በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢዮብ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል

ኢዮብ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል

ኢዮብ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል

‘የይሖዋ ስም ብሩክ ይሁን።’—ኢዮብ 1:21

1. የኢዮብን መጽሐፍ የጻፈው ማን ሳይሆን አይቀርም? የተጻፈውስ መቼ ሊሆን ይችላል?

ሙሴ፣ ፈርዖን እንዳይገድለው በመፍራት ከግብፅ ሸሽቶ ወደ ምድያም ሲሄድ 40 ዓመት ገደማ ሆኖት ነበር። (ሥራ 7:23) በምድያም ምድር ሳለ በአቅራቢያው በሚገኘው ዖፅ በተባለ አገር ይኖር በነበረው በኢዮብ ላይ ስለደረሱት ፈተናዎች ሳይሰማ አይቀርም። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሙሴና የእስራኤል ብሔር የምድረ በዳ ጉዟቸው እየተገባደደ በነበረበት ወቅት በዖፅ አቅራቢያ ይገኙ ነበር። በዚህ ጊዜ ሙሴ፣ በዖፅ ይኖር የነበረው ኢዮብ በሕይወቱ የመጨረሻ ዓመታት ስላጋጠሙት ነገሮች ሰምቶ ሊሆን ይችላል። የአይሁድ ታሪክ እንደሚገልጸው ከሆነ ሙሴ የኢዮብን መጽሐፍ የጻፈው ኢዮብ ከሞተ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው።

2. የኢዮብ መጽሐፍ፣ በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን የይሖዋ አገልጋዮች እምነት የሚያጠነክረው በምን መንገድ ነው?

2 የኢዮብ መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን የአምላክ አገልጋዮች እምነት ያጠነክራል። በምን መንገድ? ይህ ታሪክ በሰማይ የተፈጸሙትን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ክንውኖችና በአምላክ የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ላይ የተነሳውን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው አከራካሪ ጉዳይ እንድንረዳ ያስችለናል። በተጨማሪም የኢዮብ ታሪክ ንጹሕ አቋምን መጠበቅ የሚያካትታቸውን ነገሮች በተመለከተ ያለንን እውቀት የሚያሳድግልን ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ በአገልጋዮቹ ላይ ሥቃይ እንዲደርስ የሚፈቅድበትን ምክንያት እንድንገነዘብ ይረዳናል። ከዚህም በላይ የኢዮብ መጽሐፍ፣ ሰይጣን ዲያብሎስ የይሖዋ ዋነኛ ባላጋራና የሰው ልጆች ጠላት እንደሆነ ይገልጻል። በተጨማሪም እንደ ኢዮብ ያሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ከባድ ፈተና ቢደርስባቸውም ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ጠብቀው መኖር እንደሚችሉ ያሳያል። እስቲ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን አንዳንድ ክንውኖች እንመልከት።

ሰይጣን ኢዮብን ፈተነው

3. ኢዮብ ምን ዓይነት ሰው ነበር? የሰይጣን ዒላማ የሆነውስ ለምንድን ነው?

3 ኢዮብ ባለጸጋና ተሰሚነት ያለው ሰው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ጥሩ ሥነ ምግባር ያለው የቤተሰብ ራስ ነበር። የተቸገሩትን ይረዳ የነበረ ሲሆን ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠው መካሪ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክን የሚፈራ ሰው ነበር። ኢዮብ “ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” ሰው እንደሆነ ተገልጿል። ሰይጣን ዲያብሎስ ኢዮብን የጥቃት ዒላማ ያደረገው ባለጸጋና ተሰሚነት ያለው ሰው ስለነበር ሳይሆን ለአምላክ ያደረ በመሆኑ ነው።—ኢዮብ 1:1፤ 29:7-16፤ 31:1

4. ንጹሕ አቋም መያዝ ሲባል ምን ማለት ነው?

