በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአገልግሎት መጽናት የምትችለው እንዴት ነው?

በአገልግሎት መጽናት የምትችለው እንዴት ነው?

በአገልግሎት መጽናት የምትችለው እንዴት ነው?

በጣም ተስፋ ከመቁረጥህ የተነሳ በስብከቱ ሥራ መካፈልህን ለማቆም አስበህ ታውቃለህ? ከባድ ተቃውሞ፣ ጭንቀት፣ ጤና ማጣት፣ የእኩዮች ተጽዕኖ ወይም የምንሰብክላቸው ሰዎች ጥሩ ምላሽ አለመስጠታቸው በአገልግሎታችን እንዳንጸና እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። ይሁንና ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ አስብ። ኢየሱስ “ከፊቱ ለሚጠብቀው ደስታ ሲል” በጣም ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን በጽናት ተቋቁሟል። (ዕብ. 12:2) ኢየሱስ በአምላክ ላይ የተሰነዘሩት ክሶች መሠረተ ቢስ መሆናቸውን ማረጋገጡ የይሖዋን ልብ እንደሚያስደስት ያውቅ ነበር።—ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም

አንተም በአገልግሎት በመጽናት የይሖዋን ልብ ማስደሰት ትችላለህ። ይሁን እንጂ በአንዳንድ እንቅፋቶች የተነሳ ለመስበክ ኃይል እንደሌለህ ቢሰማህስ? ዕድሜያቸው ከመግፋቱም በላይ የጤንነት ችግሮች ያሉባቸው እህት ክርስቲና እንደሚከተለው ብለዋል፦ “አብዛኛውን ጊዜ የሚደክመኝ ከመሆኑም ሌላ በትካዜ እዋጣለሁ። ጤና ማጣትንና የኑሮ ጭንቀቶችን የመሳሰሉ ከዕድሜ መግፋት ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ለጊዜውም ቢሆን የአገልግሎት ቅንዓቴን ያዳክሙብኛል።” እንዲህ ያሉ እንቅፋቶች ቢኖሩብህም በአገልግሎት መጽናት የምትችለው እንዴት ነው?

ነቢያት የተዉትን ምሳሌ ኮርጅ

ታማኝ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በስብከቱ ሥራ ለመጽናት ከፈለጉ የጥንት ነቢያት የነበራቸው ዓይነት አመለካከት ለማዳበር መጣር ይገባቸዋል። ኤርምያስን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኤርምያስ ነቢይ ሆኖ ሲሾም የተሰጠውን ኃላፊነት ለመቀበል አቅማምቶ ነበር። ያም ሆኖ ኤርምያስ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ በመተማመን የተሰጠውን ከባድ ኃላፊነት ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት በጽናት መወጣት ችሏል።—ኤር. 1:6፤ 20:7-11

ወንድም ሄንሪክ፣ ኤርምያስ ከተወው ምሳሌ ማበረታቻ አግኝተዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “በአገልግሎት ባሳለፍኳቸው ከ70 የሚበልጡ ዓመታት ውስጥ ሰዎች በሚሰጡት ምላሽ እንዲሁም በሚያሳዩት የጥላቻና የግዴለሽነት መንፈስ ተስፋ የቆረጥኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። በእነዚህ ጊዜያት ኤርምያስ የተወውን ምሳሌ ለማስታወስ እጥራለሁ። ይህ ነቢይ ለይሖዋ ፍቅር የነበረው መሆኑና በመንፈሳዊ ጠንካራ መሆኑ በነቢይነት እንዲቀጥል ኃይል ሰጥቶታል።” (ኤር. 1:17) ራፋው የተባሉ ወንድምም ኤርምያስ በተወው ምሳሌ ተበረታተዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ኤርምያስ በራሱና በሚፈልጋቸው ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በአምላክ ይታመን ነበር። በወቅቱ አብዛኞቹ ሰዎች ለእሱ ከፍተኛ ጥላቻ የነበራቸው ቢሆንም በድፍረት መስበኩን ቀጥሏል። እኔም የእሱን ምሳሌ ሁልጊዜ ለማስታወስ እጥራለሁ።”

