋ እንዲህ ያለ ትንቢት ማስነገሩ ልጁ በታማኝነት እንደሚጸና ሙሉ በሙሉ እንደሚተማመን ይጠቁማል። ኢሳይያስ የተናገረውን ትንቢት መመርመራችን ልባችን በአመስጋኝነት መንፈስ እንዲሞላና እምነታችን እንዲጠናከር ያደርጋል።

“የተናቀ” እና ‘ያልተከበረ’ አገልጋይ

3. አይሁዳውያን ኢየሱስን ሊቀበሉት ይገባ ነበር የምንለው ለምንድን ነው? እነሱ ግን ምን አደረጉ?

3 ኢሳይያስ 53:3ን አንብብ። የአምላክ አንድያ ልጅ በአባቱ ዘንድ ሆኖ ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ ትቶ ሕይወቱን ቤዛ በማድረግ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል ወደ ምድር መምጣት ምን ያህል ትልቅ መሥዋዕትነት እንደጠየቀበት እስቲ አስበው! (ፊልጵ. 2:5-8) በሙሴ ሕግ ሥር ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች ጥላ የሆኑለት የክርስቶስ መሥዋዕት ለሰው ልጆች ኃጢአት እውነተኛ ስርየት ያስገኛል። (ዕብ. 10:1-4) ከዚህ አንጻር በተለይ አይሁዳውያን ኢየሱስን ሊቀበሉትና ሊያከብሩት ይገባ ነበር፤ ምክንያቱም እነዚህ ሕዝቦች ተስፋ የተደረገበትን መሲሕ ይጠባበቁ ነበር። (ዮሐ. 6:14) አይሁዳውያን ግን ኢሳይያስ እንደተነበየው ክርስቶስን ‘የናቁት’ ከመሆኑም ሌላ ‘አላከበሩትም’ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ “ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ነገር ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም” በማለት ጽፏል። (ዮሐ. 1:11) ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአይሁዳውያን እንደሚከተለው ብሏቸዋል:- “የአባቶቻችን አምላክ . . . እናንተ አሳልፋችሁ የሰጣችሁትንና ጲላጦስ ሊፈታው ወስኖ ሳለ በጲላጦስ ፊት የካዳችሁትን አገልጋዩን ኢየሱስን አከበረው። አዎ፣ እናንተ ይህን ቅዱስና ጻድቅ ሰው [ካዳችሁት]።”—ሥራ 3:13, 14

4. ኢየሱስ ደዌን ያውቅ የነበረው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ “ሥቃይ ያልተለየው [‘ደዌን የሚያውቅ፣’ የ1954 ትርጉም]” እንደሚሆንም ኢሳይያስ ተንብዮ ነበር። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን ድካም ተሰምቶት የነበረ ቢሆንም ታሞ እንደሚያውቅ የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም። (ዮሐ. 4:6) ይሁን እንጂ የሰበከላቸውን ሰዎች ሕመም ያውቅ ነበር። ለእነዚህ ሰዎች ያዘነላቸው ከመሆኑም ሌላ ብዙዎቹን ፈውሷቸዋል። (ማር. 1:32-34) በዚህ መንገድ ኢየሱስ “በእርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ” የሚለውን ትንቢት ፈጽሟል።—ኢሳ. 53:4ሀ፤ ማቴ. 8:16, 17

‘በአምላክ እንደ ተመታ’

5. አብዛኞቹ አይሁዳውያን ኢየሱስ የሞተበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር? ይህስ በኢየሱስ ላይ ተጨማሪ ሥቃይ ያስከተለበት ለምን ነበር?

5 ኢሳይያስ 53:4ለን አንብብ። ኢየሱስ የተሠቃየበትና የሞተበት ምክንያት በዘመኑ ለኖሩት ለአብዛኞቹ ሰዎች ግልጽ አልነበረም። አምላክ በአስከፊ በሽታ እየቀጣው እንዳለ ተሰምቷቸው ነበር። (ማቴ. 27:38-44) አይሁዳውያን፣ አምላክን እንደተሳደበ በመግለጽ ኢየሱስን ከሰውታል። (ማር. 14:61-64፤ ዮሐ. 10:33) ኢየሱስ ኃጢአት እንዳልሠራም ሆነ አምላክን እንዳልተሳደበ ምንም ጥርጥር የለውም። ለአባቱ ከፍተኛ ፍቅር አለው፤ በዚህም የተነሳ የይሖዋ አገልጋይ በመሆኑ ከሚደርስበት መከራ ሌላ አምላክን እንደሰደበ ተወንጅሎ መገደሉ ተጨማሪ ሥቃይ አስከትሎበታል። ያም ሆኖ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም ዝግጁ ነበር።—ማቴ. 26:39