4 በኢዮብ መጽሐፍ መግቢያ ላይ የሚገኘው ታሪክ መላእክት በሰማይ በይሖዋ ፊት እንደተሰበሰቡ ይገልጻል። ሰይጣንም በመካከላቸው በመገኘት በኢዮብ ላይ ክስ አቀረበ። (ኢዮብ 1:6-11ን አንብብ።) ሰይጣን፣ ኢዮብ የነበረውን ሀብት የጠቀሰ ቢሆንም በዋነኛነት ትኩረት ያደረገው በኢዮብ ንጹሕ አቋም ላይ ነበር። “ንጹሕ አቋም” መያዝ ሲባል ትክክለኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን መከተል እንዲሁም ነቀፋ የሌለበት፣ ጻድቅና እንከን የለሽ መሆን ማለት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ሲታይ አንድ ሰው ንጹሕ አቋም አለው ሊባል የሚችለው በሙሉ ልቡ ለይሖዋ ያደረ ሲሆን ነው።

5. ሰይጣን በኢዮብ ላይ ምን ክስ ሰንዝሯል?

5 ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያመልከው ንጹሕ አቋም ይዞ ለመኖር ብሎ ሳይሆን በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ እንደሆነ ተናግሯል። በተጨማሪም ኢዮብ ለይሖዋ ታማኝ የሚሆነው አምላክ እስከባረከውና እስከጠበቀው ድረስ ብቻ ነው የሚል ክስ ሰንዝሯል። ይሖዋ፣ ሰይጣን ለሰነዘረው ክስ ምላሽ ለመስጠት ሲል ሰይጣን በዚህ ታማኝ ሰው ላይ ጥቃት እንዲያደርስ ፈቀደለት። በዚህም የተነሳ ኢዮብ በአንድ ጀምበር ከብቶቹን በሙሉ አጣ፣ አገልጋዮቹ ተገደሉ እንዲሁም አሥሩ ልጆቹ ሞቱ። (ኢዮብ 1:13-19) ታዲያ ኢዮብ ሰይጣን በሰነዘረበት ጥቃት ተሸንፎ ንጹሕ አቋሙን አጎደፈ? በመንፈስ መሪነት የተጻፈው ዘገባ ኢዮብ ለደረሰበት መከራ የሰጠውን ምላሽ ሲገልጽ ‘ይሖዋ ሰጠ፤ ይሖዋ ነሣ፤ የይሖዋ ስም ብሩክ ይሁን’ ይላል።—ኢዮብ 1:21

6. (ሀ) በሰማይ በተደረገው ሌላ ስብሰባ ላይ ምን ተከናወነ? (ለ) ሰይጣን የኢዮብን ንጹሕ አቋም በተመለከተ ጥያቄ ባነሳበት ወቅት እነማንን ጭምር በአእምሮው ይዞ ነበር?

6 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በሰማይ ሌላ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በድጋሚ ሰይጣን በኢዮብ ላይ የሚከተለውን ክስ አቀረበ፦ “‘ቍርበት ስለ ቍርበት ነው’ እንዲሉ ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል፤ እስቲ እጅህን ዘርግተህ ዐጥንቱንና ሥጋውን ዳስ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል።” ሰይጣን በዚህ ወቅት የሰነዘረው ክስ ሌሎች ሰዎችንም እንደሚያጠቃልል ልብ በል። ዲያብሎስ “ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል” ብሎ መናገሩ በኢዮብ ላይ ብቻ ሳይሆን ይሖዋን በሚያመልክ በማንኛውም “ሰው” ንጹሕ አቋም ላይ ጥያቄ እንዳነሳ ያሳያል። በዚህ ጊዜ አምላክ፣ ሰይጣን ኢዮብን በሚያሠቃይ ሕመም እንዲመታው ፈቀደለት። (ኢዮብ 2:1-8) ይሁንና የኢዮብ ፈተና በዚህ አላበቃም።

ኢዮብ ከወሰደው አቋም ትምህርት ማግኘት

7. የኢዮብ ሚስትም ሆነች ሊጠይቁት የመጡት ሰዎች በኢዮብ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩት እንዴት ነው?

