በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ይሖዋን በሚፈሩት ዙሪያ የይሖዋ መልአክ ይሰፍራል’

‘ይሖዋን በሚፈሩት ዙሪያ የይሖዋ መልአክ ይሰፍራል’

‘ይሖዋን በሚፈሩት ዙሪያ የይሖዋ መልአክ ይሰፍራል’

ክሪስታቤል ኮኔል እንደተናገረችው

እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ፣ ክሪስቶፈር ላነሳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ እየሰጠነው ነበር፤ በውይይቱ በጣም ከመመሰጣችን የተነሳ ጊዜው ምን ያህል እንደመሸም ሆነ ክሪስቶፈር በተደጋጋሚ በመስኮት ወደ ውጪ ይመለከት እንደነበር ልብ አላልንም። በመጨረሻም ክሪስቶፈር “አሁን ሁኔታው የተረጋጋ ይመስላል፤ ልትሄዱ ትችላላችሁ” አለን። ከዚያም ብስክሌቶቻችንን እስካቆምንበት ቦታ ድረስ ሸኘንና ተሰናብቶን ተመለሰ። ክሪስቶፈር የተመለከተው አደገኛ ሁኔታ ምን ነበር?

የተወለድኩት በ1927 በሼፊልድ፣ እንግሊዝ ውስጥ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቤታችን በቦንብ ስለተደበደበ ትምህርቴን እስክጨርስ ድረስ ከአያቴ ጋር እንድኖር ተላክሁ። በምማርበት የካቶሊክ ትምህርት ቤት የሚገኙትን ሴት መነኮሳት በዓለም ላይ ይህን ያህል ክፋትና ዓመፅ የበዛው ለምን እንደሆነ በተደጋጋሚ እጠይቃቸው ነበር። ሆኖም መነኮሳቱም ሆኑ ሌሎች የሃይማኖት ሰዎች ለጥያቄዬ አጥጋቢ መልስ ሊሰጡኝ አልቻሉም።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በነርስነት ሞያ ሠለጠንኩ። ከዚያም ለንደን በሚገኘው ፓዲንግተን አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ መሥራት ጀመርኩ፤ ሆኖም በከተማው ውስጥ የተመለከትኩት ዓመፅ የከፋ ነበር። ታላቅ ወንድሜ በኮሪያ ወደተደረገው ጦርነት ከዘመተ ብዙም ሳይቆይ ከምሠራበት ሆስፒታል ፊት ለፊት አንድ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ሲደበደብ ተመለከትኩ። ግለሰቡ በድብደባው የተነሳ ዓይኑ ቢጠፋም ማንም እርዳታ አላደረገለትም። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ከእናቴ ጋር ወደ አንድ ሙታን ሳቢ ሄድን፤ ያም ሆኖ በዓለም ላይ ክፋት የበዛበትን ምክንያት መረዳት አልቻልኩም።

መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ማበረታቻ ተሰጠኝ

የይሖዋ ምሥክር የሆነው ታላቅ ወንድሜ ጆን አንድ ቀን ሊጠይቀኝ መጣ። ጆን “እነዚህ ሁሉ መጥፎ ነገሮች በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?” ብሎ ጠየቀኝ። እኔም “አላውቅም” አልኩት። ጆን መጽሐፍ ቅዱስ አውጥቶ ራእይ 12:7-12⁠ን አነበበልኝ። በዚህ ጊዜ በዓለም ላይ ለሚታየው ክፋት በዋነኝነት ተጠያቂ የሆኑት ሰይጣንና አጋንንቱ መሆናቸውን ተገነዘብኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጆንን ምክር በመቀበል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። ሆኖም በወቅቱ ሰዎችን ስለፈራሁ ከመጠመቅ ወደኋላ አልኩ።—ምሳሌ 29:25