6, 7. ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዩን ‘አደቀቀው’ ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? አምላክ በዚህ ‘ደስ የተሰኘውስ’ እንዴት ነው?

6 በኢሳይያስ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው በወቅቱ የነበሩት ሰዎች፣ ክርስቶስ “በእግዚአብሔር እንደ ተመታ” አድርገው ያሰቡበትን ምክንያት መረዳት ብንችልም በትንቢቱ ላይ “ይሖዋ ራሱ እሱን በማድቀቅ ደስ ተሰኝቷል” መባሉ ግን ያስገርመን ይሆናል። (ኢሳ. 53:10 NW ) ይሖዋ “አገልጋዬ፣ በእርሱም ደስ የሚለኝ ምርጤ ይህ ነው” ብሎ ከተናገረ አገልጋዩን ‘በማድቀቅ ደስ ሊሰኝ’ የሚችለው እንዴት ነው? (ኢሳ. 42:1) ይህ ሁኔታ ይሖዋን አስደስቶታል ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው?

7 ይህንን ትንቢት ለመረዳት እንድንችል ሰይጣን የይሖዋን ሉዓላዊነት በተገዳደረበት ጊዜ በሰማይም ሆነ በምድር የሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ታማኝነታቸውን መጠበቃቸው አጠያያቂ እንዲሆን ማድረጉን ማስታወስ ያስፈልገናል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:3-5) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆኖ በመጽናት ሰይጣን ላስነሳው ጥያቄ የማያዳግም መልስ ሰጥቷል። ይሖዋ፣ ክርስቶስ በጠላቶቹ እንዲገደል ቢፈቅድም የመረጠው አገልጋዩ ሲገደል መመልከቱ ሥቃይ እንዳስከተለበት ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ ልጁ እስከ መጨረሻው ታማኝነቱን እንደጠበቀ ሲመለከት እጅግ ተደስቷል። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም) ከዚህም በላይ የልጁ ሞት ንስሐ ለሚገቡ የሰው ልጆች ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች ማሰቡ ታላቅ ደስታ አምጥቶለታል።—ሉቃስ 15:7

“ስለ መተላለፋችን ተወጋ”

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ ‘ስለ መተላለፋችን የተወጋው’ እንዴት ነበር? (ለ)  ጴጥሮስ ይህንን ሐቅ የገለጸው እንዴት ነው?

8 ኢሳይያስ 53:6ን አንብብ። እንደባዘኑ በጎች ሁሉ ኃጢአተኛ የሆኑት የሰው ዘሮችም ከአዳም ከወረሱት በሽታና ሞት የሚያድናቸው በመፈለግ ሲቅበዘበዙ ቆይተዋል። (1 ጴጥ. 2:25) የአዳም ዘሮች ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው አንዳቸውም ቢሆን እሱ ያጣውን ነገር መልሰው ማግኘት አይችሉም። (መዝ. 49:7) ይሖዋ ግን ታላቅ በሆነው ፍቅሩ ተነሳስቶ “የሁላችንን በደል [በሚወደው ልጁና በመረጠው አገልጋዩ] ላይ ጫነው።” ክርስቶስ ‘ስለ መተላለፋችን ለመወጋትና ስለ በደላችንም ለመድቀቅ’ ፈቃደኛ በመሆን በመከራ እንጨት ላይ ኃጢአታችንን ተሸክሞ ስለ እኛ ሞተ።

