በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታላቁ ሙሴ የሚጫወተውን ሚና መረዳት

ታላቁ ሙሴ የሚጫወተውን ሚና መረዳት

ታላቁ ሙሴ የሚጫወተውን ሚና መረዳት

“ይሖዋ አምላክ ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል። እሱ የሚነግራችሁንም ነገር ሁሉ ስሙ።”—ሥራ 3:22

1. ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ውስጥ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት አንድ ሕፃን ሲወለድ በሰማይ የሚገኙ እልፍ አእላፋት መላእክት አምላክን ያወደሱ ሲሆን ይህን ሲያደርጉም አንዳንድ እረኞች ሰምተዋቸው ነበር። (ሉቃስ 2:8-14) ይህ ልጅ ሠላሳ ዓመት ሲሆነው በምድር ላይ አገልግሎቱን ጀመረ፤ አገልግሎቱ የዘለቀው ለሦስት ዓመት ተኩል ብቻ ቢሆንም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ጉልህ ለውጥ አምጥቷል። በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ፊሊፕ ሻፍ የተባሉ ታዋቂ የታሪክ ምሑር ይህንን ሰው በተመለከተ እንዲህ በማለት በአድናቆት ተናግረዋል፦ “አንዲት ዓረፍተ ነገር ያልጻፈ ቢሆንም ብዙዎች ስለ እሱ ለመጻፍ ብዕራቸውን እንዲያነሱ ገፋፍቷቸዋል፤ እንዲሁም [ያስተማራቸውና ያደረጋቸው ነገሮች] ለበርካታ ስብከቶች፣ ንግግሮችና ውይይቶች ብሎም ጥልቀት ያላቸው መረጃዎችን ለያዙ መጻሕፍት እንዲሁም ለሥነ ጥበብ ሥራዎችና ለውዳሴ መዝሙሮች መነሻ ሆነዋል። በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን ከተነሱት በርካታ ታላላቅ ሰዎች መካከል የእሱን ያህል የተጻፈለት ወይም የተነገረለት አንድም ሰው የለም።” ይህ ሁሉ አድናቆት የተቸረው ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2. ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስንና ያከናወነውን አገልግሎት በተመለከተ ምን ብሏል?

2 ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ስላከናወነው አገልግሎት የሚገልጽ ዘገባ ከጻፈ በኋላ በመደምደሚያው ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እርግጥ ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ እነዚህ ሁሉ በዝርዝር ቢጻፉ ዓለም ራሱ የተጻፉትን ጥቅልሎች ለማስቀመጥ የሚበቃ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።” (ዮሐ. 21:25) ዮሐንስ፣ በርካታ ነገሮች በተከናወኑበት በዚያ ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ከተናገራቸውና ካደረጋቸው ነገሮች መካከል መዘገብ የሚችለው በጣም ጥቂቱን ብቻ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን ዮሐንስ በወንጌል ዘገባው ላይ ያሰፈራቸው በታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጣቸው ክንውኖች ከፍተኛ ጥቅም አላቸው።

3. ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ያለንን ግንዛቤ ማስፋት የምንችለው እንዴት ነው?

3 ጠቃሚ ከሆኑት ከአራቱ የወንጌል ዘገባዎች በተጨማሪ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም የኢየሱስን ሕይወት በተመለከተ እምነታችንን የሚያጠናክሩ ዝርዝር ሐሳቦችን አስፍረዋል። ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ስለኖሩ አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ያለንን ግንዛቤ የሚያሰፉ መረጃዎችን ይዘዋል። እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

ለክርስቶስ ጥላ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች

4, 5. ለኢየሱስ ጥላ ሆነው ያገለገሉት እነማን ነበሩ? ጥላ የሆኑለትስ በምን መንገዶች ነው?