ብዙ ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው እንዲጸኑ የረዳቸው በምሳሌነት የሚጠቀስ ሌላው ነቢይ ደግሞ ኢሳይያስ ነው። ኢሳይያስ የሚናገረውን መልእክት ወገኖቹ እንደማያዳምጡት አምላክ አስቀድሞ ነግሮታል። ይሖዋ “የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፤ ጆሮአቸውን ድፈን” ብሎታል። ታዲያ የኢሳይያስ ልፋት ከንቱ ነበር ማለት ነው? በፍጹም፣ በአምላክ ዘንድ ዋጋ ነበረው! ኢሳይያስ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል ተልዕኮ ሲሰጠው “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” ብሏል። (ኢሳ. 6:8-10) ይህ ነቢይ የተሰጠውን ተልዕኮ በጽናት ፈጽሟል። አንተስ ምሥራቹን እንድትሰብክ ለተሰጠህ ትእዛዝ እንዲህ ዓይነት ምላሽ ትሰጣለህ?

ሰዎች ለምሥራቹ ግዴለሽ ቢሆኑም ኢሳይያስ እንዳደረገው በአገልግሎታችን ለመጽናት እንድንችል የምንሰብክላቸው ሰዎች በሚሰጡን ጥሩ ያልሆነ ምላሽ ላይ ማተኮር የለብንም። ወንድም ራፋው ተስፋ መቁረጥን ለመቋቋም የሚወስዱትን እርምጃ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ሰዎች በሚሰነዝሩት ደግነት የጎደለው ሐሳብ ላይ ላለማውጠንጠን እጥራለሁ። በክልሌ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የፈለጉትን አስተያየት የመስጠት መብት እንዳላቸው ይሰማኛል።” አናም እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች በሚናገሯቸው ጥሩ ያልሆኑ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ላይ ከማውጠንጠን እቆጠባለሁ። ይህን እንዳደርግ የረዳኝ አገልግሎት ከመውጣቴ በፊት ወደ ይሖዋ መጸለዬና የዕለቱን ጥቅስ ማንበቤ ነው። ይህም አፍራሽ ሐሳቦችን እንዳስወግድ አስችሎኛል።”

ነቢዩ ሕዝቅኤል ያገለገለው በግዞት ወደ ባቢሎን ተወስደው በነበሩት አንገተ ደንዳና አይሁዳውያን መካከል ነበር። (ሕዝ. 2:6) ሕዝቅኤል የአምላክን ቃል ለሕዝቡ ሳይናገር ቢቀርና አንድ ኃጢአተኛ ማስጠንቀቂያውን ሳይሰማ ቢሞት ነቢዩ በዚህ ሰው ሞት ተጠያቂ ይሆን ነበር። ይሖዋ ሕዝቅኤልን “አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ” ብሎታል።—ሕዝ. 3:17, 18

ወንድም ሄንሪክ እንደ ሕዝቅኤል ዓይነት አመለካከት ለማዳበር ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ ብለዋል፦ “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ መሆን እፈልጋለሁ። ውድ የሆነው የሰው ሕይወት አደጋ ላይ ነው።” (ሥራ 20:26, 27) ዝብግንየቭ የተባሉት ወንድምም ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው፦ “ሕዝቅኤል፣ ሰዎች ምንም አሉት ምን በሥራው መቀጠል ነበረበት። ይህን ማወቄ ፈጣሪያችን ለስብከቱ ሥራ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዳዳብር ረድቶኛል።”

ብቻህን አይደለህም

በስብከቱ ሥራ የምትካፈለው ብቻህን አይደለም። እኛም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ማለት እንችላለን። (1 ቆሮ. 3:9) እህት ክርስቲና አልፎ አልፎ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንደሚዋጡ ከተናገሩ በኋላ “በዚህም ምክንያት ይሖዋ ኃይል እንዲሰጠኝ በተደጋጋሚ እለምነዋለሁ። እሱም አሳፍሮኝ አያውቅም” ብለዋል። አዎን፣ በአገልግሎታችን የአምላክ መንፈስ ድጋፍ ያስፈልገናል!—ዘካ. 4:6

