በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የግል ምርጫህን ለመተው ፈቃደኛ ነህ?

የግል ምርጫህን ለመተው ፈቃደኛ ነህ?

የግል ምርጫህን ለመተው ፈቃደኛ ነህ?

ሁለት ትናንሽ ልጆች እየተጫወቱ እያለ አንደኛው የሚወደውን መጫወቻ ከጓደኛው በመንጠቅ “የራሴ ነው!” አለው። ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ገና ከትንሽነታቸው ጀምሮ በተወሰነ መጠን የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። (ዘፍ. 8:21፤ ሮም 3:23) ከዚህም በላይ በጥቅሉ ሲታይ ይህ ዓለም የራስ ወዳድነት መንፈስ ያንጸባርቃል። እንዲህ ያለውን መንፈስ ለማስወገድ የራስ ወዳድነት ዝንባሌን መታገል ይኖርብናል። ይህን ካላደረግን ሌሎችን በቀላሉ የምናደናቅፍ ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ጋር ያለን ግንኙነት ሊበላሽ ይችላል።—ሮም 7:21-23

ሐዋርያው ጳውሎስ የምናደርገው ነገር በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ልናስገባ እንደሚገባ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሁሉም ነገር ይጠቅማል ማለት ግን አይደለም። ሁሉም ነገር ተፈቅዷል፤ ሁሉም ነገር ያንጻል ማለት ግን አይደለም።” ጳውሎስ አክሎም “እንቅፋት ከመሆን ተቆጠቡ” ብሏል። (1 ቆሮ. 10:23, 32) እንግዲያው የግል ምርጫችንን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲያጋጥሙን እንደሚከተለው በማለት ራሳችንን መጠየቃችን የጥበብ አካሄድ ነው፦ ‘የጉባኤው ሰላም እንዳይናጋ ስል መብቴ የሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ለመተው ፈቃደኛ ነኝ? የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እንኳ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ?’

ከሥራ ምርጫህ ጋር በተያያዘ

ብዙዎች የሥራ ምርጫቸው በሌሎች ላይ እምብዛም ተጽዕኖ የማያሳድር የግል ውሳኔ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ በደቡብ አሜሪካ በምትገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚኖር በንግድ ሥራ ላይ የተሠማራ አንድ ሰው ያጋጠመውን ሁኔታ እስቲ እንመልከት። ይህ ሰው ቁማርተኛና ሰካራም በመሆኑ ይታወቅ ነበር። ይሁንና ግለሰቡ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና መንፈሳዊ እድገት ያደረገ ሲሆን በአኗኗሩ ላይ ለውጥ መታየት ጀመረ። (2 ቆሮ. 7:1) ይህ ሰው ከጉባኤው ጋር በመሆን በስብከቱ ሥራ ለመካፈል እንደሚፈልግ ሲገልጽ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ስለ ሥራው እንዲያስብበት በዘዴ ነገረው። ግለሰቡ በሚኖርበት ከተማ ውስጥ ከሸንኮራ አገዳ የሚሠራ አልኮል ዋና አከፋፋይ ነበር። ይህ አልኮል በርካታ ጥቅሞች ቢኖሩትም በዚያ አካባቢ በአብዛኛው የሚያገለግለው ከለስላሳ መጠጥ ጋር ተደባልቆ የሚያሰክር መጠጥ ለማዘጋጀት ነው።

ሰውየው እንዲህ ያለውን አልኮል እየሸጠ በስብከቱ ሥራ ቢካፈል በጉባኤው ላይ ነቀፋ እንደሚያስከትልና ከአምላክ ጋር ያለው ዝምድና ሊበላሽ እንደሚችል ተገነዘበ። በመሆኑም የሚያስተዳድረው ትልቅ ቤተሰብ ቢኖረውም አልኮል መሸጡን አቆመ። በአሁኑ ጊዜ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ወረቀት በመሸጥ ነው። በአሁኑ ወቅት ይህ ሰው፣ ባለቤቱ እንዲሁም ከአምስቱ ልጆቻቸው መካከል ሁለቱ የተጠመቁ ሲሆን ምሥራቹን በቅንዓትና በነፃነት ይሰብካሉ።