4 ዮሐንስና ሦስቱ የወንጌል ጸሐፊዎች እንደጠቆሙት ኢየሱስ የአምላክ ቅቡዕ እንዲሁም እጩ ንጉሥ በመሆን ለሚጫወተው ሚና ሙሴ፣ ዳዊትና ሰለሞን ጥላ ሆነው አገልግለዋል። በጥንት ዘመን የኖሩት እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ለኢየሱስ ጥላ ሆነው ያገለገሉት በምን መንገድ ነበር? ስለ እነዚህ ሰዎች ከሚገልጹት ዘገባዎችስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

5 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሙሴ ነቢይና አስታራቂ እንዲሁም ነፃ አውጪ ወይም አዳኝ እንደነበረ ይገልጻል። ኢየሱስም እንዲሁ ነው። ዳዊት እረኛና የእስራኤልን ጠላቶች ድል ያደረገ ንጉሥ ነበር። ኢየሱስም እረኛና ድል አድራጊ ንጉሥ ነው። (ሕዝ. 37:24, 25) ሰለሞን ለአምላክ ታማኝ እያለ ጠቢብ ንጉሥ የነበረ ሲሆን በግዛት ዘመኑም እስራኤላውያን በሰላም ይኖሩ ነበር። (1 ነገ. 4:25, 29) ኢየሱስም በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለው ከመሆኑም ሌላ “የሰላም ልዑል” ተብሏል። (ኢሳ. 9:6) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ክርስቶስ ኢየሱስ በጥንት ዘመን ከኖሩት ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ሚና ይጫወታል፤ ይሁንና ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያለው ድርሻ ከእነሱ እጅግ የላቀ ነው። እስቲ በመጀመሪያ ኢየሱስን ከሙሴ ጋር በማወዳደር በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ይበልጥ ለመረዳት እንሞክር።

ሙሴ ለኢየሱስ ጥላ ነበር

6. ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን መስማት አስፈላጊ መሆኑን የገለጸው እንዴት ነበር?

6 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የጴንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሙሴ የተናገረውን ትንቢት በመጥቀስ ትንቢቱ በኢየሱስ ላይ ፍጻሜውን እንዳገኘ ገልጿል። ጴጥሮስ ይህንን የተናገረው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለተሰበሰቡ አይሁዳውያን ነበር። ጴጥሮስና ዮሐንስ፣ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረ ለማኝ በፈወሱበት ጊዜ ሕዝቡ “እጅግ ተደንቀው” ሁኔታውን ለማየት ግር ብለው እየሮጡ ወደ ቤተ መቅደሱ መጡ። ጴጥሮስ ይህ አስደናቂ ድርጊት የተፈጸመው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባገኙት የይሖዋ መንፈስ አማካኝነት እንደሆነ ገለጸ። ከዚያም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በመጥቀስ እንደሚከተለው በማለት ተናገረ፦ “ደግሞም ሙሴ እንዲህ ብሏል፦ ‘ይሖዋ አምላክ ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል። እሱ የሚነግራችሁንም ነገር ሁሉ ስሙ።’”—ሥራ 3:11, 22, 23፤ ዘዳግም 18:15, 18, 19ን አንብብ።

7. ጴጥሮስ ከሙሴ ስለሚበልጠው ነቢይ የተናገረውን ሐሳብ አድማጮቹ ሳያውቁት አይቀሩም የምንለው ለምንድን ነው?

7 ጴጥሮስን ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ሙሴ የተናገረውን ሐሳብ ሳያውቁት አይቀሩም። አይሁዳውያን በመሆናቸው ለሙሴ ከፍተኛ አክብሮት ነበራቸው። (ዘዳ. 34:10) ከሙሴ የሚበልጠው ነቢይ የሚመጣበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ይህ ነቢይ ግን እንደ ሙሴ በአምላክ የተቀባ ሰው ብቻ ሳይሆን “የተመረጠው [የይሖዋ] ክርስቶስ” ማለትም መሲሑ ነው።—ሉቃስ 23:35፤ ዕብ. 11:26

ኢየሱስና ሙሴ የሚመሳሰሉባቸው መንገዶች

8. ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን ሕይወት ከሙሴ ሕይወት ጋር የሚያመሳስሉት አንዳንድ ክንውኖች ምንድን ናቸው?

