በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተደሰት

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተደሰት

ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ተደሰት

“ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴ. 28:19

1-3. (ሀ) ብዙዎች፣ ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ማስጠናት ምን ይሰማቸዋል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

በዩናይትድ ስቴትስበሂንዲ ቋንቋ በሚመራ ቡድን ውስጥ የምታገለግል አንዲት እህት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ከፓኪስታን የመጡ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ላለፉት 11 ሳምንታት [መጽሐፍ ቅዱስ] ሳስጠና ቆይቻለሁ። ከዚህ ቤተሰብ ጋር ወዳጅነት መሥርተናል። ይህ ቤተሰብ በቅርቡ ወደ ፓኪስታን እንደሚመለስ ሳስብ እንባዬ በዓይኖቼ ግጥም ይላል። ከዚህ ቤተሰብ ጋር በመለያየቴ ባዝንም እነሱን ስለ ይሖዋ በማስተማሬ ያገኘሁትን ደስታ ሳስታውስ ዓይኖቼ እንባ ያቀራሉ።”

2 አንተስ እንደዚህች እህት አንድን ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ችለሃል? ኢየሱስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ተከታዮቹ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ከፍተኛ ደስታ አግኝተው ነበር። ኢየሱስ ሥልጠና የሰጣቸው 70 ደቀ መዛሙርት ከአገልግሎት ተመልሰው አስደሳች ሪፖርት በነገሩት ጊዜ “ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሴት አድርጎ” ነበር። (ሉቃስ 10:17-21) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በጣም ይደሰታሉ። በትጋት የሚያገለግሉ በርካታ አስፋፊዎች በ2007 በአማካይ በየወሩ ስድስት ሚሊዮን ተኩል የሚያህሉ ሰዎችን ማስጠናታቸው በዚህ ሥራ እንደሚደሰቱ የሚያሳይ ማስረጃ ነው!

3 ይሁንና አንዳንድ አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ኖሯቸው አያውቅም። ሌሎች ደግሞ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አላገኙ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው ሰው ለማግኘት ጥረት ስናደርግ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ? እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ “ሂዱና . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት የሰጠውን መመሪያ ለመታዘዝ የተቻለንን ሁሉ ስናደርግ ምን በረከት እናገኛለን?—ማቴ. 28:19

ደስታ ሊያሳጡን የሚችሉ ፈታኝ ሁኔታዎች

4, 5. (ሀ) በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ሰዎች ለምሥራቹ ምን ምላሽ ይሰጣሉ? (ለ) በሌሎች አገሮች የሚኖሩ አስፋፊዎች ምን ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

4 በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች፣ ሰዎች ጽሑፎቻችንን በደስታ የሚቀበሉ ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስን ከእኛ ጋር ለማጥናት ፈቃደኞች ናቸው። ከአውስትራሊያ መጥተው በዛምቢያ ለተወሰነ ጊዜ ያገለገሉ አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ስለ ዛምቢያ የሰማነው ሁሉ እውነት ነው። በዚህች አገር በስብከቱ ሥራ ብዙ ፍሬ ይገኛል። መንገድ ላይ የምናከናውነው አገልግሎት በጣም አስደሳች ነው! ሰዎቹ ራሳቸው መጥተው የሚያነጋግሩን ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ የሚፈልጉትን መጽሔት እትም ለይተው ይጠይቁናል።” በዛምቢያ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች በቅርቡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ200,000 በላይ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንተዋል፤ ይህ ደግሞ አንድ አስፋፊ በአማካይ ከአንድ በላይ ጥናት መርቷል ማለት ነው።

5 በሌሎች አገሮች ግን አስፋፊዎች መጽሔት ማበርከትም ሆነ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ሰዎችን ቤታቸው አያገኟቸውም፤ ቤታቸው የሚገኙት ሰዎች ደግሞ ለሃይማኖት ግድ የለሾች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ያደጉት ሃይማኖተኛ ባልሆነ ቤተሰብ ውስጥ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ የሚታየው ግብዝነት ሃይማኖትን እንዲጠሉ አድርጓቸው ይሆናል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ሰዎች በሐሰተኛ እረኞች የተገፈፉና የተጣሉ በሌላ አባባል በመንፈሳዊ የተጎዱ ናቸው። (ማቴ. 9:36) እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት የሚቀርብላቸውን ግብዣ ለመቀበል ቢያንገራግሩ የሚያስገርም አይደለም።

6. አንዳንድ አስፋፊዎች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?

