በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ታላቁ ዳዊትና ታላቁ ሰለሞን በመሆን የሚጫወተውን ሚና መረዳት

ኢየሱስ ታላቁ ዳዊትና ታላቁ ሰለሞን በመሆን የሚጫወተውን ሚና መረዳት

ኢየሱስ ታላቁ ዳዊትና ታላቁ ሰለሞን በመሆን የሚጫወተውን ሚና መረዳት

“ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።”—ማቴ. 12:42

1, 2. ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር ሲታይ ሳሙኤል ዳዊትን ለንግሥና እንዲቀባው መታዘዙ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

ነቢዩ ሳሙኤል፣ ወጣቱን ሲመለከተው እረኛ ከመሆን አልፎ ለንጉሥነት ይበቃል ብሎ አላሰበም ነበር። የዚህ ወጣት የትውልድ ከተማ የሆነችው ቤተልሔምም ብትሆን እምብዛም ታዋቂ አልነበረችም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህቺን ከተማ በተመለከተ “በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ” በማለት ይናገራል። (ሚክ. 5:2 የ1954 ትርጉም) ያም ሆኖ ነቢዩ ሳሙኤል፣ አነስተኛ በሆነች ከተማ ውስጥ የተወለደውንና በሰዎች ዘንድ ብዙም ቦታ ያልተሰጠውን ይህን ወጣት ወደፊት የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ሊቀባው ነው።

2 የዳዊት አባት የሆነው እሴይ፣ ሳሙኤል እንዲቀባው መጀመሪያ ያቀረበው ወጣቱን ዳዊትን አልነበረም። ሳሙኤል፣ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ከሆነው ከእሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች መካከል አንዱን የወደፊቱ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ለመቀባት ወደ እሴይ ቤት በሄደበት ወቅት የመጨረሻው ወንድ ልጅ የሆነው ዳዊት ቤት ውስጥ እንኳ አልነበረም። ያም ሆኖ ይሖዋ የመረጠው ዳዊትን ሲሆን ትልቅ ቦታ የሚሰጠውም ይኸው ነው።—1 ሳሙ. 16:1-10

3. (ሀ) ይሖዋ አንድን ግለሰብ በሚመረምርበት ወቅት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ዳዊት ከተቀባ በኋላ ምን ተከሰተ?

3 ይሖዋ፣ ሳሙኤል ማየት የማይችለውን ነገር ተመልክቶ ነበር። አምላክ የዳዊትን ልብ ማንበብ ይችል የነበረ ሲሆን የተመለከተውም ነገር አስደስቶታል። አምላክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለአንድ ሰው ውጫዊ ገጽታ ሳይሆን ለውስጣዊ ማንነቱ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7ን አንብብ።) ሳሙኤል፣ ከእሴይ ሰባት ወንዶች ልጆች መካከል ይሖዋ አንዳቸውንም እንዳልመረጠ ሲገነዘብ የእነሱ ታናሽ ወንድም በጎችን ከሚያሰማራበት ቦታ እንዲጠራ አደረገ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ስለዚህ [እሴይ] ልኮ [ዳዊትን] አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። እግዚአብሔርም፣ ‘የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው’ አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ [“አደረበት፣” የ1980 ትርጉም]።”—1 ሳሙ. 16:12, 13

ዳዊት ለክርስቶስ ጥላ ነበር

4, 5. (ሀ) ዳዊትና ኢየሱስ የሚመሳሰሉባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀስ። (ለ) ኢየሱስ፣ ታላቁ ዳዊት ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

4 ዳዊት ከተወለደ ከ1,100 ዓመታት በኋላ ኢየሱስም እንደ ዳዊት በቤተልሔም ተወለደ። አብዛኞቹ ሰዎች ኢየሱስም ንጉሥ የሚሆን አልመሰላቸውም ነበር። በሌላ አባባል ኢየሱስ፣ በርካታ እስራኤላውያን ይጠብቁት የነበረው ዓይነት ንጉሥ አልነበረም። ይሁንና ልክ እንደ ዳዊት የይሖዋ ምርጫ እሱ ነበር። እንደ ዳዊት ሁሉ ኢየሱስም በይሖዋ ዘንድ የተወደደ ነበር። * (ሉቃስ 3:22) ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት ‘የይሖዋ መንፈስ አድሮበታል።’