8 ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው ሕይወት በአንዳንድ መንገዶች ከሙሴ ሕይወት ጋር ይመሳሰላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴም ሆነ ኢየሱስ ሕፃናት ሳሉ ጨካኝ በሆኑ ገዥዎች ከተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ አምልጠዋል። (ዘፀ. 1:22 እስከ 2:10፤ ማቴ. 2:7-14) ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም ‘ከግብፅ ተጠርተዋል።’ ነቢዩ ሆሴዕ “እስራኤል ገና ሕፃን ሳለ ወደድሁት፤ ልጄንም ከግብፅ ጠራሁት” ሲል ጽፏል። (ሆሴዕ 11:1) ሆሴዕ እየተናገረ ያለው የእስራኤል ብሔር አምላክ በሾመው በሙሴ እየተመራ ከግብፅ ስለወጣበት ጊዜ ነበር። (ዘፀ. 4:22, 23፤ 12:29-37) ይሁን እንጂ ሆሴዕ የተናገረው ስላለፈው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ስለሚፈጸም ክንውን ጭምር ነበር። የሆሴዕ ትንቢት፣ ንጉሥ ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ይዘው ከግብፅ በተመለሱበት ወቅት ተፈጽሟል።—ማቴ. 2:15, 19-23

9. (ሀ) ሙሴና ኢየሱስ ምን ተአምራት ፈጽመዋል? (ለ) ኢየሱስንና ሙሴን የሚያመሳስሏቸውን ሌሎችን ነገሮች ጥቀስ። ( “ኢየሱስና ሙሴ የሚመሳሰሉባቸው ሌሎች መንገዶች” የሚለውን በገጽ 26 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

9 ሙሴም ሆነ ኢየሱስ ተአምራትን የፈጸሙ ሲሆን ይህም አምላክ ይደግፋቸው እንደነበር ያሳያል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተአምራት እንደፈጸመ የተጠቀሰው የመጀመሪያው ሰው ሙሴ ነበር። (ዘፀ. 4:1-9) ለምሳሌ ያህል፣ ሙሴ ከውኃ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተአምራትን ፈጽሟል፤ በአባይ ወንዝ እንዲሁም በምንጮች፣ በቦዮችና በኩሬዎች ውስጥ የሚገኘው ውኃ ወደ ደም እንዲለወጥ፣ ቀይ ባሕር ለሁለት እንዲከፈል እንዲሁም በምድረ በዳ ከዐለት ውኃ እንዲፈልቅ አድርጓል። (ዘፀ. 7:19-21፤ 14:21፤ 17:5-7) ኢየሱስም ከውኃ ጋር በተያያዘ ተአምራት ፈጽሟል። ኢየሱስ የፈጸመው የመጀመሪያው ተአምር በአንድ ሠርግ ላይ ውኃን ወደ ወይን መቀየሩ ነበር። (ዮሐ. 2:1-11) ከጊዜ በኋላም በማዕበል ይናወጥ የነበረውን የገሊላ ባሕር ጸጥ አሰኝቶታል። እንዲያውም በአንድ ወቅት በባሕር ላይ እየተራመደ ሄዷል! (ማቴ. 8:23-27፤ 14:23-25) ሙሴና ታላቁ ሙሴ የሆነው ኢየሱስ የሚመሳሰሉባቸውን ሌሎች መንገዶች  በገጽ 26 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ መመልከት ይቻላል።

ክርስቶስ ነቢይ በመሆን የሚጫወተውን ሚና መረዳት

10. እውነተኛ ነቢይ ከሚያከናውናቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ሙሴ እንዲህ ዓይነት ነቢይ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