6 በታማኝነት የሚያገለግሉ አንዳንድ አስፋፊዎች ደስታቸውን የሚያሳጣ ሌላም ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። በአንድ ወቅት ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በትጋት ይካፈሉ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የጤንነታቸው ሁኔታ ወይም ከዕድሜ መግፋት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንቅፋት ሆነውባቸዋል። በተጨማሪም በራሳችን የምንፈጥራቸውን ሌሎች እንቅፋቶች እንመልከት። ለምሳሌ፣ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ብቃት እንደሌለህ ይሰማሃል? ምናልባትም ሙሴ፣ ፈርዖንን እንዲያነጋግር ይሖዋ በላከው ወቅት የተሰማው ዓይነት ስሜት ያድርብህ ይሆናል። ሙሴ “ጌታ ሆይ፣ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋር ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም” በማለት ተናግሯል። (ዘፀ. 4:10) ብዙውን ጊዜ ብቃት እንደሌለው የሚሰማው ሰው ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ‘አይሳካልኝ ይሆናል’ የሚል ፍርሃት አለው። ጥሩ አስተማሪ ስላልሆን አንድን ሰው ደቀ መዝሙር እንዲሆን መርዳት እንደማንችል በማሰብ እንጨነቅ ይሆናል። እንዲህ ያለው ስሜት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ከማስጠናት ወደኋላ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ከላይ የተመለከትናቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

ልብህን አዘጋጅ

7. ኢየሱስ አገልግሎቱን እንዲያከናውን ያነሳሳው ምን ነበር?

7 እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለማሸነፍ የሚረዳን የመጀመሪያው እርምጃ ልባችንን ማዘጋጀት ነው። ኢየሱስ ‘አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው’ ብሏል። (ሉቃስ 6:45) ኢየሱስ አገልግሎቱን እንዲያከናውን ያነሳሳው ለሰዎች ደኅንነት ከልቡ ማሰቡ ነበር። ለአብነት ያህል፣ አይሁዳውያኑ ምን ያህል በመንፈሳዊ ተጎድተው እንደነበር በተመለከተ ጊዜ ‘እጅግ አዝኖላቸው’ ነበር። ለደቀ መዛሙርቱ “አዝመራው ብዙ ነው፤ . . . የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት” ብሏቸዋል።—ማቴ. 9:36-38

8. (ሀ) ስለ የትኞቹ ነገሮች ማሰባችን የተገባ ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠና አንዲት ሴት ከሰጠችው አስተያየት ምን እንማራለን?

8 ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በምንካፈልበት ወቅት ልናስታውሰው የሚገባ ነገር አለ፤ አንድ ሰው ጊዜውን መሥዋዕት አድርጎ መጽሐፍ ቅዱስ ስላስጠናን ምን ያህል እንደተጠቀምን ማሰብ ይኖርብናል። ከዚህም በተጨማሪ በአገልግሎት ላይ ስለምናገኛቸው ሰዎችና እነዚህ ሰዎች የምንናገረውን መልእክት መስማታቸው ምን ያህል እንደሚጠቅማቸው እናስብ። አንዲት ሴት በምትኖርበት አገር ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ቤቴ መጥተው [መጽሐፍ ቅዱስ] የሚያስተምሩኝን የይሖዋ ምሥክሮች ምን ያህል እንደማደንቃቸው ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ። አንዳንድ ጊዜ እንደማደክማቸው ይሰማኛል፤ ምክንያቱም በርካታ ጥያቄዎችን የምጠይቃቸው ከመሆኑም ሌላ ሁልጊዜ ረዘም ላለ ሰዓት አቆያቸዋለሁ። ያም ቢሆን የሚታገሡኝ ሲሆን ያወቁትን ነገር ለእኔ ለማስተማር ጉጉት አላቸው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ስለተገናኘሁ ይሖዋንም ሆነ ኢየሱስን አመሰግናለሁ።”

9. ኢየሱስ ትኩረት ያደረገው በምን ላይ ነበር? እኛስ ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?