7 በመጀመሪያ፣ ኢዮብ ላይ የደረሰው መከራ በእሱ ላይ ብቻ ሳይሆን በሚስቱም ላይ ጉዳት አስከትሏል። ልጆቿ መሞታቸውና የቤተሰቡ ሀብት መውደሙ እጅግ አስደንግጧት መሆን አለበት። ከዚህም በላይ ባሏ በከባድ ሕመም ሲሠቃይ ማየቷ ስሜቷን ክፉኛ ጎድቶት መሆን አለበት። ኢዮብን “አሁንም ታማኝነትህን አልተውህምን? ይልቁን እግዚአብሔርን ርገምና ሙት!” ብላው ነበር። ከዚያም ኤልፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተባሉ አጽናኝ ተብዬዎች ኢዮብን ለመጠየቅ መጡ። እነዚህ ሰዎች ኢዮብን ከማጽናናት ይልቅ አሳሳች የሆነ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን ‘የሚያስጨንቁ አጽናኞች’ ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በልዳዶስ የኢዮብ ልጆች ኃጢአት እንደሠሩና የእጃቸውን እንዳገኙ የሚጠቁም ሐሳብ ሰንዝሯል። ኤልፋዝ ደግሞ ኢዮብ መከራ እየደረሰበት ያለው ቀደም ሲል በሠራው ኃጢአት የተነሳ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ገልጿል። እንዲያውም ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎችም እንኳ ለአምላክ የሚሰጡት ምንም ጥቅም እንደሌለ አድርጎ ተናግሯል። (ኢዮብ 2:9, 11፤ 4:8፤ 8:4፤ 16:2፤ 22:2, 3) ኢዮብ እንዲህ ያለ ከባድ ተጽዕኖ ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን አላጎደፈም። እርግጥ ነው፣ ‘ከአምላክ ይልቅ ራሱን ጻድቅ ማድረጉ’ ስህተት ነበር። (ኢዮብ 32:2) ያም ሆኖ የደረሰበትን ፈተና ሁሉ ተቋቁሞ በታማኝነት ጸንቷል።

8. ኤሊሁ በዛሬው ጊዜ ምክር ለሚሰጡ ሰዎች ግሩም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

8 በመቀጠልም ኢዮብን ለመጠየቅ ስለመጣ ኤሊሁ የተባለ ሰው የሚናገር ሐሳብ እናገኛለን። ኤሊሁ በመጀመሪያ ላይ ኢዮብና ሦስቱ ወዳጆቹ የሚያደርጉትን ውይይት ሲያዳምጥ ነበር። ከአራቱ ሰዎች በዕድሜ የሚያንስ ቢሆንም ታላቅ ጥበብ እንዳለው አሳይቷል። ኢዮብን አክብሮት በተሞላበት መንገድ ያነጋገረው ከመሆኑም ሌላ የጽድቅ ጎዳና በመከተሉ አመስግኖታል። ሆኖም ኤሊሁ፣ ኢዮብ ራሱን ከጥፋት ነፃ በማድረግ ላይ ብቻ እንዳተኮረ ከመናገር ወደኋላ አላለም። ከዚያም አምላክን በታማኝነት ማገልገል ምንጊዜም ጠቃሚ እንደሆነ አረጋግጦለታል። (ኢዮብ 36:1, 11ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ምክር ለሚሰጡ ሰዎች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ኤሊሁ ትዕግሥት አሳይቷል፣ በጥሞና አዳምጧል፣ ለማመስገን የሚያስችል ምክንያት ሲያገኝ አመስግኗል፤ እንዲሁም የሚያበረታታ ምክር ሰጥቷል።—ኢዮብ 32:6፤ 33:32 NW

9. ይሖዋ ኢዮብን የረዳው እንዴት ነበር?

9 በመጨረሻ፣ ኢዮብን ያናገረው እንግዳ በታላቅ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲዋጥ አድርጎታል! ዘገባው “እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰለት” ይላል። ይሖዋ፣ ኢዮብን የተለያዩ ጥያቄዎች በመጠየቅ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል በደግነት ምክር ሰጥቶታል። ኢዮብም የተሰጠውን ተግሣጽ ያለማንገራገር በመቀበል “እኔ ከንቱ ሰው [ነኝ፤] . . . በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ” በማለት ተናግሯል። ይሖዋ ኢዮብን ካነጋገረው በኋላ “ቅን ነገር” ወይም እውነቱን ባለመናገራቸው ምክንያት በሦስቱ ሐሰተኛ አጽናኞች ላይ ቁጣው ነደደ። ኢዮብ ለእነሱ መጸለይ አስፈልጎት ነበር። ከዚያም “ኢዮብ ለወዳጆቹ ከጸለየ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደ ገና አበለጸገው፤ ቀድሞ በነበረው ፈንታ ዕጥፍ አድርጎ ሰጠው።”—ኢዮብ 38:1፤ 40:4፤ 42:6-10

ይሖዋን ምን ያህል እንወደዋለን?

