በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት​—ክብር ያለው፣ መጠነኛና አምላክን የሚያስደስት

የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት​—ክብር ያለው፣ መጠነኛና አምላክን የሚያስደስት

የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት​—ክብር ያለው፣ መጠነኛና አምላክን የሚያስደስት

አካባቢው የሐዘን ድባብ አጥልቶበታል። ለየት ያለ ጥቁር ልብስ የለበሱ ሐዘንተኞች መሬት ላይ እየተንደባለሉ አምርረው ያለቅሳሉ። የሙዚቃውን ምት ተከትለው የሚጨፍሩ ሰዎች አሉ። ሌሎች ደግሞ ሲበሉና ሲጠጡ፣ ጮክ ብለው ሲስቁ እንዲሁም ሲፈነጥዙ ይታያሉ። አንዳንዶች እንደ ልብ በቀረበው ወይንና ቢራ ሰክረው መሬት ላይ ተዘርረዋል። ይህ ሁሉ የሚከናወነው በምን ዓይነት ሥነ ሥርዓት ላይ ነው? በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሟቹን ለመሰናበት በሚሰበሰቡበት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማየት የተለመደ ነው።

በአብዛኞቹ ማኅበረሰቦች ውስጥ ሰዎች በአጉል እምነት የተተበተቡ ከመሆናቸውም ሌላ ሙታንን አጥብቀው ይፈራሉ። የብዙዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ዘመዶችና ጎረቤቶችም እንዲህ ያለው እምነት ተጽዕኖ ያደርግባቸዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ አንድ ሰው ሲሞት በሕይወት ያሉትን መጥቀምም ሆነ መጉዳት የሚችል መንፈስ እንደሚሆን ያምናሉ። እንዲህ ያለው እምነት በአብዛኞቹ የቀብር ልማዶች ላይ ይንጸባረቃል። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ሲሞት ሐዘንን መግለጽ ያለ ነገር ነው። ኢየሱስም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ የሚወዷቸው ሰዎች ሲሞቱ አልቅሰዋል። (ዮሐ. 11:33-35, 38፤ ሥራ 8:2፤ 9:39) ይሁንና በወቅቱ ይደረግ እንደነበረው ሐዘናቸውን የገለጹበት መንገድ ቅጥ ያጣ አልነበረም። (ሉቃስ 23:27, 28፤ 1 ተሰ. 4:13) ለምን? አንዱ ምክንያት ሞትን በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት የነበራቸው መሆኑ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ሲል በግልጽ ይናገራል፦ “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ . . . ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቶአል፤ . . . ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለም።” (መክ. 9:5, 6, 10) በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ ጥቅስ የሞተ ሰው ምንም እንደማያውቅ በግልጽ ያሳያል። የሞተ ሰው ማሰብ፣ መናገር ወይም መረዳት አይችልም፤ እንዲሁም ምንም ነገር አይሰማውም። ክርስቲያኖች ይህን አስፈላጊ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መረዳታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት በሚያከናውኑበት ጊዜ ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይገባል?

‘ርኩስ የሆነውን ነገር መንካት አቁሙ’

የይሖዋ ምሥክሮች ብሔራቸውም ሆነ የአካባቢያቸው ባሕል ምንም ይሁን ምን፣ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለና ሙታን በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊጠቅሙ ወይም ሊጎዱ እንደሚችሉ ከሚገልጸው እምነት ጋር ከተያያዙ ልማዶች በሙሉ ይርቃሉ። ከቀብር በኋላ የሚዘጋጅ ድግስና ጭፈራን፣ ተዝካርን፣ ለሙታን መሥዋዕት ማቅረብን እንዲሁም የትዳር ጓደኛቸው የሞተባቸው ሰዎች ከሟቹ ዘመዶች ጋር የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ወይም ለወራት ሰውነታቸውን ሳይታጠቡ እንዲቆዩ ማድረግን የመሳሰሉት ልማዶች ሁሉ ነፍስ ወይም መንፈስ አይሞትም ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ የአጋንንት ትምህርት ጋር የተያያዙ ናቸው። በዚህም ምክንያት እነዚህ ልማዶች ርኩስ ከመሆናቸውም ሌላ አምላክ አይደሰትባቸውም። (ሕዝ. 18:4) እውነተኛ ክርስቲያኖች “‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል [ስለማይችሉ]” እንደነዚህ ካሉት ልማዶች ይርቃሉ። (1 ቆሮ. 10:21) “ራሳችሁን ለዩ . . . ርኩስ የሆነውንም ነገር መንካት አቁሙ” የሚለውን መመሪያ ይታዘዛሉ። (2 ቆሮ. 6:17) ይሁንና እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰድ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም።