ከጓደኛ ምርጫህ ጋር በተያያዘ

ከማያምኑ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ በግል ምርጫችን ላይ ተመሥርተን የምንወስነው ነገር ነው? ወይስ በዚህ ረገድ ልንከተለው የሚገባ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት አለ? አንዲት እህት አማኝ ካልሆነ ወጣት ጋር ወደ አንድ ግብዣ ለመሄድ ፈለገች። እንዲህ ማድረጓ አደጋ እንደሚያስከትልባት ቢነገራትም መብቷ እንደሆነ ስለተሰማት ወደ ግብዣው ቦታ ሄደች። በግብዣው ቦታ ላይ የሚያደነዝዝ ዕጽ የተቀላቀለበት መጠጥ ተሰጣት። ይህች እህት ከበርካታ ሰዓታት በኋላ ስትነቃ ጓደኛዬ ያለችው ወጣት እንደደፈራት አወቀች።—ከ⁠ዘፍጥረት 34:2 ጋር አወዳድር።

ከማያምኑ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ሁልጊዜ እንደዚህ ዓይነት አሳዛኝ መዘዝ ያስከትላል ማለት ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ያስጠነቅቃል፦ “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።” (ምሳሌ 13:20) መጥፎ ባልንጀርነት ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ምንም ጥያቄ የለውም! ምሳሌ 22:3 “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ይላል። ጓደኞቻችን ጎጂ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን እንዲሁም ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና እንዲበላሽ ሊያደርጉ ይችላሉ።—1 ቆሮ. 15:33፤ ያዕ. 4:4

ከአለባበስና ከአጋጌጥ ጋር በተያያዘ

ፋሽን በየጊዜው ይለዋወጣል። መጽሐፍ ቅዱስ አለባበስንና አጋጌጥን በተመለከተ የሚሰጠው መመሪያ ግን ምንጊዜም አይለወጥም። ጳውሎስ፣ ክርስቲያን ሴቶችን “በልከኝነትና በማስተዋል ሥርዓታማ በሆነ ልብስ ራሳቸውን እንዲያስውቡ” አሳስቧቸዋል፤ ይህ መመሪያ ለወንዶችም ይሠራል። (1 ጢሞ. 2:9) እዚህ ላይ ጳውሎስ የሚያምር ልብስ መልበስ እንደሌለብን ወይም በአለባበስ ረገድ ሁሉም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ምርጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ መናገሩ አልነበረም። ታዲያ ልከኛ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? አንድ መዝገበ ቃላት ልከኝነት የሚለውን ቃል “ከትዕቢት ወይም ልታይ ልታይ ከማለት መራቅ . . . በአለባበስ፣ በአነጋገር ወይም በድርጊት ሥርዓታማ መሆን” በማለት ፈቶታል።

ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘የራሴን ምርጫ የማድረግ መብት እንዳለኝ በማሰብ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት በሚስብ መንገድ የምለብስ ወይም የማጌጥ ከሆነ በእርግጥ ልከኛ ነኝ ማለት እችላለሁ? አለባበሴ ስለማንነቴ ወይም ስለምመራበት የሥነ ምግባር አቋም የተሳሳተ መልእክት ያስተላልፋል?’ ‘ስለ ራሳችን ጉዳይ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ጉዳይ ትኩረት በመስጠት’ በአለባበስና በአጋጌጥ ረገድ “በምንም መንገድ ማሰናከያ የሚሆን ነገር” ላለማድረግ መጣር ይኖርብናል።—2 ቆሮ. 6:3፤ ፊልጵ. 2:4

ከገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ

በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ሐቀኝነት የጎደለው ወይም የማታለል ድርጊት በተፈጸመበት ወቅት ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “እናንተ ራሳችሁ ብትበደሉ አይሻልም? ደግሞስ እናንተ ራሳችሁ ብትታለሉ አይሻልም?” ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ወንድማቸውን በፍርድ ቤት ከመክሰስ ይልቅ ጥቅማቸው ቢቀርባቸው እንደሚሻል የሚገልጽ ምክር ሰጥቷል። (1 ቆሮ. 6:1-7) በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ወንድም ይህንን ምክር በተግባር አውሏል። ክርስቲያን የሆነ አሠሪው ሊከፍለው ከሚገባው ደሞዝ ጋር በተያያዘ በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። ሁለቱ ወንድሞች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመከተል በተደጋጋሚ ጊዜ ስለ ጉዳዩ ቢነጋገሩም ለችግሩ መፍትሔ ማግኘት አልቻሉም። በመጨረሻም ጉዳዩን ‘ለጉባኤው’ ይኸውም ለክርስቲያን ሽማግሌዎች ተናገሩ።—ማቴ. 18:15-17

ያም ሆኖ ችግሩ ሊፈታ አልቻለም። ተቀጣሪ የሆነው ወንድም በጉዳዩ ላይ አጥብቆ ከጸለየ በኋላ ሊከፈለው እንደሚገባ ከሚያስበው ገንዘብ አብዛኛውን ለመተው ወሰነ። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ይህ ወንድም ከጊዜ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “በመካከላችን የተፈጠረው አለመግባባት ደስታ እያሳጣኝ እንዲሁም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ላውለው የምችለውን ውድ ጊዜ እያባከነብኝ ነበር።” ይህ ወንድም እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ካደረገ በኋላ እንደ ቀድሞው ደስተኛ እንደሆነና ይሖዋም አገልግሎቱን እንደባረከለት ተሰምቶታል።

ትንንሽ በሚመስሉ ጉዳዮች ጭምር

ትንንሽ በሚመስሉ ጉዳዮችም እንኳ የግል ምርጫዬ ካልተከበረ ብለን ድርቅ አለማለታችን በረከት ያስገኝልናል። አቅኚዎች የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በአንድ የአውራጃ ስብሰባ የመጀመሪያው ቀን ላይ ቀደም ብለው በመድረስ የሚፈልጉትን መቀመጫ ያዙ። ፕሮግራሙ ሲጀመር ብዙ ልጆች ያሏቸው አንድ ባልና ሚስት በሰው ወደተሞላው አዳራሽ ገቡና ቦታ መፈለግ ጀመሩ። አቅኚዎቹ ባልና ሚስት፣ ይህ ቤተሰብ በቂ ቦታ እየፈለገ መሆኑን ሲመለከቱ ቦታቸውን ለቀቁላቸው። በመሆኑም ሁሉም የቤተሰቡ አባላት አንድ ላይ መቀመጥ ቻሉ። የአውራጃ ስብሰባው ካለቀ ከጥቂት ቀናት በኋላ አቅኚዎቹ ባልና ሚስት ከዚህ ቤተሰብ የምስጋና ደብዳቤ ደረሳቸው። የዚህ ቤተሰብ አባላት ወደ አውራጃ ስብሰባው አርፍደው በመምጣታቸው በጣም አዝነው የነበረ ቢሆንም አቅኚዎቹ ባልና ሚስት ያሳዩአቸው ደግነት ልባቸው በደስታና በአድናቆት እንዲሞላ ማድረጉን በደብዳቤው ላይ ገልጸዋል።

እንግዲያው አጋጣሚውን ስናገኝ ለሌሎች ጥቅም ስንል የግል ምርጫችንን ለመተው ፈቃደኞች እንሁን። የአምላክ ቃል ፍቅር “የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም” ይላል፤ እንዲህ ዓይነት ፍቅር ማሳየታችን የጉባኤው ሰላም እንዳይናጋ የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ይረዳናል። (1 ቆሮ. 13:5) ከሁሉ በላይ ደግሞ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ያስችለናል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአለባበስ ረገድ የግል ምርጫችንን ለመተው ፈቃደኛ ነን?

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንበርህን ለወንድሞችህ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ነህ?