10 ብዙ ሰዎች ነቢይ የሚባለው ስለ ወደፊቱ ጊዜ ትንቢት የሚናገር ሰው እንደሆነ ያስባሉ፤ ይሁንና ትንቢት መናገር ነቢይ የሆነ ሰው ከሚያከናውናቸው ነገሮች አንዱ ብቻ ነው። እውነተኛ ነቢይ፣ በመንፈስ ተመርቶ “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” የሚያውጅ የይሖዋ ቃል አቀባይ ነው። (ሥራ 2:11, 16, 17) እንዲህ ያለው ነቢይ ከሚያከናውናቸው ነገሮች መካከል ስለ ወደፊቱ ጊዜ ትንቢት መናገር፣ የይሖዋን ዓላማ የተለያዩ ገጽታዎች መግለጽ እንዲሁም የአምላክን የፍርድ መልእክት ማወጅ ይገኙበታል። ሙሴ እንዲህ ያሉ ተግባራትን የሚያከናውን ነቢይ ነበር። በግብፅ ላይ ስለሚመጡት አሥር መቅሰፍቶች አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። በሲና ምድረ በዳ የሕጉን ቃል ኪዳን ለሕዝቡ ነግሯቸዋል። እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ለሕዝቡ አስተምሯል። ያም ሆኖ ከጊዜ በኋላ ከሙሴ የሚበልጥ ነቢይ እንደሚመጣ ተነግሮ ነበር።

11. ኢየሱስ ከሙሴ የሚበልጥ ነቢይ መሆኑን ያስመሠከረው እንዴት ነው?

11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ዘካርያስ፣ ከልጁ ከዮሐንስ ጋር በተያያዘ የአምላክ ዓላማ ምን እንደሆነ በተናገረ ጊዜ ነቢይ ሆኖ አገልግሎ ነበር። (ሉቃስ 1:76) አጥማቂው ዮሐንስ በመባል የሚታወቀው የዘካርያስ ልጅ፣ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው ከሙሴ የሚበልጠው ነቢይ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ አውጇል። (ዮሐ. 1:23-36) ኢየሱስ ነቢይ እንደመሆኑ መጠን በርካታ ትንቢቶችን ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሞቱ ማለትም እንዴት እንደሚሞት፣ የት እንደሚሞት እንዲሁም ማን እንደሚገድለው አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 20:17-19) በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ኢየሩሳሌምም ሆነች ቤተ መቅደሷ እንደሚጠፉ የተናገረ ሲሆን ይህም አድማጮቹን አስደንቋቸው ነበር። (ማር. 13:1, 2) ኢየሱስ ስለ ዘመናችንም ትንቢት ተናግሯል።—ማቴ. 24:3-41

12. (ሀ) ኢየሱስ ለዓለም አቀፉ የስብከት ዘመቻ መሠረት የጣለው እንዴት ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ያለብን እንዴት ነው?

12 ኢየሱስ ነቢይ ብቻ ሳይሆን ሰባኪና አስተማሪም ነበር። ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች የሰበከ ሲሆን ይህን ወንጌል የእሱን ያህል በድፍረት ያወጀ ማንም የለም። (ሉቃስ 4:16-21, 43) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ተወዳዳሪ የሌለው አስተማሪ ነበር። ሲያስተምር የሰሙት አንዳንድ ሰዎች “ማንም እንደዚህ ሰው ተናግሮ አያውቅም” ብለዋል። (ዮሐ. 7:46) ኢየሱስ ምሥራቹን በቅንዓት ያወጀ ከመሆኑም ሌላ ተከታዮቹንም ልክ እንደ እሱ ስለ መንግሥቱ በቅንዓት እንዲሰብኩ አበረታቷቸዋል። በዚህ መንገድ ዛሬም ለሚከናወነው ዓለም አቀፍ የስብከትና የማስተማር ዘመቻ መሠረት ጥሏል። (ማቴ. 28:18-20፤ ሥራ 5:42) ባለፈው ዓመት ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ የክርስቶስ ተከታዮች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በመስበክና ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር 1,500,000,000 ያህል ሰዓት አሳልፈዋል። አንተስ በዚህ ሥራ አቅምህ የሚፈቅድልህን ያህል እየተካፈልክ ነው?

