በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ያስተማረው ነገር አመለካከትህን ይቅረጸው

ኢየሱስ ያስተማረው ነገር አመለካከትህን ይቅረጸው

ኢየሱስ ያስተማረው ነገር አመለካከትህን ይቅረጸው

“አምላክ የላከው የአምላክን ቃል ይናገራል።”—ዮሐ. 3:34

1, 2. ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ያስተማራቸው ነገሮች ከምን ጋር ሊወዳደሩ ይችላሉ? የኢየሱስ ትምህርት ‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተመሠረተ ነው እንድንል የሚያደርገን ምንድን ነው?

ስታር ኦቭ አፍሪካ የተባለው ባለ 530 ካራት አልማዝ በትልቅነታቸው ከሚታወቁት አልማዞች አንዱ ነው። ይህ የከበረ ድንጋይ በጣም ውድ ነገር እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም! ይሁንና ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ያስተማራቸው መንፈሳዊ ነገሮች ከዚህ የከበረ ድንጋይ የበለጠ ውድ ናቸው። ይህ መሆኑ ምንም አያስገርምም፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ያስተማራቸው ነገሮች ከይሖዋ የተገኙ ናቸው! መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “አምላክ የላከው የአምላክን ቃል ይናገራል” ብሏል።—ዮሐ. 3:34-36

2 ኢየሱስ በተራራ ላይ ሆኖ ያቀረበው ንግግር የወሰደው ጊዜ ከግማሽ ሰዓት ያነሰ ሊሆን ቢችልም ከስምንት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ 21 ጥቅሶችን ይዟል። ከዚህ ለማየት እንደምንችለው የኢየሱስ ትምህርት ሙሉ በሙሉ ‘በአምላክ ቃል’ ላይ የተመሠረተ ነበር። የአምላክ ተወዳጅ ልጅ በተራራ ላይ ሆኖ ባቀረበው ግሩም ንግግር ላይ ከጠቀሳቸው በዋጋ የማይተመኑ በርካታ ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹን እንዴት በተግባር ማዋል እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

“በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር እርቅ ፍጠር”

3. ኢየሱስ ተቆጥቶ መቆየት ስለሚያስከትለው መዘዝ ደቀ መዛሙርቱን ካስጠነቀቀ በኋላ ምን ምክር ሰጥቷል?

3 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ስላለን ደስተኞችና ሰላማውያን ነን፤ ምክንያቱም ደስታና ሰላም የአምላክ መንፈስ ፍሬ ናቸው። (ገላ. 5:22, 23) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሰላማቸውንና ደስታቸውን እንዲያጡ ስላልፈለገ ለረጅም ጊዜ ተቆጥቶ መቆየት የሚያስከትለው ጉዳት ወደ ሞት ሊመራ እንደሚችል አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴዎስ 5:21, 22ን አንብብ።) ቀጥሎም እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲያው መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ፤ በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር እርቅ ፍጠር፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።”ማቴ. 5:23, 24

4, 5. (ሀ) በ⁠ማቴዎስ 5:23, 24 ላይ ኢየሱስ የገለጸው “መባ” ምን ያመለክታል? (ለ) ቅር ከተሰኘብን ወንድማችን ጋር እርቅ መፍጠራችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

4 ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው “መባ” ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚቀርበውን ማንኛውንም መሥዋዕት ያመለክታል። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ሕዝቦች ለእሱ የሚያቀርቡት አምልኮ የእንስሳት መሥዋዕትንም ይጨምር ስለነበር እንዲህ ያለው መሥዋዕት አስፈላጊ ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር እንዳለ ገልጿል፤ ለአምላክ መባ ከማቅረባችን በፊት ቅር ከተሰኘብን ወንድማችን ጋር እርቅ መፍጠር ይኖርብናል።

5 ‘እርቅ መፍጠር’ ሲባል ‘መታረቅ ወይም መስማማት’ ማለት ነው። ታዲያ ኢየሱስ ከሰጠው ከዚህ ምክር ምን ትምህርት እናገኛለን? ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም። (1 ዮሐ. 4:20) በእርግጥም በጥንት ጊዜ አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ካልነበረው ለአምላክ የሚያቀርባቸው መሥዋዕቶች ዋጋ ቢስ ይሆኑ ነበር።—ሚክያስ 6:6-8ን አንብብ።