10. ይሖዋ፣ ሰይጣንን ችላ ብሎ ያላለፈው ወይም ያላጠፋው ለምንድን ነው?

10 ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ሲሆን የፍጥረታት ሁሉ ሉዓላዊ ገዥ ነው። ይሖዋ፣ ዲያብሎስ የሰነዘረውን ክስ ችላ ብሎ ያላለፈው ለምንድን ነው? አምላክ ሰይጣንን ችላ ብሎ ማለፍ አሊያም እሱን ማጥፋት ለተነሳው ጥያቄ መልስ እንደማያስገኝ ያውቅ ነበር። ዲያብሎስ፣ የይሖዋ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ኢዮብ ሀብቱን ቢያጣ ለአምላክ ታማኝ ሆኖ እንደማይቀጥል ተናግሮ ነበር። ኢዮብ ፈተና ቢደርስበትም እስከ መጨረሻው ታማኝ ሆኗል። ከዚያም ሰይጣን፣ ማንኛውም ሰው አካላዊ ሥቃይ ቢደርስበት አምላክን እንደሚተው ተናግሮ ነበር። ኢዮብ ሥቃይ ቢደርስበትም ንጹሕ አቋሙን አላላላም። በመሆኑም ፍጹም ያልነበረው ኢዮብ ታማኝነት በማሳየቱ ሰይጣን ውሸታም መሆኑ ተረጋግጧል። ሌሎቹን የአምላክ አገልጋዮች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?

11. ኢየሱስ፣ ሰይጣን ለሰነዘረው ክስ የማያሻማ መልስ የሰጠው እንዴት ነው?

11 እያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ፣ ሰይጣን በሚያመጣበት በየትኛውም ፈተና ሳይሸነፍ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ የሚመላለስ ከሆነ ይህ ጨካኝ ጠላት የሰነዘራቸው ክሶች ሐሰት መሆናቸውን በግለሰብ ደረጃ ማረጋገጥ ይችላል። ኢየሱስ ወደ ምድር በመምጣት ሰይጣን ለሰነዘረው ክስ የማያሻማ መልስ ሰጥቷል። ኢየሱስ እንደ መጀመሪያው አባታችን እንደ አዳም ፍጹም ሰው ነበር። እስከ ሞት ድረስ ታማኝ በመሆን ሰይጣን ውሸታም እንደሆነና የሰነዘራቸውም ክሶች ሐሰት እንደሆኑ በማያዳግም ሁኔታ አረጋግጧል።—ራእይ 12:10

12. እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ምን የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎበታል?

12 ያም ሆኖ ሰይጣን በይሖዋ አምላኪዎች ላይ ፈተና ማምጣቱን አላቆመም። እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ ንጹሕ አቋማችንን በመጠበቅ ይሖዋን የምናገለግለው በራስ ወዳድነት ተነሳስተን ሳይሆን ለእሱ ባለን ፍቅር ተገፋፍተን መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል አጋጣሚ ያለን ከመሆኑም ሌላ እንዲህ የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎብናል። ታዲያ ይህን ኃላፊነት እንዴት እንመለከተዋለን? ለይሖዋ ታማኝ መሆን መቻል ትልቅ መብት እንደሆነ ይሰማናል። በተጨማሪም ይሖዋ ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጠን እንዲሁም ልክ እንደ ኢዮብ እኛም ከአቅማችን በላይ እንድንፈተን እንደማይፈቅድ ማወቃችን ያጽናናናል።—1 ቆሮ. 10:13

ሰይጣን—ቦታውን የማያውቅ ጠላትና ከሃዲ

13. የኢዮብ መጽሐፍ ሰይጣንን በተመለከተ ምን ዝርዝር ሐሳቦችን ይዟል?

