በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን ፈጽሞ ልትረሳው አይገባም

ይሖዋን ፈጽሞ ልትረሳው አይገባም

ይሖዋን ፈጽሞ ልትረሳው አይገባም

አንዳንዶቹ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። አብዛኞቹ ግን ወንዝ ለሁለት ተከፍሎ ምንም ውኃ ሳይነካቸው በእግራቸው ሲያቋርጡ ይህ የመጀመሪያቸው ሲሆን ከዚህ በኋላም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አላጋጠማቸውም። ይሖዋ የዮርዳኖስ ወንዝ ቁልቁል መፍሰሱን አቁሞ እንደ ክምር እንዲቆለል አደረገው። ከዚያም በሚሊዮን የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ወንዙን በደረቅ መሬት አቋርጠው ወደ ተስፋይቱ ምድር ገቡ። ከ40 ዓመት በፊት ቀይ ባሕርን እንደተሻገሩት አባቶቻቸው ሁሉ ዮርዳኖስን የተሻገሩት አብዛኞቹ እስራኤላውያንም ‘ይሖዋ በዚህ ቦታ ያደረገውን ነገር ፈጽሞ አልረሳውም’ ብለው ሳያስቡ አልቀሩም።—ኢያሱ 3:13-17

ይሖዋ ግን አንዳንድ እስራኤላውያን ‘ያደረገውን ወዲያውኑ እንደሚረሱ’ ያውቅ ነበር። (መዝ. 106:13) በመሆኑም ይሖዋ፣ እስራኤላውያን 12 ድንጋዮችን ከወንዙ ወስደው መጀመሪያ በሚሰፍሩበት ቦታ እንዲያስቀምጧቸው መሪያቸው የነበረውን ኢያሱን አዘዘው። ኢያሱ ‘እነዚህ ድንጋዮች ለእስራኤል ሕዝብ መታሰቢያ እንደሚሆኑ’ ተናግሯል። (ኢያሱ 4:1-8) ይህ የድንጋይ ክምር እስራኤላውያን የይሖዋን ታላቅ ሥራ እንዲያስታውሱ የሚረዳቸው ከመሆኑም ሌላ ምንጊዜም እሱን በታማኝነት ማገልገል የሚገባቸው ለምን እንደሆነ ያስገነዝባቸዋል።

ይህ ዘገባ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች የያዘው ትምህርት አለ? አዎን። እኛም ይሖዋን ፈጽሞ ልንረሳው አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ እሱን ሁልጊዜ በታማኝነት ማገልገል ይኖርብናል። ለእስራኤል ብሔር የተሰጡት ሌሎች ማሳሰቢያዎችም በዛሬው ጊዜ ለሚገኙት የይሖዋ አገልጋዮች ጠቃሚ ትምህርት ይዘዋል። ለምሳሌ ሙሴ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ትእዛዙን፣ ሕጉንና ሥርዐቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳው ተጠንቀቅ።” (ዘዳ. 8:11) ይህ ጥቅስ አንድ ሰው ይሖዋን መርሳቱ እሱን ለመታዘዝ እምቢተኛ እንዲሆን ሊያደርገው እንደሚችል ያሳያል። ዛሬም ቢሆን እንዲህ ዓይነት አደጋ አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በምድረ በዳ የነበሩትን የእስራኤላውያንን “ያለመታዘዝ ምሳሌ” እንዳይከተሉ ለክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—ዕብ. 4:8-11

አምላክን መርሳት እንደሌለብን ጎላ አድርገው የሚያሳዩ በእስራኤላውያን ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ አንዳንድ ክንውኖችን እስቲ እንመልከት። ከዚህም በተጨማሪ ሁለት ታማኝ እስራኤላውያን ከተዉት ምሳሌ የምናገኘው ትምህርት፣ ይሖዋን በጽናት እንድናገለግለውና ላደረገልን ነገሮች አመስጋኝ እንድንሆን እንዴት እንደሚረዳን እንመርምር።

ይሖዋን እንድታስታውስ የሚያደርጉ ምክንያቶች

እስራኤላውያን በግብፅ በኖሩባቸው ዘመናት ይሖዋ ፈጽሞ አልረሳቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ይሖዋ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አሰበ’ ይላል። (ዘፀ. 2:23, 24) እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ ለማውጣት የወሰደው እርምጃ ፈጽሞ የሚረሳ አልነበረም።