9 ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “የተጠራችሁት በዚህ ጎዳና እንድትሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል። ከኃጢአታችን ነፃ እንድንወጣና ለጽድቅ እንድንኖር እሱ ራሱ በገዛ አካሉ ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።” ጴጥሮስ የኢሳይያስን ትንቢት በመጥቀስ “ደግሞም ‘በእሱ ቁስል እናንተ ተፈወሳችሁ’” በማለት አክሎ ተናግሯል። (1 ጴጥ. 2:21, 24፤ ኢሳ. 53:5) ይህ ሁኔታ ኃጢአተኞች ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ መንገድ እንደከፈተ ጴጥሮስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ጻድቅ ሰው የሆነው ክርስቶስ እንኳ ለዓመፀኞች ሲል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሞት ከኃጢአት ነፃ አውጥቷቸዋል። ይህንም ያደረገው እናንተን ወደ አምላክ ለመምራት ነው።”—1 ጴጥ. 3:18

“እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ”

10. (ሀ) መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስን ምን ብሎ ጠርቶታል? (ለ)  ዮሐንስ ይህን ማለቱ ተገቢ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

10 ኢሳይያስ 53:7, 8ን አንብብ። መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ ሲመለከት “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 1:29) ዮሐንስ፣ ኢየሱስን እንዲህ ብሎ የጠራው “እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ” የሚለውን የኢሳይያስ ትንቢት በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል። (ኢሳ. 53:7) ክርስቶስ ‘እስከ ሞት ድረስ ነፍሱን እንደሚያፈስ’ ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሯል። (ኢሳ. 53:12 NW) ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ባቋቋመበት ምሽት ላይ ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት የወይን ጽዋ አንስቶ ከሰጣቸው በኋላ “ይህ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ ‘የቃል ኪዳን ደሜ’ ማለት ነው” ብሎ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው።—ማቴ. 26:28

11, 12. (ሀ) ይስሐቅ መሥዋዕት ለመሆን በፈቃደኝነት መስማማቱ ክርስቶስ ስላቀረበው መሥዋዕት ምን ያሳየናል? (ለ)  የመታሰቢያውን በዓል ስናከብር ከታላቁ አብርሃም፣ ከይሖዋ ጋር በተያያዘ ልንዘነጋው የማይገባን ነገር ምንድን ነው?

11 በጥንት ዘመን የኖረው ይስሐቅ እንዳደረገው ኢየሱስም መሥዋዕት ሆኖ ለመቅረብ ፈቃደኛ ነበር። (ዘፍ. 22:1, 2, 9-13፤ ዕብ. 10:5-10) ይስሐቅ መሥዋዕት ለመሆን በፈቃደኝነት ቢስማማም መሥዋዕቱን ለማቅረብ የሞከረው ግን አብርሃም ነበር። (ዕብ. 11:17) በተመሳሳይም ኢየሱስ ለመሞት ፈቃደኛ ቢሆንም ቤዛውን ያዘጋጀው ግን ይሖዋ ነው። አምላክ፣ ልጁ መሥዋዕት እንዲሆን መፍቀዱ ለሰው ልጆች ጥልቅ ፍቅር እንዳለው ያሳያል።

12 ኢየሱስ ራሱ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐ. 3:16) ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ለእኛ እንዲሞት በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።” (ሮም 5:8) በመሆኑም የመታሰቢያውን በዓል በማክበር ለክርስቶስ አክብሮት እንዳለን ብናሳይም ቤዛውን ያዘጋጀው ታላቁ አብርሃም፣ ይሖዋ መሆኑን መዘንጋት አይኖርብንም። የመታሰቢያውን በዓል የምናከብረው እሱን ለማወደስ ነው።

የአምላክ ባሪያ “ብዙዎቹን ያጸድቃል”

13, 14. የይሖዋ ባሪያ ‘ብዙዎችን ያጸደቀው’ እንዴት ነው?

13 ኢሳይያስ 53:11, 12ን አንብብ። ይሖዋ የመረጠውን ባሪያውን በተመለከተ “ጻድቅ ባሪያዬ . . . ብዙዎቹን ያጸድቃል” ብሏል። (ኢሳ. 53:11, 12) ባሪያው ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ቁጥር 12 መጨረሻ ላይ ያለው ሐሳብ ፍንጭ ይሰጠናል። ጥቅሱ ባሪያው “ስለ ዐመፀኞችም ማለደ” ይላል። የአዳም ዘሮች በሙሉ ኃጢአተኞች ሆነው ስለተወለዱ “ዐመፀኞች” ናቸው፤ በመሆኑም ‘ለኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ’ ማለትም ሞት ይገባቸዋል። (ሮም 5:12፤ 6:23) በይሖዋና ኃጢአተኛ በሆኑት የሰው ልጆች መካከል እርቅ መውረድ አለበት። በ⁠ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይ የሚገኘው ትንቢት ኢየሱስ፣ ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ዘር ‘የማለደው’ እንዴት እንደሆነ ግሩም በሆነ መንገድ ገልጿል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።”—ኢሳ. 53:5