13 የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ሰይጣን ይሖዋን በመቃወም የፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊት በዝርዝር የሚገልጹ ከመሆኑም ሌላ የሰው ልጆችን እንዴት ወደ ተሳሳተ ጎዳና እንደመራ ያብራራሉ። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ደግሞ ሰይጣን፣ በይሖዋ ላይ ስላነሳው ተቃውሞ የሚገልጹ ተጨማሪ መረጃዎችን እናገኛለን። ከዚህም ሌላ የራእይ መጽሐፍ የይሖዋ ሉዓላዊነት እንደሚረጋገጥና ሰይጣን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚጠፋ ይገልጽልናል። የኢዮብ መጽሐፍ፣ ሰይጣን ስለተከተለው የዓመጽ ጎዳና ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል። ሰይጣን በሰማይ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኘው ይሖዋን ለማወደስ ብሎ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ዲያብሎስ መጥፎ ዓላማና ክፉ ዝንባሌ ነበረው። በኢዮብ ላይ ክስ ከሰነዘረና ኢዮብን እንዲፈትነው አምላክ ከፈቀደለት በኋላ “ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።”—ኢዮብ 1:12፤ 2:7

14. ሰይጣን፣ ለኢዮብ ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበረው አሳይቷል?

14 በመሆኑም የኢዮብ መጽሐፍ፣ ሰይጣን ጨካኝ የሆነ የሰው ዘር ጠላት እንደሆነ ይገልጻል። በኢዮብ 2:1 ላይ የተገለጸው ስብሰባ የተካሄደው በኢዮብ 1:6 ላይ የተገለጸው ስብሰባ ከተከናወነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። በዚህ መሃል በነበረው ጊዜ ውስጥ ኢዮብ ከባድ ፈተና ደርሶበታል። ኢዮብ ታማኝ ሆኖ መገኘቱ ይሖዋ፣ “ያለ ምክንያት [ኢዮብን] እንዳጠፋው ብትወተውተኝም፣ ይኸው ፍጹምነቱን [“ንጹሕ አቋሙን፣” NW] እንደ ጠበቀ ነው” በማለት ለሰይጣን መልስ እንዲሰጥ አስችሎታል። ይሁን እንጂ ሰይጣን በኢዮብ ላይ የሰነዘረው ክስ ሐሰት መሆኑን አምኖ አልተቀበለም። ከዚህ ይልቅ በኢዮብ ላይ ሌላ ከባድ ፈተና ማድረስ እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠየቀ። በመሆኑም ዲያብሎስ ኢዮብን ባለጸጋ በነበረበት ወቅት ብቻ ሳይሆን ችግር ላይ በወደቀበት ጊዜም ፈትኖታል። ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሰይጣን ለተቸገሩም ሆነ በአደጋ ለተጎዱ ሰዎች ቅንጣት ታክል ርኅራኄ የለውም። ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎችን ሁሉ ይጠላል። (ኢዮብ 2:3-5) የሆነ ሆኖ ኢዮብ በታማኝነት በመጽናት ሰይጣን ውሸታም መሆኑን አሳይቷል።

15. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ከሃዲዎችን ከሰይጣን ጋር የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?

15 በጽንፈ ዓለም ውስጥ የክህደት ጎዳናን የተከተለ የመጀመሪያው ፍጡር ሰይጣን ነው። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ከሃዲዎችም የዲያብሎስን ዓይነት ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። እነዚህ ሰዎች በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችን፣ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ወይም የበላይ አካሉን የመንቀፍ ዝንባሌ ተጠናውቷቸው ይሆናል። አንዳንድ ከሃዲዎች ይሖዋ በሚለው መለኮታዊ ስም መጠቀም ተገቢ አይደለም ብለው ይሟገታሉ። ስለ ይሖዋ የመማርም ሆነ እሱን የማገልገል ፍላጎት የላቸውም። እንደ አባታቸው እንደ ሰይጣን ሁሉ እነዚህ ከሃዲዎችም ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎችን ዒላማ ያደርጋሉ። (ዮሐ. 8:44) የይሖዋ አገልጋዮች ከእነዚህ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዲኖራቸው አለመፈለጋቸው አያስገርምም!—2 ዮሐ. 10, 11