ታላቅ እህቴ ዶሮቲም የይሖዋ ምሥክር ሆና ነበር። እሷና እጮኛዋ ቢል ሮበርትስ በ1953 በኒው ዮርክ ከተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ሲመለሱ አንዲት የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን እንዳስጠናችኝ ነገርኳቸው። ቢል “ጥቅሶቹን በሙሉ እያወጣሽ ታነቢያቸው ነበር? መልሶቹንስ በመጽሐፉ ላይ አስምረሽባቸዋል?” በማለት ጠየቀኝ። እንዲህ እንዳላደረግኩ ስነግረው “እንደዚያ ከሆነ አጥንተሻል ማለት አይቻልም! ያስጠናችሽን እህት አነጋግሪያትና እንደገና ጥናት ጀምሪ!” አለኝ። በዚህ ጊዜ አካባቢ አጋንንት ጥቃት ይሰነዝሩብኝ ጀመር። ይሖዋ ከአጋንንት ጥቃት እንዲጠብቀኝና ከሚያሳድሩብኝ ተጽዕኖ እንዲያላቅቀኝ እጸልይ ነበር።

በስኮትላንድና በአየርላንድ በአቅኚነት ማገልገል

ጥር 16, 1954 ተጠመቅሁ፤ ከዚያም በነርስነት ለመሥራት የፈረምኩት ኮንትራት በግንቦት ወር ሲያበቃ ሰኔ ላይ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ከስምንት ወራት በኋላ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል በግሬንጅማውዝ፣ ስኮትላንድ ተመደብኩ። ራቅ ብሎ በሚገኘው በዚያ አካባቢ ባገለገልኩበት ወቅት የይሖዋ መላእክት ‘በዙሪያዬ’ እንዳሉ ይሰማኝ ነበር።—መዝ. 34:7

በ1956 በአየርላንድ እንዳገለግል የተጠየቅሁ ሲሆን ከሁለት እህቶች ጋር በጎልዌይ ከተማ ተመደብኩ። ገና በመጀመሪያው ቀን አገልግሎት ስወጣ የአንድን ቄስ ቤት አንኳኳሁ። ብዙም ሳይቆይ አንድ ፖሊስ መጣና እኔና ጓደኛዬን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰደን። ፖሊሱ ስማችንንና አድራሻችንን ከመዘገበ በኋላ ወዲያውኑ ስልክ ደወለ። ከዚያም “አዎ፣ አባ የት እንደሚኖሩ አውቄያለሁ” ሲል ሰማነው። ፖሊሱን የላከው ቄሱ ነበር። ቤት ያከራየን ሰው ከቤቱ እንዲያስወጣን ተጽዕኖ ተደረገበት፤ በመሆኑም ቅርንጫፍ ቢሮው አካባቢውን ለቀን እንድንወጣ ሐሳብ አቀረበልን። ባቡር ጣቢያ የደረስነው ባቡሩ ከሚነሳበት ሰዓት አሥር ደቂቃ ዘግይተን ቢሆንም ባቡሩ እየጠበቀን ነበር፤ ከዚህም በተጨማሪ ባቡሩ ላይ መሣፈራችንን ለማረጋገጥ ቆሞ የሚጠብቀን ሰው ነበር። በጎልዌይ የቆየነው ሦስት ሳምንት ብቻ ነበር!