5 ዳዊትና ኢየሱስ የሚመሳሰሉባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊትን የቅርብ አማካሪው የሆነው አኪጦፌል ኢየሱስን ደግሞ ሐዋርያው የነበረው የአስቆሮቱ ይሁዳ ክደዋቸዋል። (መዝ. 41:9፤ ዮሐ. 13:18) ዳዊትም ሆነ ኢየሱስ ይሖዋ ለሚመለክበት ቦታ ከፍተኛ ቅንዓት ነበራቸው። (መዝ. 27:4፤ 69:9፤ ዮሐ. 2:17) በተጨማሪም ኢየሱስ የዳዊት ወራሽ ነበር። ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት አንድ መልአክ ለእናቱ እንዲህ ብሏታል፦ “ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል።” (ሉቃስ 1:32፤ ማቴ. 1:1) ያም ሆኖ ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ ፍጻሜ የሚያገኙት በኢየሱስ ላይ በመሆኑ ኢየሱስ ከዳዊት ይበልጣል። ኢየሱስ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መሲሐዊ ንጉሥ ነው።—ዮሐ. 7:42

እረኛ የሆነውን ንጉሥ ተከተሉ

6. ዳዊት ጥሩ እረኛ መሆኑን ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

6 ኢየሱስ እረኛም ነው። ጥሩ እረኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው ነው? ጥሩ እረኛ መንጋውን በታማኝነትና በድፍረት ይንከባከባል፣ ይመግባል እንዲሁም ይጠብቃል። (መዝ. 23:2-4) ዳዊት ወጣት እያለ እረኛ የነበረ ሲሆን የአባቱን በጎች በሚገባ ይንከባከብ ነበር። መንጋው ለአደጋ እንዳይጋለጥ በድፍረት ይከላከል የነበረ ከመሆኑም ሌላ ለሕይወቱ ሳይሳሳ በጎቹን ከአንበሳና ከድብ ያስጥላቸው ነበር።—1 ሳሙ. 17:34, 35

7. (ሀ) ዳዊት በንግሥና ላከናወናቸው ሥራዎች ዝግጁ እንዲሆን የረዳው ምን ነበር? (ለ) ኢየሱስ ጥሩ እረኛ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

7 ዳዊት ያሰማራቸውን በጎች በመጠበቅ ያሳለፋቸው ዓመታት፣ ከጊዜ በኋላ ለእስራኤል ብሔር እረኛ እንዲሆን የተሰጠውን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆን ረድተውታል። * (መዝ. 78:70, 71) ኢየሱስም በምሳሌነት የሚጠቀስ እረኛ ነው። እረኛ የሆነው ኢየሱስ ‘ትንሹን መንጋውን’ እና ‘ሌሎቹን በጎቹን’ ሲጠብቅ ከይሖዋ ብርታትና መመሪያ ያገኛል። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 10:16) በመሆኑም ኢየሱስ ጥሩ እረኛ ነው። መንጋውን በደንብ ስለሚያውቀው እያንዳንዱን በግ በስሙ ይጠራዋል። በጎቹን በጣም ስለሚወዳቸው በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሕይወቱን በፈቃደኝነት ሰጥቷቸዋል። (ዮሐ. 10:3, 11, 14, 15) ጥሩ እረኛ የሆነው ኢየሱስ፣ ዳዊት ፈጽሞ ሊያደርጋቸው የማይችላቸውን ነገሮች ያከናውናል። የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሰው ዘር ከሞት ባርነት ነፃ የሚወጣበትን መንገድ ከፍቷል። ይህ ጥሩ እረኛ፣ ‘ትንሹ መንጋ’ በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት እንዲያገኝ ከማድረግ ምንም ነገር ሊያግደው አይችልም፤ በተመሳሳይም ‘ሌሎቹ በጎቹን’ እንደ ተኩላ ካሉ ነጣቂዎች በጸዳና ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንዲወርሱ ያደርጋል።—ዮሐንስ 10:27-29ን አንብብ።

