በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓይናችሁ ምንጊዜም ሽልማቱ ላይ ያተኩር

ዓይናችሁ ምንጊዜም ሽልማቱ ላይ ያተኩር

ዓይናችሁ ምንጊዜም ሽልማቱ ላይ ያተኩር

“ሽልማት አገኝ ዘንድ ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው።”—ፊልጵ. 3:14

1. ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ሽልማት ተዘጋጅቶለት ነበር?

የጠርሴሱ ሳኦል ተብሎ የሚታወቀው ሐዋርያው ጳውሎስ የተወለደው ከትልቅ ቤተሰብ ሲሆን የአባቶቹን ሃይማኖት ያስተማረው ታዋቂ የሕግ መምህር የነበረው ገማልያል ነው። (ሥራ 22:3) ጳውሎስ በብዙዎች ዘንድ ከፍ ተደርጎ የሚታይ ሥራ የመሥራት አጋጣሚ የነበረው ቢሆንም የቀድሞ ሃይማኖቱን እርግፍ አድርጎ በመተው ክርስቲያን ሆነ። ከዚያም በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ውስጥ የማይሞት አካል ለብሶ ንጉሥና ካህን በመሆን የሚያገኘውን የዘላለም ሕይወት ሽልማት በጉጉት ይጠባበቅ ጀመር። ይህ መንግሥት ገነት የምትሆነውን ምድር ያስተዳድራል።—ማቴ. 6:10፤ ራእይ 7:4፤ 20:6

2, 3. ጳውሎስ በሰማይ የሚያገኘውን የዘላለም ሕይወት ሽልማት ምን ያህል ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር?

2 ጳውሎስ ይህን ሽልማት ምን ያህል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ለእኔ ትርፍ የነበረውን ነገር ሁሉ ለክርስቶስ ስል እንደ ኪሳራ ቆጥሬዋለሁ። አዎ፣ ደግሞም ስለ ጌታዬ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ከሚገልጸው የላቀ ዋጋ ያለው እውቀት የተነሳ ሁሉንም ነገር እንደ ኪሳራ እቆጥረዋለሁ። ለእሱ ስል ሁሉንም ነገር አጥቻለሁ፤ ያጣሁትንም ነገር ሁሉ እንደ ጉድፍ እቆጥረዋለሁ።” (ፊልጵ. 3:7, 8) ጳውሎስ፣ ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ በትክክል ከተረዳ በኋላ ብዙ ሰዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጧቸውን ነገሮች ይኸውም ሥልጣንን፣ ሀብትን፣ ሥራንና ክብርን እንደ ጉድፍ ቆጥሯቸዋል።

3 ከዚያን ጊዜ አንስቶ ጳውሎስ ስለ ይሖዋና ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን ውድ እውቀት ከፍ አድርጎ መመልከት ጀመረ። ኢየሱስ ወደ አምላክ ሲጸልይ ይህን እውቀት አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።” (ዮሐ. 17:3) ጳውሎስ “አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሰጠውን የላይኛውን ጥሪ ሽልማት አገኝ ዘንድ ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው” በማለት በፊልጵስዩስ 3:14 ላይ የተናገረው ሐሳብ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው ያሳያል። አዎን፣ ጳውሎስ የአምላክ መንግሥት መስተዳድር አባል በመሆን በሰማይ በሚያገኘው የዘላለም ሕይወት ሽልማት ላይ አተኩሮ ነበር።

በምድር ላይ ለዘላለም መኖር

4, 5. በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምን ሽልማት ያገኛሉ?

4 የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የመረጡ አብዛኞቹ ሰዎች ጥረት የሚያደርጉት አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት ነው። (መዝ. 37:11, 29) ኢየሱስ “ገሮች ደስተኞች ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉ” በማለት ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም አረጋግጧል። (ማቴ. 5:5) መዝሙር 2:8 እንደሚያመለክተው ምድራችንን በዋነኝነት የሚወርሰው ኢየሱስ ራሱ ሲሆን በሰማይ አብረውት የሚገዙ 144,000 ገዥዎች ይኖራሉ። (ዳን. 7:13, 14, 22, 27) በምድር ላይ የሚኖሩት በግ መሰል ሰዎች ‘ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላቸውን’ መንግሥት ምድራዊ ግዛት “ይወርሳሉ።” (ማቴ. 25:34, 46) ይህን ቃል የገባው አምላክ ‘ሊዋሽ ስለማይችል’ ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች ነን። (ቲቶ 1:2) ልክ እንደ ኢያሱ እኛም አምላክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም መተማመን እንችላለን። ኢያሱ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ [አላስቀረባችሁም]፤ . . . አንዱም ሳይቀር ሁሉም ተፈጽሞአል።”—ኢያሱ 23:14