9 እርግጥ ነው፣ የኢየሱስን ትምህርት ተቀብለው የእሱ ተከታይ የሆኑት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። (ማቴ. 23:37) አንዳንዶች ለተወሰነ ጊዜ የተከተሉት ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ትምህርቶቹን በመቃወም “እሱን መከተላቸውን [አቁመዋል]።” (ዮሐ. 6:66) ይሁንና ኢየሱስ ትምህርቱን አንዳንዶች ስላልተቀበሉት የሚሰብከው መልእክት ዋጋ እንደሌለው አልተሰማውም። ኢየሱስ የዘራው አብዛኛው ዘር ፍሬ ባያፈራም እሱ ያተኮረው በሚያከናውናቸው መልካም ሥራዎች ላይ ነበር። አዝመራው እንደነጣና ለመከር እንደደረሰ የተገነዘበ ሲሆን በመከሩ ሥራ በመካፈሉ በጣም ተደስቶ ነበር። (ዮሐንስ 4:35, 36ን አንብብ።) እኛስ፣ ከአዝመራው ሥር ያለውን ደረቅ መሬት ብቻ ከመመልከት ይልቅ በተሰጠን የአገልግሎት ክልል ውስጥ ሊገኝ በሚችለው ፍሬ ላይ ማተኮር እንችላለን? እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በምትዘራበት ጊዜ ምርት የመሰብሰብ ግብ ይኑርህ

10, 11. በአገልግሎትህ ደስተኛ ሆነህ ለመቀጠል ምን ማድረግ ትችላለህ?

10 አንድ ገበሬ ዘር በሚዘራበት ወቅት ምርት የመሰብሰብ ግብ ይኖረዋል። በተመሳሳይ እኛም ምሥራቹን ስንሰብክ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማግኘት ግብ ሊኖረን ይገባል። ይሁን እንጂ በመስክ አገልግሎት አዘውትረህ ብትካፈልም ብዙ ሰዎችን ቤታቸው የማታገኛቸው ቢሆንስ? አሊያም ያነጋገርካቸውን ሰዎች እንደገና ማግኘት ቢያስቸግርህስ? እንዲህ ያለው ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ይህ ከቤት ወደ ቤት ማገልገልህን እንድታቆም ሊያደርግህ ይገባል? በፍጹም! አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚገናኙት ለዘመናት በተሠራበትና ውጤታማ በሆነው በዚህ የስብከት ዘዴ አማካኝነት ነው።

11 ያም ቢሆን በአገልግሎትህ ደስተኛ ሆነህ ለመቀጠል እንድትችል በሌሎች የስብከት ዘዴዎችም ሰዎችን ለማነጋገር ጥረት ማድረግ ትችል ይሆን? ለምሳሌ ያህል፣ ለሰዎች በመንገድ ላይ ወይም በሥራ ቦታቸው ለመመሥከር ሞክረህ ታውቃለህ? በስልክ መመሥከር ትችላለህ? ወይም ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት የነገርካቸውን ሰዎች እንደገና ለማግኘት እንዲረዳህ የስልክ ቁጥራቸውን መቀበል ትችል ይሆን? በአገልግሎትህ ከጸናህ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ሰዎችን ለማነጋገር ጥረት ካደረግህ ስለ አምላክ መንግሥት ለሚናገረው መልእክት በጎ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን በማግኘት ልትደሰት ትችላለህ።

የሰዎችን ግድ የለሽነት መቋቋም

12. በአገልግሎት ክልላችን የሚገኙ ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት ግድ የለሾች ቢሆኑ ምን ማድረግ እንችላለን?

12 በአገልግሎት ክልልህ ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች ለሃይማኖት ግድ የለሾች ቢሆኑስ? ትኩረታቸውን የሚስብ መግቢያ መጠቀም ትችላለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙት የእምነት ባልንጀሮቹ እንዲህ በማለት ጽፎላቸዋል:- “ለአይሁዳውያን እንደ አይሁዳዊ ሆንኩ። . . . በአምላክ ፊት ከሕግ ነፃ ያልሆንኩ . . . ብሆንም እንኳ . . . ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደሌለኝ ሆንኩ።” ጳውሎስ እንዲህ እንዲያደርግ የገፋፋው ምን ነበር? “በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን አድን ዘንድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር ሆንኩ” ብሏል። (1 ቆሮ. 9:20-22) እኛስ በአገልግሎት ክልላችን የምናገኛቸውን ሰዎች ትኩረት የሚስብ ርዕስ በማንሳት ልናወያያቸው እንችል ይሆን? ሃይማኖተኛ ያልሆኑ በርካታ ሰዎች ጥሩ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ ይፈልጋሉ። እንዲሁም የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ ይሆናል። ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት እንዲህ ያሉትን ሰዎች ትኩረት በሚስብ መንገድ መናገር እንችል ይሆን?