13. ‘ነቅተን እንድንኖር’ ምን ይረዳናል?

13 ይሖዋ፣ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ እንደሚያስነሳ የተናገረውን ትንቢት እንደፈጸመው ምንም ጥያቄ የለውም። ይህንን ማወቅህ ለአንተ ምን ትርጉም አለው? በቅርቡ ስለሚፈጸሙት ነገሮች በመንፈስ መሪነት የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ያለህን እምነት ይበልጥ አጠናክሮልሃል? አዎን፣ ታላቁ ሙሴ በተወው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን አምላክ በቅርቡ ከሚፈጽማቸው ነገሮች ጋር በተያያዘ ‘ነቅተን እንድንኖር እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታችንን እንድንጠብቅ’ ይረዳናል።—1 ተሰ. 5:2, 6

ክርስቶስ አስታራቂ በመሆን ለሚጫወተው ሚና አድናቆት ይኑራችሁ

14. ሙሴ በእስራኤላውያንና በአምላክ መካከል አስታራቂ ሆኖ ያገለገለው እንዴት ነበር?

14 እንደ ሙሴ ሁሉ ኢየሱስም አስታራቂ ነበር። አስታራቂ በሁለት ወገኖች መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር የሕግ ቃል ኪዳን በገባ ጊዜ ሙሴ እንደ አስታራቂ ወይም መካከለኛ ሆኖ አገልግሏል። የያዕቆብ ልጆች የአምላክን ሕግጋት እስከታዘዙ ድረስ የአምላክ ልዩ ንብረት ማለትም የእሱ ጉባኤ ሆነው መቀጠል ይችላሉ። (ዘፀ. 19:3-8) ይህ ቃል ኪዳን ከ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ እስከ አንደኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ድረስ ይሠራ ነበር።

15. ኢየሱስ ከሙሴ የላቀ አስታራቂ የሆነው በምን መንገድ ነው?

15 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይሖዋ ‘የአምላክ እስራኤል’ ከተባለው አዲስ የእስራኤል ብሔር ጋር ከቀድሞው የተሻለ ቃል ኪዳን ገባ፤ ይህ ብሔር ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ነው። (ገላ. 6:16) ሙሴ መካከለኛ የሆነለት ቃል ኪዳን አምላክ በድንጋይ ላይ የጻፋቸውን ሕግጋት ያካተተ ሲሆን ኢየሱስ አስታራቂ ወይም መካከለኛ የሆነለት ቃል ኪዳን ግን ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። አምላክ የዚህን ቃል ኪዳን ሕግጋት የጻፈው በሰዎች ልብ ላይ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:5ን እና ዕብራውያን 8:10ን አንብብ።) በአሁኑ ጊዜ ‘የአምላክ እስራኤል’ የአምላክ ልዩ ንብረት ማለትም የመሲሐዊውን መንግሥት ‘ፍሬ የሚያፈራ ሕዝብ’ ነው። (ማቴ. 21:43) የዚህ መንፈሳዊ ብሔር አባላት በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ይታቀፋሉ። ያም ቢሆን በአዲሱ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ የሚሆኑት እነሱ ብቻ አይደሉም። በአሁኑ ጊዜ በሞት አንቀላፍተው የሚገኙ ብዙዎችን ጨምሮ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች በዚህ የላቀ ቃል ኪዳን የተነሳ ዘላለማዊ በረከቶች ያገኛሉ።

ክርስቶስ አዳኝ በመሆን የሚጫወተውን ሚና ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱ

16. (ሀ) ይሖዋ፣ እስራኤላውያንን ለማዳን ሙሴን የተጠቀመበት እንዴት ነበር? (ለ) በዘፀአት 14:13 መሠረት መዳን የሚገኘው ከማን ነው?

