በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የያሻር መጽሐፍ’ እንዲሁም ‘የይሖዋ የጦርነት መጽሐፍ’ የተባሉ ጽሑፎችን ይጠቅሳል። (ኢያሱ 10:13፤ ዘኍ. 21:14) ሆኖም እነዚህ ሁለት መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተካተቱም። እነዚህ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉና ከጊዜ በኋላ የጠፉ መጻሕፍት ናቸው?

እነዚህ መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉና ከጊዜ በኋላ የጠፉ ናቸው ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ምንም ማስረጃ የለም። በአምላክ መንፈስ መሪነት መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች በርከት ያሉ ሌሎች ጽሑፎችን ጠቅሰዋል። ከእነዚህ መጻሕፍት አንዳንዶቹ በዘመናችን ከምንጠቀምበት ስያሜ በተለየ መንገድ የተጠቀሱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሊሆኑ ይችላሉ። ለአብነት ያህል፣ 1 ዜና 29:29 ‘ስለ ባለ ራእዩ ሳሙኤል የታሪክ መጽሐፍ፣’ ‘ስለ ነቢዩ ናታን የታሪክ መጽሐፍ’ እንዲሁም ‘ስለ ባለ ራእዩ ጋድ የታሪክ መጽሐፍ’ ይናገራል። እነዚህ ሦስት መጻሕፍት በአሁኑ ጊዜ አንደኛና ሁለተኛ ሳሙኤል ተብለው የሚጠሩትን መጻሕፍት ወይም የመሳፍንትን መጽሐፍ የሚያመለክቱ ሊሆኑ ይችላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ መጻሕፍት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሆኑት መጻሕፍት ጋር ተመሳሳይ መጠሪያ ቢኖራቸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይሆኑ ይችላሉ። ይህን ለመረዳት አራት ጥንታዊ መጻሕፍትን እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን፤ እነዚህም፦ ‘የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ፣’ ‘የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መዛግብት፣’ “የእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ” እንዲሁም ‘የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ’ ናቸው። እነዚህ አራት መጻሕፍት፣ አንደኛና ሁለተኛ ነገሥት ከሚባሉት መጻሕፍት ጋር የሚመሳሰል መጠሪያ ቢኖራቸውም በአምላክ መንፈስ መሪነት አልተጻፉም፤ እንዲሁም የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል አይደሉም። (1 ነገ. 14:29፤ 2 ዜና 16:11፤ 20:34፤ 27:7) እነዚህ መጻሕፍት ነቢዩ ኤርምያስና ዕዝራ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ዘገባ በጻፉበት ወቅት የነበሩ የታሪክ መዛግብት ናቸው።

በእርግጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በጊዜው የነበሩ ሆኖም በአምላክ መንፈስ መሪነት ያልተጻፉ ታሪካዊ ዘገባዎችን አሊያም መዛግብትን በማመሳከሪያነት ተጠቅመውባቸዋል ወይም ከእነዚህ መዛግብት ጠቅሰው ጽፈዋል። አስቴር 10:2 ‘ስለ ሜዶንና ፋርስ የታሪክ መጽሐፍ’ ይጠቅሳል። በተመሳሳይም ሉቃስ፣ የወንጌል ዘገባውን ሲጽፍ “ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ [እንደመረመረ]” ገልጿል። ሉቃስ ይህን ሲል በወንጌሉ ውስጥ የሚገኘውን የኢየሱስ የዘር ሐረግ ዝርዝር ሲጽፍ በጊዜው የነበሩትን መዛግብት ማመሳከሩን መግለጹ ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 1:3፤ 3:23-38) ሉቃስ በማመሳከሪያነት የተጠቀመባቸው መጻሕፍት በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ባይሆኑም እሱ ያዘጋጀው የወንጌል ዘገባ ግን በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ይህ ወንጌል ጠቃሚ የሆነ ሐሳብ ይዞልናል።

ከላይ ባለው ጥያቄ ላይ የተጠቀሱት ሁለት መጻሕፍት ማለትም ‘የያሻር መጽሐፍ’ እና ‘የይሖዋ የጦርነት መጽሐፍ’ በአምላክ መንፈስ መሪነት ያልተጻፉ በጊዜው የነበሩ የታሪክ መዛግብት ሳይሆኑ አይቀሩም። በዚህም ምክንያት ይሖዋ እነዚህ መጻሕፍት እስከ ዘመናችን ተጠብቀው እንዲቆዩ አላደረገም። እነዚህ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱበት መንገድ ምሑራን፣ መጻሕፍቱ እስራኤላውያን ከጠላቶቻቸው ጋር ያደረጓቸውን ውጊያዎች የሚያወሱ ግጥሞችን ወይም መዝሙሮችን የያዙ ናቸው ወደሚለው መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። (2 ሳሙ. 1:17-27) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው እነዚህ መጻሕፍት “በጥንቷ እስራኤል ይኖሩ የነበሩ ዘማሪዎች ያሰባሰቧቸውን የግጥም መድብሎችና መዝሙሮች” የያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። አምላክ የላካቸው አንዳንድ ነቢያት ወይም ባለ ራእዮች የጻፏቸው ነገሮችም እንኳ ይሖዋ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፋቸው አይደሉም፤ ወይም ደግሞ ይሖዋ እነዚህ መጻሕፍት በዛሬው ጊዜ “ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናት” በሚጠቅሙት ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንዲካተቱ አላደረገም።—2 ጢሞ. 3:16፤ 2 ዜና 9:29፤ 12:15፤ 13:22

አንዳንድ መጻሕፍት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መጠቀሳቸውና ለመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች መነሻ ሆነው ማገልገላቸው በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው ብለን እንድንደመድም ሊያደርገን አይገባም። ይሖዋ አምላክ ‘የአምላካችንን ቃል’ የያዙት መጻሕፍት በሙሉ እስከ ዘመናችን ድረስ ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደረገ ሲሆን እነዚህ መጻሕፍት ‘ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ።’ (ኢሳ. 40:8) አዎን፣ ይሖዋ “ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ በመታጠቅ ሙሉ በሙሉ ብቁ” ሆነን ለመገኘት የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ አሁን ባሉን 66 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ውስጥ እንዲካተት አድርጓል።—2 ጢሞ. 3:16, 17