13, 14. ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የበለጠ ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

13 ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ አስፋፊዎች አብዛኞቹ ሰዎች ለሃይማኖት ግድ የለሾች በሆኑበት አካባቢ የሚኖሩ ቢሆንም እንኳ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ የበለጠ ደስታ ማግኘት ችለዋል። እንዲህ ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው? የሌላ አገር ቋንቋ በመማር ነው። በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት በጉባኤያቸው የአገልግሎት ክልል ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው እንደሚኖሩ አስተዋሉ። ወንድም እንዲህ ብለዋል:- “በዚህም የተነሳ ቻይንኛ እንድንማር ማበረታቻ ተሰጠን። ቋንቋውን ለማጥናት በየቀኑ ጊዜ መመደብ ቢኖርብንም በአካባቢያችን የሚኖሩ በርካታ ቻይናውያንን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ችለናል።”

14 የሌላ አገር ቋንቋ መማር ባትችልም እንኳ ከአንተ የተለየ ቋንቋ የሚናገር ሰው ሲያጋጥምህ ለሰዎች ሁሉ የሚሆን ምሥራች የተባለውን ቡክሌት ጥሩ አድርገህ ልትጠቀምበት ትችላለህ። ከዚህም በተጨማሪ በአገልግሎት የምታገኛቸው ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማግኘት ትችል ይሆናል። ከአንተ የተለየ ቋንቋና ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር ለመግባባት ተጨማሪ ጊዜ መመደብና ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግህ እሙን ነው። ይህም ቢሆን ‘በብዛት የሚዘራ በብዛት ያጭዳል’ የሚለውን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝ መሠረታዊ ሥርዓት አስታውስ።—2 ቆሮ. 9:6

መላው ጉባኤ አስተዋጽኦ ያበረክታል

15, 16. (ሀ) አንድን ሰው ደቀ መዝሙር የማድረጉ ሥራ የሁሉንም የጉባኤ አባላት ጥረት ይጠይቃል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ረገድ አረጋውያን ምን ሚና ይጫወታሉ?

15 ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ አንድ ግለሰብ ብቻውን በሚያደርገው ጥረት ላይ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የጉባኤው አባላት በሙሉ አንድን ሰው ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ይካፈላሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ኢየሱስ “በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:35) በእርግጥም፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ ሲገኙ በሚያዩት ፍቅር ብዙውን ጊዜ ይደነቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠና አንዲት ሴት “በስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም ያስደስተኛል። በዚያ የሚገኙት ሰዎች ባይተዋርነት እንዳይሰማኝ ያደርጉኛል!” ስትል ጽፋለች። ኢየሱስ፣ ሰዎች የእሱ ተከታዮች ሲሆኑ የሥጋ ዘመዶቻቸው ሊቃወሟቸው እንደሚችሉ ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:35-37ን አንብብ።) ይሁንና በጉባኤ ውስጥ በርካታ መንፈሳዊ “ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችን” እንደሚያገኙ ቃል ገብቶላቸዋል።—ማር. 10:30

16 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ በተለይ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። እንዴት? አንዳንድ አረጋውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ባይችሉም እንኳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጡት የሚያንጽ ሐሳብ በዚያ የሚገኙትን እምነት ያጠናክራል። “በጽድቅ መንገድ” ሲመላለሱ መቆየታቸው ለጉባኤው ውበት የሚጨምርለት ከመሆኑም በላይ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ አምላክ ድርጅት እንዲሳቡ ያደርጋል።—ምሳሌ 16:31 የ1954 ትርጉም

ፍርሃታችንን ማሸነፍ

17. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራት ብቃት የለኝም የሚለውን ስሜት ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው?

17 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራት ብቃት እንደሌለህ የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይሖዋ፣ ለሙሴ መንፈስ ቅዱስን በመስጠትና ወንድሙ አሮን አጋር እንዲሆነው በማድረግ እንደረዳው አስታውስ። (ዘፀ. 4:10-17) ኢየሱስ በስብከቱ ሥራችን የአምላክ መንፈስ እንደሚደግፈን ቃል ገብቷል። (ሥራ 1:8) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት የላካቸው ሁለት ሁለት አድርጎ እንደነበር አስታውስ። (ሉቃስ 10:1) እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ከከበደህ ጥበብ ለማግኘት አምላክ መንፈሱን እንዲሰጥህ ጸልይ፤ እንዲሁም ድፍረት እንዲኖርህ ሊረዳህ ከሚችል ተሞክሮ ያለው አስፋፊ ጋር አብረህ አገልግል። ይሖዋ ይህንን ታላቅ ሥራ እንዲሠሩ የመረጠው “የዓለምን ደካማ ነገር” ማለትም ተራ ሰዎችን እንደሆነ ማስታወሳችን እምነታችን እንዲጠናከር ያደርጋል።—1 ቆሮ. 1:26-29

18. የምናስጠናው ሰው ደቀ መዝሙር እንዲሆን መርዳት እንደማንችል የሚሰማን ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን?