ድል አድራጊውን ንጉሥ ተከተሉ

8. ዳዊት ድል አድራጊ ንጉሥ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

8 ዳዊት ንጉሥ እያለ የአምላክ ሕዝብ የሚኖርበትን ምድር ከጠላት የሚጠብቅ ደፋር ተዋጊ ነበር፤ ይሖዋም “ዳዊት በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን [ይሰጠው ነበር]።” በዳዊት የግዛት ዘመን ከግብፅ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ያለው አካባቢ የእስራኤላውያን ነበር። (2 ሳሙ. 8:1-14) ዳዊት፣ በይሖዋ እርዳታ ኃያል ንጉሥ መሆን ችሎ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “የዳዊት ዝና በየአገሩ ሁሉ ተሰማ፤ እግዚአብሔርም መንግሥታት ሁሉ እንዲፈሩት አደረገ” ይላል።—1 ዜና 14:17

9. ኢየሱስ እጩ ንጉሥ በነበረበት ወቅት ድል አድራጊ የሆነው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስም ምድር ላይ እያለ እንደ ንጉሥ ዳዊት ደፋር ነበር። እጩ ንጉሥ በነበረበት ወቅት ሰዎችን ከአጋንንት ተጽዕኖ ነፃ በማውጣት በአጋንንት ላይ ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። (ማር. 5:2, 6-13፤ ሉቃስ 4:36) ቀንደኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ እንኳ በኢየሱስ ላይ ምንም ኃይል የለውም። ኢየሱስ በይሖዋ እርዳታ በመታገዝ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለውን ዓለም ድል ማድረግ ችሏል።—ዮሐ. 14:30፤ 16:33፤ 1 ዮሐ. 5:19

10, 11. ተዋጊ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በሰማይ ምን ሚና ይጫወታል?

10 ኢየሱስ ከሞተና ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ከሄደ ከ60 ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ተዋጊ ንጉሥ በመሆን በሰማይ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ትንቢታዊ ራእይ አይቶ ነበር። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደፊት ገሠገሠ።” (ራእይ 6:2) የነጩ ፈረስ ጋላቢ ኢየሱስ ሲሆን ‘አክሊል የተሰጠው’ በ1914 በሰማይ ባለው መንግሥት ላይ ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ነው። ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት “ድል እያደረገ [ወጥቷል]።” በእርግጥም ኢየሱስ እንደ ዳዊት ድል አድራጊ ንጉሥ ነው። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ ብዙም ሳይቆይ ከሰይጣን ጋር ባደረገው ውጊያ ድል የነሳ ሲሆን ሰይጣንንና አጋንንቱን ወደ ምድር ወርውሯቸዋል። (ራእይ 12:7-9) የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ‘ድሉን እስኪያጠናቅቅ’ ድረስ በድል አድራጊነት መጋለቡን ይቀጥላል።—ራእይ 19:11, 19-21ን አንብብ።

11 ያም ቢሆን ግን ኢየሱስ እንደ ዳዊት ርኅሩኅ ንጉሥ ነው፤ በመሆኑም በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦችን’ ከጥፋት ይጠብቃቸዋል። (ራእይ 7:9, 14) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስና አብረውት የሚነግሡት ከሞት የተነሱ 144,000 ሰዎች በሚገዙበት ወቅት “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት [ይነሳሉ]።” (ሥራ 24:15) በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኙ ሰዎች ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይከፈትላቸዋል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ምድር ለታላቁ ዳዊት በሚገዙ ጻድቅና ደስተኛ ሰዎች በምትሞላበት ጊዜ በሕይወት ለመገኘት እንድንችል ‘መልካሙን ማድረጋችንን’ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—መዝ. 37:27-29

ሰለሞን ጥበብ ለማግኘት ያቀረበው ጸሎት ተሰማለት

12. ሰለሞን ምን እንዲሰጠው ጸለየ?

