በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የአምላክ ጸጋ መጋቢ’ ነህ?

‘የአምላክ ጸጋ መጋቢ’ ነህ?

‘የአምላክ ጸጋ መጋቢ’ ነህ?

“በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።”—ሮም 12:10

1. የአምላክ ቃል የትኞቹን የሚያበረታቱ ሐሳቦች ይዟል?

ተስፋ በምንቆርጥበት ወይም ልባችን በሐዘን በሚሰበርበት ወቅት ይሖዋ እንደሚረዳን የአምላክ ቃል በተደጋጋሚ ጊዜያት ያረጋግጥልናል። ለአብነት ያህል፣ የሚከተሉትን የሚያበረታቱ ሐሳቦች ልብ በል:- “እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤ የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል።” “ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል።” (መዝ. 145:14፤ 147:3) ከዚህም በተጨማሪ በሰማይ የሚኖረው አባታችን ራሱ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ” ብሏል።—ኢሳ. 41:13

2. ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚደግፋቸው እንዴት ነው?

2 ይሁንና በሰማይ የሚኖረው ይሖዋ ‘እጃችንን የሚይዘው’ እንዴት ነው? ልባችን በሐዘን ተሰብሮ ‘ስንወድቅ የሚያነሣን’ እንዴት ነው? ይሖዋ አምላክ እንዲህ ያለውን ድጋፍ የሚያደርግልን በተለያዩ መንገዶች ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለሕዝቦቹ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጣቸዋል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ዮሐ. 14:16, 17) በተጨማሪም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ኃይል ያለው መልእክት የአምላክ አገልጋዮችን ያበረታታቸዋል ወይም ከወደቁበት ያነሳቸዋል። (ዕብ. 4:12) ይሖዋ እኛን የሚያጠናክርበት ሌላስ መንገድ አለ? የአንደኛ ጴጥሮስ መጽሐፍ መልሱን ይሰጠናል።

“በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ”

3. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ ፈተናዎችን በተመለከተ ምን ብሏል? (ለ) የአንደኛ ጴጥሮስ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው አካባቢ ስለ የትኛው ጉዳይ ይናገራል?

3 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ በአምላክ መንፈስ የተቀቡት አማኞች ታላቅ ሽልማት ስለሚጠብቃቸው እንዲደሰቱ የሚያደርግ በቂ ምክንያት እንዳላቸው ጽፎላቸዋል። ከዚያም “አሁን ለአጭር ጊዜ በተለያዩ ፈተናዎች ለማዘን” እንደተገደዱ ገልጿል። (1 ጴጥ. 1:1-6) እዚህ ላይ “በተለያዩ” የሚለውን ቃል ልብ በል። ይህ ቃል ክርስቲያኖች የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚደርሱባቸው ይጠቁማል። ይሁንና ጴጥሮስ፣ ወንድሞቹ እንዲህ ያሉትን የተለያዩ ፈተናዎች መቋቋም መቻል አለመቻላቸውን ሳይገልጽ አላለፈም። ከዚህ ይልቅ ክርስቲያኖች የሚያጋጥማቸው ፈተና ምንም ዓይነት ቢሆን ይሖዋ እያንዳንዱን ፈተና እንዲቋቋሙ እንደሚረዳቸው እርግጠኞች መሆን እንደሚችሉ ጴጥሮስ ገልጾላቸዋል። ሐዋርያው ይህን ማረጋገጫ የሰጠው ‘ስለ ሁሉም ነገር መጨረሻ’ በገለጸበት በደብዳቤው መገባደጃ አካባቢ ነው።—1 ጴጥ. 4:7

4. በአንደኛ ጴጥሮስ 4:10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ያጽናናናል የምንለው ለምንድን ነው?