5 አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕይወት እንደ አሁኑ ተስፋ አስቆራጭ አይሆንም። በዚያን ጊዜ የሚኖረው ሕይወት ፍጹም የተለየ ይሆናል። ጦርነት፣ ወንጀል፣ ድህነት፣ የፍትሕ መጓደል፣ ሕመምና ሞት አይኖርም። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች ፍጹም ጤንነት የሚኖራቸው ሲሆን ገነት በሆነች ምድር ላይ ይኖራሉ። ያን ጊዜ ሕይወት ከምናስበው በላይ አርኪና አስደሳች ይሆናል። አዎን፣ በዚያን ጊዜ ሰዎች እያንዳንዱን ቀን በደስታና በሐሴት ያሳልፋሉ። ይህ እንዴት ያለ ግሩም ሽልማት ነው!

6, 7. (ሀ) አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረውን ሁኔታ ኢየሱስ በተግባር ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የሞቱ ሰዎችም እንኳ ሳይቀሩ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሚከፈትላቸው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ በአዲሱ ዓለም ውስጥ በመላው ምድር የሚከናወኑትን ድንቅ ነገሮች በተግባር ማሳየት እንዲችል አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ሰጥቶት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ለ38 ዓመታት ሽባ ሆኖ የኖረን አንድ ሰው ‘ተነስና ተራመድ’ ብሎት ነበር። በዚህ ጊዜ ሰውየው ተነስቶ እንደተራመደ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዮሐንስ 5:5-9ን አንብብ።) በሌላ ወቅት ደግሞ ኢየሱስ “ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው” አጋጥሞት የነበረ ሲሆን ይህንንም ሰው ፈውሶታል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይህ ግለሰብ፣ ስለፈወሰው ሰው በተጠየቀበት ወቅት እንዲህ በማለት መልሷል፦ “ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች የከፈተ አለ ሲባል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። ይህ ሰው ከአምላክ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም ነበር።” (ዮሐ. 9:1, 6, 7, 32, 33) ኢየሱስ ይህን ሁሉ ማድረግ የቻለው አምላክ ኃይል ስለሰጠው ነው። በሄደበት ሁሉ ‘ፈውስ የሚያስፈልጋቸውን ፈውሷል።’—ሉቃስ 9:11

7 ኢየሱስ የታመሙትንና የአካል ጉዳት ያለባቸውን መፈወስ ብቻ ሳይሆን የሞቱትንም ማስነሳት ችሏል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት የ12 ዓመት ልጅ በሞተችበት ጊዜ ወላጆቿ እጅግ አዝነው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “አንቺ ልጅ፣ እልሻለሁ ተነሽ!” አላት። እሷም ተነሳች! ወላጆቿና በዚያ የነበሩት ሰዎች ምን ተሰምቷቸው እንደነበር መገመት ትችላለህ? (ማርቆስ 5:38-42ን አንብብ።) አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ‘ጻድቃንና ዓመፀኞች ከሞት ሲነሱ’ የሚኖረው ‘ደስታ’ ልዩ ይሆናል። (ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 5:28, 29) እነዚህ ሰዎች አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የሚከፈትላቸው ሲሆን ለዘላለም የመኖር ተስፋም ይኖራቸዋል።

8, 9. (ሀ) በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ምን ይሆናል? (ለ) ሙታን ፍርድ የሚሰጣቸው በምን መሠረት ነው?