ይሖዋ በግብፅ ምድር ላይ ዘጠኝ መቅሰፍቶችን ያመጣ ሲሆን የፈርዖን አስማተኞች እነዚህን መቅሰፍቶች ማስቆም አልቻሉም። ያም ሆኖ ፈርዖን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ አሻፈረኝ በማለት ይሖዋን ተገዳደረው። (ዘፀ. 7:14 እስከ 10:29) አሥረኛው መቅሰፍት ሲመጣ ግን ይህ ትዕቢተኛ መሪ አምላክን ለመታዘዝ ተገደደ። (ዘፀ. 11:1-10፤ 12:12) የእስራኤል ብሔር ከብዙ ድብልቅ ሕዝብ ጋር በመሆን በሙሴ እየተመሩ ግብፅን ለቅቀው ወጡ፤ በአጠቃላይ ከግብፅ የወጣው ሕዝብ ወደ 3,000,000 እንደሚጠጋ ይገመታል። (ዘፀ. 12:37, 38) ሆኖም ሕዝቡ ብዙም ሳይርቅ ፈርዖን ሐሳቡን ቀየረ። ፈርዖን ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን ያካተተው ሠራዊቱ የቀድሞ ባሪያዎቹን አሳድዶ እንዲይዛቸው ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በወቅቱ የግብፅ ሠራዊት በኃይሉ ተወዳዳሪ አልነበረውም። በዚህ መሃል ይሖዋ፣ ሙሴ ሕዝቡን በቀይ ባሕርና በተራሮች መሃል ወደሚገኝ ፊሀሒሮት የተባለ መውጫ የሌለው የሚመስል ቦታ እንዲመራቸው ነገረው።—ዘፀ. 14:1-9

ፈርዖንም እስራኤላውያን ወጥመድ ውስጥ እንደገቡ ስለተሰማው ሠራዊቱ በእስራኤላውያን ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ትእዛዝ ሰጠ። ይሁን እንጂ ይሖዋ በግብፃውያንና በእስራኤላውያን መካከል የደመናና የእሳት ዓምድ እንዲቆም በማድረግ ግብፃውያን ወደ እስራኤላውያን እንዳይጠጉ አገዳቸው። ከዚያም አምላክ ውኃው በግራና በቀኝ እስከ 15 ሜትር ከፍታ ድረስ እንደ ግድግዳ እንዲቆም በማድረግ ቀይ ባሕርን ለሁለት ከፈለው፤ በዚህ መንገድ ለእስራኤላውያን በባሕሩ መካከል መተላለፊያ አበጀላቸው። በመሆኑም እስራኤላውያን ባሕሩን በደረቅ ምድር ላይ መሻገር ጀመሩ። ግብፃውያን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ሲደርሱ እስራኤላውያን ባሕሩን አቋርጠው ሲወጡ ተመለከቷቸው።—ዘፀ. 13:21፤ 14:10-22

አስተዋይ የሆነ መሪ በዚህ ጊዜ እስራኤላውያንን ማሳደዱን ያቆም ነበር። ከልክ በላይ በራሱ ይተማመን የነበረው ፈርዖን ግን ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ እንዲገቡ አዘዘ። ግብፃውያን እስራኤላውያንን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ላይ ከመድረሳቸው በፊት የእብደት ግልቢያቸው ተገታ። ይሖዋ የሠረገላዎቻቸውን መሽከርከሪያዎች ስላቆላለፈባቸው ጉዟቸውን መቀጠል አልቻሉም።—ዘፀ. 14:23-25፤ 15:9

ግብፃውያን ከጦር ሠረገሎቻቸው ጋር ሲታገሉ እስራኤላውያን በሙሉ በስተ ምሥራቅ ወዳለው የባሕሩ ዳርቻ ደረሱ። በዚህ ጊዜ ሙሴ በቀይ ባሕር ላይ እጁን ዘረጋ። ይሖዋም እንደ ግድግዳ ቀጥ ብሎ የቆመውን ውኃ ወደ ቦታው እንዲመለስ አደረገው። ባሕሩ በፈርዖንና በሠራዊቱ ላይ በመደርመስ አሰመጣቸው። ከእነዚህ የአምላክ ጠላቶች መካከል አንድም ሰው አልተረፈም። በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ከአሳዳጆቻቸው ነፃ ወጡ!—ዘፀ. 14:26-28፤ መዝ. 136:13-15