14 ክርስቶስ ኃጢአታችንን ተሸክሞ ለእኛ ሲል በመሞት ‘ብዙዎችን አጽድቋል።’ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሙላት ሁሉ [በክርስቶስ] ውስጥ እንዲኖር አምላክ መልካም ሆኖ [አገኘው]፤ እንዲሁም በመከራው እንጨት ላይ ባፈሰሰው ደም አማካኝነት ሰላም በመፍጠር ሌሎቹን ነገሮች ሁሉ ይኸውም በምድርም ሆነ በሰማያት ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእሱ በኩል ከራሱ ጋር እንደገና ለማስታረቅ [ወደደ።]”—ቆላ. 1:19, 20

15. (ሀ) ጳውሎስ የጠቀሳቸው ‘በሰማያት ያሉት ነገሮች’ እነማን ናቸው? (ለ)  በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን የመካፈል መብት ያላቸው እነማን ብቻ ናቸው? ለምንስ?

15 ክርስቶስ ባፈሰሰው ደም አማካኝነት ከይሖዋ ጋር እንደታረቁ የተገለጹት ‘በሰማያት ያሉት ነገሮች’ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ለመግዛት የተጠሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። “የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች” የሆኑት ክርስቲያኖች “ጻድቃን ተብለው በመጠራት ለሕይወት እንዲበቁ” ተደርገዋል። (ዕብ. 3:1፤ ሮም 5:1, 18) በዚህ ምክንያት ይሖዋ እንደ መንፈሳዊ ልጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘የሚወርሱት ከክርስቶስ ጋር’ እንደሆነ ይኸውም ከእሱ ጋር በሰማይ ባለው መንግሥቱ ነገሥታትና ካህናት ለመሆን እንደተጠሩ መንፈስ ቅዱስ ይመሠክርላቸዋል። (ሮም 8:15-17፤ ራእይ 5:9, 10) እነዚህ ክርስቲያኖች የመንፈሳዊ እስራኤል ማለትም ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ከመሆናቸውም በላይ ‘በአዲሱ ቃል ኪዳን’ ውስጥ ታቅፈዋል። (ኤር. 31:31-34፤ ገላ. 6:16) የአዲሱ ቃል ኪዳን አባላት እንደመሆናቸው መጠን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን የመካፈል መብት አላቸው፤ ኢየሱስ በበዓሉ ላይ የሚቀርበውን ቀይ ወይን በተመለከተ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተው አዲሱ ቃል ኪዳን ማለት ነው” ብሏል።—ሉቃስ 22:20

16. ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የተባሉት እነማን ናቸው? በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም የሚኖራቸውስ በምን መንገድ ነው?

16 ‘በምድር ያሉት ነገሮች’ የተባሉት በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው የክርስቶስ ሌሎች በጎች ናቸው። ይሖዋ የመረጠው አገልጋይ እነዚህ ክርስቲያኖችም በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖራቸው ያደርጋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው ‘ልብሳቸውን በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል’፤ በዚህም የተነሳ በይሖዋ ዘንድ ጻድቃን ተብለው ተጠርተዋል። ይህ ሲባል ግን መንፈሳዊ ልጆቹ ይሆናሉ ማለት ሳይሆን እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ተቀብሏቸዋል ማለት ነው፤ በዚህም ምክንያት ‘ከታላቁ መከራ’ የመትረፍ ድንቅ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (ራእይ 7:9, 10, 14፤ ያዕ. 2:23) እነዚህ ሌሎች በጎች በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ስላልታቀፉ ተስፋቸው በሰማይ መኖር አይደለም፤ በመሆኑም በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚቀርበው ምሳሌያዊ ቂጣና ወይን አይካፈሉም፤ ከዚህ ይልቅ በበዓሉ ላይ በመገኘት ሥነ ሥርዓቱን በአክብሮት ይከታተላሉ።

ምስጋና ለይሖዋና ለሚደሰትበት አገልጋዩ ይሁን!