8 ከሞት የሚነሱት ሰዎች ብሩህ ተስፋ ይጠብቃቸዋል። እነዚህ ሰዎች ፍርድ የሚሰጣቸው ከመሞታቸው በፊት በፈጸሙት ኃጢአት አይደለም። (ሮም 6:7) ታዛዥ የሆኑ የመንግሥቱ ተገዥዎች፣ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ቤዛው በሚያስገኛቸው በረከቶች በመጠቀም የአዳም ኃጢአት ካስከተላቸው ውጤቶች ሙሉ በሙሉ የሚገላገሉ ከመሆኑም ሌላ ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። (ሮም 8:21) በዚያን ጊዜ ይሖዋ ‘ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤ ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።’ (ኢሳ. 25:8) በተጨማሪም የአምላክ ቃል በዚያን ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች አዲስ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ሲገልጽ “የመጽሐፍ ጥቅልሎች [ይከፈታሉ]” ይላል። (ራእይ 20:12) ምድር ወደ ገነትነት ስትለወጥ “የዓለም ሕዝቦች ጽድቅን ይማራሉ።”—ኢሳ. 26:9

9 ከሞት የሚነሱት ሰዎች ፍርድ የሚሰጣቸው ከአዳም በወረሱት ኃጢአት ሳይሆን በራሳቸው ምርጫ በሚፈጽሙት ድርጊት ነው። ራእይ 20:12 “ሙታንም በጥቅልሎቹ ውስጥ በተጻፉት ነገሮች መሠረት እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው” ይላል፤ “እንደየሥራቸው” የሚለው ቃል ፍርድ የሚሰጣቸው ከሞት ከተነሱ በኋላ በሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነ ያሳያል። ይህ የይሖዋን ፍርድ፣ ምሕረትና ፍቅር የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ከዚህም ሌላ በዚህ አሮጌ ዓለም ውስጥ ሲኖሩ የደረሱባቸው አሳዛኝ ሁኔታዎች ‘አይታሰቡም፤ እንዲሁም አይታወሱም።’ (ኢሳ. 65:17) በዚያን ጊዜ የሚያንጹ አዳዲስ ትምህርቶችና ብዙ መልካም ነገሮች ስለሚኖሩ ቀደም ሲል ያሳለፏቸውን መጥፎ ነገሮች በማስታወስ የሚረበሹበት ምክንያት አይኖርም። እነዚህ አሳዛኝ ገጠመኞች ጨርሶ የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። (ራእይ 21:4) ከአርማጌዶን የሚተርፉትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የተባሉትን ሰዎች በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።—ራእይ 7:9, 10, 14

10. (ሀ) በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረውን ሕይወት ግለጽ። (ለ) ዓይንህ ምንጊዜም ሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር ምን ማድረግ ትችላለህ?

10 አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ሰዎች ዳግመኛ አይታመሙም ወይም አይሞቱም። በዚያን ጊዜ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳ. 33:24) በአዲሱ ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች በየዕለቱ ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ፍጹም ጤንነት የሚሰማቸው ሲሆን ከፊታቸው ስለሚጠብቃቸው አዲስ ቀን ሲያስቡ ይደሰታሉ። እያንዳንዱን ዕለት አስደሳች ሥራ በማከናወን እንዲሁም ከሚወዷቸውና ከሚያስቡላቸው ሰዎች ጋር በመጫወት ያሳልፋሉ። በእርግጥም እንዲህ ያለው ሕይወት ልዩ ሽልማት ነው! መጽሐፍ ቅዱስህን አውጥተህ ኢሳይያስ 33:24 እና 35:5-7 ላይ የሚገኙትን ትንቢቶች ለምን አታነብም? እነዚህን ጥቅሶች ስታነብ በቦታው እንዳለህ አድርገህ ለማሰብ ሞክር። ይህም ዓይንህ ምንጊዜም ሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር ለማድረግ ያስችልሃል።

ሽልማቱን አተኩረው መመልከት ያቆሙ ሰዎች

11. የሰሎሞንን ዘመነ መንግሥት ጥሩ ጅምር ግለጽ።

11 የምናገኘውን ሽልማት አንዴ ካወቅን በኋላ ዓይናችን ምንጊዜም ሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር የተቻለንን ያህል ጥረት ማድረግ አለብን፤ አለዚያ ሽልማቱን አተኩረን መመልከታችንን ልናቆም እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ሰሎሞን የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ለሕዝቡ በትክክል መፍረድ እንዲችል ማስተዋልና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ እንዲሰጠው በትሕትና ወደ አምላክ ጸልዮ ነበር። (1 ነገሥት 3:6-12ን አንብብ።) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ለሰሎሞን ጥበብንና እጅግ ታላቅ ማስተዋልን . . . ሰጠው” ይላል። በእርግጥም “የሰሎሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብ በጣም የላቀ ከግብፅም ጥበብ ሁሉ የበለጠ ነበር።”—1 ነገ. 4:29-32

12. ይሖዋ ለእስራኤል ነገሥታት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር?