4 ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው ስጦታ መሠረት በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች በመሆን፣ የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።” (1 ጴጥ. 4:10) እዚህም ላይ ጴጥሮስ ከላይ ከተጠቀመበት “በተለያዩ” ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ የሆነውን “ልዩ ልዩ” የሚለውን ሐረግ ተጠቅሟል። ጴጥሮስ ‘ፈተናዎች የሚመጡት በተለያዩ መንገዶች ቢሆንም የአምላክ ጸጋ የሚገለጸውም በተለያዩ መንገዶች ነው’ ብሎ የተናገረ ያህል ነው። ይህ ሐሳብ የሚያጽናና የሆነው ለምንድን ነው? ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ምንጊዜም ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችለን የአምላክ ጸጋ እንደሚኖር ስለሚጠቁም ነው። ይሁንና የይሖዋ ጸጋ የሚገለጽበትን መንገድ አስተዋልክ? ጴጥሮስ ከተናገረው ሐሳብ መመልከት እንደምንችለው የይሖዋ ጸጋ የሚገለጸው በክርስቲያን ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ነው።

“አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል”

5. (ሀ) እያንዳንዱ ክርስቲያን ምን እንዲያደርግ ይጠበቅበታል? (ለ)  ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

5 ጴጥሮስ ለክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሙሉ “ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ” የሚል ምክር ሰጥቷል። ከዚያም “እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው ስጦታ መሠረት . . . የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት” ብሏል። (1 ጴጥ. 4:8, 10) በመሆኑም እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ክርስቲያን ባልንጀሮቹን በማነጽ ረገድ የሚጫወተው ሚና ሊኖር ይገባል። የይሖዋ ንብረት የሆነ ውድ ነገር በአደራ የተቀበልን ሲሆን ይህንንም ለሌሎች እንድናካፍል ኃላፊነት ተጥሎብናል። ታዲያ በአደራ የተቀበልነው ነገር ምንድን ነው? ጴጥሮስ ይህ ነገር “ስጦታ” እንደሆነ ገልጿል። ይህ ስጦታ ምንድን ነው? ‘አንዳችን ሌላውን ለማገልገል የምንጠቀምበትስ’ እንዴት ነው?

6. ክርስቲያኖች የተሰጧቸው አንዳንድ ስጦታዎች የትኞቹ ናቸው?

6 የአምላክ ቃል “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ ከላይ ነው” ይላል። (ያዕ. 1:17) በእርግጥም ይሖዋ ለሕዝቡ የሰጣቸው ስጦታዎች በሙሉ የእሱ ጸጋ መግለጫዎች ናቸው። ይሖዋ ከሰጠን ግሩም ስጦታዎች መካከል አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ ስጦታ እንደ ፍቅር፣ ጥሩነትና ገርነት የመሳሰሉትን አምላካዊ ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ከልባችን እንድንወዳቸውና በፈቃደኝነት ተነሳስተን እንድንረዳቸው ይገፋፉናል። በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ከምናገኛቸው መልካም ስጦታዎች መካከል እውነተኛ ጥበብና እውቀትም ይገኙበታል። (1 ቆሮ. 2:10-16፤ ገላ. 5:22, 23) ያለን ጉልበት፣ ችሎታና ተሰጥኦ በሰማይ ለሚኖረው አባታችን ውዳሴና ክብር ለማምጣት የምንጠቀምበት ስጦታ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። አምላክ፣ ችሎታችንንና ባሕርያችንን በመጠቀም የእሱን ጸጋ ለእምነት ባልንጀሮቻችን የማስተላለፍ ኃላፊነት ጥሎብናል።

“ለማገልገል ተጠቀሙበት”—እንዴት?

7. (ሀ) “መሠረት” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? (ለ)  ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

7 ጴጥሮስ የተቀበልናቸውን ስጦታዎች በተመለከተ “እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው ስጦታ መሠረት . . . የተሰጣችሁን ስጦታ . . . ተጠቀሙበት” በማለትም ተናግሯል። “መሠረት” የሚለው ቃል እዚህ ላይ መግባቱ ባሕርያችንም ሆነ ችሎታችን በዓይነቱ ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ሊለያይ እንደሚችል ይጠቁማል። ያም ቢሆን እያንዳንዱ ሰው ‘የተሰጠውን ስጦታ ሌላውን ለማገልገል እንዲጠቀምበት’ ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል። ከዚህም በላይ “መልካም መጋቢዎች በመሆን፣ . . . ተጠቀሙበት” የሚለው አገላለጽ ትእዛዝ ነው። በመሆኑም እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል:- ‘የተሰጡኝን ስጦታዎች የእምነት ባልንጀሮቼን ለማበረታታት እጠቀምባቸዋለሁ?’ (ከ1 ጢሞቴዎስ 5:9, 10 ጋር አወዳድር።) ‘ወይስ ይሖዋ የሰጠኝን ችሎታ በዋነኝነት የምጠቀምበት የግል ጥቅሜን ለማሳደድ ማለትም ሀብት ለማካበት ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ለማግኘት ነው?’ (1 ቆሮ. 4:7) የተቀበልናቸውን ስጦታዎች ‘ሌላውን ለማገልገል ከተጠቀምንባቸው’ ይሖዋን እናስደስተዋለን።—ምሳሌ 19:17፤ ዕብራውያን 13:16ን አንብብ።

8, 9. (ሀ) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን የሚያገለግሉባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? (ለ)  በጉባኤያችሁ ውስጥ የሚገኙት ወንድሞችና እህቶች እርስ በርስ የሚረዳዱት እንዴት ነው?