በአፍሪካና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ሰዎች አንዳንድ ባሕሎችን ካልተከተሉ የሙታን መንፈስ እንደሚቆጣ በስፋት ይታመናል። እንዲህ ያሉ ባሕሎችን አለመከተል በማኅበረሰቡ ላይ ርግማን ወይም መጥፎ ነገር የሚያስከትል ከባድ ጥፋት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ብዙ የይሖዋ ሕዝቦች ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ከኅብረተሰቡ ወይም ከዘመዶቻቸው ነቀፋና ስድብ ያስከተለባቸው ከመሆኑም ሌላ እንደ ባዕድ ተቆጥረው ተገልለዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ማኅበረሰቡን እንደሚጠሉና ሙታንን እንደማያከብሩ ተደርገው ተወንጅለዋል። አንዳንድ ጊዜ የማያምኑ ሰዎች በኃይል ተጠቅመው የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት እነሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዲከናወን አድርገዋል። ታዲያ አምላክን የማያስደስቱ የቀብር ልማዶችን በጥብቅ ከሚከተሉ ሰዎች ጋር ግጭት እንዳይፈጠር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህም በላይ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሹ ከሚችሉ ርኩስ የሆኑ ሥነ ሥርዓቶችና ድርጊቶች ለመራቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

አቋማችሁን በግልጽ አሳውቁ

በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች የአገር ሽማግሌዎችና የሩቅ ዘመዶች የአንድን ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓት በተመለከተ በሚደረጉት ውሳኔዎች ላይ መካፈላቸው የተለመደ ነገር ነው። በመሆኑም አንድ ታማኝ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲያዘጋጁና እንዲያከናውኑ እንደሚፈልግ በግልጽ ማሳወቅ ይኖርበታል። (2 ቆሮ. 6:14-16) በአንድ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚከናወነው ነገር የእምነት ባልንጀሮቹን ሕሊና የሚረብሽ ወይም የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሙታን ምን ብለው እንደሚያምኑና እንደሚያስተምሩ የሚያውቁ ሰዎችን የሚያሰናክል ሊሆን አይገባም።

የክርስቲያን ጉባኤ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲያከናውን ከተጠየቀ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሥነ ሥርዓቱ ቅዱሳን መጻሕፍት በሚሰጡት መመሪያ መሠረት እንዲከናወን በሐዘን ላይ ላሉት ክርስቲያኖች ጠቃሚ ምክር ይሰጧቸዋል፤ እንዲሁም ከቀብር ሥርዓት ጋር የተያያዙ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን መገንዘብ እንዲችሉ ይረዷቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ርኩስ የሆኑ ልማዶችን ማከናወን የሚፈልጉ ከሆነ ጥብቅ መሆናችንና ክርስቲያናዊ አቋማችንን በድፍረት ሆኖም ደግነትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ማስረዳታችን አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥ. 3:15) ያም ሆኖ የማያምኑ ዘመዶች በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ልማዶች ካልተካተቱ ብለው ቢያስቸግሩስ? በዚህ ጊዜ አማኝ የሆኑት የቤተሰብ አባላት በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ላለመገኘት ይወስኑ ይሆናል። (1 ቆሮ. 10:20) እንዲህ ያለው ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ በሚወዱት ሰው ሞት ከልባቸው ያዘኑትን የቤተሰብ አባላት “ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ” ለማጽናናት በመንግሥት አዳራሽ ወይም በሌላ አመቺ ቦታ የቀብር ንግግር እንዲቀርብ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል። (ሮሜ 15:4) እንደዚህ ባለው ዝግጅት ላይ የሟቹ አስከሬን ባይኖርም ሥነ ሥርዓቱ የተከበረና ተቀባይነት ያለው ነው። (ዘዳ. 34:5, 6, 8) አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ደግነት በጎደለው መንገድ ጣልቃ መግባታቸው በሐዘንተኞቹ ላይ ውጥረት ሊጨምርባቸውና ሐዘናቸውን ሊያባብሰው ይችላል፤ ይሁን እንጂ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ ሊሰጠን የሚችለው አምላክ ትክክል የሆነውን ለማድረግ የወሰድነውን ቁርጥ እርምጃ አቅልሎ እንደማያየው ማወቃችን ያጽናናናል።—2 ቆሮ. 4:7