12 ይሁንና ይሖዋ ማንኛውም ንጉሥ “ብዙ ፈረሶችን ለራሱ አያብዛ” እንዲሁም “ልቡ እንዳይስትም ብዙ ሚስቶችን አያግባ” የሚል ማስጠንቀቂያ አስቀድሞ ሰጥቶ ነበር። (ዘዳ. 17:14-17) አንድ ንጉሥ የፈረሶቹን ቁጥር ማብዛቱ ሕዝቡን ከጥቃት ለመከላከል አዳኝ በሆነው በይሖዋ ከመታመን ይልቅ በወታደራዊ ኃይል እንደሚታመን ያሳያል። ሚስቶችን ማብዛት ደግሞ አደገኛ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም አንዳንዶቹ የሐሰት አማልክትን ከሚያመልኩ አረማዊ ብሔራት የመጡ ሊሆኑ ስለሚችሉ ንጉሡ ይሖዋን እንዲተውና ከእውነተኛው አምልኮ ፈቀቅ እንዲል ሊያደርጉት ይችላሉ።

13. ሰሎሞን በተሰጠው መብት ላይ ትኩረት ማድረጉን ያቆመው እንዴት ነው?

13 ሰሎሞን እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች አልሰማም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ የእስራኤል ነገሥታት እንዳያደርጉ ያዘዘውን ነገር አድርጓል። በሺዎች የሚቆጠሩ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን አከማችቷል። (1 ነገ. 4:26) ከዚህም ሌላ 700 ሚስቶችና 300 ቁባቶች ነበሩት፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በአቅራቢያው ካሉት አረማዊ ብሔራት የመጡ ናቸው። እነዚህ ሴቶች “ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ . . . በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።” ሰሎሞን ከባዕድ አገር ያገባቸው እነዚህ ሴቶች ያስተማሩትን አስጸያፊ የሆነውን የአረማውያን ብሔራት የሐሰት አምልኮ መከተል ጀመረ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ ‘መንግሥቱን ከሰሎሞን ወስዶ’ ለሌላ ሰው እንደሚሰጠው ተናገረ።—1 ነገ. 11:1-6, 11

14. ሰሎሞንም ሆነ የእስራኤል ብሔር አለመታዘዛቸው ምን ውጤት አስከተለ?

14 ሰሎሞን እውነተኛውን አምላክ መወከል መቻል ውድ መብት መሆኑን ዘንግቶ ነበር። ንጉሡ በሐሰት አምልኮ ተዘፍቆ ነበር። ውሎ አድሮ መላው ብሔር ከሃዲ ሆነ፤ በዚህም የተነሳ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጥፋት ደረሰበት። ከጊዜ በኋላ አይሁዳውያን እውነተኛውን አምልኮ መልሰው ማቋቋም የቻሉ ቢሆንም ከተወሰኑ መቶ ዘመናት በኋላ ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል” ሲል ለመናገር ተገዷል። የተፈጸመውም ይኸው ነው። ኢየሱስ “እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል” ሲል ተናግሯል። (ማቴ. 21:43፤ 23:37, 38) ሕዝቡ ታማኝ ሳይሆን በመቅረቱ እውነተኛውን አምላክ የመወከል ትልቅ መብት አጣ። በ70 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮም ሠራዊት ኢየሩሳሌምንና ቤተ መቅደሷን አወደመ፤ ከጥፋቱ የተረፉት አብዛኞቹ አይሁዳውያንም ባሪያዎች ሆኑ።

15. በጣም አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ካቆሙ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ።