ትሕትና ማሳየታችን አስፈላጊ ነው

6, 7. ቅር ከተሰኘብን ወንድማችን ጋር ሰላም ለመፍጠር በምንጥርበት ጊዜ ትሕትና ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

6 ቅር ከተሰኘብን ወንድማችን ጋር እርቅ መፍጠር ትሕትና እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ትሑት የሆኑ ሰዎች መብታቸው እንደሆነ የሚሰማቸውን ነገር ለማስከበር ሲሉ ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር አይጨቃጨቁም ወይም አይጣሉም። እንዲህ ማድረግ በወንድሞች መካከል ጥሩ መንፈስ እንዳይኖር ያደርጋል። በጥንቷ ቆሮንቶስ ይኖሩ በነበሩት ክርስቲያኖች መካከል በአንድ ወቅት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ሁኔታ አስመልክቶ የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ጽፏል፦ “እርስ በርስ ተካሳችሁ ፍርድ ቤት መሄዳችሁ ለእናንተ ትልቅ ሽንፈት ነው። ከዚህ ይልቅ እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም? ደግሞስ እናንተ ራሳችሁ ብትታለሉ አይሻልም?”—1 ቆሮ. 6:7

7 ኢየሱስ ወደ ወንድማችን የምንሄድበት ዓላማ እኛ ትክክለኛ እንደሆንን እና እሱ እንደተሳሳተ ለማሳመን እንደሆነ አልተናገረም። ዓላማችን እንደቀድሞው ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ለማድረግ መሆን ይኖርበታል። ከወንድማችን ጋር ሰላም ለመፍጠር ስሜታችንን በግልጽ መናገር አለብን። የወንድማችንም ስሜት እንደተጎዳ ማመን ይገባናል። ስህተት ሠርተን ከሆነ ደግሞ በትሕትና ይቅርታ ለመጠየቅ እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም።

“ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ”

8. ኢየሱስ በ⁠ማቴዎስ 5:29, 30 ላይ የሰጠውን ምክር ዋና ሐሳብ ተናገር።

8 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ግሩም ምክር ሰጥቷል። ፍጹማን ባለመሆናችን ምክንያት የሰውነታችን ክፍሎች አደገኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን እንደሚችሉ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። በመሆኑም እንዲህ ብሏል፦ “ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው። መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም ከሚወረወር ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል። እንዲሁም ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቆርጠህ ጣለው። መላ ሰውነትህ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ ክፍሎች አንዱን ብታጣ ይሻልሃል።”ማቴ. 5:29, 30

9. ‘ዓይናችን’ ወይም ‘እጃችን ሊያሰናክሉን’ የሚችሉት እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ በተናገረው ሐሳብ ላይ “ዓይን” በአንድ ነገር ላይ ትኩረት የማድረግ ችሎታችንን የሚያመለክት ሲሆን “እጅ” ደግሞ በእጃችን የምናከናውናቸውን ነገሮች ይወክላል። ጥንቃቄ ካላደረግን እነዚህ የሰውነታችን ክፍሎች ‘ሊያሰናክሉን’ እና ‘አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር እንዳናደርግ’ እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። (ዘፍ. 5:22፤ 6:9) እንግዲያው የይሖዋን ትእዛዝ እንድንጥስ ስንፈተን በምሳሌያዊ ሁኔታ ዓይንን የማውጣት ወይም እጅን የመቁረጥ ያህል ከባድ የሆነ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል።

10, 11. ከጾታ ብልግና ለመራቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

10 ዓይናችን በሥነ ምግባር በረከሰ ነገር ላይ እንዳያተኩር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ፈሪሃ አምላክ የነበረው ኢዮብ “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ” ብሎ ነበር። (ኢዮብ 31:1) ኢዮብ ባለትዳር የነበረ ሲሆን አምላክ በሥነ ምግባር ረገድ ያወጣውን ሕግ ላለመጣስ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። እኛም ባለትዳርም ሆንን ያላገባን እንደ ኢዮብ ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ከጾታ ብልግና ለመራቅ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ መመራት ይኖርብናል፤ ይህ መንፈስ አምላክን የሚወዱ ሰዎች ራስን የመግዛት ባሕርይ እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።—ገላ. 5:22-25