በአገልግሎት ስንካፈል መንፈስ ቅዱስ ‘በመንፈስ ፍሬ’ ውስጥ የሚካተቱትን ባሕርያት እንድናዳብርም ይረዳናል። (ገላ. 5:22, 23) ይህ ደግሞ ሰዎች ምንም ዓይነት ምላሽ ቢሰጡን በስብከቱ ሥራ እንድንጸና ያስችለናል። ወንድም ሄንሪክ እንዲህ ብለዋል፦ “በአገልግሎት መካፈሌ ባሕርዬን እንዳሻሻል ረድቶኛል። ትዕግሥተኛና ለሰው አሳቢ መሆንን እንዲሁም በቀላሉ ተስፋ አለመቁረጥን ተምሬያለሁ።” የተለያዩ እንቅፋቶች እያጋጠሙህም በአገልግሎት መጽናትህ የመንፈስ ፍሬን የበለጠ እንድታፈራ ይረዳሃል።

ይሖዋ ልዩ የሆነውን ይህንን ሥራ ለመምራት በመላእክቱ ይጠቀማል። (ራእይ 14:6) መጽሐፍ ቅዱስ፣ እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት “እልፍ ጊዜ እልፍና ሺህዎች ጊዜ ሺህዎች” እንደሆኑ ይናገራል። (ራእይ 5:11) መላእክት በኢየሱስ አመራር ሥር ሆነው በምድር ላይ የሚኖሩትን የአምላክ አገልጋዮች ይደግፋሉ። በአገልግሎት በምትካፈልበት ጊዜ ይህን ታስታውሳለህ?

አና እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎት በምንካፈልበት ጊዜ መላእክት አብረውን እንደሚሆኑ ማስታወሴ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። መላእክት በይሖዋና በኢየሱስ እየተመሩ የሚሰጡንን እርዳታ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ።” ታማኝ ከሆኑት መላእክት ጋር አብሮ መሥራት እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው!

ከሌሎች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ጋር አብረን መሥራታችንስ ለመጽናት የሚረዳን እንዴት ነው? እጅግ ብዙ ከሆኑ ታማኝ ምሥክሮች ጋር መተዋወቅ በመቻላችን ተባርከናል። “ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እውነት መሆኑን አንተም ሳትመለከት አልቀረህም።—ምሳሌ 27:17

ከሌሎች ጋር አብረን ማገልገላችን እኛ የማናውቃቸውን ውጤታማ የሆኑ የስብከት ዘዴዎች ለመማር ግሩም አጋጣሚ ይከፍትልናል። ኤልጅብየታ “ከተለያዩ አስፋፊዎች ጋር ማገልገሌ ለእምነት ባልንጀሮቼም ሆነ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ያለኝን ፍቅር ለመግለጽ አጋጣሚ ይሰጠኛል” ብላለች። ከተለያዩ አስፋፊዎች ጋር አገልግሎት ለመውጣት ጥረት አድርግ። እንዲህ ማድረግህ አገልግሎትህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆንልህ ይረዳሃል።

ለመንፈሳዊም ሆነ ለአካላዊ ጤንነትህ ጥንቃቄ አድርግ

በአገልግሎት በቅንዓት መካፈላችንን መቀጠል እንድንችል የፕሮግራም ሰው መሆን፣ ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበርና በቂ እረፍት ማድረግ ይኖርብናል። በሌላ አባባል ለመንፈሳዊም ሆነ ለአካላዊ ጤንነታችን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል።

መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) በአሁኑ ጊዜ የ88 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ወንድም ዚግመንት እንዲህ ብለዋል፦ “ለአገልግሎቴ ጥሩ ፕሮግራም ማውጣቴ ውጤታማ እንድሆን ረድቶኛል። በስብከቱ ሥራ በቂ ጊዜ ማሳለፍ እንድችል ያለኝን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት አደርጋለሁ።”

ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት ማጥናታችን በመንፈሳዊ የሚያጠናክረን ከመሆኑም በላይ በአገልግሎታችን ብቁ እንድንሆን ያደርገናል። በሕይወት ለመኖር ምግብ መብላት እንደሚያስፈልገን ሁሉ በስብከቱ ሥራችን መካፈላችንን ለመቀጠልም አዘውትረን መንፈሳዊ ምግብ መመገብ ያስፈልገናል። የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበባችንና ‘በተገቢው ጊዜ’ መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን ለአገልግሎት የሚያስፈልገንን ኃይል ይሰጠናል።—ማቴ. 24:45-47

ኤልጅብየታ አገልግሎቷን የምታከናውንበትን መንገድ ለማሻሻል ስትል በሕይወቷ ውስጥ አንዳንድ መሠረታዊ ለውጦችን ማድረግ አስፈልጓት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ለአገልግሎት የምዘጋጅበት ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ስል ቴሌቪዥን በማየት የማጠፋውን ጊዜ በጣም ቀንሻለሁ። በየምሽቱ መጽሐፍ ቅዱስ ሳነብ በአገልግሎት ክልሌ ውስጥ ስለሚኖሩት ሰዎች አስባለሁ። እነዚህን ሰዎች ሊረዷቸው የሚችሉ ጥቅሶችንና ርዕሰ ትምህርቶችን ለማግኘት እጥራለሁ።”

በቂ እረፍት ማድረግ ኃይልህ እንዲታደስና በአገልግሎት በተሟላ መንገድ ለመሳተፍ እንድትችል ይረዳሃል። በሌላ በኩል ደግሞ በመዝናናት ብዙ ሰዓት የምታሳልፍ ከሆነ በምታከናውነው ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በስብከቱ ሥራ በቅንዓት የሚካፈለው አንጄ እንዲህ ብሏል፦ “እረፍት ማጣት ኃይላችን እንዲሟጠጥ የሚያደርግ ሲሆን ይህም በቀላሉ ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል። ይህ እንዳይሆን የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ።”—መክ. 4:6

ትጋት የተሞላበት ጥረት ብናደርግም እንኳ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን አይቀበሉም። ያም ቢሆን ይሖዋ ሥራችንን አይረሳውም። (ዕብ. 6:10) ብዙ ሰዎች ሊያነጋግሩን ፈቃደኞች ባይሆኑም እንኳ ከሄድን በኋላ ስለ እኛ ለሌሎች ይናገሩ ይሆናል። ይህም ሕዝቅኤል ካጋጠመው ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል፤ መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ዘመን ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር “ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ” ይላል። (ሕዝ. 2:5) እርግጥ ነው፣ አገልግሎታችንን ማከናወን ቀላል አይደለም፤ ሆኖም ለእኛም ሆነ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ይህ ነው የማይባል ጥቅም ያስገኛል።

ወንድም ዚግመንት እንዲህ ብለዋል፦ “በአገልግሎት መካፈላችን አዲሱን ሰው ለመልበስ እንዲሁም ለአምላክም ሆነ ለሰዎች ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ያስችለናል።” ወንድም አንጄም እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወት አድን በሆነው በዚህ ሥራ መካፈል ታላቅ መብት ነው። ይህ ሥራ ይህን ያህል ስፋት ባለው መንገድ ወይም እንዲህ ባለው ሁኔታ ፈጽሞ በድጋሚ አይከናወንም።” አንተም በአሁኑ ጊዜ በሚከናወነው አገልግሎት በጽናት መካፈልህ የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝልሃል።—2 ቆሮ. 4:1, 2

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመንፈሳዊም ሆነ ለአካላዊ ጤንነታችን ጥንቃቄ ማድረጋችን በአገልግሎት ለመጽናት ይረዳናል