16 እስራኤላውያን ከግብፅ ከመውጣታቸው በፊት በነበረው ምሽት ላይ ከልጆቻቸው መካከል አንዳንዶቹ ትልቅ አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። በዚያ ምሽት የአምላክ መልአክ በግብፅ ምድር በማለፍ የበኩር ልጆችን በሙሉ ለመግደል ተዘጋጅቶ ነበር። የእስራኤላውያን የበኩር ልጆች ከአደጋው መዳን የሚችሉት ሕዝቡ የፋሲካን በግ ደም በበራቸው መቃንና ጉበን ላይ ከቀቡ ብቻ እንደሆነ ይሖዋ ለሙሴ ነግሮታል። (ዘፀ. 12:1-13, 21-23) የተፈጸመውም ይኸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ መላው ብሔር ከባድ አደጋ ተጋረጠበት። እስራኤላውያን በቀይ ባሕርና በሚያሳድዷቸው የግብፃውያን የጦር ሠረገሎች መካከል በመሆናቸው ማምለጥ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ገቡ። በዚህ ጊዜም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ቀይ ባሕር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ለሁለት እንዲከፈል በማድረግ እስራኤላውያንን አዳናቸው።—ዘፀ. 14:13, 21

17, 18. ኢየሱስ ከሙሴ የበለጠ አዳኝ የሆነው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

17 ይሖዋ በሙሴ ዘመን ሕዝቡን አስደናቂ በሆነ መንገድ ያዳናቸው ሲሆን በኢየሱስ በኩል የፈጸመው ማዳን ግን ከዚህ እጅግ የላቀ ነው። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ከኃጢአት ባርነት ነፃ የሚወጡት ወይም የሚድኑት በኢየሱስ አማካኝነት ነው። (ሮም 5:12, 18) በኢየሱስ አማካኝነት የሚያገኙት መዳን ደግሞ “ዘላለማዊ መዳን” ነው። (ዕብ. 9:11, 12) ኢየሱስ የሚለው ስም “ይሖዋ አዳኝ ነው” የሚል ትርጉም አለው። አዳኛችን የሆነው ኢየሱስ ከኃጢአታችን ነፃ የሚያወጣን ከመሆኑም በተጨማሪ ወደፊት የተሻለ ሕይወት የምናገኝበትን አጋጣሚ ከፍቶልናል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ከኃጢአት ባርነት ነፃ በማውጣት ከአምላክ ቁጣ ያዳናቸው ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዲመሠርቱ አድርጓቸዋል።—ማቴ. 1:21

18 ኢየሱስ ከኃጢአት ባርነት ሙሉ በሙሉ ነፃ ሲያወጣን ኃጢአት ካስከተላቸው አስከፊ መዘዞች ማለትም ከሕመምና ከሞትም እንድናለን። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ኢየሱስ የ12 ዓመት ሴት ልጁ ወደሞተችበት ኢያኢሮስ ወደሚባል ሰው ቤት በሄደ ጊዜ የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። ኢየሱስ “አትፍራ፣ ብቻ እመን፤ ልጅህ ትድናለች” በማለት ኢያኢሮስን አበረታቶት ነበር። (ሉቃስ 8:41, 42, 49, 50) ኢየሱስ እንዳለውም ልጅቷ ከሞት ተነሳች! ወላጆቿ ምን ያህል እንደተደሰቱ አስበው! ‘በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው በሚወጡበት’ ጊዜም ደስታችን ወሰን አይኖረውም! (ዮሐ. 5:28, 29) በእርግጥም ኢየሱስ አዳኝ ወይም ነፃ አውጪ ነው!—የሐዋርያት ሥራ 5:31ን አንብብ፤ ቲቶ 1:4፤ ራእይ 7:10