18 ‘መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናው ሰው ደቀ መዝሙር እንዲሆን መርዳት አልችል ይሆናል’ የሚለውን ፍርሃትስ ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ምግብ ከማብሰል የተለየ እንደሆነ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፤ አንድ ምግብ ጣፋጭ መሆን አለመሆኑ በዋነኝነት የተመካው ምግቡን በሚያዘጋጀው ግለሰብ ላይ ነው። አንድን ሰው ደቀ መዝሙር ማድረግ ግን በእኛ ጥረት ላይ ብቻ የተመካ አይደለም። ግለሰቡን ወደራሱ የሚስበው ይሖዋ ስለሆነ ትልቁን ሚና የሚጫወተው እሱ ነው። (ዮሐ. 6:44) እኛም ሆንን ሌሎች የጉባኤ አባላት ደግሞ በማስተማር ጥበብ በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠናው ሰው እድገት እንዲያደርግ ለመርዳት የተቻለንን ያህል ጥረት እናደርጋለን። (2 ጢሞቴዎስ 2:15ን አንብብ።) በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪው ያወቀውን ነገር በተግባር ማዋል ይኖርበታል። (ማቴ. 7:24-27) አንድ ግለሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱን ማቆሙ ያሳዝነን ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠኑ ሰዎች ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ብንመኝም እያንዳንዱ ግለሰብ ‘ስለ ራሱ ለአምላክ መልስ እንደሚሰጥ’ እናውቃለን።—ሮም 14:12

ምን በረከቶች እናገኛለን?

19-21. (ሀ) ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስጠናት ምን ጥቅሞች እናገኛለን? (ለ)  ይሖዋ በስብከቱ ሥራ ለሚካፈሉ ሁሉ ምን አመለካከት አለው?

19 ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ትኩረታችን የአምላክን መንግሥት በማስቀደም ላይ እንዲሆን ይረዳናል። ከዚህም በላይ የአምላክ ቃል እውነት በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲቀረጽ ያደርጋል። እንዴት? ባራክ የተባለ አቅኚ እንዲህ ብሏል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት የአምላክን ቃል በደንብ እንድታጠኑ ያደርጋችኋል። አንድን ሰው በሚገባ ማስተማር እንድችል አስቀድሜ የራሴን እምነት ማጠናከር አለብኝ።”

20 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሌለህ አገልግሎትህ በአምላክ ፊት ከንቱ ነው ማለት ነው? በጭራሽ! ይሖዋ እሱን ለማወደስ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። በስብከቱ ሥራ የምንካፈል ሁሉ “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።” ይሁንና ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በምናስጠናበት ጊዜ አምላክ የዘራነውን ዘር እንዴት እንዳሳደገው መመልከት ስለምንችል ተጨማሪ ደስታ እናገኛለን። (1 ቆሮ. 3:6, 9) ኤሚ የተባለች አቅኚ እንደሚከተለው ብላለች:- “አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እድገት ሲያደርግ ስትመለከቱ ይሖዋ ለግለሰቡ ድንቅ ስጦታ ለመስጠት ይኸውም አምላክን የማወቅና የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲኖረው ለመርዳት ስለተጠቀመባችሁ ይሖዋን ከልባችሁ ለማመስገን ትገፋፋላችሁ።”

21 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመርና ጥናቱ እንዲቀጥል ለማድረግ የተቻለንን ያህል መጣራችን በአሁኑ ጊዜ አምላክን በማገልገል ላይ እንድናተኩር የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ከጥፋት ተርፎ ወደ አዲሱ ዓለም የመግባት ተስፋችንን ያጠናክርልናል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በሚሰጠን እርዳታ እየታገዝን የሚሰሙን ሰዎች እንዲድኑ መርዳት እንችል ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16ን አንብብ።) ይህ እንዴት የሚያስደስት ነገር ነው!

ታስታውሳለህ?

• አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዳይመሩ እንቅፋት የሚሆኑባቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

• በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ሰዎች ለሃይማኖት ግድ የለሾች ቢሆኑ ምን ማድረግ እንችላለን?

• የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ምን በረከቶችን እናጭዳለን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት በተለያዩ የስብከት ዘዴዎች ትጠቀማለህ?