15 የአስቆሮቱ ይሁዳ ከ12ቱ የኢየሱስ ሐዋርያት አንዱ ነበር። ይሁዳ፣ የኢየሱስን ግሩም ትምህርቶች የሰማ ከመሆኑም ሌላ ኢየሱስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያከናወናቸውን ተአምራት ተመልክቷል። ይሁን እንጂ ይሁዳ ልቡን አልጠበቀም። የኢየሱስና የ12ቱ ሐዋርያት ገንዘብ የሚቀመጥበትን ሣጥን የሚይዘው እሱ ነበር። ሆኖም ይሁዳ “ሌባ [ነበር]፤ የገንዘብ ሣጥኑን ይይዝ የነበረው እሱ በመሆኑ ወደ ሣጥኑ ከሚገባው ገንዘብ የመውሰድ ልማድ ነበረው።” (ዮሐ. 12:6) ይሁዳ በጣም ስግብግብ ከመሆኑ የተነሳ ኢየሱስን በ30 የብር ሳንቲሞች አሳልፎ ለመስጠት ግብዝ ከሆኑት የካህናት አለቆች ጋር ተዋዋለ። (ማቴ. 26:14-16) በሽልማቱ ላይ ትኩረት ማድረጉን ያቆመው ሌላው ሰው ደግሞ የሐዋርያው ጳውሎስ የሥራ ባልደረባ የነበረው ዴማስ ነው። ዴማስ ልቡን አልጠበቀም። ጳውሎስ “ዴማስ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሥርዓት ወዶ፣ ትቶኝ . . . ሄዷል” ሲል ተናግሯል።—2 ጢሞ. 4:10፤ ምሳሌ 4:23ን አንብብ።

ለእያንዳንዳችን የሚሆን ትምህርት

16, 17. (ሀ) የሚደርስብን ተቃውሞ ምን ያህል ከባድ ነው? (ለ) ሰይጣን የሚያሳድርብንን ማንኛውንም ተጽዕኖ ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?

16 ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሱት ምሳሌዎች ላይ በቁም ነገር ማሰላሰል ይኖርባቸዋል፤ ምክንያቱም “እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ይሆኑ ዘንድ በእነሱ ላይ ደረሱ፤ የተጻፉትም የሥርዓቶቹ ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅ ነው።” (1 ቆሮ. 10:11) በዛሬው ጊዜ የምንኖረው በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ነው።—2 ጢሞ. 3:1, 13

17 “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ “ጥቂት ጊዜ እንደቀረው” ያውቃል። (2 ቆሮ. 4:4፤ ራእይ 12:12) በመሆኑም የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን በመጠቀም የይሖዋ አገልጋዮች ክርስቲያናዊ አቋማቸውን እንዲያላሉ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ሰይጣን ይህን ዓለምም ሆነ ፕሮፖጋንዳ የሚተላለፍባቸውን የመገናኛ ዘዴዎች ይቆጣጠራል። ይሁንና የይሖዋ ሕዝቦች “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል” አላቸው። (2 ቆሮ. 4:7) ሰይጣን በእኛ ላይ የሚያሳድረውን ማንኛውንም ተጽዕኖ ለመቋቋም አምላክ በሚሰጠን በዚህ ኃይል መተማመን እንችላለን። ስለሆነም ይሖዋ ‘ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጣቸው’ በመተማመን አዘውትረን እንድንጸልይ ምክር ተሰጥቶናል።—ሉቃስ 11:13

18. በዛሬው ጊዜ ስላለው ዓለም ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

18 ከዚህም በተጨማሪ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ሥርዓት በጠቅላላ በቅርቡ እንደሚጠፉ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ከጥፋቱ እንደሚተርፉ ማወቃችን ያበረታታናል። “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ ናቸው፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐ. 2:17) ከዚህ አንጻር ሲታይ አንድ የአምላክ አገልጋይ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ከይሖዋ ጋር ከመሠረተው ዝምድና የበለጠ ዘላቂ ጥቅም የሚያስገኝ ሌላ ነገር ሊኖር እንደሚችል ቢያስብ እንዴት ያለ ሞኝነት ነው! በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ይህ ዓለም እየሰመጠ እንዳለ መርከብ ነው። ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ክርስቲያን ጉባኤን እንደ “ሕይወት አድን ጀልባ” አድርጎ አዘጋጅቶላቸዋል። ወደ አዲሱ ዓለም እየተጓዙ ባሉበት በአሁኑ ወቅት “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ” በሚለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ መተማመን ይችላሉ። (መዝ. 37:9) እንግዲያው ዓይንህ ምንጊዜም በዚህ ግሩም ሽልማት ላይ ያተኩር!

ታስታውሳለህ?

• ጳውሎስ የተዘጋጀለትን ሽልማት በተመለከተ ምን ተሰምቶት ነበር?

• በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ ሰዎች ፍርድ የሚሰጣቸው በምን መሠረት ነው?

• በአሁኑ ጊዜ ልትወስደው የሚገባ የጥበብ እርምጃ ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስታነብ በቦታው እንዳለህና ሽልማቱን እንዳገኘህ አድርገህ ለማሰብ ትሞክራለህ?