11 ከጾታ ብልግና ለመራቅ እንዲህ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ዓይኔ፣ በመጻሕፍት ወይም በቴሌቪዥን አሊያም በኢንተርኔት ላይ በቀላሉ የሚገኙትን የሥነ ምግባር ብልግና የሚንጸባረቅባቸው ነገሮች የመመልከት ፍላጎት እንዲቀሰቀስብኝ እንዲያደርገኝ እፈቅዳለሁ?’ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደሚከተለው በማለት የተናገረውን ሐሳብም እናስታውስ፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአት ደግሞ በተግባር ሲፈጸም ሞትን ያስከትላል።” (ያዕ. 1:14, 15) ራሱን ለአምላክ የወሰነ ማንኛውም ግለሰብ የሥነ ምግባር ብልግና ለመፈጸም በማሰብ ተቃራኒ ጾታ ያለውን ሰው “በምኞት የሚመለከት” ከሆነ ዓይኑን አውጥቶ የመጣል ያህል ከባድ የሆነ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል።—ማቴዎስ 5:27, 28ን አንብብ።

12. ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም የሚገፋፋንን ምኞት ለማሸነፍ የሚረዳን የትኛው የጳውሎስ ምክር ነው?

12 እጃችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀም ይሖዋ በሥነ ምግባር ረገድ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ጥሰን ከባድ ኃጢአት እንድንሠራ ሊያደርገን ስለሚችል የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት የሰጠውን ምክር መከተል ይገባናል፦ “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።” (ቆላ. 3:5) እዚህ ላይ “ግደሉ” የሚለው ቃል ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም የሚገፋፋንን ሥጋዊ ፍላጎት ለማሸነፍ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንዳለብን የሚያጎላ ነው።

13, 14. የብልግና አስተሳሰብንና ድርጊትን ማስወገድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 አንድ ሰው ሕይወቱን ለማትረፍ ሲል እጁን ወይም እግሩን በቀዶ ጥገና ለመቆረጥ ፈቃደኛ እንደሚሆን የታወቀ ነው። እኛም የይሖዋን ሞገስ ሊያሳጣን የሚችል የብልግና አስተሳሰብን ወይም ድርጊትን ለማስወገድ ስንል በምሳሌያዊ ሁኔታ ዓይናችንን አውጥተን ወይም እጃችንን ቆርጠን ‘መጣላችን’ በጣም አስፈላጊ ነው። በገሃነም ከተመሰለው ዘላለማዊ ጥፋት ማምለጥ የምንችለው በአስተሳሰብ፣ በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆነን ከኖርን ብቻ ነው።

14 ከአዳም በወረስነው ኃጢአትና አለፍጽምና የተነሳ የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን ጠብቀን መኖር ጥረት ይጠይቃል። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ እኔ ራሴ በሆነ መንገድ ተቀባይነት እንዳላጣ ሰውነቴን እየጎሰምኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ።” (1 ቆሮ. 9:27) እንግዲያው ኢየሱስ ሥነ ምግባርን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር በተግባር ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ለክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አድናቆት እንደሌለን የሚያሳይ አካሄድ ፈጽሞ ላለመከተል እንጠንቀቅ።—ማቴ. 20:28፤ ዕብ. 6:4-6

“ሰጪዎች ሁኑ”

15, 16. (ሀ) ኢየሱስ ሰጪ በመሆን ረገድ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው? (ለ) በ⁠ሉቃስ 6:38 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው?

15 ኢየሱስ ያስተማራቸው ነገሮችና እሱ የተወልን ተወዳዳሪ የሌለው ምሳሌ የልግስና መንፈስን የሚያበረታታ ነው። ክርስቶስ፣ ፍጽምና ለጎደላቸው የሰው ልጆች ጥቅም ሲል ወደ ምድር በመምጣት ታላቅ ልግስና አሳይቷል። (2 ቆሮንቶስ 8:9ን አንብብ።) ኢየሱስ በሰማይ ያለውን ክብሩን ትቶ ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣት ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ዘሮች ሕይወቱን ለመስጠት ፈቃደኛ ሆኗል፤ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የአምላክን መንግሥት ከእሱ ጋር አብረው በመውረስ በሰማይ ባለጸጋ ይሆናሉ። (ሮም 8:16, 17) ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት እኛም ለጋስ እንድንሆን አበረታቷል፦