ከዚያም በሊምሪክ ተመደብን፤ በዚህ ከተማም ቢሆን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራት። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ተሰብስበው ይጮኹብን ነበር። ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ብዙዎች በራቸውን ከፍተው እኛን ማነጋገር ይፈሩ ነበር። ከአንድ ዓመት በፊት፣ ክሉንላራ በተባለች በሊምሪክ አቅራቢያ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ አንድ ወንድም ተደብድቦ ስለነበር በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ክሪስቶፈር በሌላ ጊዜ ተገናኝተን ያሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች እንድንወያይባቸው ሲቀጥረን ተደሰትን። በቀጠሯችን ተገናኝተን ስንወያይ አንድ ቄስ ዘው ብሎ በመግባት ከቤቱ እንዲያስወጣን ክሪስቶፈርን አዘዘው። ክሪስቶፈር ግን እንደሚከተለው በማለት በሐሳቡ እንደማይስማማ ገለጸለት፦ “እነዚህ ሴቶች ወደ ቤቴ የመጡት ጋብዣቸው ሲሆን የገቡትም በሩን አንኳኩተው ነው። አንተ ግን አልተጋበዝክም፤ ደግሞም የገባኸው ሳታንኳኳ ነው።” ቄሱ ይህንን ሲሰማ በንዴት ጦፎ ሄደ።

ከዚያም በርከት ያሉ ወንዶችን አሰባስቦ ከክሪስቶፈር ቤት እስክንወጣ ይጠብቀን ጀመር፤ እኛ ግን ይህን አላወቅንም ነበር። ክሪስቶፈር ሰዎቹ እኛን ለማጥቃት በቁጣ ገንፍለው እንደመጡ ስለተገነዘበ በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት እስኪበተኑ ድረስ እንድንቆይ አደረገ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ክሪስቶፈርና ቤተሰቡ አካባቢውን ለቀው ለመውጣት እንደተገደዱና ወደ እንግሊዝ እንደሄዱ ሰማን።

ወደ ጊልያድ ተጠራሁ

በ1958 በኒው ዮርክ በተደረገው መለኮታዊ ፈቃድ በተሰኘው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት እያሰብኩ ሳለ በጊልያድ ትምህርት ቤት በ33ኛው ክፍል እንድሠለጥን ተጋበዝኩ። ከስብሰባው በኋላ ወደ ቤቴ ከመመለስ ይልቅ በ1959 የጊልያድ ትምህርት ቤት እስኪጀመር ድረስ በኦንታሪዮ፣ ካናዳ በምትገኘው በካሊግዉድ አገለገልኩ። በስብሰባው ላይ እያለሁ ኤሪክ ኮኔል ከተባለ ወንድም ጋር ተዋወቅሁ። ኤሪክ እውነትን የሰማው በ1957 ሲሆን በ1958 አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ከስብሰባው በኋላ ካናዳ በቆየሁበት ጊዜም ሆነ በጊልያድ እያለሁ በየቀኑ ደብዳቤ ይጽፍልኝ ነበር። ከጊልያድ ከተመረቅኩ በኋላ ግንኙነታችን ምን መልክ ይኖረው ይሆን የሚለው ጉዳይ ያሳስበኝ ነበር።

በጊልያድ ያገኘሁት ሥልጠና በሕይወቴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከምሰጣቸው ነገሮች አንዱ ነው። በጊልያድ አብረውኝ ከሠለጠኑት መካከል እህቴ ዶሮቲና ባለቤቷ ይገኙበታል። እህቴና ባለቤቷ ፖርቹጋል የተመደቡ ሲሆን እኔ ግን በአየርላንድ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከእህቴ ጋር ባለመሄዴ በጣም አዘንኩ! ከአስተማሪዎቻችን አንዱን ያጠፋሁት ነገር እንዳለ ጠየቅሁት። “በፍጹም፣ አንቺና ጓደኛሽ አይሊን ማኦኒ በዓለም ላይ የትኛውም ቦታ ሄዳችሁ ለማገልገል ፈቃደኞች እንደሆናችሁ ገልጻችኋል” አለኝ፤ ልንመደብ ከምንችልባቸው ቦታዎች አንዱ ደግሞ አየርላንድ ነበር።