ይህን የሰሙ በአካባቢው የሚኖሩ ብሔራት በፍርሃት ራዱ፤ እነዚህ ብሔራት ከብዙ ዓመታት በኋላም እንኳ ፍርሃታቸው አልለቀቃቸውም ነበር። (ዘፀ. 15:14-16) እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ረዓብ ለሁለት እስራኤላውያን እንዲህ ብላቸዋለች፦ “እናንተንም መፍራት [አደረብን]፣ . . . ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ . . . ሰምተናል።” (ኢያሱ 2:9, 10) እነዚህ አረማውያን እንኳ ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ ያወጣቸው እንዴት እንደሆነ አልረሱም ነበር። በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው እስራኤላውያን ይሖዋን እንዲያስታውሱ የሚያደርጓቸው በርካታ ምክንያቶች ነበሯቸው።

‘እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቃቸው’

እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ከተሻገሩ በኋላ ‘ጭልጥ ያለና አስፈሪ’ ወደሆነው የሲና ምድረ በዳ ደረሱ። ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብና ‘ውሃ በማይገኝበት ደረቅ መሬት’ ላይ በተጓዙበት ወቅት የይሖዋ እንክብካቤ አልተለያቸውም። ይሖዋ “[እስራኤልን] በምድረ በዳ፣ ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አገኘው፤ ጋሻ ሆነው፤ ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው” በማለት ሙሴ ተናግሯል። (ዘዳ. 8:15፤ 32:10) አምላክ እስራኤላውያንን የተንከባከባቸው እንዴት ነበር?

ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ “ከሰማይ እንጀራ” አዘነበላቸው፤ “በምድረ በዳው ላይ” ያገኙት ይህ ምግብ መና ተብሎ ይጠራ ነበር። (ዘፀ. 16:4, 14, 15, 35) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ “ከጽኑ ዐለት” ውኃ ያፈልቅላቸው ነበር። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ባሳለፏቸው 40 ዓመታት ውስጥ የይሖዋ በረከት ስላልተለያቸው ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አላበጠም። (ዘዳ. 8:4) ይሖዋ፣ እስራኤላውያን አመስጋኝ መሆናቸውን ለማሳየት ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸው ነበር? ሙሴ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ዐይኖቻችሁ ያዩዋቸውን ነገሮች እንዳትረሱ፣ ደግሞም በሕይወት እስካላችሁ ድረስ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ብቻ ተጠንቀቁ፣ ነቅታችሁም ራሳችሁን ጠብቁ።” (ዘዳ. 4:9) ሕዝቡ ይሖዋ እነሱን ለማዳን ያደረጋቸውን ነገሮች በአድናቆት የሚያስታውሱ ከሆነ ሁልጊዜ እሱን ለማገልገልና ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ይነሳሳሉ። ታዲያ እስራኤላውያን ምን ያደርጉ ይሆን?

መርሳት ምስጋና ቢስ ያደርጋል

ሙሴ “አባት የሆነህን ዐለት ከዳኸው፤ የወለደህን አምላክ ረሳኸው” በማለት ተናግሯል። (ዘዳ. 32:18) ብዙም ሳይቆይ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ በቀይ ባሕር ምን እንዳደረገላቸውም ሆነ በምድረ በዳ እንዴት እንደተንከባከባቸው የዘነጉ ሲሆን ያደረገላቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ ረሱ። እስራኤላውያን በይሖዋ ላይ ዓመፁ።

በአንድ ወቅት፣ እስራኤላውያን ውኃ ማግኘት የማይቻል ስለመሰላቸው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። (ዘኍ. 20:2-5) በሕይወት ያቆያቸውን መና ደግሞ “ይህን የማይረባ ምግብ ሰውነታችን ተጸይፎታል” በማለት አጣጣሉት። (ዘኍ. 21:5) “ምነው በግብፅ ወይም በዚህ ምድረ በዳ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! . . . አለቃ መርጠን ወደ ግብፅ እንመለስ” በማለት አምላክ በወሰደው እርምጃ ላይ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ሙሴም እንዲመራቸው እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።—ዘኍ. 14:2-4

ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ታዛዥ አለመሆናቸውን ሲመለከት ምን ተሰማው? አንድ መዝሙራዊ በዚያን ጊዜ የተከናወነውን ሁኔታ በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት! በበረሓስ ምን ያህል አሳዘኑት! ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጡት። እነርሱን በዚያን ቀን ከጠላት የታደገበትን፣ ያን ኀይሉን አላስታወሱም፤ በግብፅ ያደረገውን ታምራዊ ምልክት . . . አላሰቡም።” (መዝ. 78:40-43) አዎን፣ እስራኤላውያን የተደረገላቸውን ነገር መርሳታቸው ይሖዋን እጅግ አሳዝኖታል!