16 “ሰጪዎች ሁኑ፤ ሰዎችም ይሰጧችኋል። ተትረፍርፎ እስኪፈስ ድረስ በተጠቀጠቀና በተነቀነቀ ጥሩ መስፈሪያ ሰፍረው በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል። ምክንያቱም በምትሰፍሩበት መስፈሪያ መልሰው ይሰፍሩላችኋል።” (ሉቃስ 6:38) በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች መደረቢያቸውን አጠፍ አድርገው እንደ መያዣ በመጠቀም የገዙትን ዕቃ በዚያ የመሸከም ልማድ ነበራቸው፤ ‘በእቅፋችሁ ይሰጧችኋል’ የሚለው ሐሳብ ይህንን ልማድ የሚያመለክት ነው። ከልብ የመነጨ ልግስና ማሳየታችን እኛም በምላሹ በጥሩ መስፈሪያ እንዲሰፈርልን ሊያደርግ ይችላል፤ ምናልባትም ችግር ላይ በምንሆንበት ጊዜ ሌሎች ልግስና ሊያሳዩን ይችላሉ።—መክ. 11:2 NW

17. ይሖዋ በመስጠት ረገድ ግሩም ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው? ደስታ የሚያስገኝልን እንዴት ዓይነት የሰጪነት መንፈስ ነው?

17 ይሖዋ በደስታ የሚሰጡ ሰዎችን ይወዳቸዋል እንዲሁም ይባርካቸዋል። ይሖዋ “በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል” የሚወደውን አንድያ ልጁን በመስጠት ግሩም ምሳሌ ሆኖልናል። (ዮሐ. 3:16) ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጥቂት የሚዘራ ጥቂት እንደሚያጭድ፣ በብዛት የሚዘራ ደግሞ በብዛት እንደሚያጭድ አስታውሱ። አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።” (2 ቆሮ. 9:6, 7) ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ቁሳዊ ሀብታችንን እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ መስጠታችን ደስታ እንዲሁም የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያስገኝልን ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 19:17ን እና ሉቃስ 16:9ን አንብብ።

‘መለከት አታስነፉ’

18. በሰማይ ከሚኖረው አባታችን “ምንም ብድራት” እንዳናገኝ የሚያደርገን ምን ዓይነት ዝንባሌ ነው?

18 “ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ በሰማያት ካለው አባታችሁ ምንም ብድራት አታገኙም።” (ማቴ. 6:1) ኢየሱስ “ጽድቅ” ሲል ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ድርጊትን ማመልከቱ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት ስላዘዛቸው ከላይ ያለውን ሐሳብ ሲናገር ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ድርጊቶችን ፈጽሞ በሰዎች ፊት ማከናወን እንደሌለባቸው መግለጹ አልነበረም። (ማቴ. 5:14-16) ሆኖም በቲያትር ቤት መድረክ ላይ እንዳሉ ተዋናዮች አንድን ነገር የምናከናውነው ‘ሰዎች እንዲያዩን’ እና እንዲያደንቁን ብለን ከሆነ ከሰማዩ አባታችን “ምንም ብድራት” አናገኝም። እንዲህ ያለ ዝንባሌ ካለን ከአምላክ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረትም ሆነ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ዘላለማዊ በረከት ማግኘት አንችልም።

19, 20. (ሀ) ኢየሱስ “ምጽዋት” በምንሰጥበት ጊዜ ‘መለከት ማስነፋት’ እንደሌለብን ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? (ለ) ቀኝ እጃችን የሚያከናውነውን ግራ እጃችን እንዳያውቅ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

19 ትክክለኛ አመለካከት ካለን የሚከተለውን የኢየሱስን ምክር በተግባር እናውላለን፦ “ምጽዋት በምትሰጡበት ጊዜ በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለው በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ ከፊታቸው መለከት እንደሚያስነፉ ግብዞች አትሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነሱ ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴ. 6:2) “ምጽዋት” የሚለው ቃል ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጥ እርዳታን ያመለክታል። (ኢሳይያስ 58:6, 7ን አንብብ።) ኢየሱስና ሐዋርያቱ ለድሆች ምጽዋት ይሰጡ ነበር። (ዮሐ. 12:5-8፤ 13:29) ለድሆች ምጽዋት የሚሰጡ ሰዎች ቃል በቃል ከፊታቸው መለከት ስለማያስነፉ ኢየሱስ “ምጽዋት” በምንሰጥበት ጊዜ ‘መለከት ማስነፋት’ እንደሌለብን ሲናገር ግነት የተባለውን ዘይቤያዊ አነጋገር መጠቀሙ እንደነበር ግልጽ ነው። ፈሪሳውያን ያደርጉት እንደነበረው እኛም ለሰዎች ምጽዋት እንደሰጠን ማውራት የለብንም። እነዚህ ሰዎች ስለ ሰጡት ስጦታ “በምኩራቦችና በጎዳናዎች ላይ” ያስነግሩ ስለነበር ኢየሱስ ግብዞች ሲል ጠርቷቸዋል። ግብዝ የሆኑት እነዚህ ሰዎች “ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል።” ይሖዋ ለእነዚህ ፈሪሳውያን ምንም ነገር ስለማይሰጣቸው የሚቀበሉት ብድራት ቢኖር የሰዎችን አድናቆትና በምኩራብ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑ ረቢዎች አጠገብ የፊት ወንበር ማግኘት ብቻ ነው። (ማቴ. 23:6) ታዲያ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ምን ማድረግ ነበረባቸው? ኢየሱስ እንዲህ ብሏቸዋል፦