ኢዮብ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል

16. ኢዮብ ስለ ይሖዋ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

16 ኢዮብ በይሖዋ ስም ይጠቀም የነበረ ከመሆኑም ሌላ የአምላክን ስም አወድሷል። ልጆቹ እንደሞቱ የሚገልጽ መርዶ ሰምቶ ከባድ ሐዘን ላይ በወደቀበት ጊዜም እንኳ በአምላክ ላይ ክፉ ቃል አልተናገረም። ችግሮቹን ያመጣበት አምላክ እንደሆነ አድርጎ በተሳሳተ መንገድ ቢያስብም የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ አድርጓል። ከጊዜ በኋላ ኢዮብ “እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 28:28

17. ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ እንዲኖር የረዳው ምንድን ነው?

17 ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ እንዲኖር የረዳው ምንድን ነው? ኢዮብ ችግሮቹ ከመከሰታቸው በፊት ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና እንደነበረው ግልጽ ነው። ሰይጣን በይሖዋ ላይ ስለሰነዘረው ክስ ኢዮብ ያውቅ እንደነበርና እንዳልነበር በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ታማኝ ለመሆን ቆርጦ ነበር። “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት ተናግሯል። (ኢዮብ 27:5 NW) ኢዮብ ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ የቅርብ ዝምድና ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? የሩቅ ዘመዶቹ የሆኑት አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ከአምላክ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት የሰማው ነገር በጎ ተጽዕኖ አሳድሮበት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም የፍጥረት ሥራዎችን በመመልከት አብዛኞቹን የይሖዋን ባሕርያት አስተውሎ መሆን አለበት።—ኢዮብ 12:7-9, 13, 16ን አንብብ።

18. (ሀ) ኢዮብ ለይሖዋ ያደረ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ኢዮብ የተወውን ግሩም ምሳሌ መኮረጅ የምንችለው በምን መንገዶች ነው?

18 ኢዮብ ስለ ይሖዋ ያወቀው ነገር እሱን የማስደሰት ፍላጎት እንዲያድርበት አድርጎታል። የቤተሰቡ አባላት አምላክን የሚያሳዝን ነገር አድርገው አሊያም ‘አምላክን በልባቸው ረግመው ይሆናል’ ብሎ በማሰብ ዘወትር መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። (ኢዮብ 1:5) ኢዮብ ከባድ ፈተና በደረሰበት ጊዜም እንኳ ስለ ይሖዋ መልካም ነገሮችን ተናግሯል። (ኢዮብ 10:12) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! እኛም ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ ትክክለኛ እውቀት መቅሰማችንን መቀጠል አለብን። እንደ ማጥናት፣ በስብሰባ ላይ መገኘት፣ መጸለይና ምሥራቹን መስበክ ያሉ ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶች ሊኖሩን ይገባል። ከዚህም በላይ የይሖዋ ስም እንዲታወቅ ለማድረግ አቅማችን የሚችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ የይሖዋን ልብ እንዳስደሰተ ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮችም ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቃቸው የይሖዋን ልብ ደስ ያሰኛል። የሚቀጥለው ርዕስ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል።

ታስታውሳለህ?

ሰይጣን ዲያብሎስ ኢዮብን የጥቃት ዒላማ ያደረገው ለምንድን ነው?

ኢዮብ ምን ፈተናዎች ደርሰውበታል? ምን ምላሽስ ሰጠ?

ልክ እንደ ኢዮብ ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን እንድንኖር ምን ሊረዳን ይችላል?

የኢዮብ መጽሐፍ ሰይጣንን በተመለከተ ምን እንድንገነዘብ ይረዳናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኢዮብ ታሪክ፣ በአምላክ የጽንፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነት ላይ ለተነሳውና ትልቅ ቦታ ለሚሰጠው አከራካሪ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንድንሰጥ ያደርገናል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ንጹሕ አቋምህን ሊፈትኑ የሚችሉ ምን ሁኔታዎች አሉ?