19, 20. (ሀ) ኢየሱስ ታላቁ ሙሴ በመሆን በተጫወተው ሚና ላይ ማሰላሰላችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

19 ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለማዳን ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመርዳት እንደምንችል ማወቃችን በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ እንድንካፈል ያነሳሳናል። (ኢሳ. 61:1-3) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ታላቁ ሙሴ በመሆን በሚጫወተው ሚና ላይ ማሰላሰላችን በክፉዎች ላይ የቅጣት ፍርድ ለማስፈጸም ሲመጣ ተከታዮቹን እንደሚያድናቸው ይበልጥ እንድንተማመን ያደርገናል።—ማቴ. 25:31-34, 41, 46፤ ራእይ 7:9, 14

20 አዎን፣ ኢየሱስ ታላቁ ሙሴ ነው። ሙሴ ፈጽሞ ሊያከናውናቸው የማይችላቸውን በርካታ አስደናቂ ነገሮች ፈጽሟል። ኢየሱስ ነቢይ በመሆን የተናገራቸው ነገሮችና አስታራቂ በመሆን ያከናወናቸው ድርጊቶች የመላውን የሰው ዘር ሕይወት ለውጠውታል። ኢየሱስ አዳኝ በመሆን የሚጫወተው ሚና ደግሞ ለሰው ልጆች ጊዜያዊ ብቻ ሳይሆን ዘላለማዊ መዳን አስገኝቶላቸዋል። በጥንት ዘመን ስለኖሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የሚገልጹትን ዘገባዎች በመመርመር ስለ ኢየሱስ ልንማር የምንችላቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ኢየሱስ ታላቁ ዳዊትና ታላቁ ሰለሞን በመሆን ስለተጫወተው ሚና እንመረምራለን።

ልታብራራ ትችላለህ?

ኢየሱስ ከሙሴ የበለጠ

• ነቢይ፣

• አስታራቂ፣

• አዳኝ የሆነው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

  ኢየሱስና ሙሴ የሚመሳሰሉባቸው ሌሎች መንገዶች

□ ይሖዋንና ሕዝቡን ለማገልገል ሲሉ የነበራቸውን ከፍተኛ ቦታ ትተዋል።—2 ቆሮ. 8:9፤ ፊልጵ. 2:5-8፤ ዕብ. 11:24-26

□ ይሖዋ፣ ቅቡዕ ወይም ክርስቶስ አድርጎ ሾሟቸዋል።—ማር. 14:61, 62፤ ዮሐ. 4:25, 26፤ ዕብ. 11:26

□ በይሖዋ ስም የተላኩ ነበሩ።—ዘፀ. 3:13-16፤ ዮሐ. 5:43፤ 17:4, 6, 26

□ ትሑት ነበሩ።—ዘኍ. 12:3፤ ማቴ. 11:28-30

□ ብዙ ሕዝብ መግበዋል።—ዘፀ. 16:12፤ ዮሐ. 6:48-51

□ ፈራጅና ሕግ ሰጪ ነበሩ።—ዘፀ. 18:13፤ ሚል. 4:4፤ ዮሐ. 5:22, 23፤ 15:10

□ በአምላክ ቤት ላይ ተሹመዋል።—ዘኍ. 12:7፤ ዕብ. 3:2-6

□ የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች እንደሆኑ ተገልጿል።—ዕብ. 11:24-29፤ 12:1፤ ራእይ 1:5

□ ሙሴም ሆነ ኢየሱስ ከሞቱ በኋላ አምላክ አስከሬናቸው እንዳይገኝ አድርጓል።—ዘዳ. 34:5, 6፤ ሉቃስ 24:1-3፤ ሥራ 2:31፤ 1 ቆሮ. 15:50፤ ይሁዳ 9