አቋማችሁን በጽሑፍ አስፍሩ

አንድ ሰው የራሱን የቀብር ሥርዓት በተመለከተ የሚፈልገውን ነገር በጽሑፍ ማስፈሩ እሱ ከሞተ በኋላ ስለ ቀብሩ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ የቤተሰቡን አባላት ማነጋገር ቀላል እንዲሆን ያደርጋል፤ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሟችን ፍላጎት ያከብራሉ። የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ፣ የት መከናወን እንደሚኖርበት እንዲሁም ሥነ ሥርዓቱን የማደራጀቱና የማስፈጸሙ ኃላፊነት ለማን ሊሰጥ እንደሚገባ በጽሑፍ ማስፈሩ አስፈላጊ ነው። (ዘፍ. 50:5) በምሥክሮች ፊት የተፈረመ እንዲህ ያለ ሰነድ የበለጠ ኃይል ይኖረዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ላይ በተመሠረተ ማስተዋልና ጥበብ የሚመሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ በጠና እስኪታመሙ ወይም በጣም እስኪያረጁ መጠበቅ እንደሌለባቸው ያውቃሉ።—ምሳሌ 22:3፤ መክ. 9:12

አንዳንዶች እንዲህ ያሉ ሐሳቦችን በጽሑፍ ማስፈር ይከብዳቸዋል። ይሁንና አንድ ክርስቲያን እንዲህ ማድረጉ በመንፈሳዊ የጎለመሰና ለሌሎች የሚያስብ ሰው መሆኑን ያሳያል። (ፊልጵ. 2:4) አንድ ሰው፣ ሲሞት ከሚከናወነው የቀብር ሥርዓት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ቤተሰቡ እንዲወስኑ ከመተው ይልቅ እሱ ራሱ አስቀድሞ በመወሰን በጽሑፍ ማስፈሩ በጣም የተሻለ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘን ላይ የወደቁት የቤተሰቡ አባላት ሟቹ የማያምንባቸውንና የማይፈልጋቸውን ርኩስ የሆኑ ልማዶች በቀብር ሥርዓቱ ላይ እንዲያከናውኑ ተጽዕኖ ሊደረግባቸው ይችላል።

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ መጠነኛ እንዲሆን አድርጉ

በአፍሪካ በሚገኙ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ የሙታንን መንፈስ ላለማስቆጣት ሲባል የቀብር ሥነ ሥርዓት ሰፊና ሌሎችን የሚያስደምም መሆን እንዳለበት በስፋት ይታመናል። አንዳንዶች በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታና የኑሮ ደረጃቸውን ለማሳየት በመጣር “ይታይልኝ የሚል መንፈስ” ያንጸባርቃሉ። (1 ዮሐ. 2:16) ለሟቹ “ተገቢ” የሆነ የቀብር ሥርዓት ለማከናወን ሲባል ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚባክን ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ወጪ ይደረጋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ብዙ ሰው በሥርዓቱ ላይ እንዲገኝ ሲባል የሟቹን ምስል የያዙ ፖስተሮች በተለየዩ ቦታዎች ይለጠፋሉ። የሟቹ ፎቶ የተለጠፈባቸው ካናቴራዎች ከተዘጋጁ በኋላ ሐዘንተኞቹ እንዲለብሷቸው ይሰጧቸዋል። ሰዎችን ለማስደመም ሲባል በጣም ውድ የሆኑና በሚያምር መልክ የተሠሩ የሬሳ ሣጥኖች ይገዛሉ። በአንድ የአፍሪካ አገር አንዳንድ ሰዎች ሀብታቸውንና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ለማሳየት ሲሉ የመኪና፣ የአውሮፕላን፣ የጀልባና የሌሎች ነገሮች ቅርጽ ያላቸው የሬሳ ሣጥኖችን ያሠራሉ። አንዳንድ ጊዜ አስከሬኑ ከሬሳ ሣጥኑ እንዲወጣ ይደረግና ባጌጠ አልጋ ላይ ሆኖ ለሕዝብ ይታያል። ሟቿ ሴት ከሆነች ደግሞ ነጭ ቬሎ ያለብሷታል፣ በርከት ያለ ጌጣጌጥና ጨሌዎችን ያደርጉላታል እንዲሁም በመኳኳያ ያሰማምሯታል። ታዲያ የአምላክ ሕዝቦች እንደነዚህ በመሰሉ ድርጊቶች ቢካፈሉ ተገቢ ይሆናል?