ይሖዋን ያልረሱ ሁለት ሰዎች

ይሁንና ይሖዋን ያልረሱ አንዳንድ እስራኤላውያን ነበሩ። ከእነዚህም መካከል ኢያሱና ካሌብ ይገኙበታል። እነዚህ ሁለት ሰዎች ተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ ከቃዴስ በርኔ ከተላኩት 12 ሰላዮች መካከል ነበሩ። አሥሩ ሰላዮች መጥፎ ዜና ይዘው ሲመጡ ኢያሱና ካሌብ ግን ሕዝቡን እንዲህ አሏቸው፦ “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት። እግዚአብሔር በእኛ ደስ ከተሰኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል። ብቻ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ።” ሕዝቡ ይህንን ሲሰሙ ኢያሱና ካሌብን ሊወግሯቸው ተነሱ። ኢያሱና ካሌብ ግን በይሖዋ በመታመን በአቋማቸው ጸኑ።—ዘኍ. 14:6-10

ከዓመታት በኋላ ካሌብ ኢያሱን እንዲህ ብሎታል፦ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም ትክክለኛውን ማስረጃ ይዤለት መጣሁ፤ አብረውኝ ወደዚያ የወጡት ወንድሞቼ ግን፣ የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ ሆኖም እኔ አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት።” (ኢያሱ 14:6-8) ካሌብና ኢያሱ በአምላክ በመታመን የደረሱባቸውን የተለያዩ ችግሮች ተቋቁመው ጸንተዋል። በሕይወት እስካሉ ድረስ ይሖዋን ላለመርሳት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል።

ካሌብና ኢያሱ አመስጋኞችም ነበሩ፤ ይሖዋ ሕዝቡን ለም ወደሆነ ምድር እንደሚያስገባቸው የገባውን ቃል በመፈጸሙ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በእርግጥም እስራኤላውያን በሕይወት እንዲቆዩ ላደረጋቸው አምላክ አመስጋኞች መሆን ነበረባቸው። ኢያሱ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ለቀድሞ አባቶቻቸው ይሰጣቸው ዘንድ የማለላቸውን ምድር ሁሉ ለእስራኤል ሰጠ፤ . . . እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከሰጠው መልካም የተስፋ ቃል አንዳችም አልቀረም፤ ሁሉም ተፈጽሞአል።” (ኢያሱ 21:43, 45) እኛስ እንደ ካሌብና ኢያሱ አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

አመስጋኝ ሁን

ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ ሰው “ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር ምን ልክፈለው?” የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። (መዝ. 116:12) አምላክ የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንዲሁም መንፈሳዊ መመሪያ የሰጠን ከመሆኑም በላይ እጅግ ታላቅ የመዳን ዝግጅት አድርጎልናል፤ ይህን ሁሉ ውለታውን ለዘላለም ከፍለን መጨረስ አንችልም። በእርግጥም የይሖዋን ውለታ ፈጽሞ ልንከፍለው አንችልም። ያም ቢሆን ሁላችንም ላደረገልን ነገር ምስጋናችንን መግለጽ እንችላለን።

ይሖዋ የሰጠን ምክር ችግር ውስጥ እንዳትገባ ጠብቆሃል? አምላክ ይቅር ባይ መሆኑ እንደገና ንጹሕ ሕሊና እንድታገኝ ረድቶሃል? አምላክ እንዲህ ማድረጉ ዘላቂ ጥቅም አስገኝቶልሃል፤ ስለሆነም ሁልጊዜ ልታመሰግነው ይገባል። ሳንድራ የተባለች የ14 ዓመት ወጣት ከባድ ችግር አጋጥሟት የነበረ ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ ልትወጣው ችላለች። ሳንድራ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ እንዲረዳኝ የጸለይኩ ሲሆን እንዴት እንደረዳኝ ሳስበው በጣም ይገርመኛል። አባቴ ምሳሌ 3:5, 6⁠ን በተደጋጋሚ ይጠቅስልኝ የነበረው ለምን እንደሆነ አሁን ገብቶኛል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ ‘በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።’ ይሖዋ እስካሁን እንደረዳኝ ሁሉ ወደፊትም ከጎኔ እንደማይለይ እተማመናለሁ።”