12 የዳዊት ልጅ የሆነው ሰለሞንም ለኢየሱስ ጥላ ነበር። * ሰለሞን ንጉሥ በሆነበት ወቅት ይሖዋ በሕልም የተገለጠለት ሲሆን የጠየቀውን ሁሉ እንደሚሰጠው ነግሮት ነበር። ሰለሞን ተጨማሪ ሀብት ወይም ኃይል አሊያም ረጅም ዕድሜ እንዲሰጠው መጠየቅ ይችል ነበር። እሱ ግን እንደሚከተለው በማለት ራስ ወዳድነት ያልተንጸባረቀበት ጥያቄ አቀረበ፦ “ይህን ሕዝብ ለመምራት እንድችል፣ ጥበብና ዕውቀትን ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊገዛ ይችላል?” (2 ዜና 1:7-10) ይሖዋም ሰለሞን ያቀረበውን ጸሎት ሰምቷል።—2 ዜና መዋዕል 1:11, 12ን አንብብ።

13. ሰለሞን በጥበቡ ተወዳዳሪ አልነበረውም የምንለው ለምንድን ነው? ሰለሞን ጥበቡን ያገኘው ከማን ነው?

13 ሰለሞን ለይሖዋ ታማኝ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በጥበቡ ተወዳዳሪ አልነበረውም። ሰለሞን “ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን” ተናግሯል። (1 ነገ. 4:30, 32, 34) ከእነዚህ ምሳሌዎች አብዛኞቹ በጽሑፍ የሰፈሩ ሲሆን ጥበብን የሚሹ ሰዎች አሁንም ድረስ እነዚህን ምሳሌዎች ከፍ አድርገው ይመለከቷቸዋል። በአንድ ወቅት የሳባ ንግሥት የሰለሞንን ጥበብ “አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች” ለመፈተን ስትል 2,400 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዛ ወደ ኢየሩሳሌም መጥታ ነበር። ንግሥቲቱ፣ ሰለሞን በተናገራቸው ነገሮችና በመንግሥቱ ብልጽግና እጅግ ተደነቀች። (1 ነገ. 10:1-9) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰለሞን ጥበቡን ያገኘው ከማን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በሰሎሞን ልብ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ወደ እርሱ መምጣት ይፈልግ ነበር።”—1 ነገ. 10:24

ጠቢቡን ንጉሥ ተከተሉ

14. ኢየሱስ ‘ከሰለሞን የሚበልጠው’ በየትኞቹ መንገዶች ነው?

14 ከሰለሞን የላቀ ጥበብ ያለው ሰው አንድ ብቻ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እሱ ራሱ ‘ከሰለሞን እንደሚበልጥ’ ገልጿል። (ማቴ. 12:42) ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” ተናግሯል። (ዮሐ. 6:68) ለአብነት ያህል፣ ኢየሱስ በተራራው ስብከት ላይ የተናገራቸው ሐሳቦች የሰለሞን ምሳሌዎች የያዙትን መሠረታዊ ሥርዓት ይበልጥ ግልጽ የሚያደርጉ ናቸው። ሰለሞን ለይሖዋ አምላኪዎች ደስታ የሚያስገኙ በርካታ ነገሮችን ገልጿል። (ምሳሌ 3:13፤ 8:32, 33፤ 14:21፤ 16:20) ኢየሱስም እውነተኛ ደስታ የሚያስገኙት ከይሖዋ አምልኮና አምላክ ከሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜ ጋር የተያያዙ ነገሮች እንደሆኑ ጎላ አድርጎ ተናግሯል። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና” ብሏል። (ማቴ. 5:3) በኢየሱስ ትምህርት ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች “የሕይወት ምንጭ” ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ይቀርባሉ። (መዝ. 36:9፤ ምሳሌ 22:11፤ ማቴ. 5:8) “የአምላክ ጥበብ” በክርስቶስ ተገልጿል። (1 ቆሮ. 1:24, 30) ኢየሱስ ክርስቶስ መሲሐዊ ንጉሥ በመሆኑ “የጥበብ . . . መንፈስ” አለው።—ኢሳ. 11:2