ጎልማሳ የሆኑ ክርስቲያኖች የአምላክን መመሪያዎች የማያውቁና በተግባር ለማዋል የማይጥሩ ሰዎች ከሚከተሏቸው ቅጥ ያጡ ልማዶች መራቃቸው የጥበብ አካሄድ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ከመጠን ያለፉና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ባሕሎችና ድርጊቶች ‘በማለፍ ላይ ካለው ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመነጩ እንዳልሆኑ’ እናውቃለን። (1 ዮሐ. 2:15-17) ከሌሎች በልጠን ለመታየት ስንል ክርስቲያናዊ ያልሆነውን የፉክክር መንፈስ እንዳናንጸባርቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። (ገላ. 5:26) ከተሞክሮ እንደታየው ሙታንን መፍራት በአካባቢው ባሕልና በማኅበረሰቡ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ጊዜ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች በአብዛኛው ሰፊ ስለሚሆኑ ከቁጥጥር ውጪ ይሆናሉ። የማያምኑ ሰዎች ለሙታን ከፍተኛ አክብሮት መስጠታቸው ንጹሕ ያልሆኑ ድርጊቶችን ወደመፈጸም ሊመራቸው ይችላል። እንደነዚህ ባሉት የቀብር ሥርዓቶች ላይ ሰዎች ከቁጥጥር ውጪ በመሆን እየጮኹ ያለቅሱ፣ አስከሬኑን ያቅፉ፣ ሟቹን በሕይወት ያለ ይመስል ያዋሩት እንዲሁም ገንዘብና ሌሎች ነገሮችን አስከሬኑ ላይ ያስቀምጡ ይሆናል። በአንድ ክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ቢፈጸሙ በይሖዋ ስምም ሆነ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ነቀፌታ መድረሱ አይቀርም።—1 ጴጥ. 1:14-16

ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በትክክል ማወቃችን የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን በምናዘጋጅበት ጊዜ የዓለምን መንፈስ የሚያንጸባርቅ ማንኛውንም ድርጊት ከመፈጸም ለመራቅ የሚያስችለንን ድፍረት ሊሰጠን ይገባል። (ኤፌ. 4:17-19) ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩ ሰዎች ሁሉ ታላቅና ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሰው ቢሆንም በሞተበት ወቅት የተከናወነው የቀብር ሥነ ሥርዓት ብዙ ሰው ያልተሰበሰበበትና ያልተንዛዛ ነበር። (ዮሐ. 19:40-42) “የክርስቶስ አስተሳሰብ” ያላቸው ሰዎች እንዲህ ዓይነቱ የቀብር ሥርዓት አያሳፍራቸውም። (1 ቆሮ. 2:16) በእርግጥም የክርስቲያኖች የቀብር ሥርዓት ቀለል ያለና መጠነኛ እንዲሆን ማድረግ ከቅዱሳን መጻሕፍት አንጻር ሲታዩ ርኩስ ከሆኑ ልማዶች ለመራቅ ይረዳል፤ እንዲሁም ሥርዓቱ ርጋታ የሰፈነበት፣ ክብር ያለው፣ ደስ የሚልና አምላክን ለሚወዱ ሰዎች የሚገባ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ፈንጠዝያ ሊኖር ይገባል?