20 “አንተ ግን ምጽዋት ስትሰጥ ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ፤ ምጽዋትህ በስውር ይሁን፤ በስውር የሚያይ አባትህ መልሶ ይከፍልሃል።” (ማቴ. 6:3, 4) ይህ ምክር ለእኛም ይሠራል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሥራ ስንሠራ የምንጠቀመው በሁለቱም እጆቻችን ነው። ስለዚህ ቀኝ እጃችን የሚሠራውን ግራ እጃችን እንዳያውቀው ማድረግ ሲባል የምናደርገውን ልግስና ሌሎች እንዲያውቁልን ማድረግ አያስፈልገንም ማለት ነው፤ ሌላው ቀርቶ የግራ እጃችን ለቀኝ እጃችን ቅርብ የሆነውን ያህል በጣም የምንቀርባቸው ሰዎችም እንኳ ያደረግነውን ነገር እንዲያውቁልን ማድረግ አያስፈልገንም።

21. ‘በስውር የሚያየን’ አባታችን የሚሰጠን ክፍያ የትኞቹን ነገሮች ይጨምራል?

21 ለሌሎች ስለምናደርገው ልግስና በጉራ የማንናገር ከሆነ ‘ምጽዋታችን’ በስውር የተሰጠ ይሆናል። እንዲህ ስናደርግ ‘በስውር የሚያየው’ አባታችን መልሶ ይከፍለናል። ሰዎች ሊያዩት በማይችሉት ሁኔታ በሰማይ የሚኖረው አባታችን ከሰው ልጆች አመለካከት አንጻር “ስውር” ነው። (ዮሐ. 1:18) ‘በስውር የሚያየን’ አባታችን ከእሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንድንመሠርት በማድረግ፣ ኃጢአታችንን ይቅር በማለትና የዘላለም ሕይወት በመስጠት መልሶ ይከፍለናል። (ምሳሌ 3:32 የ1954 ትርጉም፤ ዮሐ. 17:3፤ ኤፌ. 1:7) ይህ ደግሞ የሰዎችን አድናቆት ከማትረፍ ምንኛ የተሻለ ነው!

ልናደንቃቸው የሚገቡ ውድ ትምህርቶች

22, 23. ኢየሱስ ላስተማራቸው ነገሮች አድናቆት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

22 በእርግጥም የተራራው ስብከት እንደከበረ ድንጋይ ውድ የሆኑ በርካታ መንፈሳዊ ትምህርቶችን ይዟል። ይህ ስብከት፣ በመከራ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥም እንኳ ደስተኞች እንድንሆን የሚረዱን በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ትምህርቶችን እንደያዘ ምንም ጥያቄ የለውም። አዎን፣ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች የምናደንቅ እንዲሁም አመለካከታችንንና ሕይወታችንን እንዲቀርጹት የምንፈቅድ ከሆነ ደስተኞች እንሆናለን።

23 ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች “ሰምቶ በተግባር የሚያውል ሁሉ” ይባረካል። (ማቴዎስ 7:24, 25ን አንብብ።) እንግዲያው የኢየሱስን ምክር በተግባር ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ያስተማራቸውን ተጨማሪ ነጥቦች በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ እንመረምራለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ቅር ከተሰኘብን ወንድማችን ጋር እርቅ መፍጠራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ‘ቀኝ ዓይናችን’ እንዳያሰናክለን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

• መስጠትን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅር ከተሰኘብን የእምነት ባልንጀራችን ጋር ‘እርቅ መፍጠራችን’ ምንኛ ደስ ያሰኛል!

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በደስታ የሚሰጡ ሰዎችን ይባርካል