15. አምላክ ከሚሰጠው ጥበብ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

15 የታላቁ ሰለሞን ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን አምላክ ከሚሰጠው ጥበብ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? የይሖዋ ጥበብ በቃሉ ውስጥ ስለሚገኝ መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም ኢየሱስ የተናገራቸውን ሐሳቦች በጥልቀት በማጥናትና ባነበብነው ነገር ላይ በማሰላሰል አምላክ የሚሰጠውን ጥበብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (ምሳሌ 2:1-5) ከዚህም በላይ አምላክ ጥበብ እንዲሰጠን አዘውትረን መለመን አለብን። የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ከልብ የመነጨ ጸሎት የምናቀርብ ከሆነ ለጸሎታችን ምላሽ እንደምናገኝ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ያዕ. 1:5) መንፈስ ቅዱስ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እንደ ዕንቁ ውድ የሆነ ጥበብ ለማግኘት ይረዳናል፤ ይህም አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋምና ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎችን ለማድረግ ያስችለናል። (ሉቃስ 11:13) ሰለሞን፣ “ሰባኪው” ወይም ሰብሳቢው ተብሎ የተጠራ ሲሆን አዘውትሮ ‘ለሕዝቡ ዕውቀትን ያስተምር ነበር።’ (መክ. 12:9, 10) የክርስቲያን ጉባኤ ራስ የሆነው ኢየሱስም የሕዝቡ ሰብሳቢ ነው። (ዮሐ. 10:16፤ ቆላ. 1:18) በዚህም ምክንያት ዘወትር ‘ትምህርት’ በሚሰጥባቸው የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።

16. ሰለሞንን እና ኢየሱስን የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?

16 ንጉሥ ሰለሞን በርካታ ነገሮችን ማከናወን ችሏል። በመላ አገሪቱ ውስጥ ቤተ መንግሥቶችን፣ መንገዶችንና የውኃ ማጠራቀሚያዎችን የገነባ ከመሆኑም ሌላ ሥንቅ የሚከማችባቸውን፣ ሠረገሎች የሚጠበቁባቸውን እንዲሁም ፈረሰኞች የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ቆርቁሯል። (1 ነገሥት 9:17-19) በግዛቱ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እሱ ባከናወነው የግንባታ ሥራ ተጠቃሚ ሆነዋል። ኢየሱስም ቢሆን የተለያዩ የግንባታ ሥራዎችን አከናውኗል። ጉባኤውን ‘በዐለት’ ላይ ገንብቶታል። (ማቴ. 16:18) ከዚህም በተጨማሪ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚከናወኑትን የግንባታ ሥራዎች በበላይነት ይከታተላል።—ኢሳ. 65:21, 22

የሰላሙን ንጉሥ ተከተሉ

17. (ሀ) የሰለሞን አገዛዝ የሚታወቀው በምን ነበር? (ለ) ሰለሞን ሊፈጽመው ያልቻለው ነገር ምንድን ነው?

17 ሰለሞን የሚለው ስም “ሰላም” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው። ንጉሥ ሰለሞን የሚገዛው በኢየሩሳሌም ሆኖ ነበር፤ ኢየሩሳሌም የሚለው ቃል “የዕጥፍ ሰላም ባለቤት” የሚል ትርጉም አለው። ለ40 ዓመታት በዘለቀው የሰለሞን የግዛት ዘመን በእስራኤል ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሰላም ሰፍኖ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ዘመን ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “በሰሎሞን ዘመን ሁሉ ከዳን አንሥቶ እስከ ቤርሳቤህ ያለው ይሁዳና እስራኤል፣ እያንዳንዱ ሰው ከወይኑና ከበለሱ ጥላ ሥር በሰላም ለመኖር በቃ።” (1 ነገ. 4:25) ይሁን እንጂ ሰለሞን የላቀ ጥበብ የነበረው ቢሆንም ተገዢዎቹን ከሕመም፣ ከኃጢአትና ከሞት ማላቀቅ አልቻለም። ታላቁ ሰለሞን ግን ተገዢዎቹን ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ነፃ ያወጣቸዋል።—ሮም 8:19-21ን አንብብ።

18. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ አለ?