8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች አንዳቸው ሌላውን ያገለገሉባቸው የተለያዩ መንገዶች በአምላክ ቃል ውስጥ ተገልጸዋል። (ሮም 15:25, 26ን እና 2 ጢሞቴዎስ 1:16-18ን አንብብ።) ዛሬም በተመሳሳይ እውነተኛ ክርስቲያኖች የተቀበሉትን ስጦታ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማገልገል እንዲጠቀሙበት የተሰጣቸውን መመሪያ በደስታ ይታዘዛሉ። ይህን የሚያደርጉባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

9 ብዙ ወንድሞች በጉባኤ የሚያቀርቧቸውን ክፍሎች ለመዘጋጀት በየወሩ በርካታ ሰዓታት ያሳልፋሉ። እነዚህ ወንድሞች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ወቅት ያገኟቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ዕንቁዎች በስብሰባዎች ላይ በሚያቀርቡበት ጊዜ ማስተዋል የተሞላበት ንግግራቸው ሁሉንም የጉባኤ አባላት እንዲጸኑ ያበረታታቸዋል። (1 ጢሞ. 5:17) ለእምነት ባልንጀሮቻቸው በሚያሳዩት ፍቅርና ርኅራኄ የሚታወቁ በርካታ ወንድሞችና እህቶችም አሉ። (ሮም 12:15) አንዳንዶች የተጨነቁ ክርስቲያኖችን አዘውትረው የሚጠይቋቸው ሲሆን አብረዋቸውም ይጸልያሉ። (1 ተሰ. 5:14) ሌሎች ደግሞ ፈተና ለሚደርስባቸው ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ልባዊ አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ደብዳቤ በመጻፍ ያበረታቷቸዋል። አንዳንድ ወንድሞች አቅመ ደካማ የሆኑ ክርስቲያኖችን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ በደግነት ይረዷቸዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋ ምክንያት ቤታቸውን ያጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ቤት መልሶ በመገንባቱ ሥራ ይካፈላሉ። እነዚህ አሳቢ ወንድሞችና እህቶች የሚያሳዩት ጥልቅ ፍቅርና የሚያደርጉት እርዳታ ሁሉ “በልዩ ልዩ መንገዶች የተገለጸው የአምላክ ጸጋ” መግለጫ ነው።—1 ጴጥሮስ 4:11ን አንብብ።

ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው ነው?

10. (ሀ) ጳውሎስ፣ ለአምላክ የሚያቀርበው አገልግሎት የትኞቹን ሁለት ገጽታዎች ያካተተ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር? (ለ)  በዛሬው ጊዜ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

10 የአምላክ አገልጋዮች በአደራ የተሰጣቸው ለእምነት ባልንጀሮቻቸው የሚያካፍሉት ስጦታ ብቻ ሳይሆን ለሰዎች መድረስ የሚገባው መልእክትም ጭምር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ለይሖዋ የሚያቀርበው አገልግሎት እነዚህን ሁለት ገጽታዎች ያካተተ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በኤፌሶን ለሚገኙት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለእነሱ ‘ጥቅም ሲባል ስለተሰጠው የአምላክ ጸጋ መጋቢነት’ ገልጾ ነበር። (ኤፌ. 3:2) ከዚህም ሌላ “ምሥራቹን በአደራ ለመቀበል ብቁ እንደሆንን አምላክ [አረጋግጦልናል]” በማለት ጽፏል። (1 ተሰ. 2:4) እኛም እንደ ጳውሎስ ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ ኃላፊነት በአደራ እንደተሰጠን እንገነዘባለን። በስብከቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ጳውሎስ ምሥራቹን ያለማሰለስ በማወጅ ረገድ የተወውን ምሳሌ ለመከተል እንጥራለን። (ሥራ 20:20, 21፤ 1 ቆሮ. 11:1) ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት መስበክ የሰዎችን ሕይወት ሊያድን እንደሚችል እናውቃለን። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለእምነት ባልንጀሮቻችን “መንፈሳዊ ስጦታ [ለማካፈል]” የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በመፈለግ ጳውሎስን ለመምሰል እንጥራለን።—ሮም 1:11, 12⁠ን እና 10:13-15ን አንብብ።

11. ምሥራቹን እንድንሰብክና ወንድሞቻችንን እንድናበረታታ የተሰጡንን ኃላፊነቶች እንዴት አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል?