በአንዳንድ አካባቢዎች ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤቶችና ሌሎች ሰዎች የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከተፈጸመ በኋላ ለመብላትና ለመጠጣት እንዲሁም ለመዝፈንና ለመጨፈር የመሰባሰብ ልማድ አላቸው። እንደዚህ ባሉት ድግሶች ላይ የሚገኙት ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ያለ ልክ ይጠጣሉ እንዲሁም የሥነ ምግባር ብልግና ይፈጽማሉ። አንዳንዶች እንዲህ ያለው ፈንጠዝያ የሟቹ ቤተሰቦች ሐዘናቸውን እንዲረሱ እንደሚረዳቸው ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ባሕላቸው እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና ብዙዎች እንዲህ ያለው ፈንጠዝያ ሙታንን ለማክበርና ለማወደስ እንዲሁም የሟቹ ነፍስ ከሥጋው ተለይታ ከሞቱ ዘመዶቹ ጋር እንድትሆን ለማድረግ የሚረዳ አስፈላጊ ሥነ ሥርዓት እንደሆነ ያምናሉ።

እውነተኛ ክርስቲያኖች “ሐዘን ከሣቅ ይሻላል፤ ያዘነ ፊት ለልብ መልካም ነውና” የሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ጥበብ ያዘለ መሆኑን ይገነዘባሉ። (መክ. 7:3) ከዚህም በላይ ሕይወት ምን ያህል አጭር መሆኑን ማሰባቸውና በትንሣኤ ተስፋ ላይ በረጋ መንፈስ ማሰላሰላቸው ጠቃሚ እንደሆነ ያውቃሉ። በእርግጥም ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ላላቸው ሰዎች ‘ከልደታቸው ቀን የሞታቸው ቀን ይሻላቸዋል።’ (መክ. 7:1) ስለዚህ ከቀብር ሥነ ሥርዓት በኋላ የሚታየው ፈንጠዝያ ከመናፍስታዊ እምነቶችና ከሥነ ምግባር ብልግና ጋር የተያያዘ በመሆኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ዝግጅቶችን ማድረግ ይቅርና በሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘታቸው እንኳ ተገቢ አይሆንም። አንድ የይሖዋ አገልጋይ ከቀብር ሥነ ሥርዓት በኋላ በሚኖረው ድግስና ፈንጠዝያ ላይ መገኘቱ ለአምላክ አክብሮት እንደሌለው እንዲሁም ለእምነት ባልንጀሮቹ ሕሊና እንደማይጠነቀቅ የሚያሳይ ይሆናል።

ሌሎች ልዩነቱን እንዲያስተውሉ አድርጉ

በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች በተቃራኒ ሙታንን ከመፍራት ነፃ በመሆናችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ዮሐ. 8:32) “የብርሃን ልጆች” እንደመሆናችን መጠን ሐዘናችንን የምንገልጸው መንፈሳዊ ብርሃን እንደበራልን በሚያሳይ ሁኔታ ይኸውም ክብር ባለውና የትንሣኤ ተስፋ እንዳለን በሚያንጸባርቅ መንገድ ሲሆን ቅጥ ያጣ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከማድረግም እንቆጠባለን። (ኤፌ. 5:8፤ ዮሐ. 5:28, 29) የትንሣኤ ተስፋ ስላለን “ተስፋ እንደሌላቸው” ሰዎች ከልክ በላይ እንደምናዝን የሚያሳይ ነገር አናደርግም። (1 ተሰ. 4:13) በተጨማሪም የትንሣኤ ተስፋ በሰው ፍርሃት ሳንሸነፍ ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍ የሚያስችለንን ድፍረት ይሰጠናል።—1 ጴጥ. 3:13, 14

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በታማኝነት መከተላችን ሰዎች አምላክን “በሚያገለግለውና በማያገለግለው መካከል ያለውን ልዩነት [ማየት]” እንዲችሉ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። (ሚል. 3:18) ሞት የሚቀርበት ጊዜ እንደሚመጣ የአምላክ ቃል ይናገራል። (ራእይ 21:4) ይህ ታላቅ ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ ስንጠባበቅ በይሖዋ ዘንድ ቆሻሻና እድፍ የሌለብን ሆነን ለመገኘት እንዲሁም ከዚህ ዓለምና አምላክን ከማያስከብሩ ልማዶች ሙሉ በሙሉ ለመራቅ ጥረት እናድርግ።—2 ጴጥ. 3:14

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስንሞት ምን ዓይነት የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲፈጸምልን እንደምንፈልግ በጽሑፍ ማስፈራችን የጥበብ እርምጃ ነው

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት ክብር ያለውና መጠነኛ ሊሆን ይገባል