በፈተናዎች በመጽናት ይሖዋን እንደምታስታውስ አሳይ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋን ከማስታወስ ጋር ተያያዥነት ስላለው ሌላ ባሕርይ ሲጠቅስ እንዲህ ይላል፦ “በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድላችሁ ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ወደ ፍጻሜ እንዲያደርስ አድርጉ።” (ያዕ. 1:4) ‘በሁሉም ረገድ ምንም የማይጎድለን ፍጹማን’ መሆን ምን ነገሮችን ያካትታል? ይህ በይሖዋ በመታመንና በደረሰብን ፈተና ላለመሸነፍ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ያጋጠሙንን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችሉንን ባሕርያት ማዳበርን ይጨምራል። በዚህ መንገድ መጽናታችን ፈተናዎቹን በምናልፍበት ጊዜ ታላቅ እርካታ ያስገኝልናል። ፈተናዎቹ ደግሞ ማለፋቸው አይቀርም።—1 ቆሮ. 10:13

በርካታ የጤና እክሎች ያጋጠሙት ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገለ አንድ ወንድም ለመጽናት የረዳው ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ምን ለማድረግ እንደምፈልግ ከማሰብ ይልቅ ይሖዋ ምን እያደረገ እንዳለ ለማሰብ እሞክራለሁ። ንጹሕ አቋምን መጠበቅ ሲባል በራሴ ፍላጎት ላይ ሳይሆን በአምላክ ዓላማ ላይ ማተኮር ማለት ነው። ችግሮች ሲደርሱብኝ ‘ይሖዋ፣ ይህ በእኔ ላይ እንዲደርስ ለምን ፈቀድክ?’ አልልም። ከዚህ ይልቅ ያልጠበቅኩት ችግር በሚያጋጥመኝ ጊዜም እንኳ ይበልጥ ወደ ይሖዋ በመቅረብ እሱን ማገልገሌን እቀጥላለሁ።”

በዛሬው ጊዜ የክርስቲያን ጉባኤ ይሖዋን የሚያመልከው “በመንፈስና በእውነት” ነው። (ዮሐ. 4:23, 24) የእስራኤል ብሔር ካደረገው በተቃራኒ በቡድን ደረጃ ሲታይ እውነተኛ ክርስቲያኖች መቼም ቢሆን አምላክን አይረሱትም። ይሁንና የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆናችን ብቻ በግለሰብ ደረጃ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን እንድንኖር አያደርገንም። ካሌብና ኢያሱ እንዳደረጉት ሁሉ እያንዳንዳችን ይሖዋ ላደረገልን ነገሮች አመስጋኝ መሆንና እሱን በጽናት ማገልገል ይኖርብናል። አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናትም እንኳ ይሖዋ ለእያንዳንዳችን መመሪያ መስጠቱንና እንክብካቤ ማድረጉን ቀጥሏል፤ በመሆኑም አመስጋኞች እንድንሆን የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉን።

ኢያሱ እንደሠራው የድንጋይ ክምር ሁሉ አምላክ ሕዝቦቹን እንዳዳናቸው የሚገልጹት ዘገባዎችም አገልጋዮቹን መቼም ቢሆን እንደማይተዋቸው ማረጋገጫ ይሰጡናል። በመሆኑም አንተም እንደሚከተለው በማለት የጻፈው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት እንደሚኖርህ ተስፋ እናደርጋለን፦ “[የይሖዋን፣ NW] ሥራ አስታውሳለሁ፤ የጥንት ታምራትህን በእርግጥ አስታውሳለሁ፤ ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።”—መዝ. 77:11, 12

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የእስራኤል ብሔር ‘ደረቅ በሆነው መሬት’ ላይ መጓዝ ነበረበት

[የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን በቃዴስ በርኔ ሰፍረው በነበረበት ወቅት ተስፋይቱን ምድር የሚሰልሉ ሰዎች ተልከው ነበር

[የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እስራኤላውያን ለበርካታ ዓመታት በምድረ በዳ ከተንከራተቱ በኋላ ለም ወደሆነችው ተስፋይቱ ምድር በመግባታቸው አመስጋኝ መሆን ነበረባቸው

[የሥዕል ምንጭ]

Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በይሖዋ ዓላማ ላይ ማተኮራችን የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ችግር በጽናት ለመቋቋም ይረዳናል