ወደ አየርላንድ ተመለስኩ

በነሐሴ ወር 1959 ወደ አየርላንድ የተመለስኩ ሲሆን ዳን ሌራ በተባለው ጉባኤ እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚህ መሃል ኤሪክ ወደ እንግሊዝ ተመልሶ ነበር፤ ምድቤ እሱ ካለበት ቦታ ብዙም አለመራቁ በጣም አስደሰተው። እሱም ሚስዮናዊ ለመሆን ይመኝ ነበር። በወቅቱ ሚስዮናውያን ወደ አየርላንድ ይላኩ ስለነበር በዚያ አቅኚ ሆኖ ለማገልገል ወሰነ። ኤሪክ ወደ ዳን ሌራ ከተማ ተዛወረና በ1961 ተጋባን።

በተጋባን በስድስት ወራችን ኤሪክ ከባድ የሞተር ብስክሌት አደጋ አጋጠመው። የራስ ቅሉ ስለተሰነጠቀ ዶክተሮቹ ሕይወቱን ለማዳን መቻል አለመቻላቸውን እርግጠኞች አልነበሩም። ኤሪክ በሆስፒታል ውስጥ ለሦስት ሳምንታት ያህል ከቆየ በኋላ ወደ ቤት የተመለሰ ሲሆን እስኪሻለው ድረስ ለአምስት ወራት ያህል ተንከባከብኩት። አቅሜ በፈቀደው መጠን በአገልግሎት እካፈል ነበር።

በ1965 በሰሜናዊ ምዕራብ የባሕር ዳርቻ ላይ ባለችው ስላይጎ የተባለች የወደብ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ስምንት አባላት ያሉት ጉባኤ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። ከሦስት ዓመታት በኋላ ደግሞ በስተ ሰሜን ባለው በሎንደንደሪ ከተማ ወደሚገኝ አነስተኛ ጉባኤ ሄድን። አንድ ቀን ከአገልግሎት ስንመለስ በምንኖርበት አካባቢያለው አውራ ጎዳና በሽቦ አጥር ተከፍሎ ጠበቀን። በሰሜን አየርላንድ የተነሳው ብጥብጥ የጀመረው በዚህ ወቅት ነው። ወጣት ወሮበሎች መኪኖችን ያቃጥሉ ነበር። በከተማዋ ውስጥ የካቶሊኮችና የፕሮቴስታንቶች ሰፈር በመለየቱ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው መሄድ አደገኛ ነበር።

ብጥብጥ በነገሠበት አካባቢ መኖርና መስበክ

በከተማዋ ውስጥ የካቶሊኮችና የፕሮቴስታንቶች ሰፈር የተለየ ቢሆንም አገልግሎታችንን ለማከናወን ሁሉም ቦታ መሄድ ነበረብን። በዚህ ጊዜም የይሖዋ መላእክት በዙሪያችን እንደነበሩ መገንዘብ ችለናል። ባለንበት አካባቢ ረብሻ ሲፈጠር በፍጥነት አካባቢውን ለቅቀን እንወጣና ሁኔታዎች ሲረጋጉ እንመለስ ነበር። በአንድ ወቅት በምንኖርበት አፓርታማ አካባቢ ብጥብጥ በተነሳ ጊዜ በአቅራቢያችን የሚገኝ የቀለም ሱቅ በእሳት ተያያዘ። ከሱቁ የተስፈነጠረ እሳት በመስኮታችን ደፍ ላይ ሲያርፍ አፓርታማው በእሳት ይያያዝ ይሆናል ብለን ስለፈራን ሳንተኛ አደርን። በ1970 ወደ ቤልፋስት ከተዛወርን በኋላ ቀደም ሲል በነበርንበት አፓርታማ አቅራቢያ የሚገኘው የቀለም መሸጫ መደብር በጋዝ በተሠራ ፈንጂ እንደተመታና አፓርታማውም እንደተቃጠለ ሰማን።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ከአንዲት እህት ጋር ስናገለግል በአንድ ቤት መስኮት ደፍ ላይ ቧንቧ የሚመስል ነገር ተቀምጦ አየን። በነገሩ እየተገረምን አገልግሎታችንን ቀጠልን። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፍንዳታ ሰማን። የፈነዳው ቧንቧ የመሰለን ነገር ነበር። የፍንዳታውን ድምፅ ሰምተው ከየቤታቸው የወጡት የአካባቢው ሰዎች ፈንጂውን ያስቀመጥነው እኛ መሰልናቸው! በዚህ ጊዜ በአካባቢው የምትኖር አንዲት እህት ወደ ቤቷ እንድንገባ ጋበዘችን። ጎረቤቶቿ ይህንን ሲያዩ ፈንጂውን ያስቀመጥነው እኛ አለመሆናችንን ተገነዘቡ።