11 ክርስቲያኖች ከሚያከናውኗቸው ከእነዚህ ሁለት ተግባራት ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው ነው? እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት ‘አንዲት ወፍ ካሏት ሁለት ክንፎች መካከል ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው የትኛው ነው?’ ብሎ የመጠየቅ ያህል ነው። መልሱ ግልጽ ነው። አንዲት ወፍ በሚገባ ለመብረር ሁለቱንም ክንፎቿን መጠቀም ያስፈልጋታል። እኛም በተመሳሳይ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የሚጠበቁብንን ነገሮች በሙሉ ለማሟላት ከላይ በተገለጹት በሁለቱም መንገዶች አምላክን ማገልገል ይኖርብናል። በመሆኑም ምሥራቹን የመስበክና የእምነት ባልንጀሮቻችንን የማነጽ ኃላፊነታችንን ሁለት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ አድርገን ማሰብ አይኖርብንም፤ ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጴጥሮስና ጳውሎስ እንዳደረጉት እነዚህን ኃላፊነቶች እርስ በርስ የሚደጋገፉ እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን። እንዴት?

12. ይሖዋ ሊጠቀምብን የሚችለው እንዴት ነው?

12 የወንጌል ሰባኪዎች እንደመሆናችን መጠን ባለን የማስተማር ችሎታ ተጠቅመን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው የሚያበረታታ መልእክት የሰዎችን ልብ እንዲነካ ለማድረግ እንጥራለን። እንዲህ በማድረግ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ልንረዳቸው እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ ያሉንን ችሎታዎችና ሌሎች ስጦታዎች የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለማበረታታት እንጠቀምባቸዋለን፤ ይህንንም የምናደርገው በንግግራችንና በምናከናውናቸው ጠቃሚ ተግባራት ሲሆን እነዚህም የአምላክ ጸጋ መግለጫዎች ናቸው። (ምሳሌ 3:27፤ 12:25) በዚህ መንገድ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነው እንዲቀጥሉ ልንረዳቸው እንችላለን። ለሰዎች በመስበክም ሆነ ‘አንዳችን ሌላውን በማገልገል’ ረገድ ይሖዋ የሚጠቀምብን መሆኑ ግሩም መብት ነው።—ገላ. 6:10

“እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ”

13. ‘አንዳችን ሌላውን ከማገልገል’ ወደኋላ ብንል ምን ያጋጥመናል?

13 ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) በእርግጥም ለወንድሞቻችን ፍቅር ማዳበራችን የአምላክ ጸጋ መጋቢዎች በመሆን በሙሉ ልብ እንድናገለግል ይገፋፋናል። ሰይጣን ‘አንዳችን ሌላውን ከማገልገል’ ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን ከቻለ አንድነታችንን እንደሚያጠፋው እናውቃለን። (ቆላ. 3:14) አንድነት ከሌለን ደግሞ ለስብከቱ ሥራ ያለን ቅንዓት ይቀዘቅዛል። ሰይጣን ተልእኳችንን እንዳንወጣ ለማድረግ በምሳሌያዊ አነጋገር በአንደኛው ክንፋችን ላይ ብቻ ጉዳት ማድረስ እንደሚበቃው አሳምሮ ያውቃል።