17. በአምላክ አገልጋይ ላይ የሚያተኩሩትን የኢሳይያስ ትንቢቶች መመርመራችን ለመታሰቢያው በዓል አእምሯችንን እንድናዘጋጅ የረዳን እንዴት ነው?

17 በአምላክ አገልጋይ ላይ የሚያተኩሩትን የኢሳይያስ ትንቢቶች መመርመራችን ለመታሰቢያው በዓል አእምሯችንን ለማዘጋጀት ረድቶናል። “የእምነታችን ዋና ወኪልና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን በትኩረት [እንድንመለከት]” አስችሎናል። (ዕብ. 12:2) የአምላክ ልጅ ዓመፀኛ እንዳልሆነ አውቀናል። ከሰይጣን በተለየ መልኩ ኢየሱስ፣ ከይሖዋ መማር የሚያስደስተው ሲሆን ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ እንደሆነ ይቀበላል። ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ለሰበከላቸው ሰዎች ርኅራኄ ያሳየ ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹን ሰዎች ከሕመማቸው ፈውሷቸዋል፤ በመንፈሳዊም ረድቷቸዋል። ይህን በማድረጉም በአዲሱ ሥርዓት መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ ‘ፍትሕን በምድር ላይ በሚያመጣበት ጊዜ’ ምን እንደሚያከናውን አሳይቷል። (ኢሳ. 42:4) ኢየሱስ ‘ለአሕዛብ ብርሃን’ ሆኖ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበክ ያሳየው ቅንዓት ተከታዮቹም በመላው ምድር ምሥራቹን በቅንዓት እንዲሰብኩ የሚያነሳሳ ነው።—ኢሳ. 42:6

18. የኢሳይያስ ትንቢት ይሖዋና ታማኝ አገልጋዩ ላደረጉልን ነገር አመስጋኞች እንድንሆን የሚያነሳሳን እንዴት ነው?

18 ከዚህም በተጨማሪ የኢሳይያስ ትንቢት፣ ይሖዋ የሚወደውን ልጁን ለእኛ ሲል ተሠቃይቶ እንዲሞት ወደ ምድር በላከው ወቅት ስለከፈለው ታላቅ መሥዋዕት ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። ይሖዋን ያስደሰተው ልጁ ሲሠቃይ ማየቱ ሳይሆን ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ ሆኖ እንደጸና መመልከቱ ነበር። ኢየሱስ፣ ሰይጣን ሐሰተኛ መሆኑን በማሳየትና የይሖዋን ስም በማስቀደስ የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ መሆኑን በማረጋገጡ ይሖዋ እንደተደሰተ ሁሉ እኛም ልንደሰት ይገባል። ከዚህም በላይ ክርስቶስ ኃጢአታችንን በመሸከም ለእኛ ሲል ሞቶልናል። እንዲህ በማድረጉም ታናሽ መንጋ የሆኑት ቅቡዓን ወንድሞቹም ሆኑ ሌሎች በጎች በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖራቸው አስችሏል። በመታሰቢያው በዓል ላይ በምንገኝበት ጊዜ ይሖዋና ታማኝ አገልጋዩ ላደረጉልን ነገር አመስጋኞች ልንሆን ይገባል።

ለክለሳ ያህል

• ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዩ ‘በመድቀቁ’ ‘ተደስቷል’ የሚባለው ከምን አንጻር ነው?

• ኢየሱስ ‘ስለ መተላለፋችን የተወጋው’ እንዴት ነበር?

• የይሖዋ ባሪያ ‘ብዙዎችን ያጸደቀው’ እንዴት ነው?

• በአምላክ አገልጋይ ላይ የሚያተኩሩትን የኢሳይያስ ትንቢቶች መመርመርህ ለመታሰቢያው በዓል አእምሮህንና ልብህን እንድታዘጋጅ የረዳህ እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የተናቀ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም”

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘እስከ ሞት ድረስ ነፍሱን አፍስሷል’

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሌሎች በጎች” በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘት ሥነ ሥርዓቱን በአክብሮት ይከታተላሉ