በ1971 አንዲት እህታችንን ለመጠየቅ ወደ ሎንደንደሪ ተመለስን። ስለመጣንበት መንገድና ስላለፍነው ኬላ ለእህት ስንነግራት “ኬላው ጋር ማንም አልነበረም?” ስትል ጠየቀችን። “ሰዎች ነበሩ፤ ግን ምንም አላሉንም” ብለን ስንመልስላት በጣም ተገረመች። የተገረመችው ከዚያ በፊት በነበሩት ቀናት ሰዎቹ የአንድን ዶክተርና የአንድን ፖሊስ መኪኖች አቃጥለውባቸው ስለነበር ነው።

በ1972 ወደ ኮርክ ተዛወርን። ከዚያም ናስ በተባለችው ከተማ አገለገልን፤ ቀጥሎ ደግሞ ወደ አርክሎ ሄደን። በመጨረሻም በ1987 በካስልባር እንድናገለግል የተመደብን ሲሆን አሁንም የምንኖረው እዚያው ነው። በዚህ ቦታ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነባ የማገዝ ግሩም መብት አግኝተናል። በ1999 ኤሪክ በጠና ታመመ። ያም ሆኖ የይሖዋና የጉባኤው ፍቅራዊ እርዳታ ስላልተለየኝ ሁኔታውን ተቋቁሜ እስኪሻለው ድረስ ላስታምመው ችያለሁ።

እኔና ኤሪክ በአቅኚዎች የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሁለት ጊዜ ተካፍለናል። ኤሪክ አሁንም የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። አርትራይተስ በተባለው በሽታ ስለምሠቃይ በቀዶ ሕክምና አማካኝነት ሁለቱም የዳሌና የጉልበቴ አጥንቶች መተካት አስፈልጓቸዋል። ባለፉት ዓመታት በሃይማኖቴ ምክንያት የከረረ ተቃውሞ ያጋጠመኝ ከመሆኑም ሌላ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አለመረጋጋት በሰፈነባቸው አካባቢዎች ኖሬያለሁ፤ ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይበልጥ ከባድ የሆነብኝ መኪና መንዳት ለማቆም መገደዴ ነበር። መኪና ማሽከርከር አለመቻሌ ፈተና የሆነብኝ የፈለግኩት ቦታ ለመሄድ የሌሎች እርዳታ የግድ ስለሚያስፈልገኝ ነው። የጉባኤው አባላት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልኛል። በአሁኑ ጊዜ የምንቀሳቀሰው በምርኩዝ እየታገዝኩ ሲሆን ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች ለመሄድ ደግሞ በባትሪ በሚሠራ ባለ ሦስት ጎማ ብስክሌት እጠቀማለሁ።

እኔና ኤሪክ በድምሩ ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት በልዩ አቅኚነት ያገለገልን ሲሆን ከእነዚህም 98ቱን ዓመታት ያሳለፍነው በአየርላንድ ነው። ዕድሜያችን ቢገፋም አገልግሎታችንን የማቆም ሐሳብ የለንም። ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ይረዳናል ብለን ባንጠብቅም ኃያል የሆኑት መላእክቱ እሱን በሚፈሩትና በታማኝነት በሚያገለግሉት ሰዎች ‘ዙሪያ እንደሚሰፍሩ’ እናምናለን።