14. ‘አንዱ ሌላውን በማገልገሉ’ ተጠቃሚ የሚሆኑት እነማን ናቸው? ምሳሌ ስጥ።

14 ‘አንዱ ሌላውን በማገልገሉ’ ተጠቃሚ የሚሆኑት የአምላክን ጸጋ የሚቀበሉት ብቻ ሳይሆኑ ይህንን ጸጋ ለሌሎች የሚያካፍሉት ጭምር ናቸው። (ምሳሌ 11:25) በኢሊኖይስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩትን ራያንና ራኒ የተባሉ ባልና ሚስት እንደምሳሌ እንመልከት። ካትሪና የተባለችው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችን ቤቶች እንዳወደመች ባወቁ ጊዜ ሥራቸውንና ቤታቸውን በመልቀቅ አንድ ያገለገለ ተጎታች ቤት ገዙ። ከዚያም ተጎታች ቤቱን ጠግነው 1,400 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ሉዊዚያና ተጓዙ። እነዚህ ባልና ሚስት እንዲህ እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር ነው። በጊዜያቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው ተጠቅመው ወንድሞቻቸውን እያገለገሉ በሉዊዚያና ከአንድ ዓመት በላይ ቆይተዋል። የ29 ዓመቱ ራያን “በእርዳታው ሥራ መካፈሌ ወደ አምላክ ይበልጥ እንድቀርብ አድርጎኛል። ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንደሚንከባከብ ተመልክቻለሁ” ብሏል። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በዕድሜ ከገፉ ወንድሞች ጋር አብሬ በመሥራቴ ወንድሞችን እንዴት መንከባከብ እንደምችል ብዙ ተምሬያለሁ። ከዚህም በተጨማሪ እኛ ወጣቶች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የምናከናውነው ብዙ ሥራ እንዳለ ተገንዝቤያለሁ።” የ25 ዓመቷ ራኒ ደግሞ እንደሚከተለው ብላለች:- “ሌሎችን በመርዳቱ ሥራ መካፈል በመቻሌ አመስጋኝ ነኝ። በሕይወቴ ሙሉ እንደዚህ ተደስቼ አላውቅም። በዚህ ወቅት ያገኘሁት ግሩም ተሞክሮ በቀጣዮቹ ዓመታትም እንደሚጠቅመኝ እርግጠኛ ነኝ።”

15. የአምላክ ጸጋ መጋቢዎች በመሆን ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚገፋፉን ምን ግሩም ምክንያቶች አሉ?

15 በእርግጥም ምሥራቹን እንድንሰብክና የእምነት ባልንጀሮቻችንን እንድናበረታታ አምላክ የሰጠንን መመሪያ መታዘዛችን ለሁሉም ሰው በረከት ያስገኛል። የምንረዳቸው ሰዎች በመንፈሳዊ የሚጠናከሩ ሲሆን እኛ ደግሞ በመስጠት ብቻ ሊገኝ የሚችለውን ልባዊ ደስታ እናጣጥማለን። (ሥራ 20:35) እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ለሌሎች ፍቅር ሲያሳይ በሁሉም የጉባኤው አባላት መካከል ፍቅር ይኖራል። ከዚህም በላይ አንዳችን ለሌላው የምናሳየው ፍቅርና አሳቢነት እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን በግልጽ ይጠቁማል። ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:35) ከሁሉ በላይ ደግሞ አሳቢ የሆነው አባታችን ይሖዋ ይከበራል፤ ይሖዋ የተቸገሩ ሰዎችን ለመደገፍ የሚፈልግ ሲሆን በምድር ያሉት አገልጋዮቹ እንዲህ ማድረጋቸው ደግሞ እሱን ያስከብረዋል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው የተቀበልናቸውን ስጦታዎች “የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች በመሆን፣ . . . [አንዳችን] ሌላውን ለማገልገል” እንድንጠቀምባቸው የሚገፋፉን ግሩም ምክንያቶች አሉን! አንተስ እንዲህ ማድረግህን ትቀጥላለህ?—ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋ አገልጋዮቹን የሚደግፋቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• በአደራ የተሰጠን ነገር ምንድን ነው?

• የእምነት ባልንጀሮቻችንን ማገልገል የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

• በተሰጠን ስጦታ በመጠቀም ‘አንዳችን ሌላውን ማገልገላችንን’ እንድንቀጥል የሚገፋፋን ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአምላክ የተቀበልከውን “ስጦታ” የምትጠቀምበት ሌሎችን ለማገልገል ነው? ወይስ ራስህን ለማስደሰት?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሰዎች ምሥራቹን እንሰብካለን እንዲሁም ክርስቲያን ባልንጀሮቻችንን እንደግፋለን

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ በእርዳታ ሥራ የሚካፈሉ ክርስቲያኖች ሊመሰገኑ ይገባል