18 በአሁኑ ጊዜም እንኳ የክርስቲያን ጉባኤ ሰላም የሰፈነበት ነው። በእርግጥም እውነተኛ በሆነ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ እየኖርን ነው። ከአምላክም ሆነ ከሰዎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት አለን። ኢሳይያስ በዛሬው ጊዜ ያለንበትን ሁኔታ በተመለከተ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።” (ኢሳ. 2:3, 4) እኛም ከአምላክ መንፈስ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ለመንፈሳዊው ገነት ውበት አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን።

19, 20. እንድንደሰት የሚያደርጉን ምን ምክንያቶች አሉ?

19 ወደፊት ደግሞ ከዚህ የበለጠ ነገር ይጠብቀናል። በኢየሱስ አገዛዝ ሥር ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ታይቶ የማይታወቅ ሰላም የሚያገኙ ሲሆን ቀስ በቀስ ‘ከመበስበስ ባርነት ነፃ ወጥተው’ ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። (ሮም 8:21) ገሮች፣ በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ የሚያጋጥማቸውን ፈተና ካለፉ በኋላ “ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።” (መዝ. 37:11፤ ራእይ 20:7-10) በእውነትም የክርስቶስ ኢየሱስ አገዛዝ ከሰለሞን ግዛት እጅግ የላቀ ይሆናል!

20 እስራኤላውያን በሙሴ፣ በዳዊትና በሰለሞን አመራር ሥር ደስታ የሰፈነበት ሕይወት ይመሩ እንደነበረ ሁሉ እኛም በክርስቶስ የግዛት ዘመን ከዚያ በላቀ ሁኔታ በደስታ እንኖራለን። (1 ነገ. 8:66) ታላቁ ሙሴ፣ ታላቁ ዳዊትና ታላቁ ሰለሞን የሆነውን አንድያ ልጁን ስለሰጠን ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ ነው!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ዳዊት የሚለው ስም ትርጉም “የተወደደ” ማለት ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ በተጠመቀበትና በተአምራዊ ሁኔታ በተለወጠበት ወቅት ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ “የምወደው ልጄ” በማለት ጠርቶታል።—ማቴ. 3:17፤ 17:5

^ አን.7 ዳዊት በእረኛው እንደሚተማመን በግ ተደርጎም ተገልጿል። ዳዊት፣ ታላቁ እረኛ የሆነውን የይሖዋን ጥበቃና መመሪያ ለማግኘት ይጥር ነበር። “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም” በማለት በልበ ሙሉነት ተናግሯል። (መዝ. 23:1) አጥማቂው ዮሐንስ፣ ኢየሱስን “የአምላክ በግ” በማለት ጠርቶታል።—ዮሐ. 1:29

^ አን.12 የሰለሞን ሌላው ስም ይዲድያ ሲሆን ትርጉሙም “በያህ የተወደደ” ማለት ነው።—2 ሳሙ. 12:24, 25

ልታብራራ ትችላለህ?

• ኢየሱስ፣ ከዳዊት የሚበልጠው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• ኢየሱስ ከሰለሞን የሚበልጠው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

• ታላቁ ዳዊትና ታላቁ ሰለሞን የሆነውን ኢየሱስን ከፍ አድርገህ እንድትመለከተው የሚያነሳሱህ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰለሞን ከአምላክ ያገኘው ጥበብ ታላቁ ሰለሞን ላለው ጥበብ ጥላ ሆኗል

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢየሱስ አገዛዝ ከሰለሞንና ከዳዊት አገዛዝ እጅግ የላቀ ይሆናል!